የሚፈርስ አገርና የሚበተን ሕዝብ እንዳይኖር እንትጋ (መላኩ አያለው)

#image_title

በአሁኑ ባለንበት ሁኔታ የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ ለልብ የሚያስተሳስሩ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረቱ፣ የሕዝብ አንድነተን የሚያበረታቱ ድርጊቶች የተዳከሙበት በአንጻሩ ደግሞ ያሉንና የነበሩንን የጋራ እሴቶች የሚቦረቡሩ ድርጊቶች የሰፈኑበት አካሄዶች ይታዩኛል። የርስ በርስ ጥላቻው እየጎላ ሁሉም በየጎጡ ለየጎጡ ብቻ የሚያስብ ሆኖ ለኢትዮጵያዊነት የሚሰጠው ክብርና ፍቅር እየተመናመነ እየሄደ እንደሆነ በተጨባጭ የሚታይ ነው። በተለይ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ፖለቲከኞች በጥላቻ ሲያናቆሩ ማየቴ አብሮ የመኖር ችግር ላይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደአገር የመቀጠሏ ሁኔታ አደጋ እንደተጋረጠበት ይታየኛል። አመራሩ በዚህ ግንዛቤና ትንታኔ እንደማይስማማና ሕብረ ብሔራዊ ወደሆነ አስተዳደር እየሄደ እንደሆነ ይናገራል። እኔ ግን ወደዜሮ ብዜት ፖለቲካ እንዳንገባ ከፍተኛ ስጋት አለኝ።

 

ከላይ እንደገለጽኩት አሁን ያለንበት ሁኔታ እጅግ አደገኛና አስፈሪ ይመስለኛል። እስከዛሬ ፖለቲካችን ‘ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ’ አይነት ለውጥ የማያመጣ መነካከስ ነበር። እስከዛሬ ድረስ ስለ ዜሮ ድምር ፖለቲካ ነበር የሚወራው። ዜሮን ከማንኛውም ቁጥር ጋር ብንደምረው ቁጥሩ አይለወጥም። የዜሮ ድምር ፖለቲካ ማለት ለውጥ የለሽ ወይም አዲስ ነገር የማያመጣ ፖለቲካ ማለት ነው። “ቢወቅጡት እምቦጭ” ወይም “ዞሮ ዞሮ መዝጊያው ጭራሮ” እንደ ማለት ነው። አሁን እየሄድንበት ያለው የፖለቲካ ጉዞ ደግሞ ወደ “ዜሮ ብዜት” ፖለቲካ የሚወስደን ይመስለኛል። ማንኛውም ቁጥር በዜሮ ከተባዛ ቁጥሩ ጠፍቶ ውጤቱ ዜሮ ነው የሚሆነው። ውጤቱ የነበረውን ማጥፋት ወይም ማፍረስ ነው።

 

በዚህ ወቅት ጥቂት የማይባሉ ፖለቲከኞች አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት ሃገሪቷን ወደዚህ አፍራሽ ፖለቲካ ሂደት እየመሯት ይመስለኛል። ደፍረው “ኢትዮጵያ የምትባል አገር አንፈልግም” ከሚሉ የለየላቸው ጉዶች በተጨማሪ ከኢትዮጵያ በፊት “ብሔሬ”/ዘውጌ ብለው ምድሯ በዘውግ ተሸንሽኖ ሕዝቦቿ በዘር ተቧድነው ትንንሽ መንደሮችን ይዘው ማዕከላዊ መንግሥቱን አዳክመው እንደ ዘመነ መሳፍንት ወቅት ለመኖር እየታገሉ ያሉ መንደርተኞች በርካቶች ናቸው።

 

ምንም እንኳን አሁን ያለው ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ቢመስልም ሁሉም ወደ ሰዋዊ አእምሮው ሊመለስ ይችላል የሚለው ተስፋየ አሁንም አልተበጠሰም። ስለሆነም ከዚህ ምስቅልቅልና አገሪቱን ወደማፈራረስ ካደረሰን ሁኔታ የምንወጣበት መንገድ አይኖርም ብየ አላስብም። የመውጫ በሩን ለማግኘት ችግሮቻችንን አስቀድሞ ማወቅ ለመፍትሄው ግኝት ቀዳሚ ስለሆነ ችግሮቻችንን በሚከተለው መልክ በአጭሩ ለመመልከት ሞክሬያለሁ።

 

በኔ አተያይ ድህነት መሰረታዊ ችግራችን ይመስለኛል። የብሄር ማንነት ጉዳይና ከሱ ጋር ተያይዘው የተከሰቱ የወስንና የመሬት ይገባኛል፣ የቋንቋና ባህል፣ የእኩልነት ጥያቄ፣ እንዲሁም የሥልጣን ጥያቄ ከዋና ዋና ችግሮቻችን ውስጥ ናቸው። በታሪክ አረዳድና በአገር ግንባታ ሂደት ላይ አለመግባብትቶች አሉ። በሕገመንግሥትና በሕግና ፍትህዙሪያም ክፍተቶች /ችግሮች አሉብን። በአስተዳደር ክልሎችና በፖለቲካ ድርጅቶች አደረጃጀት ያለው ሁኔታ ችግሮቻችንን አወሳሰበውብናል። የፓርቲና የመንግሥት ሚና መደበላለቅ፣ የሕግ ተርጓሚው ሚና በሕግ አስፈጻሚው ያለመከበር ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ልቅነት፣ የዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብ መሰናክል ሆነውብናል። ከዚህ በተጨማሪ የእድገት ማነቆና የህብረተሰብ ብልጽግና ነቀርሳ የሆነው ሙስና በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶና ሥር ሰዶ ሊጥለን እየገዘገዘን ይገኛል።

 

ችግሮች ብዙ ናቸው መፍትሄው ወደሰዋዊ ማንነት አቅጣጫ ማሰብ ነው። ቀናነት ካለ፣ ለሕዝብ ማሰብ ከልብ ከሆነ፣ አርቆ የመምልከት አስተሳሰብ ከተፈጠረ፣ በዴሞክራሲ መርህ ላይ ስምምነት ከተደረሰና እንደሰው ማሰብ ከተቻለ ቀላል ባይሆንም የመፍትሄው መንገድ የተዘጋ አይደለም። በመሆኑም በበኩሌ ለችግሮቻችን መፍትሄ ለማግኘት ያግዛሉ ያልኳቸውን ሀሳቦች በተለያዩ ርዕሶች ሥር ቀጥየ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ።

 

የምክክር፣ የመግባባትና የፖለቲካ ባህል ለውጥ ብሔራዊ ንቅናቄ ማካሄድ

ከሁሉ በፊት ሁሉም ቆም ብሎ እየሄድንበት ያለው ጎዳና ወዴት እየወሰደን እንደሆነ ሰከን ብሎ ማየት ያስፈልገናል። ከግጭት ይልቅ ፍቅር፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላም፣ ከመለያየት ይልቅ አብሮ በእኩልነት ላይ የተመሰረት አንድነት የሚሻል እንደሆነ ደግመን ደጋግመን በማሰብ ራሳችንን ማሳመን ያስፈልጋል። በአገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን ያልሞከርነውንና ያልሄድንበትን መንገድ እናስብ። ይህ የሚሆነው ደግሞ ግልጽ ውይይት አድርጎ ያሉትን ችግሮች ነቅሶ አውጥቶ ያለፉት ስህተቶች እንዳይደገሙ ቋጭቶ የወደፊቱን አቅጣጫ በመቀየስ ይመስለኛል። ይህ በተራ ውይይትና “በአንተም ተው አንተም ተው” አይነት ሽምግልና የሚከናወን ሳይሆን ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ አገራዊ ፕሮግራም ተቀርጾ በተለየ ሁኔት በሚካሄድ ብሔራዊ ንቅናቄ አማካኝነት መካሄድ ይኖርበት ይመስለኛል።

 

እኔ የሚመስለኝን ለመወርወር እንጂ በዚህ ጽሑፍ ከማቀርበው ሃሳብ ይልቅ በማህበረሰብ ጥናት ላይ የሰለጠኑ ባለሞያዎች የተሻሉ ሃሳቦችን ሊያመነጩ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ቢሆንም እንደ አንድ ኢትዮጵያን እንደሚወድ ዜጋ ያለኝን ሃስብ ለማካፈል እሞክራለሁ። የማቀርባቸው የመፍትሄ ሃሳቦች በአጠቃላይ በዚህ “የምክክር፣ የመግባባትና የፖለቲካ ባህል ለውጥ ብሔራዊ ንቅናቄ” (ካሁን በኋላ ብሔራዊ ንቅናቄ) የምለው አካል ሥር እንደሚከናወኑ ታሳቢ የተደረጉ ናቸው።

 

በማስበው “ብሔራዊ ንቅናቄ” አማካኝነት እንዲከናወኑ የማቀርባቸው ሓሳቦች በመደበኛ አሠራር የሚከናወኑ አይሆኑም። በአለው ሕገ መንግሥት ጥላ ሥርም የሚስተናገዱ አይመስለኝም። “የሽግግር ሕግ” ተዘጋችቶ በዚያ ማእቀፍ ሥር ካልተተገበሩ በስተቀር ተፈጻሚነታቸው አጠራጣሪ ይሆናል። አገሪቱ ካለችበት አደገኛ ሁኔታ ለመውጣት ለተወሰነ ጊዜ የመብት ገደብ የሚጥል የሽግግር ሕግ ያስፈልግ ይመስለኛል። የሽግግር ሕግ አላማ አገር አቀፋዊ የአመለካከት ለውጥ ለመፍጠር ያስችላል ብዬ ላሰብኩት “ብሔራዊ ንቅናቄ” ተግባራዊነት የሚያግዝ ይሆናል።

 

ብሔራዊ ንቅናቄው በሁልም ቅቡልነት ያለው አካልና አስተባባሪ ባለቤት ተፈጥሮለት፣ ታክቲክና እስትራተጅ ተነድፎለት፣ የጊዜ ሰሌዳም ወጥቶለት እንደ አንድ የሃገሪቱ ወሳኝ ፕሮግራም ተወስዶ መተግበር ይኖርበታል። የሃገሪቱ ተቋማት በሙል ትኩረት የሚሰጡት በተለይ ሚዲያው በሙሉ ዘምቻውን በስፋት ለማካሄድ የሚችሉበት አቅም አዳብረው የሚሠሩበት ሁኔታ ሊፈጠርላቸውና ግደታቸውም እንደሆነ መመሪያ ሊሰጣቸው ይገባል።

 

መንግሥት ያቋቋመው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህን ሥራ ቢያስተከዜሮ ከመጀመር ሊያድንና ወጭን ሊቀንስ ይችላል። ሆኖም ይህን ኮሚሽን የሚቃወሙና አካታች እንዳልሆነ፣ ተፎካካሪ ድርጅቶች አይወክለንም በሚሉት በመንግሥት ብቻ የተመረጡ ኮሚሽነሮች እንደሚመራ የሚገልጹ ወገኖች ሊሰሙ ይገባል። ሁሉም ወገን ፕሮግራሙን በቀና መንገድ ይጠቅማል እስካለ ድረስ የአደረጃጀት ጉዳይ ሊያራርቀን አይገብም። እንደገና ኮሚሽኑን አደራጅቶ በባለድርሻ አካላት ማለትም በሲቪል ተቋማት፣ በሕዝባዊ ድርጅቶች፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሃይማኖት ተቋማትና በሌችም የታመነባቸው ሰዎች እንዲጨመሩበትና ቅቡልነት እንዲያገኝ ተደርጎ ብሔራዊ ንቅናቄውን እንዲመራ ማድረግ ከባድ አይደለም፤ መሠረታዊ የመርህ ጥሰትም የሚኖረው አይመስለኝም። የውይይቱና የመግባባቱ ሂደት በፓርቲዎች ላይ ብቻ ማትኮር ሳይኖርበት የሕዝቡ ተሳትፎ የጎላ ማድረግ አለበት። እንዲያውም የብሔራዊ ንቅናቄው አስተባባሪ “ሕዝብ ለሕዝብ” የሚል እራሱን የቻለ አካል አደራጅቶ የአንዱ አካባቢ ሕዝብ ወደሌላው ሄዶ የሚወያይበት ቋሚና ተከታታይ መድረክ መፍጠር ይኖርበታል።

 

በዚህ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊከናወኑ ይገባቸዋል ያልኳቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ከማቅረቤ በፊት ሁኔታውን ሊያመቻቹ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትንሽ ማለት ፈለግሁ። የንቅናቄው አስተባባሪ የመጀመሪያ ሥራው ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አጠቃላይ መግባባት በመፍጠር ላይ ማትኮር አለበት የሚል ሀሳብ አለኝ። እነዚህን ወሳኝ ጥያቄዎችን በስድስት ከፍየ አይቻቸዋለሁ። ጥያቄዎቹ በአዎንታዊ መልክ ከተመለሱ ለመግባባት አስቸጋሪ አይሆንም።

 

በአገር ግንባታ ሂደት የተፈጠሩትን ችግሮች መርምሮ የታሪክ አረዳዳችንን በውይይት ለማቀራረብ ዝግጁ ነን ወይ?

የኢትዮጵያ ሕዝብ እኩልነትና ፍትሃዊነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ አንድ ሆኖ መኖር ይፈልጋል ወይስ አይፈልግም?

 

ይህቺ እኩልነትና ፍትሃዊነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ የሁላችንም የሆነች በጋራ የምንኖርባት፣ የክልል ወሰንና ቋንቋ ሳይገድበን በየትኛውም የሃገሪቷ ክፍል ውስጥ ያለምንም ገደብ የምንንቀሳቀስባትና የምንኖርባት አገር እንድትሆን እንፈልጋለን ወይ?

 

ለአገርና ለሕዝብ እድገትና ብልጽግና እንዲሁም የችግራችን ዋና መንሳኤ የሆነውን ድህነትን ለማስወገድ የምንችለው ተነጣጥለን ሳይሆን በጋራና በአንድነት መሆኑን እናምናለን ወይ? እስከዛሬ የሄድንበት የዘውግ ፌደሬሽን ያመጣልንንና ያመጣብንን ሁኔታዎች በሰከነና በቀና መንገድ ለመገምገም ዝግጁ ነን ወይ?

 

ማንኛውንም የሃሳብ ልዩነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመወሰን፣ በአብዛኛው ሕዝብ በተወሰነው ውሳኔም ለመገዛት ራሳችንን አዘጋጅተናል ወይ?

የሚሉት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መወያየትና መተማመን ከተቻለ በኔ እምነት ሌሎች የአካሄድ ጉዳዮች ስለሆኑ ወደ ጋራ አመለካከት ላይ ለመድረስ ብዙም አስቸጋሪ አይመስለኝም። በመጀመሪያው ምዕራፍ/ዙር ላይ ስለንቅናቄው አላማ፣ ስለሚጠበቅው ውጤትና ስለአካሄዱ ሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ነው። ሊያሰሩ የማይችሉ መደበኛ ሕጎች አስቀድሞ ሊለዩና ለንቅናቄው እንቅፋት በሚፈጥሩ አሠራሮች ላይ ገደብ ማድረግ ካስፈለገ ገደብ ሊደረግባቸው የሚገቡትን ዘርፎች መለየት ያስፈልጋል። በዚሁ ዙር ላይ የሃሳብ ማሰባሰብ ሥራ በስፋት ይከናወናል። የሚመጡ ሃሳቦች ትክክል ናቸው አይደሉም በሚለው ላይ ማትኮር ሳይሆን ከላይ በቀረቡትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ነጻ የሕዝብ አስተያየት ማሰባሰብ ያስፈልጋል። የማንም ሃሳብ መናቅና መንቋሸሽ ሳይኖርበት ሃሰቡ በተግባር እንዴት እንደሚሠራና በምን ሁኔታ የተሻለ እንደሚሆን ራሱ የሃሳቡ አመንጭው እንዲያብራራ ዕድል የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል።

 

የሁለተኛው ዙር በእያንዳንዱ ሰው ወይም ቡድን የቀረቡ ሃሳቦችን አጠናክሮ በየዘርፉ ለይቶና አቀናጅቶ ማቅረብና በሃሳቦቹ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ሰፊ ውይይት ማካሄድ ነው። ይህ ውይይት በስፋትና እንደአስፈላጊነቱም በተደጋጋሚና በተከታታይ የሚካሄድ ሆኖ በጥንቃቄና በብልሃት የሚከናወን ነው። በዚህ ዙር የሚደረገው ውይይት ንቅናቄውን ከሚያስተባብረው አካል ውጭ በሚቀጠሩ ወይም ፈቃደኛ በሆኑ፣ የማወያየት ልምድ ባላቸው ገለልተኛ ባለሞያዎች አወያይነት እንዲደርግ ማድረጉ የተሻለ ነው። በዚህ የውይይት ጊዜ ነጥረው የሚወጡ ሃሳቦች በጥንቃቄ የሚገመገሙበትና የንቅናቄውን አቅጣጫ የሚወስኑ ይሆናሉ።

 

የሦስተኛው ዙር ውይይት ደግሞ በአጠቃልይ መግባባት (consensus) የተደረሰባቸውን ለይቶ ማውጣትና ከነሱ ጋር የሚሄድ ሃሳብ ካለ ለማጣጣም መሞከር ነው። መግባባት የተደረሰባቸውን ተቀብሎ መግባባት ያልተቻለባቸውን ለይቶ በማውጣት መፍትሄ የሚያገኙበትን ስልት መጠቀም ይሆናል። መግባባት ያልተደረስባቸውን በሁለት መልክ መፍታት ይቻላል። በተወሰኑት ላይ የድምጽ ብልጫ እያሰጡ በመሄድ በአገር ደረጃ የበለጠ ድምጽ ያገኙ ሃሳቦች ተቀባይ የሚሆኑበት ይሆናል። ሌሎች በድምጽ ብልጫ የማይወሰኑ ወሳኝ የሆኑ ሃሳቦች ደግሞ ሕዝበ ውሳኔ የሚካሄድባቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

 

የብሔራዊ ንቅናቄው ዓላማ የሃሰት ትርክትን በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመርኩዞ ማጥራት፤ ሕዝቡ አብሮ ለዘመናት የኖረበትን “የተሻለ” ጊዜ ማሳየትና ስሕተቶችን በግልጽ አውጥቶ ዳግም እንዳይከሰቱ ማድረግ፤ የሕዝቦችን አብሮ የመኖር ጠቀሜታ የሚያጎሉ ውይይቶችን ያለማቋረጥ በተከታታይ በማድረግ የአብሮነት ሀሳብ በሕዝቡ አእምሮ ማስረጽ ይሆናል። ዘመቻውን የሚያግዙና የሚያፋጥኑ ድርጊቶችን የሚያበረታቱና ሰላማዊ አካሄድን የሚሹ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ጥላቻን፣ መለያየትንና የሴራ ፖለቲካ ውስጥ የሚዳክሩትን ሃይ የሚያሰኝና ወቅቱን የሚመጥን “የሽግግር ሕግ” ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል። አገራችን እጅግ በጣም አስጊ በሆነ ሁኔታ ላይ ስለምትገኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባይታወጅም እንኳን ሁኔታው እስኪለወጥ ድረስ የመብት ገደቦችን አስቀምጦ ሊሰራ የሚችል ጊየሽግግር ህግ ያስፈልግ ይመስለኛል። የሚወጣው ሽግግር ሕግ መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶችን በምንም መልኩ የሚጻር መሆን አይኖርበትም። የሽግግር ሕጉ በማናቸውም ደረጃ ጥላቻን፣ አመጸን፣ ስድብንና መከፋፈልን የሚያበረታቱ፣ የሀገርን ደህንነት የሚጎዱ መረጃዎችንና ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ላይ አገርን ከመፍረስ ለማዳን ሲባል ቁጥጥር ማድረግ የግድ ነው። ይህ ሕግ ባለው መንግሥት የሚተገበር ሳይሆን የብሔራዊ ንቅናቄውን በሚያስተባብረው አካል ባለቤትነት ሥራ ላይ የሚውልበት መንገድ ሊኖር ይገባል። ገደብ ያለው ሕግ ዝርዝሩና አፈጻጸሙ በሕግ ባለሞያዎች የሚታይና የሚወሰን ስለሚሆን ጉዳት የማያስከትል ውጤት ያመጣል የሚል ግምት አለኝ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ ወዴት? ዘረኝነት: ተረኝነትና ስርዐት አልበኝነት!!! - ሃይለገብረኤል አስረስ

 

ባሉን ልዩነቶች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ታሳቢ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በሚከተለው መልክ አቅርቤያቸዋለሁ።

 

ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች ላይ ትኩረት መስጠት

2.1 የታሪክ አረዳድና የአገር ግንባታን በሚመለከት፣

ስለታሪክ ብዙም የማውቀው ነገር ባይኖረኝም አንድ አገርና ሕዝብ ያለፈበትን ኢኮኖማዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ስነልቦናዊ ሂደቶችን የሚጠቅስ ማስታወሻ እንደሆነ እረዳዋለሁ። ታሪክ ወደኋላ ተሂዶ እንደገና የማይሠራ ያበቃለት የድርጊት መዘክር ነው፤ አሁን ለምንሠራው መነሻ የሆነን ለወደፊቱም መማሪያ የሚሆነን ያለፈ ሕይወታችን መገለጫ ይመስለኛል። ከኋላ የነበረን አሁን ካለንበት ጋር የተሳሰረ የወደፊቱንም ለማለም አጋዢ የሚሆነን ግብዓትና እሴት ነው። ታሪክ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚተላለፍ ሂደት ቢሆንም አንድ ትውልድ ከሱ በፊት ያለፈው ትውልድ ለሠራው ተጠያቂ የሚሆንበት፣ ላልኖረበት ቤት ኪራይ የሚታሰብበት፣ ላልፈጸመው ጥፋት ካሳ የሚከፍልበት አግባብ ሊኖር አይገባም። ስለሆነም ታሪክን ስንገመግም በወቅቱ በነበረው የአመለካከት ደረጃ ታሪኩን የሠሩትን እንጂ የታሪክ ሠሪዎቹ ልጆችና የልጅ ልጆች ላይ ሊተኮር አይገባም።

 

ታሪክ በገዢዎች ወይም በአሸናፊዎች ይጻፋል ስለሚባል በተአማኒነቱ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች ቢኖሩም የታሪክ ባለሞያዎች ከሌሎች ኩነቶች ጋር በማመሳከር የታሪኩን እውነተኛነት የሚያረጋግጡበት ዘዴ እንዳላቸው ይናገራሉ። የኛ ችግር ታሪክን ለታሪክ ተመራማሪ ምሁራን መተው ሲገባን ሁላችንም የማህበራዊ አንቂዎችና የፖለቲከኞች መሳሪያ በመሆን በተጣመመ ታሪክ ላይ ቂም አርግዘን በቀል ለመውለድ ስንጥር እንታያለን።

 

ከታሪክ አረዳድ በተጨማሪ ስለአገር ግንባታ ያለንን ግንዛቤም ማስታረቅ ያስፈልጋል። በሃገር ምስረታ ሂደት ውስጥ የሚሠሩ ስህተቶች በሌሎች አገራትም የተፈጸሙ ስለሆነ ከሌሎች ልምድና ትምህርት ወስደን መግባባት ላይ መድረስ እንችላለን። በብሔራዊ ንቅናቄው አስተባባሪ አካል ሥር የታሪክ ምሁራንን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና አባገዳዎችን፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ ምርምር ያደረጉ የውጭ አገር ተመራማሪዎችን ያካተተ ፎረም ተፈጥሮና ጥናት ተደርጎ በሚመጣው ውጤት ላይ በመመስረት የታሪክ አረዳዳችን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊስተካከል ይገባዋል። ታሪኩን ለታሪክ ባለሞያዎች ስጥተን እነሱ የተስማሙበትን የመጨረሻ መግባቢያችን አድርገን ለመቀበል ፈቃደኛና ዝግጁ መሆን ይገባናል።

 

2.2 የማንነት ጉዳይን በሚመለከት፣

በአሁኑ ጊዜ ዋናው ችግራችን በዘውግ ፖለቲካ ዙሪያ የሚሽከረከር ነው። ከዘውግ ማንነት በተጨማሪ በርካታ ማንነቶች አሉ። የግጭት ምክንያት ግን ሊሆኑ አይገባቸውም።ሆኖም እያንዳንዱ ሰው ማንነቱን የመቀበልና ያለመቀበል፣ በዚያ የመታወቅና ያለመታወቅ መብቱ የራሱ የግለሰቡ ውሳኔ ብቻ ነው። ሆኖም በአገራችን በማንነት ጥያቄ አፈታት ላይ የየዘውጉ/”የየብሄሩ” ልሂቃን የተለያየ አቋም በመያዛቸው ችግሩ ውስብስብና የሃገሪቱ አይነተኛ የግጭት መነሻ ሆኖ ይገኛል። የተወሰነው ኢትዮጵያዊ በማርክሳዊ ፍልስፍና የተሰጠውን ትርጉም በሊበራል የፖለቲካ ፍልስፍና ውስጥ አጣጥሞ ሊያየውና መፍትሄ ሊስጠው ይሞክራል። የተቀረው ደግሞ በምዕራቡ ዓለም የተሰጠውን ትርጓሜ ወስዶ መፍትሄ ይሻል። በኛ ሁኔታ የዘውግ ማንነት ጥያቄ ባደረጃጀትና አብሮ በመኖር ጥያቄ ዙሪያ እየተከሰተ ከባድ የህልውና ተግዳሮት ፈጥሯል።

 

ድህነቱ፣ ኋላ ቀርነቱ፣ የውጭ ጠላቶቻችን ሴራ፣ የፖለቲካ ንቃተ ህሊናችን ዝቅተኛነት፣ ወዘተ እንዳለ ሆኖ የሃገሪቱ ችግሮች ዋናው ማጠንጠኛ የማንነት ጉዳይ ሆኖ ወጥቷል። ከሌሎች ማንነቶች በተለይም ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ማንነቶች ጋር ተያይዞ ግጭቶች ቢከሰቱም ለነሱ መነሳትም ምክንያት ወይም ቆስቋሽ የሆነው የዘውግ ፖለቲካ እየሆነ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል። ከጠባብ ዘውገኝነት በተጸራሪ ትምክህተኞችም ሌላ ችግር ፈጣሪዎች ናቸው። “ እኔ እንዲህ ነኝ/ነበርኩ” እያሉ በፈነዳ ኳስ ሊጫወቱ የሚፈልጉ አሉ። በአሁኑ ጊዜ ማንነትን የማያከብር፣ እኩልነትን የማይቀበል ግለሰብ ወይም የፖለቲካ ድርጅት ካለ የመሸበት ይመስለኛል ። ይህ ማለት በይፋ በመድረክ ላይ ባይወጡም የትምክህተኛነት አመለካከት ገና ያለቀቃቸው ሰዎች አይኖሩም ማለት አይቻልም። የሚረጩትም የትምክህተኛነት መርዝ የዘውገኝነትን ዓላማ ለሚያራምዱ ጠባቦች አመች መንገድ እየቀየሱላቸው እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

 

ዘውገኝነት/ “ብሄረትኝነት” ወገንተኛነት ባህሪ ስላለው የራሱን ዘውግ ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ ሲል የአገርን ሉአላዊነትና የሕዝቦችን አንድነት አሳልፎ ሊስጥ ይችላል። በአንጻሩ የዜግነት ማንነት ላይ ብቻ አትኩረው የዘውግ ማንነትን እንዳላስፈላጊ የሚያዩ የግዛት ሉአላዊነትንና የሕዝብን አንድነት ለማረጋገጥ ሲሉ የዘውግ ማንነትን ሊጨፈልቁ ይችላሉ። ሁለቱም አመለካከቶች ዋልታ ረገጥና ጤናማ ያልሆኑ አስተሳሰቦች ናቸው። የዘውግ ማንነትን በአግባቡ ለማስተናገድ ቀናነት ብቻ ሳይሆን ዘመን ተሻግሮ መመልከትን፣ የሌላውን ህመም በራስ ጫማ ውስጥ ከቶ ማየትንና ሰው መሆንን ይጠይቃል። ከዘውግ ፖለቲካ ለመውጣት ብዙ ማሰብ፣ መወያየት፣ የተለያዩ ሕዝቦችን ተሞክሮ ለማወቅ ያላሰለስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ዓለም ወዴት እየሄደ እንደሆነ መገንዘብና ራቅ አድርጎ ማየትን ይጠይቃል። ከጠባብ ይልቅ ሰፊ የሆነ አገር፣ ከጥቂት የሕዝብ ቁጥር የበለጠ በርካታ የሕዝብ ቁጥር ያለው አገር በብዙ ነገር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መገንዘብብ ያስፈልጋል።

 

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚፈልጉት ማንነታቸው ታውቆላቸው፣ ባህላቸውና ቋቋቸው ተከብሮላቸው፣ ለልማት አስፈላጊ የሆነው ሰላም ተፈጥሮላቸው በዕኩልነት አብሮ መኖርን ነው። ከዚያ መለስ ያለው የሥልጣን ፈላጊዎች አጀንዳ ነው ። ሃቀኛ የሆኑና የየዘውጋቸው አባላት በደል ተሰምቷቸው ጥያቄውን በቀና መልክ የሚያነሱ የሉም ማለት አልችልም። ጭቆና እስካለ ድረስ ፍትህና እኩልነትን ለማስፈን ትግል መኖር አለበት ። የትግሉ አካሄድ ግን ለሕዝቡ ሰላምና ጥቅም የሚያስገኝ መሆን አለበት። ይህም እኩልነትን አስከብሮ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ መኖር እንጂ ታሪክን በተዛባ መልኩ እየጠቀሱ ወደኋላ መጎተት አስፈላጊ አይሆንም።

 

በናይጀሪያ የግጭቶችን መነሻና መከላከያ ለማወቅ በተደረገ ጥናት ላይ ተሳትፌያለሁ። የሃይማኖት፣ የዘውግና የፖለቲካ ማንነቶች እየተቀላቀሉ በተፈጥሮ ሀብቷ በተለይም በነዳጅ ምርቷ ተጠቅማ በቀላሉ ልትበልጽግ የምትችለው ናይጀሪያ ሕዝቦቿ በድህነት አሮንቃ ሲማቅቁ ታዝቤያለሁ። በአንጻሩ ለተመሳሳይ ሥራ በሄድኩባቸው እንደ ሩዋንዳና ሞዛምቢክ ያሉ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የጎሳ/የዘውግ ማንነትን ቢቀበሉም ከአገራዊ ወይም ከዜግነት ማንነት በላይ ሆኖ እንዳይታይ አድርገዋል። በተለይ ሩዋንዳ በዘውግ ማንነት ምክንያት ከፍተኛ እልቂት ካስተናገደች በኋላ “ሁቱ ነኝ” ወይም “ቱትሲ ነኝ” ከማለት ይልቅ “ሩዋንዳዊ ነኝ” የሚለው ማንነት በሕጋዊ አግባብ ይሁን በአስተዳደራዊ እርምጃ መወሰኑን ባላስታውሰውም የዜግነት ማንነት ጎልቶና ገኖ እንዲወጣና የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርገዋል። በዜግነት ማንነት ላይ ባደረጉት ትኩረትና በወሰዱዋቸው እርምጃዎች ያገኙት ውጤት ጠቃሚነቱን ተረድቻለሁ። ሩዋንዳ በአሁኑ ጊዜ በእድገት ጎዳና ላይ ከሚጓዙት ታዳጊ አገሮች አንዷ እንደሆነች ይነገራል። እ ኤ አ በ1998 ለሥራ ሩዋንዳ በሄድኩበት ወቅት የነበረውና ዛሬ የምሰማው የዘውግ አመለካከት እንደተቀየረ ተረድቻለሁ። ከሩዋንዳ ትምህርት መውሰድ ይኖርብናል፤ የሕዝብ ለሕዝብ ጭፍጨፋውን ብቻ ሳይሆን ዳግመኛ ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይከሰት እየወሰዱት ካሉት የመፍትሄ እርምጃም ብንማር ጠቃሚ ነው እላለሁ ።

 

 

2.3 የቋንቋና የዘውግ ቁርኝትን በሚመለከት፣

በቀላል አነጋገር ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ ነው። ሰዎች ከምልክት ቋንቋ ወጥተው ትርጉም ያለው ሥራን በጋራ ለመሥራት ወይም ፍላጎትንና ስሜትን ለሌላው ለመግለጽ የፈጠሩት መሳሪያ አድርጌ አየዋለሁ። በብዙ አገሮች ቋንቋን የማንነታቸው መገለጫና የባህላቸው አንዱ አካል እንደሆነ ይቆጥሩታል። ይህ በተለይ ባልዳበሩ አገሮች እውነትነት ያለው ቢሆንም አሁን በደረስንበት ደረጃ የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ዓለም ሁሉን ነገር እያስተሳሰረውና ተራርቀው የነበሩ ሕዝቦችን በቴክኖሎጅ እያቀራረበ ባለበት ደረጃ ቋንቋ የአንድ ሀገር ሕዝብ ማንነት መገለጫ መሆኑ እያከተመ የሚሄድ ነው። እንግሊዝኛ የእንግሊዞች፣ ፈረንሳይኛ የፈረንሳዮች፣ ቻይንኛም የቻይኖች መገለጫ መሆኑ እየቀረ ሌላውም ሕዝብ የሚግባባበት እየሆነ መጥቷል። ይህም የቋንቋና “የብሔር”/የዘውግ ቁርኝት የሚዳከም መሆኑን ያሳያል ።

 

ይሁን እንጂ በእኛና በሌሎች ታዳጊ አገሮች ዘውግና ቋንቋ እንደተሳሰሩ ይገኛሉ። “ብሔር ብሔረሰቦች” ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ለማሳደግ ከፈለጉ እገዛ እንጂ ውግዘት አያስፈልጋቸውም። እኔ እንደግለሰብ አሁን ያለውን ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) አካሄድ ተረድቶ ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም አገር ሄደው ለመስራት የሚያስችላቸው ቋንቋዎች ላይ ትኩረት መስጠቱ የተሻላ ይመስለኛል።

 

2.4 የሥልጣን ጥያቄንና የሕዝብ ፍላጎትን በሚመለከት፣

ሕዝብ እንደሕዝብ ሥልጣን ላይ አይወጣም። ሕዝብ የመረጠው የፖለቲካ ፓርቲ ሥልጣን ይይዛል። በሕዝቡ ይሁንታ የተመሠረተ መንግሥት ሲሆን ሕዝባዊ መንግሥት ይሆናል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊደርሱበት የሚፈልጉት ግብ ሥልጣን ይዞ ለሕዝብ ይጠቅማል ያሉትን ፕሮግራማቸውን በሥራ ላይ ለማዋል እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ ጤናማ አካሄድ ነው። ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚያ ካሰቡበት ግብ ለመድረስ የሚሄዱበት መንገድ ግን አጠያያቂ ይሆናል። የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘትና ለመመረጥ የማይፈጽሙትን ቃል ይገባሉ፤ ደጋፊዎቻቸው የሌለ በደል እንደተበደሉ በማስመሰል ይሰብካሉ፤ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ለማጥላላት ሴራ ይጎነጉናሉ፤ የማይሆንላቸው ከመሰላቸው ደግሞ በሕዝቡ ውስጥ አመጽ ያስነሳሉ።

 

በተለይ በታዳጊ አገሮች ይበልጥም አንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ሥልጣን የሃብት ምንጭ ሆኗል። ሰርቶ ከሚያገኘው በሥልጣኑ ዘርፎ የሚወስደው የበዛ ነው። ታዲያ ድብቁና በይፋ የማይነገረው የፖለቲከኞች ፍላጎት ይፋ ሆኖ ከተወዳደሩበትና ለሕዝቡ ጠቃሚ ነው ብለው ሥልጣን ከያዙበት ግብ የበለጠ የራሳቸውንና የዘመዶቻቸውን ኪስ ለመሙላት የሚያደርጉት ተግባር አመዝኖ ይተገበራል።

 

ይህ በቀላሉ በአለውና በተለመደው አሠራር የሚስተካከል ስለማይሆን በብሔራዊ ንቅናቄው ሂደት ለየት ያለ አሠራር መፍጠር ያስፈልጋል። በዘላቂነት የሚስተካከለውም ፓርላማው የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ተውዳድረው የሚገቡበት አካል እንዲሆን ማድረግ ቢሆንም ለጊዜው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ሹመታቸውን ላጸደቀላቸው አስፈጻሚ ባለስልጣኖች ለሚፈጽሙት ድርጊት ፓርላማው በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆንበት ለየት ያለና ጠበቅ ያለ ጊዜያዊ ሕግ ሊደነገግ ይገባል። ቢያንስ ብሔራዊ ንቅናቄው ሥራ ላይ ባለበት ወቅት ብቃት የሌላቸውን ባለስልጣናት የሚያቀርቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ስሕተት በይፋ ለሕዝብ በመግልጽና በማሳወቅ ሌሎች ተተኪ እጩዎችን እንዲያቀርቡ በማድረግ ሃላፊነታቸውን ያልተውጡትን ሃላፊዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፓርላማው ከስልጣናቸው ሊያነሳቸው የሚችልበት መንገድ መፈጠር አለበት።

 

የፓርላማ አባላት ወደ መረጣቸው ሕዝብ ቢያንስ በየሦስት ወሩ ሄደው የሚገመገሙበት አሠራር በተለየ መልክ መዘጋጀት አለበት። ግምገማው ተወካዮቹ በሕዝብ ፊት ቀርበው የሠሩትን ሪፖርት ካደረጉና ለሕዝቡ ጥያቄ መልስ ከሰጡ በኋላ ከሕዝቡ የተመረጠ ሕዝባዊ ሸንጎ ለብቻው ተወያይቶ የሚጠበቅበትን በአግባቡ ያልተወጣውን ተወካይ ውክልናው እንዲነሳ ማድረግ የሚችልበት ቢያንስ በጊዜያዊነት የሚሠራ ሕግ ሊኖር ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “አንተ የኔ ጀግና ነህ፡፡ ብትሞትም በእውነትህ ኮርተህ ሙት!” ሰርካለም ፋሲል

 

በአደረጃጀት ጉዳዮች ላይ መስማማት

3.1. የሕገ መንግሥት ጉዳይን በሚመለከት፣

ሌላው ችግር ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተያያዘ ነው። ሕወኀት ባደራጀው ፓርላማ በ 1987 የጸደቀው ሕገ መንግሥት አይወክለንም የሚሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች አሉ። አገሪቱ አሁን ከደረሰችበት ምስቅልቅል ውስጥ የገባችው በዚህ ሕገመንግሥት እንደሆነና ከተጋረጠብን ችግር መውጫ መንገዱ ሕገ መንግሥቱን መቀየር፣ የዘውግ ፖለቲካን ማስወገድ እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚከራከሩ አሉ። ዘውግን ማጥፋት ሳይሆን ዘውገኝነትን ከላቀው የዜግነት ማንነት ሥር ተከብሮ እንዲኖር የሚያደርግ ሕገ መንግሥት መቅረጽ አስፈላጊ ይሆናል።

 

እንዲህ አይነት የከረረ ተቃውሞ ከተወሰነ የሕዝብ ክፍል ከመጣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንደገና ሊታይ ይገባል እንጂ ሕገ መንግሥቱን አይነኬ አድርጎ በመውሰድ “ምን ሲደረግ” ወይም ቀደም ብለው ሲሉት እንደነበረው “ሕገ መንግስቱ የሚቀየረው በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ነው” ብሎ ወደ ግጭት መሄድ አስፈላጊ አይደለም። በዘውግ የሚደራጅ የፖለቲካ ፓርቲ በሕግ ሊገደብ ይገባል። በሌሎች አፍሪካ አገሮች የሠራ እኛ አገር የማይሠራበት ምክንያት አይታየኝም። ሁሉም የሃገሪቱ ሕዝብ በአንድ ድምጽ የሚስማማበት ሕገ መንግሥት ላይኖር ይችላል። በተለይ የዘውግ ፖለቲካን የሙጥኝ ብለው ተደራጅተው እየሠሩ ያሉ ድርጅቶች በርካታ በሆኑበት በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግስት መቀየር ከባድ ሊሆን ይችላል።

 

ሕገ መንግሥት የመቀየሩ ሂደት አስቸጋሪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የብሔራዊ ንቅናቄው በሚገባ ከተካሄደ ከባዱ ጉዳይ ቀላል ሊሆን ይችላላ። በሚካሄደው የምክክርና መግባባት ብሔራዊ ንቅናቄ በዴሞክራሲ የሚያምን ሕብረተሰብ መፍጠር ከተቻለ በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዝ አስቸጋሪ አይሆንም። በድርጅቶች ደረጃ በውይይትና በድምጽ ብልጫ መወሰን ካልተቻለ ሕዝቡ እንዲወስን ሪፈረንደም ማካሄድና ከዚያም የሕዝቡን ውሳኔ ማክበር ነው።በኔ አመለካከት የሚቀጥለው ሕገ መንግሥት አወዛጋቢ የሆኑ አንቀጾች ተስተካክለው ኢትዮጵያ የመላው ኢትዮጵያውያን አገር መሆኗን የሚያረጋግጥ፣ አብሮ የመኖርን ስሜት እንጂ የመለያየትን መንፈስ የማይፈጥር ሕገ መንግሥት ሆኖ አብዛኛውን ሕዝብ የሚያግባባ እንዲሆን እፈልጋለሁ።

ይህ የኔ ሃሳብ ቢኖርም በአንዳንድ የሕገ መንግስቱ አንቀጾች ላይ መሻሻል እንዳይደርግበት አስቀድሞ በራሱ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተሠራ ሥራ አለ። ለምሳሌ አይነኩም በተባሉት አንቀጾች ላይ ሁሉም ክልል ተስማምቶ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አኳያ አነስተኛ ሕዝብ ያለው የሃረሬ ክልል ብቻ ባይስማማ ማሻሻል አይቻልም። ስለሆነም የተሻለ የሚሆነው ሕገ መንግሥቱን እንደአዲስ መጻፍና አሁን ካለው ሕገ መንግሥት ጠቃሚ የሆኑትን በአዲሱ ውስጥ ማካተት የተሻለ ይመስለኛል። በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የሚሻሻልበት ሕግ እንጂ እንደ አዲስ የሚቀየርበት ሁኔታ ላይ የሕግ ገደብ አላስቀመጠም።

 

 

3.2 የወሰንና የይዞታ ይገባኛል ጉዳይ

አገሪቱ እንደ ዘመነ መሳፍንት በጎጥ ከተከፋፈለች በኋላ የመሬት ሽሚያና የይዞታ ማስፋፋት አይነተኛ መወዛገቢያ ሆነ። በትግራይና በአማራ፣ በትግራይና በአፋር፣ በአማራና በአፋር፣ በአማራና በኦሮሚያ፣ በአማራና በቤንሻንጉል፣ በኦሮሞና በጋምቤላ፣ በኦሮሞና በቤንሻንጉል በኦሮሞና በሶማሌ፣ በሶማሌና በአፋር እንዲሁም በሌሎችም ‘ብሔር ብሔረስቦች” መካከል የወሰንና የመሬት ይገባኛል ጥያቄ የማይቋረጥና መፍትሄ የሌለው ችግር ሆኗል። ኢትዮጵያዊነት ሲላላ ጎጠኝነት የበላይነቱን ሲይዝ የሚሆነው ይኼው ነው። በኢትዮጵያዊነት የበላይነት ካሰብን የዘውግ መብቶቻችን ከተከበሩ ሁሉም የኢትዮጵያ ሃብት የሁላችንም በመሆኑ የምንጋጭበት ነገር አይኖርም።

 

ወልቃይትን፣ ራያን ማን የአማራ ወይም የትግራይ አደረገው። ወልቃይት ምስራቅ ጫፍ ያለው የሱማሌው፣ ደቡብ ጫፍ ያለው የሃመሩ ተወላጅ ቦታም ጭምር እንጂ የተወሰኑ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ አይደለም። ሌሎችም አወዛጋቢ ይዞታዎች እንዲሁ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ እውቅና መስጠትና ማንም ዜጋ በፈለገበት የሃገሪቱ ክፍል ኑሮውን የመመስረት፣ ንብረት የማፍራት የዜግነት መብቱ ስለሆነ ከልካይ እንዳይኖር በሕግ ብቻ ሳይሆን በተግባርም መረጋገጥ አለበት ።

 

የአዲስ አበባ ጉዳይም ሌላው የልዩነት ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል። አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን ሁሉም ያገባዋል። ሁሉም አዲስ አበባ የኔ ናት ሳይሆን የሁላችንም ናት ብሎ የኦሮሞና የአማራን ንትርክ መቃወም አለበት። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና ከመሆኗም በላይ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ናት ። የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ዋና ጽ/ቤቶች የሚገኙባት ናት። ታዲያ ወደ አዲስ አበባ አትገቡም ብሎ መንገድ መዝጋት ከተማዋ የከልካዩ ብቻ እንደሆነች አድርጎ ከማሰብ የመነጨ እንደሆነ ግልጽ ነው።

 

ሥጋት አለ ከተባለና የጸጥታ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ በቂ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም። ለአመጽ ወደ አዲስ አበባ መግባት የፈለገ በአይሮፕላን፣ በግር እና በሌሎች ዘዴዎችም መግባት አልተከለከለም። የተከለከሉት በዋና መንገዶች በመኪና የሚገቡት ናቸው ። የስጋት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ የሚያሳብቁ ሌሎች ድርጊቶች ሲፈጸሙ ይታያሉ። ለምሳሌ ዘውግ ተኮር የሆነ ቤት ማፍረስ ሥራ ይካሄዳል። ሕገ ወጥ የሆኑ ግንባታዎች አይፍረሱ ማለት ባይቻልም ገዝተው መኖሪያቸውን በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ያደረጉ ካርታ ያላቸው ሕጋዊ ዜጎች ቤቶቻቸው በላያቸው ላይ ሲፈርስባቸው፣ ንብረታቸው ሲበላሽባቸው ተስተውሏል። ሌሎች ጉዳዮችንም መጥቀስ ይቻላል። በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ጉዳይ በብሄራዊው ንቅናቄው በሚካሄደው ሰፊ ውይይት በቂ ግንዛቤ በመፍጠር የሚረግብ ይመስለኛል።

 

3.3 የክላስተርና ያልተማከለ አስተዳደር አደረጃጀት

ምንም እንኳን ሀሳቡን የሚቃወሙ ሰዎች ቢኖሩም የክላስተርን አደረጃጀት በኔ በኩል በአወንታዊ መልኩ አይቸው ነበር። መንግሥት እኔ ባየሁበት መልክ ይየው አይየው ባላውቅም። መሪዎቻችን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እያሉ የሚናገሩትን ሃሳብ ወስጄ የተለያዩ “ብሔር”/ዘውግ ያላቸውን አካባቢዎች በአንድ ላይ አደራጅቶ አብረው እንዲኖሩ ማድረግ የዘውግ ፌደራሊዝምን ለማስወገድ የመጀመሪያ የመፍትሔ እርምጃ አድርጌ ወሰድኩት ። ለምሳሌ በደቡብ ምዕራብ ክልል የተሰባሰቡት የተለያየ ዘውግና የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ናቸው። በደቡብ ኢትዮጵያም በክላስተር የተደራጁት እንዲሁ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሉበት ነው።

ደቡብ ኢትዮጵያን በዚህ መንገድ ካደራጁ በኋላ ወደ አማራና ኦሮሚያ ይመጣል የሚል ግምት በሃሳቤ ነበረ። ኦሮሚያም ሆነ አማራ በጣም ሰፋፊ ክልሎች ናቸው። እንዲህ አይነት ሰፊ መልካ ምድርና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን ክልሎች አሁን ባለው በተማከለ ሁኔታ ለማስተዳደር አስቸጋሪ ነው። ከአንዱ የኦሮሚያ ጫፍ (ለምሳሌ ቄለም ወለጋ ወይም ቦረና ) የሚኖረው ሕዝብ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ አገልግሎት ማግኘት፣ ምንጃር የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ባሕርዳር ሄዶ መገልገል ከበድ ነው።

 

ስለሆነም የኦሮምም ሆነ የአማራ ሕዝብ የፍትህ፣ የአስተዳደር፣ የልማትና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን መጉላላት ሳይደርስበት በተቀላጠፈ መንገድ ሊያገኝ የሚችለው ክልሎቹ ለአስተዳደር በሚያመች ሁኔታ ሲደራጁ ይመስለኛል። እንዴት ይደራጁ፣ ማን ከማን ጋር አብሮ ይሁን የሚለው በመስኩ ሙያውና ችሎታው ያላቸው የተለያዩ ምሁራን፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራትና የአካባቢ አባገዳዎችና ሽማግሌዎች በጋራ ሊሠሩት የሚገባ ነው። አደረጃጀቱ ቋንቋን ብቻ መሠረት ያደረገ ሳይሆን የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ትስስር፣ አብሮ የመኖር ፍላጎት፣ ሕዝቡ የሰፈረበትን ጂዖግራፊያዊ አቀማመጥ፣ እንዲሁም ለልማት ያለውን ምቹነት ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት ። የቋንቋና የዘውግ ጉዳይ የሚተው ባይሆንም ብቻውን ወሳኝ መለኪያ ሆኖ መቅረብ ግን አይኖርበተም። በዚህ መልክ የዘውግ ስም ከዜግነት በላይ ጎልቶ እንዳይወጣ ያደርገዋል። ሌሎች ክልሎችም እንዲሁ በተጠና መንገድ የዘውግ ይዘቱን በሚበውዝ መልኩ በአስተዳደር ክልል ቢደራጁ የተሻለ ውጤት ይገኛል የሚል እምነት አለኝ።

 

ይህ አካሄድ ማንነታቸውን የሚያጠፋ አደረጃጀት አድርገው የሚቃወሙ ፖለቲከኞች፣ ማህበረሰብ አንቂዎች፣ ወይም የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች መከሰታቸው አይቀሬ ቢሆንም በብሔራዊ ንቅናቄው የሚደረጉ ውውይይቶችና የሚሠሩ ሥራዎች አጥጋቢ ከሆኑ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳቡን የሚገዙት ይመስለኛል።ሕዝቡ ግን በሚገባ ካስረዱትና በጎንዮሽ ሊጠነሰስ ከሚችለው ሴራ መከላከል ከተቻለ ሀሳቡን እንደሚቀበለው ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።

 

3.4 የአገር መከላከያ አደረጃጀት

በቅርቡ መጋቢት ወር 2015 መወሰድ የተጀመረው የክልል ልዩ ኃይሎች በፌደራል ደረጃ እንዲደራጁ የሚደረገው ጥረት በመርህ ደረጃ የሚደገፍ ነው። ገዢው ፓርቲ ወይም መንግሥት አስቦበት ይሁን አይሁን ባላውቅም ይህ እርምጃ የዘውግን አደረጃጀት ለማስወገድ የሚረዳ ሌላው እርምጃ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። መሣሪያ ሳይዙ በመባላት ላይ ያሉ ብሔረተኞች መሳሪያውንም በዘውግ ከያዙት ለአንድነት ጸር መሆኑ ግልጽ ነው። የተማከለ አስተዳደር ለመመሥረት የተማከለ የአገር መከላከያ ኃይል ያስፈልገናል።

 

ይሁን እንጂ የአንዳንድ ክልል ሕዝቦች ያላቸው “የእጠቃለሁ”ሥጋት አለመወገዱና በቂ ውይይት ተደርጎ መተማመን ሳይፈጠር ወደግጭር መግባቱ አለመግባባቱን የበለጠ አክሮታል። በመርህ ደረጃ ግን የታጠቁ ኃይሎች ለዘለቄታው በየዘውጉ ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ የሚመኝም ሆነ የሚደግፍ አለ ብየ አላምንም። ልዩ ኃይሉ እየተቆጣጠራቸው ባሉ ቦታዎች ላይ የሰላም ችግር ቢፈጠር የመከላከያ ኃይል አባላት ደርሰው የሕዝቡን ሰላም ያስከብራሉ ወይ የሚለው ሌላው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። ከስካሁኑ ልምድ ተነስቼ እኔም መንግሥት በፍጥነት ደርሶ ሕዝቡን ይታደጋል የሚል እምነት የለኝም።

 

ያም ሆነ ይህ የዘውግ/”የብሔር” ማንነት እንኳን ከጦር መሳሪያ ጋር ተያይዞ ይቅርና ብቻውንም በሃገራችን ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጸዕኖ ማድረጉና የግጭት ዋና መነሻ መሆኑ የማይካ ድ ነው። ከሌሎች ማንነቶች በተለይም ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ማንነቶች ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ግጭቶች ሊከሰቱ ቢችሉምለነሱ መነሳትም ምክንያት ወይም ቆስቋሽ የሆነው ዋናው የዘውግ ፖለቲካ ነው ብየ አምናለሁ። ስለሆነም በጉዳዩ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚካሄደው ሥራ ወሳኝ ይመስለኛል።

 

3.5 የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት

በአገራችን የመድብለ ፓርቲ የተፈቀደ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ”ብሄር”/ዘውግ የተደራጁ ናቸው። ፕሮግራማቸውም ከአካባቢያቸው አልፎ የሚሄድ አይደለም። ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ውሱን ሲሆኑ እነሱም በጠባብ “ብሔረተኞች”/ዘውገኞች ማጥላላትና በሃሰት ትርክት ብዙ ተከታይ እንዳይኖራቸው ስለተደረገ ጠንክረው ወጥተው አገር መምራት ደረጃ ላይ አልደረሱም። አንዳንዶችም ለስሙ ሕብረብሔራዊ ይባሉ እንጂ ቅርንጫፎቻቸው ያው በዘውግ ምህዳር ውስጥ እንደተዘፈቁ ናቸው። ለምሳሌ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ በኦሮሞዎች የተሞላ፣ የአማራ ቅርንጫፍ በአማራው ክልል ተወላጆች የተያዘ፣ የሌሎችም እንዲሁ ባሉበት ክልል ሰዎች ብቻ የሚንቀሳቀሱ ሆነው ይታያሉ። በራሳቸው ክልል ሕዝብ ላይ የሚደርሰው መለስተኛ ችግር ብቻ የሚያንገበግባቸው በሌላው ክልል የሚፈጸመው ከባድ በደል ግን የማይሰማቸው ሆነው ነው በአንድ አገራቀፋዊ ፓርቲ ውስጥ ተደራጅተው የሚሠሩት ።

 

ከየዘውጉ ተመልምለው የአንድ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲው አባል ሆነው ሲገቡ የተወሰኑ መርሆችን ሊያከብሩ የግድ ይላቸዋል። ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በሚኖር ሕዝብ ላይ የሚደርሰው በደል በራሱ ላይ እንደደረሰ አድርጎ የሚያይበትና የሚታገልበት ባሕሪና ስነልቦና እንዲኖረው ማስተማር፣ ማደራጀትና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአባቶች ስንብት ከጋዜጠኛ (ተመሰገን ደሳለኝ)

 

ሁሉም በየዘውጉ ስለመሸገ ሕብረ ብሄራዊ የሆኑ ፓርቲዎች ከመላው የአገሪቱ ክፍል አባላትን ማፍራት አልቻሉም። ይልቁንም አብሮ መኖር እንደመሰደቢያ ተቆጥሮ “አሃዳዊ” የሚል ስም ተለጥፎባቸው የማሸማቀቅ ሥራ ተሠርቶባቸዋል። “አሃዳዊ መንግሥት” Unitary Government ዴሞክራሲያዊ በሆኑ በርካታ (አብዛኛዎቹ ይመስሉኛል) የዓለም አገሮች በሥራ ላይ የሚገኝ የመንግሥት አደረጃጀት ነው። አንዳንዶቹ አሃዳዊነት በኢትዮጵያ ለዘመናት እንደተሞከረና እንዳልሠራ ለማሳመን ይጥራሉ። ያልሠራው እኩልነትና ፍትሃዊነት በሌለበት ሥርዓት የነበረ አንድነት እንጂ አሁን እንደሚታሰበው የየዘውጉ ቋንቋ፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ የመልማትና ሌሎቹም መብቶች የተከበሩበት አንድነት ያልተሞከረ መሆኑን አይረዱም። እነዚሁ ሰዎች የዘውግ ፌደራሊዝም ከ32 ዓመት በላይ ተሞክሮ እንዳልሠራ ትችት ሲቀርብ በአግባቡ ስለአልተተገበረ እንደሆነ ይናገራሉ።ታዲያ የዘውግ ሥርዓት በአግባቡ ባለመተግበሩ እንዳልሰራ ሲቀበሉ አሃዳዊነትም ያልሰራው በአግባቡ ስላልተርጎመ መሆኑን ለመቀበል ለምን ይቸገራሉ።

 

በኛ አገር ፖለቲከኞች በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ሥልጣን ለማግኘት የዘውጋቸውን አባላት ከኋላቸው በማሰለፍ ለመደራደሪያ እንዲረዳቸው፣ ሌሎች ደግሞ በየዘውጋቸው የስልጣኑ ቁንጮ ለመሆን ስለሚፈልጉ፣ የአሃዳዊነትን ይዘት ቢያውቁም ‘አሃዳዊነት’ ጨቋኝነት፣ ጨፍላቂነት፣ ፍትህ የሌለበት ፣ ትምክህተኝነት፣ አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት ናፋቂነት ወዘተ እንደሆነ አስመስለው ተከታዮቻቸውን አሳምነዋቸዋል። ይህ የተንኮል ፖለቲካ ሊቀር ይገባዋል። አሃዳዊነት ዴሞክራሲያዊ የሆነ ተቀባይነት ያለው፣ በበርካታ አገራት የተከበር አደረጃጀት መሆኑን ሕዝቡ እንዲረዳው ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።

 

እንደኔ አስተሳሰብ በ”ብሔር”/በዘውግ የተደራጀ ፓርቲን ለማገድ ቆራጥ የፖለቲካ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። እንዲህ አይነት እርምጃ ዴሞክራሲያዊ ባይሆንም አገር ከማፍረስ የተሻለ ይመስለኛል። ወደፊት የሰከነ ፖለቲካ በሚፈጠርበት ወቅት፣ የዴሞክራሲን አጠቃቀም ሁሉም በተረዳበት ጊዜበፈለገው መንገድ የሚደራጅበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። አሁን ባለንበት ደረጃ ግን መተላለቅ እንጂ ሌላ የተሻለ ነገር አያመጣልንም፤ አይሰጠንም። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አገር አይደለችም። በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በጎሳ መደራጀትን በሕግ እንደከለከሉ መገንዘብ ያስፈልጋል።

 

ባንኩም ሆነ መኪናው “ብሔር” ተሰጥቶት በሚሠራበትና አሁን በሚታየው የተካረረ ሁኔታ በዘውግ እንዳይደራጁ በሕግ ለማገድ ከባድ ከሆነ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ አሠራራቸውና አካሄዳቸው በሕግ ገደብ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል። ሕዝብና ሕዝብን የሚያጋጩ፣ የአንዱን ባህልና ቋንቋ የሚያንቋሽሹ፣ የሌላውን ህዝብ የሚንቁና የሚሳደቡ፣ የዜጎችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይፈቅዱ፣ ዜጎች በፈለጉበት ቦታ የመኖርና ሃብት የማፍራት መብታቸውን የማያከብሩ፣ ለዘውጋቸው ተወላጆች አድሎ አድርገው የሌላውን ዜጋ መብት የሚገድቡ በአጠቃላይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጻረሩ ከሆኑ መሰረታዊ የሆኑትን መብቶች እንደጣሱ ተቆጥሮ የፖለቲካ ድርጅቶችን እስከመዝጋትና መሪዎችንም በወንጀል የሚያስጠይቅ አሰራር ሊተገበር ይገባል።

 

3.6 የሚዲያ አጠቃቀም

የሚዲያ ነጻነት በምንም መልኩ መገድብ አይኖርበትም። በመሠረተ ሃሳብ ደረጃ ሚዲያ ሕዝብና መንግሥትን የሚያገናኝ ድልድይ ሆኖ አወንታዊ ሚና የሚጫወት ነው። የመናገርና የመጻፍ መብቶች ከአለማቀፋዊ ድንጋጌዎች መካከል የተካተቱ ናቸው። ሚዲያ የዴሞክራሲ መገለጫ ብቻ ሳይሆን የልማትም አጋር ነው። የሚዲያ አዎንታዊ አመለካከትና ተግባር የሚመዘነው በተጨባጭ ያገኘውን ዜና ሳያዛባ ሲያቀርብ፣ እውነታውን በጥናት ፈልፍሎ በማውጣት ሕዝብን ሲያሳውቅ፣ መንግሥት የሚያሳየውን ድክመት በመጠቆም እንዲታረም ሲያደርግ፣ ሊከሰት የሚችል መጥፎ ክስተትንም ሆነ ጥሩ ነገርን አስቀድሞ ሲጠቁም፣ በአጠቃላይ የሕዝብ ልሳን ሆኖ ሲያገለግል ነው።

 

ይህን ግደታቸውን የሚወጡ ሚዲያዎች ቢኖሩም ከሥነምግባር ውጭ የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች ደግሞ ጥቂት አይደሉም። ወገንተኛ የሆኑና የፖለቲካ መጠቀሚያ ሆነው የሚሠሩ አይተናል። በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት ያላቸው ሳይቀሩ የሃያላን መንግሥታትን ጥቅም ለማራመድ የደሃ አገሮችን እጅ ሲጠመዝዙ ተመልክተናል። በተለይ ማህበራዊ ሚዲያው ከአላማ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጥቅም ወይም ገንዘብ ከማግኘት ጋር የተያያዙም ስላሉበት የሌለ ዜና በማሰራጨት ላይ ያሉ ይገኛሉ።

 

ይህ የዳበረ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባለበት አገር የጎላ ችግር ላያስከትል ይችላል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ግን የሃስት ዜና አገር ሊያፈርስ፣ ሕዝብ ሊበትን ይችላል። ስለሆነም ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ላይ ባሉና በተለይ የዘውግ ፖለቲካ በገነነበት አገር የተወሰነ ገደብ መኖሩ የሚጠቅም ይመስለኛል። ተራ ስድብ የሚያሽጎደጉዱ፣ ሆን ብለው ጥላቻን ለመፍጠር የሃስት ዜና የሚያሰራጩ፣ ሰላም እንዳይኖር ሌት ተቀን የሚጥሩ፣ የሕዝቦችን አንድነት ሳይሆን መለያየትን አላማቸው ያደረጉ፣ በሃገሪቱ ጠላቶች የተገዙ ተከፋዮችም ሊሆኑ ስለሚችሉ ቢያንስ አሁን ያለንበት አደገኛ ሁኔታ እስኪስተካከል ድረስ ገደብ ሊደረግባቸው ይገባል።

 

ተግባር አጋዢ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ

4.1 ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን ማስፋት ‘የብሄር”ን/የዘውግን መብት ማክበር

ባንድ በኩል በሀገርና በሕዝብ ላይ ያንዣበበው አደጋ በአስተማማኝ ደረጃ እስኪቀለበስ ድረስ በዴሞክራሲ ስም አንዳንድ አፍራሽ ሁኔታዎችን የሚገድብ ጊዜያው ሕግ ያስፈልጋል እያልን በሌላ በኩል ደግሞ የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት አለበት ስንል የሚጋጭ አመለካከት ይመስላል። ከላይ የቀረበውና ገደብ የሚጥለው ጊዜያዊ ሕግ መሰረታዊ የሆኑ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጥስ ሊሆን አይገባውም። ለከት ያጣ ጥላቻን በሚያስተጋባ፣ ግጭትን በሚያነሳሳና አብሮነትን በሚያጥላላ ሃሳብ ላይ ለጊዜው ገደብ ቢደረግም በአግባቡ የዴሞክራሲና የሰባዊ መብቶችን መተግበር የሚከለክል ሊሆን አይገባውም።

 

4.2 ፍትህን ማስፈን

ሕዝቡ ፍትህና ርትዕ ርዕትህ ጠምቶታል። ያለፍርድ ለብዙ አመታት ከኖረበት ቦታ ይፈናቀላል፤ ያፈራው ንብረት ይዘረፋል ወይም ይቃጠላል፤ አንዳንዱ ከሌላው የተሻለ መረጃ እያገኘ በኢቨስትሜንት ሥራ እንዲሳተፍ ይመቻችለታል፤ ሌላው ደግሞ በኢቬስትሜንት ስም ያለበቂ ካሳ ያለውን እንዲያጣ ይበየንበታል። አብዛኛው ጉዳይ ለማስፈጸም ሲጉላላ ይውላል፤ ከአቅሙ በላይ የሆነ ጉቦም ይጠየቃል። ጥቂቱ ባለጊዜና ባለስልጣን ደግሞ ያለ ምንም እንግልት ጉዳዩ ተፈጽሞለት ቤቱ ወይም ቢሮው ድረስ ይመጣለታል። ግልጽ የሆነ አድሎና የመልካም አስተዳደር ችግር በተራው ሕዝብ ላይ ይታያል።

 

በሕዝቦች መካከል የዕድገትና የኑሮ አለመመጣጠን ጎልቶ ይታያል። አንዱ ኋላ ቀር ሌላው የበለጸገ፣ አንዱ መብራት፣ ውሃ፣ ስልክና ሌሎች የትራንስፖርትና መገናኛ አውታሮች ተሟልተውለት የሚኖር ሌላው ፈጣሪ እንዳስቀመጠው እራቁቱን በጫካ የሚኖር ከሆነ ፍትህ የለም። ስለሆነም እድገታቸው ወደኋላ በቀሩ ክልሎች ተመጣጣኝና ፍትሃዊ የልማት ድርሻ እንዲኖራቸው መደረግ አለበት።

 

በአጠቃላይ ሕዝብ ከማንም የማያንስ ከማንም የማይበልጥ ሆኖ ክብሩና መብቱ ተጠብቆለት መኖር የሚያስችል ሁኔታ ይጠይቃል፤ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊ፣ የመንፈሳዊ አኗኗሩ ፍትሃዊ እንዲሆንለት ፍላጎት አለው። ከዚህ ውጭ ያለ ጥያቄ የፖለቲከኞች ጥያቄ ነው።

 

4.3 ሙስናን የመከላከል ሥራ

ሙስና የእድገት ጸር እንደሆነ በተለያየ መድረክ ተገልጿል። ከወታደራዊ መንግሥት ጀምሮ ሙስና ላይ ዘመቻ ያላወጀ መንግሥት አላየሁም። በደርግ ጊዜ “የቁጥጥር ኮሚቴ” የሚባል መዋቅር ከብሔራዊ አስከ ቀበሌ ድረስ የተዋቀረ አካል ተፈጥሮ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ኮሚቴው “የማያንኳኳው ቤትአይኖርም” ተብሎ ቢዘመርለትም የሚያስፈጽመው አካል አልተገኘም። በኢሕአድግ ዘመንም “የሙስና እጆችን እንቆርጣለን” ተብሎ በሃገር አቀፍ ደረጃ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ቢደራጅም ፣ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ በዋስትና ሊለቀቅ እንደማይችል በሕግ ቢደነገግም፣ በሙስና አሳቦ ተቋሚዎችን ከማሰር አልፎ ሙሰኞችን አላስደነገጠም። እንዲያውም እስካልተያዘ ድረስ ሌብነትምሥራ እንደሆነ የሌብነትን ግብረ ገባዊ ብሉሽነትን አቃለለው። በብልጽግና ጊዜ ደግሞ በባሰ ሁኔታ አይን ያወጣ ዝርፊያ ሲደረግ የሙስና ኮሚሽን የነበረው እንዲጠናከር አድርገናል ከማለት በተጨማሪ አዲስ የጸረ ሙስና አካል ተፈጥሮ ያዙኝ ልቀቁኝ ካለ በኋላ የተወሰኑ የወረዳ አመራሮችን ነካ ነካ ቢያደርግም የሙስናው ደረጃ ጨምሮ በሥራ ላይ ከመዋሉ በስተቀር ዋናዎቹ የሙስና ተወናውዮችን አላስደነገጠም፤ ሙስናም አልተነካም።

 

የሙስና ጉዳይም በየዘመኑ ይፎከርበታል፤ ድል የተገኘበት ሆኖ አልታየም። ሙስናን ለማጥፋት አንዱን ሙሰኛ ከአንዱ ቦታ ወደሌላ በማዛዋወር ልፍስፍስ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ሳይሆን አንደ አጼ ቴድሮስ የሌቦችን እጅ መቁረጥና እንደቻይናም በሞት መቅጣት ባያስፈልግም ቅጣቱ ሙሰኛውን ብቻ ሳይሆን ሕብረተስቡን የሚያስተምርና ሙስና ይቅርብኝ የሚያሰኝ መሆን ይኖርበታል። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ዘርፎ በሽዎች የሚቆጠር ብር ቅጣትና የወራት እስራት መወሰን ቅጣት ሳይሆን ሽልማት ይመስለኛል። በሙስና ያፈራውን ሃብት በሙሉ የሚያጣበት ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም እንቅስቃሴውንና መብቱን የሚገድብ ቅጣት ካልተሰጠው ሊማር አይችልም።

 

4.4 ድህነትን ማስወገድ

ድሃ የሆነ ህዝብ ክብር የለውም። ምዕራባዊያን እንዲህ አዛዥ ናዛዥ የሆኑብን ድሃ ስለሆን ነው። ከአገር በመለስ በግለሰብ ደረጃም ድሃ መሆን በወገንም ፊት የበታች ያደርጋል። ድሃ ምንም ጥሩ ሃሳብ ቢያፈልቅ የሚቀበለው የለም። ሁልጊዜ ተሸማቆ፣ ሁልጊዜ ያላቸውን ሰዎች ፊት አይቶ ነው የሚናገረውና የሚኖረውም።

 

በኔ እምነት የችግራችን ዋናው መሠረት (Root cause) ድህነታቸን ነው። ድህነት ስል በኢኮኖሚ አለማደግ ወይም ሃብት የማጣት ብቻ አይደለም። የአመለካከትና የአእምሮ ድህንነትንም ይጨምራል።

 

ሰላም በሌለበት ጦርነትና ግጭት በሰፈነበት አገር ሃብትና ንብረት ይወድማል እንጂ ልማት አይኖርም፤ ከግጭትና ጦርነት አዙሪት መውጣት አለብን። በተለያየ ምክንያት በይበልጥ በከተሞች በራሳቸው ጥረውና ግረው ሃብት ካፈሩት ይልቅ በአጭርና በአቋራጭ አምታተውና በሙስና ተዘፍቀው የከበሩ ሃብታሞች በበዙባት፣ ሃብት የሌለው ደግሞ ከመሥራት ይልቅ ለምኖ መብላት የሚመርጥ ሰው በየጎዳናው በሚታይባትእንዲሁም በተለይ ገጠር በየሰበቡ ከመሥራት ይልቅ ማንጋጠጥን የሚመርጡ አማኞች ባሉባት አገር እድገት አይታሰብም። ይህ የተንሸዋረረ የሥራ ባህልና የአመለካከት ድህነት መወገድ አለበት።

 

እንደማጠቃለያ የስልጣን ምንጭ የሆነው ሕዝብ ካልበለጸገና ቢያንስ ተስፋ ካልሰነቀ ባለስልጣኑ ሥልጣኑን አያስከብርም፤ ዝናንም አያመጣም። ዝናና ክብር በመግደል፣ በማሰር፣ በመፈራትና ሕዝቡን ሰጥ ለጥ አድርጎ በመግዛት ሳይሆን የሕዝቡን ኑሮ በማሻሻል፣ የሃገርን ሉአላዊነትና የሕዝቡን አንድነት በማስከበር እንዲሁም ሰው ተኮር የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ የሚገኝ ነው። በእኔ እምነት ሶቪየት ኅብረትን ከበታተነው ጎርቫቾቭ ይልቅ ጀርመንን አንድ ያደረጉት መሪዎች ክብርና ዝና አላቸው። እስቲ ከጀርመን መሪዎች እንማር፤ መልካም ነገር እንመኝ፤ ጥሩ ነገር እናስብ፤ ሰናይ ሥራ እንሥራ፤ ጥሩ ዜጋ እንሁንና ፈጣሪ ይለመነን እንዲሆን እንጠብቅ። ጠንካራ አገርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ያለው ሕዝብ ለመሆን እንጽና። ደካማ ጎናችንን ብቻ ሳይሆን ያለንን እምቅ የሰው ሃይልና የተፈጥሮ ሃብት እንመልከት ።

 

መላኩ አያለው (melaku.ac@gmail.com)

 

ግንቦት 2015

 

 

1 Comment

  1. በአንጻሩም የአማራ አገዛዝ ዳግመኛ እንዳይጫንብን ተግተን ፋኖን በእንጭጩ እንቀጨዉ። ዋናዉ የእኩልነት የአንድነታችን ፀር እርሱ ነውና።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share