July 16, 2023
14 mins read

የኢትዮጽያ ፊደል ብቃትና ጥራት – ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ

ጽሑፉ፣ አንድ ሞሪ (Mori) የተባሉ አንባቢ [የብዕር ስማቸው ሊሆን ይችላል]፣ በተጠቀሰው መጣጥፌ ላይ ላደረጉት ኂስ (ወይንም ስድብ) የተሰጠ መልስ

 

በመጨረሻ ላነሣ የምፈልገው እርስዎ በንቀት አቡጊዳ የሚሉትን የአማርኛ ፊደል ነው። ላቲን ይበልጣል ማለትዎ ብቻ የሚያረካ መልስ ሊሆን አይችልም። ከላቲን በምን መልክ እንደሚተናነስም ከነማስረጃው ማቅረብ ይጠበቅብዎታል። ባያውቁት ይሆናል እንጂ፣ የላቲን ፊደል ራሱ ምንጩ ከአፍሪቃ ነው። ላቲንንም እንደቋንቋ እንዲገንን ያደረጉት የአፍሪቃ ጸሓፊዎች ናቸው። አዲስ ኪዳን ሲጻፍ፣ ሮማውያን የአይሁድን አገር ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን ዓለም ይገዙ ነበር። ግን እነሱ ገዢዎች ቢሆኑም፣ በላቲን ቋንቋቸው የተጻፈ የክርስቲያኖች ቅዱስ መጽሐፍ የለም። ክርስቶስ በዘመናቸውና በግዛታቸው ሥር ኖረ ቢባልም፣ አዲስ ኪዳን ግን በቋንቋቸው አልተጻፈም። ታዲያ የተጻፈው በአረማይስጥና ዓለም ይናገር በነበረው፣ ግን በሮማዉያን ሥር በነበሩት፣ በግሪኮች ቋንቋ ነው። ታላላቆቹ የአፍሪቃ ሊቃውንት እንደነጠርጡሊያኖስ፣ እንደነአውጉስጢኖስ ያሉት ናቸው እንግዴህ፣ ላቲንን በኋላ ለክብርና ለማዕርግ ያበቁት።

 

የአማርኛ ፊደል፣ ከማንኛውም አሁን በዓለም ላይ ካሉት ፊደላት እንደሚሻል በምንም መልክ አያጠራጥርም። ይኸንንም “ከታሪክ መዝገብ፣ ለመሆኑ አማራ ማነው” በሚለው ጽሑፌ አሳይቻለሁ [ጽሑፉን እዚህ https://www.academia.edu/50156528 ላይ ሊያነቡት ይችላሉ]።  ቫወል እያሉ በሁለት ፊደል ከመጻፍ፣ ባንድ ፊደል መገላገሉ እንደሚሻል፣ ዓለም በሙሉ ያውቃል። የተጻፈውን ፊደል አለአገባቡ ከማንበብ፣ እንደተጻፈው ማንበቡ እንደሚበልጥም በዚሁ ጽሑፌ አስረድቻለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ይኸንን ወደር የሌለውን የጥቊር ሕዝብ ፈጠራ መጠቀም ከብሔራዊ ክብርና ኩራት የተያያዘ እንደሆነ መረሳት የለበትም። በፊደል ብዛት የሺኖች (ቻይናውያን) ከማንም ይበልጣል። ሲቀለድ እንኳን ሺኖች ፊደላቸውን ሕይወታቸውን በሙሉ አጥንተው ሳይጨርሱት ነው የሚሞቱ ይባላል። በአውሮጳ ተማሪ ሳለሁ፣ መደጐሚያዬ በትርፍ ጊዜዬ አስተምር ከነበርሁት የቋንቋ ትምህርት ነበር። የክፍያው ልክ በቋንቋው አስቸጋሪነት መጠን ስለነበር፣ ከሁላችንም ዕጥፍ የሚያገኝ የነበረው የሺኑ አስተማሪ ነበርና በጣም እቀናበት ነበር። ታዲያ፣ ይኸንን ያነሣሁልዎት አንድ ነገር ላሳስብዎት ነው። በቅርብ ጊዜ የአውሮጳ ጋዜጠኞች የጃፓንን መሪ፣ ለምን አገርዎ ውስብስቡንና አስቸጋሪውን የሺንን ፊደል ትቶ፣ ቀላሉንንና ለሥራ ቀልጣፋ የሆነውን የላቲንን ፊደል አይጠቀምም ብለው ሲጠይቋቸው የሰጡት መልስ፣ “የሺን ፊደል አስቸጋሪ መሆኑ ጠፍቶብን አይደለም፤ በደምብ እናውቃለን። ግን ሺን የእስያ ሥልጣኔ ነው፤ ጃፓንም የእስያ አካል ናት። ስለዚህ እኛም እስያውያን እንደመሆናችን የእስያን ሥልጣኔ ፍሬ እንጂ የአውሮጳውያኑን የምንጠቀምበት ምክንያት አይታየኝም” የሚል ነበር።

 

እንደርስዎ ያለ ግን ወደመቶ ሠላሳ ዓመታት ገደማ፣ ባገኙት በዘመናዊ መሣርያ ኀይል ከሰው ዘር በሙሉ የበላይ ነን በማለት በድፍኑ ዓለም እንደልባቸው እየፈነጩ፣ ነጭ ያልሆነውን የሰውን ዘር ያተራምሱ በነበሩበት ጊዜ፣ እርስዎን የመሰለውን ጥቁር ሕዝብ በሙሉ፣ “ከዝንጀሮ” የማይሻሉ ፍጥረት ናቸው፤ ለሰው ዘር ሥልጣኔ ያደረጉት ምንም ዐይነት አስተዋፅዖ የለምና መጥፋት ያለባቸው የጐሦች ጥርቅምቅም ናቸው፣” ይሉ የነበሩትን ነጮች ከሚያደንቁት ጥቁሮች አንዱ ይመስሉኛል። “ላም ካራጇ ጋር ትውላለች” የሚለው ያገራችን ተረት ለርስዎ ዐይነቱ የተተረተ ይመስለኛል። የጃፓኑ መሪ ግን ይኸንን ታሪክ አብጠርጥረው ስለሚያውቁና፣ የሳቸውም አገር የነጮች ዕብሪትና ምንአለብኝነት ሰለባ እንደነበረች ስለተማሩ፣ የበቀል ስሜት ሳያሳዩ፣ ለጠያቂዎቻቸው ለአውሮጳውያን ጋዜጠኞች፣ በጣም ጨዋ መልስ ነው የሰጧቸው። ከነቃና ከተማረ የሚጠበቀውም ይኸ ዐይነት ተግባር ነው።

 

እርስዎም በጥቁርነትዎ ክብርና ኩራት እንደሚሰማዎት አልጠራጠርም። በአገርዎና በሕዝብዎ ግን የሚኰሩ አይመስለኝም። እንግዴህ ነጮች ጥቁሮች አፍሪቃውያንን፣ ጊዜአቸው ያለፈባቸው የጐሦች ጥርቅምቅም እንጂ ሕዝብ ስላልሆኑ፣ ቀይ ህንዶች የሚባሉትን የአሜሪቃን ተወላጆች እንዳወደሙ፣ አፍሪቃውያንንም አጥፍተው በነጭ ሕዝብ ለመተካት ሲሉ ነው ክፍለ አገሩን በሙሉ የቅኝ ግዛት ያደረጉት። ዓላማቸውን ያከሸፈችባቸው ኢትዮጵያ በልጆቿ የተባበረ ክንድ በአድዋ ላይ በተጐናፀፈችው ድል ነው። ያሸነፈችውም እንደሌላው የአፍሪቃ አገሮች በጐሣ ጥርቅምቅም ጦር ሁና ተዋግታ አይደለም። ሁሉም ተባብረው በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ባንድ መሪና ሰንደቅ ዓላማ ሥር ተሰልፈው፣ እንዳንድ አገርና ሕዝብ በመዋጋት ነው። እንደሌሎቹ አፍሪቃውያን እያንዳንዱ ጐሣ በተናጠል ቢዋጋ ኖሮማ፣ የኢትዮጵያም ዕጣ የመላዪቷ አፍሪቃ በሆነ። የጐሣና ያንድ አካባቢ ጦር ዋጋቢስ መሆኑን በትግራይ መሪዎች ታይቷል። አንድ ጭብጥ የማይሞላ የኢጣልያን ጦር፣ በጣም ዘመናዊ የተባለውን የራስ መንገሻ ዮሐንስን ሠራዊት ባንዳፍታ ድምጥማጡን አጠፋው። የኢጣሊያኑ ጦር በዚህ ቀላል ድል ልቡ ደንድኖ፣ የኢትዮጵያም ብሔራዊ ሠራዊትም ቢመጣብኝ፣ ጽዋው ከዚያ የከፋ ይሆናል ብሎ እየደነፋ ቢቈይ፣ በመጨረሻ ላይ ቊርሱ ለመሆን እንኳን አልበቃም። የሞት ሽረት ፍልሚያ ቢገጥምም፣ ከዚያ የሚደነቀውን የክልል ሠራዊት ኢምንት ካደረገው የጠላት ጦር አንድም ሳይቀር ተደመሰሰ። አንድነታቸው እትዮጵያውያንን አኰራ፤ ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ በዳርዊን የዘገም ለውጥ ሂደት እምነቱን ጥሎ፣ የላዕላይነት ስሜት በማራጋብ ጥቊርን ከአፍሪቃ ገጸ ምድር ሊደመስስ ያልም የነበረው የነጭ ዘር ቅዠት በነነ። አፍሪቃ ከጥፋት ዳነች፤ ኢትዮጵያም አለኝታዋና የነፃነት ተስፋዋ ጭላንጭል፣ የድሏ ዐረቦን ሆነች። ድሉ በእውነት፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ነጭ ያልሆነ የድፍኑ ዓለም ሕዝብ ሁሉ አርኬሳ ነበር።

 

አሜሪቃ የነጮች ሰለባ ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ተሸንፎ የማያውቀው የነጮች የቅኝ ግዛት ጦር፣ አውሮጳዊ ባልሆነ ሕዝብ ለመጀመርያ ጊዜ በማያዳግም መልኩ ድል የሆነው በኢትዮጵያ ብቻ ነው። ቀጥላ ጃፓን ደገመችው። የእንደዚህ ዐይነት አስደናቂ ድል ፊታውራሪዎች እንደመሆናችን፣ በዚህ መኩራት አለብን። ይበልጥ ደግሞ የምንኰራው ሕዝቡን የሚያስተባብር ቋንቋ ባይኖር፣ የኢትዮጵያም ድል አጠያያቂ ሁኖ በቀረ። ስለዚህ የአማርኛ ፊደል የአንድነታችን መግለጫ፣ የሥልጣኔአችን መለዮ፣ የታሪካችን ኩራት፣ የምንነታችን ክብር ነው። እንደሺኖች ፊደላት አስቸጋሪ አይደለም። እንደሮማውያን ደግሞ ከሌሎች አልተበደርንም። ጽሑፌ ሊያስረዳዎት የሞከረው እንግዴህ፣ ለዕድገቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋፅዖ ያደረገበት አገርበቀል ፊደል ስለሆነ፣ ካስፈለገ አሻሽለነው መጠቀም አለብን እንጂ መናቅ የለብንም ነው። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ የመላ አፍሪቃ ሀብት ነው። ስለዚህም ነው እርስዎና እንደርስዎ የመሰሉት የጐሣ ታሪክ አቀንቃኞች ለነጭ ፊደል ሲያጐበጉቡ፣ ንቃት ያለው እንደአኃዜ ኲሉ አፍሪቃ [ፓናፍሪቻኒዝም] ገናናው የጋና መሪ ንክሩማ መሰሎች፣ ከዋና ዕቅዶቻቸው ከነበሩት አንዱ የአማርኛን ፊደል በመላ ጥቊር አፍሪቃ እንዲሰራጭና እንዲጠቀም የፈለጉት። የሥልጣናቸው ዘመን ባጭሩ ባይቀጭ ኖሮ፣ ፍላጎታቸውን በግብር እንደሚተረጒሙ አልጠራጠርም።

 

ከጽሑፍዎ እንደምረዳ ከሆነ፣ እርስዎ እንደጐረቤቶቻችን እንደኤርትራ መሪዎች፣ ትላንት ከአውሬ እንጂ ከሰው የማይቈጥርዎት የነበረውን ነጭ እንደሚያመልኩ፣ ግን ከነጭ ጨቋኝ እጅ ታድጋዎት ለወግና ለማዕረግ ያበቃችዎትን አገርዎን ኢትዮጵያን እንደጨቋኝ በመቊጠር እንደሚሳደቡና እንደሚያዋርዱ ነው። ተረት የሚባለው እንደዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ እንጂ፣ በሐቅ ላይ የተመሠረተ የኔ ትንተና አይደለም። ሮም አውሮጳውያንን ከአረመኔነት አወጥታ ለሥልጣኔ እንዳበቃቻቸው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ከሮም በምንም መልኩ በማያንስ ሥልጣኔዋ፣ አብዛኛውን ሕዝብ ለታላቅ ሥልጣኔ አብቅታለች። በእረኝነት እርስ በርሱ ይፋጅ የነበረውን የጐሦች ጥርቅምቅም፣ በማእከላዊ መንግሥት ሥር አደራጅታ፣ ለታላቅ ማዕርግና ወግ እንዲደርሱ አድርጋለች። እንደዚህ ዐይነቱን እውነት የጐሣ ሥርዐት አራማጆች ሊውጡት የማይፈልጉት፣ ሊናገሩት የማይወዱት ሐቅ ነው። ግን ምን ይደረግ። ከመጮህና ከመሳደብ ውጭ ሌላ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር የለም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop