ግራ እና ቀኝ ጠፋን – ከፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

ታኅሣሥ 2006

በአለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ወያኔ-ኢሕአዴግ የሚወቀስበት ሥራ በጣም ቢያመዝንም የሚመሰገንበት ሥራ የጽሑፍ ቁጥጥርን ማስቀረቱ ብቻ ነው፤ ሁልጊዜም አንድ ጥሩ ነገር የሚያስከትለው አብዛኛውን ጊዜ የማይጠበቅ ነገር ሊኖር ይችላል፤ ለምሳሌ አጠቃላይ ነጻነት ሲመጣ ወንጀለኛነት ይጨምራል፤ እንዲሁም የጽሑፍ ቁጥጥር ሲነሣ ጸሐፊዎች ይበዛሉ፤ ትምህርት በተስፋፈበትና ማንም እንደፈለገ ለመጻፍና ለማሳተም ችሎታውም ዕድሉም በማይገኝበት፣ ሳያበጥርና ሳይሰልቅ አሰር-ገሰሩን ጽፎ በአደባባይ የሚወጣውን ጥምብ-እርኩሱን አውጥተው ሁለተኛ እንዳይለምደው የሚያደርጉ የታወቁና የሰላ አእምሮና ብዕር ያላቸው አርታእያንና ሐያስያን (ገምጋሚዎች) ባሉበት ብዕሩን የሚያባልግ ጸሐፊ አይወጣም፤ ይህ ሁሉ ባልተሟላበት እንደኛ ባለ አገር ውስጥ ብዕርን ማባለግ እንደመብት ወይም እንደነጻነት እየታየ ነው፡፡

በአደባባይ የሚጽፉ ሰዎች ሁለት ነገሮችን ለይተው መገንዘብና ለሌሎችም ሲየያስተላልፉ ለይተው ማስተላለፍ አለባቸው፤ አንዱ የሆነና የተረጋገጠ ሁነት ነው፤ይህንን ሳይበርዙና ሳይከልሱ እንዳለና እንደተገኘ ማስተላለፍ ግዴታ ነው፤ ሁለተኛው የራስ አስተያየት ነው፤ የጠራውንና የነጣውን አውነት ከጎደፈ የግል አስተያየት ጋር አጋብቶ ማቅረብ ወይ አለማወቅ ነው፤ አውቀው ከሆነም ለማታለል ከመሞከር የሚቆጠር ነው፤ በአለንበት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ የምናየው ፊደሎቹን ማወቅ እንደሙሉ እውቀት ይቆጠራል፤ ወይም በሌላ አነጋገር ፊደልን ማወቅ የመጻፍ ችሎታን ይሆናል፤ ይህ ትልቅ ስሕተት ነው፤ ፊደሎችን ማወቅ ትልቅና መሠረታዊ የእውቀት ጎዳና ላይ መግባት ነው፤ ጎዳናው ግን በጣም ረጅም ነው፤ በእውቀት ጎዳና ላይ መግባት የእውቀት ባለቤት ከመሆን ጋር እንዳይደባለቅ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ በአገራችን ፊደልን ማወቅ ሌላም አደጋ አለው፤ ፊደልን ማወቅ ከሥልጣን ጋር ሲጋባ የሚያስከትለውን ውድቀት ከአንዴም ሁለቴ አይተናል፤ እያየንም ነው፤ ስለዚህም ፊደል ኃላፊነትን ያመጣል፤ አለዚያ በአለፉት ሠላሳ ዓመታት ያየነው ውድቀት እየተከበረ ይቀጥላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹ይህ ሽልማት የእኔ ብቻ አይደለም፣ የእናንተም ነው›› እስክንድር ነጋ (ኤልያስ ገብሩ ጎዳና)

