November 24, 2023
59 mins read

ያህያ ሌባ የበዛበት ዘመን

ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ/ም ቀሲስ አስተርአየ nigatuasteraye@gmail.com

Kesis Asterio

ይህ ዘመን አህያ ሰርቆ በጫካ ውስጥ አስሮ ከደበቀ በኋላ፡ ያህያዋን ባለቤት አፈላለጊ መስሎ ቀርቦ በማደናበር ላይ የነበረውን ሌባ የሚመስሉ ብዙ ሌቦች፡ ጥንታዊቷን ኦርቶዶካሳዊት ቤተ ክርስቲያንንና ኢትዮጵያን የከበቡበት ዘምን ነው፡፡

ጦማሩን ለምታነቡም ሆነ በቭዲዮ የተቀረጸውን ድምጽ ለምታዳምጡ ወገኖች ስለ ትግስታችሁ እያመሰገንኩ፡ ለሚወስድባችሁም ጊዜ ይቅርታ እየጠየኩ ወደ ዝርዝር ሐተታዬ ከመሻገሬ በፊት የሀሳብ ጠላፊና ነጣቂ አንደበተኛ የበዛበት ዘምን ስለሆነ የማቀርበውን ሀሳብ ከነጣቂወችና ጠላፊወች ለመከላከል ይህችን ማሳሰቢያ ለማስቀደም ተገደድኩ፡፡

ማሳሰቢያ

ያሳደገችኝ ያጠመቀችኝና ያስተማረችኝ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንና ኢትዮጵያ አሁን ያሉበትን አስከፊና አስቃቂ ሁኔታ ለመግለጽ ሳስብ ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ የምጽፈው ስለበደለና ስለተበደለ ሰው አይደለም በግዚአብሔርና በሰው ፊት ራሳችሁን እንድታዩ”(2ቆር 7፡12)” ብሎ የተናገረው ማሳሰቢያ ትዝ አለኝ፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ለመናገር የፈለኩት ደጋግሜ ስለማነሳቸው ስለ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋና ስለ ዳንኤል ክብረት ማንነት ለመናገር ሳይሆን፡ የተናገሩት ሕዝብንም እኔንም ያወናበደ መሆኑን ለማሳየት ብቻ ነው፡፡

ይሁን እንጅ ድርጊታቸውን ስቃወም አድራጊወችን መንካቴ አይቀርምና በጥላቻ በግል ቂምና ዘመኑንን ባረከሰው በሴራ ፖለቲካ ተገፋፍቸ አለመሆኑን ለማሳየት እንጅ፡ የነሱን ስም ለማጥፋት ለመክሰስና ለመውቀስ አይደለም፡፡

እኔ “አይጧም አትለፍ፡ ምጣዱም አይሰበር” የሚለውን ስለምከተል፡፡“ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” እያለ አይጦችን የሚያራባውን አዘናጊና የሸፍጥ መርሆ የሚከተል የዘመኑ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡

“አይጡን ትቶ ዳዋውን፡ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” እንዲሉ መደብደብ የሚገባቸውን አይጦችን እያራባ ወደ ህዝብ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚልክ፡ ተሸካሚ ጳጵሳትን ትቶ ህዝበ ክርስቲያኑን የሚደበድብ ፖለቲካ የተከሰተበት ዘመን ነው፡፡

ይህ ዘመን ስለተደባዳቢ በደለኛ መናገር ስህተት ነውር፤ ስለሚደበደበው ህዝብ መደብደቡን ገልጾና ተቃውሞ መናገርም ነውር እየሆነና፡ በሁሉም ግልጽ ሆኖ ስለሚታይና መደበቅ ስለማይችሉ ስለድብደባው ብቻ መናገር ባህል የሆነበት ዘመን ነው፡፡

Ermias 3 1 1 1 1

ይህን ባህል የፈጠሩ ፖለቲከኞች እነሱ በሰሩት ስህተትና በደል ህዝቡን እያስደበደቡት እያስጎዱት ነው፡፡ በበደላቸው በመዋሸታቸውና በመቅጠፋቸው አፍረው መጸጸት ንስሀ መግባት ሲገባቸው በፈጠሩት ርኩስ ባህል ራሳቸውን ደብቀው በተግባር የደጸሙትን በደል አሉባልታ እንዲሆን ባሉባልታነት እየሸፈኑት ናቸው፡፡

በክርስትና እምነት ራሱን የሚደብቅና ደብቆ የሚናገር “ዘእኩይ ምግባሩ ይጸልእ ብርሃነ ወኢይመጽእ ኀበ ብርሃን ከመ ኢይትከሰቶ ምግባሩ”(3፡20_21) ብሎ ክርስቶስ እንደተናገርው ደብዳቢው ቀጣፊው ውሸታሙ እራሱን እይገልጽም በሌላ እንዲገለጥም አይፈልግም፡፡

አዳምና ሄዋን ራሳቸው ፍሬዋን ቀጥፈው ከበሉ በኋል እንደገና የበሏትን የራሷን የበለሷን ቅጠል ቀጥፈው ራሳቸውን እንደደበቁባት፡ የብልጽግና ቡድንም ዳንኤል ክብረትን በመሳሰሉ ቀጣፊወች ራሳቸውን ደብቀው የሚፈጽሙት በደልና ኃጢአት እንዳይገለጥባቸው እንደገና በሌላ ቅጥፈት ራሳቸውን እየደበቁ አማራውን፡ አማረኛ ተናጋሪውንና ኦርቶዶክስ ክርስቲያኑን እየደበደቡ ናቸው፡፡

ራሳቸው ዶክተር ዳኛቸው“አንድ የስነ መለኮትና የፍልስፍና ተማሪ “ሄዋን አሳሳተችኝ አትበል ሄዋን አንተነህ” አለ ብለው ከሙሉ ጥራዙ ነጥቀው የጠቀሱት የስነ መለኮትና የፍልፍስና ተማሪ ይህን ከላይ የገለጽኩትን ለመግለጽ የሞከረበት ዓውድ ይመስለኛል፡፡

የተከሰተውን በደልና ኃጢአት ከሰሪው አካል እየነጠሉ የችግሩን ፈጣሪ እየደበቁ መናገር፡ የሰሪውን ሕልውና መካድ ሲሆን ተደብቆ የሚሰራውን ኃጢአት ሳያፍር እንዲቀጥልበት እንዳይጸጸትና ንስሐ እንዳይገባ ማድረግ ነው፡፡

ይህ አካሄድ ሊቃውንት መምህሮቼ የቀኖናችን መስራቾች ሰለስቱ ምዕት “እመቦ ዘይትናገር ውስተ ቤተ ክርስቲያን ነገረ ከንቱ ስላቅ እስመ ጌጋዩ ይከውን ላዕለ ካህን ዘይትለአክ ወአኮ ዘይኤብስ ባሕቱ ዘይትኬነን አላ ዘሂ ይትፌሳህ በኃጢአቱ ወበአሐቲ ኩነኔ ይትኬነኑ”( ሃ አ ም 22፡ቁ4) ብለው የተናገሩትን መሠረት በማድረግ ባንድምታ ጉባኤያቸው ካስተማሩኝ ጋራ የሚቃረን ይሆናል፡፡

ይህም ማለት “በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ዋዛ ፈዛዛ ቀልድና ስላቅ መናገር በደል ነው፡፡ የሚያስከትለው ፍዳ የሚደርሰው በደሉን በሚናገር ሰው ላይ ብቻ አይወሰንም ከተናጋሪው ይልቅ በካህኑ ላይ ይከብዳል”

ባብነቱ ትምህርትም ሆነ ባስኳለው ትምህርት የመደበቅ ግዴታና ጥንቃቄ እንዳደርግ የተማርኩት ለንስሐ በኑዛዜ በግል የተነገረኝን ብቻ ነው፡፡ በህዝብ ላይ ተፈጽሞ በግልጽ የሚታየውን በደል ህዝብ ሊናገረው ያልደፈረውንና ባስመሳዮች ተድበስብሶ የሚነገረውን ገልጦና አብራርቶ አለመናገር ሐላፊነቱ የኔ ብቻ ሳይሆን በቅስና በጳጵስናና በፍልስፍና ሙያ በህዝብ ፊት የቆሙትን ዶክተር ዳኛቸው የመሳሰሉትን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “እፈቱ እፍልስ እም ዓለም. . . . ወባህቱ ርቱዕ ይደሉ ሊተ ከመ አሀሉ በሕየወተ ሥጋዬ በእንቲአክሙ“ (ፊል 1፡20_23)”፡፡ ብሎ እንደተናገርው ራሳቸውን ያላስቀደሙ አንዳንድ አስተዋዮች ለሰው ክብር ለሀገር ደህንነት ያቀዱትን የተቀደሰውን ተግባር የሚቃወሙ የሰይጣን ሠራዊቶች የጀመሩትን ከግብ ሳያደርሱ እንዳያጠፏቸው ጀማሪወች ራሳቸውን ሳይገልጹ የብዕእር ስም ቢጠቀሙ ኃጢአት አይደለም፡፡

ያም ሆነ ይህ ዶክተር ዳኛቸው ዳንኤልን የነቀፍነውን ነቅፈው ዳንኤልን ሸፋፍነው ማቅረባቸው “አይጡን ትቶ ዳዋውን አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” የሚባለውን ፈጸሙ፡፡

ሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ/ም አህያየን የሰረቃት ሌባ፤ ራሱ ደብቆ አፈላላጊየ ሲሆን አህያየን እንዴት ላገኛት እችላለሁ? ”በሚል ርዕስ የጻፍኳትን ጦማር አስታወሱኝ፡፡ ማሳሰቢያን እዚህ ላይ አቁሜ ወደ ዋናው ነገሬ እሻገራለሁ፡፡

አህያ ሰርቆ በጫካ ውስጥ የሰረቃትን አህያ ደብቆ፡ ጠፍታው በመፈለግ ላይ ያለውን ባለቤቷን የሚያፈላልግ ያህያ ሌባ ታሪክ፡ በዚህ ዘመን ያለነውን የመንፈሳውያንና የፈላስፎችን የሁላችንንም ተግባር እምነትና ምንነት የሚገልጽ መሰለኝ፡፡

ከዚህ በታች የማቀርበው የነዶከተር ዳኛቸውን አካሄድ ይገልጽልኛል ብየ ያሰብኩት የተሰረቀችው ያአህያዋ ታሪክ ነው፡፡

አንድ ባላገር አህያው ጠፋቸው፡፡ ባካባቢው ያህያ አፈላለግ ልማድ “አህያ ያየህ ና ወዲህ በለኝ” እያለ ድምጽ በማሰማት ፍልጋውን ቀጠለ፡፡ ያህያዋን የእግር ምልክት (ዱካዋን) አገኘ። ዱካዋን ተክትሎ ሲሄድ አህያውን የሰረቀ ሌባ ሲመሽ ፈቶ ወደ ቤቱ ይዞ ለመሄድ አስሮ ከሚያቆይበት ጫካ ደረሰ። ሌባው ሲመሽ ፈቶ ወደ ቤቱ እስኪወስዳት ድረስ ጅብ እንዳይበላት ካካባቢው ሳይርቅ ይጠብቃል።

ያህያዋ ባለቤት በእግሯ ምልክት ማልትም በዱካዋ እየተመራ ያህያው ሌባ አህያዋን አስሮ ከጅብ ከሚጠብቅበት ጫካ ደረሰ፡፡ “ያህያዬ የእግር ምልክት (ዱካ) እየመራኝ ከዚህ ደርሻለሁ ፡፡ምናልባት የኔ አህያ በዚህ አካባቢ አይተሀት ከሆነ ልትነግረኝ ትችላለህ? ወንድሜ“ ብሎ አስሮ የደበቃትን ራሱን ያህያውን ሌባው ጠየቀው።

ሌባውም መለሰና “ቀኑን ሙሉ ሳር ሳጭድ ከብቶችንም ሳሰማራ ካካባቢው አልተለየሁም፤ አህያ ግን አላየሁም፡፡ ይህ የምትከተለው ዱካ ያህያ አይደለም፡፡ አንድ ሰው በቅሎ እየነዳ በዚህ አልፏል። የምትከተለው ፋና የበቅሎዋ እንጅ የአህያዋ አደለም። ይልቅስ እየመሸ ነውና ጅብ እንዳይሻማህ በጊዜ ወደ ሌላ ቦታ እንድትፈልጋት እመክርሀለሁ” አለው።

በመፈለግ ላይ ያለው ያህያዋ ጌታም ሌባውን ጠርጥሮ ቆሞ በመተከዝ ላይ ሳለ፡ አህያው ጠፍታው በመፈለግ ላይ መሆኑን ያወቀ አቋርጦ በመሄድ ላይ የነበረ የጎረቤት ሰው “አህያህን አገኛሀት?” ብሎ በምፈለግ ላይ ያለውን የአህያዋን ጌታ ጠየቀው። ያህያዋ ጌታም “አህያየን ሰርቆ የደበቃት ያህያየ ሌባ አፈላላጊየ ሆኖ ሳለ እንዴት አህያየን ላገኛት እችላለሁ? ብሎ መለሰለት።

ሌባው መሽቶ በጀብ ከመነጠቁ በፊት አህያዋን ካሰረበት ጫካ ፈቶ ወደ ቤቱ ይዞ ለመሄድ ቢፈልግም፡ ያህያዋ ባለቤት አህያው ከዚያ ቦታ እንዳልራቀች ተጠራጥሮ ከቆመበት አልሄደም፡፡ ሌባውም ባለቤቷ ትቶለት እንደማይሄድ ተረዳና ፊቱን አዙሮ ቦታውን ለቆ መሄድ ሲጀምር፡ ያህያዋ ባለቤት በተለመደው ያፈላላግ ዘዴ “አህያየን ተሰርቃ ከጫካ ታስራ አግኝቻታለሁ፡፡ በጅብ ተከብቤአለሁና ድረሱልኝ” ብሎ የጥሪ ድምጽ ላካባቢው ሲያሰማ ሌባው ጥሎት ፈረጠጠ፡፡ ባለአህያው አህያውን ሰርቆ ደብቆ አፈላላጊ ሆኖ ከቀረበው ሌባና ከጅብ አተረፋት፡፡

ዘመኑ ጠላፊ ነጣቂ አንደበተኛ የበዛበት ባይሆን ከዚህ በላይ ያቀረብኩት ባህያዋ ሌባ ተካቶ ስለቀረበ ሌላ ሐተታ ባላስፈለገ በበቃ ነበር፡

፡ግን የቀሰቀሰኝ ነገር በፈላስፋው በዶክተር ዳኛቸው ተጠንስሶና ተደፍዶ የቀረበ ስለሆነ በተማርኩት አንድምታ መበጥበጥ ማጥለልና ገፈታውን መለየት አለብኝና ወደ መተርጎሙ እንድገባ ተገደድኩ፡፡

መተርጉም

መተርጉም ቀደም ብሎ የተከሰተውን ተመሳሳይ ነባራዊ ክስተት መነሻ በማድረግ አዲሱን ጥሬ ክስተት በነባራዊው ክስተት መሰለቅ መፍጨትና አዲስ የሚወለደውን ክስተት መጠቆም ማሳየት መግለጽ ማለት ነው፡፡ ከነባራዊውና ካዲሱ ክስተት ድምር የሚገኘው የትርጉም ነጸብራቅ መላምት ይባላል፡፡ እምኀበ አልቦ የመጣ ፈጠራ ስላይደለ ጥንቆላም ትንቢትም አይደለም፡፡ ከነበረውና ካለው ስብቀት የሚወለድ መጻኢውን የሚጠቁም ሐሳብ ነው፡፡

በዚህ ዓለም ስንኖር በኑሯችን የሚገጥሙንን የምንተረጎምባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ ከብዙወቹ መተርጎሚያ መንገዶች ጥቂቶቹ በባህላችንና በሃማኖታችንና በጠቅላላው ኢትዮጵያውነታችን ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡

እኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን ተማሪ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያውያን መተርጉማን ክስተቶችን የሚተረጉሙ ክርስቶስ “የምድሩን ያካባቢህን ሳትረዳ የሰማዩን አውቃለሁ የምትል አንተ ግብዝ”(ማቴ 16፡2) ብሎ የተናገረውን መመሪያ በማድረግ ነው፡፡ ክርስቶስ እንዳለው አስቀድመን በዙሪያችን ባካባቢያችን ያሉትን ክስተቶች መረዳት ነው፡፡ በዙሪያችን ያሉትን ነባራዉያን ክስተቶች ተረድተን አዲስ ማለትም ጥሬና ግርድፍ ክስተቶችን በነባራዊው ክስተት መፍጨትና መሰለቅ ማለት ነው፡፡

በዚህ አቀራረቤ መፍጫው በሌባ ተሰርቃ በጫካ ታስራ በሌባው የተደበቀችው አህያ፡ ደብቆ አስሮ ባለቤቱ ሲጠይቀው ወደ ሌላ ቦታ ሄደህ ፈልግ ያለው ሌባና ባለቤቷ ያህያየ ሌባ አፈላላጊየ ሲሆን እንዴት አህያየን ላገኛት እችላለሁ የሚለው ነባራዊው ክስተት ነው፡፡

የሚፈጨው አንድ አፍታ በሚባለው መገናኛ እስጢፋኖስ አበራ እና ዙሩባሌል ዓለማየሁ በሚባሉት ጠያቂነት በተለያዩ ወቅቶች ቀርበው ዶክተር ዳኛቸው፦

“በየአድባራቱ እየዞረ የኢትዮጵያን ታርክ ቅርስ እየመረመረ ይህን ሁሉ የጻፈውን ሰው ኢትዮጵያን እኔ ነኝ የምወዳት አንተ አትወዳትም አንተ ትጠላትለህ ብየ ለምንድነው በእንደዚህ ያለ ግምት የምንቀሳቀሰው?

ብለው የተናገሩት ነው፡፡

የዶክተር ዳኛቸው ጥራጥሬ ሐሳቦች

Nichel “ሐሰት ማለት በሬ ወለደ ማለት አይደለም፡፡ፊት ለፊት የሚታየውን አላየሁም ማለት ነው፡፡ መንግሥት ስራውን እየሠራ ብቻ አይደለም፡፡ ዓቢይ ለሲኖዶሱ መከፈል ተባባሪ ነው ይባላሉ፡፡ ጠ/ምንስቴሩ ሲኖዶሱ በሶስት ተከፍሎ አያገባኝም፡ ይላሉ፡፡

ባንድ ወቅት ህግ ሲገረሰስ እኔን አይመለከተኝም በሌላ ወቅት በመንግሥቴ ስር ያላችሁ ህግ አስከባሪወች እጃችሁን እንዳታሰገቡ ይሉና እንደገና በሌላ ወቅት የፖለቲካ አዝማሚያ እያዩ አፋጣኝ ርምጃ ማለት ምን ማለት ነው? መንግሥት ወደ ቀልቡ በመመለስ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡

አቶ ሽመልስ ሸገርን ሲመሠርት ቤታቸውን አፍርሶባቸውል፡፡ በፈረሰባቸው ዜጎች መካከልና በሽመልስ መካከል ምንስቴሩ ሽማግሌ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ

ሁሉ ሲፈጸም ጠ/ ምኒስቴሩ ምንም አልተናገሩም ለጥፋቱ ተባባሪ ናቸው፡፡ እየተባለ ነው፡፡ ወሰን የደረሰውን ግፍ ለኮንግረስ በሰንጠረዥ አቅርበዋለች፡፡ በየአድባራቱ እየዞረ የኢትዮጵያን ታርክ ቅርስ እየመረመረ ይህን ሁሉ የጻፈውን ሰው ኢትዮጵያን እኔ ነኝ የምወዳት አንተ አትወዳትም አንተ ትጠላትለህ ብየ ለምንድነው በእንደዚህ ያለ ግምት የምንቀሳቀሰው? ባሜሪካና በጀርመን ያሉ ያልተማሩ ሚኒሽያወች ናቸው፡፡

እንዲያውም ሕዋት ይሻላል የሞትንም እኛ ያለንም እኛ እያለ ነው፡፡ ደርግ ፓትርያርኩን ገደለ፡፡ ወያኔ አባረረ፡፡ ይህ ደግሞ ሲኖዶሱን ለ3ት ከፍሎ በቁም ቀበረ፡፡ ለፖለቲክ ብለህ ሕግ ከሻርክ ወደክ፡፡

የወልቃይት ነገር በhouse of federation ተመክሮበት በዚያው በፌዴሬሽኑን መነገር ሲገባ ራሱ ጠቅላዩ ከፌዴሬሽኑ ነጥቆ መናገሩ፡ የቀይ ባህር ጉዳይም ተመክሮበት በውጭ ጉዳይ ምንስቴር በኩል መገለጽ ሲገባው ተሽቀዳድሞ መናገሩ በነጣቂነት ባፋኝነት ካገርበጃችን ወደአገርበጄነት መቀልበስ፡ ኮለኔል ደመቀ ከራሱ በላይ አገር ወዳድነቱንና አሳይቷል፡፡

የዲሞክራሲን መኖር የሚገለጹት liberty equality legality ሲንጸባርቁ ነው፡

፡እነዚህ ሶስቱ ከሌሉ የዲሞክራሲን አለመኖር ይገልጻሉ፡፡ በአማራ ክልል በመፋለም ላይ ያለው ፋኖ እንደ ሁለተኛ ኃይል ሆኖ ተከስቷል፡፡

ወሰን በህዝብ ላይ የደረሰው ግፍ ለኮንግረስ በሰንጠረዥ አቅርበዋለች፡፡ ባሜሪካና በጀርመን ያሉ ያልተማሩ ናቸው፡፡ ጠበንጃ እየተነጋገረ ነውና ሁሉም ዝም ይበል”

ከዚህ በላይ የሰፈረው የዶክተር ዳኛቸው ንግግር

“በየአድባራቱ እየዞረ የኢትዮጵያን ታርክ ቅርስ እየመረመረ ይህን ሁሉ የጻፈውን ሰው ኢትዮጵያን እኔ ነኝ የምወዳት አንተ አትወዳትም አንተ ትጠላትለህ ብየ ለምንድነው በእንደዚህ ያለ ግምት የምንቀሳቀሰው?” ከሚለው ንግግራቸው በቀር፡ አግደምድመው አቀረቡት እንጅ እውነት ነው፡፡

ታዲያ አግደምደመውም ቢሆን የተናገሩት ሁሉ ጥፋት በዳንኤል ክብረት ምክር እየተመሩ ጠ/ምንስቴሩ የፈጸሙት ከሆነ የዳንኤል ክብረት መወቀስና መነቀፍ ለምን ዶክተር ዳኛቸውን አመማቸው?

ራሳቸው “አሁን ጠበንጃ እየተናገረ ነው ሰው ዝም ይበል” እንዳሉት፦ አሁን በፋኖ የተነሳውን ጠበንጅ በዝምታ መቀበል ያለባቸው በዳንኤል ምክር የሚመራው ጠ/ም ዐቢይና ፋኖን ጃዊሳ ብሎ የዘለፈው ዳንኤል ክብረት እንጅ የፋኖን ሀሳብ ደግፈው ለኮንግረስ በደሉን ያቀረቡትን ወሰንንና፡ ክወሰን ሀሳብ ጋራ የሚናበብ ሀሳብ ያለንን የሚመለከተን አይመስለኝም፡፡

ባንድ በኩል የተናገሩትን ለምን በሌላ በኩል ራሳቸው በተዘበራረቀ ንግግራቸው ያፈርሱታል? “አንድ የስነ መለኮትና የፍልስፍና ተማሪ ሄዋን አሳሳተችኝ አትበል ሄዋን አንተነህ” ብሎ ተናገረ የሚለውን የጠቀሱት ምናልበት ዓቢይ የሚከሰስበት መልካም ጊዜ ቢከሰት በዳንኤል ምክር ነው በደሉን የፈጸምኩት ብሎ እንዳያመልጥና ለዳንኤል የሚያመልጥበትን ዘዴ በጠማማ መንገድ ለመጥቆም እንጅ ተሰውሯቸው አይመስለኝም፡፡

ዶክተር ዳኛቸው በየጊዜው የተናገሯቸውን በተለያዩ የፍልስፍና ዘርፎች የሰለጠኑ ባለሞያወች ቢፈተሿቸው ዳንኤል ክብረት ለኢትዮጵያ ያለውን ፍቅር ተርጉመው ሊያሳዩን የሞከሩበትን ፈሊጥ (fallacy) የተፋለሰ መሆኑን እኔ

ከማሳየው የበለጠ አድርገው እንዲሚያቀርቡት እርግጠኛ ነኝ፡

ዶክተር ዳኛቸው ከእስጢፋኖስ አበራ እና ከዙሩባሌል ዓለማየሁ ጋራ የተናገሯቸው ጥራጥሬ ሀሳቦች በሀሳብ መፍጫ ዘርፎች መፈጨት ያለባቸው ጥሬ ሐሳቦች ሲሆኑ ለባለሙያወች ትቼ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ አያይዘው ስለ ዳንኤል ክብረት በተናገሩት ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡

ዶክተር ዳኛቸው ስለ ዳንኤል የተናገሩት

በግድምድም ቢሆንም በገለጿቸው እውነቶች “በየአድባራቱ እየዞረ የኢትዮጵያን ታርክ ቅርስ እየመረመረ ይህን ሁሉ የጻፈውን ሰው ኢትዮጵያን እኔ ነኝ የምወዳት አንተ አትወዳትም አንተ ትጠላትለህ ብየ ለምንድነው በእንደዚህ ያለ ግምት የምንቀሳቀሰው?” ብለው ስለዳንኤል ተመራማሪነትና አገር ወዳድነት ተናግረዋል፡፡

ራሳቸው መልሱን በማጣት ተቸግረው በመፈልግ ላይ እንደሆኑና ሌላ መልስ ሰጭ አካል ፈላጊና አፈፈላጊ የፈለጉት መልሱ ጠፍቷቸው አይመስለኝም፡፡

አንድ ጸሐፊ “philistine በብዙ ተብለጭላጭ እውነቶች አንዲትን ሐሰት ሸፋፍኖ በማሾለክ በኑሮ ውጣውረድ በተጠመደው ብዙ ሕዝብ ጭንቅላት ላይ ያሰርጻታል” እንዳለው፦ ዶክተር ዳኛቸው አግደምድመው ባቀረቡት ሐሳብ

የዳንኤልን ሸፍጥ ሸፍነው ተመራማሪነቱንና ለኢትዮጵያ ያለውን ፍቅር በጭንቅላታች ሊያሰርጹብን የፈለጉ ይመስለኛል፡፡

ዲቁናውን፡ ሙሐዘጥበብነቱን፡ ተመራማሪነቱን ጸሐፊነቱንና ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅሩን አሁን በሚሰራው ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በነበረበት በኢሀደግ ዘመን በተናገራቸውና በሰራቸው ስመዝናቸው የዶክተር ዳኛቸው ለዳንኤል የሚሰጡት ምስክርነት ለየአይጥ ምስክር ሆና የቀረበችውን የድንቢጥን ምስክርነት የሚገልጥ ነው፡፡

ምንድነው ዲቁና? ተመራማሪነትስ ምንድነው? ሙሐዘጥበብነትስ ምንድነው? ለዳንኤል የተሰጡትን ሶስቱንም የግር ቅጽሎች መዳሰስ ሊኖርብን ነው፡፡

ዲቁና ምንድነው? በቤተ ክርስቲያናች ሕጻናት የመጾር መስቀል ይዘው ሳይገባቸው ሳይረዱ ነጽር እያሉ በቄሱ ላይ “ተንሥኡ” እያሉ በህዝቡ የሚጮሁት ብቻ ይመስላል፡፡ ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የእስጢፋኖስን የዲቁና ተግባር ተምረው ሙሉውን ሕዝባዊ የዲቁና አገልግሎት አካተው የያዙ መሆን ይገባቸው ነበር፡፡ መጮህ ያልኩት ዲያቆናት የሚያሰሙትን ቃል ማቃለሌ ሳይሆን በቀኖናችን የተገልጸውን የዲቁናውን ሕዝባዊ ተልእኮ በተግባር ለማዋል ባለመብቃታቸው ነው፡፡

ይህም የሕጻንነት ዲቁና ባንድ ወቅት የተፈጠረ ክስተት ቋሚ ባህል በመሆኑ እንጅ የሕጻናቱ ስሕተት አይደለም፡፡

ታላቁ ሰማእት አባታችን አቡኑ ቴወፍሎስ የዲቁናን ሙሉ አገልግሎት በሰበካ ጉባኤው ቃለ ዓዋዲ መሠረት ባካባቢው ህዝበ ክርስቲያን በተመረጡ በተማሩ የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተና መጠበቅና አስፈላጊም ሲሆን ተላልፈው በሚሞቱ ክርስቲያኖች እንዲተካ ሊያስተካክሉት ሞክረው እንደነበረ ደጋጋሜ ገልጨዋለሁ፡፡፡

ከዳንኤል ክብረት ይጠበቅ የነበረው በሰማእቱ ቅዱስ አባታችን በፓትርያርክ ቴወፍሎስ የታወጀውን የሊቀ ዲያቆን ቅዱስ እስጢፋኖስንን ተልዕኮ መፈጸም ነበር፡፡ ነገር ግን ባልተጠበቀበት በተቃራኒ መንገድ በመሄድ በሕጻናቱ የሚካሄደውን እንኳ ተንስኡ ብሎ አያውቅም፡፡ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ በህዝብ ላይ ጥፋት እየፈጸመ ያለውን ብልጽግ ናን አልገሰጸም፡፡ የሚጠራበት የሙሐዘጥበብነት ትርጉም ይዞ አልተገኘም፡፡ የዳንኤል ሙሐዘጥበብነት የሚያንጸባርቀው የጥንቱን philistine ባህርይንና ጠባይ ነው፡፡ በፍልስፍናው ዓውድ philistine ማለት “የገብያ ግርግር ለቀጣፊ በጀው እንዲሉ” በህብረተ ሰብ መካከል ግርግር ሲፈጠር ራሳቸውን አዋቂወች በማድረግ በተቃራኒና በከረረ መንገድ ከአዋቂወች ጋራ ተወዳዳሪወች አድርገው ራሳቸውን በማቅረብ በንግግራቸው ከሌሎች በላይ መስለው ራሳቸውን በማብለጭለጭ ወይም በማብለጥለጥ ላይ ያሉ አብያጽ ሐሳውያን ማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያችን አተረጓጎም ሙሐዘ ጥበብ ማለት የፍልስፍና መፍለቂያ ማለት ሲሆን ፡፡ በሁሉም አተርጓጎም ፍልስፍና ማለት የፍቅርና የእውቀት ድምር ማለት እንደሆነ ተነግሮናል፡፡ እንደ ዶክተር ዳኛቸው አገላለጽ በዳንኤል ሕይወት ውስጥ የሚንጸባረቀው የእውቀትና ፍቅር ድምር ፍልስፍና መሆኑ ነው፡፡ ፍልስፍና መሆኑ ቀርቶ መስተዳጉጽ በመሆኑ የዶክተር ዳኛቸው አተረጓጎም ከኢትዮጵያዊውም ከግሪኩም አተረጓጎም ጋራ ተቃረነ፡፡

መስተዳጉጽ ቁራ

በቤታችን አተርጓጎሞ ዳንኤል ከኖኅ መርከብ ከወጣው ቁራ እጅግ የከፋና መስተዳጉጽ ነው፡፡

መስተዳጉጽ ማለት “ወልሳን መስተዳጉጽ ሆኮሙ ለብዙሀን ወአስተፋለሶሙ እምህዝብ ውስተ ሕዝብ ወአሕጉር ጽኑዓተ አመዝበረት ወአብያቲሆሙ ለዐበይት አውደቀት”(ሲራክ 28፡14) ተብሎ በመጽሐፍ በተገለጸው ክፉ ባህርይ የተመረዘ ሰው ነው፡፡

ይህም ማለት የሚናገረው የሚሰራው ህብረተ ስብን አቅጣጫ የሚያስት የህዝብን አመለካከት እያፋለሰ ህዝብንና ህዝብን የሚያጋጭ ሽመልስ አብዲሳ እንደሚያደርገው ሰወች የሚኖሩበርት እያፈረሰ የህብረተ ሰቡን ኑሮ የሚያቃውስ ማለት ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናች ውስጥ በነበረበት ወቅት ዘልቆ ባልተማረው ባልተረዳው ነገረ ማርያምና ነገረ መለኮት በመግባት የውጩን ሲኖዶሱን ከውስጥ ሲኖዶስ ጋራ፡ አቡነ ማትያስን በወቅቱ ከነበረው ከዲሲው ማሕበረ ካህናት፡ ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከሰንደቅ ጋዜጣ አዘጋጅ ጋራ በማጋጨት ላይ ተሰማርቶ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከብልጽግና ጎን ተሰልፎ በማጋጨቱ ተግባር በመቀጠል ከኖኅ መርከብ ከወጣው ቁራ የባሰ ሆኖ ቀረበ፡፡

ከኖህ መርከብ የወጣው ቁራ ከመርከብ ከወጣ በኋል ጭልፊቶችን ተሽከርክሪ እባቦችን ጥርሳማ ተኩላወችንና ጅቦችን ይዞን ወደ መርከቡ ተመልሶ አልበጠበጠም፡

ዳንኤል ከቤተ ክርስቲያን ወጥቶ ወደ ብልጽግና ከገባ በኋላ ዓቢይንና በዓቢይ የሚደገፉትን ጳጳሳት አንጋግቶ ተመልሶ መጣ፡፡ እንደገና በዓቢይ የሚደገፉትን ጳጳሳት ይዞ ወደ ቤተ መንግሥት በመሄድ በነ አባ ሳዊሮስ አማካይነት የቤተ ክርስቲያንን ቁልፉ ለጠ/ም ዐቢይ እንዲያስረክቡ አደረገ፡፡ ዳንኤል ለኢትይዮጵያ ያለውን ፍቅር በዚህ ሁሉ ስለካው የምረዳው በዱኩላና በነበር መካከል ያለውን ፍቅር ነው፡፡

በነብርና በድኩላ መካከል ያለ ፍቅር

በዳንኤልና በቤተ ክርስቲያን መካከለ ያለ ፍቅር አድኖ በሚበላት ነብርና ታድና በምትበላዋ ድኩላ መካከል ያለው

ፍቅር ነው እንድል እገደዳለሁ፡፡ ነብሩ ሥጋዋን አላምጦ አጥንቷን ቆርጠሞ ደሟን ጠጥቶ ሆዱን ለመሙላት ጥማቱን ለማርካት ንፍሱ እስኪወጣ ድኩላዋን ይወዳታል፡፡

“አብሮ የበላ አብሮ ይሞታል” የምንለውን ዝየ ልፈጽም ብየ ነው ካላሉን በቀር ዶክተር ዳኛቸው የዳንኤልን አራዊታዊ ፍቅር የተረጎሙበት አተረጓጎም እጅግ የተፋለሰ ነው፡፡ በዚህ አይነት ተፋልሶ አተረጓጎም የሚያሰትምሩ ከሆነ ለተማሪወቻቸው እጅግ አዘንኩላቸው፡፡ የክቡር ብርሃኑ ድንቄንም ንግግር እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡

ክቡር ብርሃኑ ድንቄ በከንሳስና በሴንት ሉስ መካከል ባለችው ኮሎምብያ በምትባለው ከተማ ውድቀው የተረሱ ከተላላቅ ኢትዮጵያውያን አንዱ መተርጉም ነበሩ፡፡

ከከንሳስ ወደ ሴንት ሉስ፡ ከሴንት ሉስ ወደ ከንሳስ ስመላለስ ኮሎምብያን ድቅድቂያት ባለፍኳት ቁጥር የተናገሯቸው ትዝ እያሉኝ እንባየ ይፈሳል፡፡

እኒህ ታላቅ አባት በዘመኑ ትምህርት ሰለጠነናል የሚሉ ለሆዳቸው ብቻ የሚጥቅመውን መርጠው በቀረው ኢትዮጵያ ነክ በሆነው ሁሉ እንደሚዘምቱ “ኢትዮጵያውን የኢትዮጵያን ባህልና ስነ ልቡና ከሕሊናቸው አውጥተው ጥለውታል፡፡ የቀራቸው እንጀራ ብቻ ነው፡፡ እንጀራውንም እስካሁን የጠበቁት ስለ ባህልነቱ ስለቀርስነቱ አክብረውት ሳይሆን የሆድ ነገር ስለሆነባቸው ነው” ብለው ተናግረው ነበር፡፡

ዳንኤል የጻፈው ለቅርስ ለታሪክና ለኢትዮጵያዊነት ብሎ ሳይሆን የደራ ገብያ እየፈለገ መጽሐፍ ሸጦ የሚያገኘውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ለሆዱ ብሎ ነው፡፡ ዶክተር ዳኛቸው መደገፋቸው “አብሮ የበላ አብሮ ይሞታል” የሚለውን እዳ ለመወጣት ነው፡፡

ዶክተር ዳኛቸው “አንተ ትጠላትለህ ብየ ለምንድነው በእንደዚህ ያለ ግምት የምንቀሳቀሰው?” ብለው ለጠየቁት አንድ ዕብራዊ ጸሐፊ ዳንኤልን ለሚመስሉ ዕብራውያን “የሰሙት ቃል ከሰሚወች ጋራ በእምነት ስላልተዋሀደ አልጠቀማቸውም” (ዕብ 4፡2) ብሎ የተናገረው ተጨማሪ መልስ በመሆን የበለጠ የሚያረካቸው ይምስለኛል፡፡

ዳንኤል የመገልበጥ እንጅ የመመራመር ስሜት አልነበረውም፡፡ የገለበጣቸው ስለ ሰው ክብር ተላልፎ መሞትን የሚያንጸባርቁ የጻድቃን ሰማእታት ተጋድሎ ናቸው፡

፡እየተመራመረ ቢጽፍ ኖሮ ጻድቃን ሰማእታት ካደረጓቸው ብዙ ነገሮች አንዲት ነገር በህሊናው ብቅ ትልለት ነበር፡፡

ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ የዳንኤል ፈላስፋነት ከደበቁበት ፈልቅቆ ወደ ብርሃን ማውጣት እንዳይችል አድረገው በማይገሰስ ግንብ ውስጥ ከተው በማይፈታ መስነግት ቆልፈውበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኔ የሰጠችኝን “አናቅጸ ሲኦል ኢይሄይልዋ” የሚለውን ጧፍ አብርቼ ወደ ውስጥ ስገባ የዶክተር ዳኛቸውን የተሳሳተ ምለምታ አገኘሁ፡፡

መላ ምትነቱን የሳተው የዶክተር ጌታቸው መላ ምት፡፡

ፈላስፋ በፖለቲካ የማይጠለፍ ከነባራዊ በመነሳት አዲሱን ክስተት በነባራዊው ክስተት ተርጉሞ “ጻድቃን የሐውርወ ወኃጣን ይስእንዎ” እንዲል የኔ ቢጤ ያልተማረ ሚኒሽያው መተርጎምና መገምገም ያልቻለውን ለመገምገም ብቃት ያለው ማለት ነው፡፡ ባሜሪካና በጀርመን ያለን ያልተማርን ሚኒሽያወች ማየት የተሳነንን ቀድመው በማያት ለማንቃት ለመጠቆም ነበር፡፡ ይህ ሐላፊነት በመንፈሳውያን ቀሳውስት መሪወች ላይ የበለጠ ቢሆንም እንደ ዶክተር ዳኛቸው ያለውን ፈላስፋ እኩል ይመለከተው ነበር፡፡

ዶክተር ዳኛቸው ህዝቡ ከጭንቅላቱ ውስጥ አውጥቶ የጣለውን ዳንኤል ክብረትን መልሰው በህዝብ ጭንቅላት ላይ አክሊል አድርገው ለመጫን ባደረጉት ሙከራ “በዚህ እድሜየ” እያሉ በጠቀሱት ረዥሙ ዕድሜያቸው ባጠራቀሙት ልምዳቸውና በፍልስፍናቸው አሽሞንሙነው አቅረበውታል፡፡

እንኳን ዳንኤልን ከወደቀበት ሊያነሱት “ብእሲ ምሁር ዘተገሰጸ ብዙኃ የአምር ወዘአፈድፈደ ሕማመ ጥበበ ይነግር“(ሲራክ 31፡9)፡፡ በሚለው ምንባብ ላይ የተመሰረተው ኢትዮጵያዊው የአንድምታ አተርጓጎም ራሳቸውንም ከዳንኤል ጋራ ደምሮ አውርዶ ጥሏቸዋል፡፡

ማለትም፦ የተማረ ይልቁንም በረዥም ዕድሜው ውጣ ውረድ ሕይወቱ የተስተካከለ ሰው ካንደበቱ የሚፈልቀው ሰሚውን ከስህተት የሚያድን ጥበበኛ ነው፡፡ በዶክተር ዳኛቸው ይህንን ጥበብ አላገኘሁትም፡፡

ይልቁንም “እስመ ለብዙኃን አስሐቶሙ ሕልም ወወድቁ እንዘ ኪያሁ ይሴፉ”(ሲራክ 31፡7) እንዲል፦ማለትም፦ የተመኙትና ተስፋ ያደረጉት ሕልማቸው ብዙወቹን አሳሳታቸው ተብለው ከተፈረጁት አንዱ ሆነው አገኘኋቸው፡፡

ዶከተር ዳኛቸው እንደ ቀደሙ ፈላስፎች ከውጭ ሰርገው የሚገቡትን የማይጠቅሙ ሐሳቦች ይቅሩና የራስቸውን ሕልም እንኳ ከነባራዊው ክስተት ያላፈነገጠ ከሕዝብ ፈቃድ ያልወጣ እንዲሆን በመጣር ባሜሪካና በጀርመን ከምንገኝና አልተማራችሁም ሚንሻወች ናችሁ ከሚሉን የበለጠ የተጠነቀቁ ሊሆኑ ይገባቸው ነበር፡፡

ያልተማሩ ሚኒሽያ ናቸው ብለው የሚአጣጥሉን ባሜሪካና በጀርመን የምንኖር ቀድመን ተረድተን ዳንኤልን ለጠቅላይ ምንስቴሩ የምትሰጠው ምክር አገር እየጎዳ ነው፡፡ ይልቁንም ሕዝበ ክርስቲያኑን እያስጨፈጨፈ ነው እያልን ድምጻችንን እያሰማን ሳለን ራሳቸው “እኔ ገና አጣጣሜ ሳልጨርስ” እንዳሉት በዳንኤል ምክር የሚካሄደውን ገና በማጣጣም ላይ ነበሩ፡፡

ዶክተር ዳኛቸው በማጣጣም ላይ የነበሩበትን ጣእም እንመልከተው፡፡

ያጣጥሙት የነበረው የኢትዮጵያ ገጸ ምድርግ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በኦርቶዶክሳውያን ወገኖች አካል ሬሳ መሸፈኑን ነው? የገጸ ምድሩ አፈር ከፈሰሰው ከክርስቲያኖች ደም ጋራ ተቀላቅሎ በሚተንፈሱት አየር ባፍንጫቸው መጋታቸውን ነው? ከሚመነጩት ወንዞች ጋራ ተቀላቅሎ የሚጎርፈውን የወገንን ደም መጠጣቸውን ነው? በመላ ኢትዮጵያ የሚንፍሰው አየር ከወገን ደም አጽምና ሥጋ ጋራ የተቀላቀለውን አፈር ከመሬት እየጋፈ ቆሞ በሚሄደው አካላቸው ላይ በመበተን በቁማቸው መቀበራቸውን ነው? ሕጻናቱ በሙታን እናቶች ደረት ላይ ተጣብቀው ከደረቀ ጡት ወተት ለማመንጨት ሲታገሉ ማየታቸውን ነው? እናቶች የሞቱ ልጆቻቸውን እሬሳ ታቅፈውና በልጆቻቸው ሬሳ ላይ ወድቀው ማየታቸውን ነው? በትግራይ ያሉት እናቶች በልጆቻቸው ገዳዮችና አሰገዳዮች መርዶ ነጋሪነት በማልቀስ ላይ መሆናቸውን ነው? ዶክተር ዳኛቸው ይህ ሁሉ በሚፈጸምባት ኢትዮጵያ አልነበርኩም ሊሉ ነው?

ብልጽግና በወገን ላይ እያደረሰ ያለውን ይህንን ሁሉ ግፍ ለማስቆም በመታገል ያለውን ፋኖን ጃዊሳ ብሎ ዳንኤል በመዝለፉ ከብልጽግና ደጋፊ በቀር የቀረውን ሁሉ ዜጋ አስቆጥቷል፡፡ በገር ውስጥ ባሜሪካና በጀርመን የምንኖረው

ዳንኤል ለጠ/ም የሚሰጠው ምክር ልክ አለመሆኑን ገልጸን ለማሳይት ሞክረናል፡፡

በዳንኤል ላይ የተሰነዘረውን ተግሳጽ በመቃወም ዶክተር ዳኛቸው በአሜሪካና በጀርመን ያለነውን ኢትዮጵያውያን ያልተማሩ ሚኒሻወች በማለት የተናገሩት የተሰለፉበትን ሙያ “ወጉርዔ ይፈልጦ ለኩሉ ጣእመ እክል ወከማሁ ልቡ ለጠቢብ ይፈልጥ ነገረ ሐሰት”(ሲራክ 36፡29) በሚለው መጽሐፍ ስፈትሸው ገና በርበሬና ጨው አጣጥሞ ያልተረዳ ሕጻን ሆነው አገኘኋቸው፡፡

ማለትም፦ ጉረሮ ከመዋጡ በፊት የህሉን ጣእም አጣጥሞ እንደሚያውቅ የተማረ አዋቂ ነኝ ብሎ ለማስተማር በሰው ፊት የሚቆም ሰው በሀሰት በእውነት መካከል ያለውን ቁልፍልፍ ለይቶ ሊያውቅ ይገባል፡፡ ይሁን እንጅ ዶክተር ዳኛቸው በዚህ ንግግራቸው በሙያቸው ልክ ሆነውና በቅተው አላየኋቸውም፡፡

“ዕቀብ ልበከ እምነ ዘይመክረከ ቅድመ አእምር ትካዘ በዘይፈቅደከ እስመ እንበይነ ርእሱ ያመክረከ (37፡8)፡፡ እንዳለው መጽሐፍ በህዝብና ባገር ላይ ያንዣበበውን መከራ በጀርመንና ባሜሪካ ካለን ሚኒሽያውች አስቀድመው ተረድተው በገለጹት ነበር፡፡ ይህም ማለት፦”ህሊናህን ስልሎ ከሚንቅህ የቅርብ ጠላት ራስህን ጠብቅ፡፡ ወደራሱ ምኞት በመጎተት ይፈታተንሀልና ወዴት እንደሚጎትትህ እወቅ”

እንደ ዶክተር ዳኛቸው ያሉ የፍልስፍና መምህራን እንደነ ዳንኤል የመሳሳሰሉ ሸፍጠኞች በተብለጭላጭ ሸፍጣቸው የህዝብን ጭንቅላት እያሽከረከሩ ህዝብን ካደጋ አገርን ከመፍረስ እንዲታደጉ ነበር፡፡

እንዲያውም በ cortex ሀሳብ በሚመዘግበው ጨቅላቱ ላይ ምንም ያልተሳለበት መገምገሚያ የሌለው ገና ከናቱ መሕጸን ዛሬ የተወለደ ጨቅላ ሆነው የዳንኤልን ሐሳብ እንዳለ በመጋት እኛንም ሊግቱን ሞከሩ፡፡

“ዘፍጡነ የአምን ቀሊል ልቡ ወዘይገብር ኃጢአተ ላዕለ ነፍሱ ይኤብስ ”(ሲራክ 19፡4) እንዳለው ማለትም፦ የተነገርውን ሳይመረምር ሳያበጥር ፈጥኖ በመቀበል አምኖ የሚከተል ህሊናውን በጸጸት የሚጎዳ ኃጢአት የሚሰራ ቀሊለ ልብ ሆኑ፡፡

ከተማሯቸው ትምህርቶች ካነበቧቸው መጻሕፍቶች በአሜሪካና በኢትዮጵያ በቆዩባቸው ዘመናት ካጠራቀሟቸው ትዝብቶች የዳንኤልን ሸፍጥ መለየት የምታስችል ትንሽ የፈሊጥ ብልጭታ እንዴት ያጣሉ?

ዶክተር ዳኛቸው የዳንኤልን ሸፍጥ መለየት የሚያስችል ትንሽ የፈሊጥ ብልጭታ ማጣታቸው፡ ዓለም በጨለማው በነበረችበት ዘመን ጭንቅላታቸው እንደ አጥቢያ ኮከብ ያበራ የነበሩት መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የተናገሩት እንዳጤነው አደረገኝ፡፡

መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ “የኢትዮጵያን ስነ ልቡና

ሳንቀርጽባቸው ኢትዮጵያውነትን ሳናሰርጽባቸው

ስንዋጋቸው ወደ ነበሩት ፈረንጆች ይማሩ እያልን አንላኳቸው፡

፡ኢትዮጵያ የተጠበቀችበትን ስነ ሕሊና ሳናስረዳቸው ወደ ውጭ የሚሄዱ ሁሉ ባዶ ሸክላወች ናቸው፡፡ ቂማቸውን የማይረሱ ጠላቶቻችን ባዶ ጭንቅላት ሲያገኙ የራሳቸውን አመድና አተላ ይሞሏቸዋል፡፡ በባዶ ጭንቅላታቸው የዛቁቱን አተላና አመድ አምጥተው በኢትዮጵያ ላይ ይደፉባትና ለማጥራት በሚታገሉት ጀግኞች ልጆቻችን ላይ መከራ እንጭንባቸዋለን”፡ ያሉት ታሪካዊው ንግርታቸው ዛሬ ዶክተር ዳኛቸውን በመሳሰሉ ያስኳላ ተመሪወች የተፈጸመ መሰለኝ፡፡

ታላቁ ፈላስፋ አባታችን መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ባንድምታ አተረጓጎም ክሂሎታቸው በነባራዊው ኢትዮጵያዊ ኩነት ከውጭ የሚመጡትን ክስተቶች አበጥረው በማየታቸው ከሁለቱ ስብቀት የተፈነጠረውን መላምት ገለጹት እንጅ ህልምም ጥንቆላም አልነበረም፡፡

እነሆ ዛሬ ኢትዮጵያና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያህያ አፈላላጊ በሚመስሉ በብዙ philistines ማለቴ አብያጽሐሳውያን ተከበዋል፡፡ ዶክተር ዳኛቸው በመሳሰሉ ያስኳላ ተማሪወች ከውጭ እየዛቁና እየተሸከሙ አምጥተው በኢትዮጵያዊነት በኦርቶድክስነት ባማረኛ ቋንቋና ባማራነት ላይ የደፉትን አተላና አመድ ለመጥረግ በመታገል ላይ ባሉት በፍኖወችና በመሳሰሉት ኢትዮጵያውያን ላይ ወደቀባቸው፡፡

የዶክተር ዳኛቸው ንግግር ቀስቅሶኝ ያቀረብኩትን ሀተታ ባንድ ሌላ ኢትዮጵያዊ ሊቅ አነጋገር እደመድማለሁ፡፡

ባንድ ዘመን አቶ በዛ አቶ ለማና አቶ ጀንበር የሚባሉ የምንግሥት ሹማምንት ሌቦች ያገሩን ሁሉ በረት እየከፈቱ ጉረኖ ጋጥ እየሰበሩ ሙክቱን በሬውን ላሙን እየዘረፉ ሕብረተ ሰቡን አስቸገሩ፡፡ ባለአገር ለመንግሥት ቢጠቁምም ምንግሥት ራሱ ከሌቦች ጋራ እየተናበበ አድራጊና አሰድራጊ ሆኖ የሚጠቁመውን ባለአገር መደብደብ ማሰር ጀመረ፡፡

በህዝቡ መሰቃየት ይናደዱ ይበሳጩ የነበሩ መላከ ብርሃን አድማሱን የመሰሉ ሊቅ፡ ላውጫጭኝ ስብሰባ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ቆሙና “ወገኔ ባላገር ሆይ እኔን ስማኝ” ብለው በጭብጨባ ህዝቡን ዝም ካሰኙ በኋላ “ሌባው ባካባቢያችን በዛ፡፡ ባገራችንም ሌባው ለማ፡ ጀንበር በሰረቀ ቁጥር እንዴት እኛ ባላገሮች ስንሰቃይ እንኑር? ብለው ባረፍተ ነገር የሌቦችን ስም ደርድረው ተናገሩ፡፡

በምንግሥት ተደግፈው ህዝብ ሲዘርፉና ሲገሉ የነበሩትን አቶ በዛ፡ አቶ ለማና አቶ ጀንበር የተባሉትን የመንግሥት ሹመኞች ቅኔውን የተረዳው ፋኖ ከህዝቡ መካከል እዚያው አንቆ ይዞ የፍጥኝ አሰራቸው፡፡ ባለአገርም ከግፈኞች ተገላገላገለ፡፡

ይህ ዘመን በዳንኤል ክብረት ምክር እንደ ጠ/ም ዓቢይ የሚመሩ ያህያ አፈላላጊወች የበዙበትና የለሙበት ዘመን ነው፡

25

ጀንበር በወጣችና በጠለቀች ቁጥር የሚሰማው ዘረፋ መፈናቀል ስደት ብዝበዛ ግድያና ዋይታ ነው፡፡

“አሀያ ያየህ ና ወዲህ በለኝ፡ አህያየን አግኝቻታለሁና በከበባት ጅብ እንዳትበላ ርዱኝ” እያለ በውስጥም በውጭም ያለው ፋኖ ድምጹን እያሰማ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ይህን የመሰለ ችግር ሲገጥማት እጆቿን የምት ዘረጋው ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡ የምትዘረጋቸው እጆች የማይዳሰሱ አካል የሌላቸው ጥላወች አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ እጆች ተብትበው አስረው አፈላላጊ መስለው ከሚቀርቡ አፈላሊጊ ሌቦችና ከከበቧት ጅቦች ለማትረፍ በመታገል ያሉት የፍኖወች እጆች ናቸው፡፡

ካፈላላጊ ሌቦች ራሳችሁን አላቃችሁ ከፋኖ ጋራ እጆቻችሁን ለግዚአብሔር በመዘርጋት ድምጻችሁን ለዓለም በማሰማት ለሙያችሁ ክብር ብትቆሙ የሞራል ግዴታችሁን የምትወጡ ይመስለኛል ብየ ለዶክተር ዳኛቸውና ለመሰላ ችሁት ሁሉ ፋላስፎች ካልተማሩት ሚኒሽያወች አንዱ የሆንኩ ወንድማችሁ መልእክቴን በትህትና አቀርብኩላችሁ፡

ይቆየን

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop