አሜሪካ የበለጠ ትናገር! (ከጸጋዬ ገብረመድህን አርአያ)

“ ነፃነቴን ካልሰጣችሁኝ ሞትን እመርጣለሁ”
ፓትሪክ ሔንሪ Give me Liberty or Give me Death

ፍሬደሪክ ዳግላስ (1818- 1895) ከባርያ እናትና ከነጭ አባት የተወለደና ራሱም ቢሆን በቦልቲሞር (ሜሪላንድ) የቤት አሽከር ሆኖ የቆየ ሰው ነበር። አንድ ማለዳ ጁላይ 4 ቀን 1852 ን ተንተርሶ (አንተርሶ) በሮቼስተር ከተማ (ኒውዮርክ) ንግግር እንዲያደርግ ጥሪ ይደርሰዋል። ደብዳቤው ሲደርሰው እንደ እብድ ከራሱ ጋር መነጋገር ያዘ። መቸም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ለማመን የሚከብድ አጋጣሚ ሲመጣብህ ናላህ ይበጠበጣል። ፍሬደሪክ ዳግላስም “በእርግጥ ይህ ደብዳቤ ለእኔ የተጻፈ ነው? የተቀባይ ስምና አድራሻ ስሕተት ተፈጽሞ ይሆን?” ሳይል አልቀረም። ዳግላስ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ጭንቅላቱን ሲበጠብጥ ቆይቶ ትንሽ አረፍ አለ። ሲነቃ ይኸ ዕድል እንዳያመልጠው ፈለገ። ይልቁንም የሚናገርበት ርዕስ መጣለት። “ በመሰረቱ እኔን ባርያውን በዚህ በዓል ላይ እንድገኝ- ለዚያውም ተናጋሪ መሆኔን ሳስበው ይህ ሁሉ ግብዝ- የግብዝም ግብዝ ነው አለ። ይበልጥ ደግሞ ለተሰብሳቢው ስለጁላይ 4 (ነፃነት በዓል) እንድናገር እኔን ባርያውን መጋበዛቸው ሌላው ግብዝና ነው ” አለ። ለማንኛውም ንግግሩን አዘጋጀ። በዚያ ወቅት በሮቼስተር ከተማ ያደረገው ንግግር እስከ ዛሬ ድረስ ከዓለም ታላላቅ ዲስኩሮች አንዱ ለመሆን በቅቶአል። “ጁላይ 4 ቀን ለመሆኑ ለባርያው ምኑነው? What to the Slave is the Fourth of July?

ዛሬ ከብረት በከበደ ክንድ ኢትዮጵያን እየገዙአት የሚገኙት ጌቶች- አዳዲስ መሳፍንት- አዳዲስ መኳንንት፣ አዳዲስ ዲታዎች…የንግስ በዓል ከሳምንታት በኋላ ይከበራል። (በዩጐዝላቩ ጂላስ The New Class, ወይም ከሮማውያን ዘመን አንስቶ Nouveau Riche ቀላል ድግስ አያውቁም። ስለዚህ ጉንበት 20 ቀን በታላቅና ታይቶ በማያውቅ ድምቀት ይከበር ዘንድ ዝግጅቱ እየተሟሟቀ ነው። አገር ያፈራው ትልልቁ የሐረር ሰንጋ፣ ወደል ወደል የሚያክለው የወለጋ ላታም በግ ወዘተ ተመርጦ ተመርጦ ይቀርባል። ሻምፓኙ፣ ውድ ውዱ አይሪሽ መጠጥ- ዊስኪ፣ ድራንቡዬ፣…የፈረንሳይ ኮኛኮች፣ ምርጥ ወይን ጠጆች..ያልፍላቸዋል። ምንም ማጋነን የለበትም። ጫካ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ እንኳ ለድግስ ስንትናስንት ሚሊዮን ብር ሲያወጡ እንደነበረ ከጉያቸው የወጣው ጠንካራ ኢትዮጵያዊ…ገብረ መድኅን አርአያ ገልጦታል።
“ኑና ጉንበት 20ን አብረን እናክብር” ተብለው የተጠሩ ወይም እንጠራለን ብለው ቀኑን እንደወላድ እየቆጠሩ- የራቀባቸው ሰዎች የሉም አትሉም። እናንተም እንደኔ። ከውጭ የሚጋበዙ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። አዳራሾች-ሆቴሎች- በየደረጃው… ላይበቁ ነው። እሸሸ ገዳሜው፣ አስረሽ ምቺው ደግሞ የሚጠበቅ ነው። ስለገዢዎቻችን ሀብትና ንብረት ያልተባለ ነገር የለም። ይኸ ደግሞ የሞራሉን ቁልቁለት ምንኛ እንደ ተያያዙት ስም እየጠቀሰ መረጃ የሚሰጠንን ውስጥ አወቅ ኢየሩሳሌም አርአያን ማድነቅ እወድዳለሁ። በሽምግልናና ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ በሚገባቸው ዕድሜ የእኝኝ ብላ ባዝራዎች፣ አንድና ሁለት (በቀን) የማይበቃቸው የወንድ መለኮኖች አሉባቸው። ከዚህ ተራ ውስጥ ሁለት ሰዎችን ብቻ (በረከተ-መርገም ስምዖንና ስዬ አብርሃ) ነፃ ያወጣቸው ደግሞ ተስፋዬ ገብረ-አብ ነው። ስለሆነም ዳንኪራውና ስድ የሆነው በዓል የሚጠበቅ ነው። እኛም የኢትዮጵያ ጉስቁሎች የሌላ ሕዝብ በዓል በሥነ ሥርዓት መጠበቅ አለብን። የበዓሉን መንፈስ ማደፍረስ፣ ማደናቀፍና ማቃወስ በአሸባሪነትና በመሳሰለው አንቀጽ ያስቀጣል። አዎን ጉንበት 20 ቀን የድግሦች ድግሥ፣ አውራ በዓልና የድግሦችና የበዓሎች ሁሉ እናት ናት። ማን ያውቃል? ድሮ ጃንሆይ አጤ ኀይለ ሥላሴ ሐምሌ 16ን “የትዮጵያ የልደት ቀን” እንዳሉአት እነዚህ አዳዳሶቹ መሳፍንትም ጉንበት 20ን “እውነተኛው የኢትዮጵያ ናጽናት ቀን” ቢሉት አይደንቀኝም። ( ብቻ ማን ነበር- የአንዱ ሕይወት የሌላው መርዞ ነው- ያለው?)
በአገራችን የድግስ ነገር ሲነሳ ትንሽ የማስታውሳቸው ነገሮች አሉ። በአጤው ጊዜ ጃንሆይ የተወለዱበት (ሐምሌ16) እንዲሁም የነገሱበት (ጥቅምት 23) ይከበሩ ነበር። ለኢትዮጵያ ባሕልና ፖለቲካ እንግዶች የሆናችሁ ወጣቶች ምናልባት አታውቁት ይሆናል እንጂ በክብርም ቢሆን ቤተ መንግስት ስትጠሩ ግርግሩ ብዙ ስለሆነ ትንሽ ጨፈቃ ትቀምሳላችሁ። እንጀራው በእግር የተቦካ ነው ይባላል። ለማንኛውም “የንጉስ በረከት” አይናቅም ትባላላችሁ። (ይህንን የበለጠ ለማወቅ ፍቅር እስከ መቃብርን ያነብቡአል) ወደኋላ ጊዜ የሐምሌ 16 በዓል አከባበር ለአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ተሰጥቶ ነበር።
የድግስ ነገር- በመንግስት ሰፈር- ብዙ ምልኪ አለበት። ስለ ጃንሆይ መንግስት አወዳደቅ ብዙ ቢባልም ለጊዜው አንዱን አነሳለሁ። አንዳንድ ሚኒስትሮች እጅግ ከቅብጠትም ባሻገር ስለሄዱ ክራር ይዘው ወደ መሸታ ቤት መሄድ አብዝተው ነበር። የዛሬዎቹ ከእነዚያ ጋር ባይወዳደሩም ትንሽ ትንሽ ሕዝብንና አኗኗሩን ወደ መርሳቱ ደርሰው ነበርና ሌላው ቀርቶ ከመሳፍንቱ አንዱ የነበሩት ጄኔራል ዐቢይ- “አውቀን እንታረም” የሚል መጽሐፍ ደርሰው ነበር። ጠንቃቃው ጄኔራል “አውቀን ካልታረምን ሌላው ቀርቶ ሬሳችን እንኳ የወደቀበት አይታወቅም” ብለው ነበር። አዎን አርማጌዶን በዓለም ፍጻሜ ላይ የሚከሰት ሳይሆን ያልታሰበ የእልቂት መውረድም አርማጌዶን ሊባል ይችላል። ያ ወቅት የሞራል ድቀት ሥጋና ደም ገዝቶ የሚታይበት፣ ሕዝብ ሲያልቅ አንዳንድ ሹማምንት መንደላቀቅ ያበዙበት ነበር። ደርግ ጃንሆይን ከሥልጣን ሲያወርድ “ሕዝብ በሺህ ቤት ሲረግፍ እነሱ በእሸሸ ገዳሜ ተጠምደው…” እያለና የቀለጠ ድግስ በቴሌቪዥን እያቀረበ ነበር። ድግስ….
ደርግ ራስዋ በራስዋ ያመጣችው ጣጣም አለ። ወደ ሥልጣን የመጣበትን ቀን ለማክበር ብልጭልጩንም ማናምኑንም ሰልፉንም…ሲያበዛ የእንግሊዝ ጋዜጠኞች በሁለት መቶ ሺህ ዶላር ውስኪ ሸጥን አሉና…የደርግ መሰላል ወደታች ብቻ የሚያወርድ ሆነ። ድግስ እየተኮነነ መጣ። ድግስ እየተጠቀሰበት ወረደ። ሁለት መቶ ሺህ ሕዝብ በረሃብ አለቀ ብሎ ተሳለቀ ተባለ። በራሱ ጊዜ ዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብ ተርቦ ውስኪ ተራጩ ተብሎ ለወያኔ ፕሮፖጋንዳ ተመቸ። እዚህ ላይ ያነሳሁት የጉንበት 20 አከባበር ያንኑ እድል ይከተል ይሆናል- ይከተላልም- ቁልቁለቱን ጀምሮአል በሚል ነው። ድግሶች በሦስቱ መንግስታት- የሥልጣን መልቀቂያ ጊዜ ምልክቶች- ብልሽትሽቱ የወጣ መንግስት ማክተሚያ ወቅቶች ሆነው አይተናቸዋል። ( ሁሉም የእጁን ያገኛል- ብድሩን ወይም ብድራቱን ተከፈለ- በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም የሚባል አነጋገር ያለ ይመስለኛል። የእንግሊዝኛው ፈሊጥ ግን Poetic Justice ይለዋል) “ያርግላቸው!” አሜን ያድርግላቸው!!
ደርግ የተወነጀለበት 200ሺህ ዶላር ዛሬ አንድ ባለ ጊዜ ወያኔ ለልጁ ልደት ከሚደግሰው በታች ነው። በ1997ዓ.ም አባዱላ ገመዳ ለልጃቸው ዘኪያስ አባዱላ 24ኛ ልደት በዓል የ100ሺህ ዶላር ኮብራ ዘመናዊ መኪና በስጦታ መልክ አበርክተዋል። በ1994ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 14ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጦ ነበር። መለስ ዜናዊ ከ10 ዓመት በኋላ “በቀን ሶስት ጊዜ ትበላላችሁ” ባሉበት ዓመት መሆኑ ነው። የመለስ ዜናዊ መንግሥት ለተራቡት ወገኖች ደንታ አልነበራቸውም። በድርጅታቸው የተፈጠረው ቀውስ ላይ በማተኮርና ለእርሳቸው የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ሲሉ “ተሃድሶ” ብለው ለሰየሙት ቱማታ 280ሚሊዮን ብር ባጀት መድበው ካድሬዎቻቸውንና ተከታዮቻቸውን በድግስና በውስኪ ያምነሸንሹ ነበር። በዛው ዓመት ልጃቸው ሠማሃል መለስ የልደት በዓልዋን በግዮን ሆቴል ዳስ ተጥሎ አክብራለች። ለኬክ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ብር ነበር ወጪ የተደረገው። የመለስ ልጅ ልደትዋን በምታከብር እለት በግዮን ሆቴል ደጃፍ በርካታ በረሃብ የገረጡ ወገኖች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ወድቀው ነበር።
ስለ ድግስ ዝርዝር ለመጻፍ ፍላጐቱ የለኝም። ደግሼም አላውቅም። መንግስት ሲቀናጣ፣ እሸሸ ገዳሜው ልክ ሲያጣ፣ የሞራል ድጡ መጠነ ቢስ ሲሆን፣ ሰብአትካትን- ሰዶምና ገሞራን ወይም የጥፋት ውሃን ዘመን ሊያመለክተን ይችላል። ራስ ተፈሪዎች “ባቢሎን” ይሉታል። እንዲያውም በቀድሞው መንግስት በጠቅላይ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ሥዩም ሐረጐት The Bureaucratic Empire, Serving Emperor Haile Selassie በሚለው መጽሐፋቸው ያነሱት አንድ ነጥብ ስለድግስና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች ነበር። ኮረኮረኝ። ሥዩም ሐረጐት እንደጻፉት የቀ.ኀ.ሥላሴ ባለስልጣኖች የታሰሩት ጠጅ ለመጣል ምቹ ቅዝቃዜ በነበረው ሥፍራ ነበር። ከላይ የደርግ አባላት ስብሰባ ሲካሄድ፤ ሑካታ ሲፈጠር፣ ጭብጨባ ሲበዛ ወዘተ በእሥረኞቹ ላይ ይፈጠር የነበረውን የመንፈስ ጭንቀት ይነግሩናል። አሳሪዎች የእሥረኞች ሥቃይ ሊታያቸው ከቻለ በእርግጥ “ሰው” የመባል ሙሉ ባሕርይ አላቸው ለማለት ይቻላል። (የደርጉን ዘመን ግፍ ለማውራት የምደፍርበት ወኔ የለኝም። ራሳቸውን እየቀደሱ በሌሎች ግለሰቦች ላይ ከሚደነፋፉም ጋር ጠበል የምጠጣ አይደለሁም። አንድ ነገር ላይ ከተስማማችሁልኝ ደርግ በውሃ አጥምቆ ቢሆን ወያኔ ይኸውና በእሳት እያጠመቀ ይገኛል። የጥምቀቱ ተቀባይ ደግሞ መላው ወገኔ ነው።)
የአሜሪካ መንግሥት ባለፉት ቀናት የኢትዮጵያን ድንኳን ገለጥለጥ አድርጐ የአገሪቱን የሰብአዊ መብት አጠባበቅ፣ የፖለቲካ እሥረኞች አያያዝ፣ በገጠር ያለውን ብሔረሰቦችን የመከፋፈል መንግስታዊ ጫናና ወንጀል አሳውቆናል። አሳውቆልናልም። በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ሰማንያ ሺህ የፖለቲካ እሥረኞች አሉ። ከእነዚህም መካከል ስድሳ ከመቶው አእምሮ እስከ መሳት መድረሳቸውን በምስክርነት አቅርቦልናል። ዝርዝሩ ብዙ ነው። ታላቅ ወንድም (የተጠጋኸው ትልቅ መንግሥት በፖለቲካው ቋንቋ ቢግ ብራዘር ይባላልና) ምናልባትም የእሥረኛውን ቁጥር ቀንሶት ይሆናል እንጂ በኢትዮጵያ እየኖረ ወያኔንና ትውልደ ወያኔ ያልሆነ ለመሆኑ ያልታሰረ – አለዚያም እሥራት የማያስጨንቀው ማነው? ብለው የሚጠይቁ የትየለሌ ናቸው። ያልታሰሩ የሚመስላቸው ሰዎች ደግሞ የጥርስ ችግር እያለው ሕመም ሳይሰማው በመጨረሻ ላይ አምስትና ስድስት ጥርሶቹ ሲረግፉለት ለቃቅሞ ወደ ሐኪም ቤት እንደሚሮጥ ሰው ናቸው።
እንደሁም ልጆቻቸው ወይም የአገር ወጣቶች በነቂስ እየታረዱ ኅዘኑ ከቤታቸው የማይገባ፣ የቤተሰብ አውራ በባለቤቱ ፊት ታስሮ ሚስት ስትነወር፣ ንብረቱ ሲድፋፋ፣ ጐታው ሲደፋ ልቅሶውና ዋይታው ከጆሮአቸው የማይደርስ ጐረቤት ወገናችን አለ። የድንጋይ ልብ የገባለት። አንዳንድ የማውቃቸው ሰዎች – ጐይትኦም ብቻ ሳይሆን- ደባልቄና አምበርብርም ጭምር – ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ሲመለሱ ተመሣሣይ ትዝታ ይዘው ይመጡላቸዋል። አዲስ አበባ ውስጥ የሚሠራው የእድገት ምልክት የሚገለጥ አይደለም። የአለቃ ደስታና የተሰማ ግጽው መዝገበ ቃላት በቂ ቃላት የላቸውም። “እንዲያውም በእንግሊዙ ንገረኝ” ትለዋለህ። አንተም አሿፊ እሱም አሹዋፊ ትባላላችሁ። ጓድ መንግሥቱ ኅይለማርያምን ብጠቅስ እንደማትቀየሙኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በኢትዮጵያ ራዲዮ በሠራሁባቸው ዓመታት አንድ ቀን ስለ ራዲዮ አሠራር ስንገልጽላቸው ምርር ትክን ብለው “ ዘፈኑና ጭፈራው አልበዛም ወይ? ለመሆኑ ወገኖቻችን በጠላቶቻችን ሰይፍ እየተመቱ፣ አብዮታዊ ሠራዊታችን በግራም በቀኝም – በሰሜንም በምሥራቅም፣ በመሐል አገር ደግሞ በአምስተኛ ረድፈኞች ጓዶቻችን ሁሉ እተየረሸኑ..እያለቅን አይደለም ወይ? ኢትዮጵያ ራስዋ እንደ አንድ ልቅሶ ቤት መታየት የለባትም ወይ? እንዴት ነው በዚህ ሁሉ ልቅሶኛ ላይ እሸሸ ገዳሜ ዘፈን ለማሰማት ፈቃድ የምትፈልጉት? ፈቃድ የሚጠየቅበት አይደለም። እንደየስሜታችሁ ነው። ደስ ካላችሁ ዝፈኑ። አስዘፍኑ። አለዚያም ዳኝነቱ የእናንተ ነው” ብለው ነበር። አንዱ ሲደሰት ሌላው ያዝናል። ዓለም ጉራማይሌ!
ሕይወት ከዚህ መሠረታዊ አመለካከት ይጀምራል። ግን ከአለቃችን ንግግር ውስጥ ማንንም ሊነካ የሚገባው ለአገራቸው ባበረከቱት ቅንና ሕጋዊ አገልግሎት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ወደ ወህኒ ዓለም የተወረወሩትን ሰማንያ ሺህ ኢትዮጵያውያን በዓይነ ሕሊናችሁ ጐብኙልን። አሜሪካ የምትነግረን- የማናውቅወን አይመስለኝም። ራስዋን በምስክርነት አቅርባለች። ከተጠቀምንበት። ወይም ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ አንድ ሰሞን ይሉ እንደነበረው “በደርግ ጊዜ አሜሪካ በክምር ሳር ውስጥ የወደቀች መርፌ ይታያት ነበር። አሁን ግን በእልፍኝ ውስጥ የቆመው ዝሆን እንዳይታያቸው አንድ ዓይነት ግርዶሽ (ማዮፕያ) ተፈጥሮባቸዋል” አይደለም? ጉዳዩ የኢትዮጵያውን ጉዳይ ነው ተባብለናል። የኢትዮጵያን ዋና ዋና ትግሎች (ጦርነቶች) በቅጥረኛና ካልሆነም በአሜሪካ አማካይነት የምንዋጋቸው አይደሉም። ይልቁንም ዛሬ አሜሪካ የነገረችን ሁላችንም እሥረኝነት እንዲሰማን ይመስላል። ጐበዞቻችን በወህኒ እየማቀቁ ነው።
ስለ እስክንድር፣ ስለ በቀለ፣ ስለ አንዱዓለም፣ ስለ ርእዮት….ሰምተን ነበር? ከእነሱ ሌላ ሰማንያ ሺህ ማን ያውቃል 180ሺህ ሰዎች በወህኒ ዓለም ይማቅቃሉ። ሌሎች ያልታሰሩ ግን “በመተካካት መልክ” ሊገቡ ወረፋ እየጠበቁ ናቸው። አፍጥጦ የመጣብን- እስካሁንም ያልተመለሰው ከባድ ጥያቄ- ለመሆኑ እኛስ አልሞትንም ወይ? መቸም ወደፊት እንደምንተሳሰበው ከሞቱት አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ አምሳ ሺህ ውስጥ አይደለንም ወይ? የመኖር ያለመኖር ማረጋገጫ (ምናልባት ሰርተፊኬት ወይም ሊቸንሳ) አግኝተናልን? ራስ ቢተወደድ መኮንን እንዳልካቸው “አልሞትሁም ብዬ አልዋሽም” ነበር ያሉት? ሙኩሼዬ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ቀዌሳ ደግሞ ልዑል ሐምሌት የሚያንበለብለውን ዘላለማዊ ስንኝ እንዲህ ብሎ በከፊል ወደ አማርኛ መልሶታል።
መኖር አለመኖር እዚህ ላይ ነው ምሥጢሩ
የዕድል ፈተና አለንጋ ሲወናጨፍ ወስፈንጥሩ
ይህ ዕድል ያልደረሰውና የፈተናውም አለንጋ ያልገረፈው አለ ወይ? ይለናል። ኦስካር ዋይልድ ይመስለኛል በሶሻሊዝም ሥር የሰው ነፍስ (The Soul of Man under Socialism) ድርሰቱ “መኖር እጅግ ብርቅ ከሆኑ ባሕርያት ዋነኛው ነው። ብዙ ሰዎች እንዲሁ አሉ። ግን አይኖሩም ” ያለው (To live is the rarest thing in the World. Most people exit, that is all ) ይለናል በአንክሮ። የእኔው የትግል አድባር (አያውቀኝም) ፕሮፌሰር ሐጐስ ገብረ ኢየሱስ እናቱን ለመጠየቅ ጓድ መንግሥቱ ሔሊኮፕተር አዘዙለትና ወደ አድዋ ሔዶ ነበር። ሲመለስ A Requiem of History በሚል ያቀረበውን መጣጥፍ አልረሳውም። በዚያው ሰፊ ጽሑፉ ውስጥ እንደ ፈርጥ ያየሁለት “እናቴ በእርግጥ በሕይወት አለች። እየኖረች ግን አይደለም። She was alive, but Not living.” ይላል።
በ1980ዎቹ ካነበብኋቸው መጻሕፍት መካከል በሔንሪ ኪየምባና በዴቪድ ማርቲን የተገለጡ አስደንጋጭ አጋጣሚዎች በአእምሮዬ ውስጥ የተከሉት ክፉ ትዝታ አለ። በኢዲአሚን ኡጋንዳ ጊዜ የተፈጸመ ነው። እንዲያውም የ“State of Blood” የሚለው ጸሐፊ የኡጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስተር የነበረው ሔንሪ ኪየምባ ነው። ወደ ወጉ እንመለስና ኢዲአሚን በየቀኑ ሥፍር ቁጥር የሌለው ኡጋንዳዊ የሚገድልበትና የጭፍጨፋው ወፍጮ እንበለ እረፍት የሚሠራበት ሥፍራ ነበር። በዚህ “ሥራ” ላይ የተሰማሩት ባለሙያ ነፍሰ- ገዳዮች ትንሽ ፋታ ካገኙ ወደ ሰፈር መሸታ ቤት ይሄዱና ካቲካላና ቡቅር ከሚመስለው “ነፍስን ጭምር” ከሚያስረሳው መጠጥ ይጨልጣሉ። ግድያው እንደ ጫት ሐራራ ስለሆነባቸው በማይገድሉበት ሰዓት ሁሉ ሲያፋሽጉ ይውላሉ።
አንድ ቀን ያለወትሮው ግድያው በምሽት ሰዓት ሊጠናቀቅ ስላልቻለ ዋናው ገዳይ እስረኞቹን ይሰበስብና “ዛሬ ስለመሸ ሄዳችሁ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር እደሩና ነገ በጠዋት መጥታችሁ መቃብራችሁን ቆፍራችሁ ትገደላላችሁ። አሁን ሂዱ። መልካም ዕድል” ይላቸዋል። በማግስቱ እስረኞቹ ተሽቀዳድመው በመሰለፍ መቃብራቸውን ቆፍረው በተሰጣቸው ትልልቅ መዶሻ አንዱ ሌላውን ገደለ ይባላል። ተረት ወይም የፈጠራ ድርሳን አይደለም። ዴቪድ ማርቲን በኦብዘርቨር ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ያቀርብ የነበረውን ሐተታና ከላይ በርእሱ ያመለከትሁትን የሔንሪ ኪየምባ መጽሐፍ ያነብቡአል።
ገዥዎቻች፣ አንዱን ጠባብ፣ ሌላውን ነፍጠኛ በማለት የሰየፉት ወገን ቁጥር ይታወቃል? ከምዕራብ ወደ ደቡብ፣ ከደቡብ ወደ ምዕራብ እያንከራተቱ በየኪሎ ሜትሩ የረገፈው ወገናችን ቁጥር ይታወቃል? በአኅዝ የማይገለጠው መከራውና ሰቆቃው በምን ይተመን? እዚህስ ደረጃ አልደረስንም የሚያሰኝ ምን ምልክት አለ? አሁንም ለእርድ የተዘጋጀን ነን- ሁላችንም ባንሆን አብዛኞቻችን። ንጹሐን ዜጐችን ግደሉ ብንባል ዓይናችንን የማንጨፍን አለን። አሁንም ቢሆን እኛን በእኛ እየጨረሱንም እያጫረሱንም ነው። አይደለምን? የኢዲአሚኑ ሪፖርት ይዘገንናልን?
ያንን የምታውቁትን ለፍቶ ያስተማረኝ የኢትዮጵያ ገበሬ ሲባልለት የቆየውን “ናስቲለው”…አልፎ አልፎ ታስታውሱታላችሁ? ትዝ ሲላችሁ ዓይናችሁ እንባ ይቋጥር ይሆን? (ናስቲለው በሰሜን ኢትዮጵያ ገበሬ ማለት ነው።) አሜሪካ ስለ ኢትዮጵያ ገበሬ በመንግስት መሰቃየት ያርዳን? አቦ! አቦ! እንደ ብዕርና ወረቀት ያስጠላኝ ነገር የለም። ካሣ ተሰማ ትዝ አለኝ። ድንቀኛው ጸሐፊ ጓደኛዬ ብርሃኑ ዘሪሁን ካሣ ተሰማን አንድ ቀን አነጋግሮት ነበር። ለመነን መጽሔት ነበር። ብርሃኑ ወርቅ የሆነውን የካሣን ፕሮፋይል ሲያቀርበው “ቧንቧ ሠራተኛው ካሣ” በማለት ነበር። ካሣ ክራር መደርደር የለመደው በስሜት ነው። ከተቃጠለ አንጀቱ የሚያወጣውን ትንፋሽ በዘፈን ለማብረድ ነው። ካሣ ይዘፍናል። ስሜቱ ወደ ጽርሐ-አርያል ይከንፋል። እሱም ራሱ እንደ ማኰብኰብ ሲለው ክራሩን ሰባብሮ ሲጃራ መግዣ ፍለጋ ይሄዳል።
ይኸ ሁኔታ ዛሬ ይገባኝ ጀምሮአል። ከክራሩ ባሻገር የሚሰማው ድምፅ ያለ ይመስለኛል። ከመላእክት ጋር ሲነጋገር ቆይቶስ ቢሆን? ከአድማስ ባሻገር ከታላላቆቹ ተራሮች ላይ ሆኖ ስለዚች አገር ዕድል- ስለሚደርስባት አደጋ፣ ስለ ትንንሽ ልጆችዋ መቀጨት፣ እንደ ዛሬ ስላለው የመከራ ሌሊት ያጫወቱት እንደሆነ ማን ያውቃል? እንዲያ ሆኖ ሆኖ ካሣ ወደ ቧንቧ ሥራው ይመለሳል። እሱም ዘመንን ቆጥሮ ወደ መሬቲቱ ተመለሰ። ወደ ማኅፀናዋ።
እኛንም ደካሞች ልጆችዋንም እነሱንም ባሊጊዜና ቅምጥል አዳዲስ መኳንንትና መሳፍንት የኢትዮጵያ መሬት እኩል ትበላናለች ወይ? ስለ ጄኔራል ደጐል ያነበብሁት አንድ ታሪክ አለ። ጄኔራል ደጐል ሽባ ሆና የተወለደች ልጅ ነበረቻቸው። ወላጆች እጅግ እያዘኑ ልጅቱ በመንፈስ እንድትጠነክር የማያደርጉት አልነበረም። የሚችሉትን ጥረት ሁሉ ካሙዋጠጡ በኋላ ልጅቱ ትሞታለች። እናት መሆን አይቀርምና ማዳም ደጐል ምርር ብለው ያለቅሳሉ። ያዝናሉ። እሳቸውን ማጽናናትም ከባድ ሆነ። በዚህ ጊዜ ጄኔራል ደጐል ባለቤታቸውን “እስካሁን ድረስ ምኞታችንና ጸሎታችን ሁሉ እግዚአብሔር ከሰው እኩል እንዲያደርጋት ነበር። ይኸውና በሕይወት ባይሆን በሞት ከሁሉ ጋር እኩል ሆናለችና ልቅሶሽን ተይ…” በማለት ባለቤታቸውን አጽናኑአቸው።
ኢትዮጵያውያን ሽባ ሆነን አልተፈጠርንም። ወይም አዳዲሶቹ ዲታዎች (ኖቮሪሽ) በአፋቸው ላይ የወርቅ ፍልቃቂ እየነከሱ ከማኅፀን አልወጡም። ሕዝብ የሚገዛው እንዲህ ነው ተብለው ጊንጥ የሚመስል አለንጋ የሰጣቸው አንዳች ኅይል የለም። ለምን ገዥና ተገዥ፣ ገራፊና ተገራፊ ሆነን ቀረን? አንመራመር። አስፈላጊ ወዳልሆነ እሽኰለሌም አንግባ። ይልቁን ከሞት በፊት ስላለው እኩልነት እናንሳ። በሞት ሕይወትን ስለማምጣት፣ በደምና በአጥንት ነፃነትንና እኩልነትን ስለመቀዳጀት።- ውይይይይ ለአፍ አይገድም። ትግሉን፣ መስዋዕትነቱን በወረቀት ላይ ጨረስነው አይደል? በሃያኛው ክፍለ ዘመን መነሻ የተጫነው የእኩልነት ትግል እነ W.E.B Du Bois የጀመሩት የጥቁር አሜሪካውያን ተጋድሎ ስትራተጂ የሚነደፍበትና ፕሮግራሙ በሥራ ላይ የሚውልበት ስልት የሚወጣበት ነበር። ታላቁ ዱብዋ ተፈጥሮ ለሰው ልጆች እኩል የሰጠችውን መብት ከሰው ልጆች መለመንን የመሰለ ውርደት እንደሌለ ይገልጣል። የመብትና የነፃነት ልመናን የመሰለ ወራዳ አቋም የለም። W.E.B Du Bois The Souls of Black Folk በሚል ድሮ ባሳተመው መጽሐፍ “ተነሥ! የምታጣው ሰንሰለትህን ነው” ወደሚለው የተራማጆች ፍልስፍና ያመራል። እንዲያውም ሎወልን በመጥቀስ-
“Twixt old systems and the word
Truth forever on the scaffold
Wrong forever on the throne
yet that scaffold sways the future
And behind the dim Unknown
Standeth God within the shadow Keeping watch above His own”
ይላል። እውነት ዘወትር በመሰቀያው ሥፍራ፣ ውሸትና የማይገባው ሁሉ ዘወትር በዙፋኑ (በአልጋው) ላይ የመገኘቱ ነገር- ያ የመሰቀያው ጣውላ የወደፊቱን ሁሉ እየነቀነቀ መገኘቱ፣ እነሆ በጭላንጭሉ መሐል ደግሞ እግዚአብሔር ከፍ ብሎ ቆሞ የራሱን ወገኖች የማበረታታቱ ጉዳይ ዘላለማዊ ነው።
ልመለስ ወደ አሜሪካ ዓመታዊ የሰብአዊ መብት መግለጫ። ከላይ ያነሳሁአቸው የዱብዋ (አሜሪካኖች ዱባይስ ይላሉ ፈረንሳዮችን ለማብሸቅ) ወይም የፍሬደሪክ ዳግላስ ታሪኮች ለእነሱ ብዙ ይጥማቸው እንደሆነ አላውቅም። በተለይ ለሪፐብሊካኖቹ። እንደዚያም ሆኖ ይህ በእነሱ ድጋፍና ርዳታ ሞልቃቃ ሆኖ የተወለደውና የሚጨፍርብን ሥርዓት (መንግሥት) ፀረ ሕዝብ፤ ፀረ አገር፣ ፀረ እንጨት፣ ፀረ ሳር፣ ፀረ ሕዝብ፣ ለመሆኑ- እደግመዋለሁ- የእነሱ እማኝነት አለን። ጊዜው- የመለያያው- ደረሰና ነው ምሥጢሩን ሁሉ ያፈነዱት? ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። እዚያ ላይ ያለውን ነጥብ የምንመለስበት ይመስለኛል። ለአሁኑ ግን አሜሪካ በአንድ በኩል ልትረዳን የምትችላቸውን ጉዳዮች ባነሳ- ከአንባብያን ድጋፍ ካገኘሁ።
አንደኛ- እስካሁን ድረስ አሜሪካ እንዲህ ያለ በሰብአዊ መብት አከባበር ረገድ የተበላሸ አቋም፣ በፖለቲካና በአገር አንድነት ጥበቃው ረገድ አሳፋሪ ሪኮርድ፣ በሕዝብ ሰላም ጥበቃና የፍትሕ መስተንግዶ መላሸቅ ረገድ ያልሆነላቸውን መንግሥታት ወይ Evil ኤምፓየር- ወይ Rogue State አለዚያም አሸባሪ (Terrorist) ሲሉ ባጅተዋል። ወያኔ ምንድነው? በእኛ ምደባ Terrorist Regime ሊባል ይገባዋልና ስያሜው በዚሁ እንዲሆን እንጠይቃለን።
ሁለተኛ፥ ይኸ ሁሉ ከተወሳና የወያኔዎች መንግሥትም ከሕዝብ የብድርና የርጥባን ገንዘብ 20 ቢሊዮን ዶላርስ ጠልፎ ወደግል ሂሳብ ያዋለ እንደመሆኑ- የዋና ዋና ሌቦችን የስም ዝርዝር እናቅርብና ወደየምዕራቡ መዲና ሲገቡ እንዲያዙና እንድንፋረዳቸው።- ገንዘባቸው እንዳይንቀሳቀስ እንዲደረግ- ከምዕራባውያን የሚሰጣቸው ማናቸውም ርዳታ ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲቋረጥ- ኢኮኖሚው ራሱ የተጠለፈና ወደ ግል ኩባንያነት የተዛወረ ስለሆነ የትኛውም አገር ከወያኔዎች ጋር የንግድ ልውውጥ እንዳያደርግ ዘመቻችንን እንዲቀበለን ትብብር እንጠይቃለን።- ከናይን ኢለቨን ጋር በተያያዘ አሜሪካ እንዳይደርሱ እግድ የነበረባቸው አንዳንድ ዘራፊና አቀባባይ ሌቦች እንደገና ወደ አሜሪካ ብቅ እያሉ የለመዱትን የሞራል ድቀት ትርኢታቸውን እያሳዩ ናቸው። ከእነዚህ መካከል አንዱን አረብ ግለሰብ የኢትዮጵያ ትውልድ ሁሉ የሚፋረደው ስለሆነ ተይዞ እንዲመረመር እንጠይቃለን። ወርቃችን፣ ሌሎች የማዕድን ሀብቶቻችን ወዘተ በዚሁ ሰው እንደ ትንሽ ዕቃ በየቀኑ እየተጫነ እንደሚወሰድ እናውቃለን። እናስረዳለንም። …………

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ቢተዋ አማረበት..."በእርቅ ይልስ ...

በ1980ዎቹ Republic of Fear በሚል ርእስ ስለ ሳዳም ሑሴን ጨለማ አገዛዝ የሚያወሳው መጽሐፍ በእጅጉ ያሸማቅቃል። ጸሐፊው ኬናን ሜኪያ ይባላል። የኢትዮጵያ የዛሬ ሁኔታ ደግሞ ሌላ ባሕርይ ያለበት ይመስለኛል። ስለ ዋናዎቹ አምባገነኖች ሲነሣ አብዛኛዎቹ ነጠላ ናቸው። በቺሊ ፒኖቼ- በሩማንያ ቻይቼስኮ፣ በኢራቅ ሳዳም ሑሴን፣ በሊቢያ ጋዳፊ…ናቸው። ለወርቅ ጥጃቸው የማይንበረከክ፣ ለምስላቸው የማይሰግድ ከሁለት ስፍራ ይከፈላል። ያማቸው፣ ስማቸውን ያጐደፈ…የሚሰቃይበት አዳዲስ መሣሪያ አስፈልፍለዋል። ዝርዝር የማሰቃያውን ስልትና ድርጅት ከማእከላዊ ምርመራ ሠራተኛነት አምልጠው የወጡ ሰዎችን ማነጋገር ይቻላል። ባይሆን አንድ ጥያቄ በአእምሮአችሁ የሚመላለስ ወገኖቼ አትታጡም። መለስ ከሞተ በኋላም ይኸ አገር በአምባገነን የሚመራ ነው ለማለት ይቻላል ወይ? በእኔ በኩል ከሰዎች ጋር ስወያይ “አምባገነኑ የማይታወቅ አምባገነን መንግሥት” A Dictatorship without a Dictator ግን አገዛዙ መንጋ ጨካኖች፣ ነፍሰ- ገዳዮችና በዝባዦች ቢኖሩትስ? የፈረንሳዩ ታላቅ ምሁር ዣን ፍራንስዋ ሬቨል Without Marx or Jesus በሚለው መጽሐፉ እንዲህ ያሉትን አምባገነኖች ባሕርይ Collective Mediocrity and Collective bestiality ይለዋል። ነገሩ እንዲህ ነው። መለስ ሲሞት የእሱ እጓለማውታ (Orphans) መፈላለግ ያዙ። ሰብሳቢ አጣን ብለው ወደ ትካዜው ዓለም ተሰደዱና መጠራራቱን አንድ መፍትሔ አደረጉት። ምንጣፉን ቶሎ ብለው የረገጡት እነ እንቶኔ ደግሞ አራት ኪሎን የተጫጫነውና አሁንም የሚገዛውን መንፈስ በፍጥነት በማናቸውም አስማት ለማስወጣት አልቻሉም። ትንሽ ፋታ ሳያስፈልጋቸው አልቀረም። ጥቂት ጊዜ ከገዙ በኋላ የፕሮፓጋንዳውም መሣሪያ ትንሽ ትንሽ ይደፍረዋል። “መለስኮ ሰው ነው” ማለት ይጀምራል። ሰው መሆኑን ዛሬ ነው ያወቁት አትበሉአቸው። እኛ መለስን ከመቃብር አውጥተን አንፋረደውም። እነሱ ራሳቸው ከሳሽም ፈራጅም ይሆናሉ። ጠብቁ ብቻ።
በደርግ ጊዜ ስለአባካኝነትና አሻጥር ትልቅ ጉባኤ ተዘርግቶ ነበር። በንቁዝ (ኮራፕት) ባለሥልጣኖችና በመሳሰሉት ላይ ጥብቅና ወሳኝ የሆነ ርምጃ ስለሚወሰድበት ሁኔታ ውይይት ሲካሄድ በየቦታው ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ አሳብ ይቀርባል። በዚያ መድረክ ላይ የአገር አስተዳደር ሚኒስትር የነበሩት ጄኔራል ታዬ ጥላሁን የተናገሩት ትዝ ይለኛል። በአጤ ምኒልክ ዘመን እቴጌ ጣይቱ “ለአገሬ ለየጁ ያለው አንድ አፈንጉሥ ብቻ ስለሆነ ሌላ እንዲጨመርለት እጠይቃለሁ” ሲሉ እቴጌይቱን በአደባባይ ተቃውመው የማያውቁት ንጉሠ ነገሥት “እንኳን ሌላ ተጨምሮበት አንዱም ቢሆን አልተቻለም” አሉ ይባላል።
በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ከመለስ ሞት በኋላ አንድ ታዋቂና በአደባባይ ስሙና ሹመቱ የተገለጠ አምባገነን ባይኖርም ሟቹ በመጠኑ ራቅ ያደረጋቸው ሰዎች አልጋው ላይ የተረባረቡ ይመስለኛል። አቦይ ስብሐት፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ዐባይ ወልዱ፣ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ወዘተ ወዘተ…በአንድ አገር የስለላው መረብ እንዳለ ወደ ፍጹማዊ ኅይል ሲለወጥ ደግሞ የዜጐች ሁሉ (መካከለኛ ደረጃ ያሉት ወያኔዎች ሳይቀሩ) መብት ወደ ኢምንትነት ይለወጣል። የሥነ መንግሥት ምሁራን በመንግሥት ውስጥ መንግሥት (ኤስቴት ዊዝን ኤ ስቴት) የሆነውን እንዲህ ያለውን ሥርዓት “መሪ” የሚባለውን ግለሰብ ጭምር ሽባ አድርጐ የሚቀፈድደው ያደርጉታል። በአሁኑ ሁኔታ ቀስ በቀስ የመለስ የቅርብ ሕዝብ አጫራሾች ዕጓለማውታ (ኦርፋንስ) ቢመስሉም ሌሎች በርካታ አምባገነኖች ጡንቻቸውን እያፈረጠሙ ናቸው። ወትሮ አንድ አምባገነን ያልቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የብዙ አምባገነኖች ተሸካሚ ሆኖዋል። ሁሉም ነፍሰ ገዳዮች! ነፍሰ ገዳይ የማይፈራስ ማነው?
ለጊዜው በመንጋ ተንኮለኞች- ነፍሰ ገዳዮችና የዝርፊያ ሠራዊት እየተገዛን እንገኛለን። ስለእነሱ ድግስ፣ ስለ እነሱ ጥቅም፣ እነሱ የትኛዋን ጋለሞታ እንደሚጐበኙ፣ የትኛዋን መለኮን ዛሬ እንደወሰዱ እንወያያለን። በጥቃቅን ጉዳዮች አእምሮአችንን አስጨንቀናል። ወጣጥረነዋል። ይልቁን በሌላው ዓለም እየተቀጠቀጠ ማረፊያ ያጣው መንግሥታዊ አሸባሪነት የሙጥኝ ብሎ የሚገኘው በኢትዮጵያ መሆኑን እንተባበር። ይህን የሽብር መንግሥት ሌላው ቀርቶ በብረት መሞከርን ካህናቱና መነኮሳቱም መደገፍ አለባቸው። ከቶውንም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሺስቶች ጥይት ሊደበደቡ ጥቂት ሰከንዶች ሲቀራቸው “ልጆቼ ኢትዮጵያውያን ለፋሺስቶች እንዳትገዙ አውግዤአለሁ” ማለታቸው ይጠቀሳል። አዳዲስ ካሕናትና የዚህ ትውልድ ቀሳውስት ነገሩን ቸል እንኳ ቢሉ የአቡነ ጴጥሮስ ግዝትና ውግዘት አለብን። ቋሚ ነው- እስከማዕዜኑ።
ትግልና ታጋይ የሚጠይቁት አንድ ነገር ብቻ ነው። በደረትህ ውስጥ ጤነኛ ልብ፣ በጭንቅላትህ ውስጥ ጤናማ አእምሮ ካለህ ማናቸውም ችግር አይፈታህም። ጥይት አይመታህም። ድንፋታ ትርጉም አይሰጥህም። ቅጥፈትና ማስፈራራት ትጥቅህን አያስፈታህም። ልጆቼ ልላቸው የምችለው እነ እስክንድር፣ በቀለ፣ አንዱአለምና ርእዮት ይህን ወኔ በሰፊው የተቀዳጁ ናቸውና እንኮራባቸዋለን። እነሱ ወኅኒ ዓለም ሲገቡ የከዳናቸውና የቆሙለትን ዓላማ ጭምር የረሳንባቸው ከመሰላቸው ደግሞ አደራ በላነት ሊሰማን ይገባል።
ይህን ጽሑፍ የጀመርሁት በወያኔ የልደት በዓል ምክንያት ትንሽ የምለውን ለማቃመስ ነበር። ምናልባትም እንደ ፍሬደሪክ ዳግላስ ለእነዚህ ሰዎች “ጉንበት 20- ጉንበት ሃያ ትሉናላችሁ ጉንበት ሃያ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥቃይ ሁሉ እናት የሆነችው ስቃይ የመጣችበት ቀን። ጉንበት 20 የባርነትና ወደር የሌለው ውርደት መታሰቢያ ቀናችን ናት። ጉንበት 20 ለእሥራታችን መታሰቢያችን ናት።” ልንላቸው እንችላለን። ይኸ የደፋሮቹ ጋዜጠኞች – የጀግኖቹ የፖለቲካ መሪዎችና ገበሬዎች የተባበረ ድምጽ ነው። በሬሳችን ላይ የሚጨፍሩበት፣ በመቃብራችን ላይ የሚያሽካኩበት፣ ቤትና ንብረት አሳጥተው ለስደት ያበቁንና በዚህ ደስታ የሚሰክሩበት በዓላቸው- የእኛ የልቅሶ ዕለት፣ የእኛ የመከራ ቀን መታሰቢያ ነው።
በመጨረሻም እንደገና ለአሜሪካ በማቀርበው ጥያቄ ላይ ይህችን ነጥብ እደግማለሁ። ይህ መንግስት ኢቭል የምትሉት አይነት ነው? ወይስ አሸባሪ? የወያኔ ኦሮሞዎች በኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች ላይ የሚፈጽሙትን እልቂት፣ የወያኔ አማራዎች (እነበረከት አምሮች ከተባሉ) በኢትዮጵያውያን አማሮች ላይ የሚያካሄዱትን መጠነ ሰፊ ድምሰሳ፣ የወያኔ ሙስሊሞች በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እያደረሱ የሚገኙትን ወከባና ወደር የሌለው ጥቃት፣ ሟቹ የመለስ የሃይማኖት የይስሙላ ፓትርያርክና እንደ ሩሲያዊው ራስፑቲን የሚቆጠረው አባ ጳውሎስ በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያካሄደውን ሥቃይ አሜሪካ ከእኛ በላይ እንደማያውቀው ለዴሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብትና ነፃነት ስትል ርምጃ ለመውሰድ አቅዳለች? አጤ ኅይለሥላሴ በቀድሞው የመንግሥታት ማኅበር ጉባኤ ላይ ያደረጉትን ንግግር ለመጥቀስ እገደዳለሁ – “ታሪክና ትውልድ ፍርዳችሁን ይጠባበቃሉ!”
እነሆ ዛሬ በኢትዮጵያ የሰው ዘር ጠላት የሆነ ሥርዓት አለ። የሒትለርን ፀረ ሕዝብነት ለመረዳት የፖላንድ መወረር፣ የሃምሳ ሚሊዮን ሕዝብ ማለቅ፣ የስድስት ሚሊዮን አይሁድ መጨፍጨፍ መጠበቅ ይገባል? ታሪክ አላስተማራችሁምን? በአሜሪካ ላይ ስንት ክህደትና ቸልታ እንቁጠር? በፋሺስት ወረራ ዘመን ሩዝቬልትና ሴክሬተሪ ሐል ያሳዩን ክሕደትና ቸልታ አይረሳንም። አሜሪካ የበለጠ ትናገር! እግዚአብሔር ሁላችሁንም ይጠብቃችሁ!!

ተጨማሪ ያንብቡ:   የአማራ ሕዝብ ብቸኛ አማራጭ - መስፍን አረጋ

1 Comment

  1. This name ‘Tsegaye G/Madin Areya’ is a lot for me. His monthly commentary on ‘Topia-Metatif’ opened my eyes and he is my mentor. I am very happy of reading his commentary once again after more than a decades on Zehabesha. I am writing this comment before reading his commentary.

Comments are closed.

Share