መጻፍ እንደመናገር ሊቆጠር ይቻላል፤ሆኖም በመጻፍና በመናገር መሀከል ትልቅ ልዩነት አለ፤ በንግግር ላይ ከሰዎች በሚቀርበው ጥያቄም ሆነ ተቃውሞ እንዲህ ማለቴ ነው ብሎ የተናገሩትን እዚያው ለማረምና ለማስተካከል ይቻላል፤ በተጻፈ ነገር ላይ እንዲህ ዓይነቱ ወዲያው የመታረም ዕድል የለም፤ ስለዚህም ለመጻፍ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ማለት ነው፤ ከላይ እንደተገለጸው ፊደልና ሥልጣን ሲጋቡ ሰንደቅ ዓላማው ጨርቅ ነው ከማለትም ሊያልፍ ይችላል፤ ለምሳሌ የደርግን የትርፍ ቤቶች አዋጅ ብንመለከተው ‹‹ትርፍ ቤት›› ሲል ትርፍን እንተወውና ‹‹ቤት›› ለሚለው ትክክለኛ ትርጉም አልሰጠም፤ ስለዚህም በጭራሮ የተያያዘ ምንም ‹‹ቤት›› የሚያሰኘው (መኝታ ቤት፣ ወጥ ቤት፣ መታጠቢያ ቤት፣ … የሌለው) በሃምሳ ሳንቲም የሚከራይ ነገር ‹‹ቤት›› ተብሎ በሺህ ብር ከሚከራይ ቤት ጋር ተወረሰ! ያፈረ የለም እንጂ አሳፋሪ ነው!

እንዲህ ዓይነቱ ችግር ከየት የሚመጣ ነው? አንድ አጠቃላይ የአስተሳሰብ ችግር አለ፤ ለየት ያለውን ከጅምላው፣ ግዙፉን ከረቂቁ፣ አንዱን ከብዙው ያለጥንቃቄ ማደባለቅ በአማርኛ በጣም የተለመደ እየሆነ ነው፤ የአስተሳሰብ ችግር ነው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ (አበሻና ሆድ የሚለው ጽሑፍ ባሕር ተሻግሮ የአበሻን ነገር-ዓለም ትቶ የተጠበሰ ውሻ (ሆት ዶግ) የሚበላውንም አስቀየመውና ሌሎች ስለአበሻ የጻፍኋቸውን ተውኩት እንጂ አበሻና መናገር የሚለው በተለይ ለባሕር ማዶው ዘሎ-ጥልቅ ተስማሚው ነበር፤) በማናቸውም ነገር ላይ ለመቀባጠር በጣም ኃይለኛ ምኞት አለው፤ አንዱ ያስተሳሰብ ችግር ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፤ ሳያስቡና ሳይጨነቁ አፍ እንዳመጣ ከመናገር ልማድ ጋር የተያያዘ ነው፤ አሁን ደግሞ የጎሠኛነት ሥርዓት ካመጣብን ጣጣ ዋኖቹ የአስተሳሰብ ችግሮች እነዚህ ናቸው፤ የቡድን መብትን መሠረታዊ አድርጎ የግለሰብን መብት ጨፍልቆ የተነሣው የወያኔ የጎሣ ሥርዓት ከሃያ ዓመታት በኋላ በስንት ጥረት የደረሰበት አሁንም የተዛባ ድምዳሜ የቡድን መብትንና የግለሰብ መብትን ጎን ለጎን አቁሞ እኩል ናቸው ማለትን ነው፤ ለውጡ የተጣራ ባይሆንም ሃያ ዓመታት መፍጀቱ የወያኔን የመማር ፍጥነት የሚያመለክት ነው፤ የሥልጣን ጉልበትና የሥልጣን ምኞት ተጽእኖ እንደአንድነት ያለውንም የፖሊቲካ ፓርቲ ፐሮግራሙን እንዲለውጥና የግለሰቦችንና የቡድን መብቶች በአንድ ደረጃ ላይ እንዲያስቀምጥ ተደርጎአል፤ ከቡድን ውስጥ ግለሰቦች ሁሉ ሙልጭ ብለው ሲወጡ ስለቡድን መብት የሚያወራ ምን እንደሚባል እንጃ! ከቀኝ ወደግራ የዞረ? ወይስ ከግራ ወደቀኝ? ወይስ … ቀኝ ፖሊቲካ ባዶ ከረጢት ይዞ ይቀራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሰሞነ-ሕማማት የበረታ፣ በተንሳኤ ይሽራል! - ሙሉዓለም ገ/መድኀን ከሁመራ-ጎንደር

በተደጋጋሚ እንዳየሁት ለግለሰብ መብቶች የቆመ ቀኝ-ዘመም፣ ለቡድን መብቶች የቆመ ግራ-ዘመም የሚባል ይመስላል ይህ ስሕተት ነው።

ቀደም ሲል የታወቀው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እኔን ቀኝ-ዘመም እያለ ጽፎ ሳይ ይህ ሰው በአውነት አንድ መዝገበ ቃላት ማየት አቅቶት ነው? ወይስ እኔን በተለየ ዓይን ለማየት ከመፈለግ የተነሣ ነው? ወይስ የሲአይኤውን መልክተኛ ፖል ሄንዜን ሰምቶ ነው? የሱ ጎሣ አባል መሆንንና አለመሆንን እኔ የምመርጠውና የምወስነው አይደለም፤ ታምራት በኢትዮጵያዊነት ወይም በዜግነት ዓይን ሊመለከተኝ አለመቻሉም የእኔ ጥፋት አይደለም፤ ሁሉም ቢቀር በሰውነት ደረጃ ሊያየኝ ይችል ነበር፤ ይህንንም አልቻለም፤ እንግዲህ ወይ እኔ ሰው አልሆንኩለትም፤ ወይ እሱ ወደሰውነት ደረጃ አልደረሰም፤ በታምራት ነገራ ቀኝ-ግራ መጋባት እንደኔው ጥርጣሬ ውስጥ ገብቶ የነበረው ክፍሉ ሁሴን ወደጥናት ተመልሶ የታምራትን ስሕተት አረጋገጠ፤ እኔም እንዲሁ አደረግሁና የታምራት ነገራን ግራ መጋባት አረጋገጥሁ፤ ታምራት ነገራ የጎሣ ቀኝ ገብቶት ግራ ፖሊቲካ ቀኝ ሆኖበታል! ቀኝ-ግራ ፖሊቲካ በጎሣ አባልነት የሚገኝ ወይም የሚታጣ ይመስለዋል፤ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ሀብትና ሌላ ማናቸውንም ነገር ከቁም-ነገር ሳይቆጥሩ ለማንም ሰው በሰውነቱ ብቻ ማግኘት የሚገባውን መብት እንዲያገኝ ቆሞ መከራከር ለታምራት እንግዳ ነገር ይመስለኛል፤ ገና እሱ ሳይወለድ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር በተደረገ ስብሰባ ላይ ለምን የኢትዮጵያ ራድዮ በኦሮምኛ አይናገርም? በማለት ጌታቸው ኃይሌ ጋር ሆነን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰዎችን ሞግተን ነበር፤ ይህ ለታምራት የቀኝ ፖሊቲካ ነው፤ የሱ ጎሣ-ዘመም ፖሊቲካ ግራ መሆኑ ነው! ጎሠኛነት ምን ጊዜም የትም ቦታ እንደግራ ፖሊቲካ ተፈርጆ አያውቅም።

