የማይሠበረው እስክንድር ነጋ!!! – ከቴዎድሮስ ሐይሌ

 

   በእሳት ቀልጦ ወርቅ የሆነ:: በመከራ ውስጥ በጽናት ያለፈ:: በአገዛዝ ጭለማ ውስጥ ለሚኖረው የተስፉ ጭላንጭል ያሳየ ::ሁሉን ትቶ እራሱን ለአላማው የሰጠ :: ሃገሩን ከእራሱም ከቤተሰቡም በላይ ወዶ የተንከራተተ:: ዛቻ ያላስደነገጠው እስራት ትጥቁን ያላስፈታው ስቃይ ከመንገዱ ያላራቀው:: የዘመናችን ትውልድ ተምሳሌት : የጽናት አርዐያ ; የብርታት ቀንዲል! ከድርሻው በላይ ዋጋ የከፈለ ; ስለ እውነት የጠቆረ ስለወገኑ የተሰቃየ የመርሕ ሰው ! የውግዘት ፍላጻ የስድብ ወጀብ የሽሙጥ ሰይፍ የተንበርካኪዎች ማውካካት ያላስበረገገው ቆራጥ ! ተመዝኖ የከበደ ተፈትኖ ያለፈ !!

ሰውዬው ቢጫኑት የማይጎብጥ ብረት ሊሰብሩት የማይቻሉት አለት ነው:: መከራን ገና በእሩቁ ፈርተው ይጠብቁ ዘንድ የተሰጣቸውን መንጋ ጥለው ጻጻሳቱ ሲሰደዱ : ካህናቱ ለገዥዎች ሲያጎበድዱ ሼኮች ምዕመናቸውን ጥለው ሲንበረከኩ ;ምሁራን በአድርባይነት ሲሰለፉ ; ጋዜጠኛው ቴክኖክራቱ ፖለቲከኛው በየፌርማታው ሲንጠባጠብ ብቻውን ለሦስት አስዕርተ እመታት ከመስመሩ ሳይወጣ አንባገነኖችን የታገለ ብርቱ:: ጏደኞቹ በገዥዎች ሙገሳ : በስልጣን ቅልውጥ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ የካዱት :: ወዳጆቹ በባዶ ፕሮፓጋንዳ የተለዩት::አድናቂዎቹ በውዥንብር የተውት :: ሕወሃትን በብዕር ታግሎ አመድ ያደረገ:: የኦህዴድ ኦነግን የክፉት ድሪቶ የገለጠ :: የመሪውን መቀላመድ ሃሳዊ ተስፉ ያመከነ:: አስመሳዩን ለትዝብት አድርባዩን ለውርድት አጨብጫቢውን ለመናቅ ያበቃ የሃቀኝነት የማዕዘን እራስ ሆኖ በትውልድና በታሪክ ፊት የተገኘ::

ኢትዮጵያ ከአመድ አንስታ ያከበረቻቸው ; ሕዝቧ ሳይማር አስተምሮ; እየራበው አጥግቦ ;ለወግ ማዕረግ ያበቃቸው ምሁራን ; ጥቂቶች የጠቡትን ጡቷን ሲነክሱ ; የቀሩትም ሲያሴሩ ; በርካቶችም ለመጣው በማሽርገድ ሲቆሙ ; የተረፉትም ትተዋት ሲፈረጡ በጣት የሚቆጠሩት ብቻ አብረዋት ሁሉን ተጋፍጠዋል:: ከነዚህ ጥቂቶች አንዱናዋናው እስክንድር ነጋ ነው::

መከራው ሳይከብደው ስቃዩ ሳያመው ከቤተሰቡ መነጠሉ ሳያሳቅቀው ቀርቶ አይደለም ሁሉን የቻለው:: በሃይማኖቱ ካለው ጽናት ለሃገሩ ካለው ፍቅርና ለመብት ልዕልና ለዲሞክራሲ መረጋገጥ ካለው ፍጽም እምነት በመነሳት ነው::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የነዳንኤል ክብረትና የኔ - ሁለት አቢይ አህመዶች! - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ዛሬም እስክንድር ለዳግም እስር ተዳርጏል:: የሰው በላውን ኦዴፓ የግድያ ሴራ ሸሽቶ ከሄደበት አማራ ክልል ተይዞ ለአራጆች መሰጠቱ ግን እጅግ ልብ ይሰብራል:: አማራን እንደ ሕዝብ ያዋረደ አዴፓ የተባለው ቡድን ሊፈወስ የማይችል ቆሻሻ ድርጅት መሆኑ ፍጹም ያሳየ አጋጣሚ ሆኗል:: የአማራ ልዩ ሃይል ትላንት ለክብር ያበቃውን መሪውን ጀነራል ተፈራና ጏዶቺን አሰረ :: ዛሬ ደግሞ የሕዝብን ልጅ የአማራ ሕዝብን ስቃይ በአለም አደባባይ ያስተጋባውን እስክንድር ነጋን አስሮና አሳልፎ ለአራጆች አቀረበ:: እንዴት አንድ ጀግና አይሆንም የሚል ወንድ ከመሃላችሁ ጠፉ :: እስክንድር ምንም ይሁን ምን በወርቅ የተጻፈ ታሪክ ያለው ታላቅ ሰው ነው:: ይብላኝ ሱሪህን ላወለከው የአማራ ክልል አመራር ይብላኝ ለክልሉ ታጣቂ እራስህን አስንቀህ ክብርህን አዋርደሃል:: የኦሮሙማው ተረኛ መንጋ እስክንድርን በአደባባይ ለማጣጣል ቢሞክርም ከልቡ ግን ያከብረዋል:: ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ስሙ ሲጠራ የሚርዱና ሱሪያቸው የሚረጥበው ሹማምንት ቀላል አይደለም::

እስክንድር ዛሬም ከብሯል ::ለሚያምንበት አላማ ዛሬም ያው ነው:: ቀና ኮስተር እንዳለ ነው የታይው :: አስር ሞት ቢመጣም ሽብርና ፍርሃት በእርሱ ዘንድ ቦታ የላቸውም:: ዛሬም የሽንፈት ስሜት አንገትን መድፉትን አላሳየም:: እስክንድር የማይሰበር ነው:: አላማው ሕዝባዊ መንፈሱ ንጹህ ግቡም እኩልነት ነው::

ይብላኝ ለኛ ቆመን ለቀረንው:: ይብላኝ የማንም አዛባ መጫወቻ ለሆነው ከተሜ:: ይብላኝ ለዚህ አልጫት ውልድ ተስፋውን ለተቀማ እድሉ ለጨነገፈው:: እንደ ሕዝብ ተዋርደናል እንደ ሃገር ደቀናል:: ዘመን በማይዋጁ የጥንታዊ ጋርዮሽ ጉግማንጉ አራዊቶች እጅ ላይ ወድቀናል:: እስክንድርና የእሱ ብጤ ታጋዬች በስቃያቸው ውስጥ ደስታ በመከራቸው ውስጥ የአይምሮ ሰላምና የሞራል ከፍታ ማንም አይነካባቸውም ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሴት የሁላችንም እናት በመሆኗ ሠላምን እና ዳቦን አጥብቃ ትሻለች - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 

ሕዝባችንስ በዚህ ወቅት ምንድን ነው የሚጠብቀው? አዲስ አበቤስ የት ነህ ያለህው?:: አስቀድሞ አደጋውን የጠቆመህ መብትህን ለማስከበር የደከመልህ እስክንድር አላማው ዛሬም አልገባህም? በየልኳንዳና በየመሸታው ከማውደልደል መቼ ነው ለመብትህ የምትቆመው:: በኑሮህ ; በሃይማኖትህ ; በማንነትህ ;በባህልህ እያሸማቀቁህ እየረገጡና እየተፉብህ መኖር ተስማምቶሃል ?  ለገጣፎ ሱዳን ድንበር ; ስሉልታ የኬንያ ግዛት ሳይሆን ለአንተው አዲስ አበቤ አዋሳኝ ነው:: የትውልድ ማንነታቸው እየተለየ በሕገወጥ ስም ቤታቸው በላያቸው በተኙበት የሚፈርሰው በጅብ የተበሉትና በተረኞች የተገደሉት ያንተው ወገኖች ናቸው:: የመጣው አደጋ ቤት እስኪመጣ ከሆነ ተመቻችተ ጠብቀው:: ሚስትህ ቀምቶ ሃብትህን ዘርፎ አንገትህን የሚቀነጥህስ ጭራቅ መሆኑ ካልገባህ ይመችህ::

በጋራ ቆመን በድፍረትና በጽናት ለመታገል እስካልቆረጥን ድረስ መከራችን እረጅም ተስፉችንም ጭለማ  ነው:: ፍርሃትን ካልፈራን ሞትን ካልደፈርን መጨረሻችን አያምርም:: ጎበዝ የሞትም እኮ አይነት አለው:: አካልህ አንድ ባንድ እየተቆረጠ ብልትህ ተሰልቦ ወይ በቁምህ በር ተዘግቶብህ ከነልጆችህ በእሳት መቃጠልም የሞት ሞት ሞት ይባላል:: በወለጋ ሲደረግ የቆየው ይሄው ነው::

በጥላቻ ቅስቀሳ ; በተዛባ ትርክት ; በቁስ ሰቀቀን በስነልቦና ስብራት ; በበቀል ፈረስ የሚጋልብ ጠላት እየከበበህ ነው:: ብትተወው የማይተውህ :: ብትሸሸው የሚከተልህ::ካለጠፉህ አይቆምም ::ካላወደመ አይረካም:: ካልገደለ አይደሰትም:: መርህ ; አላማ ; ሞራል ; ሰብዓዊነት ሕግና ; ስርዐት የማይዳኙት መደዴ ሊሰማራብህ አቆብቁቧል::ጆሮ ያለህ ስማ ሕሊና ያለህ አስተውል:: ለሌላው ሳይሆን ለእራስህ ሕልውናና መብት ዘብ ካልቆምክ የሚያድንህ የለም::

በቅዱስ መጽሃፉ ለእራሳችሁ አልቅሱ እንዲል: ሁልህም ለእራስህ አልቅስ:: ትላንት አደጋውን የጠቆሙህ ዛሬ ሲያዙ ከማዘን ለእራስ አልቅስ ለሕይወትህ ዋጋ ከሰጠህ የሚጠበቅብህን አድርግ :: በከንቱ ከንፈር ከመምጠጥና በየሶሾል ሚድያው ከማናፉት መሬት የረገጠ ተግባር ላይ እናተኩር የተደቀነብንን አደጋ ማለፍ የምንችለው በሚቻለውና በማንኛውም መንገድ ለትግል ስንነሳ ብቻ ነው::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የእህቴ መከራ የኔም ነው - ከሞሲት የሻነህ

 

ዘላለማዊ ክብርና ምስጋና ለእግዚአብሔር!!!

ምስጋና ለቆራጡ ጀግና እስክንድር ነጋ!!!

ድል ለዲሞክራሲ!!!

2 Comments

  1. ቴዎድሮስ ሐይሌ እናመሰግናለን ልብ ይሰብራል። ሀገሩ ሌላ ቢሆን እስክንድር ለወምበር እንጅ ለእስር አይዳረግም። ህዝቡም ወጣቱም ምን እንደተዞረበት እንጃ ክብሩን ትቶ ወሬው ሁሉ ቁርጥ፣ሽሻ፣ጫት ነው። በተለይ የአማራ ክልል ምን እንደሆነ መገመት ይከብዳል ብአዴኖች እነ አገኘሁ ተሻገር ያለ አጃቢ ሲንቀሳቀሱ ስታይ ህዝቡ ላይ አፍዝ አደንግዝ የተሰራበት ይመስላል ።ህዝቡ ቢያሳዝናቸው በስተርጅና አቶ ታዲዮስ ታንቱ ታሰሩለት፣ ዘመነ ካሴ ብሩህ አእምሮ ያለው ዜጋና 13000 ፋኖ አሳስሮ ህዝቡ ቁጭ ብሏል። አማራ በክልሉና ከክልሉ ውጭ ያልሆነው የለም እንደ በግ አካሉ አንድ በአንድ ተቆራርጦ ማለቁ አይቀሬ ነው። በተረፈ ሳይበር ላይና አባቶቹ የሰሩትን ገድል እያመነዠከ ይኑር።

  2. ምን ዋጋ አለው ሰውን በፍርሃት ሱሪው ረጠበ ተጨነቀ፣ ተጨነቅን ልበለው እንጂ ምንም እንኳን ወደ 80ው ብጠጋም እኔም አለሁበትና ፈራን ልበል፣እስክንድርንማ ማንስ እስተካክላለሁ ብሎ በሱ ስም ይነሳል? ኧረ እሱስ አገሩን ከልቡ የሚወድ ጀግና ነው በእርግጥም በሕይወቴ እንደ እስክንድር መንፈሰ ጠንካራ ፖለቲከኛ አይቼ አላውቅም፣ ምን ዋጋ አለው ለነሱው እየተዋደቀ በነሱው ሲሰቃይ ደግሞ በጣም ያምማል፣ ኧረ ለመሆኑ ይኼ ብአዴን የሚባል የእንግዴ ልጅ እንዴት አይነቀልም የነኛ ርዝራዥ ቅሪት እንዴት ጸጸት አይገባውም፣ እስክንድርን አሳልፍ ለኦሮሞ አራጆች አሳልፎ ሰጠ? ይሁና! ይገርማል! ይሁን! ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ ይባል የለ? ምነው አማራው “ሱሪውን አውልቆ የእናቱን አሮጌ ቀሚስ በለበሰ! አዬ ነድዶ! ቀንኮ ያልፋል፣ እነእስክንድር ነጋ በተዋደቁበት በተሰቃየበት ነገ ከየጉስጉሻው ወጥተው ለስልጣን አይናቸውን በጨው አጥበው ብቅ ማለታቸውማ አይቀርም፣ አዬ! ኢትዮጵያ አገሬ የጉድ አገር አደረጉሽ ልጆችሽኮ አዋረዱሽ! ለጥሩ ገንዘብ ለገበያ አቀረቡሽ፣ አላፈሩም ሊሼጡሽ እያስማሙሽ ነው፣ እግዚአብሔር በቃሉ ይጠብቀሽ እንጂ በወለድሻቸውስ አልሆነልሽም!!!
    ቀን ያልፋል ግን እንደ እስክንድር ነጋ ያለፋል!!!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share