ፍልፈሉ ቀበሮና ቁማር የተጫወተባቸው በጎች!

ቀበሮ 

ላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ጉድጉዳድ ሲምስ የኖረ ቀበሮ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጉድጓድ ሲቆፍር የበለዘውን ፊቱን ቅባት ተቀብቶ፤ አይኑን  ተኳኩሎና የበግ ለምድ ለብሶ ኢትዮጵያ የሚባል አሞሌ ጨው ይዞ ብቅ አለ፡፡  ኢትዮጵያ የሚለውን አሞሌ ጨው ያዩ የኢትዮጵያ በጎችም ጉረኖ ተመታሰርና ተመታረድ የሚያድን የበግ ነፃ አውጪ መጣ ብለው እንኳን በምድር  የሚራመዱ በሰማይ የሚበሩ ፍጥረታትም ጉድ እስቲሉ ፈነደቁ፡፡ ድምጣቸውን አጥፍተው መስካቸውን ሲግጡና የት እንደነበሩ የማይታወቁት ከርሳም በጎች ሳይቀር ተጠራርተው የበግ ለመድ የለበሰውን ቀበሮ ከበው ፌስታ አደረጕ፤ ጸሎትም አደረሱ፡፡ እነዚህ በጎች “ከባችሁ የምትጨፍሩለት ፍጥረት ጉድጓድ ሲምስ የኖረና ቁማር ሊጫወት የመጣ የበግ ለምድ የለበሰ ቀበሮ ነው”  ቢባሉም “ያለ አዋቂ ወሬ ነው፤ ጆሯችን አይሰማም፤ መሰሚያችን ጥጥ ነው! አሉና የሚመክራቸውን ፍጡር ሁሉ አጣጣሉ፤ ገላመጡ፡፡

የቁማሩ መሳካት የልብ ልብ የሰጠው የበግ ለምድ የለበሰው ቀበሮም ፈገግ ብሎ  “ኢት ብኣ!” ሲል በጉረኖ ውስጥም በውጪም ያሉት የበግ መንጋዎችም ሜዳውን ሞልተው ተከትለው ያለማቋረጥ “ብኣ! ብኣ! ብኣኣ!  እያሉ ዓለም ጉድ እስቲል ጪፈራውን አስነኩ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ሳንባቸውም፣ ልባቸውም፣ እስትፋሳቸውም አሞሌ ጨው የያዘው የበግ ለምድ የለበሰው ቀበሮ እንደሆነ ጮክ ብለው ያለ ሐፍረት በአደባባይ ተናገሩ፡፡ በተለይ ተውጪ ያሉት በጎች በሁለት እጅ የማይነሳ የለመለመ ላታቸውን እንደ ጋሊሊዮ ፔንዱለም እያወዛወዙ የፈረንጁንም የኢትዮጵያውንም በግ ጭፈራ ለወራት አስነኩ፡፡

ፀጉርን እንደ አለላ በቀለም ዘፍዝፎ ማደር ሽበትን ደብቆት እንደማይቀር ሁሉ መቀባባትና መኳኳልም እውነተኛ መልክን ወይም ተፈጥሮን ለዘላለም ደብቆት አይቀርም፡፡ ይህም በመሆኑ የቁማርተኛው ቀበሮ የበግ ለምድ እየሳሳና እንደ አሮጌ አቡጀዲ እየተቀደደ መጣ፤ ኩሉ እንደ ኮሸሽላ ቅጠል ረገፈ፤ ቅባቱም እንደ ግራር ቅርፊት ተቀረፋ፡፡ ይኸንን ጉድ የተመለከቱ ከበው ሲደንሱ ከነበሩት ዘልዛላ በጎች አንዳንዶቹ የቁማርተኛውን ቀበሮ እውነትኛ መልክ ማየት ሲጀምሩ መብረቅ እንደመታው ዛፍ ክው ብለው ደርቀው ቀሩ፡፡ አብዛኞቹ ግን ቁማርተኛው ቀበሮ የሚላቸውን እንጅ ዓይናቸውን ስለማያምኑ “ብ ኣ ኣ ኣእኣ!  ያሉ አሁንም ቀበሮውን እንደ ጅራት ይከተላሉ፡፡ የተቀሩት ደሞ “ቀበሮ የበግ ለምድ ለብሶ ተበግ መሐል ይገኛል ብለን አልመንም ቃዥተንም አናውቅ ነበር” እያሉ የብሶት ድምጣቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዳያስፖራዎች ቤት ግብዣ | በእውቀቱ ስዩም

በግ ከተፈጠረበት ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ “ደጋግሜ ተሳስቻለሁ!” ብሎ ስተቱን አምኖና ከስህተቱ ተምሮ የራሱንም ሆነ የትውልዱን ኑሮ አሻሽሎ ስለማያውቅ እነዚህ በጎችም የእነሱን የማስተዋል ድህነትና ዘልዛላት ለመሸፋፈን ቀበሮ የተፈጠረበትና የተካነበትን ሙያ ስለሰራ ቀበሮን ኮንነው ራሳቸውን ቅዱስ አድርገው ቁጪ አሉ፡፡

ዳሩ ግን እነዚህ ተሳስተናልን የማያውቁ ቀበሮን ኮናኝ በጎች የሚኮንኑት ቀበሮ ተኳኩሎና አዲስ የበግ ለምድ ለብሶ እኛ በጎች በቅዱሱ መጽሐፍ 69 ጊዜ ተጠቅሰናል እያለ ነገ ቢመጣ ተውስጥም ተውጪም እንደገና ተጠራርተውና ሜዳውን ሞልተው ምድር ቁና እንስተምትሆን ይደልቃሉ፡፡

በግ የቀበሮን አፈጣጠር፣ አስተዳደግና  ቅድመ ታሪክ  ተረድቶና አንጎሉን በሚቅበዘበዘው ዓይኑና በሚያነፈንፈው የአፍንጫው ቀዳዳ ውስጥ ተመልክቶ ምን የሸር ድሪቶ እንደሚደርትና ምን ዓይነት ቁማር እንደሚቆምር አስቀድሞ ማንበብ እስካልቻለ ድረስ እግሮቹን በጉረኖ ሲታሰርና አንድ በአንድ እየተነጠለ ሲሰዋ መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ የፍልፈል ቀበሮና የዘልዛላ በጎች ታሪክ ጥንት እንዲህ ነበር፤ ዛሬም እንደዚህ ነው፤ በግ ራሱን ወደ አንበሳነት ታልቀየረ የወደፊት ታሪኩም እንደዚሁ የሚቀጥል ነው፡፡

መጋቢት ሁለት ሺ አስራ አራት  ዓ..

 

 

1 Comment

 1. እውቁ ገጣሚና ምሁር ደበበ ሰይፉ “የብርሃን ፍቅር” በተሰኘው የግጥም መድበሉ ላይ እንዲህ ይለናል።
  ከተማው ተይዞ ሲጣል ምድረበዳ
  ሰው ከራሱ በቀር ለሌላው እንግዳ
  ሆኖ ሲውል ሲያድር በብቸኝነቱ
  ሞተች ይላል ዓለም ውስጣዊ ፍጥረቱ።
  የሃገራችን ችግር ማባሪያ የሌለው የሐምሌ ዝናብ ነው። አንድ ጋ ሲቋጠር ሌላው ጋ እንደሚላላ ቋጠሮ። ይህ ግን እኛው በእኛው ላይ የምናመጣው የመከራ ዶፍ እንጂ ፈጣሪ ስለተቆጣ ወይም የሃገሪቱ የበደል ክምር ሰማይ ላይ ስለደረሰ አይደለም። ሰው ደንዝዟል። ሰው ከዘመን ዘመን ከሚወርድበት የጭቋኞች ቅጥቀጣ እፎይታ ባለማግኘቱ ከጊዜው ጋር አብሮ ተሞ ጥቂትም ቢሆን ለመሰንበት ከሚያደርገው ደመነፍሳዊ ግብ ግብ ውጭ ነገርን ረጋ ብሎ ለማየት ጊዜ የለውም። የቀኑ አለቆቹም አይፈቅድለትም። በእንባ ምድራችን የምትድን ቢሆን ኑሮ የአርቲስት ደሳለኝ ሃይሉ እንባና ሰቆቃ በበቃ ነበር። ግን ከሰማይም ከምድርም ሰሚ የለም። የሚያስቡ ሰዎችን ጭንቅላት ከሚቀላ መንግስት ጋር ምን አይነት የሰውኛ ቋንቋ መነጋገር ይቻላል? የሚያሳዝነው ትሻል በትብስ መተካቷ ነው። አሁን በስልጣን ልክ እንደ ወያኔ ጢምቢራቸው የዞረው ኦሮሞዎች ያኔም ዛሬም ተመልሰው የሚያላዝኑት አማራው ላይ ነው። እውነቱ ግን ጭራሽ ከዚህ ጋር አይገናኝም። ፓለቲከኞች ለመኖር ሰውን መከፋፈል ሙሉ ሥራቸው ነው። ሃገር ወዳድና አቃፊውን ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ በጥቂት ስመ ተምረናል የፓለቲካ ውሾች አስተሳሰብ በርዘው ይኸው እንሆ እየገደሉና እያስገደሉ፤ እየዘረፉና እያፈናቀሉ ይገኛሉ። በጭፍን ጠ.ሚን የሚደግፉ ሰዎች ሰውየውንና በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ሚዛን ላይ በማድረግ ሊመለከቷቸው ይገባል። ዛሬ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ፤ በኦሮሞ ክልል በሚባለው የአፓርታይድ መንደር የምናየው መቻቻልን፤ መተጋገዝን ሳይሆን ሃገራ አፍራሽ ስራዎችን ነው። ሂሮሽማና ናጋሳኪ በቦንብ የነገለባት ጃፓን ከአሜሪካ ጋር በሰላም ስትኖር በውሸት በሚተረክ ትርክት የሰከሩት የኦሮሞና የወያኔ መሪዎች ዛሬም የሚያላዝኑት በአማራው ላይ ነው። የጠ/ሚን አመራር ምጡቅ አድርገው የሚያዩ ሁሉ በጣፋጭ ቃሉ የተሸወድ ናቸው። ልብ ያለው እነማን ይታፈናሉ፤ ይደበደባሉ፤ ይፈናቀናሉ፤ ቤታቸው ይፈርሳል፤ ከሃገር ይባረራሉ በማለት አሃዛዊና ሲፈለግ በሚገኝ መረጃ የዛሬዎቹን የኦሮሞ ጌቶቻችን መፋለም መቻል አለበት። እንዲሁ በደፈናው ኢትዮጵያ አትፈርስም እያሉ ስለ ደሰኮሩ አፍራሽ ሥራ አይሰሩም ብሎ መገመቱ ቂል መሆን ነው። ሴራቸው ልክ እንደ ወያኔ ጥልቅ ነው፡ የተቃመሱትም የወያኔን ፓለቲካ ነው። እስቲ ይታያችሁ ትግራይ በአማራ በአብይና ኤርትራ ጦር ተወረረች በማለት ሰብስቦ እሳት ውስጥ የማገዳቸው የጦርነት ጉዳተኞች ላይ ወያኔ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱ ሮጠው እንዲያመልጡ ነው? ስንቶች ናቸው ሙሉ አካል ያላቸው? ግን የስመ ነጻ አውጭ ተግባር ሁሌ ባርነትን ማምጣት ነው። ወያኔ እንዲያውም በጥይት አልቆላቸውም። ሻቢያ እኮ እዚያው በተሰበሰቡበት ነው በጥይት የፈጃቸው። ግን ሙትን ማን ያስታውሰዋል? እነዚያ ሙታን ተረስተዋል! እንግዲህ ይህንና ሌላውንም የግፍ ሥራ እያየ ከአጥፊ ሃይሎች ጋር አብሮ የሚራመድ የበግ መንጋ ውድቀቱ የሮም ነው የሚሆነው።
  ባጭሩ አሁን በሃበሻው ምድር የሚታየው የፓለቲካ ሽኩቻና እሰጣ ገባ ከበፊቱ ቢከፋ እንጂ አይሻልም። እስቲ አዲስ አበባ ኦሮሚያ ባንክ ብቅ በልና በአማርኛ ጉዳይ ለማስፈጸም ሞክር። ግልምጫው ስድቡ መጉላላቱ። በማይገባህ ቋንቋ መሰደቡና መገፋቱ የቀን ተቀን ተግዳሮት ነው። ይህ ነው አንድነት? ሰው በዛገና በሻገተ የፓለቲካ እይታ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል? አሁን የእንደመሩም የመጽሃፍ ጋጋታ እውነትን ለመደበቅ እንጂ እየጨፈለቁና እየቀነሱ መደመር የለም። እንግዲህ በበጎች መሃል ያለውን ተኩላ ተግባሩንና የማታለያ ዘዴውን ለይቶ ላልተረዳ በተኩላዎቹ እስኪበላ ድረስ አብሮ ይንጎድ። የሚያስብ ሰው ግን ራሱን ለይቶ ለእውነትና ለመላ ሃገሪቱ ዜጎች ዘብ ይቁም። የዘርና የቋንቋ የክልል ፓለቲካው አፍሪቃን እንደ ቅርጫ ሥጋ ከተቀራመቱት የነጭ ገዥዎች የተቀዳ ጊዜና ዘመን ያለፈበት የመንደር አስተሳሰብ ነው። አክ እንትፍ እንበለው። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share