March 8, 2022
3 mins read

ከፍተኛ ባልስልጣናትን ገድለዋል የተባሉት ከ15 ዓመት- እድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ተሰጠ፡

ሰኔ 15 ቀን፣ 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ግድያ ፈፅመዋል የተባሉ 31 ግለሰቦች ከ15 ዓመት እሰከ እድሜ ልክ በሚደርስ እሰራት እንዲቀጡ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ጉዳዩ ላለፉት 2 ዓመት ከ8 ወራት በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል፡፡ ክሱ ሲመሰረት በ55 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቶ የቆየ ሲሆን፤ 24ቱ በተለያዩ ጊዜዎች ከድርጊቱ ነፃ ሆነው ከማረሚያ ቤት ተሰናብተዋል፡፡ የ28ቱን ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ለዓለፉት ዓመታት ሲያከራክር ቆይቶ በ28ቱ ተከሳሾች ላይ ከ15 ዓመት እስከ 18 ዓመት በሚደርስ የእስራት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ 2 ተከሳሾች በ15 ዓመት፣ 2 ተከሳሾች በ16 ዓመት፣ 18 ተከሳሾች በ16 ዓመት ከ6 ወር፣ 2 ተከሳሾች በ17 ዓመት፣ 4 ተከሳሾች በ18 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ሲወስን 3 ተከሳሾች ደግሞ በሌሉበት በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ተመስገን ሲሳይ ለዶይቼ ቬሌ (DW) በሰጡት አስተያየት ፍርድ ቤቱ የመሰለውን ውሳኔ ቢያስተላልፍም ቅሬታ ያሉትን አስቀምጠዋል፡፡

«በውሳኔው የማልስማማባቸው ነጥቦች አሉ፣ እነዚህን የማልስማማባቸውን ነጥቦች ደግሞ ይግባኝ የምናቀርብባቸው ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንዱና ትልቁ በተለይም ጥፋተኛ የተባሉት አንዱ ትልቁ ነገር እዚህ ያሉት ተራ ወታደሮች ናቸው፣ ትዕዛዝ ተቀብለው የሚፈፅሙ ናቸው፣ ስለዚህ ይህንን በተመለከተ በቀረበበት ድምዳሜ አንፃር ተከሳሾቹ ይግባኝ ይቅረብልን የሚሉ ከሆነ ይግባኝ ምናቀርብበት ነው» ብለዋል፡፡

ውሳኔው በተላለፈበት ወቅት ፍርድ ከተሰጣቸው መካከል ጥቂቶቹ የመተከዝና የመረበሽ ገፅታ የታየባቸው ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ግን የተለየ ነገር አልታየባቸውም፡፡

የዛሬው ችሎት ሲካሄድ በርከት ያሉ የፀጥታ አካላት በአካባቢው በተጠንቀቅ ቆመው አካባቢያቸውችን በንቃት ሲቃኙ አርፍደዋል፡፡

ሰኔ 15 ቀን፣ 2011 ዓ.ም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንንና የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ፣ በርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት በስብሰባ ላይ እንዳሉ መገደላቸው፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የነበሩት አቶ ምግባሩ ከበደ ደግሞ በእለቱ ቆስለው ከቀናት በኋላ ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡

ዘገባ፥ ዓለምነው መኮንን፤ ለዶይቸ ቬለ (DW) ከባሕርዳር

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop