ሕዝብ የሰወች ስብስብ ነው ። እግዚአብሔር ሰውን ከሌሎች ፍጥረታት ለይቶ ሲፈጥረው እንዲያስብ ፣ እንደያሰላስል ፣ በአምላክም ተራዳይነት በእውቀትና በጥበብ ተሞልቶ በዚች ዓለም እስካለ ድረስ እየለፋ ፣ እየጣረ ፣ መብቱና ግዴታውን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ኑሮውን መግፋት እንዳለበት እውነታውና የኑሮ ትብህሉ ያስተምራል።
የሰው ልጅ በጋርዮሽ ዘመን ይኖር ከነበረበት የኑሮ ዘይቤ ከወጣ በኋላ በተለይ የግል ንብረት በተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ቁጥጥር ስር እየሆነ ሲመጣ በዘመናት መካከል ሕጎች ፣ ደንቦች ፣ በኛ አባባል ፍትሐ ነገስት ፣ ፍትሃ ብሔር ፣ ወንጀለኛ መቅጫ ወ.ዘ.ተ. ርቆና ፀድቆ የሰው ልጅ በሰላምና በመከባበር መኖር ከጀመረ ዘመናት አልፈዋል።
“ሕዝብ “ ተመሪ ሁኖ “መሪምችም” ከሕዝብ መካከል በዕውቀትም ሆነ በጥበብ ሻል ያሉት ፣ በሕዝብ ተደማጭነት ያገኙ ፣ በአንፃራዊነት ሃገርን ከጠላት አደጋ የማዳን በቂ ኃይልና ችሎታ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚታሰቡት ፣ በአንፃራዊነት የተሻለ የምጣኔ ሃብት ወይም ጥሪት ባለቤት መሆናቸው ሲረጋገጥ የሃገራት መሪ ሆነው ሃገራትን በወጉና በልኩ እንዲመሩ የሕዝብ እሽታን ያገኛሉ።
በእግዚአብሔር ፈቃድና ችሮታ የህሊና እና የሃሳባዊ ልቡና ባለቤት የሆነውን ሕዝብን መምራት የሚቻለው በዕውቀትና በጥበብ ተሞልቶ እንጂ በኃይል ፣ በጉልበት ፣ በተንኮል የተጠላለፉ አጀንዳዎች በመስጠት ፣ ሕግን በመጣስና በማንለብኝነት መሆን እንደሌለበት የአምላክም ቃል ሆነ ሳይንሱ ፍንትው አድርጎ አስቀምጦታል።
ከላይ ያለውን ፅንሰ ሃሳብ መሰረት አድርገን በአሁኑ ስዓት ሃገረ ኢትዮጵያን እየመራ ያለው “ብልፅግና” የተባለው ፓርቲ ያዋጣኛል ብሎ የያዘውን የአማራር ስልት እንገመግመዋለን።
ባለፉት ድፍን አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ እያየነው ያለው የተመሪ/ሕዝብ/ና መሪ/ብልፅግና/ ግንኙነትን በሃይማኖት ቀኖና ይሁን በሳይንሱ ፅንሰ ሃሳብ አዛምደን መሳ ለመሳ ስንገመግመው መሪ ተብየው ብልፅግና አውሬ ፣ ገዳይ ፣ ሽብርተኛ ፣ የእንስሳነት ባህሪ ያለው ፣ እስስት ወ.ዘ.ተ. ሲሆን ተመሪው ሕዝብ ግን መግቢያ ያጣ ፣ በሰላም ዕጦት የሚንገላታ ፣ አምላክን “ውረድ ወይም ፍረድ” ብሎ እየፀለየ “ምን መዓት መጣብን “ በማለት ግራ ተጋብቶ ህይወቱን በሰቀቀን የሚገፋ ሲሆን የመንግስት ስርዓቱም እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ እየተንፏቀቀ ይገኛል።
የሚገርመው “ ዝምታ ወርቅ ነው” ብሎ የእግዚአብሔርን ፍርድ እየተጠባበቀ ና “ አገር ከምትፈርስ እኛ እንታገስ” በሚል አርቆ አሳቢነት ፀጥ ያለውን ሰላማዊ ሕዝብ ተርቱ እንደሚለው “ዝም ያልከው በልብህ እየሰደብከኝ ነው” ብሎ በቡጢ እንደሚማታ የጠገበ ጎረምሳ ታጋሹን ፣ መሳሪያ ያልታጠቀውን ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር የተላበሰውን ታላቁን እና ስመ ገናናውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዱርና ከበርሃ የመጡ ፣ ወፍ ዘራሾችና በበታችነት ልክፍት የተወጉ ጥርቅምቅሞች ቀን ሰጥቷቸው ሕዝብን እያንገላቱ ፣ እያሰቃዮ ፣ እየገደሉ ፣ መውጫ መግቢያ እያሳጡ ፣ እያሸበሩ ወ.ዘ.ተ. ነው።
በቅርብ እንዳየነው የአድዋ ድልንና የቅዱስ ጊዮርጊስን ዓመታዊ ንግስ ሊከውኑ የመጡትን ሕፃናት ፣ እናቶች ፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎችን ከተከበረው ቅድስ ቦታ ገብተው ማሸበር ፣ በጭስ ማፈን ፣ በቆመጥ መግረፍ ፣ ማቁሰልና መግደል በማንኛውም የኢትዮጵያ መንግስታት ዘመንና ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም። እንደሚታወቀው የሃይማኖት ተቋማት ፣ ዮንቨርስቲዎች ፣ ትምህርት ቤቶች ሆስፒታሎች ውስጥ የመንግድት የታጠቀ ኃያል እንዳይገባ በሕግ ማዕቀፍ የተከለከለ ነው።
እንግዲህ የብልፅግና መንግስት ሕግ አውጭዎች ፣ ሕግ ተርጓሚዎችና አስፈፃሚዎች ዘመኑን የማይመጥኑና የማይዋጁ ስጋ ለባሽ እንስሶች መሆናቸውን ለማወቅ ምርምር አያስፈልገውም።
“ሲበዛ ይገለማል” እንዲሉ በበደል ና ግፍ እየትንገሸገሸ ያለው ሕዝብ “ ሞት ላይቀር ጣረሞት” ብሎ እየተፋለማችሁ ፣ ብቃ እያላችሁ እና ከዚህ በፊት ከነበሩት መሰል ክፉ መሪዎች በተለየ መልኩ. “እየናቃችው” ነው።
አንዳንድ የሰባህዊ መብት ተሟጋች ፣ ማህበራዊ እንቂ ነን ባዮች ፣ የመንግስት ቃል አፈ ቀላጤዎች ፣ አስመሳይ የበየነ መረቡ ባለቤቶች ፣ የስማ በለው ጋዜጠኛች ወ.ዘ.ተ. ቡድኖችና ግለሰቦች ከብልፅግና የተለያየ አጀንዳዎችን እየተቀበሉና እያራገቡ የሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች ፣ የበቃን የምሬት ጩኅቶች ፣ የለውጥ የመንደርደር እምርታዎችንና ኩነቶችን ለመገደብ ፣ ለማዳፈንና ለማስረሳት የሚያደርጉት አጀንዳ የማስቀየስ የወረደ አካሄድና ደባ በጣም ያሳፍራል ፣ ከዚህ ድሪጊታቸው እንዲቆጠቡ እንመክራለን።
የሚገርመው ደግሞ ይህን የአጃንዳ ማስቀየሪያ ፣ ማዳፈኛና ማረሳሻ ድርጊት በረቀቀ መልኩ ሽንጣቸውን ገትረው እየከወኑ ያሉት በሃገርም ሆነ በውጭ ሃገራት እንደ እንጉዳይ የፈሉት የብልፅግና ፓርቲ ተከፋዮች ፣ አሸርጋጆች ፣ አቃጣሪዎች ፣ ሹምባሾች ፣ የድል አጥቢያ አርበኞች ፣ ነገረ ሰሪ የበይነ – መረብ ባለቤቶች ፣ ማህበራዊ አንቂዎችና ጋዜጠኞች ናቸው።
ላለፉት አምስት ዓመታት የብልፅግናን መንግስት “ይበል ፣ አልንልህ“ እያሉ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩለት የነበሩ ፣ ለዚህ የግፍ አገዛዝ ፈር ቀዳጆች ፣ በገንዘብ ፣ በቁሳቁስ እንዲሁም የሕዝብ መጨፍጨፊያ መስሪያ ብልፅግና እንዲታጠቅ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ሲታትሩና ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አሁን ቆዳቸን እንደ እስስት ቀይረው “ የአደዋ ያለህ” ሲሉ ለሰማ ዘይገርም የሚያሰኝ ነው።
ሰሞኑን በመላው ኢትዮጵያ ታላቅ የለውጥ እንቅስቃሴ እየታየ ሲሆን ይህ የሚጠበቅ የእምቢ ባይነት ና “በቃ” የሚል የሕዝብ ጥያቄና እንቅስቃሴ ያስደናገጠው የብልፅግና ፓርቲ የአድዋን የድል ክብረ ባህልን በብልጣ ብልጥነት ዱለታ ፣ የክፋት ሽረባ በበዛበት አካሄድ የለውጥ ፈላጊነትን የሰደድ እሳት እቶን ፣ የእምቢ ባይነት መንፈስ ሊያደናቅፈውና ሊያዳፍነው ለስግብግብ ሃገርና ሕዝብ ሻጮችና ለተካፋዮቹ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እያፈሰሰ ፣ ቅጥረኞቹን እያሰማራ የተለያየ አጀንዳ እየፈጠረ ሃገርና ሕዝብን እያተራመሰ ይገኛል።
ስለዚህ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ሰዓት ምንም ከጊዜ ጊዜ ግፉ ፣ ስቃዮ ፣መረሸኑ እየከፋ ፣ የመንግስት መሰሬነት እና ተንኮሉ እየናረና እየረቀቀ ቢሄድም “ የተነቃነቅ ጥርስ መነቀሉ አይቀርምና” ትግላችሁን ያለማወላወል ቀጥሉ እንላለን።
የማይጠረቃውን ከርሳችሁን ለመሙላት ስትሉ ከገዳይ መንግስት ጋር እየሸረባችሁ፣ እያሻጠራችሁ የሕዝብን ትግልና ትኩሳት ለማደናቀፍ ፣ ለማዳፈና ዋጋ ለማሳጣት የምትንቀሳቀሱ አስመሳይ ፣ በየጊዜው ቆዳችሁን እንደ እስስት እየቀያየራችሁ አጀንዳ በማስቀየር ስራ የተደመጣችሁ ፣ ከአረመኔ የብልፅግና መንግስት ተብየ ጋር የምታነፈንፉና የበልፅግና መንግስት ዕድሜ እንዲራዘም አፅንታችሁ የምትለፉ ግለሰቦችና ቡድኖች አደብ ግዙ እንላለን ። ቢቻል ይቅርታ ጠይቃችሁ ከሕዝብ ትግል ጋር ትቀላቀሉ ፣ ንስሃ ግቡ ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ባይ ነውና አስቡበት እንላለን።
ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል!!
ተዘራ አሰጉ
ከምድረ እንግሊዝ።