Getachew Reda (Editor- Ethiopian Semay) www.ethiopiansemay.blogspot.com [email protected]
“የትግራይ ህዝብ ዝምታ ሲተረጎም” https://zehabesha.info/archives/1156 በሚል ርዕስ ከመቀሌ ትግራይ ክ/ሃገር (በወያኔ የአፓርታይድ ስያሜ አጠራር -“ትግራይ ክልል”) በወጣት አብርሃ ደስታ ተጽፎ፤ ኢትዮ-ሚዲያ ድረገጽ ላይ ተለጥፎ አንብቤአለሁ። ጽሑፉ የወያኔን ኢፍትሐዊ ሥርዓትና አሰራር የሚቃወም ከትግራይ አዲስ ትውልድ የተጻፈ በመሆኑ ለጸሐፊው ‘አድናቆት እና ማበረታቻ” ላቀርብለት እፈልጋለሁ። በርታ ተበራታ! እያልኩ።
የጸሐፊው ብርታት እና ተነሳሺነት አንደተጠበቀ ሆኖ፤ የትግራይ ሕዝብ በወያኔ ሥርዓት መጨቆኑን አንጂ የጭቆናው ዝርዝር አልነገረንም። ጭቆና መኖሩን በደፈናው መግለጹ፤ ጭቆናአንዳለ አንድናውቀው የሚያሳስብ ካልሆነ በቀር የጭቆናው ደረጃ እና ጥልቀት፤ የጭቆናው ዓይነት/መራራነት ምን አንደሚመስል ለጸሓፊው ግልጽ አንደሆነ አንጂ እኛ ከሩቅ ላለነውም ሆነ ከትግራይ ክ/ሃገር ውጭ በሌሎቹ ክ/ሃገሮች ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ድፍን ነው። ስለሆነም ጸሐፊው በሚቀጥለው ጽሑፉ የጭቆናው መጠን እና ስፋት ግልጽ አንደሚያደርግልን ተስፋ አለኝ።ጸሐፊው የትግራይ ሕዝብ ጭቆና እና ብሶት ነጋሪ በማጣቱ አልተጨቆነም እያሉ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ይከራከራሉ ሲል ተቃዋሚው ቢከስም፤ትግራይ ውስጥ ጭቆና አለ ወይስ የለም ብየ ለመከራከር ሳይሆን ጸሐፊው አጋጣሚውን ተጠቅሞ የህ.ወ.ሓ.ት ሥርዓት በትግራይ ሕዝብ ላይ ግፍ እየፈጸመበት ነው ብሎ የነገረንን ድፍን አባባል በደፈናው እንጂ የጭቆናው ዓይነትና እና ብሶት ዝርዝር በጽሑፉ አልገለጸም።
ፀሐፊው በትግራይ ውስጥ ‘ጭቆና አለ’ ካለ በሗላ፤ ሰብአዊ እና የዜግንት መብቱን እየረገጠው የሚገኘው ጨቋኙ የወያኔዎቹን ሥርዓት፤’ፊት ለፊት ተጋፍጦ ተቃዉሞውን ለመግለጽ አልቻለም፡ በዚህ ላይ አንዱ ሲጨቆን ሌላው ዝም ይላል በማለት ካሁን ቀደም በጻፈው ጽሑፍ ስላተተ ይመስለኛል ፕሮፌሰር መስፍን ተስፋማርያም “በትግራይ ሰዎች ሲበደሉና ሲጠቁ ሌላው ሰው ዝም የሚለው በምን ምክንያት ነው ?” በለው ለጠየቁት መልስ ሲሰጥእንዲህ ይላል
‘ባለፈው እንዲህ ፅፌ ነበር’ – ይልና፤-
“… የትግራይ ህዝብ በሙሉ የህወሓት ደጋፊ ነው ማለት ኣይቻልም። ብዙ የሚቃወም ኣለ። ብዙ የሚጨቆን ኣለ። በትግራይ የሌለው ጭቆናን የሚያጋልጥ ሰው ነው። በሌሎች ኣከባቢዎች (ከትግራይ ውጭ) ሰው ሲታሰር ወይ ሲገደል የሚናገርለት ወይ የሚጮህለት ወገን አለው። በትግራይ ግን የለም። ኣንዱ ሲታፈን ሌላው ኣብሮ ዝም ይላል። ይሄ ነው ልዩነቱ እንጂ በትግራይ ጭቆና ስለሌለ ኣይደለም።
” ከዚህ በመነሳት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እንዲህ ጠየቁ:- ካለ በሗላ፤-
“አብርሃ ደስታ፤ ያልከውን አምናለሁ፤ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህና አንተ በተመቸህ መንገድ መልስልኝ፤ በትግራይ ሰዎች ሲበደሉና ሲጠቁ ሌላው ሰው ዝም የሚለው በምን ምክንያት ነው?”
ብለው ለጠየቁት አብርሃ ደስታ መልሱን በ6 የተለያዩ ዘርፎች የተቀመጡ ምክንያቶች መልስ ሰጥቷል።
በቀዳሚው መለስ ብንጀምር አብርሃ እንዲህ ይላል፤-
“ መልስ፤-
ኣብዛኛው የትግራይ ሰው የህወሓት መንግስት በዜጎች በደል ሲያደርስ ከመቃወም ይልቅ“ብኡ የሕልፎ” የሚል ብሂል (ወይ ኣባባል) ተግባራዊ ያደርጋል። “ብኡ የሕልፎ” የትግርኛ ኣባባል ሲሆን Literally ‘በዛ ይለፍልን’ (ወይ ‘የባሰ ኣታምጣ’) ዓይነት ትርጉም ኣለው።
ለምንድነው የትግራይ ህዝብ ‘ብኡ የሕልፎ’ (የባሰ ኣታምጣ) በሚል የህወሓትን ጭቆና‘ኣሜን’ ብሎ ለመቀበል የሚገደደው?
(1)ደርግ በትግራይ ህዝብ ብዙ ግፍ ያደረሰ ቢሆንም ህወሓት ከደርግ የባሰ ኣደገኛ ገዳይ መሆኑ የትግራይ ህዝብ በደምብ ያውቃል። የህወሓት የኣገዳደል ወይ ጭቆና ሥልት በጣም የረቀቀ ነው። በዚህ የረቀቀ መንገድ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ተገድለዋል ወይ እንዲጠፉ ተደርገዋል። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ‘ህወሓት ከደርግ የባሰ ኣደገኛ ነው’ ብሎ ያስባል፤ ይፈራልም። ለምሳሌ እኔ ህወሓትን ፊት ለፊት ስቃወም ብዙ ጓደኞቼ ህወሓት ሊገድለኝ እንደሚችል ስጋታቸው ያካፍሉኛል። (የህወሓት ተግባር በደምብ ስለሚረዱ)። ይህም ሁኖ ግን በኣሁኑ ሰዓት ብዙ የሚቃወም ኣለ። (ፓርቲውም እየተዳከመ ነው)።” ብሏል::
ባጭሩ አብርሃ እየነገረን ያለው ፤የትግራይ ሕዝብ እንደሌሎቹ በወያኔዎቹ ሥርዓት እየተጨቆነ ነው፤ ነገር ግ ን እየገጠመው ካለው ጭቆና ‘የባሰ ጭቆና” እንዳይደርስበት ‘ስለሰጋ’ ፊት ለፊት መጋፈጡን በፍርሃት ምክንያት ድምፁን ሊያሰማ አልቻለም። ለፍራቻውም ምክንያት በአጽንኦት ሲያሳየን “የትግራይ ህዝብ ‘ህወሓት ከደርግ የባሰ አደገኛ ነው ብሎ ስለሚያምን (ተቃውሞውን ለማሰማት) ይፈራል”። ይላል።
ፀሐፊው በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ ያስቀመጠውን ፍሬ ሀሳብ ለትግራይ ሕዝብ ዝመታ መምረጥን አንደ ምክንያት የሆነው በ4ኛ ረድፍ ያስቀመጠው ሌላ ምክንያት በተራ ቁጥር 1 ያስቀመጠው ለትግራይ ሕዘብ ዝመታ ምክንያቱ በሚከተለው ሲያፈርሰው ይታያል።
(4) ደርግ በትግራይ ህዝብ ጠላት ተደርጎ ነው የሚወሰደው (በፈፀመው ግፍ)። የትግራይ ህዝብ ያን የደርግ ኣገዛዝ ኣይፈልግም። ‘ደርግ ይመለሳል’ ከተባለ ታድያ (ማመዛዘን ቢያስፈልግም) ህዝቡ ከደርግ ህወሓትን መምረጡ እንዴት ይቀራል?”ይላል።
እዚህ ላይ ነው አነጋጋሪ ነጥብ ሆኖ ያገኘሁት። በ 1 ኛ ተራ ቁጥር “ የ ትግራይ ህዝብ‘ህወሓት ከደርግ የባሰ አደገኛ ነው’ ብሎ ያስባል፤ ይፈራልም።” ይለናል። በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት እና ተቃውሞውን ዝም ለማሰኘት አንዲመቸው የሚጠቀምበት ስልት “በተለያዩ ዮፖለቲካ ድርጅቶች የተሰገሰጉት ተቃዋሚዎች “ደርግ’ ስለሆኑ ፤የደርግ ሥርዓት ለማምጣት እየጣሩ ስለሆነ አርፈህ ተገዛ እና ወያኔን ምረጥ ስለሚለው “ህዝቡ ከደርግ ህወሓትን መምረጡ እንዴት ይቀራል?” በማለት የትግራይ ሕዘብ ‘ወያኔ’ ሥልጣን ላይ ሊቆይ ባይፈልግም “ደርግ መጥቶ አንደገና ከሚገዛን፤ ወያኔ አንመርጣለን እና ጭቆናው እየተቀበልን፤ ወያኔ ያቆይልን” በማለት ሳየወድ ምርጫው አድርጎታል፡ በማለት እርስ በርሱ በተምታታ ምክንያት ‘ለሕዝቡ ዝምታ’ አነኚህ እና ሌሎቹ የተዘረዘሩ ምከንያቶች ሊነግረን የፈለገው ፍሬ ሃሳብ ሳይገባን ልያሳየን የፈለገውን ስዕል ለማየት አላስቻለንም።
The New Tigray Millionaires their car matching the roof of their house |
ይህንን አንዲህ ልተወው እና ወደ ሚቀጥለው ሃተታው ደግሞ ልሂድ። ፕሮፌሰሩ “ በትግራይ ሰዎች ሲበደሉና ሲጠቁ ሌላው ሰው ዝም የሚለው በምን ም ክንያት ነው?” ብለውለጠየቁት ደግሞ “መልስ” ብሎ የሰጠው ሌላኛው መልሱ አንዲህ ይላል፡-
“በሌሎች ኣከባቢዎች ( ከትግራይ ውጭ) ሰው ሲታሰር ወይ ሲገደል የሚናገርለት ወይ የሚጮህለት ወገን ኣለው። በትግራይ ግን የለም። ኣንዱ ሲታፈን ሌላው ኣብሮ ዝም ይላል።” በማለት ለዝምታው ምክነያት ይገልጻል።
ወንድም አብርሃ አንድ የሳተው ነገር ያለ ይመስለኛል። ከላይ እራሱ የጠቀሰው የሕዘቡ ለዝምታው ምክንያት “ደርግ’ የተባለው የማዶ ጅብ ተመልሶ መጥቶ ከሚበላኝ “ወያኔ” የተባለው የራሴው ጅብ ቢበላኝ ይሻለኛል” “የባሰው አታምጣ (ብኡ የሕልፎ) ብሎ ምርጫው ላስቀመጠ ሕዝብ ሌላው ጮኸለት አልጮኸለት የሚፈይደው ምንድ ነው? ጭቆናው ስላልተነገረለት ነው ከፍርሃቱ ለመውጣት ያዳገተው? ስለ ጭቆናው የሚናገርለት ክፍል ቢያገኝስ ከፍርሃቱ ሰብሮ ለመውጣት የሚረዳው የስነ ልቦና ብርታት የሚያገናኘው ምን ነገር አለ?
