ማሪዮ ዴ አንድራዴ- ሳኦ ፖውሎ ከ1893-1945 ገጣሚ፣ መጽሀፍ ደራሲና የሙዚቃ ሳይንቲስት
ትርጉም ፈቃዱ በቀለ( ዶ/ር)
እስካሁን የኖርኩበትን ዕድሜዬን ቆጠርኩኝ፤ ከእንግዲህ ወዲያ የምኖረው ጥቂት ዓመታት ብቻ እንደሆነ ተረዳሁ።
ልክ እንደህፃን ልጅ ይሰማኛል። አንድ ህፃን ልጅ አንድ ኮሮጆ ውስጥ የታሸገ ከረሜላ ካሸነፈ በኋላ የመጀመሪያውን በጉጉት ያላምጠዋል። እያላመጠ ሲሄድ አንድ ብቻ ሲቀረው የመጨረሻው የበለጠ ይጣፍጠዋል።
ከቁም ነገር ይልቅ ስለውስጥ ደንብና አሰራር፣ እንዲሁም ህግ ብቻ በሚነገርበት ትላልቅ ስብሰባዎችና ዲስኩሮች ላይ በመገኘት ጊዜዬን ማባከን በፍጹም አልፈልግም። ይህ ዐይነቱ ስብሰባ ምንም ዐይነት ውጤት ሳይታይበት የመጨረሻ መጨረሻ ይዘጋል። እንደዕድሜያቸው ልክ አዕምሮአቸው ያልበሰሉና ድርጊታቸው ሁሉ የማይረባ ሰዎችን ማየት በፍጹም አልፈልግም። እንዲሁም በጣም ዝቅተኛ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ለመታገልና ለመጨቃጨቅ በፍጹም ጊዜ የለኝም። ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የሚቅበጠበጡ፣ በራሳቸው ንግግር በሚረኩና ደረታቸውን ከሚነፉ ሰዎች ጋር መታየት በፍጹም አልፈልግም። አታላዮችንና አድርባዮችን እንዲሁም በውሸት ሌላውን ለማሳመን የሚፈልጉ ሰዎችን ማየት ይቀፈኛል።
የሰውን ችሎታ በመጥፎ የሚተረጉሙና፣ራሳቸውን አጉልተው ለማሳየት የሚፈልጉ፣ የዝቅተኝነት ስሜት ያላቸውንና ቀናተኞችን እሸሻለሁ። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችን ሳይ መንፈሴ በጣም ይረበሻል።
ውጤት በሌላቸው ትላልቅ ዲስኩሮች ላይ ለመካፈል በፍጹም አልፈልግም። ከእንግዲህ ወዲያ የምኖርበት ዕድሜዬ አጭር ስለሆነ ቁም ነገር ለማየትና ወደ ውጤት የሚመነዘር ነገር ላይ ማተኮር ያረካኛል። የምኖርበት ዕድሜዬ አጭር ስለሆነ ነፍሴ ቸኩላለች። ብዙ ጣፋጭ ያለበትን ኮሮጆ አልፈልግም።
የሰብአዊነት ባህርይ ካላቸው ሰዎች ጋር ብቻ ለመገናኘት እመኛለሁ። በስህተታቸው የሚስቁ፣ በውጤታቸው ግን የማይፈነድቁና በስሜት የማይታወሩ ሰዎችን አደንቃለሁ።
ቀድመው ለኃላፊነት የተመረጡ ከማይመስላቸውና፣ ኃላፊነትንም ከማይሸሹ ሰዎች ጋር መሆንን እመርጣለሁ። ለሰው ልጅ ክብር ጠበቃ ሆነው የሚከራከሩ፣ ለሀቅ የቆሙና፣ ህግ እኩልነትን ማስፈን እንዳለበት የተረዱ ሰዎችን ማየት እሻለሁ። እንደዚህ ዐይነት አመለካከትና መንፈስ ብቻ ነው ለህይወት ትርጉምን የሚሰጠው።
የሰውን ልብ ረገብ ከሚያደርጉና የሌላ ሰው ብሶት ከሚሰማቸው ሰዎች ጋር መሆን በጣም ያስደስተኛል። በህይወታቸው ውስጥ ከባድ ነገር ሲደርስባቸው ይህንን እንደትምህርት የሚቆጥሩና፣ በጥሩ ምክር ደግሞ አዕምሮአቸው እየበሰለ የሚመጣ ሰዎችን አደንቃለሁ።
አዎ ! በጣም ቸኩያለህ። ብስለትን የሚሰጠኝ ጠለቅና ከበድ ያለ ስራን እመኛለሁ። ቶሎ እንደሚበን ነገር በጊዚያዊ ህይወት መርካትን አልፈልግም። የቀረኝን አጭር ጊዜ በከንቱ ለማባከን አልፈልግም።
እስካሁን ካሳለፍኳቸውና ካባከንኳቸው ጊዜዎች ይልቅ የመጨረሻው ጊዜዬ በጣም ጣፋጭና ጠቃሚ እንደሆነ እረዳለሁ። ዓላማዬም የመጨረሻ መጨረሻ ጥሩ ነገር ሰርቼ ይህችን ዓለም በጥሩ መንፈስ ለመለየት ብቻ ነው የምመኘው።
ሁለት ህይወቶች አሉኝ። ሁለተኛው ህይወት የሚጀምረው አንድ ህይወት ብቻ እንዳለኝ ሳውቅ ብቻ ነው።