April 2, 2023
11 mins read

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ – መላ መላ ብለው ኅሊናዎን አበርትተው ለንሥሃ ይብቁ! – ከበየነ

ምናልባት የታሪክ አዋቂዎች ምርምር ቢያደርጉበት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በከንቱ የሞተው ዜጋ – ኢትዮጵያ ከአድዋ እሰከ ካራማራ በተካሄደው ጦርነት ከሞቱት ሰዎች ቁጥር ሳይበልጥ የሚቀር አይመስልም። በገበሬዎች አመጽ፣ በተማሪ እንቅስቃሴ፣ በአብዮት ፍንዳታ፣ በቀይና ነጭ ሽብር እንዲሁም ደርግ ከሻዕቢያና ወያኔ ጋር ፍልምያ ሲያደርግ በርካቶች ቢሰዉም፣ በጥቂትዋ የዶክተር አብይ ዘመን በጦር የተጨቀጨቀ አባት፣ በገጀራ የተወጋች እርጉዝ፣ በሳንጃ የታረደ ህፃን ብዛት ለጉድ ነው። ከአድዋ ጦርነት እስከ ደርግ ሥልጣን ፍጻሜ ድረስ 95 ዓመታት አልፈዋል። ምንም እንኳን የሰው ልጅ ሞት መራር ቢሆንም ነገር ግን በ95 ዓመታቱ የሞቱት ኢትዮጵያውያን አሟሟታቸው ምክንያትን ያዘለ ነበር። በነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያውያን የተሰዉት አምባገነንነትን ሲታገሉ አልያም የውጭ ወራሪዎችን ለመመከት ሲሉ ነበር። በዶክተር አብይ ዘመን የሞተውን ማን ገደለው? ለምንስ ሞተ? በምን ምክንያትስ ሞተ? ሃቅ በታሪክ ጸሃፊዎች መዝገብ ላይ ነች።

 

“የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ – ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ” – የተባለላት እናት – የሞተ ልጇን ባትቀብርም አንጀትዋን በገመድ አስራ ለሃገር ኅልውና መሰዋቱን በጸጋ ትቀበላለች። አንድነት ጋሻዋ እምነተ ጠንካራዋ ኢትዮጵያ ዘንድሮስ አቃታት። ሕዝባዊ መንግሥት የተመኘ ሕዝብ አምባገነነት እጫንቃው ላይ ወደቀበት። አምባገነትን የታገለ ሕዝብ ዘረኝነት አጋድሞ አረደው። ዘረኝነትን የታገል ሕዝብ ሽንገላ ከሠብዓዊ ፍጡርነት ውጭ አደረገው። ዛሬ ባህልና እሴት፣ ክብርና ሞገስ፣ ወግና አርአያነት የሉም። ይባሱኑ ሃገር ወዳዶች አልቀው ሃገር ጠሎች በዙ። ኢትዮጵያ ለከፋ መቅሰፍት የተዳራገችው የሥልጣን ዘመኑን በስርቆትና ሌብነት ለማርዘም የመጣው ህወህት በዝቅተኝነት መንፈስ የተጎዱ የግንዛቤ መናጢ ሆድ አደሮችን ጠፍጥፎ፣ ኅሊናቸውን አወላግዶ፣ በውን በህልም ላላሰቡት መንበር አብቅቶ ሽቅብ ሠማይ የሠቀላቸው ጊዜ ነው። ኅሊናው የተወላገደ ሰው ሲሾም አገር ትቆዝማለች። ህወሃት ኢትዮጵያን አቆሳስሎ አሽመድምዶ ቅኝ ገዥዎችን ጮቤ አስረገጠ።

 

ህወሃት አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ አኪሩ ተበጠሶ መቅኖ ራቀው። እጅግ የተንሰራፋው ሌብነትና ዘረፋ እንዲሁም በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸመው መጠነ-ሠፊ ጥቃት አመራሩን አዳክሞ በትረ ሥልጣኑን ድንገት አንሸራተተበት። ኢትዮጵያ እንዲህ ቆሳስላ ተሽመድምዳ ሳለች ነው ዶክተር አብይ ለሥልጣን የበቁት። ዶክተር አብይ ባማረ ልሳናቸው ኢትዮጵያን ቁስሏን በጨርቅ አሰሩላት። ሕዝቧም እናታቸው ከበሽታዋ ታገግም ዘንድ መድኅን አድርጎ በተማመነባቸው መሪ ላይ ተስፋውን አሳደረ። ሕዝቡ – ዶክተሩ መድሃኒት ሳይቀቡ እሾሁን ሳይነቃቅሉ ቁስሉን በጨርቅ ብቻ አስረው በሽታውን ማመርቀዛቸውን የተረዳው ኋላ ላይ ኢትዮጵያ መከራዋ ፀንቶ በወደቀች ጊዜ ነው። አበሰኛይቱ ኢትዮጵያን ጠዝጥዞ የጨረሳት ህገ መንግሥቱ ውስጥ የተሰገሰጉ እንደ ፍላጻ የሾሉ ደም የማይጠግቡ አንቀጾች ሆነው ሳለ ዶክተሩ ግን ከዚህ በሽታ እንድትፈወስ አልፈለጉም።

 

ዶክተር አብይ! ክቡር አቶ ክርስትያን ታደለ ያቀረበልዎትን ጥያቄ በጸጋ ተቀብለው እንደ መፍትሄ ቆጥረው ራስዎን ቢያዘጋጁ መልካም ይመስለኛል። መቼም እርሳቸውም ባይናገሩ የረሃብተኛው ሰቆቃና የሙታን ድምጽ ሳይረብሾት አልቀረም። በከንቱ የሞተው ኢትዮጵያዊ የጣር ጩኸት በሠላም እንደማያስተኛዎት እውን ነው። ወላጆቻቸው ሲገደሉባቸው የተመለከቱ ልጆች ወድያና ወዲህ ሲቅበዘበዙ ማየቱ ማንንም አያስደስትም። በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን የሠቆቃ ድምጽ ጠብቂዎቾን አልፈው፣ የተኙበትን ቤተ መንግሥት ግድግዳና ጣራ ሰንጥቆ ኅሊናዎን መውጋቱን አይሸሽጉም። ደሆች – ለምን ለምን – ሞቱ? የትም የትም ሲሄዱ፣ ችግኝም ሲተክሉም ሆነ አደባባይ ሲያስጌጡ እዬዬና ለቅሶ፣ እሮሮና ዋይታ ይከብዎታል።

 

ውድ ጠቅላይ ሚኒስቴር – በመሪነት የሚሄዱባት ገመድ እየቀጠነች ነው። ብልሹ አስተዳደር፣ ሌብነት፣ ዘረኝነት፣ የግንዛቤ እጥረት፣ ሞት፣ እልቂት፣ ጦርነት፣ ዋይታ፣ ወዘተ፣ ናቸው ገመዷን ያሰለሉት። ሰው ተዘቅዝቆ በሚሰቀልበት፣ ሕጻናት ከኋላቸው በሳንጃ በሚታረዱባት፣ ተማሪዎች በሚታገቱባት፣ ተቃዋሚዎች ታፍንው በሚደበደቡባት፣ አባቶች ባደባባይ በድንጋይ ተወግረው በሚገደሉባት፣ ባለሥልጣናት መሬትን በሚዘርፉባት፣ የአደገኛ እጾች መናኸርያ በሆነች አገር ህግና ሥርዓት አለ ብለው አይከራከሩም። አመራርዎ የሥልጣን ዘመኑን ለማስቀጠል ቢዘይድም የቀጠነችዋን ገመድ አያወፍራትም። በሰለለች ገመድ ላይ እየተራመዱ ድንገት መፈጥፈጦን ካላወቁ የዋህ ነዎት። ለእርስዎ የሚበጀው ወደ ሥልጣን የመጡበትን ዘዴ ረስተው ከሥልጣን የሚወርዱበትን ክህሎት መፈለግ ነው።

 

ውድ ዶክተር አብይ! ወደ ሥልጣን የመጡት በድርጅታዊ ብልሃት ነው። ሥልጣንዎን ግን በብልሃት አይልቀቁ። ከለቀቁ በጥበብ ይልቀቁ። መልቀቅዎ ካልቀረ ታሪክ አቆዩ። የፍትህ ሽግግር እያሉ ቁጥቋጦ ቁጥቋጦውን ከመዞር ይልቅ መከራ የተፈራረቀበትን ሕዝብ እውነተኛ የሥልጣን ባለቤት አድርጉትና ግፍ በፈጸሙት ላይ ፍረድም ይቅርታም ይበይን። መልቀቅዎ ካልቀረ ዳግም ለሌብነት ያነፈነፉ ዘረኞች ወደ ሥልጣን ወንበሩ እንዳይጠጉ ሕዝቡን ባለ መብት አድርጉት፣ ወደ አደባባይ ይውጣ፣ ይናገር፣ ዘረኞችንና ሌቦችን ይገስጽ። ዶክተር አብይ በሥልጣን ዘመንዎ ለተሠራው መከራና ግፍ ራስዎን ተጠያቂ በማድረግ እራስዎንም በስርዎ ያሉትን “ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ” የሆነባቸው አጋርዎችዎን ነጻ አውጡ።

 

ውድ ዶክተር አብይ! እንደው በሻሸመኔ፣ በወለጋ፣ በአጣዬ፣ ጋምቤላ፣ ቤን ሻንጉል፣ ወዘተ፣ በንጹሃን ላይ የደረሰው ግፍ ቢቀመጥ – ቤት ፈረሳው፣ መፈናቀሉ፣ በጅብ ማስበላቱ፣ ገንዘብ ማሸሹ፣ ወዘተ፣ ለሌላ ጊዜ ይቆይና – በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ምድር ላይ በከንቱ ያለቀው የሚሊዮኖች ነፍስ አያሳዝኖትም? ዓይናቸውን በጨው አጥበው ከመጡ ሹመት ወዳዶች ጋር ሲተቃቀፉ – የዛች የአማራ እናት፣ የዛች የአፋር እናት የዛች የትግራይ እናት መሪር ሃዘን አልከነከንዎትም? ዶክተር አብይ እባክዎትን በኢ-ፍትሃዊ ዘረኞች የሚሰቃየው ሕዝብ ፍትህ ይልበስ። አቶ ክርስትያን ታደለ ፖለቲካ አይደለም ያወሩት፣ ለነፍስዎም ለሃገርም የሚበጀውን ነው የተናገሩት። ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ መላ መላ ብለው ኅሊናዎን አበርትተው ለንሥሃ ይብቁ። ሥልጣኑም ወደ ሌላ ጅብ እንዳይተላለፍ ክህልዎቶን ይጠቀሙ። እባክዎትን ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በዘረኝነት፣ በአፓርታይድ፣ በምጣኔ-ኃብት ድቀት የተሰቃየውን – ረሃብ ጥማቱን ችሎ ወቶ የመግባት ዋስትና ብቻ ለሚለምነው ምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሩለት። አመሰግናለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

የኦህዴድ መራሹ ብልፅግና  መንግስት  በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በንጹሀን  ዜጎች ላይ እየወሰዳቸው ያሉ የነፃ እርምጃ  ግድያዎች  መንግስት ያሰበውን የፖለቲካ ግብ ያሳካለታል  ወይ ? በኔ አመለካከት እነዚህ የንፁሃን ዜጎች  የጅምላ ግድያዎች  በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላዎ (double edge sword) ናቸው:: ፩- መንግስት እያሰላው

 የኦህዴድ መራሹ ጅምላ ግድያዎች ስሌት (ሸንቁጥ- ከምዕራብ ካናዳ)

January 24, 2025
እነዶ/ር ደብረፅዮን እና በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መሪዎች እነጌታቸው ረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ሰራዊቱን ወደውግንና አስገብቷል። የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት ባወጡት መግለጫ ውግንናቸው ከእነዶ/ር ደብረፅዮን ጋር መኾኑን አስታውቀዋል።

በትግራይ የተፈጠረው ምንድነው?

January 23, 2025
የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ ምግቧንም ተጋርቶ ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ ማን ይኖራል ከቶ? በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት

ሰው በሰውነቱ – ከ ይቆየኝ ስሜ

Go toTop