የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ መልዕክት ከዝዋይ ማረሚያ ቤት፡ ሰው ለሆኑ ሰዎች በሙሉ!

በጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፤ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት

‹‹ይህንን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች መወያየት ክልክል ነው፡፡›› በማለት በተንጎላጀጀ ድምፅ ጠባቂው ተናገረ፡፡ ቀጠል አደረገናም ‹‹መነጋገር የምትችሉት ስለቤተሰብ ጉዳዮች ብቻ ነው›› በማለት ተናገረ፡፡ ይህን ከላይ ያለውን ሐሳብ የሚመለከት ማንኛውም አንባቢ፣ ጉዳይ የተፈፀመው እዚህችው እማማ ኢትዮጵያ ሰማይ ስር ባሉ አጃኢበኛ እስር ቤቶች፣ ቤተሰብ መጠየቂያው እንደሆነ መጣራቱ አይቀርም፡፡

ይሁንና በመግቢያው ላይ ያለው ጽሑፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ ‹እናት› ከተሰኘውና እ.ኤ.አ. በ1906 ከታተመው የስመ ጥሩው ሩስያዊ ደራሲ ማክሲም ጎርኪይ ታሪካዊ ልቦለድ ገፅ 102 ላይ ነው፡፡ የዛሬ 108 ዓመት አካባቢ ማለት ነው፡፡ አቤት ርቀቱ!… ይህ ርቀት ግን ለእኛ ምንም ማለት ያልሆነ ይመስላል፤ ለምን? ቢሉ ዛሬም ይህንንና ይህን የመሳሰለውን አስፍተን እየሠራን እንገኛለን፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች እየተጓዝን ያለነው የቁልቁለት ሩጫ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኖ ይገኛል፡፡

የነገሮች ሁሉ መድረሻ እስር ቤቶች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ‹ጠበቅ ያለ እርምጃ፣ የማያዳግም እርምጃ፣ የማስወገድ እርምጃ፣…› ወዘተ የሞሉ ከሕግ መርሕዎች ሳይሆን ከጥላቻ ፖለቲካ የሚመነጩ ፀያፍ አነጋገሮችን በሕዝብ የመገናኛ ዘዴዎች ሲተላለፉ እየሰማን እየታዘብን ነው፡፡ ቃል በቃል ‹ቀይ ሽብር ይፋፋም› ብሎ ማወጅ የቀራቸው የሕግም የግብረገብም ሚዛን ያልወጣላቸው ቀረርቶች በተለይ በእስር ቤት የምንገኝ ኢትዮጵያውያንን እየሰበሰቡን ይገኛሉ፡፡

በኢ.ቴ.ቪ. የአብዮታዊ እርምጃ ፕሮግራሞች በቀረቡ ማግስት አሁን በዝርዝር ብለው የብዙ ቤተሰቦችን ስሜት ሊያሸማቅቁ የሚችሉ ሰቆቃና እንግልቶች በአስደማሚ ስልት ተቀናብረው ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡ እስኪ የተወሰኑትን እንይ፡፡ ማንኛውም ታሳሪ ቤተሰብ በቅርብ ሊጎበኘው በሚችለው እስር ቤት ይታሰር የሚለው ሕግ የተሻረው በእኛ ላይ ነው፡፡ ዝዋይ የአገራችን ‹ሳይቤሪያ ግዞት› ማለት ናት፡፡ ቤተሰብ ያን ያህል የበርሃ ጉዞ አቋርጦ የእኛዋ ሳይቤሪያ ሲደርስ በአድካሚና ግብረ-ገብ በጎደለው ፍተሻ መከራውን ማየቱ አንሶ ጆሮ ግንዱ ላይ በቆሙ የቤተሰብ አገናኞች ቤተሰባዊ ገመናውን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ሕፃናት ልጆች ወላጆቻቸው አንድ ላይ ሆነው ናፍቆታቸውን መወጣት አይችሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶቹ ሲዘናጉልን ልጆቻችንን አቅፈን እንስማለን፡፡ ይህ ከሆነ ቁጣና ዘለፋው ምንም አይደለም፡፡ ግን በሁኔታው ሕፃናቱ ክፉኛ ይበረግጋሉ፣ የእኛ ስጋት ይጋባባቸዋል፤ በዚህም መንፈሳቸው እርብሽብሽ ብሎ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  እነ ማን ነበሩ? አሁንስ ማን ናቸው? - ከገብረመድህን አርአያ

ሁኔታው በዚህ አያበቃም፡፡ ምንም እንኳን የመጠየቂያ ሰዓቱ በግልፅ የተቀመጠ ቢሆን ከቤተሰቦቻችን ጋር ገና መነጋገር ስንጀምር ‹‹በቃ… ቶሎ ጨርሱ›› የሚባልባቸው ጊዜዎች ብዙ ናቸው፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው የእስር ቤት ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማለትም ለሳሙና፣ ለምግብ ማጣፈጫ፣ ለሻይ ለቡና፣ ለውስጥ አልባሳት፣ ለውኃ ማከሚያ/ውኃ አጋር/ ወዘተ፤ ገንዘብ የሚያስፈልገን ቢሆንም እና እንደሚያስፈልጉ ቢታወቅም ጉዳዩ ለይቶለት የማሰቃየት፣ ማንገላታት፣ መበቀል ሆኗልና ለአንድ ወር ከአንድ መቶ ብር በላይ መጠቀም እንዳንችል የተከለከልን የመሆኑ አሳፋሪ ሐቅ ነው፡፡ ይህ እየተፈፀመ ያለው ደግሞ ዝዋይ እስር ቤት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ለመግለጽ በሚከብድ ሁኔታ ሰብኣዊ ክብራችንን የማዋረድ ሙከራዎች እየተፈፀሙ ነው፡፡

በአገራችን ላይ እኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የጨረስኩት ዝዋይ በመሆኑ ብዙ ወዳጅ ዘመዶቼ በእዚህ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ለአካባቢው ነዋሪዎች በሳምንት እንዲጠይቁን የተፈቀደላቸው አንድ ቀን /ረቡዕ/ ብቻ ሲሆን ‹‹የት ነው የምታውቁት? እንዴት አወቃችሁት? ምንድን ነው የሚያመላልሳችሁ?›› በሚሉትና በሌሎችም ጥያቄዎች ተደናግጠው መምጣቱን እርግፍ አድርገው ትተውታል፡፡

ሀገሩ ሞቃታማ ነውና በዚያ ላይ በእያንዳንዱ ቤት እስከ 150 ሰው ይታሰርበታል፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ እስረኛው የቱንም ያህል ፅዳቱን ለመጠበቅ ቢሞክርም የተባዩ መርመስመስ የእነ ትኋን እንዲህ መራባት፤ ለማሰብ እንኳን ይዘገንናል፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ገላን ሲቆፍሩ ማደር ነው፡፡ ሊናገሩት ይከብዳል፣ አንባቢንም ቅር ያሰኛል፤ ግን ይህ የፊልም ትረካ ሳይሆን በእማማ ኢትዮጵያ ልጆች ላይ ሆን ተብሎ እየተፈፀመ ያለ ደባ ነው፡፡ […] ግን የባሰ አታምጣ ማለት ነው!

ግን የባሰ ነገር አለ፡፡ አፈር ቅጠል የማይል ምግብ ይቀርብናል፡፡ ‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ› ከፍተኛ የውኃ እጥረት /ዝዋይ ሀይቅ አናት ላይ ተቀምጠን/ አለ፡፡ የእስር እስር እንዲሉ ጄኔራል መኮንኖቹን ጨምሮ አብዛኛዎቹ አባሪዎቻቸውና ሌሎች ሌሎች የተወሰንን እስረኞች የምንገኘው በልዩ ቅጣት ጭለማ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ እንደምንም ለመቋቋም ጥረት ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡ አዲሱ ስልት ግን መዘዙ በጣም አደገኛ በመሆኑ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ እያንዳንዱ ሃይማኖት ያለው፣ ፈርሐ እግዚአብሔር ያለው፣ እያንዳንዱ የመሠረታዊ ሰብኣዊ መብቶችና ነጻነቶች መከበር የሚያሳስበው እያንዳንዱ ሰው የሆነ ሰው ሁሉ ሊያውቀው ይገባል ስንል ድምፃችንን እናሰማለን፤ በሕክምና ንፍገት ወደሞት እየተገፋን ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዩክሬን ወረራ (በአንድ ኢትዮጵያዊ ዕይታ) - አንዱ ዓለም ተፈራ 

ከወር በፊት ገደማ ወጣቱ የአንድነት ፓርቲ አባል ናትናኤል መኮንን ለሕክምና በሪፈር ወደ ቃሊቲ ተልኮ የነበረ ቢሆንም፣ የዛኑ ዕለት ሕክምናውን ተነፍጎ ከሌሊቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ እስካሁን በሕመሙ እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ የኢብአፓ ሊቀመንበር የነበረው ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር እንደዚሁ ለተጨማሪ ሕክምና ሪፈር ተብሎ ሲጠባበቅ ከቆየ በኋላ ዘዴው ተፈፃሚ ሆነበት እጁን አጣጥፎ ተቀምጧል፡፡ ከሕመሙ ጋር በተያያዘ በአካሉ ላይ አሳሳቢ ሁኔታ እየታየበት ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ገልጬው የነበረው የእኔ የኩላሊት ሕመም አሁን ለመቀመጥም፣ ለመንቀሳቀስ እያወከኝ የሚገኝ ሲሆን፣ እኔን ከቃሊቲ ዝዋይ ለማምጣት የተደረገው የተቀናጀ መረብ ሩብ ያህሉን ለሰብኣዊነት አውለውት ቢሆን ኖሮ እኔም ፋታ፣ እነሱም እርካታ ባገኙ ነበር፡፡ ሕመም ካልታከመ መጨረሻው ሞት ነው፡፡ የሞቱም ሰዎች አሉ!

የጄኔራል መኮንኖቹ አባሪዎች የነበሩት ኮረኔል ተስፋዬ ኃይሉ እና ኢንጂነር ክፍሌ ስንሻው፣ በዶክተር መረራ በሚመራው ኦሕኮ ፓርቲ አባል የነበሩት አሕመድ ነጃሺ፣ በጭለማ ቤት የከረመው ተስፋሀን ጨመዳ፣ የቤንሻንጉሉ አዛውንት ወዘተ ተገቢውን ሕክምና በማጣት ሕይወታቸውን ያጡ የእማማ ኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡ እንዴት ሕክምና ይከለከላል!? ግፍና ጭቆና ተቃውመው ደማቸውን ያፈሰሱና አጥንታቸውን የከሰከሱ ታጋዮችን በሥልጣን ማግስት ከፍርድ በመለስ በየእስር ቤቱ ያሉ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸው በሕክምና እጦት ሲረግፉ በእርካታ ማርመምን ከየት ተማሩት!? የኢትዮጵያ ሕዝብስ ምን ይላል!? ሰው የሆኑ ሰዎች ሁሉ ከቶ ምን ይላሉ!?

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

(ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታተመው ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ የተወሰደ)

4 Comments

  1. This is inhuman and unbelievably scary. Humanity is more authority and political leaders need to address this type of abuse/genocide if they really ant to leave a country that will be equally shared with all people/nations.
    let God help them to get back to the human side of their being.

  2. May God be with you all and keep you safe.

    I saw every thing in this piece and it is true. I have been to Kality for some time, no one would believe what I have been through. But I can say one thing, in a room of 350 – 400 people inside with different background and life style used to live and slept together. The room temprature, bed bugs bad smell and don’t ask about the food( I used to ate it so many times it’s nick name was “Deyas”) was our day to day life and almost nobody had ever been sick except few related to age and previous health issues and newcomers got sick as soon as they got in and also very tough stressand humilation by the guards, guess why every body weren’t sick? God was always there all night and all day this is not fiction or lie I have been there and I witness How God was great even if you are in hell. I pray freedom, peace, strength and love for all of the victims and their families. God bless you all.

    Please people let’s pray regardless of our religious affiliation

  3. How long we gonna let our heroes down,it is complit betrayal on our side.we give every excuse for our silence,the fact of the matter is,we betrayed them.shame on us.when I read such kind of heart breaking article about the agony of our sisters and brother in Woyane prison,I hate my self.some times I cry and ask God why he forgets Ethiopia.why God send these evils(woyanes) on our people?why???are we dead or alive?if I can not do some thing to fight evil,how can I say I am alive?what is the meaning of life if I can not save the ones who are suffering for the sake of truth?how can I call my self I am a believer,while I am betraying the word of God?

  4. እውነት ማምለጫዋ ይርቅ እንደሆነ እንጅ አንድ ቀን ማሸነፏ አይቀርም።
    እግዚአብሄር ከእናንተ ጋር ይሁን።

Comments are closed.

Share