የኢትዮጵያ ወቅታዊ ቁልፍ ችግር ፌደራል መንግስቱ “የኦሮሞ መንግስት ነው” የሚለው የኦሮሞ ፖለቲከኞች እጅግ አደገኛ ዝንባሌ ነው!!!

 

#image_title

መሰረት ተስፉ (Meserettesfu@yahoo.com)

በየትኛውም አገር ውስጥ  ካለው ስርዓት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ያላቸው ፖለቲከኞች አገር እየመራ ያለው እነሱ የወጡበት ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ነገድ ወይም ጎሳ ነው ሲሉ አይደመጡም። ለምሳሌ ባራክ ኦባማ “በዘሩ” ጥቁር አሜሪካዊ ቢሆንም እሱም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ አጋሮቹ አንድም ቀን አሜሪካን እየመሯት ያሉት ጥቁር አሜሪካውያን ናቸው ሲሉ ተሰምተው አያውቁም ነበር። ኦባማ በግሉም በፕሬዚደንትነት የተመረጥኩት የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖሊሲዎችን አስፈፅማለሁ ስላልኩ  እንጅ ጥቁር አሜሪካዊ  ስለነበርኩ ነው ብሎ የሚያስብ አይመስለኝም።

የብሪታኒያ መሪዎችም  ሃገር እየመራ ያለው  ህዝብ የመረጠው ፓርቲ እንጅ ስኮትላንድ፣ ዌልስ፣ ሰሜን አየርላንድ ወይም ኢንግላንድ  የሚባል ብሄር (አገር) ነው አይሉም።  በእርግጥ ጠቅላይ ሚ/ሩ ከአራቱ ውስጥ የአንደኛው ብሄር (አገር) አባል ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ጎርደን ብራውን እና ቶኒ ብሌየር ስኮታላንዳዊያን ናቸው። ነገር ግን እነሱ ጠቅላይ ሚ/ር በነበሩበት ጊዜ ብሪታኒያን እየመራ ያለው ስኮትላንድ የሚባል ብሄር (አገር) ነው ያሉበት ጊዜ አልነበረም። ቦሪስ ጆንሰንም እንግሊዛዊ ይሁን እንጅ ብሪታኒያን እየመራት ያለው ወግ አጥባቂው ፓርቲ እንጅ እኛ እንግሊዛውያን ናቸው ያሉበትን አጋጣሚ  አላስታውስም።

በሌሎች ሃገሮችም ቢሆን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው ብየ አላምንም። ለምሳሌ ኡሁሩ ኬኒያታ ማንነቱ/ብሄሩ ኪኩዩ ቢሆንም ኬኒያን እየመራት የነበረው ፓርቲው (The National Alliance Party) እንጅ የኪኩዩ ብሄር ነው ሲል የተሰማበት ጊዜ አልነበረም። ሩዋንዳንም ብንመለከት ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ የቱትሲ ማንነት ቢኖረውም ሃገር እያስተዳደረ ያለው ግን እሱ በሊቀመንበርነት የሚመራው Rwandan Patriotic Front እንጅ የቱትሲ ብሄር ነው ብሎ አያውቅም። ሌላውም እንዲሁ፡፡

ወደሃገራችን ተመልሰን ከጥንት ጀምሮ  በተለያዩ ጊዚያት ሃላፊነት ላይ የነበሩትን መንግስታት ስንመለከትም ከፍ ብለን ካየነው የአለም አቀፍ ልምድ የተለየ ነበር ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በንጉሶች ስትመራ በነበረችበት ወቅት ንጉሶቹ “ስዩመ-እግዚያብሄር ነን” ይላሉ እንጅ የሃገሪቱ መሪ እነሱ የወጡበት ብሄር ወይም ብሄረሰብ ነው ይሉ ነበር የሚል ታሪክ አልተመዘገበም። ።

በደርግ ጊዜ ሃገር ይመሩ የነበሩ ፖለቲከኞችም ቢሆኑ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ወታደራዊ ደርግ በኋላ ደግሞ  ኢሰፓ ነው ከማለት ውጭ ፕሬዚደንት መንግስቱ ወይም ጓደኞቹ የወጡበት ብሄር ነው ብለው የተናገሩበት አጋጣሚ አልነበረም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኢየሱስ ህይወት ፤ ሥቅለት ና ትንሣኤ ፤ የፍቅርን ኃያልነት እንማራለን - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመንም ምንም እንኳ ህወሃቶችና አጫፋሪዎቻቸው ሁሉም በእጃቸው ሁሉም በደጃቸው የነበሩ ቢሆኑም ሃገር እየተመራ ያለው በኢህአዴግ እንጅ  በትግራይ ብሄር ነው ሲሉ ተደምጠው አያውቁም። አቶ ሃይለማሪያም ጠቅላይ ሚ/ር ሆኖ ባገለገለበት ጊዜም አገር እየመራ ያለው ወላይታ ነው አልተባለም ነበር።

አሁን ላይ ግን ምቾት የማይሰጡ ዝንባሌዎች መኖራቸውን እየታዘብን ነው። በአንድ በኩል  ሃገር እያስተዳደረ ያለው ዶ/ር አብይ በፕሬዚደንትነት የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ነው ሲባል እንሰማለን። ብልፅግና ደግሞ ፓርቲነቱ የአንድ ብሄር ሳይሆን የሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንደሆነ ነው የሚገለፀው።

በሌላ በኩል ግን የኦሮሞ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን እየመራ ያለው የኦሮሞ ብሄር ተደርጎ እንዲቆጠር የመፈለግ ዝንባሌ  እንዳላቸው የሚያሳዩ ምልክቶች እዚህም እዚያም ይታያሉ። በዚህ ረገድ በምን ስሌት እንደሆነ ለመረዳት ቢያስቸግርም ጃዋር ቄሮን የኢትዮጵያ መንግስት አድርጎ የሰየመበትን ሁኔታ ሁላችንም አድምጠናል ብየ እገምታለሁ። አቶ ለማ መገርሳ በበኩሉ በተለያየ ጊዜ እየተነሳ (የኦሮሞ ብሄር አገር እየመራ ያለ ይመስል) “ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም ተባልን” እያለ ሲናገር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ዶ/ር አብይም በተመሳሳይ መንገድ ሃገሪቱን ኦሮሞ እየመራ እንደሆነ ለማሳየት የሄደባቸው ተግባራዊና ፅንሰሃሳባዊ ርቀቶች እንዳሉ ታዝበናል። ይህን ለመረዳት ደግሞ በአንድ ወቅት “መንግስታችን ተነካ በሚል ስሜት የቡራዩና የሰበታ ህዝብ ግልብጥ ብሎ ሊመጣ ነበር” ያለውን ማገናዘብ ብቻ በቂ ነው ብየ አስባለሁ። አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ላይ ቀርቦ አሁን ያለው መንግስት የኦሮሞ ሲል በጆሯችን ሰምተናል።

ሌላው ቀርቶ የፖለቲካ “ሀሁ”ን በተሻለ ሁኔታ ይገነዘባሉ የሚባሉት አቶ ሌንጮ ለታ እንኳ “ባሁኑ ወቅት ሃገር እየመራን ያለነው እኛ ኦሮሞዎች እንደሆንን “ባእዳን” እንኳ ተቀብለውታል…” ብለው የተናገሩት የዚሁ የኦሮሞ ፖለቲከኞች “ሀገር እየመራ ያለው ኦሮሞ ነው” እንዲባል የመፈለግ ዝንባሌ አንድ መገለጫ ተደርጎ ቢወሰድ ስህተት አይሆንም። አቶ ሽመልስን ጨምሮ ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲከኞች በየፌዴራል መንግስቱ መድረኮች ሁሉ  እንታይ እንታይ የሚሉትም ቢሆን ከተመሳሳይ  ፍላጎት ተነስተው እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም። አሁን አሁን ይህ ዝንባሌ የአገሪቱ ቁልፍ ችግር ሆኗል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ፡ ያቶ ደመቀ ኦነጋዊነት ለማይታያችሁ ዓይነ ግንባሮች - መስፍን አረጋ

የኦሮሞ ህዝብ  ይህን  ዝንባሌ የፈልገዋል ወይ?

በፍፁም አይፈልገውም ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል። ምክንያቱም አንድ ህዝብ እንደህዝብ ፍላጎቱ ከሌሎች ወንድምና እህትቹ ጋር በጋራ ተሳስሮ አገር ማስቀጠል እንጅ በሌላው ላይ የበላይ ሆኖ ማስተዳደር የሚሆንበት አጋጣሚ እንደነበር የሚያሳይ ታሪክ አልተፃፈም። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄም እንደሌሎቹ ብሄር ብሄረሰቦች የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የእኩልነት፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የማደግ፣ የመበልፀግና ሃገር የመገንባት እንጅ በሌላው ላይ ፍላጎቱን የመጫን ይሆናል ብየ አላስብም። ስለዚህ “አገር እየመራ ያለው ኦሮሞ ነው” እንዲባል የመፈለግ ዝንባሌ ያላቸው ፖለቲከኞቹ እንጅ  ህዝቡ እንደማይሆን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።

ታዲያ የኦሮሞ ፖለቲከኞች አገር እየመራ ያለው ኦሮሞ ነው እንዲባል የመፈለግ ዝንባሌ ለምን ይታይባቸዋል?

የኦሮሞ ፖለቲከኞች ይህን ዝንባሌ የሚያሳዩት ከተለያዩ ምክንያቶች ተነስተው ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ። አንደኛው በተሳሳተ ስሌት የኦሮሞን ህዝብ ድጋፍ ያስገኝልናል ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። ከዚህ ጋር የተያያዘውና ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ስም በመነገድ  ድጋፍ እንዳላቸው ለሌሎች የማሳየት ፍላግት ገፍቷቸውም ይሆናል። በፈጠራ ትርክት ተነሳስተው አማራ እንደህዝብ ጨቁኖናል የሚል ቅሬታ ስላላቸው በዚህ ምክንያት የተረኝነት ስሜት አድሮባቸውም እንዳይሆንም ከፍተኛ ስጋት አለኝ።

ይህን አይነት ዝንባሌ ከነሱ አልፈው ሌላው ውስጥ በስፋት ማስረፅ ከቻሉ ደግሞ ልክ የትኛውም ገዥ ፓርቲ ሊያደርገው እንደሚችለው ሁሉ እነሱም በሁሉም ጉዳዮች ላይ አዛዥ ናዛዥ እንሆናለን፤ በተለይም ደግሞ፡

  1. ሁልጊዜም ጠቅላይሚ/ሩ ከነሱ ውስጥ አንዱ ወይም እነሱ የፈቀዱለት ብቻ እንዲሆን  ለማድረግ፤
  2. የፈለጉትን ሰው በሚንስትርነት ለመሾም፣ ካቢኔውንም እንደፈለጉ ለመጠምዘዝ፤
  3. መከላከያና ፖሊስን ጨምሮ የሁሉንም ዋና ዋና ተቋማትሃላፊዎች ሹመትና ምደባ በነሱ መልካም ፈቃድ ለማስኬድ፤
  4. ሃገርአቀፍ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን፣ እነሱ በፈለጉት መንገድ ለማርቀቅና ለመተግበር፤
  5. በጀትድልድሎችና የመሳሰሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ባሻቸው መንገድ ለማርቀቅና ለማስፀደቅ፤
  6. የተቋማት ሃላፊዎችን በፈለጉት ጊዜ ለማንሳት ወይም ለመተካት፤
  7. የአዲስ አበባንና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን ህጋዊ መልክ በማስያዝ ለማስወሰን፤
  8. የሃገሪቱን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ለመቆጣጠር የሚያግደን አይኖርም የሚል እምነት ሳይድርባቸው አልቀረም ባይ ነኝ።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ከአማራ ቆዳ በተሠራ ከበሮ: ጭፋሮ !! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

ፖለቲከኞቹ ይህን ዝንባሌ ማስፋፋትና ማስቀጠል ይችላሉ ወይ? ጥቅሙስ ምንድን ነው?

ዝንባሌውን ማስፋት ይቻል ይሆናል ቢባል እንኳ ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር በቋሚነት ማስቀጠል ይቻላል ብየ አላምንም። ምክንያቱም ህወሓቶች እንደ ኦሮሞ ፖለቲከኞች ፍላጎታቸውን በአደባባይ ባይገልፁም እንኳ በተገባር ግን ሞክረውት እንዳልተሳካላቸውና የኋላ ኋላም የኢትዮጵያ ህዝብ ተንኮላቸውን በሚገባ በተረዳ ጊዜ አሽቀንጥሮ እንደጣላቸው ይታወቃል ። ከጥቅም አንፃር ከታየም የዚህ አይነት ዝንባሌ  አለመተማመንን እና መፈራቀቅን ማስፋት እንጅ ሌላ የሚፈይደው ነገር ይኖራል ብየ አላስብም።

ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው?

መፍትሄውማ የአንዱ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት የተከበረበት፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያይ፣ ማንኛውንም ዜጋ  ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊጠቅም የሚችል፣ የህግ የበላይነት የሰፈነበት፣ ቅንነትና ግልፅነት የተሞላበት፣ ተጠያቂነት ያለው በአጠቃላይም የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ነፀብራቅ የሆነ  ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ ለጊዜው የሚሳካ መስሎ ቢታይም እንኳ ዞሮ ዞሮ ሃገር አፍራሽ እንደሆነ መረዳት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው ብየ አምናለሁ።

ቸር እንሰንብት!!!

 

2 Comments

  1. ግሩም መጣጥፍ፡፡ “አይቶ አያውቅ ዳቦ ፍሪዳው” ይባላል፡፡ ሥልጣን ብርቁ የሆነ ሰው፣ በዚያ ላይ ማይምነትንና ብልሹ አስተዳደግን የደረበበት ጥፉ ዜጋ ኦህዲድ/ኦነግ እያደረገ ካለው የዘለለ ነገር እንዲያደርግ አይጠበቅም፡፡ የምናሳዝነው ለነዚህ የአጋንንት ውላጆች ተላልፈን የተሰጠነው ምስኪን ዜጎች ነን፡፡ አንድዬ በምሕረቱ በቶሎ ይጎብኘን፡፡

  2. “የኦሮሞ መንግስት ነው” የሚለው የኦሮሞ ፖለቲከኞች እጅግ አደገኛ ዝንባሌ ነው
    እነሱ በብእራቸውና በአንደበታቸው የኛ ነው ካሉ አይደለም እንበላቸው? መከላከያ፤ፖሊስ፤ኢኮኖሚውን ተቆጣጥረነዋል ባሉበት ማን ተቆጣጠረው እንበል? ሃቁን አንሽሸው እንጅ አውቀን መፍትሄ እንፈልግ ይችን ካገኙ ሌላ ነው የሚሉት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share