የአስተሳሰብንና የአካሄድን ሸውራራነት (ስህተት) ተገንዝቦ ወደ ትክክለኛው አስተሳሰብና የተግባር ውሎ መመለስ እኮ ነውር አይደለም!

July 16, 2023

T.G

በአሜሪካ (ካሊፎርኒያ ግዛት) ለሚሠራው ገዳም በእሸቱ ማህበራዊ ሚዲያ (ዶንኪ ቲዩብ) በመካሄድ ላይ ስላለው ዘመቻ ባለፈው ሳምንት (July 10) “ዛሬም ከአስቀያሚው ወለፈንዲነት (ugly paradox) ሰብሮ ለመውጣት አልሆነልንም!” በሚል ርዕስ አጨር ሂሳዊ አስተያየት ሰንዝሪያለሁ።  ይህ የዛሬው ሂሳዊ አስተያየቴም ያንኑ የሚያጠናክርና ይበልጥ ግልፅ የሚያደርግ ነው።

 

በዚያኛው አስተያየቴ እንደገለፅኩት ጥያቄዬ በሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እና የሃይማኖት መሪዎችንና አስተማሪዎችን ጨምሮ በአንዳድ በአድርባይነት ልክፍት በተለከፉ ወገኖች ምክንያት የገዛ አገሩ ምድረ ሲኦል ሆናበት ከወገን አልፎ ባእዳንን የእለት ምፅዋዐት በመማፀን ላይ ለሚገኘው መከረኛ ህዝብ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ መረባረብ ሲገባ በተሰኑ ሰዓታትና ቀናት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ካልሰጣችሁን “በረከቱ ቀረባችሁ” በሚል ዘመቻ ላይ መጠመድ እንኳንስ ለተቀደሰ ሃይማኖታዊ እምነት ለሞራልም (ለሚዛናዊ ህሊናም) በእውን ይመጥናል ወይ? የሚል እንጅ ገዳምና ሌላም አገልግሎት ሰጭ ድርጅት አያስፈልግም የሚል በፍፁም አይደለም ።

ይህንን ካልኩ ወደ ዋናው የአስተያየቴ ክፍል ልለፍ፦ የዚህ ዘመቻ አባላት ሆይ ፦ በገዛ አገሯ የምድር ፍዳ የምትቀበለውን እናት፣ መልካም አባውራነት ወደ ሰቆቃ ህይወት የተቀየረበትን አባት፣ በመከራ ውስጥ ተወልደው በማያቋርጥ መከራ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትንና ታዳጊዎችን፣ አኗኗራቸው ብቻ ሳይሆን አሟሟታቸው የከፋ እህትና ወንድሞችን፣ እና በአጠቃላይ የምድር ላይ ሲኦል ሰለባ የሆኑ ንፁሃን ወገኖችን በአንድ በኩል እና በሌላ በኩል ደግሞ የተጠመዳችሁበትን ፈፅሞ  የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን  የማይጠይቅ  እጅግ አስቀያሚ የዶላር ውለዱ ዘመቻ  ከምር በሆነ አይነ ህሊናቸሁ አጤኑትና ንስሃ ገብታችሁ እውነተኛው አምላክ ወደ የሚወደውና የሚባርከው ባህሪና ተግባር ተመለሱ!

በዚህ አይነት በእጅጉ የቅድሚያ ትኩረትን የሳተ አስተሳሰብና አካሄድ የሚገነባን ገዳም ማደሪያው የሚያደርግ እውነተኛ አምላክ ፈፅሞ የለምና እውነተኛ አማኞች ከሆናችሁ ልብ ግዙና ለመከረኛው ወገናችሁ የምትችሉትን ፈጥናችሁ አድርጉ!

እውነተኛው አምላክ የሚገኘው በእንዲህ አይነቱ የቅድሚያ ቅድሚያን ግድ በሚል የወገን ለወገን ርብርብ ውስጥ እንጅ የመከረኛውን ህዝብ የሰቆቃ ጩኸት እንደ ቁራ ጩኸት እየቆጠሩ እና የዳያስፖራን ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ህፀፆች በእጅጉ እያጋነኑ ባህር ማዶ በሚያስገነቡት ዘመናዊ ገዳም ውስጥ ፈፅሞ አይደለም! አይሆንምም!!!

