ወጣቱ አና ለነጻነት የሚደረግ የትግል መስዕዋትነት (ገዛኸኝ አበበ ከኖርዌይ)

የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ህልውና የሚወሰነው ወጣቶች ባላቸው ሚና ላይ ሲሆን በብዙ ሀገራት እንዳየነው እና እንደተመለከትነው ወጣቶች ስለ ነፃነታቸው ፊት ለፊት መንግስታትን በመጋፈጥ ለመብታቸው ታግለዋል መስዋህትነትም በመክፈል የፈለጉትን አለማና ግብ አሳክተዋል::ለዚህም የሰሜን አፍሪካ አገሮችንና የመካከለኛው ምሥራቅን የለውጥ አብዮት ያቀጣጠሉትን ወጣቶች ዞር ብሎ መመልከት ያሻል:: የአንባ ገነኖች የስልጣን አገዛዝ አልዋጥላቸው ያላቸው እነዚህ የሰሜን አፍሪካ አገሮች እንደነ ግብጽ ፣ ቱኒዚያ እና ሊቢያ ያሉ ሀገሮች የሚኖሩ ወጣቶች በጊዜው ለናፈቁት እና ለተመኙለት ነጻነት ብዙ መስዋትነትን በመክፈል ዓላማቸውን አሳክተዋል:: በወቅቱ የነበረው የዓረብ የፖለቲካ ትኩሳት መነቃቃት ለብዙ ሀገራት ወጣቶች ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ታሪክ ነው::

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመለስ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አካሄድ ወደ ኋላ ዞር ብለን በምናይበት ጊዜ በኢትዮጵያ ሲደረግ በነበረው የፓለቲካ እንቅስቃሴ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ትልቁን ሚና ይጫወት እንደነበር ከታሪክ መረዳት እንችላለን::እነሆ በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ውስጥ እያንዳንዱ ትውልድ በተለያየ ጊዚና ወቅት የራሱን አሻራ ጥሎ አልፏል፡፡ በተለይ በንጉሡ ጊዜ የመሬት ላራሹንና ሌሎችንም የፖለቲካዊ ጥያቄዎች አንግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረው የተማሪ ንቅናቄ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን በዚያን ጊዜው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩትና ግንባር ቀደሞቹ ዋለልኝ መኮንንና ጥላሁን ግዛው በድንገት በወታደራዊው ኃይል ቁጥጥር ሥር ለወደቀው የተማሪው አብዮት ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ በዘመኑ ለነበረው ሃይለኛ እና ወኔን የታጠቀ ትውልድም መታወቂያ ሆነው ማለፋቸውን የታሪክና የፖለቲካ ተንታኞች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚያወሱት የታሪክ ትውስታ ነው፡፡

ከቅርብ አመታት በፊትም ማለትም በ97 ምርጫ ሁሉም ሰው እንደሚያስታውሰው ይህ ወቅት ኢህአዴግ ወጣቶችን ሙሉ በሙሉ የገፋበት ወቅት ጊዜ እንደነበር እና መንግስት ስራ አጥተው የሚንከራተቱ ወጣቶችን “አደገኛ ቦዘኔ” የሚል ታፔላ በመስጠት የተለያዩ እስሮችና የማንገላታት እርምጃዎችን የወሰደበት እና የፈፀመበት ወቅት እንደነበር በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡ ይህ አይነቱ የመንግስት ግብታዊ እርምጃ ወጣቱን ወደ ተቃውሞ ጐራ እንዲያዘነብል አድርጐታል፡፡ ለዚህም ይመስላል በወቅቱ በምርጫ 97 ዋዜማ ኢህአዴግ ያቀረባቸውን የተለያዩ ማባበያዎች “አደገኛ ቦዘኔ ራሱ ወያኔ” የሚል ዜማ በማቀንቀን ለተቃዋሚዎች ድጋፍ የሰጠው፡፡ ኢህአዴግ በምርጫ 97 የደረሰበትን አስደንጋጭ ሽንፈት ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ ቀዳሚ ተጠቂ የሆነውም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እንደነበር እናስታውሳለን፡:ለዚህም ነው ምርጫ 97 ተከትሎ በጊዜው በአቶ መለስ መንግስት ከሃያ ሺ በላይ ወጣቶች በእስር ቤቶችና በወታደራዊ ካምፖች ታሰረው የተሰቃዩት እና ከ200 በላይ የሆኑ ባብዛኛው ወጣት የሆኑ ንፁሀን ዜጐች በግፍ በአደባባይ የተገደሉት::ይህንን ለነጻነት ትግል የተደረገን የወጣቶች የህይወት መስዋትነት ሁል ጊዜ ስናስታውሰው የምንኖረው ነው::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለብሄራዊ ህልዉና አለኝታነት እና ቀጣይነት የዓማራ መደራጀት እና አንድነት “አማራጭ አልባ አማራጭ !!”

እንደሚታወቀው በአሁን ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚኖረው ህዝብ ከፍተኛውን ቁጥር ይዞ የሚገኘው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል መሆኑ ይታወቃል:: ይህንንም ተከትሎ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከወጣቶች ብዙ የምትጠብቀው ነገር መኖሩ የማያጠያይቅ እውነታ ነው;; ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሀገራችን የወደፊት ሁለንተናዊ ህልውናዋ ያለው እና የሚወሰነውም በእነዚሁ በዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስለሆነ :: ከላይ እንደገለጽኩት በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚኖረው ሕዝብ አብዛኛውን ቁጥር የያዘው ወጣቱ እንደመሆኑ ይሄ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፍላጐቱ ሊሞላለት አልቻለም:: ከዚያም ባለፈ ወጣቶች የነጻነትም ሆነ የመብት ጥያቄያቸውን ወይም ፍላጐታቸውን መግለጥ እና መናገር የሚችሉበት አግባብ የተዳፈነ በመሆኑ፣ በአለም ላይ ኢትዮጵያን የተገፉ ወጣቶች የበረከቱባት ሀገር እና ሀገራቸውን እየጣሉ ከሚሰደዱ ወጣቶች መካከል ቅድሚያውን እንድትይዝ አድርጓታል፡፡

የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት በስልጣን በቆየባቸው ባለፉት አመታቶች እየበደለ እና እያሰቃየ ያለው በመላ ሀገሪቱ ላይ የሚኖረውን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ቢሆንም ይበልጥኑ በወያኔ ራዳር ውስጥ በመግባት በአገዛዙ ጭቆናና ግፍ እየደረሰበት ያለው በሀገራችን የሚኖረው ወጣቱ ዜጋ መሆኑ የታወቀ ነው:: ዛሬ የአማራው፣ የትግራዩ፣ የጋምቤላው፣ የኦሮሞው ፣የደቡቡ፣ የአፋሩ መላው የኢትዮጵያ ወጣት ዜጋ ለነጻነቱ በሚያደርገው ትግል በወያኔ ጨካኝ መንግስት እያተደበደበ፣ እየታሰረና እየተገደለ ለነጻነቱ መስዕዋትነትን በመክፈል ላይ ይገኛል :: ለዚህ ማሳያ የሚሆነን በሀገራቸው ፖለቲካ በመሳተፍ የተቃዋሚዎችን ጐራ የተቀላቀሉ እንደነ አንዱ አለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን እና ኦልባና ሌሊሳ የመሳሰሉ ወጣት ፖለቲከኞች እንዲሁም እንደነ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ እና ርዮት አለሙን የመሳሰሉ የወደፊቶ ኢትዮጵያ ተስፈኞች ብዙ የምትጠብቅባቸው ወጣት ጋዜጠኞች የወያኔ መንግስት እያራመደ ካለው የዘረኝነት ፖለቲካ የተለየ አቋም በመያዛቸው እና በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ሀሳባቸውን በመግለፃቸው ብቻ በአሸባሪነት ተከሰው ወደ እስር ቤት በግፍ መወርወራቸው የኢትዮጵያ ወጣቶች በገዥው ስርዓት ምን ያህል መብታቸው እየተረገጠ እና ነጻነታቸው እየታፈነ በወያኔ የግፍ አለንጋ እየተገረፉ እንደሚኖሩ አመላካች ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወሳኙ የፋኖና የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል። ኅልውናን ከማዳን እስከ ሐገር ግንባታ።

የወያኔ መንግስት በወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እየወሰዳቸው ያለው እነዚህ በግፍ የተሞሉ እርምጃዎች ወጣቶች እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ አላደረገም፡፡ ይባሱኑ ወጣቱ ሀይሉን እያጠናከረ እና ወደ ተቃዋሚ ጎራ በመግባት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለወያኔ ኢህአዲግ መንግስት የእግር እሳት እየሆነበት ይገኛል.: በዚህ አጋጣሚ ዛሬ በአዲስ አበበ በተካሄደው የሴቶች 5ሺ ሜትር ሩጫ ላይ ተሳታፊ የነበሩትን እና የተለያዩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ እንዲሁም ርዕዮትና ሌሎች የህሌና እስረኞች ይፈቱ እያሉ ሲጮኹና ድምጻቸውን ሲያሰሙ የዋሉትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወጣት ሴቶች እህቶቻችንን ሳላደንቅ አላልፍም :: በጣም የሚያኮራ ተግባር በመፈጸም ምንም ነገር ሳይፈሩ ለወያኔ መንግስት የፍም እሳት በመሆን የተነሱለትን አላማ ‹‹ለነጻነት እንሩጥ›› የሚለውን መሪ ቃል በማሳካተቸው ጀግኖች ብያቸዋለው:: በነገራችን ላይ እነዚህ ወጣት ሴት እህቶቻችን ሮጫቸውን ጨርሰው ሲገቡ ለታገሉለት ነጻነት መስዋዕትነትን ከፍለዋል:: ሲከታተሏቸው በነበሩት የወያኔ ተላላኪዎቸ በሆኑት የፖሊስና የደህንነት ኃይሎች መያዛቸውና መታሰራቸው ተገልጾል::

የነጻነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህ፣ እና የዴሞክራሲውን ጥያቄ የሰማያዊ ፓርቲ ፣ የአንድነት ፓርቲ ወይም የሌሎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ በተለይም የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጥያቄ መሆን ይገባዋል:: ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በተለያየ የትግል መስክ በመሰማራት ኢትዮጵያችንን ከወያኔ ፋሽስታዊ ስርዓት ለመታደግ፣ የሀገራችንን ሕልውናና ክብር ለመመለስ በወያኔ መንግስት ላይ የፍም እሳት በመሆን መነሳት በእንቢ አልገዛም ባይነት መንፈስ በጽናት በመታገል ከወያኔ የዘረኝነት አገዛዝ ኢትዮጵያንና እራሱን ነጻ በማውጣት ለታሪክ የራሱን አሻራ ጥሎ ማለፍ ይጠበቅበታል::

የድል ቀን እንዲፋጠን ሁላችንም ወጣቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን እንነሳ !

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምልከታ (ክፍል-2) ሸንቁጤ – ከካናዳ

gezapower@gmail.com

Share