የዘንድሮ ደግሞ ይለያል። ያፈጠጠ፥ ያገጠጠ፥ በቁማችሁ እናሞኛችሁ ዓይነት ተራ ብልጠት የተሞላበት፡ እብደትና እብሪት የተቀላቀሉበት አካሄድ ነው። ጄነራል አበባው ታደሰ ‘አጼ ሚኒሊክና እቴጌ ጣይቱን የማይፈልግ የህብረተሰብ ክፍል አለ’ ብለው ሲናገሩ ጆሮዬን ማመን ነው ያቃተኝ። የማይፈልግ የፖለቲኞችና የልሂቃን ስብስብ መኖሩ ጠፍቶኝ አይደለም። ከእሳቸውና ከቆሙለት ተቋም አንጻር ተገቢ አነጋገር መስሎ ስላልታየኝ ነው
በኦሮሚያ ክልል አስተባባሪነት በተዘጋጀውና ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በተገኙበት በተካሄደ የአድዋ በዓል ምክክር ላይ የመከላከያ አባላት የሆኑ ባለማዕረግ መኮንኖች የሚሰጡት አስተያየት አረ!? በህግ አምላክ!’ የሚያሰኝ ነው።
ታዋቂው ጸሀፊ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ በቲያትር ቤቶች ስለአድዋ አከባበር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ያካፈለን መረጃ ደግሞ በድንጋጤ ቅንድብን ከፍ የሚያደርግ ነው። ቴዎድሮስ እንደሚነግረን በቲያትር ቤቶቹ ለአድዋ በሚዘጋጀው ተውኔት ላይ አጼ ሚኒሊክና እቴጌ ጣይቱ እንዳይኖሩ ከበላይ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ይህ ሁሉ መዓት ምንድን ነው? የምን ጥድፊያ ነው? ይህቺ ሀገር ላያችሁ ላይ እንዳትናድ እሰጋለሁ
እውነት ለመናገር የዚህ አገዛዝ መልክ ዘንድሮ ግልጥልጥ ብሎ ወጥቷል። አንድ የኦሮሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ከብልጽግና መንግስት ጋር ተስማምተው ለመስራት ሀገር ቤት እንደገቡ የተናገሯት አሁን እየተፈጸመች ናት ‘We need to deconstruct Ethiopia to reconstruct a new Ethiopia’ በግርድፉ ሲተረጎም አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት አሁን ያለችዋን ማፍረስ ይገባል ነው። የቀድሞ ሚዲያ ኢሳት እያለሁ የኦሮሚያ ብልጽግና ከፍተኛ አመራር የሆኑትና የፓርቲው የፍልስፍና መሀንዲስ ከሚባሉት ውስጥ የሚጠቀሱ ሰው ያሉኝን እዚህ ማስታወስ ይገባል። ‘የእናንተ ኢትዮጵያ እኛ(ብልጽግና) ከምንገነባት ኢትዮጵያ የሰማይና የምድርን ያህል ትራራቃለች’ ነበር ያሉኝ
የእኛ ኢትዮጵያ የቷ ናት? የእኔ ኢትዮጵያ ማን ናት? ብልጽግና ሊያዋልዳት የሚያምጣት ኢትዮጵያስ ምን ዓይነት ናት? ሌላም ልጥቀስ። ከዚሁ ከኦሮሞ ፖለቲከኞች አንዳቸው ‘ላለፉት 3ሺህ ዓመታት ስልጣን በሰሜኖች እጅ ነበር። አሁን ወደ ደቡብ መጥቷል’ ሲሉ ሰምቼአለሁ። እንግዲህ መጪውን 3ሺህ ዓመት ታግሳችሁ ጠብቁ ማለታቸው ነው
ዘንድሮ የሚታየው አይን ያወጣ የታሪክ ግድፈት የዚሁ ‘deconstruct’ ኢትዮጵያ ሂደት አካል መሆኑ ነው። እዚህ አሜሪካ ከአገዛዙ ጋር ውርውር የሚሉ አንድ ምሁር አግኝቼአቸው ”አሁን ኢትዮጵያ የምትባለው ‘ፕሮጀክት’ ላይ መነጋገርና ስምምነት ላይ መድረስ አለብን” ሲሉኝ የእኔ አባት ”ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አይደለችም። የደም ዋጋ የተከፈለባት ናት” የሚል ወኔ የተሞላባት ምላሽ ሰጥቼአቸው በቶሎ ተለየኋቸው
እናም የኦሮሞ ፖለቲከኞችና ምሁራን በስልጣን ላይ ካለው አገዛዝ ውጭ እስከተበተነው ድረስ ተናበው በአንድ ነገር ላይ ተስማምተው እየሰሩ ለመሆናቸው ብዙ አስረጂ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ያለችውን ኢትዮጵያ አፍርሶ፡ እነሱን የምትመስል ‘ኢትዮጵያ’ ን ለመገንባት የሚመስል ጥድፊያ ላይ ናቸው። ኢትዮጵያን በነጠላ ትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያስገባኋት ስያሜዋ ላይ በራሱ ድርድር እናደርጋለን የሚሉ የኦሮሞ ልሂቃን ስለገጠሙኝም ነው
እንግዲሁ ብልጽግና ይህን አደጋ ከፊታችን ደቅኗል። የኦሮሞ ብልጽግና ታንኩንና ባንኩን ተቆጣጥሬአለሁ ዓይነት መታበይ ውስጥ ዘው ብሎ ገብቶ ሀገር የሚያፈርሱ ትርክቶችን ወደ አደባባይ አውጥቷል። እንደጥድፊያቸው ሳይዘጋጁ ኢትዮጵያ ላያቸው ላይ እንዳትናድ እሰጋለሁ
አጼ ሚኒሊክና እቴጌ ጣይቱ ላይ የተጀመረው ዘመቻ የሚነግረን ሌላ ምንም አይደለም። ሸገር በሚል ተመሰረተ የተባለው ከተማ ምን ፈንጂ እንደተቀበረበት ያልተገለጠለት ካለ በጊዜ ሀኪሙ ጋር ይሂድና ጤናውን ይፈትሸው። በየቦታው የሚታየው ማፈናቀል ምን ድግስ ከፊታችን እንደተደገሰልን ያልተገለጠለት ካለም በአቅራቢያው ያለ ጸበል ሄዶ ሁለት ሰባት ይጠመቅ። እናም ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥልቅ የሆነ ችግር ውስጥ ገብታለች”