በማቴዎስ ወንጌል እንደተፃፈው ክርስቶስ ብራብ አበላችሁኝን? ብጠማ አጠጠችሁኝን? ብታረዝ አለበሳችሁኝን? ብታሠር ጠየቃችሁኝን? እንግዳ ሆኘስ አስተናገዳችሁኝን በሚሉ መሠረታዊና የቅድሚያ ቅድሚያን አስፈላጊነት በሚያሳዩ ጥያቄዎች አይደለም እንዴ ተከታዮቹን ያስተማረው?

መቼና የት ተርበህ፣ ተጠምተህ፣ ታርዘህ፣ ታመህ እና ታሥረህ አየንህና ነው? ብለው ሲጠይቁትስ እውነት እውነት እላችኋለሁ በሚል ሃይለ ቃል ለሌሎች ማለትም ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙት፣ ለታመሙት እና ለታሠሩት ምስኪን ወገኖች  የምናደርገው ሁሉ ለእርሱ የሚደረግ እንደሆነ ነገረን (አስተማረን) እንጅ  የመከረኛ ወገናችን ሸክም በስሙና ለስሙ በሚሠራ (በሚገደም ገዳም) መታደግ እንደሚቻለን አልነገረንም፤ አላስተማረንምም።

እናም አገርና ወገን ለማመን ቀርቶ ለማሰብም በእጅጉ በሚከብድ (በሚዘገንን) ሁኔታ ውስጥ በሚገኙበት መሪር ሁኔታ ውስጥ የቅድሚያ ቅድሚያ ሃላፊነትንና የውዴታ ግታን በአፍ  ጢሙ ደፍቶ እጅግ በተሻለ የዓለም ክፍል የሚኖረውን ዳያስፖራ ማህበራዊና ሌሎች ችግሮችን እያጦዙ በማጋነን “ለባህር ማዶ ዘመናዊ ገዳም ማሰሪያ ያላችሁን ሳንቲም ሁሉ ካላረገፋችሁ በረከቱ ቀረባችሁ ፤  እኛም በወረፋ እየተኛን እንቀጥላለን እንጅ አንላቀቅም” የሚል ዘመቻ ከእውነተኛው አምላክ ፍላጎትና ፈቃድ ጋር ጨርሶ ግንኙነት የለውምና ልብ ያለው ልብ ይበል!!!

3 Comments

 1. Igziabher yefeqedewun indiseru beselam metew yishalal.
  YmiseT yisT. Just because they have this fundraiser, they are not taking away from other fundraising efforts. There are so many other fundraising efforts and you do not see people giving.
  There are very reliable media outlets that are dying out for luck of public support. The public is not giving donations to any of the realy needy IDP projects for luck of trust and awareness. The Government has been exposed stealing international food aid and monetary donations. They also block any direct donation to the victims like they did in Borena, Debre Birhan and Chagni, Metekel. Where are good hearted people to donate if they want to help the people and not fatten abiy Ahmed’s (EPRDF’s) caderes?

  People gave money to the Fight-genocide cause. Money was placed in a trap and did not get used for the purpose of bringing Abiy Ahmed and collaborators to justice.
  People also gave money to rehabilitation efforts for Amhara, Afar and Tigray regions. Nothing to show.
  Also there is a great need here in America for the proper education Ethiopian children. In Ethiopia, there has been a severe curtailment of spiritual, historical and cultural education. Kids are not even free to express pride in their flag.

  Honestly, had the clergy had the well-being of the children of the faithful in their heart, such a hard-push fundraiser would not even have been needed. They could have used the structure of the church to close the 5 million gap over just one weekend. Unfortunately, the majority Orthodox clergy today do not have the church and the faithful at their heart but their own comfort. The rest of the clergy are so ignorant about global events, trends and movements as well as the challenges of raising children in today’s world, it is hard to blame them.

  igziabher yameleketachewun sira yisru teyachew ihit alem. Ager bet ballew gudayima yezemenachin kahinat andim sayqeru yemiTeyequbet new. Libona yisTachew.

 2. ትክክለኛ ሀሳብህ ግልጽ አይደለም በማንኛውም ፕሮሞሽን እንደሚደረገው እሸቱ አንዳንድ ማነቃቂያ ቃላቶችን ተጠቅምዋል ያ ስህተትም ማታለልም አይደለም። ሀገር ውስጥ የትግሬ ወራሪ ከአክራሪ እስላሞችና አክራሪ ጴንጤዎች ጋር በመናበብ ቤተ ክርስቲያንን ሲያቃጥል ምእመኑን ሲያርድ በውጭ ሀገር ለሚኖረው ክርስትያን ለነብሱና ለስጋው ማደሪያ ገዳም ማሰራቱ ለምን እንዳስወቀሰው ግልጽ አይደለም። እሸቱ በስራው ሁሉ ሀይማኖቱንና ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ነው። እንዲህ ያለ ሀሳብ ያልሆነ ሀሳብ እየላኩ አንባቢን ማሰልቸት መልካም አይሆንም ከመጽሀፉም የጠቀስከው አንተን የሚደግፍ አይሆንም። ስንት የሚተቹ ሀሳቦች ባሉበት ሀገር ፍላጻህ ወደ እሸቱ መወርወሩ ከጀርባው ምን ይዞ እንደመጣ ሊያስጠርጥሩን የሚችሉ ሀሳቦች ቢኖሩም መተውን መርጠናል። ባጠቃላይ እስከ አሁን በሚሰራው ስራ ግድፈት አላየንበትምና ማሰናከሉን ተወው። እሱን ለመተቸት ከሱ በላይ ሰርቶ ማሳየትን ይጠይቃል። አእምሮህ ሰላም እንዲያገኝ እየተመኘን በዚሁ እንሰናበት።

 3. በካሊፎርኒያ ለሚሠራው ገዳም ለቀረበው ነጻ አስተያየት ማስተካከያ። ለገዳም አሻራ ካላስቀመጣችሁ አትጸድቁም እተባለ የማስፈራሪያ ስብከት የሚሰበከው፣ በተለያየ መልኩ የሚሰበሰበው ገንዘብ በባንክ ሳይሆን ከአምስት እስከ አስር አመት መከፈል ያለበት ተጨማሪ ክፍያዎችን ሳይጨምር ስምንት ሚሊዮን ዶላር የመሬቱ መግዣ ሲሆን የአመት ወለድም ስድስት መቶ ሺህ በመሆኑ ይህ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ በምዕመናኑ ላይ በአባቶች በኩል ዶንኪ በተባለው ፈስ ቡክም ሆን በሌላ የግዘታ ዘመቻ እየተደረገ ያለው። በነገራችን ላይ ጽድቅም ሆነ ኩነኔ የሚገኘው ለካሊፎርኒያ ገዳም ማሰሪያ ወይም መሬት መግዣ በመስጠትና ባለምስጠት አይደለም።ጽድቅንም ሆነ ኩነኔን ሰጬ እና ነፋጊው እንደሥራው እግዚአብሔር ብቻ ሲሆን ከላይ እንደተጠቀሰው ወድ ወገኖቻችን በርሃብ ለሚያልቁ ወገኖቻችን ቅድሚያ መስጠቱ ተገቢ ነበር።በተጨማሪ ይህ የመሬቱ መግዣ ተሰብስቦ ከተጠናቀቀ በኋላ ዲያስፖራው የማሰሪያንውንም ጓዳው ወይም ማጀቱ መቦርቦሩ አይቀሬ ነው። እንደሚገባኝ ገዳም ዓለም በቃኝ በለው መናንያን በጸሎት እና በንስሃ የሚኖሩበት ይመስለኛል። ተዲያ ይህ ገዳም የተባለው መናንያን ዲአስፖራ አለን? መልሱ በአሚሪካ በተለያዩ እስቴቶች ያሉ ሊቃነ ካህናትን፣መነኮሳትን ሊቃነ ጳጳሳትን እና የተለያዩ አድባራት አስተዳዳሪዎችን ሳያማክሩ ያለ እውቀት በራስ ፈቃድ ስምን ለማስጠራት ጀብደኛ መነኩሴ ወይ ጳጳስ መልስ ይስጡበት። በተጨማሪ እንደታሪኩ ይህ ቦታ ከሉስ አንጀለስ ያራት ሰዓት
  የመኪና መንገድ ያለው እርቀት ሲሆን በጣም ተራራማ እና ሞቃት በመሆኑ የሰው ልጅ ማረፊያ ጥላ የለውም ይባላል።በመሆኑም ጸሐፊው መልካም ማንቂያ ጽሁፍ ጽፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

184068
Previous Story

ከባድ ትንቅንቅ!! ቆቦ፣ ሮቢት አራዱም፣ ዞብል!! “ዙ 23 ወድሟል”| የአማራ ድምጽ ዜና | The Voice of Amhara

Amhara
Next Story

ባለሁለት እግሩን አሳማና የአማራው ተጋድሎ – እውነቱ ቢሆን 

Go toTop