“ለራሳቸው ክብር ባይኖራቸውም፣ ራሳቸውን የሚወዱ በመሆናቸው፣ የኦህዴዶች ተላላኪና ተልክስካሽ መሆን በአሁኑ ወቅት ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ተረድተው፣ ለራሳቸው ሲሉ ኦህዴዶችን እምቢ ማለት ይጀምሩ ይሆናል” በሚል የአማራ ክልል ምክር ቤት ቢያንስ አሁን እንኳን ከህዝብ ጋር ይወግናል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡
ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ የደቡብ ወሎ ቃሉ ወረዳ ተወካይ ናት፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዬ ፡፡ አቶ አማረ ሰጤ በጎንደር፣ የአለፋና ታኩሳ ወረዳን ወክሎ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዬ ነው፡፡ ዶር ይልቃል ከፍያለ፣ በጎጃም በዱር ቤቴ ወረዳ ህዝብ ተመርጦ፣ የክልሉ ምክር ቤት አባል የሆነና በክልሉ ምክር ቤት የክልሉ ርእስ መስተዳደር የሆነ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ያለ ህዝብ ምንም አይደሉም፡፡ አለን ያሉትን ሁሉ ስልጣን ያገኙት ከህዝብ የተነሳ ነው፡፡
ተመርጠው ስራ ሲጀምሩም፣ እጆቻቸውን አንስተው ቃለ መሃላ አድርገዋል፡፡ “ህዝብን እናገለግላለን፣ ታማኝነታችን ለህዝብ ብቻ ነው” ብለው፡፡ ሆኖም ግን መሃላቸውንና የገቡትን ቃል ረስተው፣ በህዝቡ ላይ ክህደት ፈጽመው፣ ህዝብን ከማገለገለና ከመጠበቅ፣ ህዝቡን ለችግርና ለመከራ ዳርገውታል፡፡ ፣ ህወሃቶች ተፈናቃዮች ካልተመለሱ እያሉ ሌትና ቀን ሲሰሩ፣ እነርሱ በመሪነት ቦታ ተቀምጠው፣ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ከኦሮሞ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ጉዳይ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ በአማራ ክልል በአብይ አገዛዝ ጦርንበት ሲከፈትም ማስቆም አይደለም፣ ከዝህብ ጋር ሆነ የአብይን አገዛዝ መመከት ሲገባቸው ተባባሪ ነው የሆኑት፡፡ በአብይ አህመድ ትእዛዝ በአስር ሺሆች የህዝብ ልጆች ፣ ፋኖዎችን አስረው እያሰቃዩ ነው፡፡
ምክር ቤት ሳይፈቅድ፣ የክልሉ መንግስት ጥሪ ሳያቀርብ፣ በነ አብይ አህመድ ጀብደኝነትና ጥጋም፣ በማን አለብኝነት፣ ሰላማዊ የነበረ ክልል የጦርነት ቀጠና ሲሆን፣ የክልሉ ምክር ቤት ቀደም ብሎ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ፣ እነ አብይ አህመድን ማስቆም ፣ አናቆምም ካሉ ደግሞ ከህዝቡ ጋር ሆኖ እነርሱን ለመመከት ለህዝብ ጥሪ ማቅረብ ነበረበት፡፡ ህወሃት ወረራ ስትፈጸም እንደነበረው፡፡ ሆኖም ያንን አላደረጉም፡፡ ህዝቡ በየቦታው ከተረኞች ጋር ሲተናነቅ እነርሱ ዝም፣ ቁጭ ብለው፣ ያው መደበኛ ስብሰባ መደረግ ስላለበት፣ በባህር ዳር ብዙዎች ያልተገኙበት ስብሰባ አድርገዋል፡፡
መደበኛው ስብሰባ፣ በህግ ለህዝብ በቴሌቪዥን መተላለፍ ነበረበት፡፡ ሆኖም ወ/ሮ ፋንቱ፣ አቶ አማረና ዶር ይልቃል፣ በቀጥታ የአብይ አህመድንና የኦህዴድን ትዕዛዝ በመቀበል፣ የምክር ቤት አንዳንድ አባላት እንዲተላለፍ ቢጠይቁም እምቢ ብለው ሕገ ወጥ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ለህዝብ ያላቸውንም ንቀት አሳይተዋል፡፡ የምክር ቤቱን ስብሰባ፣ ወ/ሮ ፋንቱን የመረጠው የቃሉ ወረዳ፣ አቶ አማረ የመጡበት የአለፋና ታኩሳ ወረዳ፣ የዶር ይልቃል የመጡበት የዱር ቤቴ ወረዳ ህዝብ ብቻ አይደለም፣ መላው የክልሉ ህዝብ በሜዲያ እንዳይሰማ ነው ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ያገዱት፡፡
አቶ ዮሐንስ ቧያሌው፣ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪና ሌሎች የተወሰኑ የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የህዝብን ጥያቄ በድፍረት አቅርበዋል፡፡ መሰረታዊና ስር ነቀሎ ለውጦች እንዲደረጉ፣ ክልሉን ወደ ሰላም የሚያመጡ ውሳኔዎች እንዲወሱ፣ ክልሉን እያተራመሱ ያሉ ከአራት ኪሎ የተዘረርጉ ጣቶች እንዲሰበሰቡብ ወይንም እንዲቆረጡ ተማጽነዋል፡፡ ብዙ ክርክር ነበር፡፡
ሆኖም እነ ዶር ይልቃልና ወ/ሮ ፋንቱ፣ የምክር ቤቱ አመራሮች፣ የህዝቡ ጥያቄ ልማትና የህግ የበላየነት በሚል፣ የተነሱ ጥያቄዎች አናንቀውና አደባብሰው ለማለፍ ሞከረዋል፡፡ ጥያቄዎች ሲጠነክሩ፣ ” በየዞኑ አምስት አምስት ሰው ወክለን ጥናት እናደርጋለን” ብለው ከማለፍ የዘለለ፣ ምንም አይነት ውሳኔ እንዳይወሰን አድርገው የምክር ቤት የተባለው ስብሰባ ተጠናቋል፡፡
በነወልቃይት ጉዳይ ለተነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች፣ አማራዉን ባላሳተፈው በደቡብ አፍሪካው ስምምነት ዙሪያ ምላሽ ሳይሰጡ አልፈዋል፡፡ ከነ አብይ አህመድ ጋር የአማራ ብልጽግና አመራሮች ስምምነት ስላደረጉ ፣ ምን ብለው ምላሽ እንደሚሰጡ ግራ ስለገባቸውም ይሆናል፡፡
ምን አለፋችሁ በአማራ ክልል ያለውን ችግር በመሰረታዊነት ለመፍታት፣ ሰላም እንዲመጣ ለማድረግ ትልቅ ስልጣን እያላቸው፣ ስልጣናቸውንና ከፊታችው የነበረው መልካም እድል ሳይጠቁመብት ቀርተዋል፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው፣ እነ አብይ አህመድ ከአማራ ክልል እጆቻቸውን እንዲሰበስቡ መደረግ ሲገባው፣ ጭራሽ የነርሱን ሰዎች በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ በአማራ ክልል እየሾሙ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ፣ “የዐቢይ አህመድ ቀኝ እጅ፤ የእነ ሽመልስ አብዴሳ ተላላኪ የሆነው፣ በቅርቡ የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚነት የተመረጠው፣ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ አቶ አብዱ ሁሴን፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሁኖ መሾሙን አሁን በደረሰኝ መረጃ ለማረጋገጥ ችያለሁ “፣ ሲል ዘግቧል፡፡ አሻንጉሊቱና ደካማው ፣ ለራሱ ክብር የሌለው ይልቃል ከፍያለ ቁጭ ብሎ፣ በባህር ዳር ሺመልስ አብዲሳ ቁጥር ሁለት ተቀምጦ ይልቃልን ለመቆጣጠር፣ ለማዘዝ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ያን ያህል ነው እንግዲህ የአማራ ክልል ምክር ቤት የሚባለው በተቋም ደረጃ የበሰበሰ አሳፋሪ ተቋም የሆነው፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ የምክር ቤት አመራሮች ከአብይ ተጽኖ ካልወጡ፣ በምክር ቤቱ የመተማመኛ ድምጽ ተሰጥቶ የኦህዴድ አሽከር አመራሮችን ማስወገድ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ካልቻሉ፣ ለህዝብ የወገኑ የምክር በት አባላት ፣ በምክር ቤት ውስጥ በቆዩ ቁጥር ከነ ፋንቱ ተስፋዬና ይልቃል ከፍያለ እኩል ተጠያቂ መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡ በመሆኑም አቋማቸውን በግልጽ በአደባባይ ማሳወቅ መጀመር አለባቸው፡፡ በምክር ቤት ስብሰባ እንዳንናገር ታፈን ያሉ፣ በሜዲያ ወጥተው እንዳይናገሩ የሚያፍናቸው ስለሌለ፣ ወደ ህዝቡ ይሄዱ፡፡ የህዝብን ትግል ይቀላቀሉ፡፡
(ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ከቃሉ ወረዳ ደቡብ ወሎ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዬ፣ አቶ አማረ ሰጤ ፣ ከአለፋ ጣቁሳ፣ ጎንደር የአማራ ክልል ምክር ምክትል አፈጉባዬ፣ ዶፕር ይልቃል ክፍያለ፣ ከጎጅም ዱርቤቴ፣ የአማራ ክልል ር እስ መስተዳደር)