“አይኼኼኼ!!!” – ቀሲስ አስተርአየ

መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ/ም
ቀሲስ አስተርአየ nigatuasteraye@gmail.com

ማሳሰቢያ፦ ካቀራረቡና ከወይዘሮ ውድነሽ ምስል በቀር በዚህች ጦማር የቀረበው የተፈጸመ ነው፡፡ ዶክተር ዓቢይ አቡነ መርቆርዮስን ሲያነጋግሯቸው ወይዘሮ ውድነሽ በቦታው ባአካል አልነበሩም፡፡ ባይኖሩም በስሜታቸውና በመንፈሳቸው ነበሩ፡ እንደምትመለከቱት ጦማሯ የምትገለጸውን የምንፈስ ፍጥጫ ይገልጽልኛል ብየ ስለገመትኩ የሶስቱንም የዐይን ፍጥጫ አቀረብኩት፡፡

ወይዘሮ ውድነሽ አምሳሉ፡፡ “አይ ኼ ኼ ኼ ይህ ነገር አላማረኝም” እያሉ ነው፡፡

ከወይዘሮ ውድነሽ ሕሊና የፈለቀውን ከመግለጼ በፊት በአንባቢ ሕሊና ማን ነበሩ? የሚል ጥያቄ ስለሚነሳ የሳቸው ማንነት አስቀድሞ መግለጹ በተገባ ነበር፡፡ አንባቢ የተነገረውን ነገር ቶሎ ለማግኘት ስለሚጓጓ የወይዘሮ ውድነሽ አምሳሉን ማንነት በማስከተል በሳቸው በዶ/ር ዓቢይና በአቡነ መቃርዮስ መካከል የነበረውን የመንፈስ ፍጥጫ ማስቀደሙን መረጥኩ፡፡ መቼና የት እንደተናገሩ መግለጹ ፍጥጫውን ግልጽ ስለሚያደርገው የተናገሩበትን ወቅት ላስቀድም፡፡

የተናገሩበት ወቅት በማሳሰቢያዋ ላይ እንደገለጽኩት ዶክተር ዐቢይ አቡነ መርቆርዮስን ሲያነጋግሯቸው ወይዘሮ ውድነሽ በአካል በቦታው አልነበሩም፡፡ በአካል ባይኖሩም በፎቷቸው እንደሚታየው በመካከላቸው በክፍተኛ ልዩነት ላይ የተመሰረተ የመንፈስ ፍጥጫ ነበር፡፡ የጽሑፏ መልእክት የፍጥጫቸው ነጸብራቅ ነው፡፡ የሶስቱንም የሀሳብ ፍጥጫ ይገልጽልኛል ብየ የገመትኩት ፎቶ ጋራፋቸው ብቻም አይደለም፡፡ ስነ አእምሯቸው የተገነባባቸው ክስተቶችን የመተርጎም ኃይል ያገኙባቸው የሚደግሙት ዳዊትና ፍቅርን እስከመቃብርን የመሳሰሉ ቀደም ብለው የተጻፉትው መጻሕፍት ነበሩ፡፡

ቀደም ብለው ሕዝብን ያገለገሉ የነበሩት ኢትዮሚድያ አቡጊዳና ቋጠሮ በመሳሰሉት ድረ ገጾች የማቀርባቸውን ጦማሮች ያነቡ ስለነበረ ከሁለት ሳምንት አንድ ቀን ይደውሉልኝ ነበር፡፡ ንግግሮቻቸው ስነ አዕምሯቸው በተቀረጹባቸው መጻሕፍት ላይ የተመሰረቱ ነበሩ፡፡ በዚህ ስጦታቸው ይህች ጦማር ያቀረበችውን ትንግርት ተነገሩ፡፡

ጠቅላይ ምኒስቴር ዓቢይ ሥልጣን ከተረከቡ በኋል ወደ አሜሪካ በመጡ ጊዜ ዲሲ አካባቢ ነበርኩ፡፡ መምጣቴን በስልክ ነገርኳቸው፡፡ ምን እየተካሄደ ነው? ብለው ጠየቁኝ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን እግረ መንገዳቸውን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው ለመመለስ ተዘጋጅተው እንዲቆዩአቸው ነግረዋቸው ወደ ሎሳንጀለስ ሄደዋል አልኳቸው፡፡ “አሁን አንተ የት ነው ያለኸው? አሉኝ፡፡ በዲሲ ዙሪያ ያሉት ግብረ ኃይሎች እነ አቶ ሽመልስ ብቀለና ዮሐንስ ታከለ አቡነ “መልከ ጼዴቅን ልናግኛቸው እንፈልጋለንና አብረውን ይሂዱ ስላሉኝ አቡነ መልከጼዴቅ ወደ አረፉበት ሆቴል እየሄድን ነው እንደደረስኩ እደውልለወታለሁ አልኳቸው፡፡

“አይ ኼ ኼ ይህ ነገር አላማረኝም” አሉ፡፡ ያማረውንና የተሻለውን መንገድ እግዚአብሔር እንዲያሳየን ይጸልዩ ፡ ከሆቴሉ ስደርስ በመካሄድ ላይ ያለውን እነግረወታለሁ ብያቸው ንግግራችን አቋረጥን፡፡ የመጣው እንግዳ ይስተናገድ ወደነበረበትና ለአቡነ መልከጼዴቅ ማረፊያ ክፍል ወደ ተያዘላቸው ሆቴል ሄድን፡፡ ሆቴሉ 501 New York Ave Ne Washington Dc 20002 ላይ ያለው Hampton in Hotel ነው፡፡

ከሆቴሉ ደርሰን አቡነ መልከ ጼዴቅ የሚያርፉበትን ክፍል ስንጥይቅ ገና አንዳልደረሱ ተነገረንና፡ እስኪመጡ ድረስ የምንቆይበትን ቦታ ስንፈልግ አቡነ አብርሃምን አየናቸው፡፡ ከአቡነ አብርሃም ጋራ ጥቂት ከተነጋገርን በኋል ሕዝቡ ወደተሰበሰበበት አዳራሽ ሄድን፡፡ ይመለከተኛል የሚለው ከተለያየ አገር መጥቶ በቡድን በቡድን ሆኖ አቡነ መርቆርዮስ ከዶ/ር ዓቢይ ጋራ ይሂዱ አይሂዱ እያለ ይንጫጫል፡፡ የሚካሄደውን እገልጽለወታለሁ ብያቸው ስለነበር በመካሄድ ላይ ያለውን ለወይዘሮ ውድነሽ በስልክ ገለጽኳላቸው፡፡ “አይ ኼ ኼ ይህ ነገር አላማረኝም” የምትለዋን ሐረግ ደግመው በመናገር ሚቀጥለውን ትንግርት ተናገሩ፡፡

የወይዘሮ ውድነሽ ትንግርት

“ብጹዓን ቅዱሳን የምንላቸው አባቶቻችን፡ እስካሁን በዓለምና በመላ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁት እርስበርሳቸው ተጣልተውና ተኳርፈው የጸብና የኩርፊያ አገልጋዮች ሆነው ነው። ባባትነታቸው ጸብን እያወገዙ የተጣላውን እያስታረቁ እግዚአብሔርንና ሰውንም እንዲያገለግሉ የተሰየሙለትን የማስታረቅ ተልእኮ መፈጸም ሲገባቸው ተልእኳቸውን እርስ በርስ ከሚጣላውና ከሚያጣላው ፖለቲካ እግር በታች እንዲወድቅ በማድረጋቸው አንገታችንን እንድንደፋ አድረገውናል፡፡ አሁን ደግሞ የከፋ ስሕተት ሊደገም ነው” ብለው ንግግራቸውን ቀጠሉ።

“አዲሱ ፖለቲከኛ ዶ/ር ዓቢይ የሚባለው ታረቁ ማለቱ መልካም ነው። የፖለቲካ ስራውን ፓትርያርኮችን በማስታረቅ መጀመሩም የተቀደሰ ነው። ኢትዮጵያ የሚባለውን ስም ጠልተው ሲያስጠሉና ቤተ ክርስቲያንን ከፍለው ሲያከፋፍሉ የቆዩት ፖለቲከኞች በአካል ተወግደው፤ የኦርቶዶክስን ቤተ ክርስቲያን ከአማራው ጋራ ሰበርነው የሚለው ፉከራቸው ጠፍቶ ፤ ኢትዮጵያ እናት አገራችን እያለ፤ ታሪካዊት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችንንም አገር ናት እያለ ሲመጣ እንደተአምር በመቁጠር ዶክተር ዓቢይን አሁን የማይደግፈው የለም።

በዚህ አመጣጡ ብንደግፈውም በፖለቲከኛ የሚጀመር ነገር እንደ አማረ የማያልቅ መሆኑን የቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን መዘንጋት የለብንም። ሰውየው የማስታረቁን ተግባር ከመልካም ህሊና ሊያደርገው ቢችልም እንኳ ፖለቲከኛ ነውና ውሎ አድሮ ወደፖለቲካው ውስጥ እየሰመጠ ሲገባ መመጻደቂያ ለማድረግ መፈተኑ አይቀርም። የሱን ፖለቲካ ለሚወዱት ለሚከተሉትና ለሚደግፉት የነካው የዳሰሰው የተናገረውና የተነፈሰው ሁሉ ፈውስ መድኃኒት የሚያዝናና የሚያቀናጣ ሆኖላቸው ሲያስፎክራቸው ፤ በአመራሩ ለሚጎዱት ጢስና በርበሬ እየሆነ ማስጮሁ ማስነጠሱና ማስለቀሱ የሚቀር አይደለም፡፡ አፋቸውን ለማሲያዝና ዐይናቸው ላምስጨፈን የሚበትነውን አፈርና ገለባ ማግበስበስ ይጀምራል፡፡

ያደረኩላችሁን ሌላውን ሁሉ ብትረሱት ብጹአን ቅዱሳን የምትሏቸውን የሃይማኖታችሁ መሪወቻችሁንች ያስታረቅሁላችሁ እኔ አይደለሁም!እናንተ ናችሁ!እያለ ማሸማቀቁ አይቀርም። ብጹዓንና ቅዱሳን የምትሏቸው መሪወቻችሁ መታረቅም ማስታረቅ የማይችሉ ደካሞች በመሆናቸው የኛ ደቀመዝሙር አይደለም እንዴ!ያስተረቀላችሁ! እያሉ የሃይማኖት ማህበርተኞቹ በኛ በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ መሳለቃቸውም አይቀርም። ታዘቢም ለካ ሲኖዶሱን ያስታረቀው ለፖለቲካው ማዳበሪያና ማዳመቂያ ለማድረግ ነው የሚል ትዝብትና ነቀፋ በራሱ ላይ ይሰነዝርበታልና ለራሱም ቢሆን የሚበጀው አይመስለኝም፡፡ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይም አሰደቡን አዋረዱን በሚል ስሜት በሁለቱም ፓትርያርኮች ላይ የመረረ ጥላቻ ያሳድራል” አሉኝ ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የግለሰቦች ውስጣዊ ፍላጎት ማርኪያ የሆነው የብሄረሰብ ጥያቄና መዘዙ! - ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)    

ታዲያ ምን ማድረግ ይሻላል? አልኴቸው። “ቀድሞም ያጣላቸው መንግሥት ነው ሲባል ነበር። አሁን ይህ ሰው በትረ መንግሡን ጨብጦ ታረቁ ካለ፡ ሁለቱ ፓትርያርኮች ፈዘው በያሉበት የተቀመጡት ምን እየጠበቁ ናቸው? ሁለቱም ከየተቀመጡበት ተነስተው፡ ድሮም ያጣላን መንግሥት እንጅ ከሰላምና ከፍቅር በቀር አኮራርፎና አቆራርጦ ይህን ያህል ዘመን የሚያቆይ ጸብ በመካከላችን አልነበረብንም ተባብለው እርቁን ራሳቸው ፈጥነው መፈጸም ይገባቸዋል።

አቡነ ማትያስ ፈጥነው ከመንበራቸው ተነስተው ወደ አሜሪካ መጥተው ተበደልኩ ተገፋሁ የሚሉትን አቡነ መርቆርዮስን፤ ወንድሜ ባስቀየምኩዎ ይቅርታ ያድርጉልኝ አብረን እንሂድ፤ የተደራረበ ስብራት የታወጀባቸውን ቤተ ክርስቲያናችንና አማራውን በየደብሩና በየመንደሩ እየዞርን ይቅርታ እየጠየቅን ተሰብረው ከወደቁበት እናንሳቸው፡፡ ከተበተኑበትም እንሰብስባቸው ብለው ለማስታረቅ ከተሰለፉት ሽማግሎች ጋር ብቻ ይዘዋቸው ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱ ለሁሉም የሚበጅ ይመስለኛል” አሉ ።

ወይዘሮ ውድነሽ በመቀጠልም “ሁለቱ ፓትርያርኮች ይህን እንዲያደርጉ ለመርዳት እንደጉዱ ካሣ የሚያስከትለውን አደጋ አሻግራችሁ የማየት አቅም ሊኖራችሁ በተገባ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ያላችሁ እናንት ካህናት ብዙወቻችሁ ማንነታችሁን ለይቶ ማወቅ የማይችለውንና በልማድ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመላለሰውን የሕዝብ ቀልብ ወደራሳችሁ እየሳባችሁ አላቢውን ቆሞ እንደሚጠብቅ የላም መንጋ ባጠራችሁለት በረት እየከተታችሁ ቆሞ እንዲታለብ በማፍዘዝ ላይ ናችሁ። የቀራችሁት ካህናት ራሳቸሁን ባእድና ገለልተኛ አድርጋችሁ በመታዘብ ላይ ናችሁ ።

እነደ ቀደሙ አባቶቻችን የዘመናችን ካህናት በአብነቱ ጉባዔ ትምህርት ተኮትኩታችሁ ያደጋችሁ ብትሆኑ ኖሮ ከዚህ ሁሉ ደካማ አስተሳሰብ ተላቃችሁ ቤተ ክርስቲያችን በጻፈችው በቀኖናዋ ችግሩን ለመፍታት በመጣር ለፖለቲካውም ለቤተ ክርስቲያንም የሚበጅ ትልቅ ስራ በሰራችሁ ነበር“ አሉ።

“ለቤተ ክርስቲያንም የሚበጅ ጉዱ ካሳ የሰራው አይነት እኛ ካህናቱ በዚህ ጉዳይ ላይ የምንሰራው ስራ ምን ይመስለወታል? ብየ ጠየኴቸው። እሳቸውም “ሁለቱም ፓትርያርኮች ከፖለቲካው ቀድመው በመተራረቅ ቅድም የነገርኩህን እንዲያደርጉ መምከር ነዋ!” አሉ። ቀጠሉና “አንተስ ብትሆን የማንን ጎፈሪ ታበጥራለህ? ከጥቂት አመታት በፊት ከከንሳስ ወደ ዲሲ መጥተህ አቡነ መርቆርዮስ ቀድሰው ሲያቆርቡ አብረህ ቀድሰህ ቆርበሀል። አቡነ መልከ ጼዴቅም የሚወዱህ አባትህ ናቸው፡፡ ግልጽ ባታደርገውም ከውስጡ ሲኖዶስ ይልቅ የውጩ ሲኖዶስ ደጋፊ መሆንህ በምትጽፋቸውና በምትናገራቸው የታወቀ ነው። ከፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋርም የጊዜው ፖለቲካ ለያያችሁ እንጅ ካንተ የበለጠ ቀራቢ አልነበራቸውም ፡፡ በመታረቅ የቀድሞ ፍቅራችሁ አሁን ተመልሷል ሲባል ስምቻለሁ። ለሁለቱም ፓትርያርኮች ለምን ይህን ሐሳብ አንተ አታቀርብላቸውም?” አሉ።

“በዚህ ወቅት ከራሴ ጀምሮ አንድ ቀን አቡነ መርቆርዮስን አይቷቸው የማያውቀው ሁሉ ከያለበት ተሰብስቦ አጋፋሪ፡ አስተናባሪ፡ የቅርብ መካሪ፡ አስተናባሪ፡ ሆኖ ከቧቸዋል፡፡ ሁሉም አብሮ ለመግባት ልቡ ቆሟል፡፡ መንፈሱ ስክሯል፡፡ ካባውን ሻንጣውን እያዘጋጀ ነው፡፡ በዚህ መንፈስ በሰከረ ህዝብ መካከል ይህን ሐሳብ ለአቡነ መርቆርዮስ ለማድረስ እድሉ የለኝም፡፡ እድሉ ተገኝቶ ባካፍላቸውም አብሮ ለመሄድ ልቡ በቆመው ሁሉ ተደብድቤ ከመባረራ በቀር የሚፈጸም አይደለም” አልኳቸው፡፡

በሚቀጥለው ቀን ከወይዘሮ ውድነሽ ጋራ በስልክ ተገናኘን፡፡ “እንዴት እየሆነ ነው? ብለው ጠየቁኝ፡፡ “የተሰበሰበው ሁሉ ከዶ/ር ዓቢይ ጋራ ይሂዱ ወይስ አይሂዱ” እየተባባለ በመነጋገር ላይ ነው አልኳቸው፡፡

“አይ ሄ ሄ ሄ ጉድ ሌላ ጉድ ሊፈጠር ነው” አሉና “አንተ ጉዱ ካሣን ለመሆን ለምን አትሞክርም?”አሉኝ። እንዴት አድርጌ?አልኳቸው።

“ለአቡነ መቃርዮስ የነገርኩን በማካፈል የራስህን ጉድ ፍጠራ ! ” አሉኝ፡፡ አይፈጸምም እንጅ የሚፈጸም ቢሆን ፤ በብዙ ሕዝብ በመከበብ ላይ ካሉት ከአቡነ መርቆርዮስ ይልቅ የነገሩኝን ሀሳብ ማቅረብ የሚቀለኝ ለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ነበር አልኳቸው። “ታዲያ ምን ያዘህ? ለምን አትሞክርም?

አሉኝ፡፡ የዚያኑ ማታ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስንና እኔን አቀራርቦ ባስታረቀን ወዳጃችን አማካይነት ለአቡነ ማትያስ ሀሳቡን አቀርብንላቸው፡፡

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስም “መልካም ሀሳብ ነው ለማድረግ እሞክራለሁ” አሉኝ። በበነጋው አቡነ ማትያስን በስልክ አግኝቼ መንገሬንና እንደተስማሙበትም ለወይዘሮ ውድነሽ አካፈልኳቸው። ወይዘሮ ውድነሽም “ያድርጉት አያድርጉት የራሳቸው ሀላፊነት ነው። አንተ ግን

ሀላፊነትህን ተወተሀል። አሁን ጉዱ ካሣ መሆንህን ተረዳህ አደል? ” አሉኝ። በሚቀጥለው ቀን ጠ/ ምንስቴር ዓቢይ ክሎሳንጀለስ ወደዲሲ ተመልሰው መጡ፡፡

ፓትርያርክ ማትያስ መጥተው ይዘዋቸው ይሄዳሉ ብለን በተስፋ ስንጠብቅ ዘገዩብን፡፡ ለምን እንደዘገዩ በስልክ ጠየኳቸው። “ባካባቢየ ላሉት ሀሳቡን አካፍያቸው ነበር፡፡ የሚሆን አይደለም። ያካፈልኳቸው ሰወች ቀደም ብሎ ሀሳቡ ቢደርሰን መልካም ነበር፤ አሁን ግን ሁሉም ነገር በዶ/ር ዓቢይ አመራር በተቃኙ ሰዎች እጅ ላይ ስለወደቀ፡ ብቻየን ላደርገው አልቻልኩም” የሚል መልስ ሰጡን፡፡ ይህንን ለወይዘሮ ውድነሽ አካፈልኳቸው ።

ወይዘሮ ውድነሽ ስርዝ ድልዝ እያስተካከሉ የፍቅር እስከ መቃብርን ረቂቅ በሚጽፉበት ጊዜ፡ በጭንቅላታቸው ተቀረጾ የቀረ በእነ ፍታውራሪ መሸሻና ፍታውራሪ አሰጌ ጊዜ የነበሩት ካህናት ችግሩን ከማቃናት ይልቅ፤ በጥፋታቸው ይተባበሩ ስለነበሩት ስለ እነ ቄስ ሞገሴ ጉዱ ካሳ የተናገረውን ጠቀሱት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠላቶች - በገ/ክርስቶስ ዓባይ

“የራሳቸው ሀሳብ የሌላቸው የሰውን ሀሳብ ብቻ ከዓይን ከግንባር እያነበቡ አይተው የሚተረጉሙ ሆዳቸውን እየሞላ የሚመሯቸውን

የሚከተሉ ክህነታቸውንና ተግባራቸውን ለሆዳቸው የሸጡ የለወጡ ናቸ ው” የሚለውን ጠቀሱና በመቀጠል “አየ አለመታደል አቡነ ማትያስ እነ ቄስ ሞገሴን በመሳሰሉ ሰዎች ተከበዋል ማለት ነው” አሉ። ቀጠሉና “በዙሪያቸው የከበቧቸው ሊቃውንቱን የሚያሳዱዱትን እነ አባ ሞገሴን በቤተ ክርስቲያችን ሀብት ከማበልጸግ በቀር፡ ለቤተ ክርስቲያን ለሀገርና ለህዝበ ክርስቲያኑ እስካሁን የሰሩት የለም። ከእንግዲህም የሚሰሩት አንዳች ነገር እንደማይኖር የታወቀ ነገር ነው” አሉ፡፡

ወይዘሮ ውድነሽ እንዳሉትም፤ እርቁ ከተፈጸመ በኋላ ችግሩ እየዋለ እያደረ ከቀድሞው እጅግ እየከፋ ሄደ። አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ። ምእመናን በጀዋር ትእዛዝ በሜንጫ በየቦታው ታረዱ። ወጣት ልጃገረዶች ታፈኑ” እየተባለ በሚወራው ሁላችንም በሐሳብ ባሕር የገባንበት ወቅት ነበርና ወይዘሮ ውድነሽ የአቶ መብራቱ ቦጋለ ሁኔታ ትዝ ብሏቸው የሚቀጠለውን ተናገሩ፡፡

“መነሻውና መድረሻው በማይታወቀው የሀሳብ ባህር ጠልቀው፤ ያለፈው የህይወት ታሪካቸውና ወደፊት የሚገጥማቸው አንድ ላይ ተጠራቅሞ ተደባልቆ የፈጠረው ጥልቅና የሀሳብ ማዕበልና ሞገድ እያላጋቸው ራሳቸውን እያወዛወዙ ዓይኖቻቸውን ለበስ አርገው ለምን ሚስት አገባሁ? ለምን ልጅ ወለድኩ? ከድሮው ኑሮየ ምን ቀለለልኝ? ምንስ ተሻለኝ? ባሰብኝ እንጅ! ” (ፍቅ ም 2 ገጽ 22) እያሉ አቶ ቦግአለ መብራቱ ለጠፋው ልጃቸው ለበዛብህ ካነቡትና ካፈሰሱት እንባ የባሰና የከፋ ዛሬ ከኢትዮጵያውያን ወላጆች ዐይኖች እየጎረፈ ነው” አሉ። ቀጠሉና “አሁንስ ማየቱም መስማቱም ሰለቸኝ። አላይም ብየ ዓይኔን አልጨፍን። አልሰማም ብየ ጆሮየን አልዘጋ” ብለው በዚህ ዘመን መኖራቸውን ተጸየፉት፡፡

ከሶስት ቀናት በኋላ የወይዘሮ ውድነሽን ማረፍ ሊቀማእምራን ዶክተር አማረ ካሣየ አረዱኝ። በቤተ ክርስቲያናችን የሚደረገው ሁሉ ነገር የሚያስከትለውን ጉዳት አሻግሮ የሚያይ ሰው በጠፋበት ወይዘሮ ውድነሽ መረዳታቸው እጅግ ገረመኝና አንድ ሰው ይህን ዓለም ለቆ ሲሄድ ክፉ ሲያደርግ ኖሮ ሲናገር ሲዘርፍ ሲቀማ ኖሮ ሲለይ ከሰራው ሁሉ በደል አንዲት አትጥቀሰም፡፡ ይልቁንም ያልሰራውን ያልተናገረውን እየተፈለገ ተጽፎ ይነበብለታል፡፡

የወይዘሮ ውድነሽ በዶ/ር ዓቢይ ሽምግልና የተፈጸመውን እርቅ የተመለከቱበት በከተማ ከምንኖር የዘመኑ ካህናት ይቅርና ከዘጉ ባህታውያን የተሰወረውን ያዩበት ርዕይ በቤተ ክርስቲያናችን ስንክሳር ከተጻፉት ትንግርቶች መጻፍ ያለበት እንደሆነ አሰብኩ፡፡

ጉዱ ካሣን “የራሳቸው ሀሳብ የሌላቸው የሰውን ሀሳብ ብቻ ከዓይን ከግንባር እያነበቡ አይተው የሚተረጉሙ ሆዳቸውን እየሞላ የሚመሯቸውን የሚከተሉ ክህነታቸውንና ተግባራቸውን ለሆዳቸው የሸጡ የለወጡ ናቸው” እንዲል ካስገደዱት የከፋን በመሆናችን እንኳን የተናገሩት እንዲጻፍ ልናደርግ እንዲነግርላቸውም አንፈቅድም፡፡

ለታሪክ ተጽፎ ይቀመጥ በማለት “በፍቅር እስከ መቃብር” በሚል ርእስ ግንቦት 30 ቀን 2012 በጻፍኩላቸው ለአርባቸው መታሰቢያ ከክቡራን አባቶቻቸው በወረሱት የማስተዋል ጥበብ በሲኖዶስ እርቅ ምንም የተሻለ ነገር እንደማይመጣ ይልቁንም የባሰ መከራና ሥቃይ እንደሚከተል የተናገሩትን ትንግርት በግጥም አጅቤ ጻፍኩት ፡፡

ማን ነበሩ?

አቡነ መርቆርዮስ በጠቅላይ ምንስቴር ዓቢይ ታዝለው መግባታቸው ለቤተ ክርስቲያን የሚያስከትለው ፋይዳ እንደሌለው ወይዘሮ ውድነሽ ብቻ የተመለከቱበትና ከሁሉም እንዲለዩ ያደረጋቸው ጥበብ ምንድነው ? አንተንስ ይህን እንድትጽፍላቸው ምን አደፋፈረህ? የሚል ጥያቄ ካስተዋዮች ሊነሳ ይችላል፡፡ ዘመኑ ውሸት ጽፈው ውሸት ተርከው እንዳይገለጥበቸው በሌላ ውሸትና ትርክት የሚጋርዱ ጸሐፊወች የበዙበት ዘመን ስልሆነ ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ታዲያ የምመልሰው የጻፍኩት ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ አይደለም፡፡ እውነት ለሚቀምጥበት ክቡር ጽላት ለሆነው ለአንባቢ ጭንቅላት ለመጠንቀቅ ጭምር ነው፡፡

“እሙነ ይበጽሖሙ እምኀበ አስተርአየሰ ዘእንበለ ሐሰት ፡፡ ወጥዩቀ ይከውን ቃለ ጽድቅ”(ሲራ 31፡8) ማለትም፦ ከግላዊ ጥቅም ክብርና ከንቱ ውዳሴ መሻት የነጻ ሕሊና የነበራቸው፡ የእግዚአብሄርን ስም በከንቱ ከሚጠቀሙ ከዘመናችን ፈርሳውያንና ሰዱቃውያን እጅግ የራቁና ካሳሳች ምልክቶች ንክኪ የተጠነቀቁ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊት ሕልመኛ ነበሩ፡፡

ሕግ እንተረጉማለን መመሪያ እንጽፋለን ትንቢት እንናገራለን የሚሉትን ፈርሳውያንና ሰዱቃውያን “ምሽት ላይ ሰማዩ ስለቀላ ብራ ይሆናል ትላላችሁ፡፡ ንጋት ላይም ሰማዩ ቀልቷል ከብዷልም ዝናም ይዘንባል ትላላችሁ፡፡ የሰማዩን ገጽታ ትልያላችሁ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም”(ማቴ 16፡2_4) ብሎ ክርስቶስ ከገጸሳቸው ሰዱቃያንና ፈሪሳውያን እጅግ የከፋን፦በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን ባካባቢያቸው የተከናወነውን የምንክድ፡ በፊታችን የሚፈጸመውን በደልና ግፍ ለማያት የተሳነን እውሮች ወደፊት የሚከተለውን አሻግረን የማያት የተሳነን እንስሶች በበዛንበት መካከል መገኘታቸው አስደንቆኛል፡፡

“ወጉርዓኤ ይፈልጦ ሉኩሉ ጣዕመ እክል ፡፡ ወከማሁ ልቡ ለጠቢብ ይፈልጥ ነገረ ሐሰት”(ሲራ 36፡24) ወደ ሆድ የሚገባውን የእህልን ጣእም መምረሩንን መጎምደዱንና መጣፈጡን ምላስ ያውቃል፡፡ በጉረሮ አልፎ ወደ ሆድ እንዳያልፍ ያደርጋል፡፡ እንደዚሁም የጥበበኛ አእምሮ ማስተዋል የሚያዛባ ውሸት ወደ እውቀቱ ቋት እንዳይገባ ይጠነቀቃል” የሚለውን ጠንቅቀው የተገዘቡ ኢትዮጵያዊት ነበሩ፡፡

“ያለፈው የህይወት ታሪካቸውና ወደፊት የሚገጥማቸው አንድ ላይ ተጠራቅሞ ተደባልቆ የፈጠረው ጥልቅና የሀሳብ ማዕበልና ሞገድ እያላጋቸው ራሳቸውን እያወዛወዙ ዓይኖቻቸውን ለበስ አርገው ለምን ሚስት አገባሁ? ለምን ልጅ ወለድኩ? ከድሮው ኑሮየ ምን ቀለለልኝ? ምንስ ተሻለኝ? ባሰብኝ እንጅ! ” (ፍቅ ም 2 ገጽ 22) እያሉ አቶ ቦግአለ መብራቱ ለጠፋው ልጃቸው ለበዛብህ ካናቡትና ካፈሰሱት እንባ የባሰና የከፋ የእንባ ጎርፍ ዛሬ ከኢትዮጵያውያን ወላጆች ዐይኖች እየጎረፈ ነው” ብለው ከሲኖዶሱ እርቅ ጋራ አያይዘው ወደፊት ኢትዮጵያንና ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሚገጥሟቸውን መከራና እልቂት ተናገሩት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመከራ መንስዔ (ኢህአዴግ ) ለመፍትሄ አይሆንም ?

ውለታቸው የማይረሳው ታላቁ ምስክር ክቡር አቶ አዲስ ዐለማየሁ “ውለታዋን አልረሳውም” በማለት የመሰከሩላቸው መረሳት የሌለባቸው ታላቅ ትንግርተኛ ነበሩ፡፡ ሆኖም ፍቅር እስከመቃብርን የሚያነብም የሰሚምም የሚያስታውሰው ደራሲውንና አንባቢውን እንጅ የወይዘሮ ውድነሽ ትረት ተረስቷል፡፡

“የበሬውን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ ከኋላ ተንስቶ ቀድሞ በመድረሱ” እንደተባለው፦ በሬ አርሶ ጎልጉሎና አበራይቶ ለምርት ያደረሰውን እህል በመጨረሻ የደረሰው ፈረስ ምርቱን ወደ ጎተራ እንዳደረሰው፡ አቶ ወጋየሁ ንጋቱ በተሰጣቸው የውርድ ንባብ ጸጋ ለሕዝብ ጆሮ ቢያደርሱትም፡ በቁም ጽሁፋቸው አበራይተው ወቅተው ለሕትመት አውድማ ያደረሱት ወይዘሮ ውድነሽ ናቸው፡፡

ራሳቸው ክቡር አቶ አዲስ ዓለማየሁ “ከብዙ ስርዝና ድልዝ ጋራ የጻፍኩትን የመጀመሪያውን ረቂቅ እህቴ ውድነሽ አምሳሉ በብዙ ትጋትና ጥንቃቄ እንደገና ደህና አርጋ ባትጽፍልኝ ኖሮ ብዙ ችግር ይገጥመኝ ስለነበረ ውለታዋን አልረሳውም” ብለው የመሰከሩላቸውን መሰረት በማድረግ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ “ወይዘሮ ውድነሽ በፍቅር እስከ መቃብር” በሚል ርእስ ግንቦት 30 ቀን 2012 ባቀረብኩት መታሰቢያ የተናገሩትን ትንግርት ጽፌአለሁ፡፡

በወጣት ዘመናቸው ፍቅር እስከመቃብርን ባስተካከሉበት “ብዙ ትጋትና ጥንቃቄ” በእርግና ዘመናቸው በሲኖዶስ እርቅ በኋላ የሚከተለውን የባሰ እልቂት ተመልከተውበታል፡፡ ይህችን ዓለም ለቀው በተለዩባት ወቅት ሕዝበ ክርስቲያኑ በነጃዋር ሰይፍ የሚታረዱበት፡ ልጃገረዶች ታፍነው ተወስደው ወላጆች የሚያለቅሱበት፡ አብያተ ክርስቲያናት የሚቃጠሉበት፡ እነ አቶ በቀለ ገርባ በአዲስ አበባ ፍንፍኔ የሚለውን ስም የተኩበት፡ የነጻነት ምልክት በሆነው ፊደላችን ቁቤ

የሚባለውን የቅኝ ገዥወችን ፊደል የሰነቀሩበት፡ የሰው ልጅ በኮረና ቫይረስ እየታነቀ ያለቀበት ወቅት ነበር፡፡ ከህልፈታቸው ጋራ የተገናኙትን ክስተቶች በማካተት መታሰቢያ ትሆናቸው ዘንድ በ40 ቀናቸው ከዚህ በታች የሰፈረውን ይህችን ግጥም አዘጋጀሁላቸው፡፡

ሰወች ሲሞቱ አይታ በነጀዋር ሜንጫ በደብሮች መቃጠል ሰው ሁሉ ሲንጫጫ ታየች ስትመንን አልፋ በደምበጫ ከመሰንበት መሞት ሆነ የሷ ምርጫ መበላቱን ጠላች ቆማ በቁንጫ ጠፋች ብትፈለግ በጎንቻ በሜጫ ከእግር እስከ ራሷ ተከናንባ ቢጫ። ብላ በመናገር ወስኛለሁ እኔ በአዲስ አባ መኖር መሰለኝ ኩነኔ ተውት ቤቴ ይፍረስ መረጠኩኝ ምናኔ ስሟ ተቀይሮ ከሆነ ፍንፍኔ በደብሬ አልቀበር አይግባ አስከረኔ መሆን መርጫለሁ አባ ዓለም ለምኔ። ልቧ እየተከዘ መንፈሷ እየባባ ብላ እያለቀሰች ወይ አዲስ አበባ ተዋርዳ ስታያት በበቀለ ገርባ ሄደች ላትመለስ እየረጨች እንባ ሁሉም ከሆነ እንዲህ ትቢያና ገለባ

የሚታዘልበት ከፈለገ አንቀልባ
ልቅር እንደወጣሁ እሬሳየ አይግባ።

ፈረንጅ የጻፈውን የውጩን ሲያደንቁ
አንች የጻፍሽውን ለማንበብ ሲንቁ
አዬ ድንቁርና አለመሆን ብቁ
እንደ ድመት ጸጉር በመብነን አለቁ።
እዚያው እርስ በርሳቸው እየተናነቁ።

እንዳች ለመሆን ሴቱ ቢለካካ።
ማንም አልተገኝም አንችን የሚተካ
አንች ሴቱን ሁሉ ትበልጫለሽ ለካ
አንችን ለመሸኘት ሴት ወንዱ ተነሳ
ሰብለን እንደሸኛት እንደ ጉዱ ካሳ
ሰብለ የተባልሽው ለካ አንች ነሽ እሳ።

ለኔና ለገብሬል የገርሽን ነገር
ለምን ትይናለሽ አይወሳ ይቅር
ይደበቃል ብለሽ ያንች ገድል ምሥጢር።

ምን እንመልሳለን ለዘመዶቻችን
ስትጠፊ እያየን ከመካከላችን
እርም እንዳይሆንብን ዝም ማለታችን
መጮህ አናቆምም እስኪዘጋ አፋችን።እኛ እናከብራለን ያአዲስን አደራ

እንድናስታውስሽ አብረን ከሱ ጋራ አዝማሪ ቢረሳሽ ስምሽን ባይጠራ መሬት ቀውጢ ሆኖ እስኪነሳ አቧራ ናወድሳሻለን ቆመን በየተራ። ስምሽን ባይጠራ ወጋየሁ ንጋቱ የዝናሽ ምስክር አይቀርም በከንቱ። ከእግር እስከ ራሷ ቢጫ ልብስ አጥልቃ የዝወትር ኩታዋን ቀሚሷን አውልቃ ተፈላጊነቷን መወደዷን አውቃ ከዘመድ አዝማዷ ከሰው ተደብቃ ተሰወራ ጠፋች በሌሊት ጨረቃ። ቴዴ በህሊናው፤ አሻግሮ ያየሽ አበባ ስትቀስሚ፡ ንቢቷን ሆነሽ ሰብልየ ሰብልየ፡ ሰብለዓለም ያለሽ ለአዲስ ዓለማየሁ ንቢቱ አንች ነሽ። ማርና ወለላ ፡ ጧፍም ያመረትሽ። ከወለላው ማርሽ የወጣው ሰፈፍ ባአዲስ ዓለማየሁ ተደረገ ጧፍ ወያኔ ለማጥፋት ቢያናፋ ወናፍ ነበልባሉ ታየ ካጽናፍ እስካጽናፍ። አዲስ ተነሳና በጨለማ ታጥቆ የሚቀርጸው ብዕር ሲፈልግ ሸምበቆ የፈጠረው አምላክ ፍላጎቱን አውቆ አንችን ቀረጸለት እጅግ ተጠንቅቆ በመገረም ሞተ ተደንቆ ተደንቆ። ወረቀት ሲፈልግ ረፍዶ እስኪመሽ አምላክ የራመመሽ ብራና አንች ሆንሽ። ተለየሽኝ ብሎ አዲስ ሲወቅስሽ ባለመከተልሽ በመዘግየትሽ ተባበርሽው ዛሬ በመቃብርሽ። የዲሲ ወይዛዝርት የተላቀሳችሁ ውድነሽ አምሳሉ የሞተች መስሏችሁ አለች አልሞተችም ተረጋጉ አይዟችሁ ተሰወረች እንጅ አለች በውስጣችሁ ታግሳችሁ ቆዩ እስከትጠራችሁ ወደሷ ለመሄድ በየቀጠሯችሁ ምንም ብትዘገዩ ታገኟታላችሁ።

በሕይወት ያለነውን ደቂቀ አዳም እንደ እስስት እያነቀ ከሚገለው ኮሮና ቫይረስ ጋርዶና ጠብቆ በአካለ ሥጋ ያገናኘን። ከአርባ ቀናት በፊት በሞት ከተለዩን ከናታችን ወይዘሮ ውድነሽና ቀደም ብለው ከዚህ ዓለም ከተለዩት ፍቅር እስከ መቃብርን ከደረሱት ከክቡር ዶ/ር አቶ አዲስ ዓለማየሁ፡ ካነበቡት፤ ከተረኩት ካአቶ ወጋየሁ ንጋቱ ጋራ እግዚአብሔር በሰማይ ያገናኝኝ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share