የሃገር ሰው “እባብ ለእባብ ይሄዳል ካብ ለካብ” ይላሉ። ይህ ሲባል ሁለት ተንኮለኞች ፣ ሴረኞች፣ የማይተማመኑ፣ አንዱ አንዱን ቀድሞ ለማጥፋት የሚያደቡ ከሆነ ፣ በመካከላቸው የልብ ውስጥ ስምምነት ከሌለ ፣ ቂም ከቋጥሩና ወ.ዘ.ተ. በዐይነ ቁራኛ እየተያዩና እየተጠባበቁ የጋራ ጠላታችን ፣ የሥልጣን ተገዳዳሪያችን የሚሉትንና ብቻ ለብቻ የማይችሉትን ፈርጣማ አካልና ቡድን ጊዜው ደርሶ እርስ በርስ እስኪላተሙና እስኪጣሉ ድረስ በጋራ እየገደሉ፣ እያሰሩና እያቅጎሳቆሉ ለጊዜው ሊዘልቁ ይችሉ ይሆናል።
#image_titleይህ የካብ ለካብ ጉዟቸው ግን ጊዚያዊና አንዱ አንዱን ቀድሞ እስኪሰለቅጠው ድረስ ነው።
ይህ እውነታ በአምስት ዓመቱ የህውሃትና የነብልፅግና የጋራ በስልጣን የመሰንበትና ሃገር የመበዝበር ሴራና ፍላጎት ታይቷል።
ህውሃትና የኦሮሞ ብልፅግና በለውጥ ተብየው የአምስት ዓመት ክራሞታቸው የገቡበትን ፍትጊያ ፣ ጦር ያማዘዛቸው ጉዳይ ፣ አሻጥራቸውን እና እንደገና ከተገዳደሉ በኋላ ጥምረት የመፍጠራቸው አካሄድ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል የአነገቡት ሴረኛነታቸውን፣ ስግብግብነታቸውንና ጨካኝነታቸውን ፍትው አድርጎ ያሳያል።
በመካከላችው ተቃርኖና ሽኩቻ ሲፈጠርና እርስ በርሳቸው ለመሰለቃቀጥ ሲያስቡ በኃይልና በሥልጣን ፈርጠም ያለው ፓርቲ /ብልፅግና ማለት ነው/ ስልጣኑን ለመጠበቅና ላለማስነጠቅ ሲል አስመሳይ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ፣ በተቃርኖ ያለን ቡድን ወዳጅ መስሎ በመቅረብና ሰበባ ሰበብ በመፈለግ አጋር የሆነውን ፓርቲ ያለምንም ርህራሄ /ህውሃት ማለት ነው/ በሌላ ፓርቲ /አማራንና ሌላውን ብሄር ማለት ነው/ በማነሳሳት በሸር ህውሃትን ድምጥማጡን ለማጥፋት ሞክሯል ፣ ተሳክቶልትማል።
ብልፅግና ህውሃትን በስሩ አበርክኮ ታዛዥ ለማድረግ ሲያሴር የህውሃት ተቃራኒ ነው ብሎ የሚያስባቸውን ብሄሮች ህውሃት ያደረሰባቸውን በደልና ግፍ በማመርቀዝ እናርቶአቸዋል።
አሁን ደግሞ የኦሮምያው ብልፅግና ቆዳውን ቀይሮ የትግራይን ሕዝብ “የደረሰብህ በደል ያንገፈግፋል ፣ አማራው አታሎናል፣ አማራ የጋራ የብሔር ጭቆና አድርሶብናል ፣ ወልቃይትና እራያ ያንተ ነውና የጋራ ጠላታችን አማራ ነው” እያለ እየወሸከተ ሃገርና ሕዝብን ለሌላ እልቂት እያንደረደረ ሲሆን “እባብ ለእባብ” እንዲሉ ህውሃትም ይህን የሸፍጥ አካሄድ ልቡ እያወቀ እየገፋበት ይገኛል።
አንዳንዴ የሃገረ ኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ውድቀት ሊያመሩ ሲሉ “ታስሮ እንደተፈታ ወይፈን” ይደነብራሉ ፣ ግራ ይገባቸዋል ፣ መስመራቸውን ይስታሉ፣ እውር ድንብሩን ይጓዛሉ፣ ዘላቂ ወዳጃቸውንና አጥፊያቸውን መለየት ይሳናቸዋል።
ህወሃት እንኳን እንደ “ደረቀ ኩበት” የተፍረከረከውን ብልፅግናን ይቅርና እንደ እነ ጀኔራል ፋንታ በላይ ፣ ጄነራል መርዕድ ወ.ዘ.ተ. የመሰሉ ምርጥ ዓለም ያደነቃቸው ጀነራሎች አቅፎ ይዞ የነበረውን የደርግ ሥርዓት በሴራና በተንኮል አፈር ድሜ አብልቶታል።
የራሻን መድፎች ታንኮች ፣ ተወዳዳሪ የሌላቸውን መሳሪያዎች ፣ ክላስተር ቦንቦች የታጠቀውንና በአፍሪካ ተወዳዳሪ የለውም ተብሎለት የነበረውን የደርግ ሰራዊት እነ ህውሃት ያፍረከረኩት የመዋጋት ብቁ ቁመና ኑሯቸው ሳይሆን ተንኮል አዘል በሆነው የዲፕሎማሲ አካሄዳቸው ፣ በደርግ የተበደለውን የአማራ ሕዝብ በተለይም የወልቃይት ፣ የበለሳና የወሎ ከፊል ሕዝብን አደናብረውና አታለው እንዲሁም ደርግ ይዞት የነበረውን ሕዝብን የመናቅ ትህቢቱንና ድንቁርናውን ባዶ እያደረጉ ፣ እያጋለጡና ገመናውን እያወጡ ለሕዝብ በማሳበቅ ነበር።
ከዚህ ባሻገር የአሁኑን አያድርገውና ደርግን ድምጥማጡን ለማጥፋት ከኤርትራው የሻቢያ ቡድን ፣ ህወሃት ወልቃይትን ገዥ መሬት አድርጎ ከሃገረ ሱዳን ፣ ግብፅ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሰሜን አካባቢ የክርስትና መሰረት መሆን የማይመቻቸውን የሃረብ ሃገራት እገዛ በማግኘት ደርግን ጉድ እንደሰራ ለማንም ግልፅና የማይታበይ ሃቅ ነው።
“የማይዘልቁ ፍቅረኞች በየመንገዱ ይማማላሉ እንዲሉ” በኦሮሙማ የበላይነት የተዋቀረው ጅላንፎው የብልፅግና መንግስት “ ታሪካዊ የጋራ ጠላታችን አማራ ነው ፣ አማራን ደግሞ ማበርከክ የምንችለው ከውጭ ጎረቤት ሃገራት የሚያገናኘውን የአማራን ለም መሬት ወልቃይትን እና ኩሩውን የራያን መሬት ወደ ትግራይ አጠቃለን በማካለል ብቻና ብቻ ነው” በሚል የከረፈፍ አካሄድ ከህወሃት ጋር ደም መቃባቱን ወደጎን ብሎ ተማምሎ የጋራ የጥፋት ጉዟቸውን ጀምረዋል።
ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የነበረውን የህወሃት አካሄድ ተከትለን አማራን ፀጥ አድርገን ፣ እረግጠንና አንገላተን በተለመደው መልኩ ካልገዛነው አማራ ይውጠናል የሚለውን የደናቁርት ህሳቤ ህወሃት በለመደው አስማቱና ሽወዳው ለኦሮሙማው ብልፅግና ሹክ ብሎት “ጭዋታ ፍርስርስ ያደረ እንጀራ ቁርስርስ” ዓይነት የልጆች ጭዋታ”ና “የነተሎ ተሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ” እንዲሉ ይህን በመርዝ የተለወሰ የደባና የተንኮል ውሳኔ እነ ብልፅግና “የፈንጅ ወረዳ” በመርገጥ የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰው ውሳኔያቸውን ለመተግበር ተፍ ተፍ በማለት ላይ ይገኛሉ።
“አያ በሬ ሆይ ሳሩነን አይተህ ገደሉን ሳታይ” እንዲሉ የኦሮሞው ብልፅግና ከሰላሳ ዓመት የህውሃት መወገር ፣ መታሰር ፣ መደፈር ፣ ስቃይና እንግልት እንዲላቀቅ “ የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው” ብሎ ከጎኑ የቆመውን ፣ በህግ ማስከበር የህልውና ጦርነት ወቅት ከቆላ ተምቤን ተነስቶ አዲስ አበባ ጫፍ አካባቢ ደርሶ ብልፅግናን ከስልጣኑ ሊያስፈነጥረው የነበረውን ህወሃትን መልሶ ወደ ሸጎሬው መቀሌ የመለሰለትን የአማራ ሕዝብ ክዶ “ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል አጓጉል ህሳቤ ወንድሙን የአማራ ሕዝብ ፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚኒሻ ለመውጋትና ለማፍረስ መነሳቱ የድግምት፣ የአስማትና የአፍዝዝ እደንዝዝ ውሳኔ እንጂ የበጎ ነው ብለን እኛ አማሮች አናምንም ።
ብልፅግናም ይሄን የውር ድንበር አካሄዱን መልሶ እንዲያጤነው እንመክራለን።
ከዚህም ባሻገር “ ታሞ ከመማመቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንዲሉ አይሆንም እንጂ ህወሃት በሱዳን በኩል መውጫ ቀዳዳ አግኝቶ ከግብፅና ከመሰል የኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን ለብቻቸው ለመቀራመጥ ከሚሹና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀናይ ካልሆኑ ቡድኖችና ሃገሮች ጋር ከተገናኘ እንደለመደው የአማራውም እንቢተኝነት ስለሚኖር አዲስ አባባ ገብቶ የኦሮሞን ብልፅግና አፈር ደሜ ያበላዋል፣ ጥር ጥር የለውም።
ህውሃት እንደለመደው የኦሮሞ ብልፅግና “በቁሜ ከድቶ ወጋኝና ካደኝ” ብሎ የሚያስበውን የኦሮሞ ሕዝብም ድምጥማጡን እንደሚያጠፋው የማይታበል ሃቅ ነው።
ይህ የጭካኔ የህውሃት የቂመኝነት አካሄዱ በሃያ ሰባት ዓመታት የስልጣን ዘመኑ ያሳየው በአማራውም ሆነ በኦሮሞው ላይ የተገበረው በመሆኑ ይህ እንደሚፈጠር እኛ የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝቦች አስረግጠን እንመክራለን ።
ይህን የተንኮል፣ የመሰሬነትና የፍልፈል አካሄዱን የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ የሚያውቀው ጉዳይ እንደሆነ ልብ ይሏል ።
ይህን ያልንበት ምክንያት “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ” እንዲሉ እነብልፅግና በአለበሌለ የጦር መሳሪያ ፣ በሚሲያል፣ በድሮን፣ ከአየር ላይ በሚወረወር ክላስተር ቦንብ ምድረ ትግራይን አጋይተው እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን የትግራይን ሕዝብ ከጨፈጨፉ በኋላ እነ ብልፅግና ህወሃትን አምነው “ወልቃይትና ራያን” በካሳ በመቸር ለመታረቅና እንደገና ጋብቻ ለመፈፀም መዳዳታቸው ከማሳቅ አልፎ ያንከተክታል።
እንደ ቀላል የባልና ሚስት ተጣልቶ መታረቅ አይነት ጉዳይ ካደረጉት የሚጎዳውና ይበልጥ ዋጋ የሚከፍለው የኦሮሞ ብልፅግና እና የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ስለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።
እንደ እስቆሮቱ ይሁዳ የአማራን ሕዝብ “የኦሮ አማራ ጥምረት ብሉው ጉንጭ ስመውና በሕግ ማስከበሩ አድኑን” በለው የአማራን ሕዝብ ከተማፀኑና ስልጣናቸውን ካስጠበቁ በኋላ እነ ኦሮሞ ብልፅግና አማራን መካዳቸው ታሪክ የማይረሳው ጠባሳና የሚያስተዛዝብ አካሄድ እንደሆነ ሊገነዘቡት የግድ ይላቸዋል እንላለን።
ከዚህ ባሻገር ሊታወቅ የሚገባው “ቦ ጊዜ ለኩሉ” እንዲሉ አማራ ቢገደል ፣ ቢሰቃይ ፣ ቢፈናቀልና ቢንገላታ ለነፃነቱ መታገል ከአያት ቅድመ አያቶቹ የወረሰው ስለሆነ ጊዜ ሊወስድና ብዙ መስዋህትነት ሊይስከፍል ይችል እንደሆን እንጂ አሸናፊው ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያዊውና የሃገር ካሳማና መከታ የሆነው የአማራ ህዝብ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
ወልቃይት ጠገዴ ፣ ጠለምትና ራያ ከዕርስት ባለቤታቸው አማራ ምድር ጋር ሆነው ለዘለዓለም እንደሚቀጥሉ የሚጠራጠርና የሚያቅማማ አማራ እንደሌለ ቁርጣችሁን እወቁ።
ይህን ሃቅና እውነታ እቀለብሳለሁ ብሎ የሆነ ቡድን ከመጣ ግን እንደ ታይዋኗ የቻይና አካል ፣ እንደ ካሽሚር ፣ እንደ ዮክሬን ፣ ፓሊስትያን ፣ ከርድሽ ና ሌሎችም የትግል አካሄዶች ፍልሚያው ይቀጥላል ።
የአባቶቻችንን የከለው ነገድ ምድርን እንደ ቁራሽ እንጀራ እኛ አማሮች የትዕብታችንን መገኛና መቀበሪያ ምሬታችንን ለማንም አሳልፈን አንሰጥም ፣ እርማችሁን አውጡ።
ተዘራ አሰጉ
ከምድረ እንግሊዝ።