ሰዉ እግዚአብሔር ባምሳሉ የፈጠረዉ ፍጡር መሆኑንና ፤ አገር ደግሞ የጋራ መሆኗን አንርሳ፤ ህይወትም አጭር መሆኗን

 

  1. መንደርደሪያ፤

ደጋግሜ ጽፌያለሁ፤ አዉነታዎችንንም ለመመስከር ሞክሬያሉ። ዳሩ ግን ሁኔታዎች አሁንም እየተባባሱ ይገኛሉ። ዛሬ የምንሰማዉ ዜና ሁሉ ማመን ያቅታል። ከእንስሳት በታች ሆነዉ መገኘት ከዬት የመጣ ነው? ሰዉ ከሌሎቹ ሁሉ የሚለየዉ እኮ እግዚአብሔር የሚያስብ አእምሮ ሰጥቶ በአምሳሉ ስለፈጠረዉ ነዉ። ንፁሕ ዜጋ ከቀዬው በግፍ ሲፈናቀል፤ ሲገደልና ሲሰቃይ ይታያል። ጥሮ ግሮ ከመኖር ሌላ ምን ባጠፋ? በስንቶቹ ጀግኖች ደም እና አጥንት ተገንብታ ነፃነቷን አስጠብቃ ለሌሎችም የነፃነት ተምሳሊት የሆነችዉን ዉድ አገራችንንስ ለምን ሊያፈርሷት ተነሱ? እግዚአብሔር ሁሉን አሟልቶ የፈጠራት አገር ዛሬ በዓለም ከሁሉም በታች ሆና ስትታይ ምን ይሰማቸዉ ይሆን? ተያይዘዉ መጥፋትን ሲያመቻቹስ ምን ሊጠቀሙ ይሆን?  እኔ በበኩሌ ምንም ሊገባኝ አልቻለም።

ዉድ አገራችን የእንግሊዝ፤ የጣሊያ፤ የቱርክ፤ የግብፅ፤ ወዘተ የዉጪ ወራሪ ኃይሎችን መመከት የተቻለዉ በህዝባችን ትብብርና በእግዚአብሔር ኃይል ነበር። ዛሬ ግን ያ ትብብር ላላ፡ ፈሪሃ እግዚአብሔርም እየራቀን ነዉ። የዓለም ፍፃሜ መዳረሻ ምልክቶችም በደንብ እየታዩ ናቸዉ። ታዲያ ምንድን ነዉ የምንጠብቀዉ? ስለዚህ የጎሣና የኃይማኖት ልዩነቶችንና የግል ጥቅሞችን በማስቀደም በንፁሐን ዜጎች ላይ የሚካሄደዉ ታላቃ ወንጀልና አገር የማፍረስ ሰይጣናዊ ዘመቻዎቸዉ ይቆም ዘንድ በትህትና ላሳስባችሁ እወዳለሁ።

 

  1. በአማራ ህዝብ ላይ የሚካሄዱት አሳዛኝና አስነዋሪ ወንጀሎች መቆም አለባቸዉ፡

አማራ ያለዉን እኩል ተካፍሎና ተዛምዶ አብሮ ከመኖር በስተቀር የማንም ህዝብ ጠላት ሆኖ አያወቅም። ሥልጣን ላይ ለመቆየትም ሆነ መሬት ለመንጠቅ ሲሉ የአማራን ህዝብ በዉሸት ትርክት በተሳሳተ መንገድ ሲስሉት ይታያሉ።

በተደጋጋሚ እንደተገለፀዉ፤ ህወሃት ወደሥልጣን ሲመጣ የአማራ/ጎንደር አካላት የሆኑትን ምድሮች በጉልበት ቆርጦ ወደ ትግራይ ከለለ። እነዚህም ወልቃይትን፤ ጠገዴን፤ ጠለምትን፤ ወዘተ ሲያጠቃልሉ ከወሎ ደግሞ እነራያን ይመለከታል። እነዚህን ድንበሮች በተመለከተ በቂ ታሪካዊ መዝገቦችና መረጃዎች አሉ። ዳሩ ግን ምድሮቹ ወደቀድሞዎቹ ክልሎች/ክፍሎች ይመለሱ ማለት የትግራይ ህዝብ አይኑርባቸዉ ማለት አይደለም። ህዝባችን ከጥንቱ ጀምሮ ወደፈለገበት ቦታ እየተዘዋወረ የመኖር፤ የመሥራትና የመነገድ መብት ነበረዉ። የህወሃት ከፋፋይ ሕገ መንግሥትና አምባገነንነት ያመጣብን አባዜ እንጂ በጭቁን ህዝብ መካከል ጠላትነት የለም። የትግራይ ህዝብ ለሺዎች ዓመታት በአብሮነትና በመልካል ጉርብትና ከአማራዉ፤ ከአፋሩ፤ ወዘተ ጋር በሰላም ኖሯል። ዛሬም እርቀ ሰላም ወርዶ በሰላም እንዲቀጥል መከልከል የለበትም። ልጆችን ወደትምህርት ቤቶች እንጂ እንደገና ወደጦር ሜዳዎች መላክ እጅግ በጣም ከፍተኛ ኃጢያት ነዉ። ገበሬዉ በሰላም ካላረሰ፤ ነጋዴዉ በሰላም ካልተንቀሳቀሰ ምን ሊበላ ነዉ? የዉስጥ ችግሮቻችን በሰላም መንገድ እንጂ በጦርነት የሚፈቱ አይደሉም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ልማታዊው ጓደኛዬ - ከዋስይሁን ተስፋዬ

ከነሩዋንዳ እንኳን መማር የማይችሉ ጽንፈኞች መበርከት እጅግ በጣም ያሳዝነኛል። እነዚህ ሰዎች ከስህተቶቻቸዉ እስኪማሩ ድረስ የሚሊዮኖች ሕይወት መቀሰፍ የለበትም።

ካለዚያ ጉዳቶች እየተባባሱ ይሄዳሉ፤ ወደሌሎችም ክልሎች ይቀጣጠላሉ። የተለመደዉ ርሃብ፤ ጥማት፤ እርዛት፤ ስደት፤ ልመናና እንግልት እየባሰበት ይሄዳል። ሰላም ሳይኖር ዕድገት ሊመጣ አይችልም። ተያይዞ መጥፋትን ያስከትላል።እግዚአብሔር ሁሉን አሟልቶ የፈጠራትና ለሁሉም የዳቦ ቅርጫት መሆን የሚትችል የተቀደሰች ሀገር እንደዚህ ስትዋረድ በማየቴ እጅጉን ዘዝናለሁ። የተማርነዉም፤ የታገልነዉም ለዲሞክራሲና ለዕድገት እንጂ እንደዚህ ዓይነት ዉርደትና ጥፋት ለማየት አልነበረም።

 

  1. የመንግሥት ኃላፊነት

የመንግሥት ዋና ኃላፊነት የእያንዳንዱን ዜጋ ሰብዓዊ መብት ማስጠበቅ ነበር። የማንም ዜጋ ሕይዎት በከንቱ ማለፍ የለበትም። የማንም ዜጋ ንብረት መዘረፍ ሆነ መዉደም የለበትም። የተፈናቀሉ ወገኖች ቶሎ ወደየሰፈራቸዉ እንዲመለሱ ከፍተኛ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። የመንግሥት፤ የፀጥታና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠዉ ያስፈልጋል። ሰላም ማዉረድ፤ ጥራት ያላቸዉን ትምህርት ቤቶች ማስፋፋት፤ የሥራ ዕድሎች ማመቻቸት፤ ጠፍ መሬቶችን ማልማት፤ የመስኖ እርሻዎች ማስፋፋት፤ የአካባቢ አየር ብክለት መከላከል፤ ኢኮኖሚ መገንባትና ድንበር መጠበቅ ነዉ። ዛሬ እነዚህ ሁሉ በከባድ አደጋ ላይ ወድቀዋል። ታዲያ ምንድን ነዉ የሚጠበቀዉ? አቅቶት ከሆነ በቶሎ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ያስፈልጋል። ሕገመንግሥቱ ቶሎ መሻሻል ይጠበቅበታል። በሰፊዉ ህዝባችን ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ዋናዉ መንስሔ እርሱ ነዉና። የዜጎችን የመኖር መብት አይጠብቅምና። አብሮ ከመኖር ይልቅ መገነጣጠልን ይደግፋልና።

የኢትዮጵያ ጽንፈኞች እንደሚለፍፉት አይደለም። ኢትዮጵያ የትናንትና ሀገር አይደለችም፤ ጥንታዊት ናት፤ ሰፊ ናት፤ አቃፊ ናት፤ ቸሩ አምላካችን ሁሉን ነገር አሟልቶ የፈጠራት ቅድስት ሀገር ናት። ሰላም ካለ ከራሷም አልፋ ብዙ ሀገሮችን ለመመገብ የምትችል ኃብታም ሀገር ናት። ለዐለም ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች። በቅኝ የተያዙና የተጠቁ የአፍሪቃ ሀገሮች ነፃ እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች። እንደዚያ ደግ የሆነች ሀገር ኅልዉና እንዲናጋ የሚፈለገዉ ለምንድን ነዉ? የዉጪ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ለመጥቀም ካልሆነ በስተቀር ለጭቁኑ ህዝባችን የሚበጅ ፋይዳ የለዉም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹ይህ ሽልማት የእኔ ብቻ አይደለም፣ የእናንተም ነው›› እስክንድር ነጋ (ኤልያስ ገብሩ ጎዳና)

 

ዐረቦች (በተለይ ግብፅ፤ ኢራቅ፤ ሶሪያና ሊቢያ) ተገንጣይ ኃይሎችን የደገፉት ኢትዮጵያን ለማዳከም፤ ወደብ አልባ ሊያደርጉን፤ ቀይ ባህርንና ሕንድ ዉቂያኖችን ለመቆጣጠር እንጂ ለኤርትራም ሆነ ለሌሎች ብሄረሰቦች ተቆርቁረዉ አልነበረም። ግብፅ ደግሞ በተለይ እግዚአብሔር የሰጠንን ወንዛችን ገድበን በኤሌክትሪክ ኃይል ከጭለማ እንዳንወጣ፤ በመስኖ ልማት በመጠቀም ከችጋር እንዳንላቀቅ ባላት ጽኑ ፍላጎት ምክንያት ነዉ በተገንጣይ ኃይሎችና በሱዳን የምታስጠቃን። ምዕራቦችም እንደለመዱት ሀገራትን ከፋፍለዉ በትነዉ ለመግዛት እንጂ ለማንም አስበዉ አይደለም። ለአፍሪቃ ቢያስቡ ኖሮ በባርነት፤ በቅኝ ግዛትነትና በእጅ አዙር አገዛዝ አያሽከረክሯትም ነበር። በተለይ ኢትዮጵያ አቸንፋቸዉ በነፃነት ከመቆየቷም በላይ፤ በቅኝ ለተያዙት አፍርቃ አገሮች ነፃነት እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጓ ትልቅ ቂም እንደያዙባት የምናቀዉ ሃቅ ነዉ። እነዚህን የዉጪ መርዞች በቅጡ በመገንዘብ የነርሱ ሰለባዎች ሆነን እናንቀር እያንዳንዱ ዜጋ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል።

 

  1. የጠንካራ ህብረት ወሳኘነት

ዉዲቷ አገራችን ዛሬ ከወደቀችበት መከራ እንድትወጣ እያንዳንዱ ዜጋ ከፍተኛ ህብረት መፍጠር ይጠበቅበታል። ለግል ጥቅም ሳይሆን ጭቁን ህዝባችንን ለመታደግ መበርታት ይኖርበታል። ከዉጪ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጎን መቆም መቅረት አለበት። የተባበረ ህዝብ ይነሳል፤ የተከፋፈለ ይሰበራል። ለየምንኖርባቸዉ ሀገራት የፓርላማ አባላትና ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት አስጠባቂ ድርጀቶች የብሶት ደብዳቤዎች በተደጋጋሚ ማስገባት ይኖርብናል። ከመሃላቸዉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚሰማቸዉ መልካም ሰዎችም አሉና።

ሀገርን የመሰለ ነገር የለም፤ ሀገር እናት ናት – ሕይወታችን፤ መኖሪያችንና መቀበሪያችን። በርሷ ኅልዉና መቀለድ ይቅርታ የሌለዉ ትልቅ ኃጢያት ነዉ።

 

የጨቁኖች አምላክ ይጨመርበት

 

1 Comment

  1. ጥሩ ምክር ነው ! የተቀደሰ ሀሳብ ነው ! ጥቂት የዘመን ጉዶች በስግብግብ የቁስና ሀብት ጥማት ሰክረው አደጋው አልታይ ብሏቸዋል !! ይህ ደሀ ምስኪን ፤ ጦሙን አዳሪ ፤ ፈሪአ እግዘብሔር ያለው ጨዋ ህዝብ ሰላም ከአጣ ቆየ ! ጦሙን ውሎ ጦሙን ለማደርም ሰላም አጥቷል !! እለት እለት እንደባተለ እንደባከነ እንደተከዘ ተስፋው እየመነመነ እየጨለመ ነው ! አዕምሮ ቢስ የቁስ ከርስ ስግብግቦች ሰከን ብለው ሊያዩት ሊገነዘቡ ልቦናቸው ተጋርዷል !! በዚህም ወደ አስከፊው ጨለማ እየገባን …

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share