June 5, 2023
54 mins read

በአስከፊ የፖለቲካ ሥርዓት አዙሪት ውስጥ እየጓጎጡ የሃይማኖት ነፃነት ብሎ ነገር የለም!

June 4, 2023

ጠገናው ጎሹ

religion 1
#image_title

ሃይማኖታዊ እምነትን በፈጣሪ አምሳል ተፈጠረ ብለን ለምናምንለት ሰብአዊ ፍጡር በእጅጉ የሚያስፈልጉትን የነፃነት፣ የፍትህ፣ የሰላም፣ ፣የመከባበር ፣የመተሳሰብና የጋራ ህይወት ስኬት እሴቶች እውን ሊያደርግና ሊያስደርግ ከሚችል የፖለቲካ ሥርዓት ለይቶ ማየት የሃይማኖታዊ እምነት እሴትን ራሱን ትርጉም ማሳጣት ነው የሚሆነው።

ሃይማኖታዊ እምነት በሰው ልጆች ሁለንተናዊ መስተጋብር (ህይወት) ውስጥ በእጅጉ አስፈላጊ ከሆኑ እሴቶች መካከል አንደኛው ሆኖ የኖረና የሚኖር እንጅ አንዳች አይነት የማይጨበጥ ነገር ወይም መንፈስ አይደለም።

የሃይማኖት መሪነት ፣ ሊቅነት፣ሊቀ ሊቃውንትነት፣ ሙዓዘ ጥበባትነት፣ ሊቀ ጠበብትነት፧ ሊቀ ማእምራንነት፣ መጋቢነት፣ ካርዲናልነት ፣ፓስተርነት፣ ሸህነት ፣ኡስታዝነት ስኬታማነት የሚለካውም ይህንኑ መሠረታዊ ተልእኮ እውን ለማድረግ በመቻል ወይም ባለመቻል ፈታኝ አቋምና ቁመና እንጅ የክስተቶችን ትኩሳት እየጠበቁ እግዚኦ ወይም እልል በሉ በሚል ከንቱ ውዳሴ ብቻ አይደለም

በቁጥርም ሆነ በጥራት ያለብን እጥረት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በአገራችን የገጠመንና እየገጠመን ያለው እጅግ ከባዱ ፈተና ግን እውቀትን ከሃይማኖታዊ አርበኝነት መንፈስና አቋም ጋር በማቆራኘት ለምድሩም ሆነ ተስፋ ለምናደርገው የወዲያኛው ዓለም ህይወት  የሚበጅ ሥራ ሠርቶ ለመገኘት ያለመቻል ክፉ ጎደሎነት ነው። አርበኝነት (patriotism) በቅድመ ሁኔታ የማይወሰን የአገር ፣የህዝብና የበጎ እሴት ፍቅር እና ይኸው እውን ይሆን ዘንድ የሚከፈል ዋጋን (መስዋእትነትን) የተሸከመ ጥልቅ ፅንሰ ሃሳብ ነው ።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ከዚህ ውጭ ያለው የሃይማኖት መሪነትና አስተማሪነት ከባህሩ እንደ ወጣ አሳ ነው። አዎ! የአሳ ህይወቱ ውሃው (ባህሩ) እንደ ሆነ ሁሉ የሃይማኖታዊ እምነት ህይወትም የሰብአዊ ፍጡር ደህንነትና ድነት ነው። ከባህር ውጭ ያለው አየር (ኦክስጅን) ለአሳ ህይወት ሊሆን እንደማይችል ሁሉ ከሰው ልጆች የህይወት መስተጋብር ደህንነትና ስኬት ውጭ በአየር ላይ የሚንሳፈፍ ሃይማኖታዊ እምነትም እንዲሁ ነው።

ኢሰብአዊነት የተጠናዎታቸውን ገዥ ቡድኖች ከመፀየፍ እና በአርበኝነት ስሜትና ተግባር ከምር ከመገሰፅ ወይም “መከረኛውን ህዝብ ልቀቁት” ብሎ ከመቆጣት ይልቅ መከራንና ውርደትን መታገሥ የፅድቅ መንገድ አድርጎ የሚተርክ የሃይማኖት መሪነትንና አስተማሪነትን ለመረዳት በእጅጉ ይከብዳል ። ምክንያቱም በመሬት ላይ ካለው መሪር እውነታ እና በክርስቶስ አማካኝነት በተግባር ከተገለፀው ሃይማኖታዊ  አስተምህሮት ጋር አይጣጣምም።

 የራሳችንን የውድቀት አባዜ በሃይማኖታዊ አርበኝነት መጋፈጥና ተገቢውን የእርምት እርምጃ መውሰድ ስለሚሳነን የምንመርጠው ሰንካላ ሰበብ እየደረደርን ለመቀጠል ካልፈለግን በስተቀር ለዚህ መሪር ሁኔታ እውነትነት ከእኛው ከራሳችን በላይ አስረጅና ማስረጃ የሚኖር አይመስለኝም።

በሥልጣነ መንበር ላይ እየተፈራረቁ በመከረኛው ህዝብ ላይ እንኳንስ ለማመን ለማሰብም በእጅጉ በሚከብድ ሁኔታ የመከራና የውርደት ዶፍ የሚያወርዱትን እኩያን ገዥ ቡድኖች በአግባቡ (በሃይማኖታዊ አርበኝነት ስሜት) መገሰፅ ወይም “በሰማይ ሃጤአትና በምድርም ወንጀል ነውና ልብ ግዙ” ለማለት ወኔው የሚከዳው የሃይማኖት መሪ ፣ ሰባኪና  አገልጋይ ቁጥሩ ቀላል ባልሆነበት አስፈሪ እውነታ ውስጥ ስለ ሃይማኖታዊ መብትና ነፃነት የሚዥጎደጎደውን ስብከትና ውዳሴ  አሜን ብሎ የሚቀበል እውነተኛ አምላክ የለም።

እውነተኛው አምላክ ቃልንና ተግባንር አዋህዶ ለምድራዊውም ሆነ ለሰማያዊው ህይወቱ ስኬት እልህ አስጨራሽ ጥረት ከሚያደርገው ጋር እንጅ በሰብአዊ ፍጡርነት የተፈጠረበትን ዓላማ እየረሳ ወይም እየሳተ ወይም ራሱን አቅመ ቢስ እያደረገ ጭንቀት ሲሰማው እግዚኦ ከሚለውና እና ጭንቀቱ የለቀቀው ሲመስለው ደግሞ እልልታውን ከሚያቀልጠው ጋር  በፍፁም አይደለም!

