March 4, 2014
29 mins read

“የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ አይደለም” – አብርሃ ደስታ (ከአዲስ ጉዳይ መጽሔት ጋር ያደረገው ቃለ-ምልልስ)

addis guday magazine

አዲስ ጉዳይ መጽሄት ቅጽ 8 ቁ. 205/ የካቲት 2006

አዲስ ጉዳይ፡- የህወሓት የ39 ዓመታት ጉዞ በግልህ እንዴት ታየዋለህ?

አብርሃ ደስታ፡- በእኔ አመለካከት የህወሓት ጥረት ከመጀመሪያ አንስቶ ስልጣን ለመያዝ ነው፡፡ አሁንም በስልጣን ለመቆየት ሲሉ ኢኮኖሚውን እየተቆጣጠሩት ነው፡፡ የህዝቡን መረጃ የማግኘት መብት፤ የህዝቡን አስተሳሰብ ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት፡፡ ጉዞው ስልጣን የመያዝ እና በስልጣን የመቆየት ጉዳይ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- ፓርቲው ግን ‘‘ለመመስረቴ ምክንያቱ የህዝብ ብሶት ነው’’ ይላል፡፡

አብርሃ ደስታ፡- ይህ ፕሮፓጋንዳ ነው። መጀመሪያ ለትግል ሲነሱ ህዝቡ የስርዓት ለውጥ ፈልጎ ታግሏል። ነገር ግን የህወሓት መሪዎች ስልጣን የመያዝ ዓላማ እንጂ ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ማድረግ አልነበረም። በመሆኑም የህዝቡን ብሶት ስልጣን ለመያዝ ተጠቅመውበታል። ከዚህ ውጪ ለእኔ የእነርሱ ደርግን አስወግደው ስልጣን መያዝ የደርግን ሚና ለመጣወት እንጂ ህዝቡን ለመጥቀም አልነበረም።

አዲስ ጉዳይ፡- አንዳንዶች ህወሓት ወደ ኋላ አካባቢ የትግል መስመሩን ስቷል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ፓርቲው ከመመስረቱ አንስቶ ዓላማው ስህተት ነበር ይላሉ። የአንተ አስተያየት ምንድነው?

አብርሃ ደስታ፡- እዚህ ላይ እኔ ህወሓትን የማየው በሁለት ከፍዬ መሆኑ ይታወቅልኝ። ስልጣን ፈላጊው የህወሓት አመራር እና ነፃነት ፈላጊው የህወሓት ታጋይ፡፡ ደርግ ገና ስልጣኑን ከያዘ ከወራት በኋላ ወደ ጫካ ገቡ። ስለዚህ የህወሓት አመራሮች ጫካ የገቡት የደርግ መንግስትን ጭካኔ ስላዩ ወይም የደርግን አምባገነንነት ስለተገነዘቡ ነው ለማለት አልደፍርም። ምክንያቱም በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ የህወሓት አመራሮች የደርግን ጨቋኝነት የሚያውቁበት ሁኔታ አለ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። ዓላማቸው ስልጣን ነበር። ሲነሱም እንደሚታወቀው ትግራይን ለማስገንጠል ነበር፡፡ ይሄም ሆኖ ህወሓቶች ሲንቀሳቀሱ የደርግ መንግስት የወሰደው የኋይል እርምጃ ነበር። ይሄ እርምጃ ግን በጣም በስህተት የተሞላ ሆነ፡፡ ደርግ ጫካ የገቡትን ሰዎች ለማንበርከክ ሲል ህዝቡን በማስፈራራት ብሎም የመግደል እና ሌሎችም እርምጃዎችን ይወስድ ነበር፡፡ ይሄን ተከትሎም ህዝቡ የደርግን ግፍ በመቃወም ተነሳስቷል። ህዝቡ ለትግል በተነሳበት ወቅት ህወሓትን ተቀላቅሏል፡፡ የአብዛኛው የህወሓት ታጋይም ሆነ የትግራይ ህዝብ ዓላማ ከጭቆናና ከግድያ ለመዳን እንጂ ስለ ትግራይም ሆነ ስለ ኤርትራ መገንጠል ምንም የሚያስቡበት ጊዜ አልነበራቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ይሄን የኅብረተሰቡን ጭቆና የማስወገድ እንቅስቃሴ ለራሳቸው ፍላጎት አውለውታል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ኢህኣዴግ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ቢሆንም ፍፁም የህወሓት የበላይነት በግንባሩ ነግሷል የሚሉ አሉ። ይህን ሀሳብ እንዴት ታየዋለህ?

አብርሃ ደስታ፡- አብዛኞቹ የኢህኣዴግ አባል ፓርቲዎች የህወሓት ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ህወሓት እንዲመሰረቱና እንዲደራጁ ያደረጋቸው ናቸው፡፡ በዚህ አምናለሁ፡፡ ይህንን ሃሳብም እቀበለዋለሁ፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ህወሓት ራሱ የጥቂት ግለሰቦች ስብስብ መሆኑ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- ይህንን ሃሳብ ዘርዘር አድርገህ ብታብራራው?

አብርሃ ደስታ፡- በትግሉ ወቅት በጊዜው በነበረው ጨቋኝ ስርዓት የተነሳ ህዝቡ ሌላ የተሻለ አማራጭ ስላልነበረው ህወሓትን ደግፏል፡፡ ይሁን እንጂ ህወሓት ስልጣን ከያዘ በኋላ በሺኅ የሚቆጠሩ ታጋዮችን ሆን ተብሎ እንዲባረሩ ተደርገዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ገና ፓርቲው ስልጣን እንደያዘ የአመራሩ ተነኮሎች ግልፅ እየሆኑ ሲመጡ የህወሓት ታጋዮች መቃወም በመጀመራቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ህወሓት የተወሰኑ ግለሰቦች ስብስብ መሆኑ መረሳት የለበትም የምለው፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- አንድ ወቅት ህወሓት በትግራይ የሚከተለው የፖለቲካ ስልት ‘‘እኔ ከሌለሁ ደርግ ይመጣባችኋል’’ ዓይነት መሆኑን ተናግረህ ነበር።

አብርሃ ደስታ፡- አዎ! ይሄ እውነት ነው፡፡ እንደውም ዋናው የህወሃት የትግራይ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያው እኔ ከሌለሁ ሌሎች መጥተው ይበሉሃል የሚሉት ሃሳቦች ናቸው፡፡ በእርግጥ የደርግ ስርዓት እንዳይመለስ መፈራረሱ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄ ፕሮፖጋንዳ እየሰራ አይደለም። በትግራይ ውስጥ ብዙ ተቃውሞ አለ። በእርግጥ ይሄ ‘‘ደርግ መጣ’’ የሚለው ቃል የትግራይን ህዝብ ማስደንገጡ አይቀርም። በጊዜው ብዙ ስቃይና ግድያ ያየ ህዝብ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ይደነግጥና ‘‘ከደርግማ ህወሓት ይሻለናል’’ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ደርግ ሊመለስ እንደማይችል ከዚህ በኋላ በጥቅሉ ወደ ወታደራዊ ስርዓት ልንመለስ እንደማንችል ለህዝቡ በማስረዳት ለውጥ የምናመጣበትን መንገድ እናመቻቻለን የሚል ዕምነት ነው ያለኝ፡፡ ይሄ ፕሮፖጋንዳም ካሁን በኋላ አይሰራም።

አዲስ ጉዳይ፡- ይህን የምትልበት ምክንያትህ ምንድነው?

አብርሃ ደስታ፡- ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ህዝቡ ደርግ ሊመለስ እንደማይችል በሚገባ እያመነ መምጣቱ ነው። እኛም በዚህ ላይ በስፋት እንሰራበታለን። ህዝቡም ዲሞክራሲያዊ አሰራር እና ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንደሚያስፈልገው እየተረዳ ነው። ይሁን እንጂ የህዝቡ ግንዛቤ እያደገ በመጣ ቁጥር የህወሓት አፈናም በዚያው መጠን እያደገ መምጣቱ አይቀርም። በዚህ የተነሳም ህዝብ እየታፈነ ነው። የመሰብሰብ፤ የመደራጀትና የመናገር ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን አሁን እየተነጠቀ ነው። በዚህ ላይ ተገቢውን መልካም አስተዳደር እያገኘ አይደለም። በዚህ የተነሳም ህወሓት ደርግ ይመጣል ብሎ ለሚነዛው ፕሮፖጋንዳ የትግራይ ህዝብም ‘‘እናንተም እኮ ሌላው ደርግ ናችሁ’’ እያለ ነው። ‘‘ደርግም የሚደበድበንና የሚገድለን ስንናገር መብታችንን ለማስከበር ስንሞክር እንጂ እናንተም ማፈኑንና መግደሉን ጀምራችኋል። እናንተ እራሳችሁ እያፈናችሁ በመሆኑ ደርግ መጣ አትበሉን፡፡ እናንተ እራሳችሁ እንደ ደርግ እየሆናችሁ ነው’’ በማለት ህዝቡ ግልፅ መልዕክት አስተላልፏል። በዚህ የተነሳ ይህ ደርግ ይመጣባችኋል የሚለው ፕሮፖጋንዳ የሚሰራ አልሆነም።

አዲስ ጉዳይ፡- ብዙዎች በትግራይ የህወሓት ደጋፊ እንጂ ተቃዋሚ አለ ብለው አያምኑም። አንተ ደግሞ ተቃውሞ አለ እያልክ ነው . . . .

አብርሃ ደስታ፡- አዎ! በትግራይ ተቃውሞ አለ ብዬ ለእነዚህ ሰዎች ላረጋግጥላቸው እፈልጋለሁ። እንደውም በሙሉ ነፃነት ህዝቡ ምርጫ ማድረግ ቢፈቀድለት ህወሓት በትግራይ ይመረጣል የሚል እምነት የለኝም። ለምን ብትል እኛ በተለያዩ ቦታዎች ተዟዙረን ህዝቡን በደንብ አናግረናል። በሄድንበት የትግራይ አካባቢ በሙሉ ግን ተቃዋሚ አለ። ህዝቡ እኛን እንደሚደግፍ እየገለፀልን ነው። ነገር ግን ህዝቡ የሚጠራጠረው ‘እኛ ሰው እንፈልጋለን ነገር ግን ህወሓት በምርጫ ቢሸነፍ ስልጣን ያስረክባል የሚል ግምት የለንም። እናንተን ሆነ ሌሎች ተቃዋሚዎችን ያፍናል። ከዚህ በባሰ መልኩም ሊያጠፋችሁ ይችላል። በተለይ ለዲሞክራሲያዊ አሰራር ዕድል መሆኑን ስለምናውቅ በዚህ መንገድ ለውጥ ለመምጣቱ እርግጠኞች አይደለንም’ እያሉ ነው ያሉት። ስለዚህ እኔ ከዚህ ሃሳብ የወሰድኩት ከሌሎች ግምት በተቃራኒው አፈናው በትግራይ የባሰ መሆኑን ለማሳየት ነው። ይብዛም ይነስ በሌሎች አካባቢዎች እኮ ሰላማዊ ሰልፍ እየተፈቀደ ነው። በትግራይ ግን ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ መሰብሰብ እንኳን እየተከለከለ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- አፈናው ባይበዛ በትግራይ ተቃዋሚዎች በብዛት ይኖሩ ነበር ብለህ ታስባለህ?

አብርሃ ደስታ፡- በየትኛውም የትግራይ አካባቢ ከተወሰኑ ካድሬዎች በቀር ህወሓትን የሚደግፍ የለም። ጥቂት ደጋፊዎችን ፖሊስንና መከላከያውን ይዞ ነው ህዝቡን በዘዴ የሚያቀናው እንጂ እንደ ህዝብ የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ ነው የሚለው ለእኔ አሁን የማይሰራ ሃሳብ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመደመር ህወሓት/ኢህኣዴግ እስከ 40 ዓመት በስልጣን መቆየት እንዳለበት እየተናገረ ነው።

አብርሃ ደስታ፡- ህወሓት ገና 50 ዓመት ይገዛል የሚለውን ነገር በትግራይ አዘውትረው በአደባባይ የሚናገሩት ነው። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እንዲህ ያለው አቋም የተሳሳተ ነው። በእርግጥ የእነርሱ ኋይማኖት በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ነገር ብቻ ማድረግ ነው። ልማት ያለ ዲሞክራሲ አይመጣም። ልማትን የሚያመጣው መንግስት ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ነው። ህዝቡ የልማቱ አምጪ እስከሆነ ድረስ በሙሉ ነፃነት ህዝቡ መስራት፤ በማንኛውም ቦታ በእኩልነት የመታየት መብቱ መከበርና ሰው በስራው እንጂ በሌላ አመለካከት መገምገሙ መቆም አለበት። ይሄ ነገር እስካልመጣ ድረስ ዘላቂ ልማት አይኖርም።አሁን ባለው ሁኔታ እንኳን ለውጥ ሊመጣ ቀርቶ ለውጡ እንዳለ እንኳን ለመቆየት የሚችል አይደለም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ህወሓትን ለረጅም ዓመታት ከመግዘት የሚያግደው ምንድን ነው?

አብርሃ ደስታ፡- ህወሓት በከፍተኛ ደረጃ በሙስና የበሰበሰ ነው። እንኳን በውጪው ህዝብ ይቅርና በራሱ ውስጥ እንኳን በጣም ብዙ ቅሬታዎች አሉ። በዚህ መሰረት ህወሓት ጊዜ ቢሰጠውም ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ሙስናና አድልዎ በቡድኑ ውስጥ ተበራክቷል። በህዝቡም ያለው ተቀባይነት ዝቅ በማለቱ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየቀነሰ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- የተለያዩ ሰዎች በህወሓት የተነሳ የትግራይ ህዝብ በሃብት ክፍፍሉ የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ ያምናሉ።

አብርሃ ደስታ፡- ምን አለ መሰለህ። በእርግጥ በህወሓት የስልጣን ዘመን እየበለፀጉ ያሉ ግለሰቦች አሉ። ነገር ግን እነዚህ የበለፀጉ ግለሰቦች ለባለስልጣነቱ የቅርብ የስጋ ዝምድና ያላቸው ናቸው። ወይም ራሳቸው ባለስልጣናቱ ናቸው። በመሆኑም በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች እነዚህ ትግርኛ ተናጋሪዎች ፎቅ ሲገነቡ ወይም የተለያዩ ቢዝነሶችን ሲሰሩ እያዩ የትግራይ ተወላጆች ሃብታም እየሆኑ ነው ብለው ቢናገሩ አይፈረድባቸውም። ምክንያቱም እነማን መሆናቸውን አያውቁም። ከዚህ ውጪ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በድህነት ውስጥ ስለመኖሩም መረጃ ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በድኅነት እየኖረ የባለስልጣናት ዘመዶች ሃብት እየሰበሰቡ መሆናቸውን በደንብ የምናውቀው እኛ የትግራይ ሰዎች ነን። በሌላ ቦታ በአማራ፣ በኦሮሚያም ሆነ በሌላው ክልል ሃብት የሚሰበሰብ ትግርኛ ተናጋሪ ብታይ አንተም የትግራይ ሰው ሃብት እያካበተ ነው የሚል ሃሳብ ልታዳብር ትችላለህ። በመሆኑም የሌላው ክልል ነዋሪ እንዲህ በማለቱ ሊፈረድበት አይገባም። ጉዳዩን በሚገባ ማስረዳት የሚኖርብንም እኛው የትግራይ ህዝቦች ነን። ባለስልጣናቱና ዘመዶቻቸው ከህዝብ የተሰጣቸውን ሃላፊነት አላግባብ በመጠቀም ሃብት እየሰበሰቡ መሆናቸውን ማጋለጥ ያለብን እኛው የትግራይ ሰዎች ነን።

አዲስ ጉዳይ፡- ህወሓት በኢኮኖሚው ላይ በበርካታ ድርጅቶች መሳተፉ፣ የደህንነት ኃይሉን መጠቀሙና ነፃ ሚዲያውንም ማዳከሙ ለሰላማዊ ትግሉ ተስፋ አስቆራጭ ነው የሚል ሃሳብ ይነሳል . . .

አብርሃ ደስታ፡- እውነት ነው። እንደተባለው ህወሓት ኢኮኖሚውን በስፋት መቆጣጠሩ ሚዲያውንም መቆጣጠሩ ወይም የግል ሚዲያውን አለመፈለጉ፤ በሰላማዊ ትግሉ ላይ እንቅፋት ይፈጥራል። ነገር ግን እንቅፋት ስለሚፈጥር፤ መንግስት አፋኝ በመሆኑ እና ለሰላማዊ ትግሉ በሩን በመዝጋቱ የተነሳ ተቃውሞ እንዳስፈለገ መታወቅ አለበት። እኛም እየተቃወምን ያለነው ይህንኑ አካሄድ ነው። እኛ እንደምናምነው ሚዲያውን ስለተቆጣጠረ፣ ህዝቡን ስላፈነ የሰላማዊ ትግል መንገድ ችግር ሊያደርስበት ይችላል እንጂ ሊያስቆመው አይችልም። ህዝቡ ለውጥ እስከፈለገ ድረስ መንግስት የፈለገውን አፈና ቢያካሂድ አስፈላጊን መስዋዕትነት በመክፈል ህዝቡን እያደራጀንና እያስተማርን ለውጥ ማምጣት ይቻለናል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

አዲስ ጉዳይ፡- የህወሓት ምስረታ ሲታሰብ የተለያዩ መስዋዕትነት የከፈሉ ታጋዮች ስማቸው አብሮ ይነሳል። አንተ በግልህ መስዋዕት የሆኑት ታጋዮች ዓላማ ዳር ደርሷል ትላለህ?

አብርሃ ደስታ፡- ይሄ ነገር ሲነሳ ጉዳዩን በጥንቃቄ በሁለት ከፍለን ማየት ይኖርብናል። የመሪዎቹ ዓላማ ስልጣን መያዝ ነበረ ብዬ ነው የማምነው። የእኛ ወላጆች ዓላማ ግን ነፃነት ነበር። ስለዚህ ለእኔ የትግሉ ዓላማ አልተሳካም ባይ ነኝ። ምክንያቱ ደግሞ የታጋዮቹ ዓላማ ለሰው ነፃነትን ማምጣት ነበር። አሁን ግን ነፃነት የለም። አፈና ነው ያለው። ስለዚህ የታጋይ ወላጆቻችን ዓላማ ህዝቡን ለማፈን እስካልነበረ ድረስ ዓላማው አልተሳካም የሚል እምነት ነው ያለኝ።

አዲስ ጉዳይ፡- የትግራይ ህዝብ እና የህወሓት መሪዎች በኤርትራ መገንጠልም ሆነ በኢትዮጵያዊ ህብረብሄራዊ ስሜት የተለያየ አቋም ያላቸው መሆኑ ይነገራል። እውነት ነው?

አብርሃ ደስታ፡- አዎ! የህወሓት መሪዎች ዓላማ ኤርትራን ማስገንጠልን የሚጨምር ነበር። ይሄን አቋማቸውን ደግሞ የተለያዩ ዶክመንቶች ጭምር ይመሰክሩታል። ህዝቡም ሆነ ታጋዮቹ ግን የኤርትራን መገንጠል የሚደግፉ አልነበሩም። ይሄን የህወሓት ኤርትራን ማስገንጠል ዓላማ የማይደግፉ ታጋዮች ሲገኙ ይቀጡ እና ይባረሩ ነበር። በተለይ ለኤርትራ ህዝብ ባርነት ወይስ ነፃነት የሚል ሪፈረንደም ሲቀርብ ብዙ ታጋዮች ተቃውመውታል። ይህ የህወሓት አመራር ድጋፍ ያለውን ሃሳብ በመቃወማቸው፤ የአሰብ ወደብ ጉዳይንና የዲሞክራሲ ጥያቄን በማንሳታቸው ባንድ ጊዜ ወደ 32 ሺኅ የሚጠጉ ታጋዮች ከህወሓት ተባረዋል። ከእነዚህ ውስጥ የታሰሩም የተገደሉም አሉ።

አዲስ ጉዳይ፡- ህወሓት የኢትዮጵያን የባህር በር አስነጥቋል ብለህ ታምናለህ?

አብርሃ ደስታ፡- አዎ! በትክክል አስነጥቋል ነው የምለው። ህወሓት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ምክንያት ሆኗል።

አዲስ ጉዳይ፡- የህወሓት አመራሮች የአማራ ህዝብን ከገዢው መደብ ጋር ደብሎ በመሳል የብሄር ጥላቻ እንዲከሰት አድርገዋል ተብለው ይተቻሉ። አንተ ምን ትላለህ?

አብርሃ ደስታ፡- የህወሓት አመራሮች የአማራ ህዝብን ከገዢው መደብ ጋር አንድ አለመሆኑን ያውቃሉ። ነገር ግን ሆን ብለው ህዝቡንና ገዢ መደብን አንድ አድርገው የሚያቀርቡት ደግሞ ህዝቡ ተባብሮ በአንድ ላይ መቆም ከቻለ ለስልጣናቸው ስለሚያሰጋቸው ጭምር ነው። ይህ ዓይነቱ አቋም ደግሞ ከድሮም ጀምሮ የሚያራምዱት ነው። እኛ ልጆች ሆነን የሚነገረን ደርግ ማለት አማራ ማለት ነው ተብሎ ነበር። አማራ ማለት ደግሞ ደርግ ነው። በመሆኑም አማራ ገዢና ጨቋኝ ነው የሚሉ ነገሮች ናቸው። እስካሁን ድረስ ፀረ አማራ የሆኑ ዘፈኖች አሉ። ምክንያቱም ፀረ አማራ ማለት ፀረ ደርግ እንደማለት ስለነበር ነው። ይህ አስተሳሰብ የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ እንጂ የትግራይ ህዝብ በሙሉ ህወሓት አለመሆኑ እንደሚታወቅ ሁሉ የደርግ ስርዓት እና የአማራው ህዝብ አንድ አለመሆናቸው ይታወቃል። እነርሱ ግን ይሄን ይጠቀሙበታል፣ ከስልጣን በላይ የሚያስቡት ነገር ስለሌለ ማለቴ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- ያለህበት አረና ፓርቲ በትግራይ ውጤታማ የሚሆን ይመስልሃል?

አብርሃ ደስታ፡- በእርግጥ ብዙ አፈናዎች እየተካሄዱ ነው። ህዝቡን ለማወያየት ስንሞክር ስብሰባ እየተሰረዘብን፤ ከዚያም አልፎ ድብደባ እየደረሰብን ነው። ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ ለውጥ እንደሚፈልግ ለእኛ ተስፋ ስጥቶናል። በመሆኑም እኛ ውጤታማ እንሆናለን ብዬ ነው የማስበው።

አዲስ ጉዳይ፡- አቶ ስብሃት ነጋ ‘‘አረናዎች የተቆጡ ህወሓቶች ናቸው’’ የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል። በእርግጥ አረና ህወሓት ነው?

አብርሃ ደስታ፡- አረናን እንደ ፓርቲ ከህወሓት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ነገር ግን ጥቂት የቀድሞ የህወሓት ሰዎች ወደ አረና ስለገቡ በቂም ተበሳጭተው ነው በሚል ነገር ያነሳሉ። እነዚህ ሰዎች በእርግጥ ህወሓት ነበሩ። ነገር ግን ህወሓት ችግር እንዳለበት ሲረዱ ከፓርቲው በመውጣት አረና የተሻለ አካሄድ እንዳለው ሲረዱ የእኛን ፓርቲ ተቀላቀሉ። ከዚህ ውጪ ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምም ሆነ ከአሰራር አንፃር በዓረናና ህወሓት መካከል ብዙ ልዩነቶች አሉ።

አዲስ ጉዳይ፡- ልዩነታችሁን በምሳሌ ልታስደግፍ ትችላለህ?

አብርሃ ደስታ፡- ለምሳሌ በእኛ ፓርቲ ውስጥ ማዕከላዊ ዲሞክራሲያዊነት ብሎ ነገር የለም። ሌሎች አካሄዶቻችንም በስፋት ከህወሓት የሚለዩ ናቸው። እነርሱ ወደ ኃይል እርምጃ የገቡት እኮ ለህዝቡ የእኛን አቅጣጫ በዝርዝር ስናስቀምጥ ጎልቶ በወጣው ልዩነት የተነሳ ነው። ስለዚህ ህወሓት ለስልጣን የሚቀናቀነውን ማንኛውንም ፓርቲ ማጥላላት ልማዱ ነው። ይህንን እኛም ስለምናውቀው ከህወሓቶች ለሚሰነዘር አስተያየት እኛ ያን ያህልም የምንጨነቅበት ጉዳይ አይሆንም።

አዲስ ጉዳይ፡- ህወሃት በትግራይ ወይም ኢህአዴግ በኢትዮጵያ በምርጫ ስልጣን የሚለቅ ይመስልሃል?

አብርሃ ደስታ፡- ህዝቡን መቀየር ከቻልንና ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለን ህዝቡን ካስተባበርን በምርጫ ፓርቲው ስልጣን ሊለቅ ይችላል። በእርግጥ ፓርቲው በምርጫ ስልጣን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አይደለም። የፈለገውን ያህል ኀይል ተጠቅሞ ህወሓት በስልጣን ላይ ለመቆየት እንደሚፈልግ ይታወቃል። ነገር ግን በምርጫ ተቀጥቶ ስልጣን እንዲለቅ ማስገደድ ይቻላል። ምርጫውን የሚሰርቅበት መዋቅሩን በማሳጣት ለህዝብ ድምፅ የሚንበረከክበት ዕድል አሁንም አለ።

10 Comments

  1. Recently, zehabesha appealed to its readers for financial support in order to upgrade the level of their journalism as well as the technical capability of the webpage. in spite of their dedication, I was not get convinced in order to respond to their appeal and contribute my part. Why? In simple words, I was unable to detect what their vision and strategy is. Honestly speaking, I am not sure what zehabesha want to achieve.

    Sadly to tale, zehabesha editors are still either naïve or ignorant to detect those secret woyane sympathizers like Abraha Desta. In a land where many Oromos and amhara journalists get murdered, how on earth such a man managed to stay as “a strong anti woyane and anti establishment” vocal in Mekele and able to produce a timely opposition journalism unless he himself is a secret TPLF? For me, Abraha Desta is analogues to Tesfaye Gebreab. Both have camouflaged their agenda and are skillfully manipulating the rest of the populace including zehabesha. I wish I would be wrong.

  2. ‘uu’_ ተ.ቁ 1 ላይ የተናገርከዉ ባለአስተያየት ልክ ሊሆን ይችላል:: ልክ ነህ ብዬም ልዉሰድ:: የዘሃበሻ ጥፋት ታዲያ ምኑ ላይ ነው? ይህች ድረገፅ እንደብዙዎቹ ድረገፆችና እንደወያኔ ወናፍ የዉሸት ቱሪናፋ ሚዲያ በአንድ ቅኝት እንዲዘፍን ትሻለህ ማለት ነው? የተለያዩ ሃሳቦች የሚስተናገዱበት የጋራ መድረክ ከሌለን ጫፎች; ጫፎች እንደሆኑ እንደሚቀሩ አታዉቅም? እባክህን ወንድሜ ዴሞክራሲ ማለት የሚጠሉትንም ለመዉደድ ካልተቻለም ተቻችሎ ለመኖር መሞከር መሆኑን አትርሳ:: ‘እገሌን አታሳዩኝ_ ስለእገሌ አታሰሙኝ!’ ማለት ወያኔያዊ አምባገነንነት ወይም ካለመማር የሚመነጭ ድንቁርና እንጂ ከተማረና ከሰለጠነ ሰዉ አይጠበቅም:: አንተ እንደዚያ ነህ ለማለት ፈልጌ አይደለም:: ተናደህ ሊሆን እንደሚችል ብጠረጥር እመርጣለሁ:: ደግሞም ሃሳብን በሃሳብ ተጋፈጥ እንጂ አቅጣጫ አትቀይር_ ዘሃበሻን አትርዱን ምን አመጣዉ? አንተ ስትፈልግ አትርዳ – አፍንጫህን ይዘዉ የሚያስገድዱህም አይመሰለኝም:: ሌላ ተልእኮ ይኖርህ ይሆን?
    በተረፈ (ከነ)አብርሃ ደስታ ጋር ከነልዩነታችን እየተማማርን ብንቀጥልና ከዘረኝነትና ከአምባገነንነት ነፃ የወጣች ሀገር ብንመሰርት የትግሉን ዘመን ያሳጥረዋል እንጂ ክፋት የለዉም:: አ.ደ ከአንዳንድ ምናልባትም ከርሱ ግንዛቤ ዉጪ የሆኑ ወያኔያዊ የዘረኝነት ጭቆናዎችን ለመግለጥ ‘ይለፈኝ’ ከማለቱ ዉጪ ግሩም የህዝብ ልጅ ነዉ:: ለምን አልታሰረም ብሎ መቆጨትም የጤናማነት ምልክት አይመስለኝም _ ከኔ ወገን ይህ አይነት አስተያየት ይሰነዘራል ብዬም አላስብም:: ተመስገን ደሳለኝና ሌሎቹ 22 ገደማ የሚሆኑ የፋክት መፅ. ፀሀፊዎችስ ታስረዋል እንዴ? ‘uu’ ማን ነህ?
    ዘሃበሻ ባይሆን ዘርን ከዘር ለማናከስ የሚጥሩ ወያኔያዊ አስተያየተኞች ሃይ በሉልን:: ይታወቃሉ::

  3. uu
    shall i suggest for you to go and join high school? There in case u will find some info on the what about of free media—

  4. Uu is a nameless stj pid woyanne who seemingly sympathizes but is a venomous divisive, hate-monger stupid guy. Go to hell stupid. You are trying to question our beautiful informant Ze Habesha by your capability to fund? Stop yhat dirty work you sre doing and go to school and learn to read and think.
    Well-done Zehabesha. Go on with your job. Forget such garbage as that name fits better to him for he is nameless evil.

  5. Response to AAbraha De
    ከጌታቸው ረዳ (ኢትዮፕያን ሰማይ ብሎግ አዘጋጅ)
    አንዳንድ ትችቶች ለአብርሃ ደስታ፡

    “ይሄ ነገር ሲነሳ ጉዳዩን በጥንቃቄ በሁለት ከፍለን ማየት ይኖርብናል።የመሪዎቹ ዓላማ ስልጣን መያዝ ነበረ ብዬ ነው የማምነው። የእኛ ወላጆች ዓላማ ግን ነፃነት ነበር።” ይላል አብርሃ ደስታ;

    ይህንን ሰፋ ባለ ልተንትነው። እርግጥ የነበረው የደርግ ሥረርዓት እንኳን ምድራዊ ሰው ‘ባሕታዊንም” ጭምር ወደ ጫካ የሚያስኬድ ሥርዓት ነበርና የትግራይ ታጋዮች ወደ በረሃ ሲወጡ ለነፃነት ነበር የወጡት ብለን አንቀበለው።፡ ምንም አንኳ ለነፃነት ብለው ይዋጉ አንጂ፤ አብዛኛዎቹ በረሃ ሲወጡ የተለያየ መነሻ አድርገው ነበር የወጡት (ሥራ ያጣውንም….ተገድደው የታጠቁትንም፤ ትግራይ ዓደይ ቀንይለይ፤ ሃብኒ ሓምባረይ ……የሚለውን ሙዚቃ እያዳመጠ ወደ ጫካ የከነፈውንም….ወዘተ…ወዘተ… ጭምር ማለት ነው)። በዚህ እንለፈው።

    የግድ አንድ ወጥ ምክንያት ይኑረው አይባልም እና አንድ ወጥ የሆነ ምክንያት ስላልነበረው፤ ወያኔዎች ባዘጋጁለት ወጥመድ በቀላሉ ገባ። “ጸረ አማራ” ወጥመድ ውስጥ! ማለቴ ነው። አብርሃ ደስታ ‘ደርግ እና አማራ” አመሳሰለው ቅባት ቀብተው ‘አታገሉት’ የሚለው ትንተናው ልክ ቢሆንም። አብርሃ በዚህ ብቻ መደረቱ (መወሰኑ) ግን የወያኔን ማንንት እና አጀንዳቸው ደርቶአቸዋል (ወስኖአቸዋል)። ስለሆነም፤ “ለስልጣን ብቻ እንዲጠቀሙበት ብለው ያመጡት ዘዴ ነው” የሚለው የአብርሃ መደምደሚያ አድርሶናል ማለት ነው። እስኪ ሰፋ ላድርገው።

    ‘ወያኔዎች” የነደፉት መመሪያ ስንመለከት፤ ከዚያ በፊት ማለትም ‘ደርግ’ ከመከሰቱ በፊት የነበረው ታሪክ ማየት ያስፈልጋል። ትግራይ ከአማራ አገዛዝ ነፃ መውጣት አለብን ብለው የጀመሩት ወያኔዎች ብቻ አልነበሩም እና ለነሱ ብቻ መስጠቱ መነጽሩ ሙሉ አያደርገውም።

    ሦስት ምዕራፎችን እንመለከታለን
    (1) ሥልጣን ከትግራይ ወደ ሸዋዎቹ መዛወሩ (በምኒልክ ጊዜ እነ አሉላም ሆኑ የመሳሰሉት የተናገሯቸው ንግግሮች። ምኒልክ መቀሌ መጥተው በነበሩበት ወቅት (ራስ መኮንን ከጣሊያን አገር በኤርትራ በኩል ሲመጡ የትግራይ መኳንንት እና ጦር ራስ መኮንን/ን ዓጋሜ አካባቢ ተቀብለዋቸው አጅበዋቸው ወደ መቀሌ ሲያመሩ መሶበ ዳገት (መቀሌ ጫፍ ከተማ) ሲደርሱ ከምኒልክ ወደ መሰቦ የታለኩ ጦር ጋር ሲገናኙ የተዘገቡ የጥላቻ ስሜቶች) የትግሬዎች ቅሬታ/ስልጣን ወደ ሸዋ የመዞሩ ሃዘን፤

    (2) በ1935/36 ሃይለስላሴ ሠራዊት (ኢትዮጵያ ሠራዊት) እና በሃይለማርያም ረዳ (በወያኔዎች ሠራዊት) የተደረጉ ግጭቶች በተወሰኑ አውራጃዎች ብቻ የተደገፈ ቢሆንም እና ለአመጹ ብዙ ምክንያቶች የተሰነዘሩ ቢሆንም፤ ዞሮ ዞሮ የተደመደመው “በአማራ እና በትግሬ የተደረገ ጦርነት ተመስሎ በብዙ ትግሬዎች ኣእምሮ እንዲቀረጽ በመደረጉ በአማራዎች አንገዛም ብለው ያደረጉት የአመጽ ጦርነት ሆኖ መታየቱ ነው። በአማራ እና በትግሬ ብቻ ሳይሆን በአማራ ቅኝ ገዢ ኮሎኒያሊስቶች ትግሬ መገዛቷ መሆኑ በሰፊው እስካሁንም እየነገሩን ነው።

    በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ልጀምር

    “በጣሊያን ወረራ ጊዜ የትግራይ ሕዝብ ከማንኛቸውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የበለጠ መስዋእት ከፍሏል። እኛም ለአገሩ ነፃነት ሲል ብዙ መስዋእትነት የከፈለ ሕዝብ ሲበደል እናይ ስለነበርን “ሕዝብ እየተበደለ ነው፤ ብለን ለመንግስት እናመለክት ነበር። ሆኖም ሰሚ አላገኘንም” (ትግርኛ መጽሔት ጥሕሎ ግንቦት 2001 ቅጽ 1 ቁ/8 ) ትርጉም ጌታቸው ረዳ። ሉኡሉ ከማንኛቸውም ገዢዎች ዘመናይ መስፍን በመሆን ብዙ የሚመሰገን ልማት የሰሩ ቢሆንም፤ ባኢሳቸው አስተዳዳር የተደረገው በደል ግን አልነገሩንም። ለምን በማአከላዊ መንግስት ማስታከክ ብቻ?
    አሁን ወደ አስደንጋጩ መጽሐፍ ልውሰዳችሁ፡

    ቀዳማይ ወያነ ደራሲ የማነ ገብረመስቀል 2005 ዓ.ም በገጽ 71 -72 እንዲህ ይላል በትግርኛ፡(ተረጓሚው እኔው ጌታቸው ረዳ)

    “ የትግራይ ሕዝብ (ከጣሊያን በሗላ) ያገኘው ‘ነፃነት’፤ ብልን የምንጠራው ‘ተገኘ የተባለው ‘ነፃነት’ በነጭ የባዕድ ወታደሮች ሲገዛ ቆይቶ፤ ባዕድ የሆነ አጋረዊ በሆነ ጥቁር (አበሻ) ወታደር መገዛት በመቻሉ ብቻ ነው። ልዩነቱ ያ ነጭ ነው ያ ደግሞ ነጭ ነው። ልዩነቱ የቀለም ብቻ ብቻ እንጂ ሁለቱም ለትግራይ ሕዝብ ባዕድ ወራሪዎች ናቸው። በሌላ አነጋገር ባኢድ የሆነው የፋሺስቱ ጣሊያን ቀጠልያ/አረንጓዴ ነጭ፤ቀይ ቀለም ባንዴራ ከተሰቀለቺው ወርዳ ‘በቀጠልያ፤ቢጫ እና ቀይ’ ቀለም እማሃሏ ዘውድ የደፋ የይሁዳ አንበሳ ምልክት የላት ባንዴራ የተተካች መሆኗ ብቻ ነው ልዩነቱ፡

    እሷም ቢሆን የሸዋ ገዢ መደቦች ከፈጣሪ የተሰጠቻቸው ሰማያዊ ፀጋቸው እንጂ ለእኩልነት ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ብሄር፤ብሄረሰቦች የማትወክል የገዢዎቻችን ባንዴራ ነች” ቀዳማይ ወያነ ደራሲ የማነ ገብረመስቀል 2005 ዓ.ም በገጽ 71 -72 እንዲህ ይላል በትግርኛ፡(ተረጓሚው እራሴ ጌታቸው ረዳ) ይህ መጽሐፍ ከ4 አመት በፊት ነው የታተመው።

    (3) ዳግማይ ወያኔ!!!!!!

    ይህንን ሁሉ በማጠቃለል ወደ ሦስተኛ ምዕራፍ የተሸጋገረው የአንደኛ እና የሁለተኛ አማራ እና ትግሬ ስሜት ትግል (ፌዝ/ደረጃ)፦ ስንመለከት ዳ’ግማይ ወያነ’ ን ወለደ።በ 1967 ዓ.ም በማመጽ ወደ በረሃ ገብቶ ይህንን ይዞ ብቅ አለ፦ ”

    ላሳጥረው እና ላጠቃልል።

    በ1968 (የካቲት 18) የታተመ መጸሔታቸው ደግሞ በግልጽ እንደተቀመጠው አጠቃላይ የህወሀት አላማ እና መድረሻ

    “የጨቋኟ አማራ ብሄርን” ጭቆና ለማስወገድ እና ከዚያም “የትግራይ ሪፓብሊክ ማቋቋም ነው።” “ ህዝቡ (የትግራይ ሕዝብ) በኢትዮጵያዊነቱ አያምንም በሃይል ተይዞ ለዘመናት በአንድነት የቆየ ነው። ስለሆነም አሁን ባለው የህብረት መልክ ትግል ማካሄድ ‘ምኞትና የትምክህተኞች ሕልም ነው። (መግለጫ ት.ህ.ነ.አ.ድ የመጀመሪያ እትም ገጽXI) (የወያኔ ገበና መህደር ገጽ 25 (ጌታቸው ረዳ)

    “ጨቋንዋ ብሔር (አማራ) የ3 ሺሕ አመት የሚያኮራ ታሪካችን መመኪያቸው እና መፎከሪያቸው ሆኖ ይገኛል። ስለዚህም የሰረቀቺውን የትግራይ ታሪክ ለባለቤቱ ለትግራይ ብሔር እስካልመለሰች ድረስ ሰላም አታገኝም እንታገላታለን” (ምንጭ እንደላይኛው)

    በዚህ ላይ ተተንተርሰው ሰፊ ትንተና አድርገዋል። ስለዚህም አብራሃ ደስታ የሚለው ከሞላ ጎደል ትክክል እንኳ ቢሆን እና ብስማማም፤ እሱ እንደደረተው “በደረግ የተቀባ አማራነት” ብቻ አልነበረም የተጠቀሙት። አርግጥ ለማታገል ባይናቸው የያዩትን ሥርዓት አስታክኮ ማታገል ቀልሎአቸው እንደሆነ እንጂ – የሰጡት ትምህርት ግን ከደርግ ያለፈ ወደ ሗላ ዘመን የሚጎትት ቅስቀሳ እና ጥላቻ ነበር። ስለዚህም የትግራይ ሕዝብ አማራን በጥላቻ የመመልከቱ ሁኔታ ‘አሌ’ የማይባል ፤በቀላሉ አሳንሶ የሚታይ አልነበረም፤ አይደለምም። (Identity Jilted) መጽሐፍን ይመልከቱ። ደርግ የትግራይ ጠላት ነው ለማት ወደ አማራነት የሚያስኬዳቸው አባዜ አልነበረም። በደፈናው ደርግ ያለ ነጋሪ ጨቋኝ እና ሕዝቡ በቀላሉ (ያለ ጥላቻ ቅስቀሳ) መታገል የሚችል ስለነበር፤ ወደ ደርግ የሚያዞራቸው አንዳች ነገር አልነበረም። አብርሃ በወቅቱ ልጅ የነበረ ቢሆንም፤አዋቂ ሆኖ የትልቅ ተቓም ዩኒቨርሲቲ መምህር ሆኖ “በደርግ እና በአማራ” ብቻ የተደረገ ትምህርታዊ ዘመቻ እንዳልሆነ ማወቅ ነበረበት።
    ‘መነሻቸው ጸረ አማራ አጀንዳቸው ለማካሄድ አንጂ አብርሃ አንደሚለው “ሥልጣን ብቻ ለመያዝ አልነበረም”። ምክንያቱም ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ወዲያም ቅስቀሳቸው እና ድርጊታቸው በፍጹም “ለሥልጣን የሚያደርጉት ፍለጎትና ጉጉት በጣም የተለየ ነው። የየማነ ገብረመስቀል፤ የነ ገብረኪዳን፤የነ ሙሉጌታ፤ ደባልቀው….የነ አለምሰገድ ……መጽሐፍቶች. የነስብሓት ተከታታይ ግልጽ ያልተሸሸጉ ንግግሮች እና አላማወዎችን ወዘተ…. መመርመር ነው። አገር የማፈራረስ አመራን የማስጥላት አጀንዳ ነው (የዘር ማጥፋት ዘመቻው በተግባር እየተካሄደ ነው)። ስለዚህ ደርግ እና አማራ አቀባብተው ለስልጣን መወጣጫ ነው ቅስቀሳውን የተጠቀሙት ብሎ የሚባለው የአብርሃ ደስታ አገላለጽ ‘ውሱን” ነው “ማሳነስ ነው”።

    አብርሃ ይቀጥል እና

    “ስለዚህ የታጋይ ወላጆቻችን ዓላማ ህዝቡን ለማፈን እስካልነበረ ድረስ ዓላማው አልተሳካም የሚል እምነት ነው ያለኝ።” ይላል።

    ባንዳንዶቹ ሊሆን ይችል ይሆናል። ባጠቃላይ ግን “ታጋዩ” ሕዝቡን አፍኖ ረግጦ መፈናፈኛ አድረጎት እንደነበር ነው ታጋዮቻቸው የሚነግሩን። እኔም ያየሁት ታጋዩ በወያኔ መንፈስ የሚመራ ‘አድርግ የተባለውን የሚያደርግ ነበር” እያፈነም እየገደለም፤ ማለት ነው። ማንኛውም ታጣቂ ለሕዝብ ብሎ ይናገር እንጂ ‘በረሃም ሆነ በመንግሥት ሥር ሆኖ ድርጊቱ እና አፈጻጸሙ የባለዩን ብቻ የሚፈጽም ዓይን የሌለው ጋሪ ነው። የታጋዩ መነሻ እና መድረሻ አብርሃ እንደምትለው ሳይሆን (ጥቂቶች ሊኖሩ ይችላሉ) “የተመራው ወያኔ በሰጠው አጀንዳ ነበር።” ለዚህም ነው ከጎነድር (ደብረታቦር )ወደ ወሎ ደግሞ እስከ አለውሃ ምላሽ” ድረስ ነፃ ካወጡት በሗላ “የኛ ጉዳይ አይደለም “ሁሉም የየብሔሩ ነፃ ያውጣ ብሎ እምቢ ብሎ ሳይንቀሳቀስ “አንድ አመት የቆየው። “ደውታ” ይባላል፤ (እንግሊዝኛው ፖዝ የሚባለው)። ከውይይት በሗላ ነው ወደ አዲስ አበባ መገስገስ የጀመረው። ለነጻነት ብሎ ከታገለ፤ ለየትኛው ነፃነት? ለትግራይ (ተሰምራ በቆዳ ስፋት የተሰጠቺው የትግራይ ካርታ) ወይስ ለመላይቱ አገራችን? እንደዚያ ከሆነ፤ ለምን አንንቀሳቀስም ብለው “የደውታ አድማ/ የገታ/’የቆም በል’ አድማ ተደረገ?

    በመጨረሻ አብርሃ እንዲህ ይላል።

    “ይህ አስተሳሰብ የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ እንጂ የትግራይ ህዝብ በሙሉ ህወሓት አለመሆኑ እንደሚታወቅ ሁሉ የደርግ ስርዓት እና የአማራው ህዝብ አንድ አለመሆናቸው ይታወቃል። እነርሱ ግን ይሄን ይጠቀሙበታል፣ ከስልጣን በላይ የሚያስቡት ነገር ስለሌለ ማለቴ ነው።” ይላል አብርሃ፡

    እስኪ በጋህዲ ደራሲ በአረናው አባል በአስገደ ገብረስላሴ መጽሐፍ ልጀምር፡፤

    “ኢሕአፓ በአጋሜ አውራጃ ውስጥ በአሰፈ ሰበያ እና በወረዳ ጉሎ ሞኾዳ በወያኔ ትግራይ የጠባብ ጨረታ አሸናፊነት ተበልጦ ከትሉ ከወጣ በሗላ፤ የጠባብ ብሔረተኛነት በሽታ በመላዋ ትግራይ እንደ ተላላፊ በሽታ ተስፋፍቶ ወደ ሕዝቡ በመተላለፍ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ፀረ አማራ ተንቀሳቀሰ።” ( ጋህዲ ቀ/2 ገ9ኢ 155 የትግርኛ ቅጂ 2001) (ትርጉም ጌታቸው ረዳ ይድረስ ለጎጠኛው መምህር ገጽ 17 ደራሲ ጌታቸው ረዳ)

    ከትግራይ ጭቆናም ሆነ ከማንም ነፃ ለማውጣት ተዋጊም ሆነ ተወካይ ቡድን ያልነበረው የአማራ ሕዝብ እና “ አማራ” ገዢዎች የሚሏቸው” (በምን፤ በደም፤በውክልና? በምን መሰረት ገዢዎች የተባሉ አማራዎች አንደሆኑ አልገለጹልንም) እንዲሁም ትግራይን ወክሎ ጸረ አማራ የተንቀሳቀሰ ተዋጊ ቡድን እና ሕዝብ የነበረው ድርጅት”፤በመን ተገናኝተው ነው፤ ’ያኛው እና ይኼኛው’ እየተባለ ለመልስም ለማነጻጸርም የሚቀርብ? ይገርመኛል እኔ።
    ይህነን አንዴት እናጣጥመው? በጸረ አማራ የተመረዘው ሕዝብ የአማራ ጥላቻው ለቆታል ከተባለስ “ከመቸ ጀምሮ ነው ተላላፊው በሽታ የተገላገለው/የታከመው? አመተ ምህረቱን ቢገለጽልን! ሕዝብ ስንል እኮ በማንኛውም ታሪክ ሁሉም በነቂስ አይደግፍም፤አይተኛም፤አይዋጋም፤ አይባልም፤ሥራ አያገኝም፤ አይሞትም፤አይስቅም፤አይዘፍንም፤አይጨፍርም፤ በሙሉ የሚባለው ትርጉም በተለምዶ ስለሆነ እንጂ በሙሉ ሳይሆን ባብዛኛው ተጠቃሚ ሲሆን ማለት ነው (ለዓይን የሚታይ)። ይህ ዶግማ/ሂፕክርት የቃላት ጨዋታ ባንጠቀም ጥሩ ነው።የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ ነው ስንል ብዙው የትግራይ ተወላጅ ‘አዎ ተጠቃሚ ነው”። ትግራይ ውስጥ የተተከከሉት ኢንፍራስትራክቸሩን እና ሱፕራስትራክቸሩን በምን መልኩ እነደተገነባ ማየት ነው። The pillage of Ethiopia by Dr. Assefa Negash ያንብቡ። እውነታው እዛው ያገኙታል።ምናለ ባታደክሙን ጃል!!!!!!

    ይህ ሁሉ ውጭ የሚኖር ትግሬ የወያኔ አስተዳዳር ስለተቃወመ ነው እንደ አሸን ባንዴ የጎረፈው? በየ ፓልቶኩ የጎጃም እና የጎንደር አማራ ሕዝብ የሚሳደበው ትግሬ ወያኔ ስለተቃወመ ነው? እዚህ ደልቶት ያልተቃወመ እዛ ባፈሙዝ ከተያዘ አንዴት ልክ እንደ ትግሬዎቹ በድሎት ውጭ የሚኖሩ ኤርትራዊያኖች በኢሳያስ ሲጮሁ፤ ለምን የትግሬ ተወላጆች ውጭ ሆነው ወያኔን አልተቃወሙም ደጋፊዎች ካልሆኑ? ተቃዋሚ የትግሬ ተወላጆች ድረገጽ ያለን እኔ እና አብርሀ በላይ ብቻ ነን? ለምን እንድያ ሆነ? የወያኔ ገበና የጻፈ አስገደ እና ገብረመድህን አርአያ ብቻ ናቸው። የተቀሩት ምን ዋጣቸው? በግልጽ እንነጋገር እንጂ፤ ነውር አደለም ወይ?
    ጌታቸው ረዳ Getachew Reda (Editor Ethiopian Semay) getachre@aol.com

Comments are closed.

dem alamudi
Previous Story

በአላሙዲ የሚደገፈው ፌዴሬሽን ዲሲን ጥሎ በሚኒሶታ የዘንድሮውን ዝግጅት ሊያደርግ ነው

alamudi 1
Next Story

ኢትዮጵያ እየከሳች አላሙዲ በሃብት እየወፈሩ ነው፤ የዓለማችን 61ኛው ቢሊየነር ሆኑ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop