የማለዳ ወግ .. . ዓድዋ የእኛ … የትውልድ ኩራት !

* የጦርነቱ መነሻ ምክንያት …
የዓድዋ ጦርነት መነሻ ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ሲሆን ይህ አንቀጽ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን ሆኖ በመገኘቱ እንዲሰረዝ የተደረገው ሙከራም በጣሊያን እምቢተኝነት በመክሸፉ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
* የጣሊያን ወረራ መሰማትና እቴጌ ጣይቱ …
የጣልያንን እምቢተኝነት ተከትሎ ሚኒስትሮች፣ የጦር አለቆችና መኳንንቱ ባካሄዱት የምክክር ጉባኤ ላይ እቴጌ ጣይቱ ብጡል «እኔ ሴት ነኝ፣ጦርነት አልወድም፣ሆኖም ግን ኢትዮጵያን የጣሊያን ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ ፡፡ » ሲሉ የሰጡት አስተያየት ነበር፡፡
* የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት የዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ …
ጣሊያን ውል አፍርሶ ኢትዮጵያን ሲወርር በጉልበቱ የጀግኖችን ሃገር ሊፈታው እንደማይችል ያውቅ ነበር። ጣልያን በልዩነታችን ገብቶ ሊለያየን እቅድ አቅዶም ነበር ። ይህንንም ለማሳካት በተለያየ አስተዳደር ግዛት ለይተው በሚቆራቆሱ የጦር አበጋዞችና በንጉሱ መካከል የነበረውን የከፋ ልዩነት መጠቀም ለድል እንደሚያበቃው አልሞ መነሳቱ እውነት ነበር ። ያም ሆኖ የንጉሰ ነገስቱ መኳንንቱን ፣ ሹመኞችን እና የጦር አለቆችን ሰብስበው በመምከር ብሔራዊ ክብርን ማስጠበቁ ይቅደም አንድምታ ያለው ሃሳባቸው ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ በሰለጠነ መንገድ ከመግባባት ላይ ደረሱ። ይህም ምክክርና ስምምነት ሁሉም በአንድነት ለነጻነትና ክብሩ ይተጋ ዘንድ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደርግ ዘንድ ሁሉም በየስራ ድርሻው ተመድበው መስራት ጀመሩ ።

መስከረም 1888 ዓ.ም ወር ላይ ንጉስ ምኒሊክ ጣሊያንን ለወረራ መዘጋጀቱን በስለላ ባለሟሎቻቸው በቅርብ አረጋገጡ። በወረራ ዝግጅቱ የተቆጡት ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ እንዲህ በማለት አስነገሩ …
‹‹እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአ ብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም…››
* ዓድዋና የጦሩ ዝግጅት …

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያዊነት ሰዎች በፈቃዳቸዉ ሊለዉጡት የማይችሉት ማንነት ነዉን ? (በሸንቁጥ አየለ) 

የዓድዋው ጦርነት በጣልያኖች በኩል የቆየ የቀኝ ግዛት ጥማቸውን ለማሳካት ቀድሞ የተጠነሰሰ ነበር። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን የጦርነት ዝግጅቱ እስከ ሰባት ወር የፈጀ እንደነበር ይነገራል። ዝግጅቱ ተጠናቆ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ጎህ ቀዶ እስኪጠልቅ በቀድሞዋ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት በዛሬዋ ክልል አንድ ትግራይ ውስጥ በምትገኘው በዓድዋ ከተማ ይገጥም ዘንድ ቀኑ ደረሰ ! በዓድዋው ዘመቻ በመቶ ሺሕዎች ሆኖ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛው ጦር፣ ሰይፍ፣ ጋሻና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ይዞ እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ጣሊያን በአስር ሽዎች የሰው ሃይል ፣ በዘመናዊ የጦር መሳሪያና በወታደራዊ ሳይንስ የሰለጠነ አውሮፓዊ ጦር ነበርና ከፍ ባለ ስንቅና ትጥቅ ተደግፎ ወረራ መጀመሩ ይጠቀሳል።
* አንጸባራቂው የዓድዋ ድል … የጥቁሮች ድል !
የጣሊያን ጦር በጄኔራል ባራቴሪ እየተመራ ባህር ተሻግረሮ ሲመጣ የተወረረችው የኢትዮጵያውያን ጦር የሚመራው በንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ነበር። ጀግና ብልህና አርቆ አስተዋይዋ ባለቤታቸው እትየ ጣይቱ ብጡል በዚያ ባልሰለጠነ ዘመን ስልጡን ነበሩና በባለቤታች ከሚመራው የአርበኞች ግንባር እኩል ተሰልፈው ሃገሬውን ስንቅ ትጥቅ በማስታጠቅና በማበረታታት የከፈሉት መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም። ኢትዮጵያውያን በንጉሱ ብልህ አመራርና ክተት ብለው በህብረት ተነሱ ። ከሽኩቻና ዝብሪት ተዘፍቀው የባጁት የየግዛቱ ሹሞች እና የጦር አበጋዞችም በንጉሰ ነገስት አጤ ምኒሊክ የክተት አዋጅ ልዩነታቸውን አስወግደው በህብረት ተመሙ !

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከ118 ዓመታት በፊት በዕለተ ሰንበት ክብሩ የተነካው አርበኛ ህዝብ ዓድዋ ላይ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተንቀሳቅሶ ባካሔደው ውጊያ እብሪተኛውን ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ የጣሊያን ጦር ጋር ገጠመ ! ከማለዳ አንስቶ ጀንበር እስክታዘቀዝቅ ባለው ጊዜ የተካሄደው ጦርነት እልፍ አእላፍ መስዋዕት ሆነው በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት በዓድዋ ተደመደመ !
ጣሊያን ከአንባላጌ እስከ አድዋ ተጠራርጎ እንዲወጣ ያደረገው ” የጥቁሮች ድል!” በሚል አለም ባወደሰው የዓድዋ ድል የጣሊያን መንግስት የሃፍረት ማቅን በግዱ ተከናነበ። የዓድዋ ድል በመላ በአለም ከተበሰረ በኋላ የወረራው መነሻ የሆነውን የውጫሌ ውል ፈርሶ የጣልያን መንግስት በውጫሌ ውል የነበረውን አጉል ምኞቱን ይሰርዝ ዘንድ ግድ ሆነበት ። ወራሪው በሽንፈቱ አፍሮ የኢትዮጵያን ሙሉ ነፃነት አውቆ እና ተቀብሎ የሰላም ስምምነት ያደርግ ዘንድ ተገደደ ! የስምምነት ውሉም ለአለም መንግስታት ተሰራጨ። ውሉ የደረሳቸው መንግስታት እና ሃገራት የኢትዮጵያን የተረጋገጠ ሉአላዊ መንግስትነት በውድም ሆነ በግድ ተቀብለው አረጋገጡት !
* የዓድዋ ድል በዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ድብዳቤዎች …
ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ የዓድዋን ድል አስመልክተው ለፈረንሣዊው ሙሴ ሞንዶን የዛሬ 118 ዓመት የጻፉለት የምሥራች ደብዳቤ እንዲህ ብለው ነበር “የምሥራች በእግዚአብሔር ቸርነት የየካቲት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዕለት ኢጣልያንን ድል አድርጌ መታሁት፡፡ በጨረቃ ሲገሰግስ አድሮ እሰፈሬ ድረስ መጥቶ ገጠመኝ፡፡ አምላከ ኃያላን ረድቶኝ ፈጀሁት፡፡ ደስ ብሎኛል ደስ ይበልህ››
አጤ ምኒሊክ በመጋቢት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤ ያቸው እንዲህ ብለዋል ‹‹… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ እርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግ ተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡ ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…፡፡›› በማለት ያስታወቁ ሲሆን ምኒልክ ለሞስኮብ ንጉሥ ኒቆላዎስም መጋቢት 23 ቀን 1988 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤያቸውም ‹‹እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ፡፡ ጥንት ከአህዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግሁት…›› ብለው መጻፋቸው ይጠቀሳል ፡፡
* አልፋና ኦሜጋ የማይረሳው መስዋዕትነት … አልፋና ኦሜጋ በክብር ይዘከራል !

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን!

ልክ የዛሬ 118 ኛ አመት እሁድ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓም ታላቁ የዓድዋ ድል በዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ ተበሰረ ! ይህ የጥቁር ህዝብ በቅኝ ገዥዎች ከተቀዳጃቸው የዓድዋ ድል እውን እንዲሆን አቀበት የወጡ ፣ ቁልቁለት የወረዱ ፣እርጥብ የጨሰባቸው ፣ ደረቅ የነደደባቸው ፣ ከቤታ ቸው የተፈናቀሉ ፣ የቆሰሉ ፣ የሞቱ ፣ መዳረሻቸው የጠፋ ጀግኖቻችን አልፋና ኦሜጋ የማይረሳው መስዋዕትነት ነው … ይህ አንጸባራቂ ድልም እነሆ አልፋና ኦሜጋ በክብር ይዘከራል !
ልክ የዛሬ 118 ዓመት ከዘመነው የፋሽሽት ጣሊያን ጦር እና ጦር ሰራዊት በላይ የጥቁር ህዝብ ብሔራዊ ክብርና ኩራት ልቀው የታዩበት የጦርነት አውድማ ነው ! ዓድዋ !
በዓድዋ ድል እንኮራለን ! የዓድዋን ድል በክብር እናዘክራለን !
ክብር ለደሙ ለቆሰሉና በክብር ለሞቱ ሰማዕታት !
ክብር ለጀግኖቻች አርበኞቻችን !
ከብር ለእምየ ምኒሊክ ! ክብር ለእቴጌ ጣይቱ !
ክብር ለኢትዮጵያ !
እንኳን ለታላቁ የዓድዋ የድል በአል አደረሳችሁ !
ነቢዩ ሲራክ
የመረጃ ምንጮቸ :
* በታዋቂ የታሪክ አዋቂዎች ከተጻፉት የታሪክ መዛግብት፣
*ከአድዋው ጦርነት ዙሪያ ከቀረቡት የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ፣
* በተለያዩ በጊዜ ስለ ዓድዋ ድል ገድል ዙሪያ ከተጻፉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሲሆን ለአንባብያን እንዲመች አድርጌ አቅርቤዋለሁ ።

Share