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ከዘመን ጠገቡ ፖለቲካ ወለድ ሰቆቃና ውርደት ሰብሮ ከመውጣት ይልቅ የዚያው እኩይ ሥርዓት ውላጆች ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ካስቀጠሉት ክፉ አዙሪት ሰብረን እንዳንወጣ ካደረጉን ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ይኸው በአስፈሪ አኳኋን እየተንሸዋረረና እየተሸረሸረ የመጣው የሃይማኖት ተቋማት እሴታችን ነው።

ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያውን ሃላፊነት የሚወስዱት የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች ቢሆኑም የሃይማኖት መሪዎችንና አስተማሪዎችን በአክብሮትና በአግባቡ ልክ አይደላችሁም ማለትን ነውር ብቻ ሳይሆን ሃጢአትም እንደሆነ አምኖ የተቀበለው ምእመንም ጭምር መሆኑን እየመረረም ቢሆን መረዳትና መቀበል ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ ፊደል ቆጠራ (መማር) ከእኔ ወዲያ ላሳር ነው የሚለው የህብረተሰብ ክፍል የዚህ ክፉ ስንፍና ወይም አቅመ ቢስነት ሰለባ ሲሆን እንደ አገር ከወደቅንበት ክፉ አዙሪት መቸና እንዴት እንደምንወጣ እንኳን ለማወቅ ለመገመትም ያስቸግራል።

አያሌ ንፁሃን ወገኖቹ በባለጌ፣ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ደናቁርትና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖች በግፍ ሲገደሉ፣ የቁም ስቃይ ሰለባዎች ሲሆኑ፣ በገዛ አገራቸው ውስጥ ሆነው የአገር ያለህ ሲሉ ፣ ወገን መሃል ሆነው የወገን ያለህ ሲሉ ፣ በየሃይማኖታቸው የፈጣሪያቸውን ስም እየጠሩ የሰቆቃ ጩኸት ሲጮሁ ፣ ህፃናት ሳይቀሩ የመከራቸው ምክንያት ኢትዮጵያዊያንና አማራ መሆናቸው መሆኑን አውቀው የዛሬን ማሩኝ እንጅ ሁለተኛ አማራ አልሆንም እያሉ ሲማፀኑ ፣ወዘተ የመፍትሄ ሃሳብ አምጦ ለመውለድና በተደራጀ አቋምና ቁመና ለመታደግ የፖለቲካም ሆነ የሞራል ግዴታ የማይሰማው ተምሬያለሁ ባይ የህብረተሰብ ክፍል ‘ለኢትዮጵያ ዝም አንልም’ በሚል መፈክር ስለ ባህል፣ ስለ ሞራል፣ ስለማይክሮ ችፕስ ተጠቂነት ፣ ስለ 666፣ ስለ እሉመናቴ ሰይጣናዊነት፣  ስለ ግብረ ሶዶማይነት፧ ስለ የቴክኖሎጅ የጎንዮሽ አሉታዊ ውጤት፣ ስለ የውጭ አካላት (ሃይሎች) የባህልና የሃይማኖት ወረራ ፣ እና በአጠቃላይ ስለ ትውልዳዊ ውድቀት (ቀውስ) የትረካና የትንታኔ ድሪቶ ሲደርት ከመስማት የባሰ እጅግ አስቀያሚ ወለፈንዲነት (paradox) የለም። እያልኩ ያለሁት ጎጅ ስለሆኑ ጉዳዮች ማስተማርና በተደራጀ ሁኔታ ድጋፍ ማድረግ አያስፈልግም አይደለም። በእነዚህ ጎጅ ነገሮች ተበከለና እየተበከለ ነው የምንለው ትውልድ በእኩያን ገዥ ቡድኖች የገዛ አገሩ ምድረ ሲኦል ስትሆንበት ሲሆን የተደራጀ ትግል ለማድረግ ቢያንስ ግን ከምርና በግልፅ ለማውገዝ ወይም ለመቃወም ያልሞከረ ግለሰብ ወይም አካል ጎጅ እምነቶችና ሌሎች ማህበራዊ ህፀፆች የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረቶቼ ናቸው የሚለውን ያለጥያቄ መቀበል ያስቸግራል ነው።

እንደማነኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሃጢአት (ክፉ ሥራ) የመሥራታችን እውነትነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ ከዘመን ጠገቡ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰብረን እንዳንወጣ ያደረገን ግን የገዛ ራችን ስንፍና ፧ አቅመ ቢስነት፣ ድንቁርና ፣ ምቀኝነት፣ ፍቅር አልባነት፧ ቅጥፈት፣ አድርባይነት ፣ ህብረት ማጣት ፣ ፍርሃት፣ ከመከራ ጋር መላማድ ፣ ወዘተ እንጅ የተለየን ሃጢአተኞች በመሆናችንና አምላክ ሊቀጣን ስለፈለገ በፍፁም አይደለም።  የእውነተኛው አምላክ መልካም ፈቃድ ወደ የተግባር ሃያልነት ሊተረጎም (ሊለወጥ) የሚችለው ቃልና ተግባር በተዋሃዱበት የሰብአዊ ፍጡር አቋምና ቁመና እንጅ በድርጊት አልባ ሃይማኖታዊነት ፈፅሞ አይደለም ።

የሰው ልጅ እንደ ልዩ ማህበራዊ እንስሳ ፍጡርነቱ የትክክለኛውን አስተሳሰብና አካሄድ በእጅጉ እየሳተና እያሳተ የገዛ ራሱን ዓለም የብልግና እና የመከራ የማድረጉ ወይም የተፈጠረበትን እጅግ ትልቅና ድንቅ ዓላማ የመሳቱ መሪር እውነታ ነው ፈጣሪን በክርስቶስነት ወደ ዚህ ዓለም ያመጣው።

ከሁለት ሽ ዓመተ ምህረት በኋላም ክርስቶሳዊ አስተምሀሮትን ከመነባንብነት (ከባዶ ስብከት) አውጥተን ለምድራዊውም ሆነ ለሰማያዊው ህይወት ስኬት በሚጠቅም ሁኔታ አልተረጎምነውም። ለዚህም ነው መከረኛው ህዝብ በመንበረ ሥልጣን ላይ እየተፈራረቁ የመከራና የውርደት ዶፍ የሚያወርዱበትን ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ሲሆን ለማስወገድ ቢያንስ ግን ትርጉም ባለው ሁኔታ ልብ እንዲገዙ ለማድረግ ያልተሳካለት።

በአንፃራዊነት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሃይማኖታዊ እምነት መሪ፣ አስተማሪ፣ ሸህ፣ “ነብይ”፣ ፓስተር፣ ሊቅና ሊቀ ሊቃውንት ፣ ጳጳስና ሊቀ ጳጳስ ፣ ወዘተ በሚገኝበት በዚህ በእኛው ዘመን የባለጌና የጨካኝ ገዥዎችን ሥርዓት ከምር በመፀየፍ፣ በመገሰፅና አስፈላጊም ከሆነ መስዋዕትነት ከፍሎ ንፁሃን ወገኖችን (ህዝቦችን) ለመታደግ የሚያስችል አቋምና ቁመና ደሃዎች የመሆናችን መሪር እውነት በእጅጉ ያስፈራል።

የሃይማኖታዊ እምነት መነሻው ከሌላው ደመ ነፍስ ፍጡር ተለይቶ እጅግ ድንቅ ለሆነ ዓላማና ተልእኮ የተፈጠረው የሰው ልጅ ከገባበት (ከተጠናወተው) እኩይ ባህሪውና ተግባሩ በአንፃራዊነት (ፍፁምነት ባህሪው አይደለምና) ነፃ እንዲወጣ ለማስቻል እንጅ ጀብደኝነትና የማይጨበጥ አንዳች አይነት ምትሃት ወይም ተአምር አልነበረም። አይደለምም። ለዚህም ነው ሰብአዊና መሠረታዊ መብቶቹ የተደፈጠጡበት ህዝብ (አማኝ) አምናለሁና እግዚኦ በማለት ብቻ የሚጎናፀፈው አንዳችም አይነት ነፃነትና ፍትህ ከቶ ሊኖር አይችልም ብሎ መከራከር (መሟገት) የፅድቅ እንጅ የሃጢአት መንገድ የማይሆነው።

ከሞት በኋላ ተስፋ የምናደርገው ህይወት የሰመረ መሆኑ ወይም አለመሆኑ የሚወሰነው በዚሁ በገሃዱ ዓለም በሚኖረን መልካም አስተሳሰብና በማያቋርጥ ተጨባጭ ሥራችን (ተግባራችን) እንጅ በተግባር አልባ እግዚኦታና እናምናለን ባይነት በፍፁም አይደለም። ይህንን ለመረዳት የተለየ ዓለማዊም ሆነ ሃይማኖታዊ እውቀትን ከቶ አይጠይቅም። የሚጠይቀው ቅን ፣ አስተዋይና ሚዛናዊ ህሊናን  ነው።

የእርሱን (የአምላክን) ኅያልነት አምኖ የመቀበልና ድጋፉን በቅንነትና በግልፅነት የመጠየቁ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከሌላው ፍጡር የተለየ አድርጎ የፈጠረን አምላክ ከእውነት ፣ከፍትህ ፣ ከነፃነት፣ ከሰላም፣ ከመብት፣ ከመተሳሰብ፣ ከመተባበር ፣ ከጋራ እድገት፣ ወዘተ አርበኝነት በላይ ከእኛ የሚፈልገው አንዳችም ነገር የለም። አዎ! በየትኛውም ቋንቋ ስሙን እንጥራው እውነተኛው አምላክ ይኸው ነው። ከዚህ ውጭ የምናነበንብለት አምላክ ካለ ሰነፉ ህሊናችን ውስጥ ያለው እንጅ እውነተኛው አምላክ አይደለም።

ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴን እንደ የሃጢአት ህፀፅ (ጉድፍ) እና የሃይማኖት መሪዎችንም እንደ መዳፈር በመቁጠር አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የዕርግማን (የውግዘት) ውርጅብኝ ለማዥጎድጎድ የሚቃጣቸው ወገኖች (አማንያን) ቁጥር ቀላል ባይሆን ያሳዝን እንደሆነ እንጅ የሚገርም አይሆንም። ይህ ደግሞ በዋናነት ከሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖችና ከአድርባይ ወገኖች ባልተናነሰ የራስ ወዳድነትና የአድርባይነት ክፉ ባህሪ ሰለባ ከሆኑ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች የሚመነጭ አስከፊና አስፈሪ የውድቀት ገፅታ ነው።

የሃይማኖት መሪዎች ወይም ባለሌላ ማእረግ አገልጋዮች “የሚሰብኩበትን አንደበት ተከተል እንጅ የተግባር ማንነታቸውን (አርአያነታቸውን) ለፈጣሪ ተውለት “ የሚል እጅግ  የተንሸዋረረ ልማዳዊ አስተሳሰብን እንደ ትክክለኛ የፅድቅ መንገድ አድርጎ እንዲቀበል የተደረገ ማህበረሰብ የነፃነትና የፍትህ አልባ ሥርዓት ቀንበር ተሸካሚነትንም እንደ የፅድቅ መንገድ ቢቆጥር የሚገርም ጉዳይ አይደለም። የዚህ አይነት በእጅጉ የተንሻፈፈ (የተንሸዋረረ) አስተሳሰብ ለእኩያን ገዥዎች ምቹ ሁኔታ የመፍጠሩና እየፈጠረ የመቀጠሉ  መሪር እውነታ ግን ማስገረም ብቻ ሳይሆን በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚያሳፍርም ነው።

በእንዲህ አይነት እጅግ የተንሸዋረረ አስተሳሰብና አካሄድ ውስጥ እየጓጎጥን እውነትንና እውነትን ብቻ ያስተማረውንና ለዚህም የመጨረሻውን መስዋእትነት ከፍሎ ያሳየንን የክርስቶስን (የአምላክን) ሃያልነት ማነብነብ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም። ከዚህ አይነት በእጅጉ የኮሰመነ አስተሳሰብና አካሄድ በተቻለ አቅምና ፍጥነት ሰብረን ለመውጣትና ለሰማያዊውም ሆነ ለገሃዱ ዓለም ወደ የሚበጅ ሃይማኖታዊ ማንነትና እንዴትነት ለመመለስ ፍቃደኛና ዝግጁ ሆኖ ለመገኘት እስካልተቻለ ድረስ ለማያቋርጥ ትውልዳዊ  ቀውስ ተጠያቂ ከመሆን ፈፅሞ ማምለጥ አንችልም።  “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል” እንዳለችው እንስሳ እኛም “እኛ ከሞትን (ለነገሩ በቁም ከገደሉን /ከሞትን ቆየን)  የምን የትውልድ አደራ ነው” ካላልን በስተቀር እየገጠመን ያለው መሪር እውነታ ይኸው ነው።

በእውነት ከተነጋገርን የህዝብ መከራና ውርደት ማቆሚያ እንዳይኖረው ብቻ ሳይሆን በእጅጉ አስከፊ እየሆነ እንዲቀጥል ካደረጉት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ይኸው በእጅጉ እየተደበላለቀ የቀጠለው የፖለቲከኞችና የሃይማኖት መሪዎች አስተሳሰብና አካሄድ ነው።

ግልፅና ግልፅ የሆነውን የገዛ ራሳችንን የማንነት ፣ የእንዴትነትና የወዴትነት ውድቀት በአግባቡና በጥበብ መረዳትና ማስረዳት ሲያቅተን (ሲሳነን) ነገሮችን ሁሉ ጨርሶ ከአእምሮ የተሰወሩ (absolute abstract) እያስመሰልን የማየትና የማሳየት ደካማ አስተሳሰብና አካሄድ ክፉኛ ከተጠናወተን አያሌ ዘመን አስቆጠርን።

ለሩብ ምእተ ዓመት በህወሃት የበላይነት የቆየውና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለብልግናቸውና ለጭካኔያቸው ጨርሶ ልክ በሌላቸው የዚያው ሥርዓት ውላጆች የቀጠለው ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ዛሬም ድረስ ለምን መሪር ትምሀርት የእንዳልሆነን በእጅጉ የሚገርም ነው ። የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው ከመቸውም በባሰ አኳኋን የዚህ አይነት ክፉ ልክፍት ሰለባዎች የመሆናቸው ጉዳይ ደግሞ ከምንምና ከማንም በላይ ህሊናን ይፈታተናል።

አዎ! ከሩብ ምእተ ዓመት በኋላም የአንድ እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት ውላጆች በተረኝነት ተተክተው ካወረዱትና እያወረዱ ካሉት የሰቆቃና የመከራ ዶፍ በመማር ለመሠረታዊው  የሥርዓት ለውጥ በጋራ የመነሳቱ  ትግል አልተሳካልንም። ጧት ላንሸሽና ላንከዳዳ ቃል ለሰማይና ለምድር ብለን ከተማማልን በኋላ ማታ የሰበብ ድሪቶ እየደረትን በየፈርማታው እንጠባጠባለን።

ይህ ደግሞ የፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎችና ሊቃውንት ፈተና  ሲሆን በእጅጉ ይረብሻል ፤ያስፈራልም። በአሁኑ ወቅት የምንታዘበው የአገራችን መሪር እውነትም ይኸው ስለሆነ የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች ወይም ሰባኪዎች ከማንም በፊትና ከምር ንስሃ ሊገቡና ተልኳቸውን ወደ የሚመጥን ምንነት፣ ማንነትና እንዴትነት ሊመለሱ ይገባቸዋል።

ሃይማኖታቸውን በእውን የሚወዱ ምእመናንም ስለ እውነት በግልፅና በአክብሮት የመናገርና የመነጋገር አስፈላጊነትን ሃይማኖታዊ ሥርዓትንና የሃይማኖት መሪን ወይም አስተማሪን እንደ መዳፈር ከሚቆጥር እጅግ ደካማ አስተሳሰብ ወጥተው ተገቢውን ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በአግባቡ ጠይቅና እወቅ እንጅ አትጠይቅና አትናገር የሚል እውነተኛ አምላክ ፈፅሞ የለምና።

አማኙ/ምእመኑ (ቢያንስ ፊደል የቆጠረው) ለሰማያዊውም ሆነ ለምድራዊው ህይወቱ መሠረት የሆኑት ቃልና ተግባር ተለያይተው ሲወድቁ እያየና እየሰማ ዝምታን እንደ ፅድቅ መንገድ ከመውሰድ እጅግ የኮሰመነ አስተሳሰብና አካሄድ ፈፅሞ ለመውጣት ባይችልም ቢያንስ ተገቢውን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። አሰቃቂ የመቃብር ሙትነትን ፣ለማመን ቀርቶ ለመስማት  የሚያስቸግር የቁም ሰቆቃን ወይም የቁም ሞትን፣ ልክ የሌለው ውርደትን ፣ ወዘተ ቆሞ (በዝምታ ወይም በፍርሃት) እያየና እየሰማ “ነፍስ ይማርልን፣ ምህረቱን ይዘዝልን ፣ ሰማዓትነትን ይቀበልልን፣ በቃችሁ ይበልልን ፣ ወዘተ” የሚልን ድርጊት አልባ እግዚኦታን ወይም ልመናን የሚቀበል እውነተኛ አምላክ የለምና።

እኩያን ገዥ ቡድኖች በሥልጣነ መንበር ላይ በመፈራረቅ በህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ እያወረዱ እንዲቀጥሉ ካስቻሏቸው ሁኔታዎች መከካል አንዱ የኸው እጅግ አስቀያሚና አስፈሪ የውድቀት አዙሪታችን ነውና ምንም እንኳ በእጅጉ ቢዘገይ አሁንኑ በቃ ማለት ይኖርብናል።

አገራዊ ፈተናችን ከምናውቀውና ከምንመኘው የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄ አልፎ እንደ አገርና እንደ ማህበረሰብ የመኖር ወይም ያለመኖር (existential threat) ጥያቄ ነውና ትግሉም ከዚሁ አንፃር ነው መቃኘት ያለበት። ለዚህ ነው የክስተቶችን ትኩሳት ከራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም ጋር እየመዘኑና እያስኬዱ የመከራውንና የውርደቱን ሥርዓት የሚያራዝሙ የሃይማኖት መሪዎችንና ሰባኪዎችን በአግባቡ ማሄስ ከትክክልም በላይ ትክክል የሚሆነው።

የሃይማኖታዊ እምነት ተቋሞቻችንና እኛም አማኞቻቸው ከሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች አገዛዝ ሰለባነት ሰብረን ለመውጣት ላለመቻላችን አንዱ ምክንያት የሃይማኖት መሪዎቻችን ደካማነት እና የእኛም የራሳችን ስንፍና መሆኑን ተረድተንና ተቀብለን ተገቢውን የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ድርጊት አልባ ፀሎትንና ምህላን እንደ ብቸኛ መፍትሄና የፅድቅ መንገድ የመቁጠራችን ደካማነት ነው።

ይህንን መሪር እውነታ ላለመቀበልና ተገቢውን ላለማድረግ አሁንም የሰበብ ድሪቶ የሚደርት ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር ከሆነ የነፃነትንና የፍትህን ምንነትና እንዴትነት አያውቅምና ራሱን መመርመር ይኖርበታል።

ከረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና ከብቁ የማከናወኛ አካል ጋር የተፈጠርንበትን እፁብ ድንቅ ትርጉምና ዓላማ በአፍ ጢሙ እየደፋን የምንፀልየውን ፀሎት፣ የምንፆመውን ፆም፣ የምናሰማውን እግዚኦታ፣ የምናደርሰውን ኪዳን ፣ የምንዘምረውን ዝማሬ፣ የምንቀኘውን ቅኔ፣ የምናሳልመውንና የምንሳለመውን መስቀል፣ የምንፅፈውን መፅሃፍ ወይም ፅሁፍ ፣ የምንተርከውን  ትርክት፣ የምንሰብከውን ስብከት ፣ በየአደባባዩ እና በየአዳራሹ የምናጨበጭበውን ጭብጨባና የምናቀልጠውን እልልታ፣ የምንተውነውን “አጋንንትን የማስወጣት” ትርኢት፣  በየአዳራሹና በየአደባባዩ የምናዥጎደጉደውን እጅግ አሳፋሪና አስፈሪ የነብይነት ትርዒት፣ አገር ለማሰብ በሚከብድ ሁኔታ በምትገኝበት በዚህ ወቅት በገዳም ምሥረታና በገዳማዊነት ስም ከየዋህ አማኝ መቀነትና ቦርሳ የምንለቅመውን ሳንቲም፣ በተለምዶ የምንቀራውን ቁራን ፣ ሰዓታት እየቆጠርን የምነሰግደውን ስግደት ፣ ወዘተ ለዘመናት ከዘለቀውና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዚያው ሥርዓት ውላጆች በሆኑ እኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች በአስከፊ አኳኋን ከቀጠለው እጅግ መሪር መከራና ውርደት አንፃር ከምር ስናነፃፅረው የሚሰማን ከስህተት የመመለስ ፀፀት ሳይሆን የፅድቅ ስሜት ከሆነ አሁንም ከባድ ችግር ላይ ነን ማለት ነው።

ፍፁም ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ባለጌ ፣ደናቁርትና ጨካኝ በሆኑ ተረኛ ገዥ ቡድኖች (ኦነጋዊያን /ብልፅግናዊያን) ተባብሶ የቀጠለውን አገራዊ መከራና ውርደት እንኳንስ ለማስቋም ትርጉም ያለው ማስታገሻ ለመፍጠር ያለመቻላችን እንቆቅልሽም ከዚሁ እጅግ አሳፋሪና አስፈሪ ከሆነው አስተሳሰባችንና አካሄዳችን የሚመነጭ ነው።

የሃይማኖት ተቋማት የዚህ እንቆቅልሽ ሰለባዎች የመሆናቸው ጉዳይ ደግሞ የውድቀታችንን አዙሪት ይበልጥ አስከፊ አድርጎታል ። አዎ! አስከፊ ከሆነው   የሃይማኖታዊ እምነት ፣ የሞራል፣ የሥነ ምግባር፣ የሥነ ልቦና፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ፣ የራዕይ ፣ ወዘተ ውድቀት በእውን ሰብረን መውጣት ካለብን በዚህ ልክ ነው መነጋገር ያለብን ። ብልጭና ድርግም የሚል ጊዚያዊ ክስተትን እንደ ስኬት በመቁጠር በረጅሙና በዘላቂው የነፃነትና የፍትህ ትግል ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እየቸለስንና የእኩያን ገዥ ቡድኖች ሰለባዎች እየሆን የትኛውን የሃይማኖት ነፃነትና ፍትህ እንደምንናፍቅ ለመረዳት በእጅጉ ይከብዳል።

መቸም የገዛ ራችንን ልክ የለሽ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት በግልፅ፣ በቀጥታ ፧ በአግባቡና ውጤታማ በሆነ አቋምና ቁመና መጋፈጥ ሲያቅተን ተልካሻ (ስንኩል) ሰበብ በመደርደር ዙሪያውን የመዞር ከፉ ልማድ ተጠናውቶን ነው እንጅ ጨርሶ የማያፈናፍነው መሪር እውነታ ይኸው ነው።

ነገረ ሥራችን ሁሉ ሊያጋጥም ይችላል ከሚባለው ችግር አልፎ በህይወት የመኖር ወይም ያለመኖር (የመሆን ወይም ያለመሆን) ፈተና በሆነበት መሪር እውነታ ውስጥ እየጓጎጡ እና “ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው” የሚለውን መርህ በተሳሳተ ወይም ለራስ በሚያመች ሁኔታ እየተረጎሙ ከሞራል ተጠያቂነት ለመሸሽ መሞከር እንኳንስ በመንፈስ ቅዱስ እመራለሁ ለሚል የሃይማኖት መሪና አስተማሪ ትክክለኛ ህሊና ላለው ተራ አማኝም ፈፅሞ የሚመጥን ነገር አይደለም።

በእጅጉ የሚያሳዝነው ደግሞ እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብና አካሄድ ለገሃዱም ሆነ ተስፋ ለምናደርገው ከሞት በኋላ ህይወት ጨርሶ አይጠቅምምና ልታርሙት ይገባል መባልን መንፈስ ቅዱስን (አምላክን) እንደመጋፋትና ብሎም እንደ ኅጢአት በመቁጠር ያዙንና ልቀቁን የሚሉ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሰባኪዎች፣ ሊቆችና ሊቀ ሊቃውንቶች፣ ፓስተሮች፣ ነብያት ነን ባዮች፣ አጋንንት እናስወጣለን ባዮች፣ ባህታዊያን ነን ባዮች፣ ሸሆችና ኡስታዞች ነን ባዮች ቁጥር ቀላል ያለመሆኑ ፈተና ነው።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የሃይማኖት ነፃነትን መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች እውን እንዲሆኑ፣ እንዲከበሩና እንዲዳብሩ ለማድረግ ከሚያስችል ሥርዓተ ፖለቲካ ለይቶ ማየትና ማሳየት (መስበክና ማሰበክ) ፈጣሪ ሰውን በአምሳሉ ለፈጠረበት፣ ክርስቶስ ወደ ዚህኛው ዓለም መጥቶ ላስተማረበትና የመጨረሻውን የመስዋእትነት ፅዋ በታላቅ ፀጋና በአርአያነት ለተቀበለበት እፁብ ድንቅ ዓላማና ተልእኮ ፈፅሞ አይመጥንም።

በአገራችን ያጋጠመንን እና እያጋጠመን ያለውን መሪር እውነታ በዚህ ልክ ተጋፍጠን ተፈላጊውን እርምት ሊያስደርግ የሚችል ዝግጁነትና አቅም አስካልፈጠርን ድረስ ለዘመናት ከተዘፈቅንበት ተደጋጋሚና እጅግ አስከፊ የውድቀት አዙሪት መውጫ መንገድ አይኖረንም።

ለዘመን ጠገቡና ከመሻሻል ይልቅ እየከፋ በመሄድ ላይ ላለው ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ዋነኛ ተጠያቂዎች ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥዎች ፣ ህሊና ቢስና አድርባይ ወገኖች፣ በቁም የሞቱት የተቃዋሞ ፖለቲካ ፖለቲከኞች ፣ ወዘተ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎችም ተልእኳቸውንና ሃላፊነታቸውን  በአግባቡ ለመወጣት ያለመቻላቸው ወይም ያለመፈለጋቸው ውድቀት የመከራውና የውርደቱ  ዘመን እንዲራዘም ማድረጉን  “በፖለቲካ አያገባንም” በሚል  እጅግ ደምሳሳ መከራከሪያ ለመሸፋፈን  የሚቻል አይመስለኝም። ለመሸፋፈን የሚሞከር ከሆነም ከሰው አልፎ ፈጣሪንም መሸንገል ነው የሚሆነው።

እናም ትክለኛው ፍኖተ መፍትሄ እየመረረንም ቢሆን ከሁሉም በፊት የገዛ ራሳችንን የአስተሳሰብና የአካሄድ ሽባነት አምኖ መቀበልና ለዚሁ የሚመጥን ሃላፊነትን መወጣት ብቻ ነው። እንዲህ ስንሆንና ስናደርግ ብቻ ነው እውነተኛው አምላክ ጥረታችን ሁሉ  የሚባርከው። የወለፈንዲነት አስተሳሰብ (paradoxical way of thinking) እንኳን ለእውነተኛው አምላክ ቅንና እውነተኛ ለሆነ ሰብአዊ ፍጡር ህሊናም አይመጥንም።

እንዲህ አይነቱ የገዛ ራሳችን መሪር እውነታ ህሊናችንን ካላስጨነቀውና ዘላቂውን መፍትሄ አምጠን ለመውለድ የማያስችለን ከሆነ የሰብአዊ ፍጡር መሠረታዊ መብቶች አንዱ ስለሆነው ሃይማኖታዊ እምነት ነፃነት የምንሰብከው ስብከት እና የምናነበንበው ስብከተ ወንጌል  በእጅጉ ጎደሎ (ሽባ) ነው የሚሆነው ። አዎ! የገዛ ራሳችንን የውድቀትና የውርደት አባዜ በቀጥታና በአርበኝነት ወኔ መጋፈጥ ሲያቅተን ሰንካላ ሰበብ መደርደሩ ክፉ ልማድ ሆኖብን ነው እንጅ ተምሮ እንዳልተማረ በመሆን ላይ የሚገኘው (መማርን ለችግር መፍቻ መሳሪያነት ለማዋል የተሳነው) የህብረተሰብ ክፍልም ከእንዲህ አይነቱ መሪር የውድቀት አዙሪት ውስጥ እየጓጎጠ  እስከመቼና እስከየት ድረስ  መዝለቅ እንዳለበት ከምር ራሱን መጠየቅ አለበት።