አሁን ደግሞ ሰሎሞን አብርሃም ይህንኑ የታምራት ነገራን ስሕተት ለመድገም የዳዳው ስለመሰለኝ በዝምታ ለማለፍ አልፈለግሁም፤ ሰሎሞን (liberalism) የሚለውን የአንግሊዝኛ ቃል በባሕርዩ የሌለበትን ትርጉም ሊሰጠው ይዳዳዋል፤ ሰሎሞን አብርሃም ሊጽፍበት የተነሣው ጉዳይ በእኔ ግምት በጣም ወቅታዊና አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን የግል ስሜትን ከሁነት ጋር፣ ያልተጣራ የተውሶ ሀሳብን (‹‹ፊዩዳሊዝም፣ ሊበራሊዝም››…) ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማያያዝ አስተሳሰቡን ያጎደፈው ይመስለኛል፤ ያነሣው ጉዳይ በተለይም እንደሱ ላለ ፖሊቲከኛ ከስሜተኛነትና ከወገንተኛነት የጸዳ ቢያደርገው (‹‹ወግ አጥባቂ፣ቀኝ አክራሪ›› ..)፣ወይም ደግሞ ያልተጣራ (‹‹የሊበራል ዴሞክራሲን ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ይመስላሉ፤›› እያለ በጎን ከሚጎሽም የጸዳውን እውነት ፊት ለፊት እያቀረበ ድካማቸውን ቢተነትን የሚጠቅም ይሆን ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የበግ ለምዱ የተገፈፈው ድሮ የምናውቀው “ተኩላ” - ደረጀ አያኖ

ግራና ቀኝ ፖሊቲካ የሚባለውን ከጎሣ ፖሊቲካ ጋር ለማገናኘት የሚፈልጉ ሰዎች ወጣቶችን ወደአስከፊ ስሕተት እንዳይመሩ መጠንቀቅ ያለባቸው ይመስለኛል፤ የጎሣ ሥርዓትን የሚቃወሙትን ወገኖች በሌላ መንገድ ለመቋቋም ቢሞክሩ የተሻለ ነው፤ በጎሣ ክፍፍል ማመን ሌላው ቀርቶ በሰውነት ደረጃ ለመሰለፍም ያስቸግራል፤ ለማናቸውም የጎሣ ፖሊቲካን ከግራ ፖሊቲካ ማዛመዱ እሳትና ውሀ ነው።

4 Comments

  1. በለው! “ግራና ቀኝ አጣፋን ” ወይንስ ግራም ቀኝም አጠፋን” !? በግራም በቀኝም ጠፋን!?
    አጠቃላይ ነጻነት ሲመጣ ወንጀለኛነት ይጨምራል፤ …”የሙሉ ዓለም ቱሩፋት ይህ አደለምን? የጽሑፍ ቁጥጥር ሲነሣ…እንደኛ ባለ አገር ውስጥ ብዕርን ማባለግ እንደመብት ወይም እንደነጻነት እየታየ ነው፡፡ ከማን አንሼ አንጂ እኔ ከማን ተሽዬ ነው የሚል እንዴት ጠፋ…ሃፍረት ይሉኝታ….የለችማ…. አንደኛ የተረጋጋጠ እውነትን ማስተላላፍ እንዴት ያለች ነች እውነት በደህና አለች ለመሆኑ? ሁለተኛው የራስ አስተያየት ነው፤ የስሚ ሥሚ አሉ ተባላ አሉ (ሊኒን እንዳለው ብሎ አቶ አንዳለው እንዳሉት ) ለጠቅ ብሎ እሳቸው እነደፈለሰፉት እነደፈጠሩት በራዕይ እነደታአቸው እያለ…ይቀጥልና ከራስ አስተያየት ወደ እውነተኛ የመጨራሻው የእውቀት መደምደሚያ ይወሰዳል።ያው ፊደልና ሥልጣን ሲጋቡማ ጌታዬ ማን ከልካይ አለ… እንደ ኮምጬ አምባው ጥቅስ እየተቀባባሉ መንፋት ነው። ድሮ ታጋይና ምሁር ሲጋባ አደጋ ያለው ይመስለኝ ነበር። አሁን ሥልጣንና ፊደል ሲጋቡ…. አይ ስብሃት ነጋ!
    ***ደርግን የትርፍ ቤቶች አዋጅ ብንመለከተው ‹‹ትርፍ ቤት›› ሲል ትርፍን እንተወውና ‹‹ቤት›› ለሚለው ትክክለኛ ትርጉም አልሰጠም፤ እና አባቴ ትዝ አሉኝ የመንግስት ቤት ሲባል…ይህንን በምኒሊክ ዘመን የተሰራ የእናቴን ማድቤት ቤት ብሎ ወረሰው አሉ። በጭራሮ የተያያዘ ምንም ‹‹ቤት›› የሚያሰኘው (መኝታ ቤት፣ ወጥ ቤት፣ መታጠቢያ ቤት፣ … የሌለው) በሃምሳ ሳንቲም የሚከራይ ነገር ‹‹ቤት›› ተብሎ በሺህ ብር ከሚከራይ ቤት ጋር ተወረሰ! ዓይን ምስክር ነው ። መንግስት ከወረሰው በኋላ ያከራየው ፪.ከ፶ ኢ/ት ብር ነበር። ዘመን አልፎ ታረክ ሲውጣጣ በሰፈራችን የሚገኙ ሁለት የደረግ ሹማምንት ለ፲፯ዓመት የኖሩበትን ቤት ኪራይ እንዳልከፈሉ በቂ ማስረጃ ነበር። ይህንንም አባቴ ለበላይ ዕንባ ጠባቂ ለማሳወቅ ጥቆማ በማቅረባቸው እንደገና ለእሥር ተዳረጉ። ይልቁንም ኢህአዴግ ሲገባ የቤት ባለቤትነት ማስረጃ አሠርተው ሸጠውት ታላቋ አሜሪካ የአበሻን ነገር-ዓለም ትተው የተጠበሰ ውሻ (ሆት ዶግ) መብላት ጀመሩ። ያፈረ የለም እንጂ አሳፋሪ ነው! ግን ሁላችንም የሥርዓቱና የብሔር ተጠቃሚ ተብሎ ሲነፋ እኛም እያበጠርን ሳቅን በለው!።
    **የጎሠኛነት ሥርዓት ካመጣብን ጣጣ ዋኖቹ የአስተሳሰብ ችግሮች እነዚህ ናቸው፤ የቡድን መብትን መሠረታዊ አድርጎ የግለሰብን መብት ጨፍልቆ የተነሣው የወያኔ የጎሣ ሥርዓት ከሃያ ዓመታት በኋላ በስንት ጥረት የደረሰበት አሁንም የተዛባ ድምዳሜ የቡድን መብትንና የግለሰብ መብትን ጎን ለጎን አቁሞ እኩል ናቸው ማለትን ነው፤…ሳትቧደን አትገጥምም ስለዚህ የራስህ ክልል ባንዲራና ቋንቋ አላህ ብቻ ተቧደን አለበለዚያ ‘ ልዩነታችን ውበታችን አይቀጥልም! “አንድነታችን ድምቀታችን የድሮ ሥርዓት ናፋቀነት ነው። “በአንድነት ውስጥ ያሉት የፊውዳሉ ልጆችና የልጅ ልጆች አማራዎች ናቸው እነሱ ይምሩን”አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በግላቸው በኅብረት ቋንቋ ሲተረጎም ” ህወአት ዝም አትበል አንድነትን አጥፋው ማለት ነው።” የሥልጣን ጉልበትና የሥልጣን ምኞት ተጽእኖ እንደአንድነት ያለውንም የፖሊቲካ ፓርቲ ፐሮግራሙን እንዲለውጥና የግለሰቦችንና የቡድን መብቶች በአንድ ደረጃ ላይ እንዲያስቀምጥ ተደርጎአል። ከቡድን ውስጥ ግለሰቦች ሁሉ ሙልጭ ብለው ሲወጡ ስለቡድን መብት የሚያወራ (በድን) ይሆናል። በድን ይናገራል!?
    ____የአቶ ለገሠ መለሰ አመራር የቡድን ነበር ሲሉ (የአንድ ክልል ጎሳ፣ ዘመዳሞች፣ ጋብቻሞች፣አብሮ አደግና፣ታማኞችን አካትቶ ነበር) የአቶ ኅይለመለስ ደስአለኝ አመራር የኅብረት(አመራር በደቦ) ( ከኋላም ከፊትም ሆናችሁ ደግፉኝ…በጠ/ይ ሚ/ር ማዕረግ የብሔር ብሔረሰቦች ሊ/መንበርና የሻቢያህወአት የውጭ ጉዳይ አስፈፃሚ መልዕክተኛ)
    “ጎሠኛነት ምን ጊዜም የትም ቦታ እንደግራ ፖሊቲካ ተፈርጆ አያውቅም።” “አድሃሪዎችን አውድመን አሁን ቀኝ መንገደኞች፣ ጠባብ ብሔርተኞች፣ ወንበዴዎች ፣ድልድይ አፍራሾች፣ የኢምፕሪያሊስት መልዕክተኖች ዙሪያውን ተብትበውናል ይወድማሉ!” አሉ ሌ/ኮል መንግስቱ ኀይለማርያም አሁንማ ጨዋታው ተቀይሮ “መሀል ገብተው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አረንጓዴው ልማታዊ መንግስት ሆነዋል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለዘለዓለም ያለባቸው ችግር በ፹፬ ቋንቋ የሚናገሩት ግን አድማጭ ያጡለት ነገር ቢኖር….ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ሀብትና ሌላ ማናቸውንም ነገር ከቁም-ነገር ሳይቆጥሩ ለማንም ሰው በሰውነቱ ብቻ ማግኘት የሚገባውን መብት እንዲያገኝ መሠረታዊ ፍላጎታቸው እንዲሟላላቸው ነው። የፖለቲካ ተንታኝና ፀሐፊያን ሙግት እንደ መንዝ በግ በፀጉር፣ በላት፣ በቀንድ፣በሽንጥ፣ በክብደት፣ በድምፅ፣ በቀለም፣ መዝኖ ቆይቶ መደባለቅ (የእግዝሐብሔሩን አምሳያ ፍጡር የሰውንም ልጅ ) እየለካ የቡድን መብትንና የግለሰብ መብትን ጎን ለጎን አቁሞ እኩል ናቸው ማለትን ነው፤(ግን ፀጉር፣ ቀንድ፤ ላት፣ የሌለው በግ) ከምግብነት ይቀራል። ዘር ነገዱን ብሄሩን ያልጠራ ሰው ዜግነቱን ይነፈጋልን? ተቧድኖ ያልተሰለፈ ከሰው መሆን ደረጃ የሚያንስ ፍጡር ይሆናል? ***አቤት ሊዘብን አስቦ ግራና ቀኝ የዘመመ ትውልድ በለው!። ከሀገረ ካናዳ በቸር ይግጠመን>>>>>>>

  2. Look at what this feud old man writhing. He is against freedom of writting just because a lot of younger and better writers than him came along he wants to stop this privilege by suggesting to woyane to ban the rest of the writers except him.
    He wants other people to be his servant or slave like used to be during H/silasie. What worst is that he still hate other nation nationalities and he calls his followers to do the same. Shame on you!

    I have been attending this man’s articles for a long time. But by day his writing becoming very childish and meaningless. And I am guessing this guy either getting old and in dementia ( jajitul sewuyew) or this guy is dying with the hate he has been living with for the last 80 years if his age.

    If u have the gut please tell us how H/ silasie used to kill people in millions by starving them and hanging them as you have been a living witness. Otherwise stop pretending You care for people. We know you are the remnant of the feudal regime.
    Your time is up and go away!!! The new Ethiopia will never has a place for someone like you who is hateful towards other ethnic groups.

Comments are closed.

Share