በጀርመን ውስጥ እንደ አውሮፓውያን አቆጠጠር 1971 ጀምሮ የዓመቱ ምርጥ ቃል ይመረጣል። ይህ በየዓመቱ የሚደረገው ምርጫ አዲስ የተፈጠሩ አባባሎች ወይም ቃላቶች አሮጌም ቢሆኑ በአለፈው ዓመት ውስጥ የአጠቃቀማቸው ሁኔታ ታይቶ የሚካሄድ ብሂል ነው። ለአሸናፊነት የሚበቃው ቃል በሕብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያገኘው ይሆናል። ምርጫው በኮሚቴ ዳኝነት ተሳታፊዎቹን ቃላቶች አወዳድሮ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘውን አሸናፊ ያደርጋል።
በዚህ ውድድር ማንም ሰው ሊያሸንፍ ይገባዋል የሚለውን ቃል መጠቆም ይችላል። በዚህ ዓመት የተመረጠው ቃል አሸናፊ የሆነው ከተጠቆሙት ከ2400 ቃላቶች ውስጥ ከፍተኛውን ድምጽ አግኝቶ ነው። ከተጠቆሙት 2400 ቃላቶች ውስጥ 10 ቃላት በዳኞች ይመርጡና ለሕዝብ ለድምጽ ይቀርባሉ ። ከዛም ሕዝብ ድምጽ ይሰጥበትና አሸናፊው ይወሰናል። ጀርመኖች በተለይ ከሥነ ጽሁፍ ጋር ግንኙነት
ያላቸው ቃላትን ያከብራሉ። በዓመቱ ውስጥ የዓመቱ ቃል ብቻ አይደለም የሚመረጠው። ሌሎችም ለምሳሌ የወጣቶች የዓመቱ ቃል፣ የሽማግሌዎች የዓመቱ ቃል ወዘተ . . .የሚባሉ የተለያዩ ምርጫዎች አሉ.።
በ2013 የጀርመን የዓመቱ ቃል ሆኖ ያሸነፈው “GROKO“( grossen Koalition) ሆኗል። ይህ ቃል ከሁለት ቃላት የተፈጠረ ነው። grossen – ትልቅ . . . . Koalition – ጥምረት ማለት ነው። አንድ ላይ ሲሆን ትልቁ ጥምረት ማለት ነው። ቃሉ የተመረጠው ጀርመኖች በዚህ ዓመት ምርጫ አካሂደው በዚህ ምርጫ ሁለቱ ትልልቅ ፓርቲዎች ማለትም ሶሻል ዲሞክራቱም (SPD) ሆነ ወግ አጥባቂው (CDU) ሃገሪቱን ብቻቸውን ለመምራት የሚያስችል ድምጽ ባለማግኘታቸው ጥምረት መፍጠር ስለነበረባቸው ነው። ጥምረቱን ለመፍጠር ብዙ ወራት የወሰደ ድርድር አድርገዋል። በዚህ ድርድር ወቅት ጋዜጠኞች አጭር ቃል ፈጥረው ነበር ይህን ቃል “GROKO“ የሚል ስያሜ ሰጥተው ነበር። ይህ ቃል ነው የዚህ ዓመት አሸናፊ የሆነው።
በእኛም ሃገር ይህንን መጀመር ያስፈልግ ይሆናል። በተለይ በዚህ ዓመት በወያኔ በታሰሩት የሃይማኖት መሪዎች ምክንያት የተፈጠሩ ቃላቶች አሉ።“ አል ሃብሽነ“Al Habash” ወይም ዋሃቢነት “Wahhabism” “ድምጻችን ይሰማ“ ለውድድር ሊቀርቡ ይችላሉ። ከሳውዲ ስለተመለሱት ስደተኞቻችንም በተመለከተ “የመጀመሪያው ሒጂራ“ የሚል ቃል ነበር። ቴዎድሮስ አፍሮ አለ የተባለው “ቅዱስ ጦርነትም“ ለውድድር መቅረብ ይችላል። ከዛው ተያይዞ “ጡት ቋራጭ“ የሚለውም የነ ጃዋር ክስ ሊወዳደር ይችላል። ለነ ጃዋር የወጣውም “ሜንጨኞች“ የሚለው መጠሪያ ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል። በሃገሪቱ የታወቁ ድረ ገጸች ይህንን ቢያዘጋጁና ድምጽ ቢያሰጡበት ጥሩ ይሆን ነበር።
ከዚሁ ከጀርመን ሳንወጣ ለውድድር አይቅረቡ እንጂ በኢትዮጵያውያን አዳዲስ የአማርኛ ቃላትም ተፈጥረዋል። እነዚህ ቃላት ቢወዳደሩ ሊያሸንፉ ይችላሉ። ከሁሉም ያስደነቀኝና ሊያሸንፍ ይችላል ብዬ የማምነው ቲታኒክ (Titanic) የሚለው መጠሪያ ነው። ይህ መጠሪያ የተሰጣቸው በሰሃራ በረሃ አድርገው፣ ሜዲትራንያን አቋርጠው፤ ላፓዱሳ ላይ ባሕር ላይ ሳይሰምጡ አውሮፓ የደረሱ ዜጎቻችንን ነው። ይህ ስም አትላንቲክ ውስጥ የሰመጠችውን ታላቋን መርከብ ቲታኒክ (Titanic) በማስታወስ ነው። አንድ ሰው በሳሃራ አቋርጦ አውሮፓ የደረሰ ከሆነ እሱ “ቲታኒክ” ነው ይባላል። በዚሁም ብዙ ዜጎቻችን ከአደጋ ተርፈው አውሮፓ ገብተዋል። “ቲታኒኮች” ብዙ የሚተረክ ታሪክ አላቸው። በዚህ ዓመት የጀርመንን የአማርኛ ቋንቋ በአንድ ቃል ከፍ አድርገውታል።
በጀርመን አዲስ ቃላቶች እየተፈጠሩ ቢሆንም በሌሎች አገሮች ደግሞ ያሉትን ቃላት መጠቀም እንዳይቻል አዲስ ሕግ ለማውጣት ሙከራ እየተደረገ ነው። እስራኤል ውስጥ “ናዚ” የሚለውን ቃል አላግባብ መጠቀም እንዲከለከል በእስራኤል ፓርላማ(knesset)እቅንስቃሴ ተጀምሮ የመጀመሪውን ክፍል አልፏል። እስራኤሎች በተለምዶ ፖሊስም ይሁን ወታደር ወይም ባለስልጣን ሥልጣኑን በመጠቀም ከተጋፋቸው ይህ ሰው “ናዚ” ነው ይላሉ።
http://www.haaretz.com/news/national/1.569281
ይህ ሕግ ከጸደቀ ብዙ ሕይወት ያለቀበትን የናዚ ድርጊት በተራ ቃል አለቦታው ወይም አላግባብ መጠቀም ይከለከላል ማለት ነው። ቃላትን በሕግ መከልከል ጥቅሙ የጎላ ላይሆን ይችላል። ከመናገር ነጻነት ጋርም የሚያያዝ ይሆናል። እያንዳንዳችን ከምንጠቀምበት ቃል ጋር የተያያዙ አስከፊ ነገሮችን ማሰብና የቃሉን ጥቅም ማልከስከስና የተፈጸመውን ግፍ እንደማቅለል እንዳይቆጠር መጣር ይኖርብናል። “ናዚ” የሚለው ቃል ከዘር ማጥፋት ጋር የተያያዘ ነውና። በትራፊክ ጥፋት የቀጣንን ፖሊስ ሁሉ “ናዚ” ነው ማለት የናዚን ትርጉም ዝቅ ያደርገዋል። ተራ ጠብቅ ብሎ ሥነ ሥርዓት ያስጠበቀውንም “ናዚ“ ማለት ቃሉን ትርጉም ያሳጣዋል ነው የእስራኤሎቹ እምነት።
ወደ ሃገራቸን ስንመጣ ደግሞ ብዙ ቃላትን አለ ቦታቸውና አላግባብ መጠቀም እየለመደብን መጥቷል። በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጠው ወያኔ ቃላትን አላግባብ በመጠቀም የተጨበጨበለት ነው ብንል ስህተት አይሆንም። የምዕራብያውያንን ድጋፍ በመሻትም ሆነ የፖለቲካ ጥቅምን በሚመለከት ከብዕር በስተቀር ምንም የሌለውን ጋዜጠኛ “ ሽብርተኛ“ ወይም “ፀረ ሰላም“ ብሎ ወያኔ ሲፈርጅ የትርጉም ስህተት መስሎ የሚታየን አንጠፋም። በአሁኑ ወቅት በመንግሥት የሕዝብ መገናኛ መንገዶችና(እንደ ኢቲቪ ዓይነታቸው) ደጋፊዎቻቸው “አክራሪ“ የሚባሉት በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የወጣላቸው ከእነርሱ ጋር ግንኙነት እንደሌላው የሚታወቅ ነው። ሰላማዊ ሰዎችን “ሽብርተኛ“ ወይም “አክራሪዎች“ ብሎ መጥራት እውነተኞቹ አሸባሪዎች በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትንና ወይም ያደረሱትን ጉዳት ማሳነስ ይሆናል።
በተቃዋሚ በኩልም ቃላቶች ይባክናሉ። የዓባይን መገደብ የደገፈን ወይም አባቱን ለመጠየቅ ወደ ሃገሩ ጎራ ያለውን ሁሉ “ወያኔ“ ማለት የወያኔነትን ትርጉም ዝቅ ማድረግ ይመስለኛል። ናዚነት ለእስራኤሎች ትርጉም እንደሚሰጥ ወያኔነት ለእኛም የሚሰጠን ዘግናኝ ትርጉም አለው። ስለዚህ ያለፈ ያገደመውን ስላልደገፈን ብቻ ተነስተን “ወያኔ“ ማለት የወያኔን ግፍ በጣም ማቅለል ይሆናል። ለነገሩ የአርሶ አደሮች ንቅናቄ የነበረውንና የተከበረውን “ወያኔ“ የሚለውን ስም ያልከሰከሰው ራሱ ወያኔ ነው። የሕዝብን ንቅናቄ የነበረው መጠሪያ ለአንድ ዘረኛ ድርጅት መጠሪያ ሲያደርግ ነው ነገሩ የተበላሸው። ዛሬ በወያኔ መጥፎ ተግባር ምክንያት “ወያኔ“ የሚለው ቃል የትግል መጠሪያ ሳይሆን ዘረኛ፣ ጠባብ ፣ ከፋፋይ ፣ ግፈኛ የሚል ትርጉም ይዟል።
በሌላ በኩል ደግሞ በድርጅት ውስጥ ዴሞክራሲ የጠየቀውን ሁሉም አንጃ ማለት ስህተት ነው። በተለይ እንደ ሃገራችን አቆጣጠር 1969-70 ዓ.ም በኢሕአፓ ውስጥ በነብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ማሩ ደጋፊ አንጀኞች የተፈጸመውን ግፍ ማቅለል ይመስለኛል። ይህ በአሁኑ ወቅት የምንሰማው የአንጃነት አፈራረጅ በእነ ብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ማሩ ደጋፊዎች የደረሰውን ጥፋት የሚያልከሰክስና በዚያም ወቅት ሕይወታቸውን ያጡትን ዜጎች ደመ ከልብ የሚያደርግ ሆኖ ነው የታየኝ። ፓሊስ ሲቀጣን ናዚ ማለት የቃሉን ክብደት ካቀለለው በድርጅት ውስጥ በተነሳ የሃሳብ ልዩነት የተለየንን ወይም የተቃወመንን ሁሉ አንጃ ስንልም የአንጀኞችን በደል ተራ እናደርገዋለን።
ቃላትን ትርጉም እንዲኖራቸው ስናደርግ ከግል ጥቅም አንጻር ወይም ከወቅታዊ የፖለቲካ እሰጥ አገባ ብቻ ሳይሆን እንደ ጀርመኖች ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅምና ጉዳት አኳያ እየመዘንን ቢሆን ነው ከበሬታ የሚኖረን። በዚህ ውድድር ጀርመን ውስጥ በስልጣን ያለውን መንግሥት የሚያጋልጡ ቃላት የማሸነፍ እድላቸው ትልቅ ነው። ጋዜጠኛውን “ሽብርተኛ“፣ የዓባይ ግድብን የደገፈውን “ወያኔ“፣ ከእኛ ጋር የሃሳብ ልዩነት ያለውን “አንጃ“ ብሎ ከመሬት ተነስቶ ደፍሮ መናገር ወይም መጻፍ የራስን ማንነት የሚያጋልጥ ነው። ይህ ደግሞ ወዳጅንም ሳይሆን ጠላትን እያበዛ የሚሄድ አሰራር ነው የሚሆነው። በሕዝብ ታማኝነትንም ያሳጣል። ሲበዛ ደግሞ ቀበሮ መጣብኝ ብሎ ሲያታልል እንደቆየው እረኛ፣ የእውነቱ ቀበሮ ሲመጣ ጩኸቱ እንደ ማታለል ነው የሚቆጠረው።
ቃላትን በሕግ መከልከል ልዩነት ያመጣል ብዬ አላምንም። በሕግ መገደብን ከተቃወምን ደግሞ ራሳችንን በተፈጥሮ ሕግ ማስተዳደር ይኖርብናል። ስንት ዜጎች ያለቁበትን ጉዳይና ስያሜ ወደ ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም መተርጎም ኢሰብአዊነት ነው የሚሆነው። በተለይ የምንወነጅለው ግለሰብ ነጻ ከሆነ በግለሰቡ ላይ የሰራነው ወንጀል ትልቅ ነው።እንደ ወያኔ ራስ ከሳሽ፣ ራስ ፈራጅ እስከ አልሆንን ድረስ በነጻ መድረክ መረጃ አቅርቡ ብንባል ማጣፊያው ሊያጥረን ይችላል። ማንም የሚጠይቀን የለም ብሎ ያልሆነውን መለደፍ ደግሞ የዝቅተኝነታችን ምልክት ነው የሚሆነው። መድረክ አገኘሁ ብለን ደግሞ የጠላነውን ሁሉ “አንጃ“ ብሎ መጻፍ ወይም በሰፈር ጠብ “ወያኔ“ ብሎ መሳደብ ትዝብት ላይ ይጥላል።
በሁሉ የሚገርመው እኛ በውጭ ሃገር ተቀምጠን፣ ወያኔ የማይደርስብን መሆኑን አረጋግጠን፣ አገር ውስጥ የሚችሉትን የሚያደርጉትን “ቡከን“ ብለን ብንሳደብ ማን ነው የሚሰማን? ይህንን ዓይነት ሁኔታ ቃላትን ከማባከን በላይ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም። “ቡከን“ ብለን ስንተች ሌሎች የፈሩትን እኛ ሰርተን ካላሳየን ባዶነታችን ነው ጎልቶ የሚታየው። ስድባችንም የአህያ ፈስ ነው የሚሆነው። አይሸትም አይገማም። ማንም ለአህያ ፈስ አፍንጫውን የሚይዝም አይኖርም።
በደርግ አስራ ሰባት የግፍ አገዛዝ ውስጥ የተፈጠሩ የማውገዣ ቃላት ብዛታቸውን ማስታወስ ያዳግታል። ግን ሁሉም መፍትሄ አላመጡም። ዛሬም ወያኔ የማያወጣው ስም የለም ግን ቃላት ማባከን እንጂ የሚያመጣው ትርፍ የለም። ከስድቡ ባሻገር አልፈን “ወያኔም“ ሆነ “አንጃ“ “ቡከን“ ሆነ “ሽብርተኛ“ ብለን የምንፈርጃቸው ሰዎች እውን እንደምንላቸው ናቸው ወይ? ካልሆኑ ደግሞ ችግራቸውን አጥንተን ችግሩን ለመፍታት ስንጥር ነው መፍትሄ የምናገኘው። “ጸረ ሰላም“ “ሽብርተኛ“ ብሎ ተቃዋሚዎችን መፈረጅ ችግሩን አይፈታም፣ የውስጥ ዴሞክራሲን የጠየቀውን ሁሉ አንጃ ብሎ መለደፍ ድርጅትን ዴሞክራሲዊ አያደርግም። ሙከራችን ቃላትን ማባከን እንዳይሆን ከመፈረጃችን በፊት ማሰብ መቅደም አለበት።
ሰለ ሃገራችን ሰላም የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ!
በልጅግ ዓሊ
23.01.14 ፍራንክፈርት
[email protected]