የኮንጎ፣ የኮሪያ ዘማቾች እና የኢትዮጵያ አብዮታዊ ሰራዊት ሁሌም በክብር ሊዘከሩ፣ ሊታወሱ  ይገባቸዋል!!

አገርህን ጠላት እንዳይደፍራት ወታደር ሆነህ ጠብቃት፣ እንደ አባቶችህ ጀግና ሆነህ አሳያት፣ በጀግንነት ታሪክ ሥራላት። ታሪክ ያለው ከወታደርነት ነው፣ ጀግንነት ያለው ከወታደርነት ነው። ጀብዱ ያለው ከወታደርነት ነው፣ ታላቅ ስም ያለው ከወታደርነት ነው…።›› የሚል የአባቶቻችን የጀግንነት የአደራ ቃል ውርስ አለን እኛ ኢትዮጵያውያን፡፡

በርግጥም ደግሞ ታሪካችንን ስንፈትሽም- ታላቁ የዓድዋ ድል የአርበኝነት፣ የወታደርነት ውጤት ነው፡  የአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራና የኢትዮጵያዊያን ድል የወታደርነት ውጤት ነው፡፡ ካራማራ የወታደርነት ውጤት ነው፣ የኢትዮጵያ የተከበረ ታሪክ የወታደር ታሪክ ነው፡፡ ለምን ሲባል ኢትዮጵያ የተከበረችው በጀግኖች ልጆቿ፤ በወታደሮች ብርቱ ክንድ ነውና፡፡

ዛሬ እኔም፣ አንተም ሁላችንም የቆምንባት የኢትዮጵያ ምድር በቀደሙ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት መሠረትነት የተገነባ ነው፡  ታሪክ እንደሚነግረን በኢትዮጵያ ጉዳይ ሁሉም አርበኛ፣ ሁሉም ጦረኛ ነው፡፡ ሁሉም ሰንደቁን አስቀድሞ ይገሰግሳል፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ ጀብዱ እየሠሩ ዛሬ ላይ ኮርተን የምንኖርባት አገር፣ ኮርተን  የምንናገረው፣ በአሸናፊነት የምንመሰክረው ታሪክ አኑረውልናል፡፡

ከጉንደት እስከ ጉራዕ፣ ከዓድዋ እስከ ማይጨው፣ ከኦጋዴን እስከ ካራማራ… ያበበ የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና እምቢ ለነፃነቴ ባይነት፣ የኢትዮጵያ ድንበር ሳይገድበው አውሮፓ ምድር ሮም/ጣሊያን ድረስ ተሻግሮ ዓለምን ያስደመመ፣ በኮሪያ ልሣነ ምድር፤ በአፍሪካ (በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳንና በሶማሊያ ምድር የኢትዮጵያ ሰራዊት በተጋድሎ ድልና በሰላም አስከባሪነት ትልቅ ስምና ዝናን ያተረፈ ነው።

እነዚያ ጀግኖች ታሪክ ሠርተው፣ ስማቸውን ከመቃብር በላይ ትተው ‹አገሩን ያስደፈረ ታሪክ ይውቀሰው፣ አፅማችንም እሾህ ሆኖ ይውጋው› ብለው ቃል ኪዳን አስረው፣ አደራ ሰጥተው በክብር አልፈዋል። ትናንትና በመስቀል አደባባይ ለ116ኛ ጊዜ በተከበረው የመከላከያ ሰራዊት ቀን በኮንጎና በኮሪያ ዘምተው ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በጀግንነትና በድል ከፍ ያደረጉና በክብር ያስጠሩ  አባቶቻች ተዘክረው ነበር። በወታደራዊ ሰልፍ ትርዒትም /Military Parade/ ዐይተናቸዋልና ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ክብር ተሰምቶናል። ታሪካችን ምልዑና የተከበረ  ማድረግ የምንችለው  ትናንትናን ጥለን ዛሬን አንጠልጥለን አይደለምና የኢትዮጵያን በነጻነትና በሉዓላዊነቷ አስከብረው ያቆዩልንን የትናንትና ጀግኖቻችንን ሁሌም በክብር ልንዘክራቸው ይገባል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  " የጥለዛ ፓለቲካ " ፣ሥለ ፍትህ ፣ ሥለ ሠላም ሥለ ዴሞክራሲ ወዘተ ደንታ የለውም  - መኮንን ሻውል  ወልደጊዮርጊስ 

በዚህ የጀግንነት ገድል ታሪክ ውስጥ ደማቅ ታሪክን አሻራ ከተዉ ኢትዮጵያውያን መካከል- ከበርካታ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ታላቅ አኩሪ ታሪክን ለሀገሩ ያስመዘገበውን አርበኛውንና በተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ በመሆን ኮንጎ ድረስ የዘመተውን የወላጅ አባቴን አኩሪ የታሪክ ቅርስ ፎቶዎች ላጋራችሁ ወድድኹ፡፡

ምስሉ የኢትዮጵያዊው ጀግና አርበኛ እና በኮንጎ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ሆነው ያገለገሉትና እስከ በሕይወታቸው እልፈት ድረስም በጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በጸሐፊነት ያገለገሉት ወታደራዊ መኮንን፣ አርበኛው፣ የመ/አ ወርቁ ደስታ ምስሎች ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share