የቁም ኑዛዜ – የጎንቻው (ወቅታዊ ግጥም)

በ PDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
እርም ይሁን ከእንግዲህ ስማችሁን፤ ዘራችሁን፤ ጐጣችሁን ባነሳ፤

የበኩር ልጄን፤አምሳሌን፤አብራኬን በኩርትሜ ላስታቀፋችሁኝ ሬሳ፤

ምን በሆነ ነው ? ምን ባለ? ልጄ ከፊቴ ላይ ሰውነቱ በጥይት የተበሳሳ፤

አማረልጄ በአማራነቱ የተቀጣው በለጋነቱ በሞት አበሳ፤

እንደ አባት፤ እንደ ወንድም፤ እንደ ሰው በምድር የማይረሳ፤

የቁም ኑዛዝዬ ነው ያቀረብልኝ ልጄ በሞት እስትንፋሱ ወቀሳ፤

በሙት ዓይኖቹ የገረፈኝ በዚያች ቅጽበት፤ የጊዜ ቅንጣት አናሳ፤

ግዙፍ ነበር ንግግራችን ቃል በምድር ቃል በሰማይ ለዘመናት የሚወሳ፤

አገር ብዬ፤ ፍቅር ብዬ፤ እኖር ብዬ የገበርኩት ህይዎቱን ለሁላችን ስሳሳ።

ሰላም ብዬ ስዳዳ እንደ በግ መንጋ ስነዳ በቀበሮ እረኛ ተንጋግቼ፤

ቤት ንብረረቴን፤ አንጡራ ሃብቴን አገር ክብሬን ልጄን ሰውቼ፤

ስንገላታ የመከራ ኑሮ ሰንቄ፤ ሺህ ውል እድር የቁም ሞት ሞቼ፤

እነሆ የቁም ኑዛዜ የእግር እሳት ጸጸቴ፤ ፍቅር አቅንቼ ሞት ሸምቼ፤

ዘመነኞች እጥፍ ድርብ ሲያተርፍ እሳደዳለሁ ዓይነቴን አንኳ አጥቼ

ካሁን ወዲያ ንግግሬ ከአንድዬ ነው እባጅ ዘንድ የመከራ ዳርቻዬን አውጥቼ

እርም ብዬ እንድነሳ፤ ሙት ልጅ ያቀፈ እጅ- ጉልበቴን አፍታትቼ ።

ሳር ሰርዶውን አርሜ፤ ለህይዎት መና ዘር ፍሬ በሻትኩባት ምድር፤

የኃይዎቴን እስትንፋስ እምቦቀቅላ ልጄን በስደት መንገድ ዳር ስቀበር፤

የአሳዳጆቸን ማንነት አልሻምና የሚነገግረኝ ምድራዊ ሃይል ምስክር፤

ከዚህ ወዲያማ አላነሳም ስማቸውን ጐጣቸውን ዘራቸውንም አልጨምር፤

ንግግሬ ከአንድዬ ነው፤ አንዱ ከአንዱ ሰው ከራሴ ጋር የልቤ በልብ እንዲያድር፤

ደቦ አልጠራም፤ ግርግር፤ የአገር ኮሚቴ አላዋቅር፤መቀወር እንጂ የአንዷን እጄን ጠጠር።

ጆሮዬ አልስማ አይል ሰማሁ ሌላም ጉድ፤ ተጨነን ስንጓዝ እንደ በድን፤እንደ እቃ፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዕውቀቱ ቡዳው በላን!

እርብቃም ሞታለች ጨቅላዋ ተጣብቃ፤ ከብረት ተላትማ ትንፋሿን አምቃ፤

ቁንጥጫ እማታውቀው በአፈሙዝ ተሳቃ፤ አንደበት አጥጧት ግዞት ተጨናንቃ፤

የእትብቷን መቃብር ጓዳ ቢቷን ለቃ፤ አፈር ፈጭታ ስታድግ በእግሯ አቡክታ ጭቃ፤

ለቁም ነገር ሳትደርስ ለአቅመ አዳም ሳትበቃ፤ ክታቧን ቆረጡት የልጅነት ዶቃ፤

ዓለሟን ሲያጠፉ ባዕዳ ነሽ ስትባል ከወዲያ በመጡ በቅልቦች ፍርጥም አንገት ተጠርንቃ፤

ከምድር ዋለች ሰማይ በዓለም ምጣት ታንቃ፤ወላጅ አያስጥላት አገሯን ሳታገኝ እፉኝ ተሞልቅቃ፤

ትንፋሽ ድምጽ አልባዋ በአጋዚዎች ወድቃ፤ ሞታ አረፈች አሉ ወላጅ ወገን ናፍቃ።

ነፍሰ ጡሯ እታለም የጸነሰችውን የዘጠኝ ወር ጨቅላ የሆዷን በእቅፏ በጀርባዋም አዝላ፤

ወልዳ እንኳ ባትስም ምጧን ትገላገል ስለ ወላድ ብላ ጓዳዋንም ቢሹ በጥግ ተከልላ፤

እስክትወልድ ቢራሩ አልቅሳ ብትለምን ብትማጠናቸው አሳር ተንበርክካ የሦስት ቀን ዘለላ፤

ልብ ያልሰራባቸው አንዳች ደንደሳሞች ሰይፍ ጦር አንግተው መንጋ የሚናዱ ቀነኞች ተኩላ፤

ተሻምተው በጥፊ እንደ አለሌ አህያ ዘለው ረገጧት ከጓዳ ጎትተው እየቀጠቀጡ አናቷን በዱላ፤

በአፋቸው እርግማን ስድብ እሚቀናቸው በንቀት ቋንቋቸው እሚንተባተቡ ‘ክይ’ ‘ ወዲያ’ ‘ክላ’፤

እናማ ከእንግዲህ ቃሌ ከራሴ ነው አንዱ ሰው ለአንድዬ አገር እስኪሰነቅ ዘመቻ በጅምላ፤

አልጠራም ዘር ጐሳ ስምም አላነሳ፤ የሆዴን በሆዴ የልቤን በልቤ አንድ ለአንድ ብቻ የአገር የለሽ መላ።

ያች ሚስኪን እህቴ በጠራራ ጀምበር፤ ምስራቅ ገመገሙን ጋራ ተራራውን የብስ አድማስ አካላ፤

ደመ ነፍሷን ስትጠድፍ የአያት ቅድም አያቷን ዱካ ተከትላ፤ አገርሽ ጎጃም ነው ጐንደሬም ነሽ ተብላ፤

ዳዋ ስትጥስ ዋለች ጽንሷ እንዳይጐዳ ሆዷን በመዳፏ በእቅፏ ከልላ፤

ታዲያ ምን ያደርጋል ብቻዋን ተባራ ወድቃ አረፈች አሉ በሙቀት ሃይል ዝላ፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  መኪና አሳዳጅ ውሾች! - በሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

እንጐቻዬ አራ’ሿም ተገኘ አስከሬኗ፤ ጫካ አባረው ደፍረው እርቃኗን ተጥላ።

አንድዬ! ምነው የመከራ ቋታችን መቀመቅ ጡዞ የራቀው፤

እንዲህ በእየለቱ የምድር የሰማይ መቅሰፍት የባጀው፤

‘የታችኛው መንደር’ አለቁ አሉ ሰዎች ገደል ተጥለው፤ ከድፍን ስልሳ ሰው አንድ ቅርጣን ትተው ፤

በአባይ በበርሃ ቀሩ አፈር ቅመው ፤ እርማቸውን ይብላ ንጉስ አንዳሻው፤

ቀብር የለ ለቅሶ ሬሳ ጥለው፤እርም ነጣቂዎች አውሬና ወያኔ ተቃሙባቸው፤

ጦቢያዊ በጥሊያን ከዚህም የከፋ ግፍ አላገኘው፤

ጥላት ባር ማዳ ነው ብለን ተዘናግተን ሳናስተባቃው፤ ለካስ ከአድባራች ከቀያችን ነው ፤

ከማዳበሪያ ጋር አረም ደብልቀው፤ ፈረንጆች ያቀኑት፤የምድራችንን ከርሰ ማዕድን ያደረቀው፤

ባሰበት ‘ዋድዮ’ አገር በቀል ሳማ፤ ቂጥኝ አራሙቻ ዘር ግንድ እሚበላ ጥቁር ‘አድዋው’፤

እናማ አንድዬ! ሰማይ፤ ምድር፤ አገር ብለን ከንቱ እምንጠራው፤

የታለ ቦታው? ከእንድግዲህ፤ ወዲያማ፤ ዘር፤ ስም ጐጣቸውን ጭራሽ አልጠራው፤

አፌን ደም ደም ሲለኝ፤ ሟች ልጄ በቅፌ ሆዴን ሲቆርጠው፤ ውስጤ ሲገላበጥ እያቆሰለው፤

በሆዴ በአንጀቴ፤ በልቤ ‘አንጬው’፤ የልጄን መቃብር ሃውልት አዝየው፤ እትብቱን የበላ አገር ቢነሳው።

ይኸው የሰው ሩሕያ አንድዬ ካልበጠሳት ከአካላችን ሳትላቀቅ እስካሁን ከሳሳ ከከሳ አካላችን ሳትነጠል፤

በጸሃይ ጠህኝቶ ከደረቀ ዛፍ ቅርንጫፉ ተንጠላጣል ግራና ቀኝ ስትመናተል፤ እንደ ጠነዛች ቅጠል፤

አብራን አለች ወይም አብረናት በድናችንን ተጓጉዘን እንደ እቃ ባዶ ሜዳ ስደተኞች ባዷችንን ተራግፈናል፤

ማነው አሉት ‘ቻግኒ’ ‘ፍኖተ ሰላም’ የቅርብ እሩቅ? ሰው አይቅርበን አይጠይቀን እንዲሁ አገራቹህ ነው ይሉናል፤

ሲመሽ ሲነጋ ብርድ ሙቀት በላያችን በውስጣችን ይፈራረቃል፤ የነገንማ ማን ያውቃል፤

እዚህም ባባረሩን ታጣቂዎች ታግተናል፤ የእነርሱን አገርና መንግሥት ስፋት ሳስበው በእጅጉ ይደንቀኛል፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  እግዚአብሔር ሙቷል። - መ/ር አበባው አሰፋ

ከአንግዲህ ስማችሁን፤ ጐጣችሁን፤ ዘራችሁን አልጠራም ህመም፤ ሃዘኔም ተደራርቦ ሸክማችሁ ይከብደኛል።

እነሆ በአምላክ ፈቃድ በሳምንት ውስጥ ለትንሽ ሰዓታት እንቅልፍ አሽንፎ ረታኝ፤

ስነቃ ግን ምነው እንዳሸለብኩ በቀረሁ ብዬ አጣውርኩ ዙሪያ ገባየን ለቅሶ እያጀበኝ፤

አዳሩን ሞት አንድ አዛውንት እና ህጻን ልጅ መቀማቱን አበሰሩኝ፤

በቅናት እነርሱስ እውነተኛ አገራቸውን አገኙ ብዬ አሰብኩኝ፤

አምላኬን በዘዎትር ጸሎትና ኑዛዜ በወቀሳ ሳንገጣውር፤

በዚያች አልባሌ የስደተኞች ሰፈራ አካሌ ዝሎ ሙጥኝ ባላት ምድር፤

በውድቅት ሌሊት አንጋጦ የኳተነው መንፈሴ ተጐዳኝቶ ከጨረር፤

ከአንድዬ መንፈሳዊ ራዕይ ሰማያዊ ትዕንግርት ሚስጥር፤

ለሰው ልጅ አደራ ያለኝ በምድር አጥድፎ አስነሳኝ ለታዕምር፤

ሲያስጐበኘኝ በህሊናዬ መስተዋት የጥፋተኞችን ጓዳ ጎድጓዳ ስቆጥር፤

በአርባ ጉጉ፤በበድኖ፤በአሶሳ፤ በጉራ ፍርዳ፤ቤሻንጉል፤በጋምቤላ ሲዖል አጥር፤

የምድራችን ሳጥናዔል ያረቀቁት ‘ራዕይ’ የሚሉት በላዕይሰብ የቆሪጥ ግብር፤

የጠነዛ ‘ቋንጣቸውን’ የነቀዘ አጥማቸው በአገር መዲና ‘አዚመ-መርገምቱ’ ሲኖር፤

ግባተ መሬት ላይገባ የጀመረውን ሳያስጨርስ ራዕይ የሚሉት የደንገጡራን፤ደቀመዝምር፤

የእልቂት ክንፉን እስኪዘረጋላቸው ‘መለስ’፤ ‘ሰይጣነ-መለኰታቸው’ ሊያንዣብብ በአሳቻ ቀትር፤

ከላይ መርዝ ሊያዘንቡብን፤ ከምድር ሰደድ ሊለቁብን እንደ ‘ሃውዜን’ እጥፍ በትር፤

አቅሌን ገዝቸ ሳማትር፤ዙሪያ ገባዬን እንዳስተባቃ አባተተኝ የሚሆነውን ልመረምር መልዕክቱንም ላበስር፤

ለካስ ሊቀብሩን ነው ! በአንድ ጉድጓድ ‘አነባብሮ አማሮችን’ የአባይ ግድብ ቀን ከሌሊት የሚቆፈር፤

ፍቹ ይኸ ነው! ከአንድዬ! ወገኔ! አገሬ! ተመከር! ተዘከር! ኢትዮጵያ እንጅ ጉድጓድ አይደለም ያንተ አገር፤

ከእንግዲህ! ስም፤ ዘርህን፤ ጐጥህንም አላነሳ፤ የቁም ኑዛዜዬን አድርሻልሁ፤ ሺ ጊዜ ብሞትም በከንቱ አልቆረቆር።

የጐንቻው !

yegonchaw@yahoo.co.uk

06.04.2013

በ PDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

1 Comment

  1. ለካስ ሊቀብሩን ነው በአንድ ጉድጓድ አነባብሮ አማሮችን የአባይ ግድብ ቀን ከለሊት የሚቆፈር
    ፍቾው ይሄ ነው ከአንድየ፣ አገሬ፣ወገኔ፣ተመከር፣ተዘከር፣ኢትዮጵያ እንጂ ጉድጓድ አደለም ያንተ አገር
    እውነትም ኑዛዜ ወንድሜ እጅህ ይባረክ ድላችንንም ቅርብ ያድርገው እኛንም ፈጣሪ ጀግና ያድርገን እንቢ ለሀገሬ እንቢ ለራሴ የሚለው ይብዛ

Comments are closed.

Share