September 26, 2023
17 mins read

የመስቀል በዓል እና የወዮላችሁ መግለጫ!

fd00eda212304a43b7bae4df4804f43e 640 426

September 24, 2023

T.G

በየዓመቱ ከሚከበሩት ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ እምነት የመስቀል በዓል ከሚከበርበት  ዋዜማ ላይ እንገኛለን።

ባሳለፍነው ሳምንት ሁለት የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛው አካል (የሲኖዶስ) አመራር አባላት (ሊቃነ ጳጳሳት) የዚህኑ በዓል አከባበር አስመልክቶ የሰጡትን መግለጫና ማብራሪያ በአትኩሮት ተከታተልኩት። የተከታተልኩት ግን ለዘመናት ደጋግሞ ከመውደቅ አዙሪት ከመውጣት ይልቅ ይበልጥ አስከፊነቱን ለመግለፅ በሚያስቸግር አጠቃላይ የቀውስ አዙሪት ውስጥ እየጓጎጠ የቀጠለው የአገሩ ህዝብ (ትውልድ) በእጅጉ እንደሚያሳስበው ሰውና እንደ አንድ የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ተራ (ordinary) አማኝ/ተከታይ በእጅጉ በተደባለቀ ስሜት (highly mixed feeling) ነበር።

አዎ! ለዘመናት የመጣበትና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከምንጊዜም በላይ ለመግለፅ የሚያስቸግር የመከራና የውርደት ዶፍ እየወረደበት ያለው ህዝብ ትዕግሥትም ልክ አለውና በቃ በሚል የሃይማኖታዊ እምነት ነፃነትን ጨምሮ እልህ አስጨራሽ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ እያደረገ የመሆኑ እውነታ በአንድ በኩል እና በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረውን ሰብአዊ ፍጡር (ወገንን) ከመታደግ የሚበልጥ ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ዓላማና ተልእኮ ያለና የሚኖር ይመስል የሃይማኖት መሪዎቻች የእኩያን ገዥ ቡድኖችን እጅግ አሸባሪና አደገኛ የወዮላችሁ አዋጅ ተቀብለው እኩያንና ጨካኝ የሥርዓቱ ተዋንያንን በሚያስንቅ አኳኋን ሲገልፁትና ሲዘረዝሩት መታዘብ የሚፈጥረው ድብልቅ ስሜት በእጅጉ ከባድ ነው።

የኩራት/የደስታ እና የዚሁ ተቃራኒ የሆነው የሃፍረት/የሃዘን ስሜት በአንዴ ሲደባለቁ እና ከዚህ የመውጫው መንገድ እንዴትና ወደየት እንደሆነ ተገልፆ አልታይ ሲል ሊፈጥር የሚችለውን የህሊና ፈተና ለመገመት የሚያስቸግር አይመስለኝም።

ምንም እንኳ የሃይማኖታዊ በዓላትን በእውነተኛ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የፍቅርና የሰላም መንፈስ ለማክበር ያለመታደላችን መሪር እውነታ አያሌ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከአምስት ዓመታት ወዲህ የገጠመንና እየገጠመን ያለው ግን በእጅጉ የተለየና የከፋ ነው።

የአገር (የህዝብ) በፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባ የመሆኑ መሪር እውነታ ይበልጥ እየከፋ በሄደ ቁጥር የሃይማኖት መሪዎቻችንና ሰባኪዎቻችን ( አስተማሪዎችን) በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረውን ሰብአዊ ፍጡር ከመታደግ የበለጠ ሰማያዊውም ሆነ ምድራዊ ሃላፊነትና ተልእኮ የነበረና የሚኖር ይመስል በፖለቲካ አያገባኝም እና ሰላም ያለ ይመስል  እውነቱን ብናገር/ብንናገር ሰላም ይደፈርሳል በሚል እጅግ ልፍስፍስ በሆነ  ወይም አድርባይነት (ራስ ወዳድነት)  በተጠናወተው ቀጭን መስመር ላይ ለመራመድ ሲሞክሩ ማየት (መታዘብ) በእጅጉ ይረብሻል።

ለዚህ እጅግ አስከፊና አስፈሪ ቀውስ ዋነኛ ተጠያቂዎች በየተራ እየተፈራረቁ በጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ዙፋን ላይ የሚሰየሙት ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ቢሆኑም የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎችንና አስተማሪዎችን ጨምሮ የምድር ላይ ሲኦል ሰለባ እንዲሆን የተፈረደበት ህዝብ ያደረገውንና እያደረገ ያለውን የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ስኬታማ ይሆን ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ያልተወጡና በመወጣት ላይ የማይገኙ ምሁራንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ከተጠያቂነት ነፃ ለመሆን ፈፅሞ  አይቻላቸውም።

ባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ተረኛ ገዥ ቡድን ለአምሥት ዓመታት እና አሁንም በባሰ ሁኔታ የመከራና የውርደት ቀንበር ተሻካሚ ያደረገውና እያደረገው ያለው ህዝብ ትእግሥትም ልክ አለውና ከእንግዴህ በቃ!” ብሎ በመነሳቱ በመስቀል በዓል ላይም ይህንኑ የአትግደሉንና የአታሰቃዩን ብሶቱን ሊያስተጋባ ይችላል በሚል ያዘጋጀውን የወዮላችሁ ወይም የእኛን ያያችሁ ተቀጡ አዋጅ በሃይማኖት መሪዎች በኩል እንዲተላለፍ አድርጓል ።

የሃይማኖት መሪዎችም ይህንኑ የባለጌ ፣ የፈሪና የጨካኝ ገዥ ቡድን አዋጅ በሰላምና በፍቅር አስፈላጊነት ስም  ግረውናል (አሳውቀውናል)።

በመሠረቱ የሃይማኖት መሪዎቹ የሃይማኖታዊ በዓላትን እንኳንስ በአደባባይ በቤተ እምነቶች ዙሪያ ለማክበር ስናስብም ደጋግመን እንድናስብ በተገደድንበት በዚህ እጅግ አስቀያሚና አስፈሪ ወቅትና ሁኔታ አስፈላጊውን (ተገቢውን) ማሳሰቢያና ምክር የመስጠታቸውን ተገቢነት ለመረዳት ከቶ አያስቸግርም።

የወዮላችሁ አዋጁን አይምሬነት ነግሮ (አስጠንቶ) የላካቸው የሃይማኖት መሪችዎ ከራሱ ማለትም ከመንግሥት ተብየው በተሻለ አቀራረብና አንደበት (ኮስታራነትና አፅንኦተ ቃላት)  ያስተላለፉበትን ሁኔታ  በጥሞና ለታዘበ በእውነት ምን ነካን ?  ዘመናት ሲለዋወጡ እኛ ግን እንኳን ልንለወጥ በነበርንበትም እንኳ ቆሞ መገኘት ተስኖናልና ይህን የንገሩልኝ ተውኔት ሊያስገርመን አይችልም። በእጅጉ ግን ያሳዝናል።  ወደ ማጠቃለያየ ልለፍ።

 

ለመሆኑ፦

·          ስለ መስቀል ከሚገልፅ (ከሚዘክር) በስተቀር ሌላ ማነኛውንም ንግግር ወይም ፅሁፍ ወይም ምልክት መጠቀም አይቻልም ማለት ምን ማለት ነው? የዓለማዊው ይቅርና ሌሎች የቅዱስ መፅሃፍ ቃላትና ጥቅሶችም ሁከት ያስነሳሉ ማለት ነው? ምነው ይህንን ያህል ወረድን?

 

·         እንዲህ አይነቱ ቁልቁል መውረድ እና  ክርስቶስ በመስቀል ላይ የዋለለት ክቡር ዓላማ በምን ይገናኛሉ? ክርስቶስ የተሰቀለው የምድራዊውና የሰማያዊው ህይወት ዋስትና ስለሆኑት ስለ ፍቅር ፣ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍትህና ርትዕ፣ ስለ እኩልነት፣ ስለ ነፃነት ፣ ወዘተ እንጅ  በጊዜው የነበሩትን ህዝብን የሚያጎሳቁሉ ገዥዎችን በመለማመጥና ልክ የሌለው ትዕሥትን እሹሩሩ በማለት አልነበረም። ነበር እንዴ?

 

·          ድርጊት አልባ በሆነ በመስቀሉ የእናምናለን  እግዚኦታ  እና እኩያን ገዥዎችን በመጎናበስ ወይም ደጅ በመጥናት ወይም ልክ የሌለው ፍርሃት በማሳየት እንኳንስ ሰላምንና ፍቅርን በህይወት የመኖርን መብትንስ እንዴት እውን ማድረግ ይቻላል?   ልክ የሌለው ፍርሃትና አርበኝነት ፍፁም ተቃራኔዎች አይደሉም እንዴ

 

·         ለመሆኑ የሃይማኖት መሪዎች መታገሥን እንደ ፍርሃት ፣ አስተዋይነትን እንደ የአቅምና የሞራል ማጣት ቆጥረው በህዝብ ላይ የመከራ ዶፍ የሚዘንቡትን ገዥ ቡድኖች አደብ ግዙ ብሎ ለመገሰፅ ለምን አቅም አጡ

 

·         የመታገሥን (የትዕሥትን) ነገር አደራ የሉናል። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በትእግሥት ስም መሸከም ያለበት ምን ያህልና ምን አይነት መከራና ውርደት? ለስንት ጊዜና እስከ የትስ  ድረስ ነው ?

 

·         ፈቃድ ወይም ባጅ ሳይኖር በፈቃደኝነት ማነኛውንም የድጋፍና  የማስተባበር እንቅስቃሴ ማድረግ እንደ ወንጀል ስለሚቆጠር ተጠንቀቁ ሲሉን ምን ምን ነካችሁ? ብሎ መጠየቅ ከማክበር ወይም ካለማክበር ጋር ግነኙነት እንዴት ሊኖረው ይችላል?

 

·         አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለው ነገር ሁሉ ይዛችሁ ከተገኛችሁ የሰላም መደፍረስ ምክንያት ትሆናላችሁና ተወዮላችሁ የሚል እጅግ የወረደና አዋራጅ አዋጅ እያወጁ የመስቀል በዓል የደስታና የፍቅር ይሁንላችሁ ማለት እንዴት ስሜት ይሰጣል?

 

·         መስቀልን እንደ አባቶቻችን በሥርዓት፣ በፍቅርና በእምነት እናክብረው ስትሉን አባቶቻችን እንደዚህ እንደ እኛ የገዛ ወገን በሆነ ገዥ ቡድን ከሰብአዊ ፍጡር በታች በሚያውል ሁኔታ ነበር እንዴ መስቀልን ያከብሩት የነበረው ?  አባቶቻችን አገራቸውንና ሃይማኖታቸውን የሚዳፈረውን ሁሉ በአርበኝነት እየተናነቁ ታላቅ ታሪክ ሠርተው አለፉ እንጅ እንደ ዛሬዎቹ እንደኛ ነገረ ዓለሙ የተምታታባቸው ነበሩ እንዴ?

 

·         አዎ! “የመዳን ቀን አሁን ነው” ይላል መፅሃፉ። የመዳን ቀን በእውን ይዳንበት ዘንድ አናስድንም የሚሉ እኩያን ገዥዎችን በጅ ካሉ ልብ እንዲገዙ ማስገደድ ካልሆነ ግን ሥርዓታቸውን እንደ ሥርዓት አፈራርሶ የመዳንን ቀንን ትርጉም የሚያውቅና ለመዳን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ሥርዓት እውን ማድረግ እንጅ የዮላችሁ አዋጅን እየተቀበሉ ማስተጋባት ምን ይባላልምንስ የሚሉት የሃይማኖት መሪነት ነው?

 

·         አዎ! ቤተ ክርስቲያንና አማኞቿ በአስከፊ ፈተና ውስጥ መጓጎጥ ከጀመሩ እኮ ዓመታት ተቆጥረዋልና አዲስ ክስተት አይደለም። ጥያቄው የአስከፊው ፈተና ዋነኛ ምክንያት እኩያን ገዥ ቡድኖች መሆናቸው የታወቀ ቢሆንም የእነርሱን የብልግና እና የጭካኔ አዋጅ (መግለጫ) ተቀብላችሁ ከእነርሱ በበለጠ ሁኔታ እያስተጋባችሁ ባላችሁበት አስቀያሚ ሁኔታ ውስጥ ፈተናው እንዴት ይወገዳል? የሚለው ነው።

 

·         መከራና ወርደት ፣ቂምና ጥላቻ፣ እና መገዳደል ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ እጅግ ክፉ ደዌ ከሆነ እኮ ብዙ ዓመታት ተቆጠሩ ። አሁን ያለንበት ወቅት ለመግለፅም የሚያስቸግር ነው። ታዲያ በዚህ ላይ የእናንተ የገዥዎችን ማስፈራሪያ /ማሸበሪያ አዋጅ ተቀብላችሁ አስፈሪ በሆነ አቀራረብና ሃይለ ቃል የማስተጋባታችሁን ነገር  ምን እንበለው ?ቀብሎ ማስተጋባ ሲጨመርበት ሌላ የተለየ ለውጥ እንዴት መጠበቅ ይቻላል?

 

በዚህ ሁኔታችን ለብዙ ዘመናት በመከራና በውርደት ሥርዓት ሥር ሆነን ጊዜ ብቻ እያሰላን ለይስሙላ (ያለ እውነተኛ ደስታ)  በዓላትን አከበርን ከምንልበት ራሳችንን የማታለል ልማድ ከቶ ለመላቀቅ አይቻለንምና ልብ ካለን ልብ እንበል!

ለዚህ ብቸኛው መውጫ መንገድ የእኩያን ገዥዎች ሥርዓትን አስወግዶ የሃይማኖትና ሌሎች መሠረታዊ የሰው ልጅ ወይም የዜጎች ሁሉ መብቶች የሚከበሩበት ሥርዓትን አምጦ መውለድ ነው። ለዚህ እውን መሆን ደግሞ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም በየሙያውና በየአቅሙ እልህ አስጨራሽ ድራሻውን መወጣት ይኖርበታል!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

383752559 3713068635593267 5669511217268944015 n 1 1 1
Previous Story

“ውሃ … ውሃ” የሚል ድምፅ በተቀበረ ቱቦ ውስጥ የድረሱልን ጥሪ

186077
Next Story

በተለያዩ ግንባሮች ከፍተኛ ውጊያዎች እየተደረጉ ነው፥ የአገዛዙ ሰራዊት አባላት እየጠፉ ነው፥ የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ተዘጋ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop