ከሥርጉተ ሥላሴ ሲዊዘርላንድ ዙሪክ
እኔ ነኝ አቶ ሂደትን አፍንጫውን እንዲልስ የፈለኩት። ሃሳቤን የሚጋራ ትብብር ካለም ደስታውን አልችለውም። በ16.03.2014 ጀንበር ዘቅዘቅ ከመለቷ በፊት ዘሀበሻ ስገባ አንድ አዲስ መረጃ አገኘሁ። የአንድነትና የመኢአድ ቅድም ውህደት መሰናዶ።
https://zehabesha.info/archives/13623 ዘግዬት ብሎ ደግሞ ማምሻ ላይ ለሁለተኛው ቀን በደብተራ ክፍል አዲሱን ዜና አበሰሩ ለታዳሚው የአንድነቱ አቶ ሃብታሙ አያሌው። እንደ ድሮው ቢሆን እንዴት? ወዴት? ለምን? እያልኩ መንፈሴን አመሰው፤ አውከው ነበር። አሁን ግን አዳማጠኩ አቶ ሂደትን ማዬት ነው ፍሬውን። በቃ! ጅልነት ቀረ ወላለቀም። ነገም የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ከባዶ ሳጥን ቆጠራ በኋላ አቶ ሂደት ሌላ ትዕይነት ይዞ ከች ቢል አፍንጫህን ላስ በመጣህበት መንገድ ብዬ ቅንጡን አብርሬ ማሳፈር። ሞኙን ይፈልግ …. ይበቃል የተዳቀቅነው —-
ይልቅ አቶ ሀብታሙ በ16.03.2014 በነገሩን ሰበር ዜና ላይ የተፈለፈለ ቁምነገር አብሬ አዳመጥኩኝ። ኮረቻ ላይ ቁጢጥ ያለ „ኢጎ“ አላሰራም ካላ በመጣበት መንገድ ለመሸኘት መወሰኑን። ይህ ማለፊያ ነገር ነው። ግን ላይ ብቻ ነው „ኢጎ“ ያለውን አቶ ሀብታሙ? ታችም አለና ታቹም ላዩም በተገባው ይቃኝ ባይም ነኝ። እንዲውም መጋኛው ያለው ከታች ይመስለኛል። ለማንኛውም እኔ ጅልነትን ስለቀበርኩት አቶ ሂደት በፈለገው ቅርጽና ይዘት ሊያወናብድ ቢያነፈንፍ ቅስሙን እንኩት። የጀመረውን የማተራመስ ማሳ ለቀቅም አድርጌለት ከቻልኩ ማገዝ በሰተቀር ግን መፈሳፈስ፤ መፈራረጅን፤ አጋ ለይቶ በገጀሞ መከታከትን እሱ እንደሚጠብቀው ስለማውቅ አፍንጫህን ላስ ብዬዋለሁ። አሁን ተዋውቀናል። በዛች ቆልማማ አፍንጫው እሱ ከመሳቁ – ከመሳለቁ በፊት እኔ ቅድም …. ማን ሞኝ አለ።
ሌላው አቶ ሂደትን የምጠብቀው ቁም ነገር እንዳለ እስቲ ላስታውስህ። በዚህ ገጥመህ በሰፋኽው ማሳህ ብቃት ያላቸው ሴቶች ከገንዘብ ያዥነት ወይንም አቻዎቻቸውን ከሚመሩበት „የሴቶች ጉዳይ ክፍል“ ሸገር ያለ ወንዝ የሚያሻግር ላቅ ያለ ድርሻ እንዲያው ታምነው ይስጣቸው ይሆን?! ያው በአጭሩ ቢቀረጠፍም አንድነት የመጀመሪያው ፓርቲ ነው ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳን የሊቀመንበርነቱን ቦታ ሲሰጥ። ለዚህም ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ከአንድ ብሄራዊ ፓርቲ መሪዎች ዝርዝር ታሪክ ውስጥ አይኔ በክብር አለችና።
ከዛም በኋላ ምን ነበረ? ርዕዮትዬን ስጠብቅ ጭራሽ ተፈናቃይ አደረጋት አቶ ሂደት። አሁንስ ከቶ ምን እዬተመከረ ይሆን? …. እርግጥ እነ ወይንዬም ጠንከር ብለው ጎልተው እዬወጡ ነው። …. „በሴትነታችን ሳይሆን በብቃታችን“ በማለት …. ለማንኛውም ዘመነኛው ሂደት ይጠበቃል። መፍትሄውን እዬዘለለ ይህ ሂደት የሚባል ጉድ እኛንም አሞ ከሞ ያጫውተናል እንጂ የድሉ መናገሻ ፍሬ ነገር እኮ ይታወቃል። እነ ሚሚ እነ ቱቱ እነ እሙዬ እነ ሜላት ተናገሩ እኮ! ውይ! አንድ ነገር ረስቼ „ነገረ ሴቶችን“ የሚያዳምጥ ጆሮ የሚገዛበት ቦታ የምታውቁ አላችሁን? ከሰማችሁ እባካችሁ ….?! ለሚነግረኝ ትንሽ ሽልንግ ቢጤ በመቀነቴ ቆጣጥሬ እዬጠበኩ ነው ….
ሌላ ምን ነበር? ብቃትና አቅም አዬሁኝ ከ15.03.2014 ከአቶ ሃብታሙ አያሌው የደብተራ ሩም ቆይታ። ወያኔ አዘጋጅቶ በነበረው የሚዲያ ፓናል ዲስክሽንም ክርክም ያለች፤ ክሽን ያለች አንጀት አርስ ቦንብ ነበር ያጎረሱት ሽፋታውን ወያኔ፤ ወያኔ ከጫካ ወደ ከተማ ኑሮውን ሲያደላድል የ2ኛ ክፍል ተማሪ የነበሩት አቶ ሃብታሙ አያሌው። ለነገሩ አዲስ አበባም እኮ ለወያኔ ጫካው፤ መንፈሱ ጫካ፤ ህሊናው ጫካ …. ለአራዊትነት የተፈቀደ ግዛት ….. በጫካ ቲወሪ መደናበር —-
የአንድነት አዲስ መዋቅር፤ የመድረክ ምስረታ ሰሞናትም የአደራ ጠባቂው አቶ አንዶአለም አራጌ እንዲህ ከዓይን ያውጣህ የተባለ መንፈሰ ሊጋባ ነበር። የእኔ ስጋቴ እንዲህ ጎልብቶ የወጣ አቅምን ማዬት የሚፈልጉ፤ ማድመጥ የሚሹ፣ እንደ ብርቅ የሚያዩ፣ ይህን ሃብት ጥቅም ላይ ለማዬት የሚጓጉ የመኖራቸውን ያህል ተመሳስለው ያሉ የግል ኢጎ ቁስለኞች ደግሞ ከአረሙ ጋር በማበር ሌላ የጨለመ ትዕይነት እንዳይመጣ እንቅልፍ አለባው ሥርጉተ ትሰጋለች። ይፈቀዳል አይደል መስጋት …. ? ? ?
እኔ እነዚህ የትውልድ አዲስ ተረካቢ ወጣቶቹ ጥንካሬ ፈጽሞ የማይጠበቅ እዬሆነበኝ ነው። ግንዛቤያቸው፣ ዕያታቸው ከምኑ ነው የዛቁት? ይገርማል – ይገራል። ከመራራው የዕንባ ጅረት ሳይሆን አንደማይቀር ሰማይ ቤት ላይ ያለው የክሮስፖንዳንስ ሠረተኛ ጠቁሞኝ ነበር አንድ ቀን እንደ ዋዛ። …. ታዲያ እኛ ይህን የሚያሰተናግድ ንጡህ መንፈስ አለን ነው ጥያቄው … ከዚህው ከአቶ ሃብታሙ ማህደር ሳልወጣ ትንሽ ቆዬት ባለቸው የቃሌ ክፍል ቃለ ምልልሳቸው „መንገዱ ተጀመረ“ ልጃቸውን የትዳር ጥንዶቹ በጉራጌኛ የጠሩበት ስያሜ ነው። የኢትዮጵያን ቀለማም ማንነት እንዲህ ፈቅደው ያስጌጡ ናቸውና ተዚህ ላይ አቶ ሂደትን ቸር ወሬ ስላሰማኝ ለጥ ብዬ አመሰገንኩት። ውሳኔው ያስተምራል – ይመራል። የአዲሱን ትውልድ መንፈስም አሳምሮ ያሳያል …. ሌሎቻችንም ይልመድብን። እኔ ትርጉም የሚሰጡኝን ነገሮች በአግባቡ ነው አክብሬ የምይዛቸው። ጠብ ብላ የምትፈስ ጠበል የለችም። ሥጋና ምን ተባለዬ ቤት አይደለሁም ….
ገጥሞ መስፋት ያልኩት በአሉታዊ እንዳይታይብኝ። አዎንታዊ ነው። አኔ እራሴ ተገጥሜ ተሰፍቼ ነው በህይወት ቁሜ እንደ ጥንቱ ከሞት ተርፌ ሰው ሆኜ ቆሜ ያለሁት። የእውነት እምተርፍበት ሁኔታ በጣም ስስ ነበር። ግን ፈጣሪ ይመስገን ተገጥሜ ከተሰፋሁ በኋላ ሶስት ዓመት ተጨመረልኝ። በኋላም ይመጣሉ ተብለው የተሰጉት ነገሮችም በሃኪሞቼ እንደተተነበዩት አይደለም በጣም በእጅጉ የቀነሰ ነው።
ሌላ አንድ ነገር የቀረ ደግሞ አለኝ። አቶ ሂደት አለህ? ሆሆ ትሰማኛለህ? ከልብህ እባክህ አዳምጠኝ – ቢተ? (bitte? እባክህ?)? ገጥመህ ስትሰፋ ደስ ብሎህ ፍንክንክ ፍልቅልቅ ብለህ ተቀበሉኝ እንደምትለን ሁሉ „ተገጥሜ ለመሰፋት ጊዜዬ ገና ነው“ ላላው ልጅህ ደግሞ ነፃነቱን ፈቃዱን ጠብቅለት። ከነፃነቱ ጋር እዬሄድክ አትላተም። „ጊዜ ገቢረ ለእግዚአብሄር“ ይላል ወንጌሉ። እሱን መለስ በልና ገልበጥ አድርገህ ከቃሉ ጋር ጥድፊያህን አሰማማው። „ሲሮጡ የላኩህም“ አትሁን። አደብ የትውልዱ መንፈስ ነው፤ ለነገሩ ይሄ ሚስጥር ጠጠር ብሎብሃል አይደል?። ከሌለህ ደግሞ ቅዱስ ወንጌል ያለውን ይሄው እኔው እህትህ አስታወስኩህ። ካለጊዜው የተፈጸመ ድርጊት ታምራዊ አንድ ነገር ብቻ ነበር። የቃና ዘገሊላ የድንግል ማርያምና የልጇ ፍቅራዊ ሂደት። „መጠበቀን“ የመሰለ ነገር የለም። መጠበቅ ለእኔ የዲያመንድ ጮራ ነው።
ለነገሩ አንተ መስማማትን አትወድም። በምን አቅልህ? እንደ ሽፍታው ወያኔ እኮ አቅልህ የተዘቀዘቀ ሸውሻዋ ነህ። ደግሞ ታስፈራራለህ ወዮ! እያልክ አትስማሙ እያልክ፤ በእንትን በቅብጥርስ እያልክ ስታምሰን ከረምክ። አሁን ተነቃብህ። አፍንጫህን ላስ ተበላክ …. ጉድህ ፈላ …..። እዬተወላገዱ ሙድ ማሳት ተመነጠረ። አዬህ አቶ ሂደት …. መንፈስ ሲሰበሰብ አቅም ወግ ይደርሰዋል።
ብቻ አደራ እንደዚህ ለግለግ እያሉ የሚወጡትን ቀንበጦቼን ወደ ቃሊቲ …. እንዳታስባቸው እንጂ፣ እኛም ልክ እንደ ጀግናው አበበ ቢቂላ ቀደመንህ ልብ ገዛን። ከአንተ ጋር አብረን ወገኖቻችን በሰባራ ሰንጣራው መውቃት፤ መድቃት፤ ማብጠልጠል ቅርት፤ ምን ይውጥህ? ትላንትን አሳዬህን፤ ዛሬንም ሻምላ ጋሬጣ አዘጋጅተህ በሉ ልያችሁ የማን ደም ፈሰሰ ቀረ። „አሞራው በረረ ቅሉ ተሰበረ“ ሆነልህ – ትልምህ። እኛ ምናችን ሞኝ?! እቴ! ሞኝህን ፈልግ ብለን … በተደሞ ማዬትን መረጥን። ስንችል ደግሞ የምንችለውን ማጉረስ። ምን ይውጥህ?! ….. አንተ ምንትሶ – ቅብጥርሶ፤ ደልቅ ከዘመንኛው ጥጋበኛ ወያኔ ጋር … አንድ ቀን አንተም እንዲህ እዩዩኝ ስትል እንክት ትልና …. እንደ ጦር የምትፈራው „ገናናው ኢትዮጵያዊነት“ በአኃቲ ማዕዶት … በሽንጣም ሞሰብ ቅብጥን ቅልጥ በማለት በናፍቆት ማር የምታዘንበው ሀገራችን ላይ … ተግባባን ጌታው አቶ ሂደት። ለነገሩ ሰንደቅአላማን ገንባሌ አድርጎ ቀን ሳይታደል ካለአለአቅሙ፣ ካለወርዱም የተኮፈሰው ውሽልሽል የጎጥ ቅራቅንቦ „ኢትዮጵያዊነት“ ከእኔ ወዲያ ላሳር እያለ ነው አሉ …. አያልቅበት ቀዳዳ ዲሪቶ መጣፍ። ሰው ይተዘበኛል አይል? አይኑን በጥሬጨው ያሸ ጉድ …. „መሳቂያው ፓርላማ“ አለ አቤ ቶኪቻው። በል ከመሰናበቴ በፊት ተጠይቅ አስሰኪ አንድ ጥያቄ ከቶ መቼ ነው ከዚህ ኪስ አውላቂ የድቡሽት ቤት ጎጠኛ ሽፍታ ጋር የምትፋታው? የናፈቀኝ አሱ ነው …. ህልም አይከለከል ነገር ..
የእኔዎቹ እንዴት ናችሁልኝ። አብረን በመቆዬታችን ደስ ሲለኝ ስንበቱን ሳስብ ደግሞ ክፍት አለኝ። ባር ባር እያለኝ ናፍቆቴን በፍቅር ጥበብ አሳምሬ ቸር እንድተሰነብቱልኝ ተመኝቼ ልሰናበት። መልካም ጊዜ። ማይክ ፍሪ ….
እልፍ ነንና እልፍነታችን በተግባር እልፍ እናድርገው።
እግዚአበሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ ሥላሴ።