ዛሬ አንድ የፌስ ቡክ ጓደኛየ የአቶ በቀለ ገርባን ሽሽት ከተመለከተ በኋላ የሚከተለውን መልእክት ጻፈ። ” አገሩን አርማጌድዮን አደገህ ብልሆች ወደ ሰሩት አገር በነጻነት ለመኖር ሄድክ? “
አባባሉ እኔንም ወደ ዛሬ ስድስት አመት ትዝታየ ወሰደኝ።
በወቅቱ በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ ወዘተ በወያኔ አፋኝ መንግስት ታስረው ፎቶአቸው እየተያዘ Free Bekele Gerba, Free Eskindir Nega.. የሚባልበት ወቅት ነበር። አስደናቂው በጎንደር ህዝቡ የበቀለን ፎቶ ይዞ ሰልፍ ይወጣ ነበር።
መፈታት አይቀርምና ሁሉም ተፈቱ። በዲያስፖራው ትልቅ ደስታ ሆነ። እኛም በጀርመን የምንገኝ የተወሰን ሰዎች አዳራሽ ውስጥ ሁነን በጋራ ስልክ ተመስገን ደሳለኝ ቤት እንዳሉ ሁሉንም የቀድሞ የፖለቲካ እስረኞችን አነጋገርናቸው።
የግብዣ ወረቀት እንደምንልክላቸውና መጥተው የናፈቃቸውን ኢትዮጵያዊ እንዲያገኙት። ከበቀለ ውጭ ሁሉም እሽ አሉ። በቀለ ሰንካላ ምክንያት ሰጥቶ እንደማይችል ነገረን። በማግስቱ ወያኔ ያልተፈቀደ ባንድራ ሰቅለዋል ብሎ ከበቀለ ውጭ ሁሉንም እንደገና አሰራቸው። በጥቂት ቀናትም መልሶ ለቀቃቸው።
ለውጥ መጣ ህዝብ በደስታ ሰከረ። ኦሮማራ ጥምረት ተብሎ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር በፍቅር አበደ።
እስረኞች ሁሉ ተፈቱ። በዚህ ወቅት ህዝብ በደስታ ጡዘት ባለበት በቀለ ገርባ ፍጹም ሙልጭ ባለ አረመኔነትና ክህደት በተሞላበት አምስት የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶችን ሰብስቦ ራሱ በሚያነበው መግለጫ ሰጠ። አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት፣ መኖር የፈለገ መኖር ይችላል። ያልፈለገ ግን ለቆ መሄድ ይችላል የሚል።
እነሆ ታላቁ ጦርነት ተጀመረ!
ሁሉ ነገር ትርምስምሱ ወጣ። በየ አቅጣጫው የቃላት ውርወራው ተጀመረ። ሟቹ የአማራ ክልል ፕሬዝደንት ዶ/ር አምባቸው ፍርጥም ያለ መልስ ስለ ጉዳዩ ሰጡ። እነ በቀለ የዲቃላ ፖለቲካን ጀመሩ። ኦሮምኛ ላላወራችሁ እቃ አትሽጡ አለ በኢፋ ወጥቶ። በሰበብ ባስባቡ ረብሻ በማስነሳት የሰው ደም እንደ ጎርፍ ፈሰሰ። መቀሌ ሂዶ ከቀድሞ አሳሪዎቹ ጋር በይፋ ተጨባበጠ። ከሰማኒያ አመት በፊት በጀርመን የነበሩ ናዚዎች የተጠቀሙበትን ቃላት ሁሉ በይፋ በየሚድያው ሰበኩ።
የቀድሞው የእስር ቤት ጓደኛው፣ ከተፈቱም በኋላ አብረው በአንድ ቤት ውስጥ በስልክ ያወራናቸው ጓደኛው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ጓደኞቹ በአዲስ አበባ ካሳንችስ ባልደራስ በተባለ ቦታ ያን በንዴት የጦፈን የአዲስ አበባ ወጣት ስብሰባ ጠርተው መጀመሪያ እንደ ሲቪክ ማህበር በኋላ የፖለቲካ ድርጅት የሆነን ፖርቲ አቋቋሙ። የለውጡ ሞተር ነን የሚሉት መንገዳቸው ቁልቁለቱ የዚያን ግዜ ጀመረ።
በቀለና ጓደኞቹም በየቦታው እየዞሩ የዘረኝነቱን ስብከት ቀጠሉበት። እነሱንም ተከትሎ በዘረኝነት የሰከሩ ወጣቶች ጅምላ ግድያውን ገፉበት። ምድሪቱ ሲኦል ሆነች። በመጨረሻ በቀለም እስክንድርም እንደገና እስር ቤት ገቡ። እስክንድር ለምን እንደገባ እስከ አሁን ለኔ ምንም ግልጽ ምክንያት አላገኘሁም።
ዛሬ ያ በየስርቻው ለአምስት አመት ደሙ የፈሰሰው ሚስክን የአማራ ገበሬ በደሉ ተሰምቶ ሁሉን አቀፍ የነፍጥ ውጊያ በመላው አማራ ክልል ተከፈተ። በሌሎች ቦታዎችም ህዝቡ የራሱን ጥያቄ ይዞ ተቃውሞ እየወጣ ነው። ነገሮች በፍጥነት እየተቀያየሩ ነው። በዚህ ወቅት በቀለ ገርባ እሱ ችቦውን የለኮሰው የጥፋት እልቂት ባመጣው ጣጣ ህዝብ እምቢ ብሎ ሲነሳ እሱ ብልሆች በጥንቃቄ በህግና በስርአት ወደሰሯት ታላቋ አሜሪካ ገብቶ ጥገኝነት ጠየቀ። ከአማራ ጋር አትጋቡ፣ ንግድ አትነግዱ ወዘተ እያለ በአንድ ሀገር ውስጥ መኖር ያልቻለ ሰው በሰው ሀገር ከነጭ ጋር አብሮ ሊኖር ተሰደደ።
እውነተኛው ፍርድ በመጣ ግዜ የትስ ቢገባ ማምለጥ ይቻላል። የእነዛ አገር ደህና ብለው በየጎጆአቸው ተቀምጠው የነበሩ ሴቶችና ህጻናት፣ አዛውንቶች አማሮች በከንቱ የፈሰሰ ደም በምድርስ በሰማይስ ያስቀምጣል ወይ?
ማጠቃለያ፣
ባንድ ወቅት የነገረኝን ሰው ብረሳውም። የበቀለ የቅርብ ዘመድ ህዝቡ የእሱን ፎቶ ይዞ በየሰልፉ ሲወጣ አይቶ። ” አየ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀለን ቢያውቀው ምንኛ ያዝን” አለ የተባለውን ሳስታውስ የኢትዮጵያ ህዝብ እጅጉን አንጀቴን ይበላኛል። ላለፉት አርባ አመት በላይ የሚፈልገውና እየሆነበት ያለው ነገር ከሰማይና ከምድር የተራራቀ በመሆኑ ወደፊት እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት ጉዞ ማድረግ እንዳለበት እመክራለሁ።
በቄ ሆይ የለኮስከው ጦርነት የድሀውን ልጅ ብቻ በልቶ አይቀርም። አንተንም ለፍርድ አደባብይ ያቀርብሀል።
ይዘገያል እንጅ ወንጀለኛ ለፍርድ ይቀርባል!!!