በዚች አጭር ጽሁፌ ፤ የቀደምት የግሪክ ታሪኮች ( Classical mytology) ስለ ሔርኩል (Hercule) በተጠቀሰች አጭርና ውስጠ ወይራ በሆነች ጥቅስ መንደርደር መረጥኩ ::
« On ne se baigne jamais deux fois dans le même fleuve »
« በአንድ ወንዝ አንድ ጊዜ እንጂ፤ ሁለት ጊዜ አንጠመቅም » ይላል
ይህን ጥቅስ እንድዋስ ያስገደደኝ፤ በኢትዮጵያ የዘንድሮውን የ127ኛ የአድዋ ድል በዓል አከባበር፤ በተመለከተ፤ የሚደረገውን የታሪክ ሸፍጥ፤ « ተረኞች ነን » ባዮቹን፤ ህዝብ አደብ ግዙ እንዲላቸው ለማሳሰብ ነው ::
ታሪክ፤ በአድራጊውና በተደራጊው መሃል፤ በአንድ ወቅት፤ በተወሰነ ቦታና : በተወሰነ ጊዜ፤ በበጎ ወይም በጎጂ መልኩ፤ በአሸናፊና በተሸናፊ መሃል የሚደረግ ግብ ግብ ሲሆን፤ በመጨረሻም በመኖር ወይም ባለመኖር መሃል ይቋጫል::
የአድዋ ድል፤ በእምዬ ምኒልክና እተጌ ጣይቱ አዝማችነት፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ጀግንነት፤ በወራሪው የጣሊያን ፋሽስት ላይ፤ የተገኘ የአብሮነታችን ድል ከመሆኑም በላይ፤ የመላው አፍሪካ የጥቁር ህዝቦች ድል እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ::
የዘመኑ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች፤ የአድዋን ድል ከኢትዮጵያዊነት ማማው ለማውረድ፤ ከመሬት ስበት በከፋ መልኩ ቁልቁል ወደታች በመጎተት፤
ያለ ድሉ ባለቤቶች፤ እምዬ ምንሊክ፤ እተጌ ጣይቱና ጀግኖቻችን፤
ያለ ቦታው፤ የአድዋ ድል አደባባይ ፊት ለፊት፤
ያለ አብሮ ዘማች ታቦቱ፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን
ያለ ሰንደቅ ዓላማችን፤ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለሙ፤ እንዲከበር ወስነዋል ::
አይምሯቸው፤ በዘርና በጎሣ ከታጠረ ግለሰቦች፤ ማህበረሰ’ባዊም ሆነ አገራዊ ዕሳቤ ስለማይመነጭ፤ አብሮነትን በሚያቀጭጭ፤ ክብርን በሚያጎድፍ፤ ታሪክን በሚከልስ ሁኔታ፤ እንዲከበር የወሰኑትን አጠፊዎች፤ ህዝብ በአንድነት እንዲጠየፋቸው አደራ እላለሁ ::
እግረ መንገዴንም፤ በእስር ለሚጉላሉት :
– ጋዜጠኛና የታሪክ ምሁር፤ ጋሼ ታዲዎስ ታንቱ፤
– በአዲስ አበባ አካባቢና በአማራ ክልል፣ ለሚፈናቀሉ ወገኖቻችን፤
– የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታይ ለሆኑት ወገኖቻችን፤
– ለአርበኛ ዘመነ ካሴና፤ ለመላው የፋኖ አባላት ፍትህን እጠይቃለሁ ::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!
ነፃነት፤ እኩልነትና ወንድማማችነት ይለምልም !!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !!
የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም (28/02/2023) እኤአ