ትላንት የጥላቻ ንግግርን የተመለከተ ጥናት ማሟያ ውይይት ላይ ተሳትፌ ነበር። በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በሰፊው የምመለስበት ቢሆንም፥ ቀብዱን ግን እነሆ፦
ርዕሱ በኢሕአዴግ እና በደጋፊዎቹ አተረጓጎም “የጥላቻ ንግግር” ተብሎ ሊመደብ ይችላል። አንድ የዴሞክራሲ ሕልመኛ ርዕሱ ላይ የተጠቀሰውን ዓ/ነገር ቢናገር ኢ-ዴሞክራሲያዊም ሆነ ጥላቻ ሰባኪ አያሰኘውም ባይ ነኝ እኔ ግን። እኔ ራሴ ርዕሱ ላይ የተጻፈውን ያለምንም ጥላቻ ከውስጥ ፍላጎቴ ነው ያፈለቅኩት።
ከዴሞክራሲ ዐብይ ባሕርያት አንዱ ገዢ ፓርቲዎች ወርደው የሕዝብ ምርጫ በሆኑ ተቃዋሚዎች መተካት የሚችሉበት እና ገዢ የነበሩ ተቃዋሚ ሆነው የሚሮጡበት ስርዓት ማመቻቸት ነው። ስለዚህ ለኔ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊነት መፍጨርጨሯ ሐቀኛ ነው ልል የምችለው ኢሕአዴግ ወርዶ ተቃዋሚ ሆኖ ሳየው ነው።
የጥላቻ እና የፍቅር ንግግሮች የሉም ማለት አልችልም። ነገር ግን የጥላቻም ይሁን የፍቅር ንግግሮች ዋጋቸው ከአንድ ክበብ አያልፍም። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ነክ የአገር ውስጥ እና የውጭ ሚዲያዎች በባሕሪያቸው መድባቸው ብባል በሦስት እመድባቸዋለሁ፦
1ኛ) አፍቃሬ-ኢሕአዴግ፣
2ኛ) ኢሕአዴግን-አያሳየኝ እና
3ኛ) I-don’t-know-what-to-doዎች በማለት።
የመጀመሪያዎቹ [አፍቃሬ-ኢሕአዴግ]ዎቹ ዋነኛ ሥራቸው በማንኛውም መንገድ ኢሕአዴግን ማንቆለጳጰስ እና ከተቃዋሚዎች ክፉ ዓይን መጠበቅ ናቸው። አዳም ሲፈጠር ጀምሮ “በስም መስጠት ነው (naming)” ነው ሥራውን የጀመረው እንዲሉ እኔም በዚህ ምድብ የምፈርጃቸውን ጥቂቶች ልዘርዝር፤ ኢቴቪ፣ ዛሚ ኤፍኤም፣ ኢትዮ-ቻናል፣ ትግራይ ኦንላይን እና ወዘተ ናቸው።
ሁለተኛው ምድብ ውስጥ የሚገኙት [ኢሕአዴግን-አያሳየኝ]ዎች ደግሞ የሚደግፉት (የሚያፈቅሩት) የተለየ የተቃዋሚ ቡድን የላቸውም፣ የሚራሩለት እንጂ። ነገር ግን ያለምንም ጥርጥር ኢሕአዴግን አይወዱም። ስለዚህ ሥራቸው ኢሕአዴግን መተቸት ነው። እነዚህ ውስጥ ኢሳት፣ ፋክት፣ ኢትዮጵያን ሪቪው እና ወዘተ ይገኛሉ።
ሦስተኛው ምድብ [I-don’t-know-what-to-do]ዎች ውስጥ ያሉት ደግሞ በመሐል ቤት ይዋልላሉ። ለዚህ ቡድን አሪፍ ምሳሌ የሚሆኑት ደግሞ አዲስ አድማስ ጋዜጣ እና ሸገር ኤፍ ኤም ናቸው። በተረፈ ጥቂቶች ብቻ ለመፈረጅ የማይመች የሚዲያ ሥራ እና ሊረዱት የሚከብድ የአቋምና አቀራረብ ልዩነት ያሳያሉ።
ለምን እነዚህን ፍረጃዎች እና ስየማዎች ማድረግ አስፈለገኝ? ምክንያቱም የጥላቻ ንግግሮች በማን፣ እንዴት እንደሚተረጎም ቀላል ማስረጃ ስለሚሆነኝ ነው። ምድብ አንድ ውስጥ ለሚገኙ ማንኛውንም ዓይነት ኢሕአዴግ ላይ የተሰነዘረ ትችት የጥላቻ ንግግር ነው።
ምድብ ሁለት ውስጥ ለሚገኙትም ከኢሕአዴግ አፍ የሚወጣ ሁሉ ክፉ ነገር ነው። ሦስተኛው ምድብ ከቻለ ሁሉንም ለማስደሰት ካልቻለ ሁሉንም ላለማስከፋት ይፈጨረጨራል። በመሐል ቤት እውነት ማደሪያ ታጣለች። ሁሉም ለዓላማው እጇን ይጠመዝዛታል።
በአገራችን የጥላቻ ንግግር የሚባሉት ሁሌም ከጥላቻ የመነጩ ላይሆኑ ይችላሉ። በባሕላችን የሰውን ስህተት ፊት ለፊቱ መንገርን እንደአለመከባበር የሚያስቆጥር ስህተት ነው። ስለዚህ የአንድን ሰው ጉልህ እንከን እንዲህ ነህ ብሎ መንገር በጣም አስደንጋጭ ነው የሚሆነው። እንዲያውም በጠብ ወቅት ብቻ የሚከሰት ነገር ነው። ስለዚህ በትልቁ (በፓርቲና በፖለቲካዊ አመለካከት ላይ) ሲሰነዘር የእርምት አስተያየት መሆን ቀርቶ የትችት ማዕረግ እንኳን አያገኝም። የጥላቻ ይመስላል (ይባላል)።
ነገር ግን፤ ድክመትን እየሸሸጉ ብርታትን እንደመንገር ያለ አደገኛ ንግግር (dangerous speech) አይቼም ሰምቼም አላውቅም። ለግለሰብም ይሁን ለቡድን ግብዝነት ይዳርጋል። ድክመት ሲነገረው እልል ብሎ በፈገግታ ተጉመጥምጦ የሚውጥ ግለሰብም ይሁን ቡድን ገጥሞኝ አያውቅም፤ ከትችቱ አለመማር ግን እየሰሙ አይቻልም፤ ከስህተት ላለመማር መፍትሔው እንደኢሕአዴግ ተቺውን ማፈን ብቻ ነው። ትችት ካደመጡት ግን ምናልባት ለመዋጥ ጊዜ ይወስድ ይሆናል እንጂ ዘልቆ መቆጥቆጡ አይቀሬ ነው።
ይሄ ሁሉ ግን ስለጠሉ ብቻ የሚተቹ፣ ስለወደዱ ብቻ የማይሞገሰውን የሚያወድሱ የሉም ማለት አይደለም። ጥላቻና ፍቅርም ምክንያታዊ አይሆኑም ማለት ይከብዳል። ነገር ግን ክርር ያሉት የሥነ ልቦና ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
የጥላቻ ንግግርን መብት ከሐሳብን የመግለጽ መብት ለይቶ ለማስቀረት ሁነኛው መፍትሔ የማንፈልገውን ብቻ ሳይሆን የምንፈልገውንም ጭምር ማወቅ አለብን፤ አራማጅ ተራማጅነታችንም በመርሕ እንዲመራ ማድረግ መድኃኒቱ ነው።