ያው አዲስ ነገር የለም። እንደተለመደው እሳቸው ሌላ ዓለም ላይ መሆናቸውን ዛሬም ከዚያው ቦታቸው ንቅንቅ ያላሉ እንደሆኑ ከማሳየት ያለፈ ፍሬ የሚቋጥር፡ እውነት የሆነ፡ ሀገርን ከመጣባት አደጋ የሚያድናትን መፍትሄ የሚናገሩ መሪ ሆነው አላገኘኋቸውም።
በኢኮኖሚ የደቀቀች፡ በግጭቶች አቅሏን የሳተች፡ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ጎሮሮዋ የታነቀ፡ ዘረኝነት የሚያምሳት፡ የዜጎቿ ሲዖል የሆነች ሀገር መሪ አይመስሉም። አሁንም ሌላ ቦታ ናቸው።
ሀቅን ሊኖሯት አልቻሉም። መሬት ላይ ያለውን እውነታ መምሰል ተስኗቸዋል። የእሳቸውን ጉድፍ ለማየት ወኔ ያጠራቸው፡ በአብዛኛው ንግግራቸው የራሳቸውን ድክመትና ክፍተት ”የተቀደሰ” የሌላውን ችግር ”ውእግዝ ከማዕሪዮስ” የሆነ አድርገው ለማሳየት እዚህም እዚያም ሲረግጡ እንጂ ያየኋቸው ወገብ የሚቆርጥ ምጥ ይዟት የምትሰቃይን ሀገር የሚያስተዳድሩ መሪ ፈጽሞ አይመስሉም። እየራበው ያለን ህዝብ ነገ ስለምትበለጽግ ረሃቡን እንደበረከት ቁጠረው የሚሉ ደፋር ሰው ናቸው። ኢትዮጵያ እናንተ ጭንቅላት ውስጥ ነው የፈረሰችው ብለው ሲናገሩ ኢትዮጵያ በእሳቸው የአእምሮ ጓዳ ብቻ በልጽጋ እየታየች ስለመሆኗ ይዘነጉታል። ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ። እሳቸው ወዲያ፡ ሀገሪቱ ወዲህ። አልተገናኝቶም።
አቶ ክርስቲያን ታደለ ”ስልጣንዎን ለመልቀቅ አያስቡምን?” ብለው በትህትና ለጠየቋቸው ጥያቄ ለምን እንደዚያ እንደተገረሙ አልገባኝም። ስልጣን መልቀቅ እኮ ታላቅነት ነው። ለዚያውም ሀገሪቱን እንደዚህ ዓይነት መጠነ ሰፊ አደጋ ላይ የጣላትን መሪ ይቅርና ”ሴትን ልጅ ጎነተልክ” ተብሎ የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ የሚቀርብባት ዓለም ላይ መኖራቸውን ዘንግተውታል። እውነት ለመናገር ለእሳቸው ስልጣን ልቀቁ የሚለው ጥያቄ ሀቀኝነት ያለው፡ ምንም እንከን የማይወጣለት ተገቢ ጥያቄ ነው። በዚህ መልኩ በክብር መጠየቃቸውን ማመስገን ሲገባቸው ለመሳለቅና በተረት ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ ጠያቂውን ለማበሻቀጥ መሞከር ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው።
ቀርበው የኢትዮጵያን ህዝብ ቢያዳምጡትና ስለእሳቸው ምን እያለ እንዳለ ቢያውቁ አቶ ክርስቲያን ያቀረቡላቸው ጥያቄ አያስደነግጣቸውም ነበር። የመለሱበት መንገድ ቅንነት የጎደለው ብቻ አይደለም። ለስልጣን ያላቸውን ጥልቅ ጥማት ያጋለጠባቸውም ጭምር ነው።
ሀገሪቱን በዚህ በኩል እለውጣታለሁ ብለው ሞከሩ። አልተሳካም። ስለዚህ ለሌላው እድል ልስጥ የሚል ታላቅነትን የሚያንጸባርቅ፡ ከእኔነትነት ይልቅ ህዝቤንና ሀገሬን ላስቀድም ከሚል በሳልና አስተዋይ መሪ የሚጠበቅ ትንሹ እርምጃ መሆኑን ጭራሽ አያውቁትም። የኢትዮጵያ የብርሃን መንገድ የእኔ ብቻ ነው የሚል ክፉ ደዌ ደማቸው ውስጥ የተቀበረ መሆኑ እሳቸውንም ሀገሪቱንም መላቅጥ እንዲያጡ አድርጓቸዋል።
ስለዛሬው ውሎአቸው አንድ በአንድ፡ መስመር በመስመር መሞገት ትርጉም የለውም።
እሳቸው አሁንም ሌላ ዓለም ላይ የጀመሩትን ኑሮ መቀጠል መፈለጋቸውን ነግረውናል። ወደእኛ ሊመጡ አልፈቀዱም። ወይም ወደእሳቸው ዓለም ሊወስዱን አልፈለጉም። እሳቸው እዚያ ህዝባቸው እዚህ እየኖሩ እንዴት መግባባት ይቻል ይሆን?