በማተብዋ ልዳኝ – ወድቃ የተነሳችው – (ከስንሻው ተገኘ)

ወደ ትዝታ ዓለም ወደ ትዝታ ጊዜ በትዝታ ሰረገላ ልወስዳችሁ ነው። እኔ እንኳ በአጻጻፌ አበባዊ ቋንቋ አልወድድም። ለማንኛውም ግን አብረን እንድንነጉድ እጋብዛችኋለሁ። ወደ እንግሊዝ አገር! 1953 እ.አ.አ ወደ አንድ የለንደን ስብሰባ አዳራሽ እንገባለን። እንግዶች የነፃነት ታጋዮች ወደ አዳራሹ ከመግባታቸው በፊት የዌስት ኢንዲስ ተወላጅና የዓለም አቀፍ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ንቅናቄ መሪ የሆነው ጆርጅ ፓድሞን በአዳራሹ ውስጥ ፕሪዚደሙን ለብቻ ይዞታል። የእኔንና የእርስዎን ቡጢ (ጭብጥ) የሚያህል ወፍራሙን ትምባሆ (ቶስካኖ) ጐርሶአል። ጐርናና ድምፁ ሰውንም አዳራሹንም የሚቆጣጠር ዓይነት ነው። ከአፉ የሚወጣው ጢስ በአካባቢው አንዳች ዓይነት ጉም ሠርቶአል። በመካከሉ የሚያሰማው ባለ ግርማ የሆነው ሳሉ ለሰውየው ተጨማሪ ክብር አሸክሞታል።

“ ክቡራትና ክቡራን! አዳራሹ ተከፍቶ ንግግር የሚያደርጉት የአፍሪካ ነፃነት ንቅናቄ መሪዎች ወደ ውስጥ ይዝለቁ!” ጆርጅ ፓድሞን ትእዛዝ ሰጠ። አዳራሹ ደግሞ ከግድግዳ እስከ ግድግዳ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቆአል። በአራቱም ማዕዘናት ቄንጠኛ በሆኑ ረዣዥም ሰንደቆች ላይ ወርቃማና ቀለማማ በሆነ መደብ ላይ በጉልህ የሚታዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዎች አሉ። ትርኢቱ እንባ ካልጋበዘ ስሕተቱ የኔ ነው። ደካማ ጋዜጠኛ ሰነፍ ጸሐፊ….

አዳራሹ ተከፈተ። የማኦማኦ ንቅናቄ መሪ ወጣት የማይመስሉት ጆሞ ኬንያታ ብቅ አሉ። በደረታቸው ላይ የቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ ምስል ያለበት ፒን አድርገዋል። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንደ ሻሽ አድርገው በራሳቸው ላይ ጠምጥመውታል። ቀጥል። የጐልድኮስቱ (በኋላ ጋና) የነፃነት ግንባር መሪ ካዋሚ እንኩሩማህ- ፈርጠም ያለ…ደልደል ያለ..ተክለ ሰውነታቸው ጉልህ የሆነ አርበኛ። ሰንደቅ ዓላማውን በሙሉ ለብሰውታል። የጃንሆይን ምስል ደግሞ በግራ ኮታቸው ክሳድ ላይ ሰክተውታል። ሑፍዌ ቩዋኘ (ኮትዲቮር) ሔስቲንግስ ባንዳ (ማላዊ) ወዘተ ተራ በተራ መጡ። ከመካከላቸው ጐፈር በራሳቸው ላይ ያደረጉ….በእጆቻቸው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ የጃማይካ፣ የደቡባዊ አፍሪካ ታጋዮች ነበሩ። በብዙ ቁጥር። ሁሉም በመንፈስ ኢትዮጵያዊ ነበር። ያ ዘመን ደግሞ በትውልዱ ጃማይካዊ የነበረው ማርከስ ጋርቪ (Black nationalism and Pan-Africanism)ን እንዲሁም የራስ ተፈሪያኒዝምን ፍልስፍና የሚያስፋፋበት ነበር። የሁሉም አገር – ነፃነትዋን ለሺህ ዓመታት አስከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ናት። ዓይናችሁን ጨፍኑና ጊዜን አጣጥፋችሁ ወደዚያ ዘመን (1952-53) ብረሩልኝ። መጀመርያ ስለዚህ ጉዳይ ዴቪድ ሜሬዲት The first dance of freedom ን መጽሐፍ አነበብሁና (በ1985) ወዲያው እጅግ ወዳጄ ለነበሩት ለልጅ ሚካኤል እምሩ አነሳሁባቸው። በወቅቱ በእንግሊዝ አገር ስለነበሩ በግል በትኩረት የሚያውቁት መሆናቸውን አረጋገጡልኝ። ከላይ ያቀረብሁት ዘገባም የማርቲን ሜሬዲትና የልጅ ሚካኤል እምሩ ጭምቅ ሪፖርት ነው። (ልጅ ሚካኤል ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ላይ ወደ እንግሊዝ አገር ከሄዱ ተማሪዎች አንዱ ነበሩ።)

የወቅቱ ተራማጅ ሁሉ ይህንን በጽሞና ሲከታተል ኋይት ሖል (የእንግሊዝ መንግሥት) በዚያው ሰሞን (1953) በኢትዮጵያና አንድነትዋ ላይ ትልቅ ሴራ ሲያቀጣጥል ነበር። ሊቆራርጠን። አርነስት ቤቪን የተባለው የሌበር ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሶማሊያ ነፃ ስትሆን የኢትዮጵያን ኦጋዴን፣ ሪዘርቭድ ኤርያና – ሐውድ እንዲሁም ጅቡቲንና የኬንያን ሰሜናዊ ምዕራብ ግዛት አጠቃልላ ታላቅዋን ሶማሊያ ስትመሠርት በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ ከአለውሀ ባሻገር ያለው መሬት በሙሉ (ማለትም ትግራይና ኤርትራ ተዋህደው ትግራይ ትግርኝ የሚባል አገር ለመፍጠር ሽርጉድ ይዘው ነበር።) lyndon larouche የተባለውና በመደበኛው አስተሳሰብ አክራሪና የተወናበደ የፖለቲካ ነውጠኛ የአገሩን ፖለቲካ ጨረሰና ዛሬ በመላው ዓለም እየደረሰ ያለው ችግር እንግሊዝ ዘርታ ያበቀለችው አድርጐ ነው የሚያቀርበው። ይኽ አይጠረጠርም። በበኩሌ እንደማውቀው እንግሊዙ አርነስት ቤቪን የጀመረውን አይኤም ሌዊስ ካልፈጸምሁት ብሎ እነ በረከት ሀብተ ሥላሴን፣ እነ መለስ ዜናዊን ይዞ ለዓመታት ተንደፋድፎአል። (መለስ በዜግነት ሶማሊያዊ ነበር)- በነገራችን ላይ እነ በረከት ሀብተሥላሴ፣ መለስ ዜናዊ ወዘተ ተወልደው ያደጉባት፣ ተምረው የተሾሙባት ኢትዮጵያ፥ ዓለማቸውን ያዩባት ውብ አዲስ አበባ- ወደ ኢምንትነት እንድትመለስ ሲፍጨረጨሩ እንደ ራስ ተፈሪ ያሉ ሕዝቦች “ቤታችን መግቢያችን (ራስታ የምንላቸው)” በማለት ወደዚያች አገር መጉረፍ ይዘው ነበር።

ተመስገን ደሳለኝ ወደ ጐንደር ሄዶ ነበር አሉ። ባዶ እጁን አልተመለሰም። ወያኔ ያነወራት፣ እንደ ተስፋዬ ሐቢሶ ያሉ (በተቆላበት የሚያፈሉ) ሰነፎች የተሳለቁባት፣ በመንፈሳዊና ሕዝባዊ ክብርዋ መለስ ያሾፈባት፣….ወያኔዎች በባዶ እግራቸው የረጋገጡአትና የኮሾሮ (የአምባሻ) መያዣ ያደረጉአት….በእኔ ዕድሜ ጅማሬ ላይ “ወድቃ የተነሳችው” እየተባለች ስትጠቀስ የቆየችው ሰንደቅ ዓላማ በጐንደር ምንኛ ታላቁን ክብርዋን ይዛ – እንዳለችና እንደምትኖር የምሥራቹን ነግሮናል። ብሥራት ነውና ምሥር ብላ! ለዚህ ጽሑፍ ያነሳሳኝ ይኸ ወጣት ጋዜጠኛ ነው።
ኢጣሊያ የኤርትራን ደጋማ አውራጃዎች ለመያዝ የቻለችው በ1889ዓ.ም እንደ አ.አ ነው። እዚህ ላይ የንጉሠ ነገሥቱን (አጤ ዮሐንስ) አጐት ራስ ደበብንና በኋላ ጊዜ የራስ ሥዩምን ሴት ልጅ ያገቡትን ደጃዝማች ገብረሥላሴን ማውገዝ ወይስ ማወደስ ይገባ እንደሆነ አላወቅንም እንጂ በእነሱ ድጋፍና መሪነት ነው ኤርትራ የተያዘችው። ዛሬ አኪሩ ዞሮ ባንዳ የሚወደስበትና የሚቀደስበት፣ ወደል ወደል መጽሐፍም በውዳሴ መልክ የሚቀርብበት በመሆኑ ነው ግራ የተጋባነው። አዎን ዓላማዬ በማንም ዜጋ ላይ የፍትሕ ድንጊያ ለመወርወር አይደለም። የእግዜሩን መንገድ ካወቅነው ጸሎታችን “ማረን” እንጂ “አፈራርደን” መሆን የለበትም።
ኢትዮጵያን የሚታደጋት የራስዋ የኢትዮጵያ ልጅ መሆን እንደሚገባው ስንነጋገርና ስንስማማ ከቆየን በኋላ ሁሉም ነገር የተለዋወጠ ሆኖአል። ኢትዮጵያውያን አገራቸውንም ራሳቸውንም ማዳን አቅቶአቸው በአገሪቱ የሚጫወቱት ወገኖች የተነሱለትን አጥፊ ዓላማ ለመፈጸም አንዳች እንቅፋት አልገጠማቸውም። በተናጠል መስዋዕትነት የሚከፍሉ ግለሰብ የፖለቲካ ተዋናያውያንና ጋዜጠኞች ደግሞ የሚሞቱለትን ሕዝብ ሊቀሰቅሱ አልቻሉም። ስለሆነም ኢትዮጵያ ያሉአት ልጆች እነዚህ ብቻ ናቸውን? እስከማለት የደረሱ አሉ። “የኢትዮጵያ ልጆች በደማቸውም በአጥንታቸውም ኢትዮጵያን ከእልቂት ለማዳን ካልቻሉ ወዴት ይኬዳል? ወደ ማን ይጮኻል?” ነቢዩ ዳዊት (ልበ አምላክ የሚባለው) ለዚህ አምላክ ራሱ በጆሮው የነገረው ቁም ነገር ነበር ይላሉ መጽሐፉን የሚተረጉሙ ሰዎች። “በልጆችዋ መተማመን ያቃታት፣ ልጆችዋ በግፈኞችና በጨቋኞች ያለቁባት ኢትዮጵያ ናት፤ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር የዘረጋችው” ይሉናል። ተስፋ ከመቁረጥ የመጣ አሳብ አይደለም። የአምላኩንም ሚና እንዳንረሳ ለማሳሰብ ነው። ውዳሴ ማርያምም ባይሆን ጥቂት እግዚኦታ!

ተጨማሪ ያንብቡ:  በህወሀት አርያና አምሳል የተፈጠረው ብአዴን ለአማራ ሊቆም አለመቻሉ - ምስጋናው አንዱዓለም

እንደ ዛሬዋ ጐንደር ሁሉ ጣልያን ኤርትራን ከያዘ በኋላ ለስድሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ነፃነት ምልክትና የክብርዋ ዘላለማዊ መግለጫ የሆነችው አረንጓዴ፣ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በደብረ ቢዘን ቤተ ክርስቲያን አናት ላይ ስትውለበለብ ቆይታለች። እግዚአብሔር በቤቱ (ቤተክርስቲያኑ) ላይ ያዋላት ለዚህ ሕዝብ መልእክት ኖሮት ይሆናል በማለት የገዳሙ አበምኔት በ1980 ገልጠውልኛል። በዚያን ዘመን ኤርትራ በጣልያን ሥር ብትወድቅም በየበዓላቱ ሕዝቡ ይዞት የሚወጣው ሰንደቅ- አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ነበር። አንድ ኤርትራዊ ሲሞት የአስክሬኑ ሳጥን በዚችው ሰንደቅ ዓላማ ያሸበርቃል። ሠርጐች ግርማማ የሚሆኑት በዚችው ሰንደቅ ዓላማ ሲንቆጠቆጡ ነው። አብያተ ክርስቲያናት ይኽ ሰንደቅ ዓላማ ተለይቶአቸው አያውቅም። ለብዙ ዓመታት ወደ ኤርትራ ስመላለስ የኖርሁ፣ ሕዝቡን የማውቅና የማከብር ስለነበርሁ ዛሬ ይኽ ወገኔ ከዚያች ከታቦት እኩል ከሚያያትና የሕልውናው ተስፋ ከነበረችው ሰንደቅ ዓላማ ሲለይ ምን ተሰማው? እያልሁ ራሴን እጠይቃለሁ። ወይስ አዲሱ የኤርትራ ትውልድ ይኽንን ቁም ነገር አያውቀውም ነበር? እዚህ ባለሁበት አገር እንደኔው በስደት ላይ የሚገኙ ኤርትራውያን አረጋውያን አውቃለሁ። ለሁሉም እንደ ቀልድ “አዲሱ ሰንደቅ ዓላማ የሚለመድ ነው?” እላቸዋለሁ። በሻዕቢያ ውስጥ ከአሥርና ከአሥራ አምስት ዓመት በላይ መቆየታቸውን የሚነግሩኝ ብዙ ጐበዞችን በየቀኑ አገኛቸዋለሁ። ሁለቱ በአንድ ቀን የአሜሪካ ዜግነት እንዳገኙ ሲነግሩኝ እንደ ቀልድ አድርጌ “አሜሪካዊ ለመሆን ነው ሰላሳ ዓመት የወጋችሁኝ?” እላቸዋለሁ።

ኤርትራውያኑ ራሳቸው በአጸፋው “እናንተስ ሰንደቅ ዓላማውን መቸ አስከበራችሁና ነው እኛን የምታሽሟጥጡን?” ሊሉን ይችላሉ። እግዜር ይመስገን የወያኔ ሕግ በማይሰራበት በዋሽንግተን፣ በለንደን፣ በጄኔቫ…በስዊድን…የምናምንባት የእናት ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንደ ልብ ትውለበለባለች። ስለዚህ ለኤርትራውያን ወገኖቻችንም “የተዋችኋትን ሰንደቅ ዓላማ በምትመለሱበት ጊዜም በዚያው ሞገስ ታገኝዋታላችሁ” ለማለት ይቻላል። (የኢትዮጵያ ሕግ በማይሰራባቸው በስዊድን ወዘተ ስል እህታችን ብርቱካን ሚደቅሳ ትዝ ትለኛለች። ለካንስ ስቶክሐልም ላይ የተናገሩት አዲስ አበባ ላይ ያስቀጣል?)
ከማንም በላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሲያከብር የኖረው የኤርትራ ሕዝብ ነበር ስል ሌላው ሕዝብ ደንታ እንዳልነበረው መግለጤ አይደለም። ግመሎቻችን፣ በጐቻችን፣ የጋማ ከብቶቻችን፣ የቤትና የዱር እንስሶቻችን አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ የሆነውን የክብር ዓርማ ያውቁታል እያሉ የሚያወጉአችሁ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተወላጆች ብዙ ናቸው። የአውሳው ርእሰ መኳንንት ቢተወደድ አሊሚራሕ አንፍሬ በአንድ ወቅት “እንኳን አፋሩ ሕዝባችን ግመሎቻችንም ሰንደቅ ዓላማችንን ያውቁታል” ማለታቸው ይጠቀሳል። አጋጣሚ ነገር ላንሳና ኮማንደር ለማ ጉተማ የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ዋና አስተዳዳሪ በነበሩበት ጊዜ የመሥሪያ ቤቴን ቅርንጫፍ ሥራ ለማስተባበር ወደዚያ እመላለስ ነበር። ሁለት ጊዜ ያህል የኢሳውን ባላባትና ሱልጣን ደጃዝማች ዑጋዝ ሐሰንን ተዋውቄአቸው ነበር። “ትልቁ ልጄን ትመስለኛለህ” ሲሉኝ ልዩ ፍቅር አደረብኝ። ታዲያ በ1983 አካባቢ ቢትወደድ አሊ ሚራሕ የተናገሩትን ቃል በቃል ደጃዝማች (ዑጋዝ) ሐሰን ሲናገሩት ሰምቻቸዋለሁ። ማጋነን ባይመስል ግመሎቹ ቀጥ ብለው እንደሚቆሙ ይናገራሉ። ጐበዝ! “ግመሎቻችን ለኢትዮጵያ ከእኛ የበለጠ ታማኝ ናቸው” ብል በድፍረት ትወስዱብኝ ይሆን? ግመሎቻችን ጭምር የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያውቁታል! እነመለስ ከዚያች ቅርጽ የለሽ እንስሳ ማነሳቸው ከተሰማችሁ አብሬአችሁ ልከሰስ እችላለሁ።

ፋሺስቶች ባላደረጉት ድፍረትና ብልግና በቀለም እኛን ይመስል የነበረው መለስ የሕገ መንግሥት ጉባዔ ሲመራ ያቺን ሰንደቅ ዓላማ እንዴት እንዳብጠለጠለ ታስታውሳላችሁ። እዚያ ጉባዔ ውስጥ በጀግንነትና በታላቅ ወኔ ይቺን ሰንደቅ ዓላማ ያወድሱ፣ የቆሙላትና ስድቡን ሁሉ የተሸከሙላት ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ (ነፍሰ ሄር) ብቻ ነበሩ። እዚያ አዳራሽ ውስጥ የነበሩ መንጋ ወሮበሎች ፋሺስቶች ቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ በመንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) የኢትዮጵያን ጉዳይ ሲያሰሙ ያሰማሩባቸውን ሥራ ፈቶችና ማጅራት መችዎችን አስታውሶኝ ነበር። ይችም አገር ዛሬ (በ21ኛው ክፍለ ዘመን) በዋልጌዎች፣ በጫካ አደጐች፣ በቀማኞች…እጅ እንደገባች ሁላችንም ተከሰተልን። ያን ጊዜ ከመታኝ ብራቅ እስካሁን አላገገምኩም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመላከ ብርሀን አድማሱ ጀምበሬና የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ አጽም ፍልሰት -  ቀሲስ አስተርአየ

እኛ ኢትዮጵያውያን – ከእኛም በፊት የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ትውልዶች- በነፃነት ተጸንሰን፣ በነፃነት ተወልደን በነፃነትም ተጠልለን ኖረናል። የሰውን ልጆች እኩልነት የምትመሰክረውን ሰንደቅ ዓላማ፣ የሕዝባችንን የታሪክ ቅሬቶች፣ ሐውልቶችና የነፃነት ምልክቶች–የክብርና የማዕረግ ሀብቶቻችንን ስንንከባከብ ኖረናል። አገሪቱ ትኖር ዘንድ በሰንደቅ ዓላማቸው ሥር ተንበርክከው የፈጸሙትን መሐላ ያከበሩትን ጀግኖች በፈንታችን አክብረናቸዋል። በእስዋ ተመርተን ወደ ሞት አደባባዮች ነጉደናል። ይቺ ሰንደቅ ዓላማ ከሁለት መቶ ሺህ ከማያንስ ሠራዊትና መሪዎቻቸው ጋር ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አድዋ ዘምታ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ድል የሆነውን ግዳይ ተወጥታለች። ይቺ ሰንደቅ ዓላማ እኛ ባለቤትዋ ሆንን እንጂ የዓላም ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ አለኝታ ነበረች። ያስረዳሁ ይመስለኛል።

የዚያድ በሬ ወራሪዎች ያሳደዱአት አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ የክብርና የአንድነት ምልክታችን በጐዴ፣ በካራማራ፣ በጅጅጋ በገላዲ…እንደገና ስትውለበለብ አይቻለሁ። በወረራው ወቅት የሶማሊያ እብሪተኛ ኅይል ባደረሰብን ጥቃት የተቃጠለና ያለቀሰ አንጀታችን ሰንደቅ ዓላማችን ዳግመኛ ስትውለበለብ እንደገና ማልቀሳችን ትዝ ይለኛል። አልፎ አልፎ እንደዚያ ያለ ጥቃት አይጠላም። ለነፃነትህና ለአንድነትህ ዘወትር እንደ ቆቅ ተጠንቅቀህ መቆምና መሞት ግዴታ መሆኑን እንዳትረሳ ያስገነዝብሃል።

የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ሲነሣ – አሁንም ተመስገን ደሳለኝ አነሳብኝና- ከውስጤ አንድ እሳተ ጐመራ መሳይ ነገር ሊፈነዳ ይደርሳል። ትዝታዎች አሉኝና። በኤርትራ በረሃዎች፣ ቅጥልጥል የሆኑ የመስሐሊት ሸንተረሮች፣ በሰሎሞና፣ በሸኢብ…ከኢትዮጵያ የአንድነት ሠራዊት ጋር የዘመቱት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰንደቅ ዓላማዎችን ዛሬ ዓይኔን ጨፍኜ አያቸዋለሁ። እዚያው ከሰንደቅ ዓላማው አጠገብ ክንዳቸውን እየተንተራሱ እየጣሉ የወደቁትን፣ በኋላም ነጭ የሰላም ዓርማ እያውለበለቡ እንኳ በፈሪዎች (ካወርድ የሚለው የእንግሊዝኛው ቃል ጠንካራ መልእክት አለው) የተረሸኑት ኅልቁ መሳፍርት የሌላቸው ወገኖቼ ከፊቴ ድቅን ይላሉ። የብዘዎቹን አዛዦች አውቃቸዋለሁ። ለወረራ የተሰማራ ኅይል የለንም። ይልቁንም የኤርትራን ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ክብርና ነፃነት ለማስጠበቅ፣ እያስጠበቀም ለመሞት በሰንደቅ ዓላማው “ምሎ” የተመመ ነበር። ተሳስተን ነበር ያለቅነው? ተሳስተን ነበር እንደወጣን የቀረነው – ሬሳችን የአራዊት ሲሣይ – የሆነው- ቀባሪ ያጣው….? የኤርትራ ሕዝብ ምነው አስቀድሞ ቢነግረን ኖሮ! በአርማጌዶን እንድንገናኝ ቀጠሮ መያዝ እንችላለን።

ከጥንት ጀምሮ- ለእኔ ጥንት ከሰባ ዓመት የማይበልጠው ነው- ከዚች ሰንደቅ ዓላማ ጋር የሚያስተሳስር ታሪክ አለኝ። የራሴ ትንሽ ታሪክ! ትንሽም ትዝታ። ታላቅ እህቴ ወይዘሮ ውርስ-አረፍ ልዑልአየሁ የፋሺስቶችን እርግጫና ጡጫ ታስታውሳለች። በዚህ የተነሣ ዘወትር የአገር ልብስዋ ጥለት በሙሉ አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ነበር። ይኸ ብቻ አይደለም። በአሥራ አራት ዓመቴ ሁለተኛ ደረጃ ከገባሁ በኋላ ከ17 ዓመት በፊት ወደ ስደቱ ዓለም እስክዛወር ድረስ በየዓመቱ ጋቢ ፈትላ ትልክልኛለች። ሌሎች ዘመዶቼ ጋቢ አስለምደውኛል። የወይዘሮ ውርሰአረፍ ጋቢ ግን ሁልጊዜ በአረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ጥለት የደመቀ ነበር። ከአሥራ ሁለት ዓመት በፊት (በሞት ያረፈችበት ዘመን) የመጨረሻውን ጋቢ ልካልኛለች። ታዲያ ይኽንን ልማዴን ታውቅ የነበረችው ታላቅ እህቴ ወይዘሮ ይታይሽ ልዑልአየሁ “እቴቴን (ሟች እህታችንን) እንድታስባት ብዬ በእስዋ ምትክ ጋቢ ልኬልሃለሁ” ብላ ወደዚህ በመጣ ሰው አደራዋን ተወጣችው። አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ። ይቺኛይቱ እህቴም ወደ ታላቅዋ ዘንድ ሄደች። አላውቅም፥ ይገናኙ አይገናኙ። ለእኔ ግን ሰንደቅ ዓላማዬ ናፍቆቴ ሆኖአል። ተከናንቤው የምተኛው ጋቢ ባላጣም። (በነገራችን ላይ ውድ ወዳጄ ጐሹ ሞገስ በዚህ ረገድ ረስቶኝ አያውቅም።)
የኢትዮጵያ ድምፅ፣ በኋላ ደግሞ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ከበደ አኒሳ እንደ እናቴ ልጅ የምቆጥረው ነው። በንጉሡ ዘመን በየሳምንቱ ቅዳሜ ወደ አራት ሰዓት ላይ ይመጣና “ና ቡና ጠጥተን እንመለስ” ይልና ይዞኝ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት በኩል ይነዳል። ልክ ቤተ መንግሥቱ አጠገብ ስንደርስ እኔም እሱም አንገታችንን አውጥተን ግቢውን እንቃኛለን። ሁለት የሰንደቅ ዓላማ መስቀያ የብረት ምሰሶዎች አሉ። አንደኛው አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ የሚውለበለብበት ነው። ሁለተኛው (አጠር ያለው) ደግሞ አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ዓርማ መሐል አንበሳ አለው። ያ የጃንሆይ ሰንደቅ ዓላማ ሲሆን እሳቸው በከተማው ከሌሉ አይውለበለብም። የንጉሠ ነገሥቱ በከተማው መኖር አለመኖር ምልክት ያ ነበር። ስለዚህ ትንታጉ ጋዜጠኛ ከበደ አኒሣ “ዛሬ ጀንሆይ በአዲስ አበባ ስለሌሉ መንግሥት በሌለበት ከተማ ምን እናደርጋለን?” ይልና ወደ ደብረ ዘይት፣ ናዝሬት፣ ሶደሬ ወዘተ እንከንፋለን። ብቻ በየሳምንቱ ከአዲስ አበባ ለመውጣት ሰበብ የምናደርገው የጃንሆይን ሰንደቅ ዓላማ አለመውለብለብ ይሆንና “መንግስት ከሌለበት ከተማ ምን እናደርጋለን?” እያልን እብስ ማለት እንደ ባሕል ተያዘ። በእኛ ዘመን ቡድናችን (የእግር ኳሱ-አለዚያም ጊዮርጊስ) ቢያሸንፍም በደስታ፣ ቢሸነፍም በንዴት በቢራው ማዝገም የተለመደ ነበር። ስትናደድም ትጠጣለህ፣ ሲከፋህም ትጠጣለህ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የወቅቱ የኢትዮጲያ የፖለቲካ ችግር መዘዝ (Root Cause) (አበራ ቱጂ)

ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን እንደ ወረረች እነ ማርከስ ጋርቪ ሦስት ሺህ ጥቁር ወታደሮች መልምለው በክተት ተጠንቀቅ ላይ ነበሩ። አጤ ኅይለሥላሴ የእንግሊዝን ጦር እየመሩ በመሄዳቸው ራስ ተፈሪያውያኑ ማርከስ ጋርቪና ራስ መኰንን (ራስታ) ጃንሆይን ተቀይመው እንደነበረ በወቅቱ ሲወራ ነበር። በጽሑፍም ቆይቶናል። ይቺን አገር- ይህን ሰንደቅ ዓላማዋን- ይህን ጐላ ያለ ታሪክዋን- ወደፊትም አውስተን የማንጨርሰውን- ትዝታዋን እነዚህ ሳንቀጣቸው ያደጉ፣ በማይምነታቸው የማያፍሩ ደፋሮች ይዘን መጓዙ ራሱ ሕመም ነው። ኅብረተሰብ ይጠይቀናል። ሰላምን በሰንሰለት፣ ዳቦን በባርነት የሚሸምቱ ሰዎች ዘመን ላይ መድረሳችን ይገርመኛል። ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ የሚያውቁአትና የሞቱላት ሰንደቅ ዓላማ መደፈር እንደ እብድ አድርጐአቸው እንደነበረ አስታውሳለሁ። ወዲያው ጋዜጠኞች ሰብስበው ንግግር አድርገው አንድ ብዕር በሽልማት መልክ ሰጡኝ። እኔም ለዚች ሰንደቅ ዓላማ ምን ያህል ታማኝ እንደሆንሁ- የሻለቃ አድማሴን ቃልም ምን ያህል እንደጠበቅሁ አላውቅም። ይቺ ሰንደቅ ዓላማ ደግሞ ያለ ጠባቂ መሆንዋ እውነት ነው። ያለ እስዋ ነፃነታችን ባዶ መሆኑ ይሰማኛል። ባለ አምባሻዋን የመለስን ድሪቶ አደራችሁን በምትክነት አናንሳው!

የነፃነት እጦት የሚመሰክረው የሰንደቅ ዓላማ መዋረድና የአገር መደፈር ምን ማለት እንደሆነ ዘላለማዊው ሐዲስ ዓለማየሁ “ትዝታ” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጠውታል። ራስ እምሩ፣ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ አቶ ይልማ ዴሬሳ…በኢጣልያ ደሴት ታስረው በቆዩበት ጊዜ የቪክቶር ኢማኑኤል ሳልሳዊ የባሕር ማዶ ቅኝ ግዛት ኅላፊ ራስ እምሩን እንዲያነጋግር ታዝዞ ይሄዳል። ቆፍጣናው መስፍን በመኝታ ቤታቸው ባለችው አንዲት ወንበር ላይ ተቀምጠዋል። ሰውየው ቆሞ ሲያናግራቸው ይሉኝታ የያዛቸው የእኛ ሰዎች ወንበር ፍለጋ ወደየ ክፍላቸው ሊሄዱ ሲሉ ራስ እምሩ “ወንበር ልታመጡለት እንዳይሆን፤ እንዳታደርጉት” በማለት ቅኝ ገዥውንና የሀገሩ ባለቤት የሆነውን ባለሥልጣን አቁመው አነጋገሩት። በኢትዮጵያዊ ክብርና ኩራት እየተደበቡ “ ወዳጄ እኛ ዘንድ ምን አመጣህ?” ይሉታል። እሱም እንደ ባለስልጣን ሳይሆን እንደ አሽከር ቆሞ “ ግርማዊ የኢጣልያ ንጉሥ ኢማኑኤል ሳልሳዊና የመንግስቱ መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ ያለዎትን ሀብት ንብረትዎን፣ ርስትዎንና ሌሎችንም እንደ ገንዘብ ያለውን ሀብትዎን ሊመልሱልዎ ወስነዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ሊረከብልዎ የሚወክሉት ሰው ካለ ይነገረውና ይረከብልዎ!” ይላቸዋል።

የራስ እምሩ ቃል ለሰውየውም እዚያ ላሉትም አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምርኮኞች እስደንጋጭ ሆነባቸው። ባልተጠበቀው መልሳቸው ራስ እምሩ “የእኔ ሀብትና ንብረት የቀረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በተደፈረ- አገሬ በእናንተ በተረገጠች ጊዜ ነው። አሁን ሀብትና ንብረት የለኝም። ይህን የምትጠቅበውን ሀብትና ንብረት ለምትወድደው ሰው ልትሰጠው ትችላለህ።” ይሉታል። አጭር መልስ። ዲቦኖ፣ ባዶልዩ፣ ዱካ ዳውስታ፣ ግራዚያኒ፣ ፍራንካ..ወዘተ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መርገጣቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ የለኝም። ይልቁን ቀደም እንዳልሁት ይቺው ሰንደቅ ዓላማ በኤርትራ ምድር እንዲያ ስትከበር በማንም ላይ በምንም ጊዜ ስላደረሱት ጥቃት ብዙም አልሰማንም። እኛ ኢትዮጵያውያን ግን አምባገነን ሥርዓት አወረድሁ በሚል ግለሰብ ዓርማችን ስትናቅና ስትገፋ ለማየት ችለናል። የት? በጣይቱ ከተማ- በአዲስ አበባ! ባዕድና ጠላት፣ አስገባሪና ወራሪ የተባሉትም በዚህ ነው። የበላዔ ሰብን፣ የሒትለርንና የስታሊንን፣ የቀያፋን፣ የሔሮድስንና የጲላጦስን፣ የአስቀሮቱ ይሁዳን….ኅጢአት የደመሰሰ አምላክ ይሁነውና መለስ እንደ ገና ሲያላግጥብን ትልቅዋን ዓርማችንን ቡትቱ አስመስሎ ከማምጣቱም በላይ “የነፃነት ቻምፒዮን” ሆኖ ተከሰተ። ከቶውንም የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበርን እንደ ማካካሻ ሰጠን። ጥሩ ተጫውቶአል። እግዜር ይመስገነው በውጭ ያለነው ከሰንደቅ ዓላማችን ጋር አልተለያየንም። እንደኔማ ቢሆን ሰው ሁሉ “ወፈፌ” ወይም የጀማመረው ካላለኝ በየቦታው ለብሼ ብሔድ ደስታዬ ነበር።

ለእኔ ሰንደቅ ዓላማዬ ሁሉንም ነች። የነፃነት ብሥራት፣ ቀጥ ብሎ ቆሞ በክብር የመንጐራደድ ዋስትናዬ ናት። ይቺ ሰንደቅ ዓላማ የአፍሪካ ታጋይ ኅይሎች እየተመለከቱአት ቅኝ አገዛዝን ድባቅ የመቱባት ኅይል ናት። የአፍሪካ አገሮች ወደ ፍጹም አንድነት ይመጡ ዘንድ ታሪካዊ ጥሪ ያስተላለፈች ናት። ዛሬ ደግሞ ከወደቀችበት ትነሣለች። ሰው ሁሉ ኢትዮጵያን ቢክዳት “ኢየሩሳሌም ሆይ ብከዳሽ ቀኜ ትክዳኝ” ያለው አምላክዋ ወደ ክብርዋ ይመልሳታል። እንደ ተዋረድን አንቀርም። ወደ ታሪካዊ አንድነታችን በእርግጥ እንመለሳለን። አንዳንድ ደካማ “ነፍሳት” (አዎን “ነፍሳት”) የሚያናፍሱት መፍረክረክ ከንቱ ከንቱ…ሆኖ ያልፋል። አሜን አሜን!

2 Comments

  1. GETACHEW REDA (Editor Ethiopian Semay)
    ለበርካታ አመታት የመንፈሴ ምርኩዝ የነበረው ጦቢያዊው ብዕር ከተለየኝ በርካታ አመታት ሆኖት መንፈሴ ተረብሾ ነበር። ይህ የብዕር መቅደስ ቀደም ብሎ ካረፈበት ወጥቶ ቢደመጥ ኖሮ ቀበቶው ላልቶ ወዲያ ወዲህ የሚወላገደው በርካታ ወጣት እራሱን ለመፈተሽ ይረዳው ነበር። ሆኖም አሁንም ‘ይመስገነው’ አምበሳው ካረፈበት የተነሳ ይመስላል። ለዚህም አምበሳው ብርታቱ ይስጠው። በአንበሳው ዙርያ የከበቡት ድምቢጦች ግን ለጆሮው ጥራት ሲል መፈተሹ አስፈላጊ ይመስለኛል። የህ ቅዱስ ብዕር መደበኛ አንዲሆን አምላክ ብርታቱ እና ዕድሜ እንዲሰጥዎት ከልቤ እመኛለሁ።
    ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ)

  2. ከህልፈተ-ጦቢያ ረጅም አመታት ቆይታ በሁዋላ ብቅ በማለትዎ ደስታዬ ወሰን የለውም። አማርኛዎ እንደ አማራ ደሮ ወጥ እጅ ያስቆረጥማል። የሃሳብ ልዩነት ጌጥ ነው። የሚሉትን ባልስማማበትም ጽሁፍዎን ወዲጄዋለሁኝ። የገረመኝ ግን በፊት በጦቢያ መጽሄት ሲጽፉት ከነበረው ምንም ለውጥ አላየሁባትም። Politics is an art of possibilities ያለው ማን ነበር አው አቶ ስንሻው? ያለፈው ሃያ አመት ያሳዬን ነገር ቢኖር ከሚጻፈው የተገላቢጦሹን ነው። እርስዎና መሰሎችዎ እምትጽፉት ነገር ጨለምተኝነት ያጠቃዋል። በሁሉም ነገር ራስህን ትክክለኛ፤ አገርወዳድ፤ የቁርጥ ቀን ልጅ፤ አድርጎ ሌላውን ቀለም በመቀባት ቁም ነገር መስራት አይቻልም። ፖለቲካህ ዋጋ የሚያወጣው ለሌላው ሃሳብ ክብርና ሰንሲቲቪቲ ሲኖርህ ነው። ካልሆነ “አገሮች ሁሉ ወደ ሶሻሊዝም ይመጣሉ” ይባል እንደነበረው ሁሉም ወደኛ ካልመጣ ማለትን ብትተዉ መልካም ነው። ጌታዬ 23 አመት ቀላል አይደለም። አዲስ ትውልድ ተተክቶ ቦታውን ይዞአል። ይህ ትውልድ የርስዎና ያቦይ ስብሃትን ፊውዳላዊ እስጥ አገባ የሚሸከም ትከሻ የለውም። የራሳችሁን ጊዜ በንትርክ ጨርሳችኋል። መንገዱን ለፌስቡክ ትውልድ ለቀቅ።

Comments are closed.

Share