ዕውቅና ለሚገባው የተሰጠ ተገቢ ዕውቅና— ለመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተፈራ ደግፌ

የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተፈራ ደግፌ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ዕለት በሚያስመርቀው ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ እና የ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ለ5 የላቀ አስተዋፅዖ ላደረጉ የቀድሞው የባንኩ አመራሮች የአክብሮትና የዕውቅና የምስክር ወረቀት እንዱሰጣቸው አድርጓል። ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ አባት የሚባሉት ዶ/ር ተፈራ ደግፌ አንዱና ዋነኛው ናቸው።

የኢትዮጵያ የባንክ ሥርዓት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ብዙ ባለሙያዎች አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የአገሪቱን የባንክ ዘርፍ የመሩት የመጀመሪያዎቹ የባንክ ሥራ አስኪያጆች የውጭ አገራት ዜጎች ነበሩ። ‹‹ኢትዮጵያውያን ለባንክ ሥራ አመራር ብቁ አይደሉም›› የሚለውን አስተሳሰብ በመስበር አመራሩን ከነዚህ ዜጎች ተረክቦ ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ ቀላል አልነበረም። በዚህ ከፍተኛ ጥረትና ጥበብ በሚጠይቅ መንገድ ተጉዘው ዘርፉን ውጤታማ ካደረጉት ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያውያን መካከል አቶ ተፈራ ደግፌ ግንባር ቀደምት ተጠቃሽ ባለሙያ ናቸው።

ዶ/ር ተፈራ የተወለደው ሰኔ ስምንት ቀን 1918 ዓ.ም. በቀድሞው የሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ አንኮበር አውራጃ፣ አንበሴ በሚባል ቀበሌ ነው። አባቱ አቶ ደግፌ በላይነህ፤ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ እርገጫቸው ገብረ ማርያም ይባላሉ። እድሜው ሰባት ዓመት ሲሆን ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአክስቱ ወይዘሮ ጌጤ ገብረማርያም ዘንድ መኖር ጀመረ። ከአንድ ቄስ ዘንድ ፊደል ከቆጠረ በኋላ አሊያንስ ፍራንሲስ (Alliance Française) በሚባል የፈረንሳይኛ ትምህርት ቤት ገብቶ ዘመናዊ ትምህርት መማር ጀመረ።

በትምህርት ቤቱ ለሁለት ዓመታት ያህል እንደተማረ በ1928 ዓ.ም. የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በመውረሩ ትምህርት ቤቱ ተዘጋ፤ ተፈራም ትምህርቱን አቋረጠ። ተፈራ በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ኢጣሊያ የወራራ ዘመን የኖረው ሌቭድሮዝደቭስኪ ከተባሉ የሩስያ ዜጋ ጋር ነበር። በጊዜውም ታዳጊው ተፈራ የሰውየው ረዳት ሆኖ አገልግሏል። ከሰውየው ልጅ ጋር በመማርም የሩስያና የጣሊያንኛ ቋንቋዎችን አወቀ። በነዚህ ቋንቋዎችም ብዙ መጽሐፍትን ማንበብ ቻለ።

በ1933 ዓ.ም. የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ሲባረር የተፈራ ረዳት የነበሩት የውጭ አገር ዜጎች ከኢትዮጵያ ስለወጡ ታዳጊው ተፈራ ከባድ የሕይወት ፈተና አጋመው። የትምህርት ዕድል ስላላጋጠመውም በአንድ የስፌት መኪና ኩባያ ውስጥ በአስተርጓሚነት ተቀጠረ። በኩባንያው ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ከሠራ በኋላ የመማር ጉጉት ስለነበረው ሥራውን ለመተው ወሰነ።

 

እንዳጋጣሚ ሆኖ አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ (State Bank of Ethiopia) ቋንቋ የሚያውቁ ሠራተኞች እየፈለገ ይቀጥራል መባሉን ሰምቶ ማመልከቻውን በፈረንሳይኛ ቋንቋ አቀረበ። የባንኩ ሥራ አስኪያጅም ተፈራ እንዲቀጠር ፈቀዱ። በ1936 ዓ.ም. በ18 ዓመቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በጸሐፊነት (Filing Clerk) ተቀጠረ። ሥራውን ለማከናወን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ አስፈላጊ ስለነበር ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ‹‹ብሪቲሽ ኢንስቲትዩት›› በተባለው ተቋም እንግሊዝኛ ለመማር ተመዘገቡ። በባንኩ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ከሠራ በኋላ ከሌሎች ወጣት ሠራተኞች ጋር ተመርጦ ትምህርቱን ለማሻሻል ኮተቤ ወደሚገኘው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተላከ። ለአንድ ዓመት ተምሮ በ1938 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ካናዳ ተላከ። ይህም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ካናዳ ከተላኩት የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መካከል አንዱ ያደርገዋል። ካናዳ እንደደረሰም መጀመሪያ ያመራው ካልጋሪ፣ አልበርታ ወደሚገኘው የንግድ ኮሌጅ (Garbutt Business College) ነበር። በአንድ ዓመት ውስጥ ትምህርቱን ጨርሶ በዲፕሎማ ተመረቀ። ወዲያውኑም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለመቀጠል ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ (University of British Columbia – UBC) ገባ። ኮሜርስ ፋኩሊቲ በየዓመቱ የበጋ ትምህርት ጭምር እየወሰደ በ1942 ዓ.ም. በዲግሪ ተመረቀ። ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት የሕግ ትምህርት ተከታትሎ በ1945 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የባንክ አገልግሎቱን ቀጠለ።

እነ ተፈራ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ባንኩ አድጎ፤ የሠራተኛው ቁጥርም ጨምሮ ነበር። ሌሎች ሠራተኞችም ትምህርትና የባንክ ሥራ ሥልጠና እንዲያገኙ እነ ተፈራ ማሳሰብ ጀመሩ። ሠራተኛው በየደረጃው የማታ ትምህርት እንዲከታተል ታስቦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በባንኩ ዕርዳታ የማታ ትምህርት የሚያስተምሩ ምሁራን ተቀጠሩ። የባንክ ሠራተኞች ትምህርት ከጀመሩ በኋላ ከሌሎችም መንግሥታዊ ድርጅቶች ብዙ የማታ ተማሪዎች ተመዘገቡ። የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ሊደረጅ የቻለው በባንክ ድጋፍ የተጀመረው ትምህርት ተስፋፍቶ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መነሻና መዳረሻችን የሕዝባችን ክብርና ጥቅም ማስከበር ነው!

የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ተወግዶ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደገና በመቋቋም ላይ ሳለ ኢትዮጵያ የራሷን ባንክ ለማቋቋም ስትነሳ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋት ነበር። እንግሊዝ በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረውን የባንክና የገንዘብ ሥርጭት ከምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛቶቿ ጋር አቀላቅላ የማስተዳደር ፍላጎት ነበራት። ሆኖም ችግሩን በውስጥ ምክርና ድፍረት በማለፍ በ1934 ዓ.ም ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ›› በአዋጅ እንዲቋቋም ተደረገ።

በጦርነቱ ጊዜ የታላቋ ብሪታኒያን የጦር ሠራዊት ተከትሎ መጥቶ የኢጣሊያ ባንኮችን አስወግዶ የባንኩን ሥራ ተረክቦ የሚያስተዳድረው ባርክሌይስ ባንክ (Barclays Bank) ነበር። ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ›› ይህንን የእንግሊዝ ባንክ ተክቶ ነው ሥራውን የጀመረው። ባንኩ የተዋቀረው የጠቅላይ (ማዕከላዊ) ባንክንና የንግድ ባንክን ሥራ አጣምሮ እንዲሠራ ነው። ባንኩ ሥራውን ሲጀምር የነበሩት አብዛኞቹ ሠራተኞች የውጭ አገራት ዜጎች ነበሩ። ብዙዎቹ ከኢጣሊያ ወረራ በፊት የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ ሲያገልግሉ የነበሩ ናቸው።

ሠራተኛው እርስ በእርስ እየተረዳዳ ይማማር ነበር፤ የባንኩ ሥራ እየተስፋፋ ሲሄድ የገጠር ቅርንጫፎች መከፈት ጀመሩ። የእነዚህ ቅርንጫፎች ኃላፊዎችም የውጭ አገራት ዜጎች ነበሩ። በ1937 ዓ.ም. አዲስ የኢትዮጵያ ገንዘብ በአሜሪካ በምስጢር ተዘጋጅቶ ታውጆ ወጣ። በዚህም የኢጣሊያ ሊሬ እና የምሥራቅ አፍሪካ ሽልንግ በአዲሱ የኢትዮጵያ ብር ተለወጠ። የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክም የባንክ ሥራው ቀስ በቀስ እየሰመረለት ሄደ። የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ እንደ ንግድ ባንክ ሆኖ ሲሠራ መጀመሪያ የሚሰጠው አገልግሎት የተንቀሳቃሽ ሂሳብና የገንዘብ ማዛወር /ማስተላለፍ ሥራ ነበር። ሥራው እየደረጀ ሲሄድ ተደራቢ ሥልጣን ተሰጠው። በ1938 ዓ. ም የቁጠባ ሂሳብ (Saving Account) አገልግሎት መስጠት ጀመረ:: የባንኩን ሥራ ለህዝቡ ለማለማመድና በባንኩ እምነትን ለመፍጠር ብዙ ዓመታትን ፈጅቷል። ባንኩ በሠራተኞቹ ትጋትና በመንግሥት ድጋፍ ሁለገብ ድርጅት ሆኖ ጠቅላላ የባንክ አገልግሎትን ማስፋፋቱን ቀጠለ። ዘመናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲጀመርና ትምህርትም እየተስፋፋ ሲሄድ ኢትዮጵያውያን ሥራውን እየተላመዱ፣ የባንኩን የአመራር ሥራም እስከመያዝ በቁ። ታዲያ በነዚህ ሁሉ ሂደቶች ውስጥ የእነ ተፈራ ጥረትና አበርክቶ ከፍተኛ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በውጭ አገራት የሚሠሩ ሁለት ቅርንጫፎች ነበሩት። የመጀመሪያው የትራንዚት ሥራ የሚሠራ የጂቡቲ ቅርንጫፍ ነበር። ሁለተኛው ለባንክ አገልግሎት ሱዳን ውስጥ የተቋቋመው የካርቱም ቅርንጫፍ ነበር። እ.ኤ.አ በ1957 የወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክትል ሚኒስትር በነበሩት አቶ ጌታሁን ተሰማ የሚመራ የንግድ ልዑካን ቡድን ወደ ሱዳን ሲሄድ ተፈራም የቡድኑ አባል ሆኖ ሄደ።

የቡድኑ ጉዞ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የነበረው ንግድ የሚዳብርበትን ዕቅድ ለማጥናትና የንግድ ውል ለመደራደር ነበር። ለዚህ ዓላማ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ቅርንጫፍ በካርቱም ቢከፈት ለሁለቱ አገሮች የጋራ ንግድ እንደሚረዳ ታምኖበት ጥያቄው ቀረበ። የሱዳን መንግሥትም የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ቅርንጫፍ በካርቱም እንዲቋቋም ፈቀደ።

የንግድ ልዑካኑ ሪፖርት ቀርቦ ከተፈቀደ በኋላ ለታቀደው የባንክ ቅርንጫፍ ብቁ የሆነ ሥራ አስኪያጅ በአስቸኳይ ተመርጦ እንዲቀጠር ባንኩ ታዘዘ። በወቅቱ የባንኩ ገዥ የነበሩት አሜሪካዊ ጆርጅ ሬይ ‹‹በሥራው የሰለጠነ ኢትዮጵያዊ የለም›› በማለት የአንድ እንግሊዛዊ ዜጋ ስም አቀረቡ። ይሁን እንጂ ‹‹ለታቀደው ዓላማ የውጭ ዜጋ አይበጅም›› ተብሎ የባንኩ ምርጫ ውድቅ ሆነ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከዓባይ በፊት ሴረኝነታችሁን ገድቡልን

በዚያን ጊዜ አቶ ተፈራ የሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ይሠራ ነበር። አቶ ተፈራ የባንኩን የካርቱም ቅርንጫፍ እንዲመሩ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በጽሕፈት ሚኒስቴር ማዘዣ ተሾሙ። ከምክትል ሥራ አስኪያጁ ከአቶ ከበደ ሠረቀ ብርሃን ጋር ሆነው ቅርንጫፉን ለማቋቋም ወደ ሱዳን ሄዱ። ከዋናው መሥሪያ ቤት አራት ኢትዮጵያውያን ኃላፊዎች ተመርጠው ተልከው በ1950 ዓ.ም. የባንኩ የካርቱም ቅርንጫፍ ተከፈተ። ለቅርንጫፉ የሚስማሙ ሱዳናውያን እየተመለመሉ እንዲሰለጥኑና እንዲቀጠሩ ተደረገ። በተቻለ መጠን የባንኩ ገጽታ አፍሪካዊ እንዲሆንም ጥረት ተደርጓል። ቅርንጫፉ በአጭር ጊዜ ብዙ ደንበኞችን አፍርቶ ተወዳጅ ሆነ። የባንኩ ሙሉ ስም ለዓረብኛ ተናጋሪዎች ስለሚያስቸግር የባንኩ ደንበኞች ቅርንጫፉን በወዳጃዊ አጠራር ‹‹ባንክ ኤል ሐበሺ›› ብለው ሰየሙት።

በወቅቱ ሱዳን ውስጥ ስድስት የውጭ አገራት ባንኮች ነበሩ። ከነዚህ መካከል ብቸኛው አፍሪካዊ ባንክ/ቅርጫፍ ደግሞ የኢትዮጵያው (የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የካርቱም ቅርንጫፍ) ነበር። በአቶ ተፈራ ደግፌ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የካርቱም ቅርንጫፍ ከደረጁ የምዕራባውያንና የዓረብ አገራት ባንኮች ጋር ተወዳድሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ደንበኞች ማፍራትና አትራፊ ለመሆን በቃ። ይህም ቅርንጫፉ ለኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አስችሎታል።

የካርቱሙ ቅርንጫፍ ለአስር ዓመታት ያህል ካገለገለ በኋላ በጄኔራል ኒሜሪ ዘመነ መንግሥት እ.ኤ.አ በ1969 የግል ባንኮች ሁሉ በሱዳን መንግሥት ሲወረሱ አብሮ ተወረሰ። በ1960ና በ1970ዎቹ በአገር ውስጥ ለባንክ አመራር ብቁ ሆነው ያገለገሉት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የባንክ ባለሞያዎችና ኃላፊዎች ካርቱም ቅርንጫፍ እየሠሩ በቂ ልምድ ያገኙ ናቸው። ለአብነት ያህልም አቶ ከበደ ሠረቀብርሃን፣ አቶ መስፍን በለጠ፣ አቶ ታደሰ አበበ፣ አቶ ስሜ ታከለ፣ አቶ ቸርነት በየነ፣ አቶ ተሳለ ወርቁ፣ አቶ ጌታቸው ደስታ እና ወይዘሮ በላይነሽ ማንደፍሮ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች ታዋቂ የባንክ ባለሙያዎች ሆነው እያንዳንዳቸው በብሔራዊ ባንክና በንግድ ባንክ ውስጥ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ መድረስ ችለዋል።

እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ገዥዎች የውጭ አገራት ዜጎች ነበሩ። ኢትዮጵያውያን በከፊል ሥልጣን መጋራት የጀመሩት አቶ የወንድ ወሰን መንገሻ እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም የባንኩ ምክትል ገዥ ሆነው ሲሾሙ ነው። በ1953 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ደግሞ አቶ ተፈራ ደግፌ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የባንኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ። ይህ የአቶ ተፈራ ሹመት ‹‹ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክን ለመምራት ብቁ አይደሉም፤›› የሚለውን አስተሳሰብ ውድቅ ያደረገና ከ1937 እስከ 1952 ዓ.ም. ድረስ በስድስት የውጭ አገራት ዜጐች ሲተዳደር የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክን በኢትዮጵያዊ ሥራ አስኪያጅ መመራት መጀመሩን ያበሰረ የለውጥ እርምጃ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።

አቶ ተፈራ የሥራ አስኪያጅነቱን ሥራ ከተረከቡ በኋላ ከሠራተኞቹ ጋር በመተባበር ሥራው ሳይዛነፍ በሚገባ እንዲቀጥል ማድረጋቸው ምስጋናና አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል። በባንኩ ድጋፍ አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያው የአክሲዮኖችና የገንዘብ ሰነዶች መሸጫ ገበያ ተቋቋመ። የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት መግለጫም ተሻሽሎ መታተም ጀመረ። ከዚያ ቀደም ያልታየና ከፍተኛ የሆነ የብድር ዕድገት፣ የቅርንጫፎች መስፋፋትና የገቢ መጨመር ተመዘገበ።

የአገር ውስጥ ንግድ መንቀሳቀስ ሲጀምር ልማቱን ለማበረታታት ቀስ በቀስ የባንክ አገልግሎትም በየከተማው በመጠኑ መሰራጨት ጀመረ። የተሟላ የባንክ አገልግሎት በአዲስ መልክ ለማቋቋም ዕቅድ ወጣ። ይህ የባንክን አቋም የማሻሻል ዕቅድ ሰፊ ጥናት እንደሚያስፈልገው ታውቆ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ( International Monetary Fund – IMF) አንድ ባለሙያ በመቅጠርና ጥናት በማስጠናት አዲስ የባንክ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለፓርላማ ቀረበ። በአዋጁ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ለሁለት ተከፍሎ አንዱ ማዕከላዊ (ብሔራዊ) ባንክ፤ ሌላው ደግሞ የንግድ ባንክ ሆነው እንዲቋቋሙ ተወሰነ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከማይናማር ለተፈናቀሉ ሙስሊሞች እርዳታ ሲያጓጉዝ የነበረ መኪና ተገልብጦ ሰዎች ሞቱ

በታህሳሥ 1956 ዓ.ም ሁለቱ ባንኮች (‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ›› እና ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ››) ተደራጅተው ሥራቸውን ጀመሩ። አቶ ምናሴ ለማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ፤ አቶ ተፈራ ደግፌ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ1960ዎቹ ከፍተኛ ዕድገት ሲያስመዘግብ አቶ ተፈራ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ይመሩት የነበረውና በ20 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነበር።

ባንኩ በአዲስ መልክ ሥራውን እንደጀመረ ዋና ዕቅዱ ሠራተኞቹን ማሰልጠንና የባንክ ቅርንጫፎቹን ማስፋፋት ነበር። የባንክ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ማዕከል በመክፈት የሠራተኞቹን አቅም ለማሳደግ ሰፊ ጥረት አድርጓል። በዚህም ባንኩ ጥሩ አፈፃፀም እንዲኖረው ማድረግ ተችሏል። ሌሎች የገንዘብና የመድን ተቋማት ያለባቸውን የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለልም ሚናው የጎላ ነበር።

አቶ ተፈራ ባንኩ አዳዲስ አሠራሮችን እየተገበረ፣ የሠራተኞቹን አቅም እያጎለበተ፣ የቅርንጫፎቹን ቁጥር እየጨመረ፣ ከውጭ አገራት ባንኮችና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ግንኙነት እየፈጠረ … ከፍተኛ መሻሻል እንዲያሳይና አስደናቂ ዕድገት እንዲያስመዘግብ እንዲሁም የብድርና የቁጠባ አቅሙን እያሳደገ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። በእርሳቸው ፋና ወጊነት የተጀመረው የኢትዮጵያውያን የባንክ መሪነትም እስካሁን ድረስ ተጠናክሮ ዘልቋል። ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ በመሆን አገልግለዋል።

ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን በያዘ ማግሥት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወርሶ በብሔራዊ ባንክ ሥር ሆነ። አቶ ተፈራም ‹‹ለአብዮቱ እንቅፋት እንዳትሆን›› ተብለው ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ያህል ለእሥራት ተዳረጉ። ከእሥራት ከተፈቱ በኋላም ኑሯቸውን በተማሩባት ካናዳ አድርገው ቆይተዋል። በዚምባብዌና በስዋዚላንድ የባንክ አማካሪ ሆነውም ሠርተዋል። የተማሩበት ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲም የሕግ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል። በአዲስ አበባ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸውን ለአዲስ አበባ የፌስቱላ ሆስፒታል በስጦታ ያበረከቱት አቶ ተፈራ፤ ከካናዳዊት ባለቤታቸው ሁለት ልጆችን አፍርተዋል። አንጋፋው ባለሙያ በሥራቸው ላበረከቷቸው አስተዋፅዖዎች የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ‹‹A Tripping Stone›› እና ‹‹Minutes of an Ethiopian Century›› የተሰኙ መጻሕፍትንም ጽፈዋል።

የማኅበራዊ ጥናት መድረክ (Forum for Social Studies – FSS) በ1999 ዓ.ም ‹‹ከድህነት ወደ ልማት፣ ዕውቀትን ለትውልድ ማስተላለፍ›› በሚል ባዘጋጀው የውይይትና የገለፃ መርሃ ግብር ላይ አቶ ተፈራ ‹‹የባንክ ዕድገት ለአገሪቱ ልማት ያደረገው አስተዋጽኦ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ ‹‹ … በ1991 ዓ.ም. ለአቢሲኒያ ባንክ ምረቃ ተጋብዤ ወደ አዲስ አበባ በመጣሁበት ጊዜ በጦቢያ መጽሔት ተጠይቄ ቃለ ምልልስ ተለዋውጠን ነበር። ለአገሬ ያለኝን ራዕይና ምኞት ተጠይቄ በሰጠሁት ምላሽ ‹እኔ ለኢትዮጵያ የምመኘው ከጦርነት ውጥረትና ከሚያስከትለው ጥፋት አምልጠን በመልማት ላይ እንዳሉት ሌሎች አገሮች ወደ ልማቱና ማኅበራዊ ዕድገት እንድትደርስ ነው። ለዚህ ደግሞ ራዕይ ያለው አመራር፣ ተግባብቶ የሚኖር ሕዝብ፣ በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ የሚኮራና አገሩን የሚያስከብር ዜጋ መኖር ወሳኝ ነው› ብዬ ነበር። አሁንም ምኞቴና ጸሎቴ ይኸው ነው›› በማለት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የባንክ ሥርዓት እንዲዘምን ካደረጉት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት አቶ ተፈራ ደግፌ፤ የካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም በተወለዱ በ89 ዓመታቸው አርፈው ሥርዓተ ቀብራቸው በቫንኩቨር ካናዳ ተፈፅሟል።

የሕይወት ታሪክ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ/ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share