ተው ስማ ወገኔ!ተው ስማ ተው አድምጥ!

ሄሮድስ ፈሪሳውያን ዙፋን ተቀምጠው፣
እነ ጲላጦስም ችሎት ተጎልተው፣
ስቅለትን ማስቀረት ዘበት ዘበት ነው!

ክርስቶስን ሰቅሎ በርባንን ተፈታ፣
ፍትህን መጠበቅ አንጋጦ ጧት ማታ፣
አንድም ድንቁርና ሁለትም ወስላታ!

እውነት ክርስትና በዓለም የተስፋፋው፣
የጴጥሮስ ጳውሎን አንገቶች ያስቀላው፣
የሮም ሕዝብ ጠልቶ አንቅሮ የተፋው፣
አረመኔው ኒሮ ራስ ሲያጠፋ ነው፡፡

ተላይ ታስቀመጥከው ሌባ ቀጣፊውን፣
ክብርና ማእረግን አይቶ እማያውቀውን፣
ሲተፋብህ ያድራል ልሐጩን ምራቁን፡፡

አለቅደም አያትህ ሞኝ ሆነህ ተታተለህ፣
መደብ ለአውሬ ሰጥተህ ወለል ተቀምጠህ፣
እንኳንስ መተኛት ክብር ማእረግ ለብሰህ፣
ራቁት ማደርም ተሰማይ እራቀህ፡፡

ለላም አሸናፊ አውቀህ ተተሸነፍክ፣
ስትቆም አታስቆምህ ስተኛ አታስተኛህ፡፡

እርቅን ሽምግልናን የሚያረክስን አምነህ፣
ዛሬም እንደ ትናንት ለድርድር ቁጭ ታልክ፣
እንኳንስ መለኮት ሰይጣን ይታዘብህ፡፡

ተው ስማ ቀበሌ! ተው ስማ አገር መንደር!
ተከሀዲ ቅዬ ተቀጣፊ ሰፈር፣
እርቅ ሽምግልና ለሰከንድም አይሰፍር፡፡

ተው ስማ ወገኔ! ተው ስማ ተው አድምጥ!
ሲወጡ እንዳይረግጡህ ሲወርዱ እንዳትዳጥ፣
ለአንዲት ደቂቃ እንኳን ተግርጌ አትቀመጥ፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዘመኑ መንፈስ (በእውቀቱ ስዩም)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share