አንድን አገር የመከፋፈል አደጋ የሚገጥመው ስልጣንና መሳርያ የያዘው ክፍል በግድ የተሳሳተ አማራጩን ተፈፃሚ ስላደረገ ወይ በሚፈፅማቸው ደባና ስህተቶች እንዲሁ መገነጣጠል ፋላጎቱና አላማው ስለሆነ ብቻ አይደለም። ለለውጥ የሚታገሉ ክፍሎች ሲበዙና ልዩነታቸውን አቻችለው በቀጣይ ሀላፊነቱን በጋራ ለመቀበል ሳይዘጋጁና ችግሩን በአግባቡ ተረድተው መከላከያውን የሁሉን ቡድንና ዜጋ ፍላጎት በሚያስማማና በአንድ ሊያሰልፍ በሚችል ብለሀት ሰፊ የጋራ መፍትሄ ሊሰሩለት ሳይችሉ ሲቀሩ ነው። በእርግጥም ያገራችን የወደፊት እጣ ፋንታ በጥሩ ወይ በመጥፎ ፍፃሜ የሚያገኘው በወያኔ ብቻ አይደለም። በድብቅም ሆነ በግልፅ ዘረኛ አጀንዳቸውን የያዙ ጎልበት ሲያገኙ ወይ ስልጣን ላይ ከተፈናጠጡ አደጋው አይቀሬ ነው። ሁሉ በየዘሩ ተደራጅቶ ባለበት ያገራችን እውነታ ይሄ ወይም ያንኛው ክፍል አንድነቷ እንደተጠበቀ እንዲቀጥል የፀና ፍላጎታችን ነው ቢሉም በምንም ደረጃ የሚገለፅ ዘረኛና አግላይ አጀንዳ በጉያቸው እስከያዙ ችግሩን አጋግለው የመጨረሻ ውጤቱ ተመሳሳይ ወይም የሚፈራው ነው የሚሆነው። ዘረኛ ቢሆኑም ለህልውናችን ስጋት አይሆኑም የሚለው ፈሊጥ በኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ አይሰራም። ይህም ብቻ አይደለም ዘረኛ አጀንዳ ኖሮ አይደለም የሚመጣው ለውጥ ብዙና የተለያየ የሆነውን ሀሳብ፤ ፍላጎትና ስጋት የሚሸከምና አስማምቶ የሚሄድ ካልሆነም አደጋ አለው።
የኛን አገር ሁኔታ ልዩ የሚያደርገው ኢትዬጵያ የምትኖረው እኛ ስልጣን ላይ እስካለን ብቻ ነው የሚሉ ዘረኛ ውላጆች ናቸው ስልጣኑ ላይ ያሉት። ይህን አላማቸውን አልደበቁም። በጠራራ ፀሀይ ሁላችንም እንድናየው አድርገው እየሰሩበት ነው። በቀላሉ ተፈጻሚ ለማድረግ ያስፈልጋሉ ያሏቸውን ነገሮችን አመቻችተዋል። ላለመቀበል ካልወሰንን በቀር ይህንን ሁላችንም እናውቃለን። እንደውም ጠቅላላ ሁኔታዎች የሚያሳዩት ለውጥ መጥቶ ሳይጠራርጋቸው በፊት ይህን እኩይ አላማ ተፈፃሚ ለማድረግ ከጊዜ ጋር እየተሽቀዳደሙ እየሰሩበት እንዳሉ ነው። ለለውጥ የሚታገለው ክፍል እዚህ ያፈጠጠ ችግር ላይ ካለው ጠቅላላ ግንዛቤና የሰጠው ትኩረት ከችግሩ ክብደት አኳያ ባዶ ሊሰኝ የሚችል ነው። ይባስ ብሎ የበዛው ዜጋም ሆነ ፖለቲከኛ ዘርን መሰረት ባደረገ እኛና እነሱ በሚል መነሻ ነው ጠቅላላ አገራዊ እይታው የተቃኘው። ስለዚህም ችግሩ ላይ ያለው መረዳት ከተጨባጩ እውነታ በጣም የራቀ ነው። ያዋጣል ብለው እየሰራንበት ነው የሚሉትና የያዙት መፍትሄ የተሳሳተ መሆኑ ተደምሮ ገዥዎቻችን የወሰኑ ጊዜ በቀላሉ ይህን ተግባራዊ አድርገው እስታ ማለት የሚከብዳቸው አይደለም።
ይህ አፈራራሽ አገራዊ ችግር የተለያየ ፍላጎት ቢኖራቸውም በለውጥ ፈላጊዎች በሙሉ ድርሻ በሚያደርጉበት ሰላማዊ የጠረቤዛ ዙሪያ ውይይት ከሚመጣ ስምምነት መፍትሄ ሊሰራለት ይገባል። ይህን ማድረግ ይቻላልም። በተወሰኑ ቡድኖች ዘረኝነት፤ጥላቻና ጠባብ እይታ ተውጠን ወይ ተሸንፈን ነው እንጂ ኢትዬጵያዊነት ሰፊ ነው። የማይመልሰው የመብት ጥያቄ፤ የማያካትተው ሀሳብ፤ የማይሞላው ፍላጎትና የማይሸከመው ልዩነት የለም። አፈጣጠሩም ሆነ መሰረቱም ድሮም ቢሆን በልዩነት ላይ ነው። ብዙ በተሸከመ ቁጥር እየጠነከረ እንጂ እንዲዳከም ሆኖ ያለ አይደለም። ከንደዚህ አይነት ጥልቅ መረዳት የሚነሳ መፍትሄ ስራው መጀመር ያለበት ዛሬ ነው። ለነገ ስንተወውና አንድ ቀን ተኝተን ስንነሳ ብንን ብሎ ይጠፋል የሚመስለው በብዙ ፖለቲከኞችና ተቆርቋሪ ዜጎች የሚራመድ ሀሳብ ስህተትነትም አደጋም እንዳለው ለማሳየት የሚሰማ ጠፋ እንጂ በተደጋጋሚ ተሞክሯል።
ለጊዜው የሚያስከፍለውን ግዚያዊ ፖለቲካዊ ኪሳራ። ሊፈጠር የሚችለውና ጫጫታ ሳይፈሩ እዚህ አገራዊ ችግር ላይ በውይይትና በመቀራራብ የሚመጣ መፍትሄ አገራዊ ፋይዳው ግዙፍ ነው።ትግል ላይ እንዳለ አንድ ክፍል መሰዋትነት በቀነሰ በቶሎ አሸናፊ ለመሆንም የተባበረ ሀይልን የመጠቀም ወሳኝነት ትክክለኛ ፖለቲካዊ እርምጃ አድርገው ወስደውት የሞከሩት በእርግጥ አሉ። እነዚህ ክፍሎች ከዚህ አትለፉ የሚለውን ያደጋ ምልክት ያለበት ማስፈራራት ተላልፈው ለመቀራራብና ተባብሮ ለመታገል ሞክረዋል። ከዛም በላይ በውይይት ከሚመጣ መቀራረብ አንድነታችንን ባስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል የሚያስችል መነሻ የሚሆን አንድ አይነት ስምምነት ለመቋጠር ጥረት ያደርጋሉ።
ሁላችንም እንደምናውቀው ማበላሸትና እንቅፋት መሆን እንደመስራት ከባድ አይደለም። ትናንሿንም ሙከራ ከስር ከስር እየተከታታሉ አምርረው የሚቃወሙና በተቀናጀና በተባበረ መንገድ እንዳይሳካ የሚሰሩ ነበሩ። አሁንም አሉ። እነዚሁ ክፍሎች ናቸው ዛሬ ጎራ ለይተው እያየነው ያለነውን አደገኛ፤ ከፋፋይና አብሮነታችንን የሚገዳደር መዘረጣጥና እንኪያ ሰላንታ ውስጥ ያሉት። በጥቂቶች የተሞከረው ልዩነትን የማጥበብና የመተባበር ጥረት የራስ ዳሸንን ተራራ ያህል ገዝፎ ሲነገረን የነበረውን የልዩነት ግንብ ሰብሮ እታች ህዝብ ውስጥ ድረስ የሚታይ ትብብርን፤ አብሮነትንና ያንድነት መንፈስ ያጸና ነበር። በርግጥም ትክክለኛና ተስፋ ሰጪም ጅማሮ ነው።
በእርግጥ ይህ መፍትሄ ከዚህና ከዛ ወገን በተነሳ ተቃውሞ ቢደበዝዝም ዘረኛ ውላጆች ጉለበት ያገኙ በመሰላቸው ጊዜ ሁሉ የበለጠ ተፈላጊ፤ ፍጽም መፍትሄ ሆኖ ባብዛኛው ዜጋ ተቀባይ የሚሆን ነው። በርግጠኛነት ሞተ ሲሉ አፈር እየላሰ ይነሳል። ምክንያቱም ያገራችን ችግር ሌላ አቋራጭም መፍትሄም የለውም። በውይይትና በመቀራረብ የሚመጣና ፍቅር የሚገለጽበት መፍትሄ ላይ ስንደርስ ብቻ ነው ነፃነታችንን የምናቀርበው። አንድነታችን አስተማማኝ መሰረት ላይ የሚቀመጠው። ይህን ማድረግ ካልቻልን ወደፊት መራመድ አይደለም አስከዛሬ ከሄድንበት ወይ ዝንፍች። ሲተውላቸው እንዴት እንደሚያጨማልቁት እያየን ነው።
አፅኖት ሰቶ ለተከታተለው በጥቂቶች በመለስተኛ ደረጃ የተሞከረው ለወደፊቱም አገራዊ ችግሮቻችን ላይ አስተማማኝ መፍትሄ ለመስራት ትክክለኛውም የሚሰራው አንድና አንድ ይህው መንገድ ብቻ መሆኑን ያየንበት ነው። መልካምና ትክክለኛ የነበረውን ጅማሮ የምር ተደርጎ ግን አልተያዘም፤ ዛሬ ጎራ ለይተው ለመላተም ቀንዳቸውን ወደታች ቀስረው በጎሪጥ እየተያዩ መሬት የሚደበደቡ ክፍሎች የሚያሰሙት ጫጫታ ሲበዛ በፅናት አልተቀጠለበትም። በቂ ክትትልና ያብዛኞቻችንን ድጋፍና እርብርቦሽ ስላላገኘ ዛሬ ለምናየው አፍራሽና አሳፋሪ አገራዊ ክስተት ቦታውን ሰጥቷል። ፖለቲካችን ዘር ተለይቶ አንዱ ሌላው ላይ በሚያሳየው ጥላቻ ንቀትና ስድድብ ተሞልቷል። ወያኔን መታገል ተረስቶ የተጨቋኞች የርስ በርስ ልፊያ ትግል ሆኗል። በድጋሚ ለወደፊቱም ለነዚህ ክፍሎች የበላይነቱንና ተሰሚነትን እንዲያገኙ በፈቀድን ቁጥር የሚፈጠረው ዛሬ እየታዘብን ያለነው አፍራሽና አገዳዳይ ድርጊት እየጨመረ መሄድ ብቻ ነው። መዳረሻችንም የሚሆነው መከፋፈልና የዜጎች እርስ በርስ መጎዳዳት ነው።
ዘረኛ ውላጆች በድርጅታዊ ጥንካሬ ፤ በገንዘብ አቅም፤ ተከታዬችን በማብዛት፤በመገናኛው ዘርፍ። በሚያሳዝን ሁኔታ አንቱ የተባሉ ዜጎችን ምሁራንን አሰልፈዋል። ማሰለፍ ብቻ አይደለም እውቀታቸውን ሊዚህ አፍራሽ ሚና እየተጠቀሙበት ነው። በአጠቃላይ እነዚህ ቡድኖች ሁለንተናዊ የበላይነት የያዙበት ፖለቲካዊ አየር ነው አሁን ያለው። ይህንን አይነቱን የበላይነት ያገኙት ሁሌም እርምጃቸው ውስጥ ሁሉ ዘረኝነት ስላለበት ነው። የዘር አቁፋዳቸው ውስጥ ያልከተተውን ስለሚያስፈራሩና ስለሚያገሉትም ነው። ሁሌም ሁሉን ነገር ሀላፊነት በሌለበትና በማን አለብኝነት ስለሚሰሩ ነው። ውሸትን አብዝተው ይጠቀማሉ። የመጨረሻው ደረጃ ድረስ ወስደው ቆምንልህ የሚሉትን ዘር አባላት ሊበላህ ነው ጅቦ ይሉታል። ሽብር አብዝተው ይነዙበታል። የመልክታቸው ፍሬ ነገር ሲጨመቅ የዛ ዘር መኖር ለኛ መጥፊያችን ነው የሚመስለው። ሁሉንም አጋጣሚ ይጠቀማሉ። አፄ ሚኒሊክን መቃወም አማራን ማጥቃት ነው። አፄ ሚኒልክን ማወደስ ኦሮምን ለማጥቃት አድርገው ይጠቀሙበታል። ታሪክን፤ የጋራ የሆነውን ጭቆና፤ በውድድር ያሸነፈ እስፖርተኛ፤ ወይ አገዛዙን የተጋፈጠን ጀግና…. ሳይቀር ዘሩን አጣርተው ይጠቀማሉ። በተጨማሪ ወያኔዎችም ጉልበት ሰጥተዋቸዋል። ስልጣን ይዞ ለመቀጠል ሁሌም ሲጠቀሙበት የነበረና ለወደፊቱም በእጅጉኑ የሚያስፈልጋቸው ስለሆነ ይህን ማድረጋቸው ግን አይገርምም። ቤንዚን በማቅረብና ክብሪት በመስጠት እየተባበሯቸው ነው። ሀውልቶች እየገነቡላቸው ነው። ጥንካሬውን እያገኙት እና ሀይል እየተሰማቸው እንደሆነ ሁለቱም ጎራዎች አውቀዋል። ዘረኝነት፤ ንቀትና ብልግና ልጓማቸውን በጥሰው እየቧረቁ ነው። ወንጀሉና ብልግናው አድጎ እንደሁሌው ግለሰቦችና ድርጅቶች ወይም ቡድኖች ላይ ያለመና የሚያቆም አልሆነም።
ዳባ የሚል ስም ይዞ በዚህ ፖለቲካዊ አየር ይህን አይነት እውነት መናገር ምን ያህል ሚዛናዊ ተደርጎ ሊወሰድና ተቀባይ ሊሆን እንደሚችል ደጋግሜ እራሴን ጠይቄአለሁ። ለወትሮው ሀይ የሚሉ ሰዎችን ብጠብቅ ዝምታን ስለመረጡና ይባስ ተብሎ ጓሮ ጓሮውን ሲራመድ የነበሩ የከፉ ዘረኝነቶችና ጥላቻዎች ለለውጥ የቆሙ ወይም እኔንም ጨምሮ አብዛኛው ዜጋ የሚጠቀምባቸው መገናኛዎች ላይ ሽፋን እያገኘ ስለሆነ። ለዛውም ሚዛናዊ ባልሆነና በጥሬው መሆኑን ስለታዘብኩ ልፅፍበት ተገድጃለው። ዘር እየጠሩና እየለዩ ህዘብ ላይ የሚፈፀም አፍ መክፈትና ወንጀል በየቀኑ እየጨመረ ነው። እውነትነት ስላለውና ሚዛናዊ ለመሆን ግን ለወትሮው በጅምላ አማራው እንዲህ ነው ከሚለው ወንጀል ዛሬ ዛሬ ኦሮሞ ወይ ሙስሊሙ የሚለው እጅጉኑ አይሏል። ይህን ምስክርነቴን ለመቀበል የተቸገረ ነገር ግን ነገሮችን ሁሉ አጥርቶ በማወቅና በሚዛናዊነት የሚያይ አንባቢ እንደጥቆማ ወስዶት አስተርጓሚም እየተጠቀመ ቢሆን ከዛሬ ጀምሮ የራሱን ክትትል ማካሄድ ይችላል። ድምዳሜው እኔ ከገለጽኩትም በላይ የሚያስደምም ሊሆን ይችላል።
ታላቅ በሆነው ኢትዬጵያዊነት ስር ተሸጉጦ ለየትና ረቀቅ ባለ መንገድ የሚራመድ ዘረኝነት ለሌሎች ያለ ጥላቻ፤ ንቀትና ወንጀል እየደባበቅነው ነው እንጂ የቆየና ስር የሰደደ ችግር ነበር። ነውም። ዛሬ ለገባንበት ማጥ ውስጥም የከተተን ይህው ነው። ሀይላችንን አስተባባረን ዘረኛ አንባገነኖችን ከላያችን እናዳናራግፍ አላራምድ ብሎ በጭቆና ስራ እንድንኖር ካደረጉን ምክንያቶች አንድም ነው። ፖለቲካዊ ችግሮቻችን ላይ ከዘመኑ ጋር የሚስማማ፤ ከጠረቤዛ ዙሪያ ውይይት የሚወለድ ሰላማዊ መፍትሄ እስቀምጠን ተባብረን ነጻ እንዳንወጣና ወደ ብልፅግናው ጎዳና እንዳንገባ እንቅፋት ነው። ይህን አይነቱን ዘረኝነትና የነዚህን ዜጎች ወንጀል ዛሬ እነደከዚህ በፊቱ ለመሸፋፈንም ሆነ ለማስተባበል የማያቻልበት ደረጃ ደርሷል።
ኢትዬጵያዊነት ትልቅም ጠንካራም ነው። ለረጅም አመታት በግልጽ በየጎጡ ተደራጅተው ዘረኝነትና ልዩነት ላይ የሚሰሩ ብድኖችን ማዳከም መቋቋም ችሏል። ስልጣኑ ላይ ያለው አገዛዝ ዘረኝነትና አድሏዊነትን በከፋና ለማንኛችንም በሚሰማና በሚያም መንገድ ለረጅም አመታት በሚራመድበት እውነታ ውስጥም ። አሁን ጉልበት እያገኘና እያገጠጠ የመጣው በሽፋንና በመሸጎጥ በዛ ላይ ከኛ በላይ ላሳር ኢትዮጵያዊ በሚል ማጭበርበሪያ የሚካሄድ ዘረኝነት ግን ሊያስከትል የሚችለው አደጋ በቶሎ ካልተገታ በጭራሽ በጭራሽ ቀላል ሆኖ አልታየኝም። ለማንኛውም እስከሚቀጥለው ምርጫ የጥላቻና የዘር ፖለቲካ ናላችንን እንደሚያዞረን እንጠብቅ። ተቃዋሚዎች በሙሉ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለዚህ ተመቻችተው ነው ያሉት። ለነገሩ ጣት ይቀሳሰራሉ እንጂ ሁሉስ መቼ ፅዱ ናቸው። ለማንኛውም በሚያናድድ ሁኔታ ከሂደቲ ተጠቃሚ ሆኖ የሚወጣው እንደሁሌው አርቆ የሚያቅደውና መጠቀምን የሚችልበት ይሆናል።
ዳዊት ዳባ Sunday, March 23, 2014 [email protected]