በጣም የሚገርመው ደግሞ ስለ ትግራይ ሕዝብ ጭቆና ለዓለም እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚናገርለት የለም! የሚለው አባባል ተቀባይነት አለው አንኳ ብንልም፤ ዞሮ ዞሮ፤ ስለትግራይ ሕዝብ ስቃይ መጮህ እና ስለ ሕዝቡ መብት በወያኔ ስርዓት መረገጥ ሊናገሩለት የሚገባቸው እና ሕዝባዊ አመጽ ማስነሳት እና ሕዝቡን አስተባብሮ ከጭቆና ለማላቀቅ ለድል ማብቃት ግምባር ቀደም ሐላፊነቱን ሚና መሸከም የነበረባቸው የትግራይ ወጣቶች እና “የትግራይ ምሁራን” የት አሉ? ምንስ እየሰሩ ነው? ብሎ አብርሃ ደስታ በተጠያቂነት መቆም ያለባቸው በተለይ የትግራይ ምሁራንን በትንታኔው ውስጥ አንዳች ሐረግ ትንፍሽ አላለም።በተጠያቂነትም አላስቀመጣቸውም።ወጣቱ የስርዓቱ ተገዥ እና አምላኪ ነው? ከሆነስለምን? በምን መልክስ እራሱን ነፃ ማውጣት ይችላል? የሚሉት ትንታኔዎችን አልነካም። ለምን?
ሕዝቡ የባሰ አታምጣ ብሎ መስጋቱ የሚያስገርም አይደለም። ሰው አንደሰው መጠን መከራው ሲበረታበት ወደ ተ ገዢነት ያ ደላል ( የተለያዩ ተቃራኒ ትንታኔዎች በሌላ በኩል ማስቀመጥ የሚቻል ቢሆንም)። ታዲያ የጭቆና ቅምበር ተጭኖበት ‘ዝምታን” የመረጠ ሕዝብ፤ ከዘምታው ዓለም ጐትቶ ሊያወጣው ግምባር ቀደም ሚና ሊኖረው የሚገባው ያለው የትግራይ ምሁር፤ለትግራይ ሕዝብ በመብት ቀዳሚ ጠብቅና አለን ብለው በድርጅት መልክም ሆነ በግል የቆሙ የትግራይ ምሁራን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስቃይ መገመት በሚያስቸግር ከባድጥፋት አድርሰዋል እያልን እኔም ሆንኩኝ መሰል ኢትዮጵያ ወንድሞች/እህቶች ሳይሰለቸን ተናግረናል። አለመታደል ሆኖ፤ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ነባር ተቃዋሚዎችም ሆኑ አዲስ ትኩስ ሃይሎች እየሆኑ የመጡ ጥቂቶች አንደ አብርሃ ደስታ የመሳሰሉ ተቃዋሚ የትግራይ ተወላጆች፤ በትግራይ ምሁራን ላይ ለመተቸት ለምን ግራ እንደሚጋቡ ለኔ ግልጽ አይደለም።
ሁለት ዓይነት የትግራይ ምሁራኖች አሉ። አንደኛው ቡድን ወያኔን በግልጽ የሚቃወሙ፤ ነገር ግን “ዞር አሉ አልሸሹም” ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ከሚያሞቃቸው “የጎሳ ቀፎ” መውጣት የማይፈልጉ ናቸው (ትንሽ ስታካቸው እና ክርክሩ ጠበቅ ሲልባቸውና ሲበሳጩ ወያኔነታቸው በቀላሉ የሚነበብባቸው ማለት ነው)። ወያኔ መቃወም ብቻ አያስፈልግም፤ መልካሙን ነገርም አውሱለት፤ እየተሰራ ያለው ሕንጻ፤ሆቴልናፋብሪካ አወድሱለት ወዘተ…. የሚሉ ናቸው (ሂትለር ጀርመንን በኢንዱስትሪ በር ከፍቶላታል እና ስለ ሂትለር በጐነት አውሩ አንደማለት)። አንዲህ አይነት የተምታታ አቋም ያለቸው የትግራይ ምሁራኖች ብዙዎቹ ቢሆኑም ለምሳሌ ለምጥቀስ አንደ ዶ/ር ገላውዴዎስ አርአያ እና ዶ/ር ሃይሉ መንገሻ የመሳሰሉት መጥቀስ ይቻላል።
ሌላው ቡድን ደግሞ በግልጽ የወያኔን ፖሊሲ አቅፎ ደግፎ “እልል” እያሉ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ እየተቀበሉ የሚተገብሩ እና የጥፋት መልእክተኛ የነበረው የመለስ ዜናዊ አወዳሾች አንደ እነ ዶ/ር ተወልደብርሃን ገ/አግዚአብሔር (የደራሲው የስብሐት ገ/እግዚአብሔር ወንድም)http://youtu.be/f75zPblWSiI የሕዝቡን መከራ የሚያራዝሙ፤ጠባብ ብሔረተኛነት ሕሊናቸውን ያሰወራቸው “ዑውራን” ምሁራን ይገኙበታል። አነኚህ እና የመሳሰሉ የትግራይ ምሁራን 1ኛ የሕዝብቻው ስቃይ እያዩም ቢሆን ባድርባይ ጸባይ እና ወያኔ በለገሰላቸው ምቾት ታውረው ተባበሪ የሆኑ ናቸው።
ዛሬ ዛሬ ቀዝቀዝ አሉ እንጂ፤ሌሎቹ ደግሞ መጽሔት አቋቁመው የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው በጸረ አማራነት እና በጸረ ኢትዮጵያነታቸው የታወቁ ከኤርትራ ምሁራን ጋር እጅ እና ጓንቲ ሆነው “ጸረ አማራ” (እነሱ ነፍጠኛ የሚሉትን) መስመር በማራመድ፤ የማይገቡ አሳዛኝ ቅስቀሳዎች በመዝራጋት መጥፎ የታሪክ ጠባሳ የተው ናቸው። አንዳንድ አንባቢዎች ከባዶ ሜዳ ተነስቼ ለሃሜት የጻፍኩት እንዳይመስላቸው ከኤርትራ ምሁራን ጋር ግምባር ፈጥረው “ወያኔን እያወደሱ” በነዚህ ምሁራኖች በአማራነት የሚጠሩ አንዳንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን በማይገባ በመዝለፍ (በመጽሔቱ ላይ ለምሳሌ አቡነ መርቀሬዎስን “ዘ አዘር ዶግ/ሌላኛው ውሻ” በማለት በፎቶአቸው ላይ ተጽፏል) ወይንም ዶኩመንቶችን በማዛባት የሕዝቡን አፍ ለማስዘጋት ሲሞክሩ ነበሩ ዝነኚህ የትግራይ ምሁራን እና የኤርትራ ምሁራን ስም ዝርዝር ለማየት ከፈለጉ ለምሳሌ “ኢትዮጵያን ኮመንታተር” የተባለው መጽሄት አዘጋጆች የነበሩትን መጥቀስ ይቻላል። ባንዳንድ ጸሐፊዎች አባባል መጽሔቱን “ሻዕቢያ ወያኔ ፒስ ማውዝ” ሲሉት ነበር።
ስም ዝርዝር፤ ማነጂንግ ሲኒየር ኤዲተር ኤንድ ፓብሊሺንግ ዶ/ር ሃይለማርያም አበበ፤
Editors ዶ/ር ገላውዴዎስ አርአያ (ኒው ዮርክ)፤ ክንፈ አብርሃ (ስቶክሆልም ስዊድን) ፤ዶ/ር ሶሎሞን ዑንቋይ (ካምብርጅ- ዩናይትድ ኪንግዶም) ዘመነ ልብነድንግል(ፎርት ኮሊስ ኮሎራዶ)
አምደኞች (Contributors)፤ መስፍን አርአያ (አርሊንገተን ቨርጂኒያ)፤ ዶ/ር ደስታ በየነ፤ ዶ/ር ተክኤ ፍስሃጽዮን ( ሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ፤ባልቲሞር ኤም ዲ) ሻዕቢያ (ኤርትራዊ)፤ ጆርዳን ገብረመድህን (ኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርሲቲ- ቦስተን) በህይወት የለም- ነገር ግን ሻዕቢያ (ኤርትራዊ)፤ ዶ/ር አሰግድ ሐጎስ (ዩኒቨርሲቲ ዋሺንገተን ዲሲ) ጸጋይ ሃይሉ (ከኢትዮጵያ)፤ዶከተር ግደይ ወለደገብሪኤል (ሎስ አልሞስ ላብ-ኤን ኤም) አማኑኤል አሰፋ (ዋሺንግተን ዲሲ)፤ዑቕባዝጊ ዓባይ (ሰንሰናቲ- ኦሃዮ)
Editorial Advisors ዶ/ር አምሃ አሰፋ (ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ- ዋሺንገተን ዲሲ (አገር ውስጥ እያለ በወጣትነታችን የቅርብ ጓደኛነት የነበረን አሁንም የወያነ ደጋፊ አንደሆነ ነው የሚነገረኝ)፤ ሐጎስ ካፊል (ካላማዙ ኤም አይ)፤ዶ/ር ገብረህይወት ተስፋጊዮርጊስ (ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዊስካንሰን)፤ ዶ/ር ፀሃየ ተፈራ (ዳይሬክተር ኢትዮጵያን ኮሚኒቲ ዴቨለፕመንት ካውንስል አለክሳንድርያ -ቨርጂኒያ)፤ዶ/ር ያዕቆብ ፍስሃ (ምቺጋን ዩኒቭርሲቲ)።
እነዚህ በሙሉ ዶክተሮች ናቸው። ይታያችሁ የላቸው መዓረግ እና የዘፈቁበት የብሄረተኛ ፕሮፓጋንዳ ስታነጻጽሩት፤ በወያኔ ለተረገጠው የኢትዮጵያ ሉአላዊነት እና የሕዝቡን መብት መረገጥ ተገቢውን መስመር ለማስያዝና ለፍትሕ መቆም ሲ ገባቸው፤ ፀ ረ ኢትዮጵያ ከሆኑት ሻዕቢያ “ኤርትራዊያን” ጋር ግምባር ፈጥረው የጎሰኞች ፕሮፓጋንዳ ለማራገብ በጸረ አማራነታቸው ከታወቁት ከነኚህ ኤርትራኖች ከነ ዶ/ር ተክኤ ፍስሃጽዮን፤ጆርዳን ገ/ብረመድህን ጋር አጅ እና ጓንቲ ሆነው በታሪክ ላይ ጠባሳ ንድፍ ትተዋል።
አነኚህ እና የመሳሰሉ የትግራይ ምሁራንን ዛሬ ምን እየሰሩ እንደሆነ በግምባር ቀደም ከመውቀስና ከመተቸት ይልቅ “የፖለቲካ ተቃወሚዎች” የትግራይን ሕዝብ ወደ ወያኔ እየገፉት ነው ይለናል። አብርሃ ደስታ አንዲህ ይላል፤
“በዚህ መሰረት (የትግራይ ሕዝብ) ህወሓትን እየተቃወመም ቢሆንም የተቃዋሚ ድርጅቶች ግን ከህወሓት ሊብሱ ይችላሉ ብሎ እንዲያስብ ስለሚገደድ ግራ ተጋብቶ ‘የባሰ ኣታምጣ’ብሎ ኣብሮ ዝም ይላል።ለዝምታው ምክንያት አለው” ሲል በተቃዋሚው ላይ ትችቱን አሹሏል። ይገርማል።
ወጣት አብርሃ ደስታ የትግራይ ምሁራን ምን ያህል በቆሸሸው የወያኔ ፖለቲካ አንደተዘፈቁ እና የሕዝቡን እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት ሲደፈር አፋቸው ዘግተው አይተው እንዳላዩ ሲሆኑ፤ አብዛኛዎቹ ደግሞ “ወያኔ የሚያደርገው ጸረ ሉዓላዊ” አርምጃ “እሰየው” እያሉ የወንጀሉ ተባባሪዎች እየሆኑ አንደሆነ ብዙ ያወቀው አልመሰለኝም።
የትግራይ ህዝብ ከትግራይ ውጭ አሻግሮ በወሬ የሚያዳምጣቸው “የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን” የማይምን ከሆነ፤ ከጉያው ውስጥ ያሉት “ዓረና ትግራይ” የተባለው ድርጅትስ መነዋ ማመን አቃተው? እንምራህ ብለው ተነስተዋል፤ ብዙ ዓመት ሆኗቸዋል አመርቂ አንቅስቀሴ ሲያደርጉ አልታዩም። ባለፈው ሕዝባዊ ምርጫ፤ የምርጫው ውጤት ትግራይ ውስጥም አንደተጭበረበረና ተጽእኖ አንደተደረገላቸው የታወቀ ነው። ታዲያ “የትግራይን ሕዝብ እንደ ሌሎቹ “በጠላትነት” የማይፈርጁት፤ “ከወያኔ ጋር የማያደባልቁት” “መረገጡን” የሚያስተጋቡለት፤ የዓረና ተቃወሚዎች ከጉያው ትግራይ ውስጥ እያሉ ለምን ሆ ብሎ አነሱን ደግፎ “ተቃዉሞውን አላጧጧፈም?
ሰለዚህ የትግራይ ሕዝብ ሲጨቆን “ሌላው” በፍርሃት “ዝም” ስለሚል ነው፤ ወይንም ተቃወሚዎቹ “አንደጠላት” ስለሚፈርጁትት ነው፤ የሚለው አንካሳ ምክንያት አንደ ምክንያት ተቀባይነት የለውም፤፡ መጀመሪያ ነገር ወያኔ የሚያወራው ተቃዋሚዎች “የትግራይን ሕዝብ አንደጠላት ያዩታል” የሚለው የወያኔ ፕሮፓጋንዳ አብርሃ ደስታም ሆነ ሌሎቹ የትግራይ ተወላጆች ተቀብለው እያስተጋቡት ነው። የፖለቲካ ተቃዋሚዎች የትግራይ ሕዘብ በጣላትነት የፈረጀ አንድም (በኢትዮጵያ የሚያምኑ ተቃዋሚዎች) በመረጃ የሚያቀርብ ከአብርሃ ጀምሮ እስከ ሺዎቹ የሚቈጠሩ የትግራይ ምሁራን ማስረጃ አስደግፎ የሚያቀርብ እስካሁን ድረስ አላየሁም። መረጃው አለን የሚሉ ከሆነም ይሄው “ቻለንጁ” ግብዣው እና ሜዳው።
ተቃዋሚው በትግራይ ሕዝብ ተቃባይነት አንዳይኖራቸው ለማድረግ ወያኔ ዘርግቶት የነበረው እና አሁንም እየገፋበት ያለው የውሸት ፕሮፓጋንዳ እየተቀበሉ ማስተጋባት አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን የሚያስገምት ነው። የመለስ ዜናዊ “ኢንተርሃሙዌ” ፕሮፓጋንዳ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ተቀብለውት አንደነበረ የምናስታውሰው ነው፤፡ አሁንም አብርሃ እያለን ያለው፤-
“ስለዚህ ተቃዋሚዎች ከትግራይ ህዝብ ጋር መወያየትና መግባባት ያስፈልጋቸዋል። ምክንያቱም ሳያውቁት (በሚጠቀሙት የፖለቲካ ስትራተጂ) የትግራይን ህዝብ (targetየሚያደርጉ ስለሚመስሉ) በህወሓት ቢጨቆን እንኳ ህወሓትን ላለመቃወም እንዲወስን (የባሰ እንዳይመጣ) ያደርጉታል። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ዝምታ ምክንያት ኣለው (ህወሓት ስለሚደግፍ ግን ኣይደለም)።
ምንድ ነው ተቃዋሚዎቹ ሳያውቁት “በትግራይ ሕዘብ ላይ እያራመዱት የሚገኙት “የፖለቲካ ስትራተጂ”? የትግራይን ሕዝብ ‘ታርጌት’ ያደረገ በጣለትንት የፈረጀ የፓቲካ ስተራተጂ የቱ አንደሆነ ወይንም ማን ድርጅት እና ተቃዋሚ እንዲህ ያለ ስትራተጂ እየተከተለ አንደሆነ በመረጃ እስካልቀረበ ድረስ “ለትግራይ ሕዝብ ዝምታ ተቃዋሚው ለዝምታው “ምክንያት” ነው ብየ አልቀበለውም።አብርሃ የቤት ስራውን ከዚህ በተሻለ መስራት ይኖርበታል።
የሕዝቡ ዝምታ ወያኔን ላለመቃወም ምክንያት ብሎ አብርሃ ሲገልጽልን ‘አንድ ጊዜ ተቃዋሚው በሚያራምደው የፖለቲካ ስትራተጂ ነው “ዝምታ ሊመርጥ የቻለው” ይለናል፡ አንድ ጊዜ ደግሞ ከጭቆናው ላላመላቀቅ የመረጠው “ስለፈራ” ነው ይለናል። ‘ፍርሃት’ በተጠቀሰው አባባል፤ በማሕበራዊ ትንተና እንደ ምክንያት የሚያስኬድ ቢሆንም። 21 ዓመት ባነስተኛው “ከፍርሃቱ”በጥሶ መውጣት ካልቻለ፤ ሌላ ያልተመረመረ ምክንያት አለው። ያ ምክንያት ምንድ ነው? (እዚህ ላይ ዝምታው የትግራይ ሕዝብ ብቻ ተወቃሽ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ በደማቅ ላሰምርበት እሻለሁ። ምክንያቱም ዝምታው በሌሎቹም እየታየ ያለው አሳዛኝ ሲንድሮም ነውና)። ቢሆንም በትግራይ ላይ መተኰር ያለበት ልዩ ምክንያት ስላለ ፤ በዚህ እንቀጥል፤፡ ለትግራይ ሕዝብ ዝምታ መነሻው ምንድ ነው?
Selas Samson Biru, center, a farmer from Tigray, Ethiopia, compares crops with Sonia Kendrick, left, and Linda Barnes, right, both Iowa farmers and Oxfam |
የተቀረው ኢትዮጵያዊ ለምሳሌ አማራው ሕዝብ እና ኦሮሞ፤ጋምቤላ… አንዲሁም ሌሎቹ በደርግ እና በወያኔ ንጽጽር ምርጫ ቢገቡ ከወያኔ ደርግ እንደሚሻላቸው ይምርጣሉ። ኤርትራኖቹም አንደዚሁ (እራሳቸው በየቀ
ኑ የሚያቀርቡት የሕዝቡ ዘገባ መመልከት በቂ ነው)።፡ትግራይ ውስጥ ግን ምርጫው የነዚያ ተጻራሪ እንደሆነ አያጠራጥርም። አሁንም ቀደም ብየ ወደ ገለጽኩት “የባዕድ ጅብ ከሚበላን የኛው ጅብ ይብላን” ወደ ሚለው አብርሃ ቀደም ብሎ ወደ ተነተነው “ደርግ እና ወያኔ” ወደ ማወዳደሩ ስንገባ “የብሔረተኛነት” ስነ ልቦና እዚህ ላይ ትልቅ ሚና አንዳለው መዘንጋት የለብንም።
ሕዝቡ ለ38 ኣመት በትግራይ ብሔረተኛነት ተሰብኮ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ተቀብሎ እያራመደው አንዳለም አብርሃ ሊገልጽልን ያልቻለበት ምክንያት አልገባኝም። የትግራይ ሕዝብ ከሌለው በተሻለ መንገድ በወያኔ ስርዓት “ተጠቃሚ” መሆኑን ለብዙ ጊዜ ተከራክረንበታል። አብዛኛዎቹ የትግራይ ምሁራን ይህንን እውነታ ሊቀበሉት አልፈለጉም። ሁለት ምከንየቶች አሉዋቸው። አንደኞቹ “ ተጠቃሚ እየሆነ አንዳለ ቢገባንም” ለወደፊቱ በሌሎቹ አካባቢ ሕዝብ ቅሬታ ፈጥሮ ለአደጋ ሊጋለጥ ስለሚችል፤ ይህን ከማስተጋባት መቆጠብ አለብን” ብለው የተናገሩኝ የትግራይ ተወላጆች አሉ። ለዚህ መለስ ካሁን በፊት ጽፌአለሁ። አልደግመውም።
2ኛው/ሌላኛው ክፍል ደግሞ፡ ጭራሽኑ ከነበረበት ከደርግ ጊዜ ብሶበታል አንጂ አልተጠቀመም የሚሉ አሉ (የትግራይ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ይህንን ውሸት የሚያስተጋቡ፤ በተቃዋሚ ጐራ የቆሙ አሁን አስመራ ከተማ የሚኖር የግንቢት 7 ዋና ጸሐፊው አንዳርጋቸው ጽጌም ጭምር-በዴምህት (ዴሞክራሲያዊ ምንቅስቓስ ህዝቢ ትግራይ) አስመራ ውስጥ ቃለ መጠይቅ ተደርጐለት ያስተጋባው አድር ባይ ውሸትን ልብ ይለዋል)። አንዲህ ዓይነቱ የተዛባ ሙግት ማቅረብ ለምን እንደሚጠቅም ግራ ይገባኛል። የምናወራው “ሪል ፖለቲክ” ነው። አገርና ህዘብን የሚመለከት ትንተና እና ዘገባ ነው። ገና ከመነሻው የብሔረተኛ ቀዳሚ ምኞቱ እና እቅዱ ማወቅ ያስፈልጋል። ወያኔ ብሔረተኛ/ጎሰኛ ነው።ብሔረተኛ ደግሞ፤ መጀመሪያ “የራሱን ብሔር” ይብዛ ይነስ ከሌሎቹ ቅድሚያ መስጠት ነው ተቀዳሚ የቤት ስራው። ለዚህም ነው ወያኔዎችና የወያኔ ጀሌዎች (የወያኔ አባሎችም ያልሆኑ ጭምር) በመተባባር “ትግራይ ልማት መረዳጃ ማሕበር” /ልምዓት ዓዲ ብወዲ ዓዲ’ በሚል መርሆ ታቅፈው ፡በትግራይ ላይ ጉልበታቸው፤ገንዘባቸው፤አውቀታቸው በማስተባባር ለጎሳቸው ቅድሚያ በመስጠት፤ ወያኔ ባሰመረላቸው የጎሰኛነት መመሪያ መሰረት እየተመሩ “ትግራይን ወደ ላቀ ደረጃ አድረሰዋት” የሚገኙት።
ወያኔ ትግራይን በማልማት፤ ፋሲሊቴሺኑን በማዘጋጀት እና በተቻለ መጠን አንድ አገር አንደ አገር ሊያቆመው የሚችል መረታዊ ልማቶችን መዋቅሮችን በትግራይ ዘርግቷል።በዝርፍያ፤በገሃድ፤በሕጋዊ እና ሕገውጥ በሆኑ መንገዶች ሁሉ ለራሱ ዘርፎ ከሚተርፈው የዝርፊያ ሃብት ወደ ትግራይ በማፍሰስ ቀዳሚ የልማት ምሳሌ የሆነችበት ምክንያት ወጣት አብርሃ ሊነግረን አልፈለገም። ሕብረተሰቡ ብናምን ባናምንም የወያኔ ትግራይ ዳረጐት እያመሰገነ ከልቡ ተቀብሎታል። ከወያኔ ሌላ ለትግራይ ልማት እና እድገት የሚያስብ ስርዓት አይመጣም የሚል ድመዳሜም እንደሚያስቀምጥ ምንም አያከራክርም። ደግሞ ከወያኔ በላይ ማን ለትግራይ ቅድሚያ ይሰጣል? ስልጣን ላይ ያሉት የትግራይ ተወላጆች ናቸው፤በየውጭ አገሩ እየተላኩ ወታደራዊ እና ሲቪላዊ ስልጠና የሚለኩት ትግሬዎች ናቸው (ከቁጥር አንጻር ስትመለከቱ አብዛኛዎቹ ከትግራይ ናቸው)፤ አምባሲው፤ ስለላው፤ወታደሩ፤ ስልጣኑ፤ንግዱ…..በማን እጅ ነው ያለው? በትግሬዎች!
ወያኔዎች ትግሬዎች አይደሉም? ናቸው። ስንት ናቸው? በጣም ፤ እጅግ በጣም በሚሊዮኖች የሞቆጠሩ። አነኚህ የትግራይ ሕዝብ አካል አይደሉም? ናቸው። ጥቂት እየተባለ የሚነገረው ‘አሃዝ” የፖለቲካ አላዋቂነት ወይንም ሆን ተብሎ የተሸፈነ አባባል አንጂ “ተጠቃሚዎቹ” “ጥቂቶች” በሚያስብል ግምት ውስጥ አይደሉም። አንድ ሕዝብ በታሪክ ምዕራፎች ብንመለክት፤ በየትም ዓለም “ሁሉም” ሕዝብ “ተጠቃሚ” ማድረግ አይቻልም።ግን በዓይን የሚታይ የሚዳሰስ ጠቀሜታ እና ተጠቃሚ እስካለ ድረስ “ግምገማችን” መሰረት አድርገን “ተጠቃሚ ነው” ብለን መመጐት አንችላለን።
ለም መሬቶች እየመረጠ ከጎንደር እና ከወሎ ነጥቆ ለትግሬው እንካ ሲለው “እሺ” ብሎ እየተጠቀመበት ያለው ሕዝብ ማን ነው? አንዲህ ያለ ሥርዓት በጠምንጃ ጉልበት ከሌሎቹ ወንድሞቹ ሰፊ መሬት ነጥቆ ለትግራይ የሚሰጥ ሥርዓት ከቶ ለወደፊቱ ሊመጣ ይችላል? ጐሰኛ ስራው ምንድ ነው? ከመነሻው ማንንሰ ለመጥቀም እና ነፃ ለማውጣት ነው የተነሳው? አንደዚህ ዓይነቱ ጥቅማጥቅም በጉልበትም ሆነ በሕጋዊ መንገድ እየተጠቀመ ቅድሚያ ለራሱ ጎሳ ለማጐናጸፍ ነው። ይህንን ሰፊ መሬት እና የታመጸ አማራ ኗሪ ሕዝብ መብት ሳይጠብቅ ወደ “እራሱ ጐሳ” ወደ ትግራይ እንዲቀላቀል የተደረገው ማንን ለመጥቀም ነው? ትግራይን ለመንጠቅ ካልሆነ ማንንነ ነው? ሑሞራ ላይ ያለው እርሻ ማን ነው እየተጠቀመበት ያለው? ትግሬው ወይስ አማራው (የጎንደር ሕዝብ)?
እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። ትግሬው “የሚዳሰስ፤የሚጨበጥ፤የሚታይ” ጠቀሜታ እና ዕድገት በአከባቢውም ሆነ በግል ህይወቱ ከሌላው በተሻለ አግኝቷል። ለዚህም ነው “እንደ ወያኔ” ለኤርትራኖች ነፃነት እና “ለትግራይ ዕድገት” የሚቆረቆር ሥርዓት ከቶ ለወደፊቱ አይገኝም’ የሚል ሙጉት የምሞግተው። ሰለሆነም፤ የትግራይ ሕዝብ ይከፋም ፤ይደግም፤ እጁን አጣምሮ ዝመታ የመረጠበት ምክንያት ከፍርሃቱ ሌላ ያልተመረመረ ስዕል ከፊት ለፊቱ ያገደው ያለ አንደሆነ አብርሃ አሁንም ከሰጠን ትንተኛ ሌላ ወደ ውስጥ መቆፈር ይገባዋል እላለሁ። ሕዝቡን ወደ ጎን ትትን ወደ ምሁራኑ ክፍል ብናተኩር፤ ያ ያልተመረመረው ስዕል አሁንም በትግራይ ምሁራን ዝምታ ታጭቆ ያለው ብሔረተኛነት ነው የሚል አስተያየት አለኝ። የትግራይን ሕዝብ ጸረ ወያኔ ፊት ለፊት እንዳይነሳ ያገደው ጠባብ ብሄረተኛነት ነው።
ኤርትራኖች አሁን ያሉበት እና የትግራይ ምሁራን ያሉበት ስታወዳድሩ ፤ ኤርትራኖቹ አንዲያ በዘምባባና በአበባ የተቀበሉት፤ደማቸውና ገንዘባቸው ያፈሰሱበት “የሻዕቢያ” ድርጅት ገበና በብዙ መጽሐፍት እያሳተሙ በቃለ መጠይቅ በየራዲዮኑ እና በየፓልቶኩ እያገላጡ ሕዝቡ አንዲነሳበት እያደረጉት ይገኛሉ። የትግሬ ምሁራን እና ታጋዮች ግን ፤ ከቆራጦቹ ከነ አስገደ ገብረስላሴ ፤ገብረመድህን አርአያ፤ተስፋይ አጽብሃ/ቸንቶ፤ እና ጓደኞቹ እንዲሁም ጥቂቶች……በስተቀር የትግራይ ታጋዮች እና ምሁራን በብሔረተኛነት ገመድ ስለተበተቡ በጣም በሚያሰዝን ሁኔታ “ዝምታን” መርጠዋል። እነ አብርሃ ደስታ መመርመር ያለባቸው በተቃዋሚው ስትራቴጂ ላይ ምክንያት አድርጎ የተተነተነ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ከማተኮር ይልቅ በጠቀስኩት ላይ ትኩረታቸው ቢያደርጉ ለጠቃሚ ውይይት በር ይከፍታል።
TIGRAY TECH STUDENTS ON THEIR SCHOOL LOUNGE. |
በመጨረሻ ልለው የምፈልገው ነገር፤ የተማረው የትግራይ ምሁር፤ በራሱ ጠባብ ብሔረተኛነት ስሜት ምክንያት ተተብትቦ የወያኔ ተበባሪ ሆኖ የሕዝቡ መከራ “ጀሮ ዳባ’ ብሎ ከጨቋኙ የወያኔ ቡድን ጋር ከወገነ፤ ሕዝቡ እየደረሰበት ካለው መከራ ራሱን ነጻ ለማውጣት እያገደው ያለው“ፍርሃት” የሚባል አንቅፋት አንደምክንያት ከተወሰደ ፤ የትግራይ ሕዝብ ከራሱ በላይ የተሻለ ነፃ አውጪ ከየት አንዲመጣ ይጠብቃል? ደርግን ያክል የተደራጀ ታላቅ ሠራዊት መክቼ አሸንፋለሁ ብሎ በተግባርም ተቃውሞው አሳይቶ መምታት ከቻለ፤በወያኔ ላይ ሲደርስ ደርግን አንደመታው ወያኔን ላለመምታት ጉልበቱን ተብትቦ ያሰረው “ክር” ምንድነው? ፍርሃት ብቻውን እንደምክንያት በቂ ሊሆን አይችልም። የ21 ዓመት ተባባሪነትና ዝምታ በመካከላቸው የተዘረጋው ‘ገመድ’/ ‘እትብት’ መመርመር ይኖርበታል።
ብሐረተኞች የዘረጉት ፖለቲካ በቀላሉ የሚተነተን ሳይሆን በመስኩ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ለዚህ ተገቢውን መልስ አንደሚኖራቸው አምናለሁ።በትንተናው ላይም አንዲሳተፉበት እጋብዛለሁ። ይህ ጽሑፍ የአብርሃ ደስታ ጽሑፍ በተለጠፈው በኢትዮ ሚዲያ እንዲለጠፍ ተልኳል (ደምቡም መሆን ያለበት ያ ነበር) ሆኖም አዘጋጅ ፖለቲካን ወደ ግል ስሜት እየለወጠ እልህ ውስጥ ገብቶ የምናስተላልፋቸው የሕዝብ ጉዳዮች በድረገጹ ተለጥፈው አንዳይነበቡ ማገዱን ብዙዎቹ የተስማሙበት ችግር መሆኑን የታወቀ ቢሆንም፤ ይህ ጽሁፍ ልኬዋለሁ። ቢያወጣው መልካም፤ባያወጣውም ፤ለሬከርድ/ለትዝብት አንተወዋለን። ሆኖም ጽሑፉ ድንገት ታፍኖ እንዳይቀር ወደ ሌሎቹ ድረገጾች ለሕትምት ተልኳል) አመሰግናለሁ። ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ) www.ethiopiansemay.blogspot.com Email [email protected]