ከማይናማር ለተፈናቀሉ ሙስሊሞች እርዳታ ሲያጓጉዝ የነበረ መኪና ተገልብጦ ሰዎች ሞቱ

ማይናማር ውስጥ እየተፈጸመባቸው ያለውን አሰቃቂ ጥቃት በመሸሽ ሀገር ጥለው ለተሰደዱ ሙስሊሞች እርዳታ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ መኪና ተገልብጦ የሰዎች ህይወት ተቀጠፈ፡፡ ሮሂንጊያዎቹ ወደሚገኙበት የባንግላዴሽ ድንበር እርዳታ በማጓጓዝ ላይ የነበረው የጭነት መኪና መገልበጡን ተከትሎ ዘጠኝ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ከአስር በላይ የሚሆኑ ደግም መጎዳታቻውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

እንደዘገባው፣ መኪናው አደጋ ያጋጠመው ዳገት በመውጣት ላይ ሳለ ሲሆን፣ ተንሸራቶም ከአንድ የሩዝ ማሳ ውስጥ ሊገለበጥ ችሏል፡፡ በማይናማር በሙስሊሞች ላይ የተከፈተውን የጥቃት ዘመቻ ተከትሎ በርካታ ሮሂንጊያዎች ሀገር ጥለው ወደተለያዩ አካባቢዎች በመሸሽ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ የጥቃት ሰለባዎቹ ከሸሹባቸው ሀገራት አንዷ ባንግላዴሽ ስትሆን፣ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይም በርካታ ስደተኞች ሰፍረው ይገኛሉ፡፡

የተጠቀሰው የመኪና አደጋ ከደረሰ በኋላ ስድስት ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ ሶስቱ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ መሞታቸውን ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡ በስፍራው ያለውን የቀይ ጨረቃ ማህበር ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች የቀን ሰራተኞች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም አደጋው ደርሶባቸው ከሞት የተረፉትም የቀን ሰራተኞች ሲሆኑ፣ ሟቾቹም ሆነ ተጎጂዎቹ እርዳታውን ለማከፋፈል አብረው ሲጓዙ የነበሩ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ ከማይናማር ወደ ባንግላዴሽ የሚፈልሱ ሮሂንጊያዎች ቁጥር እያሻቀበ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስም ቁጥራቸው 422 ሺህ መድረሱን ዘገባው አመልክቷል፡፡

 

Source: BBN News

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕወሃት አይኑን በጨው አጥቦ፣ ራሱ መራጭ፣ ራሱ ተመራጭ፣ ራሱ ታዛቢ፣ ራሱ ምርጫ ቦርድ (ከአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበራት የተሠጠ መግለጫ)
Share