(በፍሬው አበበ)
ከመጋቢት 14 -17 ቀን 2005 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ የተካሄደው የኢህአዴግ ጉባዔ በ2003 መጀመሪያ ዓመት ላይ በይፋ የተጀመረውን የመተካካት ዕቅድ ያስቀጥላል የሚል ተስፋ በድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ ነበር። ይህ ተስፋ ከጉባዔው አስቀድሞ አባል ድርጅቶቹ (ህወሃት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን) በተናጠል ባካሄዷቸው ጉባዔዎች በተሟላ መልኩ እንዳልተከናወነ ታየ። አንዱና ዋናው ጉዳይ ነፍሳቸውን ይማርና አቶ መለስ ዜናዊ በተገኙበት ከመስከረም 3-7/2003 ዓ.ም በአዳማ በተካሄደው 8ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በይፋ ተጨብጭቦላቸው፣ ተመርቀው ከአድናቆት ጋር ተተክተዋል የተባሉት አቶ አዲሱ ለገሰን ጨምሮ ጎምቱዎቹ ነባር አመራሮች አሁንም ከፓርቲ ስልጣናቸው ለመልቀቅ በጎ ፍቃዳቸውን ያለማሳየታቸው ጉዳይ መነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ ነበር። ባልተለመደ መልኩ በኢህአዴግ 9ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ ሐሜትን ጭምር ያስከተለውም ይኸው የከፍተኛ አመራሩ በመተካካት አፈጻጸም ረገድ ሸርተት ብሎ የመታየቱ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ብአዴን ይበልጥ ተወቃሽ ሆኗል።
ከመተካካት አንጻር የመለስ ዕቅድ ምን ነበር
በአንድ በኩል አቶ መለስ ዜናዊ ለ20 ዓመታት በከፍተኛ የመንግስት ሥልጣን ላይ የመቆየት ጉዳይ በጋዜጠኞችና በአንዳንድ ዴሞክራት ኃይሎች “ስልጣንዎ ገደብ የለውም ወይ” የሚሉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ በሌላ በኩል ደግሞ የእድሜና የጤና ጉዳይ ነባር አመራሩን በአዲስ ለመተካት አስገዳጅ የመሆኑ ጉዳይ ለመተካካት አጀንዳ መምጣት በር መክፈቱ ይነገራል። በዚህ ምክንያት ኢህአዴግ በሶስት ምዕራፎች በመከፋፈል ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2007 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት ጊዜያት ነባሩን አመራር ከፊት መስመር እያስለቀቁ በወጣት ኃይል የመተካት ዕቅድ በመንደፍ ወደ ትግበራ ተሸጋገሩ። በዚሁ መሰረት ጥቂት የማይባሉ ከፍተኛ ነባር አመራሮች በ2003 እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን በተለይ የአቶ አዲሱ ለገሰ ስንብት ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ጭምር የተሰጠውና ደማቅ ነበር። ይህ ዕቅድ በሰሞኑ ጉባዔ በተጀመረው መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሎ በታሰበበበት ወቅት ቀድሞ የተሰናበቱት አንዳንድ አመራሮች በፓርቲያቸው ስራአስፈጻሚነትና ማዕከላዊ ኮምቴ አባልነት እንደገና ብቅ ማለት ብዙዎች አስገርሟል። አንዳንዶችም ክስተቱን የመተካካት ዕቅዱ መክሸፍ ጥሩ ማሳይ አድርገው በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
መተካካት ወይስ ለስልጣን ገደብ ማበጀት
ኢህአዴግ የመተካካት ዕቅድን ስራ ላይ ማዋል የፈለገው ነባሩ አመራር በዕድሜ መግፋት መስራት የማችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በአዲስ ኃይል በመተካት ገደብ የለሽ ስልጣኑን ማስቀጠል ዓላማ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።
በምርጫ 2002 ኢህአዴግና አጋሮቹ 99.6 በመቶ በማግኘት አሸንፈናል ካሉ በኋላ ለሕትመት የበቃው አዲስ ራዕይ የሐምሌ-ነሐሴ 2002 ዕትም ግንባሩ ከተተካኪ የፓርቲ ስርዓት ወደ አውራ ፓርቲ ስርዓት መሸጋገሩን ይፋ አድርጓል። ይህም ግንባሩ ለቀጣይ 30 እና 40 ዓመታት እንዴት በስልጣን ላይ ሊቆይ እንደሚችል የራሱን አቅጣጫ ያሳየበት ነበር ማለት ይቻላል። የአውራ ፓርቲ ስርዓት እንደመነሻ የሚወስደው ጃፓንና ሲዊዲንን ነው። የርዕዮተ ዓለም መጽሔቱ እንዲህ ይላል። በጃፓን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአውራ ፓርቲ ስርዓት በመከተል ለስድሳ ዓመታት ገዥው የጃፓን ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ማስተዳደሩን ያስታውስና ከ60 ዓመታት በኃላ ሶስተኛ ትውልድን የያዘው ተቃዋሚ ኃይል ማሸነፉን ያወሳል። በሲዊዲንም በተመሳሳይ መንገድ ገዥው ፓርቲ ለረዥም ጊዜያት ስልጣን ላይ መቆየቱን የሚያስታውሰው ይህው መጽሔት ይህ የአውራ ፓርቲ ስርዓት (ዶሚናንት ፓርቲ ሲስተም) እንደሚባል ያስረዳል።
እናም አቶ መለስ እንደጻፉት የሚነገርለትና በአዲስ ራዕይ ከመታተሙ በስተቀር እምብዛም በግንባሩ ሌሎች አመራሮች የማይጠቀሰው ይህው ጹሑፍ ኢህአዴግ ልክ እንደጃፓን እና ሲዊዲን ራሱን ወደአውራ ፓርቲነት ማሸጋገሩን በማብሰር በምርጫ 2002 አስገራሚ ድል ያስገኙለትን መሰረታዊ ባህሪዎች ጠብቆ ከተጓዘ በቀጣይ አንድና ሁለት ምርጫዎችን ያለስጋት ሊያሸንፍ እንደሚችል ይተነብያል። ይህ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ የሚቆይበትን ጠቅላላ ጊዜ ወደ30 ዓመት እና ከዚያ በላይ ያደርሰዋል።
አንዳንዶች የኢህአዴግ የመተካካት ዕቅድ መዋቅራዊ ለውጥ ባላመጣበት ሁኔታ የሚካሄድ በመሆኑ የጉልቻ መለዋወጡ ብቻውን ለሕዝቡ የሚያስገኘው ፋይዳ አይኖርም ይላሉ። ሌሎች ወገኖች ደግሞ ሕገመንግስቱ ጭምር የጠ/ሚኒስትሩን የሰልጣን ዘመን እንዳይገድብ በተደረገበት ሁኔታ ግለሰቦች ሲያረጁ የመተካካት ካርታን ከመሳብ ውጪ ሌላ አማራጭ በመጥፋቱ የተደረገ ነው በማለት መቅደም የነበረበት ስልጣንን በሕግ መገደብ መሆን ነበረበት ሲሉ ይሟገታሉ። ለዚህም እንደአብነት የሚያነሱት ከአራት ዓመታት በፊት በኬንያ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ምርጫ በኃላ ኬንያዊያን ሕገመንገስታቸውን ጭምር እንዲሻሻል ማድረጋቸው፣ ከማሻሻያው አንዱ ደግሞ የስልጣን ገደብ ማካተቱ መሆኑን ያስታውሳሉ።
አቶ አብዱራህማን አህመዲን የቀድሞ ፓርላማ አባል የሰዎች መተካካት በራሱ የፖሊሲ ለውጥ ባያስከትልም ምንም ለውጥ አይኖርም ብሎ መውሰድ አይቻልም ሲሉ ይከራከራሉ። “ለምሳሌ አቶ ኃ/ማርያም አቶ መለስን ተክተዋል። ሁለቱ ሰዎች አንድ ዓይነት፣ ልምድ፣ ትምህርት፣ ፍልስፍና የላቸውም። ምንም እንኳን በአንድ ርዕዮተዓለም ቢመሩም ለውጦች ይኖራሉ። የቀድሞ የቻይና መሪዎች ሚስቶቻቸውን በአደባባይ ይዘው የመታየት ልምድ አልነበራቸውም። የአሁኖቹ ተተኪዎች ግን ሚስቶቻቸውን በአደባባይ ይዘው ይታያሉ።ይህ ዓይነት ቀላል የሚመስሉ ለውጦች በግለሰቦች የሚመጡና የሚተገበሩ ናቸው” ሲሉ ያስረዳሉ።
ኢህአዴግ በውስጥ ፖሊሲው በፓርቲ ስልጣን ላይ ለመቆየት ዕድሜ 65 ዓመት፣ በመንግስት ሃላፊነት ከሁለት የምርጫ ጊዜ በላይ መቆየት እንደማይቻል በከፍተኛ አመራሮቹ ሲጠቀስ ስምቼአለሁ ካሉ በሃላ ይህ ጥሩ ጅምር ይመስለኛል በማለት ያስቀምጣሉ።
በመተካካት ስም የፓርቲ ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ያስረከቡት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በአንድ ወቅት ይህንኑ የኢህአዴግ የመተካካት ዕቅድ አስመልክቶ ለዚህ ዘጋቢ እንደተናገሩት መተካካት ሒደቱ በታሰበው መልክ ቢከናወን እንኳ ለውጥ ያስገኛል ብለው እንደማያስቡ ይናገራሉ። “… መተካካት ለሃገራችን የፖለቲካ ባህል በጎ ፋይዳ የለውም። እንዲያውም ሒደቱ ቤተመንግስታዊ መሿሿም ዓይነት ነው። …የኢህአዴግ ባህርይ የሚመነጨው በትጥቅ ትግል በነበሩና ባልነበሩ ሰዎች በመመራቱ አይደለም። እነዚህ የሚተኩ ሰዎች ስልጣን ለመያዝ የሚያስፈልግ ችሎታ አላቸው ወይ የሚለው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ስልጣን ለወጣቶች የምታስተላልፈው የዴሞክራሲ እሴቶችን በመናድ ሊሆን አይገባም” ብለዋል።
ከመጀመሪያው ምዕራፍ መሻገር ያልቻለው የመተካካት ጅምር
አቶ መለስ ዜናዊ ባወጡት ዕቅድ መሰረት በተለይ በ2003 ዓ.ም መጀመሪያ የተካሄደውን የኢህአዴግ 8ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ተከትሎ በመተካካት ስም ጎምቱ የተባሉ ሚኒስትሮቻቸውን ከከፍተኛ የመንግስት የስልጣን እርከን ላይ አንስቷል። መስከረም 25 ቀን 2003 ዓ.ም ለፓርላማ አቅርበው ካሾሙአቸው የካቢኔ አባላት ዝርዝር ውስጥ አቶ አዲሱ ለገሰ ምክትል ም/ጠ/ሚኒስትር፣ አቶ ስዩም መስፍን የውጪ ጉዳይ ሚ/ር፣ አቶ ግርማ ብሩ የንግድና ኢንዱስትሩ ሚ/ር፣ አቶ አስፋው ዲንጋሞ የውሃ ሐብት ሚ/ር፣ ወ/ሮ ሙፍረሂት ካሚል የሴቶች ጉዳይ ሚ/ር፣ አቶ መሐመድ ድሪር የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር፣ አቶ ሐሰን አብደላ የሠራተኛና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚ/ር፣ ዶ/ር ካሱ ኢላላ የስራና ከተማ ልማት ሚ/ር፣አቶ ተፈራ ዋልዋ የአቅም ግንባታ ሚ/ር የነበሩትን ሳያካትቱ ቀርተዋል።በተጨማሪም አቶ ተሾመ ቶጋ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባዔ፣ አቶ ደግፌ ቡላ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባዔ በአዳዲስ ሰዎች እንዲተኩ አድርገዋል። ይኸው የመተካካት ዕቅድ በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት በያዝነው ዓመት የተወሰኑ ሰዎችን በአዲስ በመተካት በቀጣዩ 2007 ዓ.ም የማጠናቀቅ ዕቅድ በአቶ መለስ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ እንደታሰበው አለመከናወኑ ብቻም ሳይሆን ከሁለት ዓመት በፊት በኢህአዴግ ጉባዔ ተጨብጭቦላቸው በክብር የተሸኙት እነአቶ አዲሱ ለገሰ በፓርቲ ከፍተኛ አመራር ውስጥ እንደገና ብቅ ማለት በዚህ ረገድ የግንባሩ ራዕይ እንደከሸፈ በመጥቀስ ለመከራከር አስችሏቸዋል።
አቶ አብዱራህማን አህመዲን ቀድሞ ፓርላማ አባል የመተካካቱ ሒደት አቶ መለስ ባስቀመጡት ዕቅድ መሰረት አለመከናወኑን እንደሚያምኑ ይናገራሉ። አያይዘውም ግንባሩ የመተካካት ዕቅዱን ማስፈጸሚያ ፖሊሲ ያለው እንደማይመስላቸው፣ ይህም መሆኑ በሰሞኑ ጉባዔ የተካፈሉ ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የሚናገሩት በአፈጻጸም ረገድ ግልጽነት እንደሌለ የሚያመለክት ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በራሱ አባላት ጭምር ከፍተኛ ትችት እየቀረበበት የሚገኘው ኢህአዴግ ግን የመተካካት ዕቅዱ በተቀመጠለት መርሃ ግብር መሠረት እየተጓዘ መሆኑን በመግለፅ የቀድሞ መሪውን የአቶ መለስን ራዕይ ለማስፈፀም እንደሚተጋ ጮክ ብሎ ከመናገር አልቦዘነም።( ይህ ጹሑፍ በሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 395 ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2005 ታትሞ ለንባብ የበቃ ነው)