July 16, 2023
30 mins read

ኦሮ-ትርያ – አስቻለው ከበደ አበበ _ሜትሮ ቫነኩቨር ካናዳ

በሃገራችን ውስጥ ብዙ ብሔሮችና ብዙ ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ የዲ.ኤን.ኤ(ዘረመል) ቋቱ ሲጠቃለል ግን ጥቂት ነው፡፡ ሲጠናና ሲመረመር፣ ዛሬ ብሔር ነን ብለው በቋንቋ መስመር ላይ እራሳቸውን አስምረው እርስ በእርስ የሚዋጉት ሁሉ እንድ ህዝብ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ለነገሩ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦችስ ከመተላለቅ ማን አገዳቸውና? ሱማሊያ አንድ ቋንቋ ተናጋሪና አንድ አይነት እምነት ተከታይ ህዝቦች ናቸው፡፡ ዛሬ የት አሉ? የኤርትራ ትግሬና የኢትዮጵያ ትግሬዎችስ መች ተላቀቁና፡፡ በሃያ አምስት አመት ውስጥ በኤርትራና ትግራይ፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስንት ህይወት ጠፋ?

ዛሬ ላይ በለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት ከሐይማኖት በላይ የሆነው ኦሮሙማ፣ ለኢትዮጵያውያን በተለይም ለኦሮሞው ጠቅላላ የጥፋት ድግስ ይዞ ሲጓዝ ይስተዋላል፡፡ በካፈርኩ አይመልሰኝ መርሆ የሚጓዘው የኦህዴድ(ኦዴፓ)- ብልጽግናም ጫንቃውን አጉብጦ ለሚገዛው ህዝብ የሚያበላው ሲያጣ እለት እለት ልዩ ልዩ አጀንዳ በመስጠትና ህለውናው ላይ ክፉ ጥላን በማጥላት ርሃቡን ለማስረሳት ሲተጋ እናየዋለን፡፡

ታላቁ የቻይና ፈላስፋ ኮንፊሸስ እንዲህ ብሎ ነበር “ጥሩ አሰተዳደር ባለበት ሃገር ድህነት  በእራሱ ውርደት ነው፡፡” በምርቃና ውስጥ የሚኖረው ኦህዴድ -ብልጽግና ረሃብ የሚያሰከትለውን ጥያቄ ለማሰቀረት ህዝብን ማተራመስ ሆኗል መልሱ፡፡

የኦሮሙማ መሪዎች በአለም አቀፍ ዲፐሎማሲ መስክ የህጻን ልጅ ጨዋታ ሲጫወቱ ነው የሚሰተዋሉት፡፡ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የነቀዘ የፈረንጆቹን ስንዴ አንፈልግም አሉ፡፡ ወደ አሜሪካና አውሮፓ መጓዝ እንደማይፈልጉም በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጉዞ ማዕቀብ ሊደረግ ነው ሲባል ተናገሩ፡፡ ወቼ ጉድ ለተራበው ህዝቤ ስንዴ ስጡኛ ብሎ የሚለምን መሪ፣ የነቀዘ ስንዴቸውን አልፈልግም ሲል አይገርምም? ስለምነተማሪያም ብሎ እበርህ ላይ ለልመና የቆመ ሰው፣ አይ የማሽላም ሆነ የገብሰኛ ጤፍ እንጀራ አልፈልገም ትኩሱን የማኛ ጤፉን አምጣ ብሎ ቢናገርህ እንደ ማለት ነው፡፡

ሟቹ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን የሚያግድበት ህግ ሲያወጡ፣ እርዳታው ሁሉ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ስር ሊሆን ነው የሚል መነሻ ይዘው ነበር፡፡ የምርአባውያኑ እርዳታንም * ከፈለጉ ኋላ ኪሳቸው ውስጥ ይጨምሩት* ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ያው ኋላ ኪሳቸው…ማለት መቀመጫቸው ውስጥ ይጨምሩት እንደማለት ነው፡፡ ይህን ሲሉ ግን ከ1998 ዓ.ም. በኃላ ሶማሌ ውስጥ ጦር አዝምተው የውክልና ውጊያውን አጧጥፎላቸው ስለነበር ሚዛኑን ጠብቀው መሄድ ችለው ነበር፡፡

ታዲያ የብልጽግናው ኦሮሙማ ፕሮጀክት በ””ልዋጥህ ተደበልበል” መርሆው ትዕቢት በታከለበት ሁኔታ ኦሮሞው ላይ ዙሪያ ገብ ጦርነት ሊያሰከፍትበት ተነስቷል፡፡ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ህዝቦች( አማራ፣ ጉራጌ፣ወላይታ፣ጋሞ፣ ሱማሌ፣ሲዳማ፣ አፋር…) ከኦሮሞ ፖለቲካ ጋር ያለቸውን የፍረሃትና እራስን መጠበቂያና መከላከያ ርቀት(Flight Distance) የኦሮሞ ፖለቲከኞች በመጣስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ለዝሆንና እባብ የሰው ልጅ ምግባቸው አይደለም ግን የሰው ልጅን ለምን ያጠቃሉ? ሁሉም ራስን የመጠበቂያ የደህንነት ርቀት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ያ ርቀት 100 ሜ. ቢሆን ከ100ሜ. ርቀት በላይ ከሰው ጋር ቢገናኙ ሰው ያጠቃናል ብለው ስለማያስቡ ዝም ብለው ጉዛቸውን ይቀጥላሉ ወይንም ይሸሻሉ፡፡ ከዚያ ርቀት ባጠረ ርቀት ላይ ሰውን ቢያገኙ ግን ሳይቀድመኝ ልቅደመው በሚል ደመነፍስ ሰውን ያጠቃሉ፡፡

አውራ ፓርቲ ፈጣሪው የብልጽግና ኦሮሙማ ይህን የህዝቦች የደህንነት መስመር በተደጋጋሚ ሲጥስ ይሰተዋላል፡፡ የራሱን ክልል ልዩ ሃይል እያጠናከረ የሌሎች ክልሎችን ልዩ ኃይል በማፍረስ የመተማመን ግነቡን እያፈረሰ ይገኛል፡፡ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦችን ለመምታት ቃላት ፈጥሮ ታርጋ በመለጠፍ ተክኖበታል፡፡ ባለፈው ሰሞን ጁንታ ጁንታ ሲጫወት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ጽነፈኛ የሚለውን ቃል ፈጥሯል፡፡ ወለፈንዴና የሩቁን ማየት በተሳነው ዳፍንታም ርዕዮቱ ምስራቅ አፍሪካን ሊያምሳት ተነስቷል፡፡ የስንት ሚሊዮን ህዝብ የደም ግብር ለፖለቲካ ዛሩ በቂ እንደሆነም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

ሁል ግዜ አንደኞቹ

አሁን በህይወት ያሉት የቀድሞው ጠ/ሚ ታምራት ላይኔ ያኔ መለስ ወደ ወህይኒ በወረወራቸው ግዜ ብዙ ገጽ ደብዳቤ ለመንግስት ጽፈው ለማንብብ ታድዬ ነበር፡፡ በኮሚኒስቱ ርዕዮት እሰቤ በሂስቶሪካል ማቴሪሊዝምና ዳይሌክቲካል ማቴሪሊዝም ሃሳቦች የተሟሸ ደብዳቢያቸው፣ በሽረት ሽረት ትግል ጽንሰ ሃሳብ የነመለስ ስልጣ እንደሚያበቃ አጽዕኖት ሰጥቶ ያትታል፡፡ የሚገረመው ነገር አልበርት አንስታይን ሁሉ ጠቅሰው መጻፈቸው ነበር፡፡

ታዲይ እኚህ ሰው እስርቤት ውስጥ በፓስተር በቀለ ወ/ኪዳን በኩል ጌታን ተቀበሉና ክርስቲያን ሆኑ ተባለ፡፡ ሱማሌ ሄደው እዚህ ከክልሉ ውጭ የተገኘ አማራ ዳግመኛ ሽርጣም አይላችሁም ብለው የምስራቅ ኢትዮጵያን ህዝብ በማነሳሳት ለብዙ አማሮች ሞት ምክነያት የሆኑ ሰው ነበሩ፡፡ ከአስራ ሁለት አመት እስር በኋላ ከእስር ሲወጡ ሰባኪ ሆኜ ልረፍ አሉ፡፡ የጥሞና ግዜም አላሰፈለጋቸውም፡፡ ሁልግዜ አንደኛ ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ ሰው ግደሉም ለማለት አንደኞች፡፡ ክርሰቶስ በርቶልኛል ቃሌን ሰሙኝ ደግሞም ተከተሉኝ ለማለት እንዲሁ አንደኞች ናቸው፡፡

አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ አበባ መጥተው ሹመት ያደብርልህ በተባሉበት ያን ሰሞን፣ የሳቸውን ንግግር ላይ ተሰይመው የነበሩትን የጠ/ሚ አብይ ፊት ላይ አጃይብ የሚያሰኝ ነገር ተመልክተናል፣ ከነባለቤታቸው በፈገግታ ተሞለተው ነበር፡፡

መቼም ከሁለት አመት በፊት ጦርነቱን ከሴቹዮሽን ሩም የመረቱ እሳቸው አይመስሉም ነበር፡፡ ያ ሁሉ የጀናሎች ምስጋና ጋጋታ ተከትሎ የመጣው የደቡብ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሸዋና አፋር ውድመት የምርቃና ላይ ሲሳይ ነበር፡፡ ጁንታው፣ጁንታው … ተባለ፡፡ አሁን ደግሞ የፕሪቶሪያ ስምምነት ተብሎ ኦቦ ሽመልስ ድቄት የሆኑት ሰፈር ሄደው መቀሌ ላይ ሹፌር ሆኑ፡፡

የሚገርመው ነገር ጠ/ሚሩ ሁሉ ቦታ ላይ አንደኛ ሆነው የመገኘታቸው ነገር ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በጦርነቱ ከለቀ በኋላ ምነም እንዳልተፈጠረ የሰላም ግዜ ፈገግታ ያሰዩናል፡፡ እንዴት አንድ ሰው በጦርነትም ግዜ ዋና መሪ፣ የሰላሙም ግዜ ዋና መሪ፣ ሰባኪም፣ በሁሉ መድረክ ላይ ተንታኝና አስተማሪ(ያውም ያለ ሙያው ጥልቅ እያለ) ሁሉን አዋቂ(The know all) አድርጎ እራሱን ያቀርባል? ይህ በሽታ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል? በዙሪያቸው ያሉት ከፍርሃትም ሆነ ከጭፍን ድጋፍ የተነሳ ዝም ቢሏቸውም መጨረሻው ግን አሁን በዚህ ሰሞን በፓሪሱ ጉባኤ ላይ የታየውን የጠ/ሚ የከፍታ መጨረሻን(ውርደት) እንደ ሃገር ማስተናገድ ነው፡፡

 

ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት

መቼም የአሜሪካ ፕሬዚደንቶች አጃይብ የሚያሰኝ አቋም በኢትዮጵያ ላይ ሲያካሂዱ ከርመዋል፡፡ ከባራክ ሁሴን ኦባማ ልጀምር፡፡ እኚህ ሰው ኢትዮጵያ ለጉብኝት በመጡበት ግዜ እንደእኔ ያሉ በዲሞክራሲ የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ ፀረ ዲሞክራሲ የነበረውን ወያኔን  አንድ ነገር ይሉልናል የሚል ከፍተኛ እምነት ነበረን፡፡ እሳቸው ግን 99% የፓርላማውን መቀመጫን ጠቅልሎ የያዘውን ወያኔ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው ብለው አረፉ፡፡

ባራክ ኦባማ፣ በእሳቸው ዘመን የሊቢያው መሪ ከተወገደ በኋላና ሊቢያውያን ያገኙት የነበረው መንግስታዊ ድጋፍ ላይመለስ ካጡት በኋላ የፕሬዝድነታቸውን ዘመን ጨረሱ፡፡ አሁን ላይ ሲጠየቁ የሚቆጫቸው ነገር በስልጣን ዘመናቸው ሊቢያ ላይ እጃቸውን ማስገባታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይገርማል በሚሊዮን የሚቆጠር ሊቢያውያን ህይወታቸው ከታመሰ በኋላ መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡ የኛ ህይወት ለቀጣይ ዘመናት ይታመሳል እነርሱ ደግሞ ጸጉራቸውን እያከኩ ትንሽ የሚቆጨኝ ነገር እያሉ ሪፖርት ያደርጉናል ማለት ይህ ነው፡፡

የሳቸው ቀደም በነበሩት ቢል ክሊንተን ዘመን ኢትዮጵያ ላይ የተሸረበ ትልቅ ሴራ(?) ነበር፡፡ ግሬት ሆርን እኒሼቲቭ በሚል የምስራቅ አፍሪካ ሃገሮችን የተመለከተ አንድ ፕሮጀክት ነበራቸው፡፡ በግዜው ለአሜሪካውያኑ የአፍሪካ ወኪል ሆኖ ያገለግል የነበረው የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዮሪ ሞሶቮኒ ነበር፡፡ እሱም አፍሪካን በስድስት ግዛት የሚከፍል ካርታ አዘጋጀ፡፡

እነ ኡጋንዳ፣ኬኒያ፣ ሩወንዳ፣ታንዛኒ፣ብሩንዲ የሚገኙበት ሰዋዋህሊ ሪፓብሊክ ብሎ ሲሰይም፣ ኢትዮጵያ፣ኤርትርያ፣ ጅቡቲና ሱማሌን አደባልቆ ኤርትሮሚ የሚል ሃገር ፈጠረ፡፡ በግዜው ኤርትራ ከወያኔ ጋር ስምም የነበረችበትና ብቅ ብቅ እያለች ያለችበት ግዜ ነበር፡፡

ዋናው ነገር እዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚለው ነባር የአፍሪካውያን መከታ የሆነ ስም ተሸሮ ገና አዲስ በተፈጠረችው ሃገር ኤርትራና አዲሰ ኢትዮጵያው ውስጥ በተፈጠረው ክልል ኦሮሚያን አጣምሮ የተተካ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ዛሬ ላለው የኦሮሙማ ቅዠት መነሻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በኋላ ግዜ መለስ ዜናዊ ኦሮሞ ከፈለገና ከቆረጠ ማን ይችለዋል እንኳን ኢትዮጵያን አፍሪካንም…ብሎ አረፈ፡፡ ጮሌው መለስ ያን የተናገረው ለፖለቲካ ፍጆታ እንጂ ወያኔ ለኦሮሞው የነበረው አመለካከት በአባይ ፀሐዬ እንደተነገረው ልክ እናሰገባቸዋለን…የሚለው አይነት ነበር፡፡

መካሪ ያጣው ኦሮሙማ መተማን ሞቱማ ነው፡፡ አሰመራ ፣መቀሌ፣አዲግራት፣ አክሱም ሁሉ የኦሮሞ ቃላት ናቸው ሲል ከርሞ አሁን ደግሞ ወደ አሰብ ብቅ ብሏል፡፡ እንግዲህ ወደብ አሰፈላጊም አይደል? ግድ ይላል፡፡ የኢሊባቡሩንና ክብረመንግሰቱን “ቡሬ” ከተሞች  ከአሰብ ቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው ቡሬ ጋር አያዞ አሰብን የኦሮሞ ግዛት ነበር ማለት ጀምሯል፡፡

ፋዘረ ጀሮም ሎቤ በቀይ ባህር ዳርቻ በሉባ ህግ የሚተዳደሩ ኦሮሞዎችን አየሁ ብሎ የጻፈውን ታሪክ የሚጠቅሱም ተነስተዋል፡፡ ፋዘር ጀሮም ከሦስት መቶ ሃምሳ አመት በፊት በ17ኛው ክ/ዘ በጎንደር የኖረ ጀዝዊት ሚሽነሪ ሲሆን በአፄ ሶሶኒዎስ ግዜ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ እመነትን ወደ ካቶሊክነት ለመቀየር ከሞከሩት አንዱ ነው፡፡

A Voyage to Abyssinia (ኤ ቮዬጅ ቱ አቢስንያ) በሚለው ጽሑፉ በቀይ ባህር ዳርቻ ስላገኛቸው ሁለት ሺህ አካባቢ የሚሆኑ ኦሮሞች ጽፏል፡፡ግን በመልካም ገጽታ አደለም ያነሳቸው፡፡ ፍጹም ባርባሪያን፣ ህጻን ሽማግሌ ሳይለዩ የሚገድሉ አድርጎ ነው የገለጻቸው፡፡ ፋዘር ጅሮም ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ህዝቦች ስልጡንነት ሲገልጽ፣ አማራ በጣም ትሁትና እጅግ ስልጡን፣ ትግሬ የሰለጠነ፣ አገውና ዳሞቶችን ስልጣኔ የነካካቸው አድርጎ ነው የሚገልጸው፡፡ አሰብን ፍለጋ ሲኬድ ታዲያ ይህን ሰው መጥቀስ ምን ይጠቅማል? የዚህ እብደት ማብቂያው ምን ይሆን? ኦሮሞትርያ? የኤርትራን ወደቦች የጠቀለለች ኦሮሚያን መዳረሻ የደረገ ቅዠት ሳይሆን ይቀራል?

በእርግጥ ኦሮምኛ ብዙህ ህዝብ የሚናገረው ታላቅ ቋንቋ ነው፡፡ ይህም ቋንቋው በፍጹም ተጠያቂ በማይሆንበት ሁኔታ በታሪክ አጋጣሚዎች በኢትዮጵያ ሲስፋፋና ሲነገር ቆይቷል፡፡ ኦሮሞም ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በሰላምም ይሁን በጦርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ አመታትን ወስዶ ሲወሃድ በውስጡ የያዛቸውን ባህሎች ሰጥቶና ተቀብሎም ኖሯል፡፡

ኦሮሞ እንደማንኛውም መሃበረሰብ ሁሉ አንድ ቋንቋ ይናገር እንጂ የተለያየ ባህል የነበረውና ያለው ህዝብ ነው፡፡ በእምነት፣ በአኗኗር ዘይቤ፣ ከሌሎች ባህል ጋር በነበረው ንክኪ …የተለያየ ስነልቦናን ቀርጾ የሚጓዝ ህዝብ ነው፡፡

ይሀንን በጭፈራው፣ በሓይማኖቱ ስርአቶች፣ በፖለቲካ አስተዳደሩ( ወለጋና ጂማ በንጉስ ይተዳደሩ ነበር) እናየዋለን፡፡ ይህ ለምን ተፈጠረ ማለት አይቻልም፣ በአለም ላይ ያሉ ባህሎች ሁሉ በውስጣቸው ይዘውት የሚጓዙት ነገር ነውና፡፡

አንድ ቋንቋ መናገር ማለት አንድ ባህል አለ ማለት አይደለም፡፡ለምሳሌ ጀርመንና ኦስትሪያ አንድ አይነት ቋንቋ ነው የሚናገሩት፡፡ ነገር ግን የተለያየ ባህል ነው ያላቸው፡፡ ሊያውም በዚህ አለም በጠበበችበትና ግሎባላይዝድ የሆነ ባህል እየመጣ ባለበት ግዜ ማለት ነው፡፡

ከመቶዎች አመታት በፊት በባሪያ አሳዳሪና በፊውዳል ስርዓተ መሃበር ውስጥ ህግ የለሽ ጦርነት በተለያ የአለማችን ክፍል ሲካሄድ የነበረና የተለመደ ነው፡፡ ብሔሮችን ወደ ኃላ መቶ አመታት ሄዶ አሁን ባለው የጄኔቭ አለማቀፍ የጦርነት ህግ መክሰስ ግን ፖለቲካዊ ዳፍታምነት ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቋንቋን ተንተርሶ በብሔር ላይ የተመሰረተው ግልብተኝነት፣ ተከታዩ ጀሌውን ምን ያህል የውር ድንብር እንደሚነዳው ማየት ያሳዝናል፣ ያማልም፡፡ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች ውስጥ የቱ ነው ባህር የሚያሸግረው? ምንም የለም፡፡ ኦሮሚኛ እንዳትሉ ብቻ? እንኳን ባህር ሊያሻግር ቀርቶ ዋቢሸበሌንና ገነሌ ወንዞችን አያሻግርም፡፡ አባይን አሻግሮ ከአረቦቹ ጋር አያገናኝም፡፡ የአዋሽ ወንዝ መጨረሻ ላይ እንኳን ተቀይሮ አፋርኛ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ንግዳቸውን ለማሳለጥ የሚያዋጣው በተጨማሪ እንግሊዘኛ፣ አረብኛና ስዋህሊ ቢናገሩ ነው፡፡

እባካችሁን ዘመኑ የሚጠይቀው፣በብሔር ግርግርታ ላይ ሆኖ መፋጠጥን ሳይሆን፣ ይዞ መገኘትና ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ከያኒውስ ብሎት አይደል፤

ብለው በመደንበር                                                                          በቀጫጭን መስመር

አንዴ ኦሮሙማ አይዶሎጂ ነው ወይም ኦሮሙማ ከሐይማኖት በላይ ነው ማለት ለአዋጪነት የሚቀርብ ጥያቄ አይደለም፡፡ ቆይተህ እየው እንዳልል እርግማንም ይሆናል፣ ለዚያም የሚሆን ግዜ የለም፡፡ መቼም መደበቂያው እኛ ነውና፣ የእኛ ሃገር መሬት በከርሰ መዐድን የበለጸገ ነው ብትለኝ፣ ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ ሙሉ መሬቱ እንዲያ ነው ብዬ ነው የምመልስልህ፡፡ ነገረ ግን ሃበቱን በዶማ ቆፍረህ ማውጣት አትችልም፡፡ ትልልቅ ማሽነሪዎችና አለምአቀፍ ፋይናንስ ያስፈልጋል…አሁንስ ገባህ፡፡

የክርስትና፣ እስልምናና የአይሁድ እምነት ያለቸውን ኃይል መገንዘብ የማይችሉ ሰዎች አዲስ ቃል ፈጥረው(ኦሮሙማ) የሁሉ የበላይ ሊያደርጉት ይፈልጋሉ፡፡ በከፍተኛ ሳይንሳዊ ፍልስፍናና ስነ ስርዓት እኒህን እምነቶች ሲተጋተግ የነበረው ኮሚኒዚም እንኳን ይኸው አይንህ ላፈር ከተባለ ሰላሳ አመታት አለፈውታል፡፡

ከሐይማኖት በላይ ነው የተባለው ኦሮሙማ፣ ገናሌን፣ አባይንና ሸበሌን ማሻገር ሳይችል ምን ሊፈጥር ይችላል? የእስልምና ቆጠሮው እኮ መካ መዲና ላይ ነው ያለው፡፡ የክርስትናና አይሁድ እምነት ደግሞ እይሩሳሌም ላይ ይገኛል፡፡ በሺህ አመታት ሂደት ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ውስጥ ገዝፈው የቆሙ እኒህን ሃውልታት በፈጠርከው ኢምንት ጠጠር መተህ ለመጣል መሞከር ምን የሚሉት ቅዠት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ዶሮን ሲታልሏት…የሚለው ቢህል እናንተ ላይ እሙን የሚሆነው፡፡ ቅንነቱ ካለ ግን ከታሪካችን መልካም መልካሙን እየመረጥን አዲስ እየተፈጠረ ላለው አለም አቀፋዊ ባህል አካል ማድረግ እንችላለን፡፡

ስለ ኮንፊሸስ

ከክርስቶስ ልደት በፊት 551 ዓ.ዓ. የተወለደው እውቁ የቻይና ፖለቲከኛና ፈላስፋ ኮንፊሸስ በጃፓን፣ ኮረያና ቻይና ህዝቦች ዘንድ በፍልስፍና፣ ትምህርተና የእለት ተእለት ኑሮ ውስጥ እስከዛሬ ድረስ አሻራውን ማሰቀመጥ የቻለ ሰው ነው፡፡ አንድ ግዜ የእሱ ተማሪ የነበረ ሰው ስለ መንግስት ይጠይቀዋል፡፡

እሱም መንግሰት ለዜጎቹ ማሟላት ያለበትን ነገሮች “በቂ ምግብ፣ በቂ ወታደራዊ መሳሪያዎችና ህዝቡ በመንግስት ላይ ትምምን እነዲኖረው ማድረግ” ናቸው ሲል መለሰለት፡፡ ተማሪውም መልሶ “ሦስቱንም ማሟላት ባይቻልስ የትኛው ይቅር ?” ሲል ጠየቀ፡፡ ኮንፊሸስም “የጦር መሳሪያው” አለ፡፡ ተማሪውም ሌላ ሦስተኛ ጥያቄ ጠየቀ”ከምግብና ከአመኔታስ ምረጡ ብንባል የቱን እንምረጥ?” የኮንፊሸስ መልስ እንዲህ የሚል ነበር”ምግብን ተወው፡፡ ሞት ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጅ ህይወት አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ሰዎች ግን በገዢዎቻቸው ላይ እምነት ካጡ፣ ሃገር አይጸናም፡፡”

እንግዲህ የብልጽግናን የፖለቲካ ጉዞ በኮንፊሸስ ቃል ስንመዝነው በኖና ተኖ እናገኘዋለን፡፡ የጦር መሳሪያ ሸመታው የተጋጋለ ቢሆንም፣ እኒያ ጠ/ሚ ሲያሽሞነምናቸው የነበሩት ጀነራሎች በጦርነቱ ወቅት ግማሹን ትግራይ ውስጥ ጥለው ወጥተዋል፡፡ በሃገሪቱ ላሉ ሌሎች አማጺያንም ይህንኑ የሃገር ሃብት በእጅአዙር ማስታጠቅም ቀጥለዋል፡፡

ህዝቡን መመገብ አቅቶታል፡፡ ኑሮ ተወዷል፡፡ በሰው ስራሽ(በመንግስት አካላት ጣልቃ ገብነት) ምክነያት መሰረታዊ የምግብ ዋጋ ከ60% በላይ ሲጨምር ተመልክተናል፡፡ የጤፍን ዋጋ ማየት በቂ ነው፡፡ ለእርዳታ የመጣ እህልም በመንግስት አካላት እየተሸጠ ይገኛል፡፡

መንግስት የህዝብ አመኔታን ማግኘት አልቻለም፡፡ ለዚህ ምክነያቱ ደግሞ “የአሳ ግማቱ ከአናቱ” እንዲል፣ በአሳምነህ ወይም አደናግረህ ግዛው መርሆ የሚመራው የብልጽግናው ኦሮሙማ ነው፡፡ ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ የኮንፊዩዝና ኮንቪንስ የፖለቲካ መርሆዋቸውን ከነገሩን ስንት ግዜ ሆነ? ከዚህስ በኋላ እንዴት አድርገን የኦሮሙማውን ፖለቲካ እንመን?

የኦሮሙማው በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት ፈጥሮ(A government within a governmet) ስለእኩልነት ሊሰብከን ይፈልጋል፡፡ አብያተ እምነቶችን በግልጽ በመንግስት መዋቅር እያፈረሰ፣ ስለ እመነት ነጻነት ይደሰኩራል፡፡ በጭር ሲል አልወድም እሳቤው አሁን ደግሞ ኤርትራ ላይ አይኑን እያጉረጠረጠ ይገኛል፡፡

ኦሮሞ በኢተበሃሉ “ነገሩ ይደር” (ዱቢና ቡለቱ) ይላል፡፡ ይህ መልካም አባባል ነው፡፡ ነገር ግን ህዝቡ ሰለ ህልውናው ሲል ህን አባባል ግዜው ያለቀበት አድርጎታል፡፡ ኦሮሙማው ኳሷን ኤርትራ ወደቦች ላይ ለመጫወት ሲያስብ፣ ሩቅ አሳቢ(ቃዢ) ቅርብ አዳሪ ሆኗል፡፡ እናስ ከዚህ በኋላ  ኳሷን ወዴት?

 

አስቻለው ከበደ አበበ

ሜትሮ ቫነኩቨር ካናዳ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop