June 5, 2023
6 mins read

ኢትዮጵያን መክሰስ እና መዉቀስ የት ሊያደርስ ?

አበዉ የገበያ ግርግር ለዘራፊ በጀዉ ይላሉ ፡፡

በአንድ ወቅት አምስት በሬዎች ነበሩ ቀለማቸዉም ይለያይ ነበር ይባላል ፡፡ ይሁንና አባ ጅቦ ሊበላቸዉ አስቦ የበሬዎች አንድነት ፈርተ ነበር እና በተናጠል ሊበላቸዉ መላ መታ ፡፡ ይኸዉም ከመካከላቸዉ በቀለም ከሩቅ የሚታይ ወይም የሚረብሽ የትኛዉ በሬ እንደሆነ መጠየቅ እና ማረጋገጥ ነበር ፡፡ ይህን መላ ምት ይዞ ከናንተ መኃል በሩቁ ለጠላት የሚታይ ነጭ በሬ አለ ይህም ብቻ አይደለም የሚረብሽ የቱ ነዉ….እያለ ተራ በተራ ጨረሳቸዉ ይባላል ፡፡

ይህ ለኢትዮጵያዉያን በግላጭ የሚሰራ ዕዉነት ነዉ ፡፡

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊ ዓማራ ህዝብ በአንድነት እና በህብረት መንቃት እና መደራጀት ተስኖት ለሠላሳ ዓመታት የመከራ እና የሞት ቋጥኝ እንዲሸከም ወዶ እና ፈቅዶ በመቀበል አስከዛሬ ሁለተናዉን ከነሙሉ ባርነት እና ስደት ለበአዴን አስረክቦ በተናጠል ሲገለል እና ሲበደል እዚህ ደርሷል፡፡

አሁንም እንደከዚህ በፊት በእኔ ዕምነት ለኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ወይም ዕጣ ፋንታ በዓማራዉ እና የዓማረዉን እና የኢትዮጵያን የቀደመ እና መጪ ትስስር የሚረዳ እና የሚያሳስበዉ ኢትዮጵያዉያን መዳፍ ስር ነዉ ፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዉያን እና ዓለም ቀርቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚስማሙበት አንድ ነገር አለ ኢትዮጵያን የግል ንብረት አድርጎ ለመቀጠል እና በኢትዮጵያ ፍርስራሽ የምኞት አገር ጎጆ ለመመስረት ብቸኛዉ መንገድ ዓማራን ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ መነጠል እና ማግለል ነበር ፡፡

ይህም በኢትዮ ጠል ኃይሎች የፈጠራ ትርክት ጨቋኟ ኣማራ ብሎ ከብሄራዊ የፖለቲካ ፣የምጣኔ ሀብታዊ እና ኃይማኖታዊ ሚና ማግለል ነበር ይህን አሳክቷል ፡፡  ይህም በጠላት ጥንካሬ ሳይሆን በዓማራ እና አገራቸዉን በሚወዱ ኢትዮጵያዉያን ህብረት እና የጋራ የዓላማ አንድነት እና ፅናት ማጣት ነበር ፡፡

ሁሉም በየተራ በጂብ አስኪነጠቅ ጠላቱ እንዲታደገዉ ወይም ሌላዉ እንዲሞትለት በመጠበቁ በየጊዜዉ ተራዉን ጠብቆ የተበላ ተበላ ያልተበላ ሊበላ አሁንም በተስፋ አይሉት በወረፋ ሞቱን ይጠብቃል ፡፡

በአዴን የተሰፋለትን ካባ ማዉለቅ ወይም መቀየር የማይችል በግዑዝነት ወደ ምንም “በድንነት ” የተሸጋገረዉ ገና በኢህአዴግ ምስረታ የኢትዮጵያን እና የዓማራን ህዝብ መራራ የትግል ዉጤት እና ድል አሳልፎ ለትህነግ በ1982 ዓ.ም ኣሳልፎ ሲሰጥ በልኩ ከተሰጠዉ ካባ ዉጭ ምንም ማድረግ የማይችል መሆኑን አሜን ብሎ በመቀበል አንኴንስ  የኢትዮጵያን እና ዓማራን ህዝብ ጥቅም እና ስም ሊያስጠብቅ ቀርቶ የራሱን ድርጂት እና የሞቱለትን ጓዶች መዘከር የማይችል መሆኑን ድሮ ነዉ ያስመሰከረዉ ፡፡

ይባስ ብሎ በወረራ እና በዕብሪት የወደመዉ የሠዉ እና የብሄራዊ ሀብት ሳይበቃ ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር በጎጃም ፣ ጎንደር ፤ ወሎ እና ሸዋ ላይ በህዝብ እና በኃይማኖት ተቋማት ላይ ዕልቂት እንዲሆን የሚፈቅድ ወይም ሲሆን የሚያይ ድርጂት ከጅምሩ አገር እና ህዝብ ለመጉዳት እንጂ ለመታደግ የማይችል መሆኑን ከዚህ በላይ ማሳያ አይኖርም ፡፡

ቢመሽም ሁሉም ኢትዮጵያዉያን እና በተለይም የዓማራ ህዝብ የዘመናት መከራ ቀንበር በጋራ እንዲጫንበት የፈቀደ ነገር ግን በተናጠል እየሞተ ያለዉ ከራሱ መሞት ባሻገር የትዉልድ እናየአገር ሞት መዳረሻ ምዕራፍ ላይ መሆኑን አዉቆ ለአገሩ እና ለራሱ ህልዉና መቀጠል አንድነቱን እንደብረት ማጠንከር ይኖርበታል ፡፡

ይህ ባይሆን የአምስቱ በሬዎች እጣ እና መጨረሻም በመቃብሩ የጂቦች ዋሻ ይመሰረታል ፡፡

በጦርነት ጊዜ አንተን ያሉ ሁሉ፣

ዓማን ቢሆን ነዉ ወይ  ጥለዉህ የበሉ ፡፡

ይህ ስነ ቃል ፡ ለመላ ኢትዮጵያዉያን የቁርጥ ቀን ልጆች ዋኖች /ጀግኖች ይሁን ፡፡

አንድነት ኃይል ነዉ !

 

አለን -ፀ. ሥላሴ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop