ጉዳዩ፤ ኢትዮጵያ እንደ አገር የመቀጠል ወይንም ያለመቀጠል ነው!

አንዱ ዓለም ተፈራ
ሐሙስ፣ የካቲት ፱ ቀን ፪ ፻  ዓ. ም.

 

በቅድሚያ በአገራችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተፈጠረው የውስጥ ችግር ተፈትቶ ዕርቅ መደረጉና ውጥረቱ መርገቡ ደስ የሚያሰኝ ነው። ይኼ የጉዳዩ መጨረሻ ነው ወይ? የሚለውን ውለን አድረን የምናየው ይሆናል። ለጊዜው ግን ቢያንስ በቤተክርስትያኗ ውስጥ ሰላም ሰፍኗል። ይህ በፖለቲካው ዙሪያ ባሉት መካከል ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል? ሌላው ጥያቄ ነው። ይህ በዚህ እንዳለ፤ የአገራችንና የቤተክርስትያኗ ትልቁ ችግር ይህ የቤተክርስትያኗ የውስጥ አሰራር ብቻ እንዳልነበረ መረዳት አለብን። አሁን በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ኃላፊነቱን ከተረከበ በኋላ፤ አንድ ጊዜ አንድ ጉዳይ፣ ሌላ ጊዜ ሌላ ጉዳይ እየተነሳ፤ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸው አልፏል። ለምን? ነገ የሚከተለውስ ጉዳይ ምን ይሆን? በዚህ ጽሑፍ ያሰፈርኩት፤ መንግሥት የሠራዉን ወይንም ያልሠራውን መመርመርና ማውገዝ ሳይሆን፤ ጠቅለል ባለ መልኩ ለሌሎቻችን መልዕክት ማስተላለፍ ነው።

እስካሁን የተከሰቱት ጉዳዮች ምንድኖች ናቸው? ለምን ተነሱ? እኔ የምጽፋቸውን ለሚከታተሉ መልዕክቴን መገመት አይከብዳቸውም። ከኔ ክልል ውጣ! ወደ አዲስ አበባ አትገባም! የኔ ክልል ደንበር ትክክል አልተሰመረም! እኛም የራሳችን ክልል ይኑረን! ኡእራሳችን የሃይማኖት ክፍል ይኑረን! በቋንቋችን ይሄ ይደረግልን! ያ ይደረግልን! የኛ የበላይነት ጥግ የለውም! የሥራ ፈላጊው ቁጥር እየበዛ ሥራ ግን አልተፈጠረም! የተነሳንበትን ጉዳይ ሕገ-መንግሥቱ ይፈቅድልናል! የመሳሰሉት ናቸው። እኒህን ሁሉን የሚያያይዛቸው ምንድን ነው? ይህ ነው መታየት ያለበት። እንዲያው እያንዳንዱን እየለዩ ቢያባጥሉት፤ መልሶ መልሶ! ይሆናል። ይህ ሁሉ ባንድ ላይ ሲሰበሰብ፤ የአገርን እንደ አገር መቀጠል ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ጉዳይ ነው። እናም የአገርን ጉዳይ መመልከቱ ዋና የአሁን ጥያቄ ነው። አንዳንዶች በአንዱ ጉዳይ ተጠምጥመው መፍትሔ ለማግኘት ይሯሯጣሉ። ለማንኛውም ጉዳይ መፍትሔ መሻቱና ማግኘቱ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን፤ ከላይ የደፈረሰን ፈሳሽ ከታች እናጥራው ቢሉ፤ ለድካም ከመዳረግ ሌላ ትርፉ ባዶ ነው። እናም ከመንግሥት ሥልጣን ውጪ ያለን፣ በአገራችን ያለውን የፖለቲካ ሀቅ የተረዳን፣ አደጋውን ተረድተን የመፍትሔው አካል መሆን የምንፈልግ፣ ኢትዮጵያ ነገ ቀጥላ ለወደፊቶቻን እንድናተርፋት ከፈለግን፤ መምከር አለብን። በኢትዮጵያ ያለው አንገብጋቢ ጥያቄ፤ የአንድ ጎሳ፣ የአንድ ሃይማኖት፣ የአንድ አካባቢ፣ የአንድ ተበዳይ፣ የአዲስ አበባ፣ የወልቃይት፣ የራያ፣ የጉራጌ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የጉጂ፣ የሲዳማ፣ የተነጣጠለ ጉዳይ አይደለም። የአገር እንደ አገር መቀጠል ወይንም አለመቀጠል ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለምን ከምንወዳት አገራችን እንሰደዳለን? ክፍል 1 (በይበልጣል ጋሹ)

ይሄ ግራ የሚያጋባ ነው። ኢትዮጵያ አለች! ለወደፊቱም ትኖራለች! በሚል ግትር የተፈጥሮን ሕግ በውል የማይመለከት ጭፍን እምነት የተሰለፉ አሉ። ይሄን በቀላሉ የታሪክ መዝገብን በማገላበጥ መረዳት ይቻላል። ከኢትዮያ የገዘፉ ታላላቅ አገሮችና መንግሥታት ፈርሰው ዛሬ የሉም። ገናናዎቹ የግሪክ፣ የሮማ፣ የሞንጎሊያ፣ ፀሐይ አይጠልቅበትም የተባለው የእንግሊዞች አገር(ከደሴቷ በስተቀር)ና መንግሥታት፤ በታሪክ መዝገብ ብቻ ነው ያሉት። ትናንት ዩጎዝላቪያ ነበረች። ዛሬ ስሟን ከመጽሐፍ በማገላበጥ እንጅ፤ በዓለም ካርታ ላይ አያገኙትም። ኢትዮጵያ የተለየች አገር አይደለችም! እኛ ካልጠበቅናት ሌላ ጠበቃ የላትም። በሃይማኖት ለሚተማመኑት፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት በሙሉ የፈጣሪ አገራት ናቸው። ያዳላል ካላልን በስተቀር ሁሉም አገራት አንድ ናቸው። ኢትዮጵያዊያንንም ከሌሎች አብልጦ ወይንም አሳንሶ አይመለከትም። እናም ኢትዮጵያ ከሌሎች አገር የተለየ ምንም ነገር የላትም። ያሏት እኛ ብቻ ነን። እኔ አንድ እግሬን ወደ መቃብር በመስደድ ላይ ያለሁ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኢትዮጵያን ግን በታትኜ ለማለፍ ዝግጁ አይደለሁም። ሌሎች ሲያፈርሷት ደግሞ፤ እነሱ ናቸው ብዬ እጄን በሌሎች ላይ ልጠቁም አልፈልግም። የራሴ ኃላፊነት አለብኝ። የኢትዮጵያዊነትና የትውልድ ኃላፊነት አለብኝ። ይሄን ከመወጣት አኳያ፤ ኃላፊነቱ ከሚሰማቸው ጋር በኢትዮጵያ እንድ አገር መቀጠል ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ።

ከላይ የዘረዘርኳቸውና ሁላችን የምናውቃቸው ጉዳዮች መሠረታቸው፤ ወንበሩን ለሌሎች እንዲለቅ ተገዶ የተባረረው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጥሎት የሄደው ሕገ-መንግሥትና፤ በቦታው አስቀምጦ እንዲወርስ ያደረገው መንግሥታዊ መዋቅር ነው። ይህ አገራችንን ወደ መፈራረስ እየወሰዳት ነው። በምን መንገድ ይሄ እንዳይሆን መከላከል ይቻላል? ምናልባት በሥልጣን ላይ ያሉት፤ እኛ በትክክል እየመራናት ነው! ብለው ሊምኑ ይችላሉ። አልፈርድባቸውም፤ በሚያውቁት የሚያውቁትን እያደረጉ ነው። ጥያቄው፤ ከነሱ ውጪ ያለነው፤ ያለውን ተጨባጭ ሀቅ ተረድተን፤ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ወይ? ነው። የፖለቲካ ፓርቲ፣ የዝመናና ሥልጠና ጉዳይ፣ የልማትና የማደግ ጉዳይ፤ ቦታ ቦታ አለው። አሁን አገር የማዳን ጉዳይ ሁሉን ጨፍልቆ ስለመጣ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ መምከሩ ግድ ነው እላለሁ። በተለያዩ ድርጅቶች የተሰባሰባችሁ ሁሉ፤ ይሄ ዋና ጉዳይ ነው ብላችሁ ካመናችሁ፤ ይሄ ጥሪ ከየትም ይምጣ ከየት፤ የራሳችሁ ጥሪ ነው። እናም እናንተም ጥሩት ሌላው፤ መሰባሰቡ አጣዳፊ ነው። ይህ ለነባር ታጋዮች ወይንም ለነገ ተረካቢዎች የተደረገ ጥሪ አይደለም። ለማንኛውም ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያን ለማዳን ለሚሻ ሁሉ ነው። ይህን ማድረግ፤ የገንዘብም ሆነ የጉልበት አቅም አይጠይቅምና እኔ እገፋበታለሁ። አለን የምትሉ ጥሩኝ፤ እገኛለሁ። ነገ ለመቆርቆር ጊዜ አይኖረንም። ዛሬ ኢትዮጵያ በንጥልጥልም ብትሆን ባለችበት ደረጃ እንድረስላት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወንጌልና ወንጀል፤ ቁራንና ቅጥፈት፤ ምን አገናኛቸው ?!  ( አሥራደው ከካናዳ )

eske.meche@yahoo.com

 

3 Comments

  1. መሬት ላይ ያለውን እውነት አይቶ ሃገሪቱ ቀጣይነት አላት ወይስ እንደተደናበሰችና ልጆቿን እየበላችና እያስበላች ትፍገመገማለች ለሚለው ጥያቄ መልስ ያገኛል፡፡ በመጀመሪያ ወያኔ እያለ ኢትዮጵያ ሰላም አይኖራትም፡፡ በቅርቡ የትግራይ ፓርቲ ለተባለ ድርጅት እንዲሰበሰቡ ፈቃድ የሰጠው ወያኔ መልሶ ተሰብሳቢዎችን በጠበንጃ አንጋቾች ሲያስበትን አዳራሽ አከራዪን ባለ ሆቴልም አስፈራርቷል፡፡ አንባቢ ለምን መጀመሪያ ፈቀድ በህዋላ ከለከሉ ይል ይሆናል፡፡ ወያኔ ሰው ለመለየት የሚጠቀምበት የቆዬ ስልቱ ነው፡፡ አሳይቶ መቀማት፡፡ አሁን ደግሞ አንዴ ታደሰ ወረደ ሌላ ጊዜ ደግሞ ልበ ቢሱ የትግራይ ፕሬዚዳንት የሚናገሩትን ላዳመጠ ገና ጦርነት ላይ ናቸው፡፡ ወሬአቸው ሁሉ አማራና ኤርትራ ከያዙት መሬት ካልወጡ ገለ መሌ ይላሉ፡፡ ስለሆነም ጠ/ሚ አብይን በተደጋጋሚ በህይወቱ ላይ ገበጣ እየተጫወቱበት እንደሆነ በይፋ ያሳያል፡፡ እርዳታው፤ የባንኩ መከፈት፤ ከአማራና ከአፋር የዘረፉትን ፍትህ ፈላጊ ሳይኖር በላይ በላዪ ከፌዴራል ተብየው መንግስት የሚጫነው ገንዘብና የህክምና እና የቁሳቁስ እቃ የወያኔን ልብ አሳበጠው እንጂ አላስተነፈሰውም፡፡ ስለሆነም እየገደሉ፤ እያጋደሉ፤ በትግራይ ህዝብ ስም እየነገድ የቃልም ሆነ በጦር መሳሪያ የታገዘው ውጊያ ይቀጥላል፡፡ በፊት ሌሎች ሃይሎች እንደገቡበት አሁንም ገብተውበታል፡፡
    በሌላ መልኩ ልክ እንደ ወያኔ ተገንጥዬ ሃገር እሆናለሁ የሚለው የኦሮሞው የፓለቲካ ሽር ደግሞ ማቆሚያ ወደሌለው ግጭትና ግድያ እንዳስገባን የየቀኑ ወሬ ይናገራል፡፡ አማራው እርስ በእርሱ የማይተማመን በየደረሰበት ወንዝ ዳግም የሚማማል በመሆኑ ራሱን አስታጥቆ ለመመከት ያለው አቅም ያለቅጥ በውስጥና በውጭ ሴራ ተመናምኗል፡፡ ለዚህም ነው አሁን በፋኖ ላይ ፍትህ ያጣ ዘመቻ የተከፈተው፡፡ ወያኔና የኦሮሞ ፓለቲከኞች የሚጠሉት ኢትዮጵያዊነትን በመሆኑ ከየትኛውም ክልል ይሁን ጎጥ በዚህ ሃሳብ የጠነከረ እይታ ያላቸውን ሰዎች እየመረጡ ያጠፋሉ፤ ያፈናቅላሉ፤ ይገድላሉ፡፡ ግባቸው ሃገር ማተራመስ ነውና፡፡
    እንግዲህ ባጭሩ የምድሪቱ ሁኔታ እንዲህ በዚህም በዚያም የሚጎተትና ቋጠሮው እየጠበቀ ውሉ እየጠፋ የሚሄድ ከሆነ የኣለም ፓለቲካን ስናይ የሚነግረን ምን ጉዳይ አለ?
    ኤርትራ ሳይታስበ አፍቃሪ ራሺያ መሆኗ አውሮፓንና አሜሪካን አስኮርፏል፡፡ በዚህም የተነሳ እድሜ ለጠ/ሚ አብይ የወያኔ መሪዎች ከአሜሪካው የክፋት ሸር ጋር እንደገና በስልክና በሌላም መንገድ እየተገናኙ የኤርትራን መንግስት ለማዳከም ብሎም ለመገልበጥ ትጥቅና ስንቅ እንደሚያቀብሏቸው የታወቀ ነው፡፡ በእርግጥም የኤርትራው መሪ እንዳሉት “የሰላም ስምምነቱ ህወሃትን ለማዳን በአሜሪካ ግፊት የተደረገ ነው”፡፡ ሌላው አተካራና ማብራሪያ ሁሉ ሰውን ለማደናበር የሚጠቀሙበት ዘይቤ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ለሞተው ልጅ ያለው ድንኳን ጥሎ የሌለው በደሳሳ ጎጆው እንዳያለቅስ የሚከለክል አውሬው ወያኔ ዛሬም ጫንቃው ላይ አልወረደም፡፡ ረጋ ብሎ በሰውነት ሂሳብ ወገንተኝነትን በመተው ጉዳዪን ላሰላው የኢትዮጵያ ጉዳይ ትንፋሽን ይቀማል፡፡ አሁን በኦርቶዶክስ ቤ/ክ ላይ የተከፈተው ዘመቻና ረገበ ተብሎ የተነገረንም ቢሆን ጭራሽ ማቆሚያ የለውም፡፡ ችግሩ መንግስት ብቻ አይደለም፡፡ ህዝቡ ራሱ ቀጣፊ ሆኗል፡፡ ሰውና ሃገሪቱም በንዋይና በዘመናዊ ቁሳቁስ ፍቅር ያለቅጥ መሰረታቸው ስለተናወጠ እኖራለሁ እንጂ እሞታለሁ የሚል የለም፡፡ የምድሪቱን ህግ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪንም የማይፈራ ህዝብ ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ ተገለባብጧል፡፡ የእኛን ጉዳይ በደንብ የሚገልጠው የሚከተለው የጀርመን ተወላጅ አሜሪካዊው ያሰፈረው የእንግሊዘኛ ግጥም ነው፡፡ ልብ ያለው አንቦና አዳምጦ ይረዳ፡፡ ግጥሙን እንሆ (The genius of the Crowd by Charles Bukowski (read by Tom O’bedlam) በቃኝ!

  2. Ato Andualem said “በቅድሚያ በአገራችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተፈጠረው የውስጥ ችግር ተፈትቶ ዕርቅ መደረጉና ውጥረቱ መርገቡ ደስ የሚያሰኝ ነው።”

    This implies Ato Andualem still has faith in Abiy Ahmed he thinks the Devil is a promise keeper. Sir, he could be your grandkid, but he continuously cheats you with candy.

    What is wrong with people like Ato Andualem? Are you guys out of your mind? We are tired of unreal hope and beginning, beginning and beginning?

    Why do not you fight, take power, and change the constitution instead of begging others to do it?

    • Dear Girma,
      If only you read all through!
      I never stated having any faith in him.
      The fact that I acknowledged what I learned the day I wrote the article does not make me having any hope. If only you continued reading and follow my doubts and read what is written, you would have understood my firm believe that this will not end and it didn’t. Just reading the first sentence does not give you the whole idea.
      What I did was acknowledge what is on the floor and analyze it to where that will take us.
      I have put my solution forward? Would you do the same? I don’t just blame and loose hope on the land. I do ask my self what do I do? Blaming and lamenting on the situation does not take us any place forward. You could also write your own article and suggest what must be done.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share