ከሞት በኋላ ተስፋ ለምናደርው ህይወት ዋስትናው በዚች ምድር ላይ የምንሆነውና የምናደርገው (ቃልን/ ንድፈ ሃሳብን ከድርጊት ጋር የሚያዋህድ እኛነት/ ሰብአዊ ፍጡርነት) እንጅ የመቃብር ውስጥ ሙቶች ከሆን በኋላ የሚፈጠር ተአምር አይደለም። ለዚህ ደግሞ ታላቁን ሃላፊነትና ተጠያቂነት መሸከም ያለባቸው የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው ናቸው።

እውነተኛው አምላክ በሰጠው ረቂቅ አእምሮ እና ብቁ አካል እየታገዘ የተፈጠረበትን ዓላማና ሃላፊነት በአግባቡ የሚወጣና ለዚህም የእርሱን (የአምላክን) የተቀደሰ እርዳታ የሚጠይቅን ሰብአዊ ፍጡር እንጅ ድርጊት አልባ እግዚኦታን የስንፍናው ምሽግ (ሽፋን /መሸሸጊያ) እያደረገ ማቆሚያ በሌለው የውድቀት አዙሪት ውስጥ የሚጓጓጉጥ ሰብአዊ ፍጡር አልፈጠረም። አይፈጥርምም።

አዎ!  ከሌላው ፍጡር ሁሉ ተለይቶ በታላቅ ክብርና ለታላቅ ዓላማ የተፈጠረው የሰው ልጅ ማቆሚያ በሌለው የመከራና የውርደት አዙሪት ውስጥ ከመጓጎጥ እንዳይወጣ ያደረገው ራሱ እንጅ የፈጣሪ ቁጣ ወይም ያለመታደል ጉዳይ ሆኖበት አይደለም። በእውነት ስለ እውነት እየተነጋገርን ከሆነ የገዛ ራስን ልክ የሌለው የውድቀት አባዜ በፈጣሪ እያላከኩ (እያመካኙ) “እግዚኦ ካልወረድክ” ማለት የምር ከሆነ (በድርጊት ከታዘ) ፀሎትና ንስሃ ጋር ጨርሶ ዝምድና የለውም ። ለዘመናት የመጣንበትና አሁንም የቀጠልንበት እጅግ አስቀያሚውና መሪሩ እውነታ ይህ መሆኑን ከመካድ ወይም ለምን ተደፈርኩ በሚል ያዙኝና ልቀቁኝ ከማለት ይልቅ እያመመንም ቢሆን ተቀብለን ከአስከፊው አባዜ ሰብሮ ለመውጣት እልህ አስጨራሽ ጥረት ማድረግ ነው የሚሻለን።

እያልኩ ያለሁት የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው የፖለቲካ መስመሩን ጥሰው ይግቡ አይደለም።  እያልኩ ያለሁት በክርስቶስ አምሳል የተፈጠረውና ክቡር እንደሆነ የምናምንለት የሰው ልጅ በእኩያን ገዥ ቡድኖች ምክንያት በመኖርና ባለመኖር ወይም ሰው በመሆን ወይም ባለመሆን እጅግ ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንዲገኝ በተገደደበት በዚህ ወቅት ከምር በሆነ ቁጣ ነውር ነው ብቻ ሳይሆን በምድርም ሆነ በሰማይ ኅጢአት ነውና ወደ ህሊናችሁ ተመለሱ ለማለት ወኔው የከዳው የሃይማኖት መሪም ሆነ አስተማሪ ስለ ሃይማኖትና ስለሃይማኖታዊ እምነት ነፃ አውጭነትና አዳኝነት የሚሰብከው ስብከት ባዶ ስብከት ነውና ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል

ዘመን ጠገቡና አስከፊው የውድቀት አዙሪታችን የሚጀምረው በጎሳና በመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች የሚዘወረው እጅግ አስከፊ የመከራና የውርደት ሥርዓት ይበልጥ እየከፋ በሄደበት መሪር እውነታ ውስጥ እየጓጎጥን በፖለቲካ አያገባንም የሚል እጅግ ደምሳሳ ሰበብ መደርደር የጀመርን እለት ነው።

ከ27 ዓመቱ ህወሃት መራሹና ከአምስት  ዓመቱ እጅግ አሰቃቂ ኦህዴድ (ኦነግ) መራሹ አገዛዝ  ለመማርና የተሻለ ሥራ ሠርቶ ለመገኘት አለመቻል በእጅጉ አስከፊና አስደንጋጭ ነው። ይህ ደግሞ የፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው፣ የሰባኪያን እና የእኛም የምዕመናን መገለጫ ሲሆን በእጅጉ ያማል፧

ከክፉው አዙሪት ሰብረን መውጣት እንዳይሳካልን ካደረጉን ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ሃይማኖታዊ እምነት በራሱ የእኩያን ገዥዎችን ኢሰብአዊ ባህሪና ድርጊት የምንታገልበት አንደኛው መሣሪያ መሆን ሲገባው እንዲያውም ይባስ ብለን የሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ የጎሳ/የመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ተጠቂ (victim) የማድረጋችን መሪር እውነታ ነው።

እንከን አልባ አለመሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ዴሞክራሲ ማለት የብዙሃኑ ፍላጎትና መብት ገዥ የሚሆንበት፣ ነፃና ትክክለኛ የህዝብ ምርጫ የሚረጋገጥበት ፣ የጥቂቶቹ ፍላጎትና መብት የማይጨፈለቅበት፣ የፍትህና ርትዕ ሃያልነት የሚሰፍንበት (መሪ ሂዶ መሪ በተተካ ቁጥር የማይናወጠበት)፣ የሞራልና የሥነ ምግባር  እሴቶች ልእልና ለጊዜያዊ ጥቅምና ፍላጎት ቦታውን የማይለቅበት፣ መንፈሳዊ እሴት (spiritual value) በቁሳዊ ስግብግብነት የማይጎሳቆልበት፣ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበት ፣ እውነተኛ ፍቅር መስሎና አስመስሎ የመኖርን ክፉ  ደዌ የሚያሸንፍበት ፣ የሃላፊነትና የተጠያቂነት ወርቃማ መርህና ደንብ የሚረጋገጥበት ፣ፖለቲካ የእድገት ግሥጋሴ እንጅ የድህነትና የተመፅዋችነት ምክንያት የማይሆኔበት ፣ በእጅጉ ብጥስጥሱ የወጣው ትውልዳዊ ቅብብሎሽ በፅዕኑ መሠረት ላይ የሚቆምበትና በጠንካራ ሰንሰለት የሚተሳሰርበት፣ክፉ ገዥዎች በፖለቲካ ወለድ መርዛማ ፕሮፓጋንዳ ናላውን አዙረው የገዛ ወገኑን እንዲጨፈጭፍና እንዲያሳድድ ያደረገት ወጣት ትውልድ ዘላቂ ፈውስ የሚያገኝበት ፧ እንደ አብይ አሀመድ አይነት ጨካኝና ባለጌ ገዥዎች ፈጣሪን (እምላክን) ሳይቀር  የገዳይና አስገዳይ ፖለቲካቸው ተባባሪ የማድረጋቸው እጅግ አስከፊ ሁኔታ የሚያከትምበት ፣ ወዘተ ሥርዓት ማለት  ነው።

ይህ እውን እስኪሆን ግን የሃይማኖታዊ እምነት ነፃነት ብሎ ነገር አይኖርም ። ምክንያቱም መሠረታዊው የሰብዊና የዜግነት መብቶች በሴረኛ፣ ሸፍጠኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች በተደፈጠጡበትና በሚደፈጠጡበት እጅግ መሪር እውነታ ውስጥ የሚከበር አንዳችም አይነት ነፃነት፣ ፍትህ፣ መብትና እኩልነት አይኖርምና።

ይህንን ለመረዳት ደግሞ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እና የኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት መሪዎች የገቡበትን አስከፊ የፖለቲካና የሃይማኖት ድብልቅልቆሽ  ልብ ማለት በቂ ነው። በፖለቲከኞች ሸፍጠኝነት (hypocracy) ስንገረም የሃይማኖት መሪዎችም በዚሁ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሲጓጉጡ ለሚታዘብ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ሰው የሚያሳድረው የህሊና ህመም ከባድ ነው።

የነፃነትና የፍትህ ትግሉ እጅግ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ በራሱ የግል ዝና ፍለጋ ሱስ ህሊናው የተበከለ ፣ ውሸታም፣ ተራ አጭበርባሪ ፣ የሞራል ዝቃጭ፣ ፈሪና ፍፁም ጨካኝ በሆነው አብይ አህመድ የቅጥፈት አንደበት ተታለን  እንዲኮላሽ (እንዲጨነግፍ) ያደረግን እለት ነበር በራሳችን ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ መከራና ውርደት ያመጣነው ።

በእጅጉ የሚያሳዝነው ደግሞ አብይን “የዘመናቸን ሙሴ” ብለው ያንቆለጳጰሱት “በዚህ ዘመን የፈጣሪን ቃል በአሳሳች አንደበታቸው እየሰበኩ ሰውን የሚያስቱ ሰዎች አሉና ተጠንቀቁ“ እያሉ የሚሰብኩን የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች የመሆናቸው መሪር እውነት ነው። ዛሬም ከአምስት ዓመታት መሪር ተሞክሮ ከምር የተማሩ አለመሆናቸውን ናስተውል ከዘመን ጠገቡ የውድቀት አዙሪት እንዴትና መቼ ሰብረን እንደምንወጣ እንኳንስ ለማወቅ ለመገመትም ያስቸግራል።

ስለሆነም የሃይማኖት መሪዎቻችንና አስተማሪዎቻችን በፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ቀንበር ሥር እየማቀቀም ቢሆን ፈጣሪውን ተመስገን የሚለውን ህዝብ በእምነትህ ፅና የማለታቸው ተገቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ እራሳቸውም ንስሃ ገብተው ወደ ትክክለኛው የሃይማኖት መሪነትና አስተማሪነት ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ እንዲመለሱ በግልፅ፣ በቀጥታና በአክብሮት መንገር የግድ ነው። ከዚህ ውጭ ያለውን አላስፈላጊ የመሽኮርመምና እራስን አቅመ ቢስ የማድረግ ክፉ ልማድ ለዘመናት ሞክረነው ወድቀንበታልና ከአሁን በኋላ የውድቀቱን አስተሳሰብና አካሄድ መፀየፍና ደጋግሞ ላለመውደቅ እልህ አስጨራሽ ትግል ግድ ይለናል።

ለዘመናት ከዘለቀውና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተረኞች እጅግ አስከፊና አስፈሪ በሆነ ሁኔታ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከበሰበሰና ከከረፋ የእነ አብይ ፣ የእነ ሽመልስና የአሽከሮቻቸው የብአዴናዊያን  አገዛዝ በጎ የለውጥ ውጤት መጠበቅ ፍፁም የሆነ  የፖለቲካ ድንቁርና ፣የሞራል ዝቅጠት እና የመንፈሳዊ እሴት ውድቀት እንጅ ከቶም ሌላ ሊሆን አይችልምና ልብ ያለው ልብ ይበል!

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop