January 21, 2014
16 mins read

6 ቅን ጥያቄዎች ለአውራምባው ዳዊት ከበደ

ክዳጉ ኢትዮጵያ

ዳዊት ከበደ… የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነት ምሩቁ ዳዊት… በ1997ዓ.ም ምርጫ መባቻ በነጻ ጋዜጠኝነቱ ምክንያት ከወቅቱ የቅንጅት አመራሮች ጋር ለሁለት አመት ጥቂት ፈሪ ጊዜ ከቃሊቲ በሮች ጀርባ ተከርችሞ የነበረው ዳዊት… ከቃሊቲ መልስ እጅግ በጠበበው የጋዜጠኝነት መከወኛ ክፍተት ከአጋሮቹ ጋር አውራምባ ታይምስ ጋዜጣን የመሠረተው ዳዊት… የአለም አቀፍ የጋዜጠኝነት ተሸላሚው ዳዊት… ከሁለት አመት ግድም በፊት “በገዢው ፓርቲና በአጫፋሪዎቹ ሚድያዎች የተከፈተብኝ ዘመቻ በደህንነቴ ላይ አደጋ ደቅኖብኛል በሚል በባሌ ሳይሆን በቦሌ ወደ ሰሜን አሜሪካ የተሰደደው ዳዊት… “ስደት ከምወደው የጋዜጠኝነት ሙያዬ አይነጥለኝም” በሚል አውራምባ ታይምስ ድረ-ገጽን የመሠረተው ዳዊት… በድረ-ገጹ ምስረታ ማግስት በሚያስተናግዳቸው ጽሑፎችና የምስል-ወ-ድምጽ መረጃዎች ከዲያስፖራ ሚዲያዎችና አለፍ ሲልም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የቆየው ዳዊት… ወደ ኢት”ዮጵያ ተመለሰና ለመንግስታዊው ዘመን መጽሔት ስለ ዲስፖራ ተቃዋሚዎች የቁጥር አናሳነት፣ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች በዓል ጥልቅ ትርጓሜ ወዘተ… ለማታዊ ማብራሪያ ሰጠ! ወይም የባለ ሽሙጡን የአቤ ቶኪቻውን አገላለጽ አዙሬ ለመጠቀም ይፈቀድልኝና “ከመውጣት” “መግባትን” መረጠ፡፡ ምክንያት- የጋዜጠኝነት ሙያን በስደት ሆኖ መከወን አዳጋች ነው በማለት፡፡

የዳዊት ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እዚህ አገር ቤት በምንገኘውም ሆነ በውጪ ሐገር ባሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሯል፡፡ አበጀህ ያሉት እንዳሉ ሁሉ የዳዊት ሚና ለየለት ሲሉ የተደመጡም አሉ፡፡ መመለሱን በሐገሪቱ ለጋዜጠኞች ምቹ የስራ ከባቢ እንዳለ ማረጋገጫና የፕሬስ ተቆርቋሪ ተቋማትን አፍ ማስዘጊያ አድርገው የወሰዱት የመኖራቸውን ያህል የዲያስፖራው የፖለቲካ ንቃተ ሕሊና ደረጃ ለሠርጎ-ገብ ጋዜጠኝነት እንደማያመች በመረዳት የተደረገ የመልስ ጉዞ አድርገው የቆጠሩትም ጥቂት አይደሉም፡፡
በእኔ በኩል የዳዊትን ወደ “ቅድስቲቱ ሐገር” መመለስ ከማወደስም ሆነ ከማውገዝ በፊት ራሱ ዳዊት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች ቢመልስ ሸጋ ይሆን ነበር ባይ ነኝ፡፡ ጥያቄዎቼ በቅንነት እውነታውን ለማጥራት ከመፈለግ በመነጨ፤ ነገር ግን ያለምንም መሸፋፈን የቀረቡ ናቸው፡፡ ልቀጥል ዳዊት?

1. ከሁለት አመት ገደማ በፊት በስደት ወደ ሐገረ አሜሪካ ለማቅናትህ በምክንያትነት ያቀረብከው በወቅቱ “ገዢው ፓርቲ የሚቆጣጠራቸውና ለአገዛዙ ቅርበት ያላቸው ሚዲያዎች የከፈቱብኝ ዘመቻ በደህንነቴ ላይ ስጋት ደቅኖብኛል” የሚል እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ከስደትህ በኋላ በኢትዮጵያ የነጻ ሚድያ ከባቢ ምን አዲስ ነገር ተከሰተ?… የፍትሕ ጋዜጣ በስርአቱ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ተዘጋች፣… በፍትሕ እግር የተተኩት ልዕልና ጋዜጣና አዲስ ታይምስ መጽሔትም የፍትህ ጋዜጣ ጽዋ እንዲደርሳቸው ተደረገ፣ የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነችው ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ “በማተሚያ ቤት እጦት” ከሕትመት ውጪ ሆነች (መንግስት የሚቆጣጠረው ማተሚያ ቤት በማያስፈልገው ድረ-ገጽ መታተሟ ቢቀጥልም)፣ ሐገር ቤት ትታተም በነበረችው አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ያንተ ምክትል ሆኖ በአዘጋጅነት ሲያገለግል የነበረው የውብሸት ታዬ የይቅርታ ጥያቄ ውድቅ ተደረገ (በተቀራራቢ ጊዜ ተመሳሳይ የይቅርታ ጥያቄ ያቀረቡት ስዊድናዊያን ጋዜጠኞች ምንም እንኳ ከውብሸት ጋር ተመሳሳይ የደም ቀለም ቢኖራቸውም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደሐገራቸው ተሸኝተዋል)፣ ገዢው ፓርቲ የሚቆጣጠራቸውና ለአገዛዙ ቅርበት ያላቸው ሚዲያዎች (የአዲስ ዘመኑ አጀንዳ አምድ፣ የሚሚ ስብሐቱ የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ ወዘተ) አሁንም ከሥርዓቱ ተጽዕኖ በአንጻራዊነት ነጻ የሆኑ ሐሳቦችን ለማስተናገድ ድፍረት የሚያሳዩ ቁጥራቸው እንደዋሊያ የተመናመነ ጥቂት የህትመት ውጤቶችን በግንቦት ሰባትነትና በሻዕቢያ ተልዕኮ ፈጻሚነት በመወንጀል እርምጃ እንዲወሰድባቸው መወትወታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ደጋግሜ ባስብም በስደት ወደአሜሪካ ከማቅናትህ በፊት ከነበረው የሚድያ ከባቢ የተለየ ለነጻ ጋዜጠኝነት ምቹ መደላድልን የሚፈጥር ሁኔታን መመልከት አልቻልኩም፡፡ ስለሆነም ለመመለስ ውሳኔ ያበቃህ ለእኔ ያልታየኝ አወንታዊ የሚዲያ ከባቢ ለውጥ ይኖር ይሆን? ወይስ አስቀድሞ ለስደት አብቅቶኛል ስትል ገልፀኸው የነበረውን ምክንያት ስህተትነት ገልፀህ ትስብ ይሆን?

2. በቅርቡ አንጋፋውን የህወሐት ሰው አቦይ ስብሀት ነጋን ጨምሮ በርካታ የስርዓቱ ቁንጮ ሰዎች በሰሜን አሜሪካ ተልዕኮው ብዙም ግልጽ ያልሆነ ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ ለተልዕኳቸው በምክንያትነት ከቀረቡ መላ ምቶች “አንዱ አንድ እግራቸውን ሐገር ቤት ሌላኛውን በዲስፖራው መሐከል ያደረጉ” (አገላለፁ የCivilityው አባመላ ነው) የሚዲያ ሰዎችን ወደ ሐገር ቤት እንዲመለሱ ማማለያ ማቅረብ ነው የሚል ነበር፡፡ የስርዓቱ ቁንጮዎች ጉብኝት በመመለስ ውሳኔህ ላይ አንዳች ተጽዕኖ ይኖረው ይሆን? ከዚህ ቀደምም ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አንድ አንጋፋ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ጋዜጠኛን በብሮድካስት ፈቃድ አማልለው ከፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት ወደ ካድሬ ጋዜጠኝነት አስደናቂ መገለባበጥ እንድታሳይ አድርገው እንደነበረ በሰፊው ስለሚታመን የአንተ መመለስ ተመሳሳይ ውጤት እንደማይኖረው ማረጋገጫ ልትሰጠን ትችል ይሆን?

3. በሰሜን አሜሪካ ቆይታህ በድረ-ገጽህ በምታስተናግዳቸው ጽሑፎችና ሌሎች መረጃዎች ከዲያስፖራ የሚዲያ ተቋማትና አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ውዝግብ ውስጥ እንደነበርክ ይታወቃል፡፡ የመመለስ ውሳኔህ ይህ ውዝግብ በውስጥህ የፈጠረው አንዳች የመገፋት ስሜት ውጤት ይሆን? ከሆነስ ይህ የመገፋት ስሜት ወደሌላኛው ጽንፍ እንዳልወሰደህና በሐገር ቤት ልትሰራው በምታስበው የጋዜጠኝነት ሥራ ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው ማረጋገጫ ልትሰጠኝ ትችላለህ?

4. ወደ ሐገር ቤት ለመመለስ ውሳኔህ እንደ መነሻ ያቀረብከው በስደት ዓለም ሆኖ በሐገር ቤት ላይ ያተኮረ ጋዜጠኝነት መከወን አዳጋች የመሆኑን እውነታ ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሐገራችንን በስደተኛ ጋዜጠኞች ብዛት ከዓለም በቀዳሚነት ያሰለፏት ጋዜጠኞች እንደ ጨው ዘር በመላው ዓለም ለመበተናቸው ሰበቡ ልክ ያጣው የአገዛዙ ውክቢያ እንጂ የስደት ዓለም ኢትዮጵያ ላይ ላተኮረ የጋዜጠኝነት ሥራ ምቹ ነው የሚል እምነት አይደለም፡፡ ምርጫው ያለው መንግስታዊ ውክቢያና ተግዳሮትን፤ አለፍ ሲልም የህትመት ፈቃድ መከልከልን ተቋቁሞ በመዝለቅ ወይም በስደት ሆኖ የቦታ ርቀትን በቴክኖሎጂ አቅም እያጠበቡ የሙያ ግዴታን ለመወጣት በመሞከር መካከል ይመስለኛል፡፡ ሌላው ምርጫ… ምርጫ ከተባለ… የጋዜጠኝነት መታወቂያ ይዞ በተግባር ግን የካድሬ ተግባር መከወን ነው፡፡ ምርጫህን ታሳውቀኝ ዳዊት?

5. አይበለውና፤ አገዛዙ በአንዳች ምክንያት የሕትመት ፈቃድ ቢከለክልህ አማራጭ ዕቅድ (plan B) ይኖርሃል? ወይስ ከዚህ ሥጋት ነፃ የሚደርግ አንዳች አይነት ማረጋገጫ ከመጋረጃው ጀርባ (Behind the scene) አግኝተሃል? መቼም እንዴት የህትመት ፈቃድ እከለከላለሁ ብለህ እንደማትጠይቀኝ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡ ይህን መሳዩን ክልከላ በእስክንድር ነጋ፣ ሲሳይ አጌና ወዘተ ላይ በተደጋጋሚ አይተነዋልና፡፡

6. አውራምባ ታይምስ ድረ-ገጽ በተጀመረች በቀናት ውስጥ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ በአገዛዙ የታገዱ ድረ-ገፆችን በመቀላቀሏ ይዘቷን ለማየት የምንፈልግ የዚህች የነፃነት ጠኔ ከዳቦ ጠኔ ባልተናነሰ ያጠቃን ምስኪን ዜጎች ፕሮክሲ ሰርቨሮችን በመጠቀም ከአገዛዙ ጋር ድብብቆሽ ለመጫወት ተገደን ቆይተናል፡፡ ነገር ግን የድረ-ገፁ ይዘት የአገዛዙን ፍላጎት በሚያንሟላ መልኩ መቃኘት ከጀመሩ በኋላ ያለአንዳች ከልካይ በሐገር ውስጥ መታየት ከመጀመሯም በላይ አይጋ ፎረምን የመሳሰሉ አፍቃሬ መንግስት ድረ-ገጾችም ወደ አውራምባ ታይምስ የሚመሩ አስፈንጣሪዎችን (Links) በገፆቻቸው ላይ አካተቱ፡፡ በድረ-ገጿ ላይ የተደረገው ክልከላ መነሳት በራሱ አንዳች ችግር ባይኖረውም፤ ይልቁንም ላይ ላዩን ሲታይ በጎ እርምጃ ቢመስልም ለዚህ በጎ እርምጃ ከጀርባ የተከፈላ ዋጋ ስለመኖሩ ጥያቄ ቢነሳ የሚገርም አይሆንም
ከላይ የዘረዘርኳቸው ነጥቦች እኔ እና በርካታ እኔን መሰል በኢትዮጵያ ጠንካራ የሚድያ ተቋማትን ለማየት የምንናፍቅ ዜጎች የአንተን ወደሐገር ቤት የመመለስ ውሳኔ ለማሞገስም ወይም ለመንቀፍ አቋም እንድንይዝ ከአንተ ዘንድ ምላሽ ልናገኝባቸው የሚገቡ የትኩረት ነጥቦች (concerns) ናቸው፡፡ ስለሆነም ፊት ለፊትና በተቻለ መጠን ከፍረጃ በፀዳ መልኩ ምላሽ እንደምትሰጠን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የምንኖርበት ዘመን በመረጃ አብዮት በእጅጉ የተቃኘና የመረጃ ኃይልነት ከጥርጥር በፀዳ መልኩ የተረጋገጠበት ጊዜ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ነፃ የመረጃ ፍሰትን እንደ ዋነኛ የስልጣን ስጋት የሚያይ ሥርዓት በሐገራችን ሰፍኗል፡፡ የበለጠ እንደ አለመታደል ሥርዓቱ ነፃ የመረጃ ፍሰትን በሥጋት በማየት ሳይወሰን ይህን ፍሰት ለመገደብ አፋኝ ህጎች፣ የተደራጁ መዋቅሮች፣ ግዙፍ በጀትና ቀላል ቁጥር የሌለው የሰው ኃይል በመመደብ እንቅልፍ አጥቶ መሞከሩ ነው፡፡ ይህ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ሰፍኖ ባለባት ሐገር ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ የጋዜጠኝነት ሥራን ለመስራት የሚደረግ ማንኛውም ውሳኔ አድናቆት ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡ ስለሆነም የውሳኔህ መነሻ ምንም ሆነ ምን… በሙያ ህይወትህ ላይ ውሳኔ የማድረግ መብትህን አከብራለሁ፡፡ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥምህም ልባዊ ምኞቴ ነው!
አክባሪህ
ዳጉ ኢትዮጵያ
(ይህች ጽሑፍ የዳዊት ከበደ ወደሐገር ቤት መመለስ እንደዛሬው ታሪክ ሳይሆን ዜና በነበረበት ወቅት የጻፍኳት ነች፡፡ አሁን የዳዊትን የዘመን መጽሔት ቃለ መጠይቅ ሳነብ ከመጠነኛ ለውጥ ጋር ለንባብ በቅታለች)

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop