መሪ አልባው የአማራ ህዝብ

ከባለፉት 50 ና 60 ዓመታት ጀምሮ የአማራ ህዝብ መሪ አልባ ሆኖ ቆይቷል፡፡ መሪ አልባ እንዲሆን ያደረጉት በዋናነት አራት ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላል፡፡

1. በአማራ ክልል ውስጥ በተካለሉ ክፍለ ሐገራት የወጡ “ልሂቃን’” ራሳቸውን በአማራነት ማዕቀፍ ውስጥ አይተው ለአማራ ህዝብ መታገል ራስን ዝቅ አድርጎ እንደ ማየት በመቁጠራቸው ነው፡፡ ይህ አማራ ሆኖ ኢትዮጵያዊ ልሂቅ ነኝ ባይ እንደ እሳቤው በሲቨል ብሔርተኛነት ተደራጅቶ ከፍተኛ ሀይል አግኝቶ አገሪቱን እየመራት ያለውን ንዑስ ብሔርተኛ መታገል አልቻለም፡፡ የፖለቲካል ተለዋዋጭነት (political dynamism) እንኳ ተርድቶ ወቅቱ በሚጠይቀው ፖለቲካዊ አወቃቀር ተደራጅቶ የአማራን ህዝብ ለማታገል አልቻለም፡፡ በተለይ ቀደም ባሉት ዘመናት (60ና 70ዎቹ) በከፍተኛ ትምህርት ተመርቀው በተለያዩ የአለም ክፍሎች ያሉ ምሁራን ተብየዎች በሐይለስላሴ ዘምን የነበረውን የኢትዮጵያ ግዛት አወቃቀር (Territorial administration) ብቻ አዋጪ ነው ብለው እስካሁን ድረስ ሲንገታገቱ ይታያሉ፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት አክራሪ ንኡስ-ብሔርተኝነት ሰማይ ደርሶ እንደማይቀለበስ መረዳት አልቻሉም፡፡ ፖለቲካ በጣም ተለዋዋጭ መሆኑን አልተገነዘቡትም፡፡ እኒህ አማራነኝ ብለው ራሱን ለመጥራት የሚጠየፉ ኢትዮጵያዊ ነን ባይ ልሂቃን ከ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ትርክት የህልውና አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል በመገንዘብ ለወጣቱ ትውልድ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሙከራ አላደረጉም፡፡ በተለይ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የደረሱ ግፎችን በግልጽ ለአማራ ህዝብ ለማሳወቅ የተደረገው ተነሳሽነት አነስተኛ ስለነበር፤ በልሂቃን ዘንድ ቁጭት ተፈጥሮ መሪ መፍጠር አልተቻለም፡፡

2. ደርግና የደርግን መንግስት ለመጣል ይታገሉ የነበሩ ነጻ አውጪ ድርጅቶች ሆን ብለው በኢህአፓ፤ በመኢሶንና በሌሎች ድርጅቶች ይሳተፉ የነበሩ ሰዎችን እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሰዎች በማሳደድና በመግድል የአማራ ህዝብ መሪ አልባ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በተለይ የቀይ ሽብር ጭፍጨፋ ብዙ ተጽኖ ፈጣሪ የአማራ ልጆችን ከማሳጣት ባሻገር ቀረው ትውልድ ፖለቲካንና ኮረንቲን በሩቁ የሚል አመለካከት እንዲይዝና የፖለቲካል ትግል ተሳትፎው ዝቅተኛ እንዲሆን ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል፡፡

3. ወያኔ መራሹ የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ከያዘ በኋላ በትግል ወቅት በአምሳሉ የጠፈጠፈው ኢህዴን ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአማራነት ስለልቦና የሌለው ብአዴን ክልሉን በምስለኔነት እንዲመራ በመደረጉ በክልሉ በራሱ የሚተማመንና ውሳኔ ሰጭ መሪ እንዳይኖር ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል፡፡ ይባስ ብሎ በዚህ ቡድን ተላላኪነት ለአማራ ህዝብ ተቆርቋሪ የሆኑ ሰዎችን በመግደል፤ በማሰርና እንዲሰደዱ በማደረግ መሪ አልባነት እንዲሰፍን ተደርጓል፡፡ የትህነግ ስርዓት አማራ ለስልጣኑ ተገዳዳሪ እንዳይሆን በዋናነት ይጠቀምባቸው ከነበሩ ስትራቴጅዎች መካከል ዋነኛው አቅም ያላቸውን የአማራ ልሂቃን መሰወር፤ መግደልና ማሳደድ ነበር፡፡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና የሌላቸውንና አላማቸው የራሳቸውን ጥቅም ብቻ መሰረት ያደረጉ ሰዎች በስርዓቱ ውስጥ በማስገባት ሎሌ ሆነው እንዲያገለግሉት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ይህ መሰረታዊ ችግር ከ2010 ነውጥ በኋላ ይፈታል የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ያደረ ቢሆንም፡ ችግሩ ከድጡ ወደ ማጡ አየሆነ መጥቷል፡፡ በእኔ ግምት በብአዴን ውሥጥ የተሰገሰገው ህሊና-አልባ ስብስብ እስካለ ድረስ የአማራ ህዝብ መሪ ያፈራል የሚል ተስፋ አልነበረኝም፡፡ ምክንያቱም የድርጅቱ አባላት እሳቤ ፖለቲካ አባል መሆን የሐብት ምንጭ እንጂ ለህዝብ ጥቅም መታገያ አይደለም፡፡ በተጨማሪም በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉ ግለሰቦች አቅም የሌላቸው ናቸው፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካ አካሄድ ተገንዝበው ለክልሉ የሚበጅ ፖለቲካል ስትራቴጅ ሊድፉ አይችሉም፡፡ ሌላው ቢቀር “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”፤ “ስንኖር ኢትዮጵያ ስንሞት ኢትዮጵያዊ የሚሉት የኦህዴድ/ኦነግ መሪ ድስኩሮች” የፖለቲካ ታክቲክ እንደሆነ እንኳ መረዳት የተሳነው ስብስብ ነው ብአዴን ማለት፡፡ በኦነግ የፖለቲካ ትርክት ያደገ ግለሰብ ስለ ሲቪል ብሔርተኝነት (civil nationalism) ሲሰብክ ለይስሙላ ወይም እያሾፈ እንደሆ መረዳት የማይችል ነው ብአዴን ማለት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግብጽ በየአቅጫው ሩጫ ላይ ና - መሳይ መኮነን

አብይ አህመድ እንደ ወላጅ አባቱ (ትህነግ) የአማራ ህዝብ መሪ አልባ እንዲሆን ተመሳሳይ ስልቶችን በመከተል ላይ ነው፡፡ ጥሩ ሎሌ የሚሆኑ ግብዝ ብአዴናውያንን (ደመቀ መኮንን፤ ብናልፍ አንዱአለም፤ ተመስገን ጥሩነህ፤ ግርማ የሺጥላ፤ ሰማ ጥሩነህ) በክልል ደረጃም ሆነ በፌደራል ደረጃ ባሉ የስልጣን እርከኖች ማስቀመጥና ቀጭን ትዛዝ መስጠት አንዱ ስልት ነው፡፡ ጠንካራ አቋም ያላቸውን ግለሰቦች አንድም በማስገደል (ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ጀኔራል አሳምነው ጽጌ)ና ከስርዓቱ በማግለል ለአገዛዙ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ እዚህ ላይ ላነሳው የሚገባ ብዙ ህዝብ የሰኔ 15ቱ የክልሉ ባለስልጣናት ግድያ እርስ በራስ እንደሆነ ያምናል፡፡ በአብይ መንግስት እንደተቀነባበረ የሚያምነው ሰው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ሽመልስ አብዲሳ አባይ ማዶ ሄደን የሰራነውን እናውቃለን የሚለውን አባባል እንኳ ተረድቶ ግድያ ፈጻሚው የአብይ ቡድን መሆኑን መረዳት የቻለው ቤት ይቁጠረው፡፡ የአማራ ደናቁርት አክቲቪሰት ነኝ ባዮች በየሰፈሩ ተቧድነው አንዱን ሟች ወገን ሌላውን ሟች ባዕድ በማድረግ ያሰራጩት የነበረው ፕሮፖጋንዳ በአማራ ህዝብ አንደነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል፡፡ ብአዴናውያንማ ድሮውኑም የሰፈር ኔቶርክ እድርተኛች ስለነበሩ ከ ሰኔ15 በሗላ የቡድን አመራር ፈጥረው የህዘቡን ውስብስብ ችገር ከመቅረፍ ይልቅ እርስ በራሳቸው ሲካሰሱ ቆይተዋል፡፡

ከአንድ የክልል ም/ቢሮ አላፊ መረዳት እንደቻልኩት የብአዴንን ጎጣዊ/ቡድናዊ ኔቶርክ አብይ አህመድ አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ ግንኙነቱ ከቁልፍ የክልል አመራሮች ጋር መሆን ሲገባው ም/ቢሮ ሃላፊ ጋ ደውሎ አለቆቻችሁ መስራት ስላልቻሉ ይህን በአስቸኳይ ሰርታችሁ ሪፖረት አድርጎ እንደሚል መረዳት ችያለሁ፡፡ የኮሌኔሉ ዋና አላማው ስራ እንዲሰራ ሳይሆን በክልል አመራር ተብየው መካከል መከፋፈል እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ቀኝ እጄ የሚላቸው አመራሮች (ግርማ የሺጥላ፤ ተመስገን ጥሩነህ፤ ሰማ ጥሩነህ፤ መላኩ አለበል) በአንድ በኩል በሚፈለገው ደረጃ ፍላጎቴን አያሳኩም በሚላቸው ግለሰቦች በሌላ በኩል መተማመን እንዳይኖር አድርጓል፡፡ እንደ መረጃዎቹ ከሆነ አለመተማመን ስለበዛ የባልስጣናት አጃቢዎች ምድባ የሚደረገው መንደርን መሰረት ያደረገ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ተዋሕዶን ለማወክ የሚፈጸመው የአቢይ አህመድ መንግሥታዊ ሽብር በደል እስከ መቼ?

የክልል አመራሮች አብዛኛውን ጊዜ በፌደራል ደረጃ በሚዘጋጁ ስብሰባዎች ላይ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ማደረግ ሌላኛው የአብይ ታክቲክ ነው፡፡ በፌደራል ደረጃ በሚዘጋጁ ስብሰባዎች የክልሉ ባለስልጣናት እንዲያዘወትሩ የሚያደርገው በሁለት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፡፡ አንደኛው ከላይ ወደ ታች የሚተላለፈውን ትእዛዝ ወይም ውሳኔ ብቻ ተቀባይ እንዲሆኑና በራሳቸው ውሳኔ ክልሉን እንዳይመሩ ማድረግ ሲሆን 2ኛው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ለልማት ስራ እንዳያውሉ ማድረግ ነው፡፡ ቅርበት ካላቸው ሰዎችና ቀደም ሲል የክልል ከፍተኛ አመራር ከነበረ ማህበራዊ ድህረ-ገጽ መረዳት እንደቻልኩት የአዲስ አበባ ስብሰባዎች ካለቁ በሗላ ወዲያውኑ ወደ መደበኛ ስራቸው አይመለሱም፡፡ አዲስ አበባ ከሚኖሩ አማራ ነን ከሚሉ ባለሐብቶች ጋር ውስኪ ቤቶች ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ይነገራል፡፡ የጥገኛ ባለሐብቶች ውስኪ ግብዣ አላማ ያለምንም ሊዝ ጨረታ የሚፈለጉትን መሬት ለመቀበል ሲሆን ባለስልጣኖቹ ደግሞ ቤት ወይም ንብረት እጅ መንሻ ለማግኘት ነው፡፡ ከውስኪ ግብዣ በተጨማሪ የቆንጆ ሴቶች ግብዣ የተለመደ መሆኑን ከቅርብ አዋቂዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ባለሀብቶቹ የባለስልጣናትን መመጋጥ በቪዲዮ በመቀረጽ የምፈለግውን ካላደረክ አጋልጥሀሉ በማለት እንደ ማንገራገሪያ እንደሚጠቀሙበት ይነገራል፡፡ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ሰፊ ክልልን እመራለሁ የሚል የግብዞች ስብስብ ምንያህል የጥቂት ጥገኛ ባለሐብት ና የአብይ አህመድ ስርዓት አገልጋይ እንደሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡

የብልግናው መንግስት ሰጠሁት ባለው የስሙላ መናገርና መደራጀት መብትን ተጠቅመው ህዝብን እያነቁና እያደራጁ ያሉ የአማራ ልጆችን ማዋከብና ማሰር ሌላኛው የአብይ አህመድ የአማራን ህዝብ መሪ አልባ ለማድረግ የሚጠቀምበት ዋና ስትራቴጂ ነው፡፡ ባለፉት 4 አመታት በአመራ ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ማፈናቀልና ግድያ ለሚዲያ በማቅረብ የአብይ Totalitarian regime በማጋለጣቸው በተደጋጋሚ ወደ ወህኒ ቤቶች ሲወረወሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህ አመት እጅግ በተጠናከረ መንገድ ቀጥሎአል፡፡ ለብዙ አማራ ህዝብ እልቂትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ፖለቲከኞችና የጥላቻ ትርክት የሚያላዝኑ የኦሮሞ ጽንፈኞችማ የራሴ ናቸው በሚል እሳቤ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ድጋፍ ይሰጣል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለኢሳት፣ ለኦኤምኤን እና ለሕወሓት በያላችሁበት – ምሕረቱ ዘገዬ (አዲስ አበባ)

4. የመጨራሻው የአማራ ህዝብ መሪ አልባነት ምክንያት ከራሱ ከህዝቡ የሚመነጭ ነው፡፡ በአብዛኛው የአማራ ህዝብ የብሄር ንቃተ-ህሊና ዝቅተኛ ሊባል የሚችልበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ከአብራኩ የሚወጡ ግልሰባዊ ወይም ቡድናዊ ግጭትን እሳቤ በማድረግ ለአማራ ህዝብ ተቆርቋሪ መሪዎችን ለአማራ ጠል መሪዎች አሳልፎ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም በጊዜያዊ ጥቅም በመደለል መሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች ጎን ከመሰለፍ ይልቅ ለጸረ-አማራ መሪዎች ጎን በመሰለፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት የተለመደ ነው፡፡
መፍትሔዎች

1. ከብአዴን ውስጥ ጠንካራ ሰዎች ካሉ (ምንም እንኳ ከዝንጀሮ መንጋ ቆንጆ መምረጥ አስቸጋሪ ቢሆንም) ለእነሱ ድጋፍ መስጠት፡፡ ይህን እንደ አንድ መፍትሔ የወሰድኩበት ምክንያት በፖሊተካው አለም የሴራ ፖለቲካ እንደ ዋና ስትራቴጅ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ስለሆነም ብአዴናውያን የፖለቲካ ሴራ በጣም የገባቸው ባይሆንም በፖለቲካ ውስጥ ካልነበሩት የተወሰነም ቢሆን ይገባቸዋል፡፡ ትህነግም ሆነ የኦሮሞ ብልግና የሴራ ፖለቲካ እንዴት እንደ ስልት እንደሚጠቀምበት በጥቂቱም ቢሆን ያውቃሉ፡፡ የፖለቲካ ሊደርሽፕ በፖለቲካው አለም ስለቆዩ የተወሰነ ልምድ ሊኖራቸው ስለሚችል ነው፡፡

2. በተለያዩ የአለም አገራትም ሆነ በአገር ውስጥ ያለው ተማርኩ የሚለው የአማራን ህዝብ ያለመበትን ችገር ተገንዝቦ ከፍርሐት ቆፈን በመውጣት የህዝቡን ሁለንተናዊ ችግሮች ለህዝቡና ለአለም ማህበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበት አለበት፡፡

ከበሀይሉ ምኒልክ

2 Comments

  1. ምክር ቢጤ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወደ ጽንፍ ለሄዳቺሁ “የአማራ” ፖለቲከኞች/አክቲቪስቶች
    1ኛ፤ ኢትዮጲያ ዉስጥ ከዚህ በኋላ በማንም በምንም መንግስት በጉልበት መቀየር የማይበጅም የማይቻልም መሆኑን መቀበል።
    2ኛ፤ አማራነትን እና ኢትዮጵያዊነትን ማላቀቅ [decouple]፣ “እኛ ብቻ ነን ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ” ከሚል አባዜ መላቀቅ፣
    3ኛ፡ በአማራ ክልል ያለውን አማራ እና በሌሎች ክልሎች ተወልዶ ያደገውን [በተለይ በኦሮሚያ፤በደቡብ እና በሶማሌ ከተሞች ዉስጥ የሚገኘውን] የአማራ ተወላጅ የስነልቦና ልዩነት በአግባቡ ማጤን እና መረዳት። ቢቸና ተወልዶ ያደገ እና ጂማ ተወልዶ ያደገ የአማራ ልጅ አስተሳሰባቸው አይገናኝም።
    4ኛ፡ የአማራ ብልጽግናን (ባዴን) በጠላትነት ከመፈረጅ እና ከማዋረድ ፖለቲካ መቆጠብ እና ተቃውሞውን በልኩ እና በአግባቡ ማድረግ
    5ኛ፡ የአማራን ጥቅም በሰላማዊ መንገድ እናስጠብቃለን ብለው በአማራነት የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን (ለምሳሌ አብን) ማጠናከር እና ወደ መሪ ድርጅትነት ማምጣት። መሪ ድርጅት የሌለው “ትግል” የትም እንደማይደርስ ሰመኑን አዬነው አይደል?
    6ኛ፡ በምርጫ መወዳደር እና አቅምን መፈተሽ
    ከዚህ ዉጭ ምንም የሚፈጠር ተአምር የለም፣ ምናልባት ትርፉ የሚሆነው የራስን ክልል ወደ ሥርዓት አልበኘት መቀየር ብቻ ነው።
    ሃገሬ ሰላምሽ ይብዛ!

    • በእርግጠኝነት ብሄርህ አማራ አይደለም።በአመለካከትህም አማራ ጠል ከሚባሉት የምትመደብ ነህ ከዚህ ቡሇላ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን በሀይል ፈፅሞ አይሆንም ብለሀል ያ ሁኑን ፋሽሽታዊ መንግስት በስልጣን እንዲቆይ በመውደድ ለአንተ ስለተመቸህ ለአማራው ግን ቁጭ ብሎ ተጨፍጪፉ ተገድሎ ከማለቅ እየታገለ በጠላት ለመጣበት ሰይፉን ይዞ መዋደቁ ይጠቅመዋል በጥረቱ ውስጥ ነው በደሉን አይቶ አምላክም የሚረዳው

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share