October 3, 2023
86 mins read

ለመሆኑ አንድ ዐይነት አመለካከት ያላቸው ምሁራን አሉ ወይ? አንደኛውስ ከሌላው በምን ይለያል?

          ግልጽ ያልሆኑና አወዛጋቢ ነገሮችን ለመፍታት ያህል!

         ፈቃዱ በቀለ(/)

        ጥቅምት 03 2023

 

ምሁራንና ምሁራዊ አስተሳሰብን አስመልክቶ በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ አለመግባባት አለ። አብዛኛውን ጊዜ ምሁሩ ቢስማማ፣ ወይም ደግሞ ለመተባበር ቢችል ኖሮ ይህ ሁሉ ነገር ባልተፈጠረ ነበር የሚል አነጋገር ይሰማል። ዋናው ችግር ግን የመስማማትና ያለመስማማት ጉዳይ ሳይሆን እንዳንስማማ የሚያደርጉን ነገሮች በመኖራቸው ብቻ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ መንፈሳችን በጥሩ ዕውቀት ስላልተኮተኮተና፣ አስተሳሰባችንም ክሪቲካል አመለካከት እንዲኖረን ሆኖ ለመዳበር ባለመቻሉ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሳይንስና ኢ-ሳይንሳዊ በሆነው የአስተሳሰብ፣ የምርምርምርና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በማንበብና በመረዳት፣ ወይም በድሚገባ ባለማንበብና ባለመረዳት መሀከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ባለመቻላችን ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግም በአገራችን ምድር ከመሰረተ-ትምህርት ቤት ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እስክንገባ ድረስ የሚሰጠው ትምህርት ሳይንሳዊና ፍስልፍናዊ አስተአሰብን በጭንቅላታችን እንዳናዳብርና መመሪያችንም ለማድረግ ባለመቻአችን ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንዶች አሜሪካ የተማሩ ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ አውሮፓ ውስጥ የተማሩ አሉ። አሜሪካ የተማረውና ብዙ ዓመታት የኖረው በዚያ የህብረተሰብ የአኗኗር ስልት አስተሳሰቡና  መንፈሱ የታነፀ ሲሆን፣ አውሮፓ ውስጥ የተማረውን በሌላ ዐይን ነው የሚመለከተው። ራሱንም የሚያየው እንደ አሜሪካኑ የኦሊጋርኪ መደብ ስለሆነ ሌሎችን በበላይነት ስሜት ነው የሚመለከተው። ሰልሆነም ልክ እንደ አሜሪካኑ ኦሊጋርኪ መደብ ስለሰው ልጅ፣ ስለ ህብረተሰብና ኢኮኖሚ ዕድገት ያለው አስተሳሰብ ለየት ያለና፣ የአንድ አገር ችግር በነጻ የገበያ ኢኮኖሚ ብቻ የሚፈታ ነው ብሎ የሚያምነው።  በሌላ ወገን ሁሉም ባይሆን  አውሮፓ ውስጥ የተማረው የህብረተሰብን ዕድገትና የሰውን ልጅ ሚና በልዩ መነፅር ነው የሚመለከተው። ይህም ማለት ከአገራችን ወጥተን የተለያዩ አገሮችና አህጉራት ውስጥ የተማርንና የኖርን፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ሲሰሩ የነበሩና ጡረታ ወጥተው የፖለቲካ ሜዳውን ያጣበቡት ሁሉ ለአገራችን የሚበጅ ሁላችንንም የሚያስማማ አንድ ዐይነት እሴት ሊኖረን አይችልም። ከዚህም በላይ ባለፉት ሰላሳና አርባ ዓመታት የአገራችንና የዓለምን ሁኔታ አስመልክቶ የመከራከሪያ መድረክ ለማዘጋጀትና ለመከራከር ባለመቻላችን ለአገር ግንባታ የሚያመች ተመሳሳይ እሴትና የአገር ወዳድነት ስሜት በፍጹም ልናዳብር አልቻልንም።  በተለይም በፖለቲካ ውስጥ ገብተን እዚህና እዚያ የምንሯሯጥ መመሪያችንና የተወሳሰቡ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደምንችል የሚታወቅ ነገር የለም። ሁሉም በየፊናው ፖለቲከኛ ነኝ በማለት ሲናገር ይሰማል። ስለሆነም በአንድ በኩል ስለአገራችንና ሰለፖለቲካ እያወራን፣ የምናወራው ግን በተለያየ ቁንቋ ነው። ይህም ማለት በመሀከላችን ከፍተኛ አለመግባባት አለ ማለት ነው።

ከዚህ ሀቅ ስንነሳ ጥያቄ የመጠየቅ፣ የመከራከርና የነገሮችን አመጣጥ ሂደት ጠጋ ብሎ ለመመለከት የሚያስችል በሁሉም አቅጣጫና በጥልቀት እንድንመረምር የሚያስችለን ዕውቀት በፍጹም ለማዳበር አልቻልንም። የዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በአገራችን የሚሰጠው ትምህርት ካለምንም ጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም ለተሟላና ለተስተካከለ ዕድገት ያመች አያመች እንደሆነ ትችታዊ ወይም ክሪቲካል በሆነ መልክ ሰተት ብሎ እንዲገባና በየትምህርትቤቱና በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሰጥ በመደረጉ ነው። አንዳንዶቻችንም ወደ ውጭ አገር ወጥተን የመማር ዕድል ስናገኝ ቀድሞውኑ አስተሳሰባችን በተወላገደና ጭንቅላትን በማያድስ ትምህርት ስለተቀረፀ በየካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ያለውን በደንብ የተደራጀ፣ የተቀላጠፈና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተውን የአመራረት ስልት ጠጋ ብሎ የመመርመር ፍላጎት የለንም። አብዛኛዎቻችንም በፍጥነት ትምህርታችንን ጨርሰን ስራ ለማግኘትና ደሞዝ ለመብላት ስለምንፈልግ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮችና በአሜሪካን ምድር በሳይንስ ኮሙኒቲው ውስጥ ስለህብረተሰብ ዕድገት፣ ስለባህልና ስለተፈጥሮ ሳይንስ የሚደረገውን ትምህርታዊ ክርክር እዚያ ገብተን ስለማንሳተፍና በቀሰምነው የአካዴሚክስ ትምህርት ብቻ ስለምዝናና በአጣቃላይ  ሲታይ በተለይም በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጸው የካፒታሊስቱ ዓለም ከዝቅተኛ ሁኔታ በመነሳት እዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበ ደረጃ ላይ እንዴት ሊደርስ ቻለ? ብለን ጥያቄ በማንሳት መልስ ለመፈለግ በፍጹም አንቃጣም። በአብዛኛዎቻችን ዕምነት ይህ ዐይነት ዕድገት ለዝንተ-ዓለም የኖረ የማይለወጥና በዚያ የሚጓዝ ነው የሚመስለን። አሊያም ደግሞ ከሰማይ ዱባ እንዳለ ነገር ነው ተደርጎ የሚወሰደው። በተለይም ከአንትሮፖሎጂና ከፍልስፍና ዕውቀት ጋር ያለን ዝምድና በጣም የላላ ስለሆነ የህብረተሰብን ዕድገት ታሪክ ጠጋ ብሎ የመመርመር ፍላጎት የለንም።  ጊዜም እያለፈ ሲሄድ ባለን የኑሮ ደራጃ በመደሰት ተጠቃሚ ከመሆን በስተቀር ወደ ውስጥ ጠጋ ብሎ በመመልከት ትምህርታዊ ጽሁፎችን የማውጣት ልምድ ለማዳበር አንፈልግም። ይህ ዐይነቱ የመንፈስ አቀራረጽ ሳንወድ በግድ የግዴታ ወደ አለመስማማት፣ አንዳንዱ ደግሞ በአውቃለሁ ባይነት ሌላው የሚለውን ለመስማት ባለመፈለግ የተነሳ አንድ ሰው ክሪቲካል አስተሳሰብ ያለው ከሆነና ጥያቄም የሚጠይቅ ከሆነ ሰይጣናዊ የሆነ አስተሳሰብ እንዳለው፣ ወይም ከሌላ ፕላኔት እንደመጣ ተደርጎ ይቆጠራል። ዞሮ ዞሮ ለእንደዚህ ዐይነቱ የዕምቢተኝነት ስሜት ወይም ለመስማማት አለመፈለግ ዋናው ምክንያት በጥልቀትና ከሁሉም አቅጣጫ ጭንቅላታችን እንዳያይ ከመጀመሪያውኑ ስለተጋረደ  ብቻ ነው።

ያም ተባለ ይህ በእኛ በኢትዮጵያውያን መሀከል ያለው ትልቁ ችግር ስለምሁር ያለን ግንዛቤ የተሳሳተ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ምሁር ማለት በተወሳሰበ መልክ የሚያስብ፣ በነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለና፣ አንደኛው ለሌላኛው እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል፣ ወይም ደግሞ በተክክል መልክ ከተዘጋጀ ወይም ከተስተካከለ በአጠቃላይ ሲታይ ዕድገትን አጋዥ አንደሚሆን ስንቶቻችን እንደምንረዳ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው።  በተለይም በአሁኑ በግሎባላይዤሽን ዘመን ሁሉም ነገር ተዘበራርቆ በሚገኝበትና፣ ዕውነትን ከውሸት መለየት በማይቻልበት ዓለም ውስጥ የምሁርን ታርጋ የለጠፈ ሁሉ ተመሳሳይ ዕውቀትና ነገሮችን የመረዳት ኃይል ሊኖረው በፍጹም አይችልም። በተለይ ደግሞ እንደኛ በመሰለ ህብረተሰብ ውስጥ ሳይንሳዊ ዕውቀት ማለት ምን ማለት ነው? ሎጂካዊና ዲያሌክቲካዊ አስተሳሰብስ በምን መልክ ይገለጻሉ? ተብሎ ጥናት በማይካሄድበት አገር በተራ የአካዴሚክስ ትምህርት የሰለጠነን ሰው ምሁር ነው ብሎ መጥራት በፍጹም አይቻልም። ምክንያቱም አንድ ሰው ምሁር ነው የሚያሰኘው ከተራ አካዴሚክስ ስልጠና ባሻገር ልዩ ልዩ መጽሀፎችን በማንበብ ጭንቅላቱን ሲያዳብርና፣ በየጊዜውም በህብረተሰባችን ውስጥ ያለውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ በነጻ ገበያ ስም የሚስተጋባውን የውንብድና አመለካከትና ሰፊውን ህዝብ እንዳይላወስና እንዳያስብ፣ እንዲሁም ፈጣሪ እንዳይሆን ቆልፈው የያዙትን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ከውጭ ሰተት ብለው የገቡትን የህዝባችንን ኑሮ የሚያመሰቃቅሉ ነገሮችን እየተከታተለ በማጥናትና ህዝቡ በሚገባው የአጻጻፍ ስልት ተከታታይ የጥናት ጽሁፎችን ለአንባቢያን የሚያቀርብ እንደሆን ብቻ ነው። በተለይም የዶክትሬት ዲግሪ ጨብጦ በየጊዜው ሳይንሳዊ ጽሁፎችን የማያወጣና ለዕድገት የሚያመቹ መጽሀፎችን የማይጽፍ በፍጹም እንደምሁር ሊቆጠር አይችልም። በመሰረቱ የዶክትሬት ዲግሪን ጨብጠው የህብረተሰብ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ ተከታታይ ሳይንሳዊ የጥናት ጽሁፎችንና መጽሀፎችን የማይጽፉ ዲግሪያቸው መነጠቅ ያለበት ይመስለኛል።  በተለይም በነጻ ገበያ ስም የሚያወናብዱና ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል እንዲፈጠር የሚያደርጉ እንደነዚህ ዐይነት በምሁራን ስም የሚነግዱና ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ከመቅረፍና ከማስወገድ ይልቅ የሚያባብሱ ግለሰቦች የግዴታ በህግ ፊት ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ብቻ ሳይሆን የዶክትሬት ማዕረጋቸውም መነጠቅ አለበት።

ለማንኛውም በአገራችን ምድር ያለውንና በውጭው ዓለም የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ምሁር ባይ ነኝ ችግር ለመረዳት ከአውሮፓው ሁኔታ ጋር እያወዳደርን እንመልከት። ይሁንና ግን በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካን ምድር በተለይም የኒዎ-ክላሲካል ወይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ አስተሳሰብ ባላቸውና በሌላ ወገን ደግሞ በፍልስፍናና በሳይንስ ኮሙኒቲው  ውስጥ በመካተት ጠለቅ ያለ ጥናት በሚያካሂዱት መሀከል የሰማይንና የምድርን ያህል ርቀት አለ። በሌላ አነጋገር፣ በኒዎ-ክላሲካል ወይም በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ የሰለጠኑና የሚሰለጥኑ ሰዎች ህብረተሰብን እንደህብረተሰብ፣ ሰውንም እንደሰው ሳይሆን የሚመለከቱት ጥቅሙን እንደሚያሳድድ እድርገው ስለሚገነዘቡና ማህበራዊ ባህርይም እንደሌለው አድርገው ስለሚቆጥሩ ነው። በአሁኑ ወቅትም ይኸኛው በተለይም ከአሜሪካን በመነሳት በዓለም አቀፍ የተስፋፋው የተወላገደ ወይም ኢ-ሳይንሳዊ አስተሳሰብ በመስፋፋቱ፣ ለማህበራዊ፣ ለፖለቲካዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ፣ ለባህል፣ ለህሊናና እንዲሁም ለአካባቢ ቀውስ ምክንያት በመሆን አንድ ህብረተሰብ ጤናማ በሆነ መልክ እንዳይገነባ ለማድረግ በቅቷል ማለት ይቻላል። በተለይም ክሪቲካል አመለካተት ባላቸው ምሁራን የሚሰጠው ትንተናና ጥናት ይህንን ሀቅ ነው የሚያረጋግጠው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ኢትዮጵያዊው ምሁር ነኝ ባይ ከአንድ ቦታ በመነሳት በተለይም እንደኛ ያለውን አገር እዚያ በዚያው የሚያንደፋድፈውንና ባህልንና ስነ-ልቦናን አውዳሚና አድካሚ የሆነውን በነፃ ገበያ ስም የሚስፋፋውን መርዛማ ርዕዮተ-ዓለም የመረዳት ኃይሉ እጅግ ደካማ ነው ማለት ይቻላል።

ከዚህ ሀቅ ስንነሳ በአውሮፓ ምድር ውስጥ አንድ በፍልስፍና ሙያ የሰለጠነ ሰው ተፈጥሮንና የሰውን ልጅ ባህርይ፣ ከዚያም በመነሳት ፖለቲካዊ ሂደቶችን ለመመርመር የሚጠቀምበት መሳሪያ አንድ በኢኮኖሚክስ ሙያ ሰለጠነ ከሚባለው በብዙ እጅ የሚለይበት ነገር አለ። በፍልስፍና ሙያ የሰለጠነው ሰው የአንድን አገር ሁኔታ በአጠቃላይና በጥልቀት ሲመለከት ኢኮኖሚስት ነኝ ባዩ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ነገሮችን የሚመለከተው በጠባቡና በተናጠል ነው። የሱም ተግባር የአንድን አገርና ህዝብ ችግር ንጹህ በንጹህ በገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት ለመፍታት የሚሞክር ነው። በየዩኒቨርሲቲዎችም ውስጥ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ከታሪክ ሂደት ጋር እየተነፃፀረ ስለማይሰጥና፣ በተለይም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የሚታየው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዕድገት የሚገለጸው አጠቃላይ ዕድገት ካለምንም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ንጹህ በንጹህ በአቅራቢና በጠያቂ ህግ መሰረት እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው ተብሎ በትምህርት መልክ ስለሚሰጥ አንድ በኢኮኖሚክስ ሙያ የሰለጠነ ሰው ይህንን ከታሪክና ከሳይንስ ውጭ የሆነውን የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ እንደ ዕውነት አድርጎ በመቀበል በዚያው በመግፋት  አንድ አገርና ህብረተሰብ በቀላሉ ሊወጡ የማይችሉበት ማጥ ውስጥ ይከታቸዋል።  የጊዜው አዝማሚያም ይህ ነው። አንድን ህብረተሰብ እንዳለ የገበያ መድረክ አድርጎ በመቁጠር የጠቅላላውን ህዝብ ፍላጎት  ፍጆታን መጠቀምና ገንዘብን ማግኘትና መሽቀርቀር ነው። በሌላ አነጋገር አንድ ሰው በዚህች ዓለም ሲኖር ዋናው ተግባሩ ስራ ከመስራት፣ ገንዘብ ከማግኘትና ልዩ ልዩ ነገሮችን ገዝቶ ከመጠቅም ውጭ ሌላ ፍላጎት የለውም። እያንዳንዱ ግለሰብ የማህበራዊ አካል ሳይሆን እንደግለሰብ ስለሚታይ አገርን እንደ አገር፣ ማህበረሰብን እንደማህበረሰብ ለመጠበቅና ለተከታታዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ምን ምን ነገሮች ደረጃ በደረጃ መተግበር እንዳለባቸው በፍጹም ሊገነዘብ አይችልም። እያንዳንዱ ግልሰብም ራሱን የተፈጥሮ አካል አድርጎ ስለማይቆጥርና በተፈጥሮ ላይ ብቻ በመመካት መኖርን እንደሚችል ስለማይገነዘብ አስተሳሰቡ ከጊዚያዊ ነገሮች ባሻገር ጠልቆ የሚያስብ አይደለም። ይህም ማለት ለመኖር ብቻ የሚኖር እንጂ ህብረተሰብአዊና ታሪካዊ ግዴታዎች እንዳሉበት የሚገነዘብ አይደለም። በተለይም ምንም ዐይነት ክሪቲካል አስተሳሰብ ባልዳበረበት እንደኛ ባለው አገር ውስጥ ዛሬ እንደምናየው ከመንግስት ባለስልጣናት ከሚባሉት ጀምሮ እስከተራ ንዑስ ከበርቴው ድረስ በተራ የውንብድና ስራ ላይ በመሰማራትና ሴቶችን በማገናኘት አገርንና ባህልን የሚያፈራርስ ነገር ሲሰራ እንደ ተራ ነገር አድርጎ መቁጥር የሚያረጋግጠው አብዛኞቻችን የቱን ያህል በደካማ አስተሳሰብ መንፈሳችን እንደተቀረጸ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በሳይንስ የተጠና ባህላዊ ዕድገት፣ ጥበባዊ የከተማ አገነባብ፣ ሰብአዊነት ያለው የመንግስትና የፖለቲካ አወቃቀር፣ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የሰውን ኃይልና በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ለዕድገት የሚያገለግሉ የጥሬ-ሀብቶችን የሚያንቀሳቅሱ በሰለጠነ ሰው የሚገለገሉ ተቋማት እንደ ቅድመ-ሁኔታና አስፈላጊም ሆነው  በማይታዩበት አገር ውስጥ እንደዚህ ዐይነት ለዐይን የሚቀፍና ለጆሮም የሚዘገንን ነገር መስማቱ ይህን ያህልም የሚያስደንቅ ጉዳይ አይደለም።

በሌላ ወገን ግን በአብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን እንደሚገመተው ሳይሆን በራሱ በኢኮኖሚክስ ውስጥ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ምሁራን እንዳሉ ግልጽ አይደለም። አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚክስን እንደኢኮኖሚክስ አድርገው ነው የሚመለከቱት እንጂ በታሪክ ውስጥ የካፒታሊስት አገሮች ህብረተሰባቸውን ለመገንባት የተከተሉትን የተለያዩ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪዎችና ፖሊስዎች እንደነበሩና በምሁራንም ዘንድ የጦፈ ክርክር ይደረግ እንደነበር በፍጹም የሚታወቅ ነገር የለም። ባጭሩ አንድ ሰው ኢኮኖሚክስ ካጠና ኢኮኖሚስት ነው ተብሎ ይጠራል። የአውሮፓን የህብረተሰብ የዕድገት ታሪክ ስንመለከት ግን የተለያዩ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች እንደነበሩና እንዳሉም ነው የምንረዳው። ስለሆነም ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ይሰራ የነበረበት ቲዎሪና ፖሊሲ በአሁኑ ጊዜ አይሰራበትም። አባዛኛዎች ህብረተሰቦችም እየተወሳሰቡ ስለመጡና ችግሮችም እየተደራረቡ በመምጣታቸው የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን አለበት እየተባለ ቢሰበክም በተግባር የሚታየው ግን መንግስታት ንጹህ በንጹህ የገበያን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል የየህብረተሰቦቻቸውን ችግር ለመፍታት አይሞክሩም። ነገሩም በፍጹም አያስኬድም። ከዚህ ዐይነቱ ግልጽ ያልሆነ ሁኔታ ስነሳ በእኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በግልጽ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የትኛውን ዘዴ መከተል እንዳለብን የሚታወቅ ነገር የለም። ሁሉም የሚያውቀው የነፃ ገበያን ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትንና በዓለም አቀፍ ተቋማት ተብለው በሚጠሩ የሚደነገገውን ዝም ብሎ አንገትን ደፍቶ ከመቀበል በስተቀር፣ ይህ ነገር ለእኛ አገር፣ በብዙ የተወሳሰቡ ነገሮች ፍዳውን ለሚያይ ህዝብ አይበጅም ብሎ ሽንጡን ገተሮ በመከራከር በአገሬ የውስጥ ጉዳይ ማንም ሰው ጣልቃ የመግባት መብት የለውም ብሎ ለመከራከር የሚችል ህብረተሰብአዊ ኃይል የለም። ስለሆነም አገራችንና ህዝባችን የዓለም አቀፍ ተዋናይ ነን በሚሉ የህብረተሰብን ዕድገት በሚያጣምሙና ባህልን በሚያወድሙ ወንበዴ ኃይሎች ፍዳውን እንዲያይና እንዲናቅ ለመደረግ በቅቷል። ይህ ዐይነቱ ምሁራዊ የዝቅተኝነት ስሜትና ለዓለም አቀፍ ተቋማት ለሚባሉት ተገዢ መሆን በእኛ አገር ብቻ ያለ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ሳይንሳዊ ዕውቀት ባልተስፋፋበትና አምባገነን አገዛዞች የሚባሉ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት የሌላቸው የመንግስቱን መኪና በጨበጡበት፣ የመንግስትን መኪና ንጹህ በንጹህ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት በለወጡ አገሮች ሁሉ የሚታይ ችግር ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በየአገሮች ውስጥ  በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጹና የተወሳሰቡና የተደራረቡ ችግሮችን ሊያስፈታ የሚችል ምሁራዊ እንቅስቃሴ በፍጹም ሊዳብር አልቻለም።

ወደ ኢትዮጵያዊው የምሁር ሁኔታ ስንመጣ በተለይም ባለፉት 40 ዓመታት የተደረገውን ትግልና ትግሉንም ለመደገፍ ሲባል የሚወጡ ጽሁፎችን ስመለከት ሳይንሳዊ መነሻቸውና ዘዴያቸው ምን እንደሆነ በፍጹም በግልጽ አይታወቅም። በትግል ስም የተደረገው ደም መፋሰስና አገርን መከስከስ የመጨረሻ ዓላማውም ምን እንደሆነ በፍጹም አልገባኝም። አንድ ሰላም የሰፈነበት፣ ሳይንሳዊ አስተሳሰብና በስልት ላይ ያተኮረ፣ እንዲሁም ያሉንን መሰረታዊ ችግሮች ደረጃ በደረጃ በማጥናት መፍትሄ የሚጠቁም ሆኖ በፍጹም አላገኘሁትም።  ዋናው ችግራችን አብዛኛውም በትግል ውስጥ የተሳተፈውና፣ ምሁር ነኝ በማለት በየተሌቪዥን ጣቢያዎች በመጋበዝና በየዩቱቭ ቻናሎች የሚወጣውን ገለጻ ሳዳምጥ ነገሮችን ግልጽ ከማድረግ ይልቅ ውዥንብር የሚነዙ ሆነው እመለከታቸዋለሁ። አስቸጋሪው ነገር ግን ሁሉም በምሁር ስም የሚነግድና አቋሙንም በግልጽ ለማሳየት ያለመቻሉ ሁላችንንም ግራ ሲያጋባ ይታያል። የትግላችንም ዓላማ ግልጽ አለመሆኑና የምንመራበትም አንዳች ፍልስፍናና ሳይንሳዊ ስልት ባለመኖሩ ሁላችንም በደመነፍስ የምንኳትንና አንደኛው ሌላኛውን ለማጥፋት እንደሚቅበዘበዝ ሰው ሆነን እንታያለን። ሆበስ የሚባለው የ16ኛው ክፍለዘመን የእንግሊዙ ፈላስፋ የሰው ልጅ ልክ እንደ ቀበሮ ባህርይ ያለው፣ አንደኛው ሌላውን እየፈራውና እየጠረጠረ የሚኖር ነው የሚለው አባባሉ በእኛ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ነን በምንባል ሰዎች ዘንድ የሚሰራ ነው። በሆበስም አመለካከትና ዕምነት ከዚህ ዐይነቱ አንዱ የሌላው ጠላት ሆኖ በሚታይበት፣ ምሁራዊ አስተሳሰብና ጦርነት ለመማዘዝ ዝግጁ በሆነበት አገር ውስጥ አንድ ሁሉንም ረግጦ የሚገዛና ዲስፕሊን የሚያስዝ አገዛዝ ያስፈልጋል ይለናል። ይሁንና ይህ የሆበስ አባባል ተቀባይነት እንደሌለው በሱ ዘመን የነበረ እንደ ሁም የመሳሰሉ ፈላስፋዎች የሰው ልጅ ሌሎች ቀና ባህርይም እንዳሉት ለማረጋገጥ ሞክረዋል። ወደኛ አገር ስመጣ ይህ የሆበስ አባባል ተፈጥሮአዊ ባይሆንም በተለይም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት አብዮት ፈነዳ ከተባለበት ጊዜ አዲስ የመፈራራትና እንደጠላት የመተያየት ሁኔታ በመፈጠሩና ወደ መገዳደል በማምራቱ ይህ ዐይነቱ ህብረተሰብአዊ ዕድገትንና ለውጥን በተሳሳተ መልክ መተርጎሙ ወደ መገዳደል እንዲያመራን አስገድዶናል። ወያኔ ስልጣን ከወጣ ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የጎሳ ፌዴራሊዝምና የኒዎ-ሊበራል የነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሰውን ጭንቅላት በማጠብ ርህራሄ እንዳይሆን ለማድረግ በቅቷል። ናኦሚ ክላይን የምትባል የኢኮኖሚስት ምሁርና የኢኮሎጂ ተመራማሪ The Shock Doctrine  በሚባል ግሩም መጽሃፏ ውስጥ እንዳረጋገጠችው በነጻ ገበያ ስም አሳቦ የአሜሪካን የፖለቲካል፣ የኢኮኖሚ፣ የስለላ ድርጅትና የሚሊተሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብ ኤሊት የሰዎች ጭንቅላት እንዳለ ከድሮውና ኋላ-ቀር አስተሳሰቡ በመላቀቅ ልክ እንደ ነጭ ወረቀት(Tabula Rasa) በአዲስ መልክ የሚጻፍበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብሎ ያስፋፋው አስተሳሰብ በአገራችን ምድር በአለፈው አርባ ዓመት ተግባራዊ ለመሆን በቅቷል። ባህለ-ቢስ የሆነ የህበረተሰብ ክፍል  እንዲፈጠር በማድረግ ታሪክንና ህብረተሰብ አዊእሴቶችን እንዲንቅ ተደርጓል። ሁሉም ነገር ወደ ገንዘብ የሚለወጥበት ሁኔታ በመፈጠር አብዛኛው ህዝብ ወደ አጭበርባሪነት ተቀይሯል ማለት ይቻላል። በዚህም መልክ ታሪክና ስልጣኔ የማይሰራበት ሁኔታን መፍጠር የአሜሪካንና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት ዋናው ስትራቴጂ ነው። የዓለም ህዝብ ሁሉ የራሱን እሴትና የአኗኗር ስልት በመርሳት፣ ወይም በአዲስና በሰለጠነ መልክ ከማዘጋጀትና ከመገንባት ይልቅ የአሜሪካን ኤሊት የሚሰውን ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ተግባራዊ ማድረ አለበት። በዚህም መልክ እያንዳንዱን ህብረተሰብ መቆጣጠርና እንደፈለጉት መበወዝ ይቻላል።  ክዚህ ስነሳ ስንቱ  ምሁር ነኛ ባይ ነው ይህንን የተወሳሰበ ሁኔታ ለመረዳት የሚችለውና የሚዋጋውስ?

ለማንኛውም ሁሉም ምሁር ነኝ የሚል አንድ ዐይነት አመለካከትና የአሰራር ስልት በፍጹም ሊኖረው አይችልም። በሌላው ወገን ግን በአብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያውያን ምሁራን ዘንድ ስልትና(Method) ሳይንሳዊ የአሰራር መንገድ ምን እንደሆኑ በግልጽ የሚታወቁ አይደሉም። ይህ ዐይነቱ የተወናበደ አካሄድ በራሱ በአገራችን ምድር የሚታየውን የጠለቀና የሰፋ ችግር ለማየትና ለማጥናት እንዳንችል አድርጎናል ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው በሳይንስ ዕውቀት(Scientific Knowledge) አማካይነት አንድ ሰው መነሳት ያለበት ጉዳይ ከሚታዩ፣ ከሚጨበጡና ከሚዳሰሱ ነገሮች ነው። ይህም ኦብዘርቤሽን በመባል ይታወቃል። በዚህ ዐይነቱም ሳይንሳዊ ዕውቀት ነገሮችን የማየትና የመመራመር ዘዴ በነገሮች መሀከል መተሳሰር አለ። አንደኛው ነገር የግዴታ በሌላው ነገር ላይ አዎንታዊም ሁነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ የመንግስቱና የፖለቲካው አወቃቀር የተበላሸ ከሆነና በስልጣን ላይ የተቀመጡትም ግለሰቦች መንፈሳቸው በሳንይሳዊ ዕውቀት ያልታነፀና ያልዳበረ ከሆነ በምድር የሚታየውም የተዘበራረቀ ሁኔታ የዚህ ዐይነቱ የመንግስት መኪናና የፖለቲካ አወቃቀር ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ውጭ ማሰብ ስህተት ብቻ ሳይሆን እንደ ከፍተኛ ወንጀል መስራትም የሚያስቆጥር ነው። ሌላው በኢትዮጵያውያን ምሁራን ዘንድ ሰለመንግስት ምንነትና የፖለቲካ ስልጣንን ምን ዐይነት ሰዎች መያዝ እንዳለባቸው ያለን አመለካከት የተወላገደ ነው ማለት ይቻላል። መንስትን እንደተሰጠ ወይም ከሰማይ ዱብ እንዳለ እንጂ የህብረተሰብ ሂደት ውጤት እንደሆነና፣ በየጊዜውም ከተወሳሰቡ ሁኔታዎች ጋር እንዲስተካከል በመሆንና ችግሮች እንዲፈቱ በተጠና መልክ መሻሻል እንዳለበት ግንዛቤ ውስጥ የለም። በመሰረቱ በተለያየ መልክ የሚገለጸው የመንግስት መኪና አምራችና ፈጣሪ ሳይሆን በህብረተሰብ ውስጥ የሚመረተውን ምርትም ሆነ የአገልግሎት መስጫ ተጠቃሚ ነው። የመንግስቱ መኪና በምድር ላይ ከሚታየው የህብረተሰቡ የማምረት ኃይል በጣም የደለበ ከሆነ ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ሀብትን መጣጭ በመሆን ሁለ-ገብ ዕድገት እንዳይኖር ያግዳል። በተለይም በአሁኑ በግሎባል ካፒታሊዝም ዘመን የእኛው አገር የመንግስት መኪና ከውስጥ ኦርጋኒካሊና በስነ-ስርዓት ባልተገነባበት አገርና፣ በተለይም የሚሊታሪው፣ የስለላው፣ የቴክኖክራሲውና የቢሮክራሲው ኃይል በውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በወደቀበት አገር በነፃ የማሰብ፣ ህብረተሰብአዊ ሀብት(National Wealth) ሊፈጠር የሚችልበትንና፣ ከዚህም በመነሳት ድህነት ሊቀረፍበትና ኋላ-ቀርነት ሊወገድበት የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ድህነቱና ኋላ-ቀርነቱ ስር እየሰደዱ በመሄድ ከአንድ ትውልድ ወደሌላው በመተላለፍ ዘለዓለማዊ ህብረተስብአዊ ነቀርሳ ሆነው ይቀራሉ ማለት ነው።  በመሰረቱ እነዚህ ነገሮችን መመልከትና መመርመር የምሁራን ኃላፊነትና ተግባር መሆን ነበረበት።  ይሁንና ምሁር ነኝ የሚለው ኃይል በአንድ ጎራ ውስጥ ስለሚጠቃለል የተለያዩ አስተሳሰቦችን ለማዳበርና ጥያቄም ለመጠይቅ የማይችል ለመሆን በቅቷል።

ለምሳሌ የካፒታሊስት አገሮችን የህብረተሰብ አወቃቀር ስንመለከት የተለያየ ዕይታ ወይም ዝንባሌና የአሰራር ስልት የሰለጠኑና ለየት ያለ ግንዛቤም ያላቸው ምሁራን አሉ። እያንዳንዱ ምሁርም የአገሩንና የዓለምን ሁኔታ የሚመለከትበት ርዕይና የሚተነተንበትም ዘዴ አለው። ለምሳሌ ጥንታዊውን የፍልስፍና አመለካከት ዘዴ ስንመለከት ተጨባጭ ሁኔታዎችንና የሰውን አስተሳሰብ ለማንበብ ፈላስፋዎች የሚጠቀሙበት ዘዴ፣ 1ኛ) ራሺናሊዝም ወይም ኢሴንሺያሊዝም በመባል ሲታወቅ፣ 2ኛ) ደግሞ ኢምፔሬሲዝም በመባል ይታወቃል። በመጀመሪያው አመለካከት፣ በተለይም እነ ሶክራተስና ፕሌቶ እንደሚያስተምሩን ከሆነ የሰው ልጅ በሙሉ ሲወለድ ከአስተሳሰብ ጋር ነው የሚፈጠረው። ስለሆነም ዕውቀትም በጭንቅላት አማካይነት ጭንቅላትን በማስጨነቅ የሚፈጠር ነው ይሉናል። ይሁንና ግን ዕውቀትን ለማፍለቅ የግዴታ ተፈጥሮንና ኮስሞስን በሚገባ መቃኘት ያስፈልጋል። በእርግጥም የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት ስንመለከት፣ በአጠቃላይም ሲታይ የሰው ልጅ ከዝቅተኛ የአኗኗር ሁኔታ በመነሳት ቀስ በቀስ ከተማዎችን መገንባት፣ ዕደ-ጥበብ መፍጠርና ማዳበር፣ ይህንንም ለተለያዩ የስራ-ክንዋኔዎች ማዋል፣ በዚያም አማካይነት በምድር ውስጥ ያሉ የጥሬ-ሀብቶችን፣ እንዲያም ሲል የእርሻ ሰብሎች ወደሚበላ ነገር መለወጥ፣ እንደ ንግድ የመሳሰሉትን ነገሮች መፍጠርና የስራ-ክፍፍልንም ማዳበር፣ የንግድ ልውውጥም በአንዳች የሁሉም መመዘኛ ሊሆን በሚችል በገንዘብ አማካይነት መገበያየት እንደሚቻልና፣ ይኸኛውም ቀላሉ መንገድ መሆኑን መረዳት፣ ከዚያም በመነሳት ሳይንስንና ቴክኖሎጂን መፍጠርና ማዳበር ስንመለከት እነዚህ ሁሉ ቀደም ብለው ሳይታዩ ወይም ሳይኖሩ በጭንቅላት አማካይነት በመጀመሪያው ወቅት በሙከራና በእርማት፣ የኋላም ኋላም የንቃተ-ህሊናን በማዳበር በጭንቅላት የማሰብ ኃይል የተፈጠሩ ናቸው ማለት ይቻላል። ከዚህም አልፎ በመሄድ የኮስሞስን ህግ በመመርመር እንደ መሳሳብ(The Law of Gravity)፣ የእንቅስቃሴን ህግና(The Law of Motion) ሌሎችንም የሂሳብ የአሰራር ዘዴዎች መፍጠር ስንመለከት ቀደም ብለው ሳይታወቁ ወይም ሳይኖሩ በተገለጸላቸውና ኮስሞስን ጠጋ ብለው ለመመልከትና ለመደነቅ በቻሉ ልዩ ዐይነት ሰዎች የተፈጠሩ ናቸው ማለት ይቻላል። ይሁንና ግን እነ ስክራተስና ፕሌቶ ዕውቀት በጭንቅላት አማካይነት የሚፈጠር ነው ብለው ቢያስተምሩም፣ በሌላ ወገን ደግሞ በማየት፣ በመስማት፣ በስሜትና በማሽተትም የነገሮችን ሁኔታ መረዳት እንደሚቻል አይክዱም። ለምሳሌ የመጀመሪያዎች ዕውቀቶች ከዳበሩና ወደ ተግባርም ከተለወጡ በኋላ በመኮረጅና በማሻሻል፣ በአጣቃላይ ሲታይ ዕውቀት ሊስፋፋ እንደቻለ እንመለከታለን። ይሁንና ይኸኛውና የልምድ ጉዳይ ለዕውቀት ግኝት አስተማማኝ እንዳልሆኑ እንደ ሬኔ ዴካ የመሳሰሉት የፍልስፍናና የማቲማቲክስ አዋቂዎች ያረጋግጣሉ። በአጭሩ ጭንቅላታችን የመፍጠር ጭሎታ ብቻ ሳይሆን የማጥፋትም፣ ወይም ነገሮችንና ድርጊቶችን ለማየት የማይችልበት ሁኔታም እንዳለም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።

እንደዚሁም በአንድ አገር ወይም ህብረተሰብ ውስጥ የሚሰሩና የሚፈጠሩ ሁኔታዎች በሙሉ ከጭንቅላት ውጭ ሊሆኑ አይችሉም። ለምሳሌ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ፖለቲካዊ ውዝግብ ካለ፣ የርስ በርስ ጦርነት የሚካሄድ ከሆነ፣ ከተማዎችና መንደሮች በዕቅድ ያልተሰሩ ከሆነ፣ ድህነት ካለ፣ ባጭሩ ነገሮች ሁሉ ተዘበራርቀውና ተዝረክርከው የሚገኙና የሚታዩ ከሆኑ፣ ለዚህ ዋናው ምክንያት የዕውቀት ችግር፣ ወይም በፕሌቶ አገላለጽ Lack of true knowledge or the problem of thought  ብሎ ይገልጸዋል። ጭንቅላት በስነስርዓት ካልተዋቀረ፣ ወይም በተራ አካዴሚክስ ትምህርት ከሰለጠነ በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮችን የማየትና የማስተካከል ችግር አለበት ይላል። ይህ ዘዴ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የፖለቲከኛ ነን ባዮችን የአዕምሮ አቀራረጽ ይገልጻል፡፡ 2ኛው) መንገድ ደግሞ ኢምፔሪሲዝም ተብሎ ይታወቃል። ይህ ዐይነቱ ፍልስፍና ወይም አመለካከት በእንግሊዞች ምሁራን፣ በጆን ሎክ፣ ዴቪድ ሂዩምና በሌሎች የ17ኛውና የ18ኛው ክፍለ-ዘመን የእንግሊዝ ፈላስፋዎች የሚወከል ነው። በእነዚህ ምሁራንም አስተሳሰብ የሰው ልጅ ሲፈጠር ጭንቅላቱ እንደ እንዳልተጻፈበት ነጭ ወረቀት(Tabula Rasa) ነው። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ ከአተሳሰብ ጋር አይፈጠርም፤ ዕውቀትንም ሊቀስም የሚችለው በሴንስ ኦርጋኖቹ አማካይነትና በልምድ ነው ይላሉ። በእነዚህ ምሁራን አስተሳሰብ መሰረት በነገሮች መሀከል መተሳሰር  ወይም ግኑኝነት የለም፤ ሁሉም ነገር ተነጣጥሎ የሚታይ ነው። የመጀመሪያውና የሁለተኛው ዕውቀትን የማፍለቅና ተጨባጭ ሁኔታዎችን የማንበብ ጉዳይ እስከ አስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የነበረ የመከራከሪያና ተፈጥሮንና ህዋን፣ እንዲሁም በፖለቲካ አማካይነት የሚከሰቱ ጉዳዮችን መቃኛና መልስም መፈለጊያ ዘዴዎች እንደነበሩ ይታወቃል። በተለይም በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የነበረውን በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎችና በዲስፖታዊ አገዛዞች የሚወከለውን ጭፍንና ጨቋኝ አገዛዝ ለመወጋት የግዴታ በራሽናል ቅኝት አማካይነት የሊበራል አስተሳሰብን ማዳበር ተችሏል። በከተማዎች ማደግ፣ በዕደ-ጥበብ መዳበርና በንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት የተነሳ ከጊዜው የጭቆና አገዛዝ ባሻገር ዘልቀው ለመሄድ የሚፈልጉ ውስጠ.-ኃይላቸው ከፍ ያለ የህብረተሰብ ኃይሎች ብቅ ማለት ይጀምራሉ። ሳይንሳዊ አስተሳሰብ መስፋፋትና ጥንታዊውን አገዛዝ መፈናፈኛ እንዳያገኝ ማድረግ የግዴታ የፖለቲካ መድረኩን እንዲሰፋ አስገደደ። ጊዜው ከጨለማ በመላቀቅ ብርሃንን በማየት አዳዲስ አስተሳሰቦች የሚፈጠሩበት ሁኔታ ሆነ። የከበርቴው መደብ በማደግና የምርት-ኃይሎች አንቀሳቃሽ በመሆን በፖለቲካው መድረክ ላይ ተፅዕኖ ማሳደርን ቻለ።

ከዚህ ወጣ ብለን ስንሄድ በተለይም ካፒታሊዝም እየዳበረ ሲመጣና ከፍተኛውን ቦታ ሲይዝ በነማርክስ የተፈጠረ አስተሳሰብ አለ። በእነሱ ዕምነትም ማንኛውም ፖለቲካዊ ውዝግብና ህብረተሰብአዊ ግጭት ሊፈጠር የሚችለው ስልጣንና ሀብትን በሚቆጣጠሩት ኃይሎች ነው። እነዚህ ኃይሎችም የራሳቸውን ርዕዮተ  ዓለም በመፍጠር ይህ አስተሳሰባቸው በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርጋሉ። ይህ ዐይነቱ መንገድ ማቴሪያሊስቲክስ አመለካከት በመባል ይታወቃል። በሌላ አነጋገር በምድር ላይ የሚታዩት ነገሮች፣ የሀብት ክፍፍል ጉዳይ፣ የጭቆና መኖርና የፍትሃዊነት እጦት…ወዘተ. እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚያያዙት በቀጥታ የፖለቲካ ስልጣንን በጨበጡና በመንግስት መኪናው አማካይነትና ከፖለቲካው ስርዓት ጋር በጥቅም የተሳሰሩ አብዛኛውን ሀብት በሚቆጣጠሩ ሰዎች ወይም መደብ የሚፈጠሩ ሁኔታዎች ነው ይላሉ። የእነ ማርክስን ፈለግ በሚከተሉት ዕምነት ይህንን ዐይነቱን ኢ-ፍትሃዊ አገዛዝ መቀየር የሚቻለው የፖለቲካ ስልጣን በሌላው በተጨቆነውና በመሪዎቹ እጅ ሲገባና ከዚያም በመነሳት መሰረታዊ ለውጥ የተካሄደ እንደሆነ ነው ይላል። ይሁንና ግን በማርክስ ዕምነት ሶሻሊስታዊ ስርዓት ለመገንባት የግዴታ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ንቃተ-ህሊና መዳበር እንዳለበትና የሳንይስና የቴክኖሎጂ ዕድገትም በከፍተኛ ደረጃ ላይ መገኘት እንዳለባቸው ያስተምራል። በማርክስና በኤንገልስ ዕምነትና አመለካከት እጅግ ወደ ኋላ-በቀረ ህብረተሰብ ውስጥ፣ ወይም ደግሞ የማቴሪያልና የንቃት-ህሊና ጉዳዮች ባልተሟሉበትና ባልዳበሩበት አገሮች ውስጥ ሶሻሊስታዊ አብዮትን ማካሄድ እንደማይቻል፣ ቢካሄድ እንኳ ከንቃተ-ህሊና ማነስ የተነሳ ደም አፍሳሽ ክስተቶች እንደሚፈጠሩ ያስተምራሉ። እንደሌኒን የመሰለው ደግሞ ከማርክስና ከኤንግልስ አልፎ በመሄድ ስዊዘርላንድ 17 ዓመታት ያህል በስደት ላይ  ከኖረና የከተማዎችን አገነባብና የህዝቡን አደረጃጀት፣ እንዲሁም የንግድ ልውውጥን ከተመለከተ በኋላ በእንደዚህ ዐይነቱ ማህበረሰብ ውስጥ ስለ አብዮት ማሰብ እንደ ዕብድነት ሊቆጠር እንደሚችል ይናገራል። ይሁንና በዚያው ዘመን  ከአውሮፓ አገሮች ጋር ስትወዳደር በብዙ እጅ ወደ ኋላ ለቀረችው ራሺያ አብዮት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ጽፏል። ይህንንም በተግባር ለመመንዘር ሞክሯል።

ያም ሆነ ይህ  እንደምናየው ከሆነና የአብዛኛዎችን አገሮች የፖለቲካ አወቃቀርና ስልጣንን የያዙትን  ሰዎች የአስተሳስብ ሁኔታ ስንመለከት አብዛኛዎቹ ከዕውቀት የራቁ ናቸው። በየቀኑም አስተሳሰባቸውን ለማደስ የሚችሉ መጽሀፎችን አያነቡም። አብዛኛዎቹም ከፍልስፍና፣ ከሶስዮሎጂና ከኢኮኖሚክስ ሳይንስ ዕውቀት ርቀው የሚገኙና፣ በዚኸኛው ወይም በዚያኛውም ምሁር ወይም ኤክስፐርት ነኝ ባይ የሚጠመዘዙ ስለሆነ በማሰብ ኃይላቸው የሚመሩ አይደሉም። ስለሆነም በአገራችው ምድር ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታና የሰውን አኗኗር ሁኔታ ለማንበብ፣ ጥያቄ ለማንሳትና ለማመዛዘን የሚችሉ አይደሉም። ተግባራዊ የሚያደርጓቸውም ነገሮች በሙሉ በዘፈቀደ እንጂ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ጥናትን በመመርኮዝ አይደለም። ስለሆነም የማርክሲዝም አስተሳሰብ ከተፈጠረ በኋላ ይህንን ለመዋጋት ሲባል የቀኝ አስተሳሰብ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ፋሺዝም የሚባለው ነገር ሊፈጠር ቻለ። በትክክል ተገንዝበን ከሆነ የማርክሲዝምም ሆነ የቀኝ አስተሳሰቦች በካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ የፈለቁ ናቸው። ይህም ማለት ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን በፊት ያልነበሩ ናቸው። ሁለቱም አስተሳሰቦች፣ በተለም ደግሞ የኢኮኖሚ ፖሊሲን አስመልክቶ ተግባራዊ የሚሆኑት የተወሰነ የመደብ ሁኔታን ተገን በማድረግ ነው። ይህንን Social or class relationship ብለው ይጠሩታል። ለምሳሌ Neo-Liberal Economics በ19ኛው ክፍለ-ዘመን እየዳበረ የመጣውን የማርክሲስት ኢኮኖሚክስ ፍልስፍና ለመዋጋት የተፈጠረ በመሆኑ የሚያንፀባርቀውም በህብረተሰብ ውስጥ የሰፈነውን ስርዓት ተገን በማድረግ ነው። ይሁንና ግን የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ  የካፒታሊዝምን ዕድገት ደረጃ በደረጃ ማደግና እየተወሳሰበ መምጣት፣ እንዲሁም ደግሞ ውስጣዊ የአሰራር ዘዴውን ሊገልጽ የሚችል አይደለም። ከሞላ ጎደል የካፒታሊዝምን ዕድገትና፣ በተሟላ መንገድ ደግሞ ውስጣዊ የአሰራር ዘዴውን በሚገባ ሊገልጽ ወይም ሊተነትን የቻለው ማርክስ በሶስቱ ቅፅ ስራዎቹ ዳስ ካፒታል ብሎ በሚጠራቸው ግሩም መጽሀፎቹ ውስጥ ነው። ማርክስ እነዚህ ስራዎችን ጽፎ ካሳለፈና ከሞተ በኋላ ካፒታሊዝም ከፍተኛ የሆነ ቴክኖሎጂያዊና ሳይንሳዊ ምጥቀትን አግኝቷል። እጅግ እየተወሳሰበ ሲመጣ፣ በአንድ በኩል የሰውን ልጅ ስራ ቢያቃልልም፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሰው ልጅ ስነ-ልቦና ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ችሏል። ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት ሰውን ከሚያቀራርብ ይልቅ የሚያራርቅ ለመሆን በቅቷል። በተለይም በካፒታሊስት ህብረተሰብ ውስጥ ግለሰብአዊነት እያየለ በመምጣቱ ተንከባካቢ ዘመድ  የሌላቸውና በጡረታ ዓለም ውስጥ የሚገኙና በጣም ያረጁ ሰዎች ከተወሳሰበውና በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኘው ቴክኖሎጂ ጋር በፍጹም አብረው ለመሄድ አቅቷቸው ሲቸገሩ ይታያሉ። ከዚህም በሻገር የቴክኖሎጂ ምጥቀትና የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚባሉት እንደፌስቡክ የመሳሰሉት ልዩ ዐይነት ጭንቀትን በመፍጠር የሰው ልጅ ከተፍጥሮ ጋር ያለው ግኑኘነት እንዲበጣጠስና በሽተኛም እንዲሆን አድርገውታል። ይህን ዐይነቱም ሁኔታ እጅግ በተወሳሰበ ዕውቀትና ሰብአዊ ህሊና ባላቸው ምሁራን አማክይነት የሚመረመር እንጂ በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ በሰለጠኑ ምሁራን ነን በሚሉ የሚታወቅ ጉዳይ አይደለም። በአብዛኛዎች ፈላስፋዎችና የካፒታሊዝም ዕድገት ተመራማሪዎች ዕምነት በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ትምህርት የሰለጠኑ ምሁራን ነን ባዮች የታሪክን ዕድገት የመረዳት ችግር አለባቸው። አንድንም ሰው ማህበራዊ አድርገው አይቆጥሩትም፤ እያንዳንዱም ግለሰብ ጥቅሙን ለማሳደድ የሚሯሯጥ በመሆኑ ማህበረሰብና ህብረተሰብ የሚባል ነገር የለም ይሉናል። ይህ ዐይነት አገላለጽ በ1980ዎች መጀመሪያ ላይ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስተር በነበሩት በሚስስ ቴቸር፣ እኔ የማውቀው ህብረተሰብንና ማህበረሰብን ሳይሆን ግለሰቦችን ብቻ ነው”  በሚል ግልጽ አነጋገር በመራባት በጊዜው በሶስይሎጂስቶች ከፍተኛ ትችት ተስጥቶበታል። ነገሩ የሚያስደንቅ አይደለም። ሚስስ ቴቸር ሙሉ በሙሉ ንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ በሁሉም አገሮች ውስጥ ተግባራዊ መሆን አለበት ብለው የሚያምኑና፣ መንግስትም ከኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ-ገብነቱን ማቆም አለበት ብለው የሚሰብኩ ናቸው። ይሁንና እዚያው በዚያው ጠቅላይ ሚኒስተሪቱ የናጠጡ ሀብታምና፣ የቆሙትም ለካፒታሊስቶችና ለትላልቅ የመሬት ከበርቴዎች እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህም ማለት አቋማቸው ፀረ ደሃ ነው ማለት ይቻላል።

ወደ እኛው አገር ችግር ጋ ስመጣ የአገራችንንንም ሆነ የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ የምናነብበትና የምንተነትንበት ዘዴ አለን ወይ? ዝም ብዬ ስመለከትና፣ በተለይም ደግሞ በድረ-ገጾች ላይ የሚለጠፉትን ጽሁፎች ስመለከት አብዛኛዎቹ ካለ ስልት የሚጻፉና፣ አንዳችም ርዕዮተ ዓለምን ወይም ፍልስፍናዊ አመለካከትን የሚያንፀባርቁ አይደሉም። ስለሆነም ጭንቅላትን ከማዘበራረቅ በስተቀር የአገራችንንና የዓለምን ሁኔታ በደንብ በማንበብ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችሉ አይደሉም። እንደሚታወቀው በአገራችን ምድር ስለሰፈኑትና በግልጽም ስለሚታዩት የተለያዩ ችግሮች የምናወራ ከሆነ ባለፉት አርባ ዐመታት በአገራችን ምድር የተፈጠሩት የተለያዩ ችግሮችና እስካሁንም ዘልቀው የሚያነታርኩን በሙሉ በሰው የተሰሩ፣ ወይም ደግሞ ካለማሰብ የተነሳ የተፈጠሩ ናቸው። ዛሬ ስልጣን ላይ ያለውም አገዛዝ ችግር፣ አገዛዝ ካልነው፣ ዋናው ምክንያት የዘር ጥያቄ መነሳቱ ሳይሆን፣ ይህንን የሚያራግቡ ሰዎች የታሪክን ሂደትና የህብረተሰብን አገነባብ አስቸጋሪነት ለማንበብ የሚያስችል ዕውቀት በጭንቅላታቸው ውስጥ ስላልተቀረጸ ብቻ ነው። ህብረተሰብ፣ አገር፣ ባህል፣ ታሪክ እንዴት እንደሚሰራ፣ በዕውቀት ወይንስ ካለዕወቀት፣ በየጊዜው ስልጣንን የያዙ ኃይሎች ታሪክን የሚያሰራ በቂ ዕውቀትና ንቃተ-ህሊና ነበራቸው ወይ? ብለው ለመጠየቅ ስለማይችሉ የማሰብ ኃይላቸውን ሁሉ በጠባብ ነገር ላይ እንዲያተኩር ያደርጉታል። ስልጣን ላይ ለመውጣት ሲሉም ዘርን ወይም ጐሳን ሽፋን ያደርጋሉ። እንደምናየው ከሆነ እንደነዚህ ዐይነት ኃይሎች የራሳቸው የሆነ ያዳበሩት ዕውቀት ስለሌለ፣ አሊያም ደግሞ የተለያዩ ዕውቀቶችን በማገናዘብ ይኸኛው ትክክል ነው ብለው የተቀበሉትና የራሳቸው ያደረጉት ነገር ስለሌ በውጭ ኃይሎች የሚጠመዘዙና አገርን የሚያተረማምሱ ናቸው።  በአጭር አነጋገር፣ ራሳቸው ውስጥ ምንም ነገር ስለሌለ ራሳቸው እንደ ቅል ነው። ቅል በእጅ ይዘው ወዲያና ወዲህ ቢያሽከረክሩት ከውስጡ ምንም የሚጮህ ነገር እንደሌለው ሁሉ ጎሳን ወይም ዘርን፣ ካሊያም ደግሞ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውን ነገር ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በሙሉ ርህራሄ የሌላቸው ናቸው፤ መንፈስ አልባ ናቸው። ይሁንና ግን ቅል ቢያንስ ጥቅም አለው። ውሃ ለመቅዳት ወይም ለመያዝ ይጠቅማል። እንደ ቅል ራሳቸው ባዶ የሆኑ መሪዎች ግን አገርን ከማፈራረስና ባህልን ከማበላሸት ይልቅ የሚሰጡት አንዳችም ጥቅም የለም። ዕውቀት የሚባለውም ነገር በጭንቅላታቸው ውስጥ ስላልተቀረፀና እንደመመሪያም አድርገው የሚንቀሳቀሱበት መሰረት ስለሌላቸው ስራቸው በሙሉ የዕውር የድንብር ነው።  አገርን ከማፈራረስ፣ ባህልን ከማውደምና ሰውን ከመግደል ምን ጥቅም ማግኘት እንደሚችሉ በፍጹም ለመገንዘብ የማይችሉ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ የሚሰሩና የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በሙሉ ግለሰብአዊና ማህበረሰብአዊ ጥቅም እስካላመጡ ድረስ ትርጉም እንደሌላቸ በፍጹም ሊገነዘቡ የማይችሉ ናቸው። ሰውን በመግደል የሚገኝ ምንም ነገር የለም፤ ትርፍም አይገኝበትም። ስለሆነም እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ማንኛውም ሰው ሊኖረው የሚገባው፣ እንደማሰብ ኃይል የመሳሰሉት፣ ርህራሄ፣ ለሌላው ማሰብና መጨነቅ የመሳሰሉት ነገሮች በጭንቅላታቸው ውስጥ የለም፤ ዕውነትን ከውሸት የመለየት ኃይልም የላቸውም። እንደ ሰው ብቻ የሚኖሩ ሰልሆነ ሌላውን አምሳያቸውን ከማሰቃየት በስተቀር የኑሮን ትርጉም የሚረዱ አይደሉም። ሰለሆነም አንድን ማህበረሰብ እንደማህበረሰብ ለመገንባትና ለማያያዝ የሚያገለግሉና በጣም ጠቃሚ የሆኑ እንደሙዚቃ፣ ስዕልና ስክለፕቸር፣ ጥሩ ጥሩ የህንፃ አሰራሮችና የከተማ ግንባታዎች፣ የስፖርት መዝናኛ ቦታዎች፣ መጻህፍት ቤቶች በየቀበሌው መስፋፋትና ወጣቱ ሻይቤት ከመዋልና ጨአት ከመቃም እንዲቆጠብ የሚያደርጉት ጭንቅላትን ቀራጭ የሆኑ ነገሮችን ማስፋፋት፣ እንደቮኬሺናል የሙያ መስጫ መስኮችን ማስፋፋት… ወዘተ. የመሳሰሉ በጭንቅላታቸው ውስጥ ስለሌሉ እንደምናየው አንድን አገር የብልግናና የማጭበርበሪያ መድረክ አድርገው ነው የሚወስዱትና ይህም እንዲስፋፋ የሚገፋፉት። የገዢዎች ነን ባዮች ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሲታይ ምሁር ነኝ ባዩ ሁሉ አንድ አገር እንደ ማህበረሰብ እንዲገነባና ተከታታይነት እንዲኖረው ከተፈለገ ምን ምን ነገሮች ከታች ወደ ላይና በየአቅጣጫው ደረጃ በደረጃ እንዴት እንደሚዋቅሩ እንደሚገነቡ የሚያውቁት ምንም ነገር የለም። የሰብአዊነት ባህርይም ስለሌላቸው አንድ አገር እንደዚህ ተዝረክርኮና ተዋርዶ ሲገኝ ምክንያቱን ለማጥናትና መፍትሄም ለመፈለፍ ትግል ሲደረግ በፍጹም አይታይም። ከዚህ ቀላል ገለጻ ስነሳ የምጠይቀው ጥያቄ፣ ለመሆኑ እኛ ምሁራን የምንባል ኢትዮጵያውን እንደሰው እናስባለን ወይ? ሞራልና ስነ-ምግባር አለን ወይ? ሰብአዊነትስ በጭንቅላታችን ውስጥ ተቀርጿል ወይ? የሰው ልጅ ባህርይስ እንዴት ነው የሚመዘነው? በስራውና ለህብረተሰብ በሚያደርገው አስተዋፅዖ ወይስ ባካበተው ሀብት? ስለፖለቲካ ኢኮኖሚክስ፣ ስለ ሳይንስና ስለቴክኖሎጂ አስፈላጊነት፣ ሰለብሄራዊ ኢኮኖሚክስና ስለ ብሄራዊ ነፃነት፣ በጠቅላላው አንድን አገር አገር ነው ብለው ስለሚያስጠሩት መሰረታዊ ነገሮች ያሉን አቋሞችና አስተሳሰብስ ከመንፈሳችን ጋር ተዋህደዋል ወይ? እነዚህን ጥያቄዎች በሙሉ ደረጃ በደረጃ መመለስ ያለበን ጉዳዮች ናቸው። ካለበለዚያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ ማውራቱና ባንዲራ ማውለብለቡ ትርጉም የላቸውም።

ለማንኛውም የፍልስፍናን ትምህርት የተከተልን ከሆነ የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ አውሬ ሆኖ በፍጹም አይፈጠርም። የሚፈጠረውም ከልዩ ልዩ ጤናማ ባህርዮች ጋር ነው። ሰብአዊነት፣ ለሌላው ማሰብ፣ ከስነ ምግባር ጋር፣ ማፈርና ሌሎች ጤናማ ባህርዮች የሰው ልጅ ባህርዮች ናቸው። ርቀንም ስንሄድ፣ የሰው ልጅ ፈጣሪ፣ ህብረተሰብን መስራችና ራሱን በራሱ በማደራጀትና በመተጋገዝ ጤናማ ማህበረሰብ ሊመሰርት የሚችል ነው። ይህንን ነው ፍልስፍናው የሚያስተምረን። ይሁንና ግን ይህ የሰው ልጅ ጤናማና ተፈጥሮአዊ ባህርይ በተወሰነ የማህበረሰብ አወቃቀርና ስልጣንን በያዙ ሰዎች የተሳሳተ ትረካና፣ አንድን ቀኖናዊ ርዕዮተ-ዓለም በመከተል የተነሳ ሊቀየር ይችላል። አክራሪ በመሆንም ሌላ አስተሳሰብ ያለውን እንደ ጠላቱ ማየት ይጀምራል። መንፈሱንም ለማርካት ሲል ተቀናቃኜ ነው የሚለውን፣ ወይም በአስተሳሰቡ የሚለየውን በአንዳች ነገር ሲያጠፉ ብቻ ነው ደስታን የሚያገኝ የሚመስለው።

ያም ተባለ ይህ አሁን ምሁራን ነን የሚሉትን በሙሉ የምጠይቀው አመለካከታችን ምንድነው? በምንስ የፍልስፍና ወይም የርዕዮተ-ዓለም አመለካከት እናምናለን?  ምን ዐይነትስ ህብረተሰብ ለመገንባት ነው የምንታገለው? ምሁሮች እንደመሆናችን መጠን ካለመመሪያና ካለ ርዕይ ልንመራ አንችልምም። የቀኝ፣ የግራ፣ የኮሙኒስት፣ የኮንሰርቫቲቭ፣ የፋሺሽት፣ የሊበራል ወይስ የሌላ አመለካከት እንዳላለን ግልጽ ማድረግ አለብን። ስለህብረተሰብና ስለአገር፣ እንዲሁም ስለሰው ልጅ የምናወራ ከሆነ ከእሴትና ከሞራል ውጭ በፍጹም ልናስብ አንችልም። የለም እንደዚህ የሚባል ነገር የለም የምንል ከሆነ ደግሞ አሁን አሜሪካኖች እንደሚያስፋፉት ጾታ የሚባል ነገር የለም፣ ሁሉም ከጾታ ባሻገር መታየት ያለበት ትራንስ ርዕዮተ ዓለም ነው ያለን የሚባል ከሆነ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ውዥንብር ከመንዛት በስተቅር ያሉንን የተወሳሰቡ ችግሮች ሊፈታልን የሚችል አይደለም። ይህ ዐይነት አስተሳሰብ ደግሞ አሁን እንደምናየው የአሜሪካንንም ሆነ የተቀሩትን የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮችን በመግደልና ሁሉም ነገር ተዘበራረቀው እንዲገኙ በማድረግ ላይ ነው። ይህ ዐይነቱ ፀረ-እግዚአብሄርና ፀረ-ተፈጥሮ አስተሳሰብ እንደኛ ባለው አገር ውስጥም በመስፋፋት በሴቶችና በወንዶች መሀከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ግራ ተጋብተናል። ለማንኛውም ይህንን ወይም ያኛውን ርዕዮተ-ዓለም ነው የምንከተለው ብለን የምናምን ከሆነ ደግሞ በምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሳሪያ የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላ-ቀርነት እንደምንቀርፍና እንድምናስወግድ ደረጃ በደረጃ ማሳየት አለብን።  ስለሆነም በድረ-ገጾችና በየዩቱቭ ቻናሎች ላይ ሃሳብ  በሚንሸራሸርበት ጊዜ አንዳች ዐይነት የአሰራር ስልትን ተመርኩዞ መጻፉና መወያየቱ  የህብረተሰባችንን ችግር ለማወቅና መፍትሄም ለመሻት ያመቸናል። ከዚህም በላይ እኔ ቀኝ፣ ወይም ግራ ነኝ፣ ወይም ሌላ አመለካከት አለኝ ብሎ የቅጩን መናገር ማን ምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም እንደሚያስፋፋ ለማወቅ፣ ለመተቸትና ለማስተካከልም ይበጃል። እኔ የማምነው በዚኸኛው ርዕዮተ-ዓለም ነው ብሎ መናገሩም የሚያሳፍር አይደለም። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንድን ሰው መተቸትም ሆነ፣ ከሱ ወገን ሆኖ መታገልና ሌሎችን ማሳመን የሚቻለው። በስምና በዝና የሚደረግ ትግል ለትግሉና ለአገር ግንባታ ጥራትን የሚሰጥ ባለመሆኑ በተለይም ታዳጊውን ትውልድ እየተወናበደ እንዲኖር ነው የሚያደርገው። ለህብረተሰባችን የምንመኘው ነገር ካለ፣ ወይም ደግሞ አገራችን እንደማህበረሰብ በስነ-ስርዓት መደራጀትና ፈጣሪ፣ እንዲሁም ደግሞ ምርታማ እንዲሆን የምንመኝ ከሆነ ከዚህ ልናመልጥ አንችልም። ካለበለዚያ የአገራችን ችግሮች እኛም ከሞትን በኋላ ለብዙ መቶ ዐመታት ይቆያሉ። ህብረተሰባችን በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ መገኘት የለበትም፤ እኛም ከእንስሳ የምንለይ ፍጡር ነን፤ ስለሆነም ህብረተሰብአችንን በተሻለና ስርዓት ባለው መልክ ማደራጀት አለብን የምንል ከሆነ ደግሞ የግዴታ ስልትና ርዕይን ወይም ደግሞ የፍልስፍና አመለካከትን መሰረት አድርገን ብንጽፍና ብንወያይ ይሻላል። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

https://www.youtube.com/watch?v=XXIKhgXxkBo

https://www.youtube.com/watch?v=YLQos2zuabo

ማሳሰቢያ፣

  1. እንደዚህ ዐይነቱን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ብዙ ጊዜንና ዝግጅትን፣ እንዲሁም ኃይልን ይጠይቃል። ሌሎች ሳይንሳዊ ስራዎችን እንዳልሰራ እያስተጓገለብኝ ይገኛል። እንደዚህ ዐይነት ጽሆፎች ፕሮፌሽናል በሆነ መልክ መዘጋጀት ያለባቸው ስለሆነ ሌሎች ጊዜና ዕውቀት ያላቸው በዚህ ላይ ቢቀጥሉበት ደስ ይለኛል። ሜዳው ለአወናባጆችና ለውዥንብር ነዢዎች መለቀቅ የለበትም።
  2. የአሁኑን የአገራችንን የፖለቲካ ትርምስ፣ የሚሊተሪ ሁኔታና የአገዛዙን መጠነ -ሰፊ ግፍ አስታኮ ሰሞኑን የአቢይ አገዛዝ አገሪቱን ማሰተዳደር አልቻለም በሚል የአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት መግለጫ አውጥቷል። እንደ አበበ ገላው የመሳሰሉ ጋዜጠኞች ይህንን እንደ አዲስ ነገር አድርገው በማቅረብ ሲያራቡ ይታያል። ለእኛ አገር ወዳድ ኢትዮጵያን አቢይ አገርን ለማስተዳደር አለመቻሉን ከአራት ዓመት በፊት የተገለጸልንና ሰፋ ያለ ትንተና የሰጠንበት ጉዳይ ነው።
  3. ከዚህ ስንነሳ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና አገሮችን የሚያተረማምሰው የስለላ ድርጅቱ ዋና ዓላማ አገራችን የገባችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በመረዳት የሽግግር መንግስት በሚል ስም ለሱ የሚያጎበድዱ አዛውንቶችን ስልጣን ላይ በማውጣት ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታ በጣም አደገኛ ስለሆነ በሲአይኤና በዋናው አዛዡ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ታግዞ ስልጣን ላይ የሚወጣ ኃይል እንዳይኖር የማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው።
  4. ከእንግዲህ ወዲያ ስልጣን ላይ የሚወጣ ኃይል ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቁጥጥር ውጭ የሆነና ስለአገርና ብሄራዊ ነፃነት በቂ ግንዛቤ ያለው ድርጅት መሆን አለበት። አንድ ግለሰብ የሚፈነጭባትና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንደፈለገው የሚጠምዝዘው ግለሰብ ስልጣን ልይ እንዳይወጣ መታገል ያስፈልጋል።
  5. ስልጣንን በብሄረሰብ ኮታነት፣ ይህ ይገባኛል በሚል ስልጣን ላይ መውጣት እንደማይቻል ከአሁኑ ግንዛቤ ውስጥ መገባት አለበት። ስልጣን ላይ ለመውጣት መመዘኛው ሳይንሳዊ ዕውቀት፣ የአገር ወዳድነት ስሜት መኖርና፣ አገርን በጠንካራ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ መሰረት ላይ ለመገንባት መቻል እንደ ዋና መመዘኛ መወሰድ ያለባቸው ጉዳይ ናቸው። ማንኛውም ስልጣን ላይ የሚወጣ ግለሰብ በእርግጥም አገሩንና ህዝቡን የሚያገለግልና ለዚህም የተጠራ መሆነኑ የሚረዳ መሆን አለበት። በማንኛውም ጊዜ ከአሜሪካን የስለላ ድርጅት ጋር ያልተሳሰረና ለእሱም ተቀጥሮ ያልሰራ መሆን ብቻ አለበት። ስልጣን ላይ የሚወጣ ግለሰብ ከዚህ ቀደም የውጭ አገር ዜግነት ያለው መሆን የለበትም። በሁለት ቢላ መብላት አይቻልም እንደሚባለው ዜግነቱን ያለወጠና በሌላ ህገ-መንግስት ያልማለ ብቻ ነው በኢትዮጵያ ምድር ስልጣን ላይ ሊወጣ የሚችለው።
  6. በሌላው ወገን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ዜግነት ቢኖረውም እንደ ተራ ዜጋ ከፈለገ በአገሩ ውስጥ ሊኖርና የራሱን ስራ ሊያከናውን ይችላል።
  7. በዓለም አቀፍ ተቋማት ስር ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ በመንግስት ተቋማት ስር ተቀጥረው የመስራት መብት እንዳይኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህ ዐይነት ግለሰቦች ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና ለዓለም ባንክ ተቀጥረው በመስራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትን ሲያስፋፉና ጥሬ-ሀብትም ከሶስተኛው ዓለም ወደ ካፒታሊስት አገሮ እንዲዘዋወሩ ሲያደርጉ የከረሙ ንቃተ-ህሊና የጎደላቸው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አሽከሮች ናቸው። ጋናና ላይቤሪያ በፕሬዚደንትነት ተመርጠው ለስምንት ዓመታት ያገለገሉት ኮፉና ሚስስ ጆን በዓለም ባንክ ውስጥ ተቀጥረው የሰሩና ከፍተኛ ቦታም የነበራቸው ነበሩ። በየአገሮቻቸው ውስጥ ፕሬዚደንት እንዲሆኑ ከተመረጡ በኋላ የህዝቦቻቸውን ችግሮች የቀረፉ አይደሉም። ድህነቱና ኋላ-ቀርነቱ ጥልቀጥና ስፋት እንዲኖራቸው ያደረጉ የአሜሪካን ኢምፔርያሊዝም ታዛዦች የነበሩ ናቸው።
  8. ስለሆነም በአገራችን ምድር መሰረታዊ ለውጥ እንደሚጣ ከፈለግን፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የምንመኝ ከሆነ፣ ተከታታይነት ያለውና ድህነትን የሚቀርፍ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን የምንፈልግ ከሀነ አገር ወዳድ የሆነና መንፈሱ በጥሩ ዕውቀት የታነፀ ድርጅትና በሺሆች የሚቆጠሩ ንጹህ ኢትዮጵያውያንን ማዘጋጀት የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በዚህ መልክ ብቻ ነው ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትሆን አገርን መገንባት የሚቻለው።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop