ሃገር ቤት ይታተም የነበረው ምኒልክ መጽሔት ዛሬ በአወዛጋቢ መልኩ የተመረጡትን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስን ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር። አንድ አድርገን የተባለው ድረ ገጽ ይህን ቃለ ምልልስ ፈልፍሎ ከፋይል በማውጣት አትሞት ነበር። እርስዎም ቢያነቡት አንድ ነጥብ ይይዙበታል ብለን እናስባለን።
መግቢያ፡-
“አቡነ ማቲያስ እባላለሁ የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነኝ ፤ በመጀመሪያ ከኢትዮጵያ የወጣሁት እ.ኤ.አ 1979 ዓ.ም ወይም በእኛ አቆጣጠር 1971 ዓ.ም ነው፡፡ በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ለ3 ዓመት ያህል ኖርኩኝ በኋላ ደርግ መንግስት እየተከታተለ ችግር ሲፈጥርብኝ ወደ አሜሪካ ሀገር ተሰደድኩኝ፡፡ ከዛም አሜሪካ ያሉትን ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት ሳሰባስብ ኖርኩኝ፡፡ አሁን ያለው መንግስት እስከተተካ ድረስ በዋሽንግተን ዲሲ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ያሉትን ኢትዮጵያውያንን ስለ ሃይማኖት ሳስተምር ፤ ስመክር ፤ ሳሰባስብ ሳስተባብር ኖርኩኝ፡፡ በ1992 እ.ኤ.አ በሲኖዶስ ስብሰባ ተጠርቼ ወደዚህ ሀገር ተመልሼ ስመጣ በነበርኩበት ሀገር የሀገሩ ሊቀጳጳስ ሆነህ ስራ ተብዬ ወደ አሜሪካን ሀገር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም ተላኩኝ፡፡ አሁን አዛው እኖራለሁ ማለት ነው፡፡”
ምኒሊክ ፡- መቼ ነው የተወለዱት ወደ መንፈሳዊ ሕይወት እንዴት ነው ሊገቡ የቻሉት
አቡነ ማቲያስ፡- የተወለድኩት በትግራይ ክፍለ ሀገር ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ በተለያዩ ገዳማት እየተዘዋወርኩኝ ተማርኩኝ አክሱም ቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ት/ቤት ተምሬአለሁ ፡፡ ከዚያ በኋላ በጎንደርና በሌሎች የኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት እየተዘዋወርኩኝ ትምህርቴን ተከታትያለሁ፡፡ ወደ ጵጵስና የተጠራሁበት በ1971 ዓ.ም ነው በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ተብዬ የተመረጥኩት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1971 ዓ.ም፡፡
ምኒሊክ፡- ከዚያ በፊት የምን ገዳም አስተዳዳሪ ነበሩ?
አቡነ ማቲያስ፡- ከዚያ በፊት አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ት/ቤት እማር ነበር፡፡ የቅድስት ሥላሴ አስተዳዳሪ ተብዬም ተመርጬ ነበር በሊቀ ስልጣናትነት፡፡ ግን አልፈለኩም አልተቀበልኩም ፤ ከዛ የቤተክህነት የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምክትልና አቡነ ቀሲስ ጸሀፊ ሆኜ ተመርጬ ነበር፡፡ ቤተክህነት የተወሰኑ ዓመታት በዚህ ዓይነት ሰርቼ ነበር፡፡
ምኒልክ፡- በአሜሪካ ለሚገኙት አብያተክርስቲያናት በምን መልኩ ነው ግልጋሎት የሚሰጡት ? በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያኖችስ በእምነታቸው ላይ ያላቸው አመለካከት እንዴት ነው?
አቡነ ማቲያስ፡- በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እስከ 1992 እ.ኤ..አ ድረስ ያለው ስደተኛው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በህብረት በአንድነት ይጸልይ ነበር፡፡ አንዳንድ ችግሮችም ቢኖሩ በሕብረት ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በአንድነት በስምምነት በፍቅር ተባብሮ አምልኮቱን ይፈጽም ነበር፡፡ ከ1992 እ.ኤ.አ ወዲህ ግን የፖለቲካ ጉዳይ ገባ ይህ ጉዳይ ደግሞ ህብረተሰቡን ከፋፍሎታል፡፡ በቤተክርስቲያን ህይወት ላይ ችግሮችን ፈጥረዋል፡፡ “ቤተክርስቲያኒቱ በእውነት የፓለቲካ ፤ የዘር ፤ የቋንቋ መድረክ መሆን የለባትም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ መድረክ ነች እንጂ ፤ የፖለቲካ መድረክ አይደለችምና የፖለቲካ መንፈሳችሁን በፖለቲካ መድረክ አድርጉት፡፡ ቤተክርስቲያኒቱን የፖለቲካ መድረክ አታድርጉ” ብለን ብዙ ብዙ ተዋግተን ነበር ግን ሊሆን አልቻለም ፡፡በርግጥ ምዕመናኑ የዚህ አይነት መንፈስ የለውም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች ወደ ቤተክትስቲያኒቱ ውስጥ ገብተው ቤተክርስቲያኒቱን በመለያየታቸው በጣም እናዝናለን፡፡ ስለዚህ እስካሁን ድረስ ችግሩ አልተፈታም ፤ ትንሽ አሁን ረገብ ብሏል፡፡ ነገር ግን አስከ አሁን ችግር አለ፡፡ ሆኖም በእግዚአብሔር ቸርነት ቀስ በቀስ አንድነቱን ሕብረቱን በማጠናከር ወደ አንድነቱ ይመለሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ አሁንም ቢሆን ጥረት ላይ ነው ያለነው፡፡ ይህ ጉዳይ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቤዋለሁ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥረት እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆቿን እንድትሰበስብ አሳስቤአለሁ ፤ የመሰብሰብ ግዴታ ስላለባት በዚህ ጉዳይ ላይ እንድትሰማራ በዘንድሮ አመት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ አቅርቤዋለሁ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በአንክሮ ተቀብሎታል፡፡ጥናት ተደርጎ ወደ አሜሪካን አገር መልዕክተኞች ተልከው በጽሁፍም ተዘጋጅቶ የዕርቅና የሰላም መልዕክተኞችን እንዲላኩና ህብረተሰቡ ወደ ሰላም እንዲመለስ የማድረግ ጥረት እንዲደረግ ሃሳብ ቀርቧል፡፡ እንግዲህ እዛ ያሉት ካህናት ጥሩ ፍላጎት አላቸው ፡፡ “ከእናት ቤተክርስቲያን ተለይተን እስከመቼ ነው መኖር የምንችለው ፤ወደ እናት ቤተክርስቲያናችን ወደ ሕብረታችን መመለስ አለብን፡፡ ታሪካችንን መጠበቅ አለብን፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጥንታዊት ቤተክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን በእንደዚህ አይነት ልዩነት መኖር የለባትም ፡፡ እኛም መጥፎ ታሪክ መስርተን መኖር የለብንም፡፡ ልዩነቱ መጥፋት አለበት ፤ ወደ ህብረታችን መመለስ አለብን “ የሚሉ አሉ፡፡ እውነቱ የፖለቲካው ተጽህኖ አስቸግሯቸው ነው እንጂ መለየቱ የካህናቱ ፍላጎት አይደለም ፡፡የአብዛኛውና የሰፊው ህዝብ ፍላጎት አይደለም፡፡ በጣም ጥቂቶች ናቸው የፖለቲካ እና የመለየት ነገር የሚያስፋፉት፡፡ እኛ መቼም ስለ ሀገሩ ፤ ስለ መብቱ ፤ ሀብት የጋራ ነው ብሎ መታገሉ ሕብረተሰቡ አያስፈልገውም ብለን አይደለም፡፡ በሆነው መድረክ መከራከር ይገባዋል፡፡ በዓለም ላይ ያለ ነገር ነው ፤ ሀብት የጋራ ነው፡፡ ስልጣን የጋራ ነው ለሁሉም መካፈል አለበት፡፡ ነገር ግን እኛ የምንለው ምንድነው? ቤተክርስቲያን ውስጥ ይህ ጉዳይ መካሄድ የለበትም ነው፡፡ ይህ ሁሉ መካሄድ ያለበት በፖለቲካው መድረክ ነው፡፡ በታሪካችም መቼም ተደርጎ አይታወቅም፡፡ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ዛሬ ብቻ አይደለም የተከሰተው፡፡ የድሮ አባቶቻችን በስልጣን ይከራከሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ፖለቲካውን ይዘው ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡ እንደ አሁኑ ያለ ነገር ተከስቶ አያውቅም፡፡ በእውነቱ በታሪካችን የሌለ ተደርጎ የማያውቅ ነው የሆነው፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ የአንድነታችን ምልክት መሆን አለባት፡፡ የቋንቋ የባህል ልዩነት አለ ነገር ግን በሃይማኖት አንድ ነው፡፡ በተለይ በግዕዝ ቋንቋችን አንድ ሆነን ነው የምንኖረው፡፡ እኛ ይሄ መጥፋት የለበት ነው የምንለው፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ፍቃዱ ሆኖ ወደ ህብረትና አንድነታችን አንደምንመለስ ትልቅ ተስፋ ነው ያለኝ፡፡
ምኒሊክ፡- በውጭ ያላችሁ ጳጳሳትና የሃይማኖት አባቶች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተለየ ሲኖዶስ እንዳቋቋማችሁ በስፋት ይነገራል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው ?
አቡነ ማቲያስ፡-በእውነቱ በ1992 ዓ.ም አንዳንድ አባቶች ጳጳሳት ከኢትዮጵያ ተሰደው ወደ አውሮፓም አሜሪካም ይኖራሉ፡፡ የተሰደዱበት ምክንያት ውስጡ ፖለቲካ አዘል ነው፡፡ ነገር ግን እነርሱ ያሉት በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ መሾም የለበትም ፤ ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ፓትርያርክ መሾም የለበትም ነው ፡፡ ይህ ጉዳይ ለመከፋፈል ትልቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ ነገር ግን እኔ አሁንም ቢሆን ደጋግሜ የምለው ነገር ምንድነው ችግርም ቢኖር እዚህ ሆነ ነበር መዋጋት፡፡ እዚህ ሆኖ ከሲኖዶስ ሳይለዩ ቢታገሉ ፤ ቢዋጉ ውጤት ያገኙ ነበር፡፡ ከሀገር ተሰዶ ሀገር ለቆ አይደለም መፍትሄ የሚገኝው፡፡ እነሱ በ1992 እ.ኤ.አ ኒውዮርክ ውስጥ አዲስ የስደተኞች ሲኖዶስ አቋቁመናል ብለው ተነስተው ነበር፡፡ በእርግጥ ስሙ አለ፡፡ ነገር ግን ሰፊው ህዝብ አልተቀበላቸውም፡፡ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተገንጥለን ምንድነው የምንሆነው ? ፤ ሁለተኛ ገንጣይ ሲኖዶስ የሚባል ነገር ተቀባይነቱ እስከምን ድረስ ነው ? ብሎ ህብረተሰቡ በሃይል ስላደገፋቸው እነሱ እንዳሰቡትና እንዳቀዱት ስላልሆነ ይህን ያህል አልገፉም፡፡ ሲኖዶሱም አልተስፋፋም፡፡ የሆነ ሆኖ እነሱ ግን ሲኖዶስ አለ ነው የሚሉት፡፡ እኛ ግን ሲስፋፋ አላየንም፡፡ አባቶቻችን ወንድሞቻችን ናቸው በእውነቱ የፖለቲካ ልዩነታችን የአስተሳሰብ ልዩነትም ቢኖር እነሱን እንደ ባዕድ ሰው አናያቸውም፡፡ ወንድሞቻችን ናቸው ፤ እኛም ወንድሞቻቸው ነን፡፡ ያደረጉትን አድራጎት ግን አንደግፍም፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ያሉት አባቶች ሁሉም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ አይደሉም ፤ ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ ናቸው፡፡ እዚህ ሆነው በሕብረት ይሰራሉ ይታገላሉ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ እንድትጠነክር ህብረተሰቡ በአንድ ላይ ሆኖ ለሀገሩ ለወገኑ እዚህ ሆነው ይታገላሉ ይሰራሉ፡፡ ውጭ የተሰደዱ ጳጳሳት ቅር ቢላቸውም ሀገር ውስጥ ሆነው መታገል ይገባቸው ነበር፡፡ ከሀገር ርቆ የሚገኝውን ሕብረተሰብ መለያየት ተገቢ አይደለም ነው የምለው፡፡
ምኒሊክ፡- እንደሚባለው ከሆነ እርስዎ በስደት ከሚገኙት ሲኖዶስም ሆነ ከኢትዮጵያ ከሚገኝው ሲኖዶስ ገለልተኛ ነዎት ይባላል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው ?
አቡነ ማቲያስ፡- እኔ በእውነት ገለልተኛ አይደለሁም ፡፡ ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ገለልተኛ ሆኜ አልወጣሁም፤ ነገር ግን ያለውን አንዳንድ ነገር አልደግፍል ፤ በቤተክርስቲያኒቱ ያሉትን አንዳንድ ነገሮች እቃወማለሁ፤ ስለዚህ እንደነሱ ተለይቼ ሌላ ሲኖዶስ አቋቁማለሁ አላልኩም ከእነሱ ጋር ህብረት የለኝም፡፡ በአስተሳሰብ አልተገናኝንም፤ ይህ ደግሞ በአስተዳር በኩል የሚታዩትን ነገሮች በማልደግፋቸው እቃወማለሁ፡፡ አሁን ሲኖዶሱ ጉዳዩን አቃንተነዋል አስተካክለነዋል ብለውኛል፡፡ ያሉትን ችግሮች እናስወግዳለን በሚል ሁኔታ ሲኖዶሱ ቃል ገብቶልኛል፡፡
ምኒልክ፡- በጥቅምት ወር በተካሄደው ጉባኤ ፤ ፓትርያርኩ በውጭ የምትገኙ ሊቃ ጳጳሳት እዚህ ካለው ሲኖዶስ ጋር አንድ ለመሆን ንስሀ ግቡ ብለዋል፡፡ ንስሀ መግባቱ ለምን አስፈለገ ? እናንተስ ንስሀ ለመግባት ምን አስፈራችሁ ?
አቡነ ማቲያስ፡- አዎ ! እሱን ቃል ማንም አይደግፈውም፡ ሲኖዶስ የተነጋገረው ቤተክርስቲያኒቱ እዛ ያሉ አባቶች ካህናት ቢያጠፉም ባያጠፉም ቤተክርስቲያኒቱ ለአንድነት ስትል ለህብረት ስትል ዕርቀ ሰላም መፈጠር አለበት የሚል ነው እንጂ የተነጋገርነው ንስሀ ስለመግባት በሚባል ነገር አልተነጋገርንም፡፡ ፓትርያርኩ ነው የተናገሩት ፤ የሲኖዶሱ ቃል አይደለም፡፡ እኛ የምንፈልገው የሚያስቆጣ ቃል መወርወር ሳይሆን እነሱን የሚስብ መሆን አለበት፡፡ ንስሀ የሚባለው ነገር አስቸጋሪ ነው የሚመስለኝ፡፡ ንስሀ ግቡ ብሎ ማለቱ ያለቦታው ገባ ቃል ነው፡፡ አልደግፈውም፡፡
ምኒልክ፡- ሲኖዶሱ በስደት ካሉት ጳጳሳት ጋር በምን መልኩ ነው መስማማት የሚቻለው ወይም ህብረት የሚፈጠረው?
አቡነ ማቲያስ፡-እንግዲህ እኔ የምለው መደረግ ያለበት ከጥንት ጀምሮ ቤተክርስቲያን የአንድነታችን ምልክት ናት፡፡ ስለዚህ እነሱም ቢሆኑ ያስቆጣቸው ነገር ካለ ትተው ፤ ይህች እናት ቤተክርስቲያን ደግሞ በእነሱ ላይ የተቆጣችው ነገር ካለ ነገሩ ለአንድነት ለህብረት ሲባል ህብረተሰቡን በሃይማኖት ፤ ለሀገር አንድነት ብሎ ሁሉን መተው አለበት ነው የምለው ፡፡ እንጂ ፓትርያርኩ እንዳሉት ንስሀ ግቡ አይደለም የምለው ፤ ይህን ማለትም አስፈላጊ አይደለም፡፡ የትኛው ወገን ነው ንስሀ የሚገባው?
ምኒልክ፡- ብዙ ጊዜ እርስዎን ከሀገር ውጪ እንዲቆዩ ያደረገዎት ዋናው ምክንያት አሁን ካሉት ፓትርያርክ ጋር አይግባቡም ፤ ይጋጫሉ ይባላል ፤ ከምን የተነሳ ነው አለመግባባት የተፈጠረው?
አቡነ ማቲያስ፡-አለመግባባት የተፈጠረው በአስተዳደር ነው፡፡ በአስተዳደር አንዳንድ ችግሮች አሉ፡፡ መቼም የአንድ ሊቀ ጳጳስ ክብር ትልቅ ነው ፤ የአንድ ሊቀ ጳጳስ ማዕረግ ከፍተኛ ነው ፤ አንድ ሊቀ ጳጳስ በተሸመበት ክፍለ ሀገር ውስጥ ራሱ መወሰን አለበት፡፡ በጥቃቅን ችግሮች ሲኖዶስ ጋር ሊደርስ የማይገባው ነገር መድረስ የለበትም ፡፡ የፓትርያርክ ስልጣን ደግሞ ከፍተኛ ስለሆነ በጥቃቅን ነገር መግባት የለበትም ነው የኔ ሃሳብ፡፡ ጣልቃ የሚገባባት ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ የሃይማት ጉዳይ የሆነ እንደሆነ ፤ አንድ ቄስ ስህተት ስለፈጸመ ይወገዝ ከተባለ ፓትርያርኩ ጣልቃ ሊገባ ይችላል፡፡ ነገር ግን የአንድ ካህን ደመወዝ ተቀንሶበታል ወይም ጎድሎበታል በሚል በትንሽ በጥቃቅን ነገር ፤ አንድን ዲያቆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ጳጳሱ አዛውሮታል በሚል በትንሽ ነገሮች ጣልቃ መግባት የለበትም ነው የኔ አባባል፡፡ በጠቅላላ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ስርዓት መያዝ አለበት፡፡ ሲኖዶስ ጠንካራ ጉልበት እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ የጳጳሳቱ ክብር መጠበቅ አለበት ፤ የቤተክርስቲያኗ ክብር መጠበቅ አለበት በሚሉትና በመሳሰሉት ነው፡፡
ምኒልክ፡- እርስዎ ፓትርያርኩ ይህን አያሟሉም ብለው ነው የሚቃወሙት?
አቡነ ማቲያስ፡- አዎ ይህንን አያሟሉም ብዬ ነው፡፡ አሁን ተስተካክሏል ብለዋል እንግዲህ፡፡
ምኒልክ፡- በሂደት ለውጥ ይኖራል?
አቡነ ማቲያስ፡-ተስፋ አደርጋለሁ ለውጡ ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው
ምኒሊክ ፡- እርስዎ በጳጳስነት ረዥም ጊዜ ቆይተዋል፡፡ የተለያዩ ፓትርያርኮች እንዳዩ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከዛ ተነስተው አሁን ያሉትን ፓትርያርክ በምን መልክ ነው የሚገልጿቸው ? አሁን እሳቸው የህዝብ ተቃውሞ ይሰነዘርባቸዋል ፡፡ አጃቢ (ጋርድ) ያበዛሉ፡፡ የተለያዩ ዘመናዊ መኪናዎች በብዛት ይጠቀማሉ፡፡ ይህ አይነቱ ነገር ለአንድ ፓትርያርክ ለሃይማኖት አባት አስፈላጊ ነው? በአጠቃላይ ፓትርያርኩን በምን መልክ ያስቀምጧቸዋል?፡፡
አቡነ ማቲያስ፡- እንግዲህ በሀገራችን 5 ፓትርያርኮች ተመርጠዋል፡፡ አሁን ያሉት አባት አምስተኛ ናቸው፡፡ አንድ ፓትርያርክ ሊቀ ጳጳስም ይሁን ቄስ ፤ ማንኛውም የቤተክርስቲያኒቱ አባት የሆነ ሁሉ መመዘን ያለበት በመንፈሳዊ ህይወቱ እና በመንፈሳዊ አቋሙ ነው፡፡ መንፈሳዊነት የቆመበት አላማ ምንድነው ? መንፈሳዊ ነኝ ብሎ ካለ አንድ ሰው ስጋዊ ነገር እንዳይሰራ መንፈሳዊነቱ ይገታዋል፡፡ መንፈሳዊ አባት እንደዛ መሆን አለበት፡፡ ያለፉትን አባቱች የተወሰኑትን አይቻለሁ፡፡ እኔ የማውቃቸው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖትን ነው፡፡ በቅርብ ያወኳቸው ማለቴ ነው፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ተሹመው እስኪወርዱ አልነበርኩኝም፡፡ በአቡነ ተክለሃይማኖት ጊዜ ግን ነበርኩኝ አብሬ ሰርቻለሁ፡፡ እንደውም አቡነ ተክለሃይማኖት መናኝ ባህታዊ ነበሩ፡፡ በደርግ ጊዜ አንዳንድ ስህተቶች ስለፈጸሙ እሳቸውን በግል እቃወም ነበር፡፡ በእርግጥ በደርግ ዘመን መቃወምም ሆነ የልብን መናገር የሚቻልበት ዘመን አልነበረም፡፡ ያ ሁሉ የተፈጸመው ችግር ለእሳቸውም አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነው ፡፡ የቀይ ሽብሩ የህዝብ እልቂቱ የሰብአዊ መብት ሁሉ ሲጣስ ለምን ዝም ብለው አዩ? እያልኩ ውጭ ሀገር ሆኜ እቃወማቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በእውነቱ አሁን ሳየው መቃወም በዚያን ጊዜ ከባድ ነበር፡፡ እሳቸው ያልተቃወሙት ከአቅም በላይ ሆኖባቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወይም ደግሞ ከተቃወምኩኝ ቤተክርስቲያኒቱን እጎዳታለሁ ብለው ሊሆን ይችላል፡፡ እሳቸው ግን በእውነት መናኝ ባህታዊ ነበሩ፡፡ አልጋ ላይ እንኳን አይተኙም ነበር፡፡ ስጋ የሚባል አይበሉም ነበር፡፡ እሳቸው ትልቅ መንፈሳዊ አባት ነበሩ፡፡ ቅድም እንዳልኩ በአንድ መንፈሳዊ አባት በመጀመሪያ ደረጃ መታየት ያለበት መንፈሳዊነት ነው፡፡ ያንን ያሟሉ አባት አቡነ ተክለሃይማኖት ነበሩ፡፡ ሰፋ ያለ አለማቀፋዊ እውቀት ባይኖራቸውም ብትህውናው ራሱ በዕውነት የቤተክርስቲያንን ጥያቄ የሚያሟላ ነው፡፡ እሳቸውን ቀርቤ ነው የማውቃቸው፡፡ከዛ በፊት የነበሩትን አባቶች በገዳማት ነበርኩ ስለ እነሱ የማውቀው ታሪክ የለም፡፡የአሁኑን ፓትርያርክ በምን ልግለጻቸው? አሁን ለማለት የምችለው በሁለት አይነት መክፈል ይቻላል፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ አለ፡፡ የዘር ጉዳይ አለ፡፡ በራሳቸው በኩል ደግሞ ሊያደርጉት የሚገባቸው ብዙ ነገር አለ፡፡ ያ ቢቀነስ ኖሮ የዘሩ የፖለቲካው ነገር ራሱን የቻለ ሆኖ እያለ በራሳቸው በኩል ከተቃውሞ የሚያድናቸውን ነገር ሊያደርጉ የሚገባቸውን ብዙ ነገር ነበር፡፡ አሁን እንደሚባለው የመኪና ብዛት ፤ የአጃቢ ብዛት በችግር በወደቀች ሀገር ውስጥ ሆኖ አያስፈልግም ፡፡ ለእንዲህ አይነት ተቃውሞ ተመቻችቶ ከመገኝት መቆጠብ ይቻል ነበር፡፡ ይህንን አላደረጉም፡፡
ምኒልክ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከጊዜ ጊዜ እየተዳከመችና እየከፋፈለች መጥታለች ፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ይመስሎታል ፤ የምዕመናኑ እና የሃይማኖት አባቶች ግዴታ ምንድነው?
አቡነ ማቲያስ፡- በእውነቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳይለያይ በመንፈስ መጠንከር አለበት፡፡ ማስተማር ይገባል፡፡ በተለይ ሲኖዶሱ አንድ አካል አንድ አምሳል ሆኖ ህብረቱን አጠናክሮ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ልዩነት ለመፍታት መሞከር መጣር አለበት፡፡ በቤተክርስቲያን መመሪያ መሰረት ያለውን ችግር ለመፍታት በሚቻለው አቅም መስራት አለበት፡፡ በእርግጥ አሁን ያለው ፖለቲካዊ ችግር ቢሆንም ቤተክርስቲያን ልታደርግ የሚገባትን ፤ አባቶች ሊያደርጉት የሚገባቸውን ነገሮች ሁሉ ማድረግ ይገባል፡፡ በእኛ በኩል በተለይ ህብረት እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ እርግጥ አባቶች ይደፍራሉ ያደርጋሉ ብዬ ነው የማምነው፡፡በየገጠሩ የተዘጋጀ ቤት ሳይኖራቸው ጠረፍ ድረስ አባቶች እየሄዱ ያስተምራሉ ይመክራሉ፡፡ የድሮ አባቶቻችን ክብራቸው ተጠብቆ ቦታ ተይዞላቸው መንበረ ጵጵስና ተሰርቶላቸው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ አሁን ግን ምንም ነገር ሳይኖር ሄዶ ሂድና ራስህ እንደሆንከው ሁን ተብሎ ወደ ገጠር ይላካሉ ያስተምራሉ፡፡ በእውነቱ በእዚህ ጳጳሳቱ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የጥንታዊ ህብረቱንና አንድነቱን ለመመለስ አሁን ካለው የበለጠ ጥንካሬ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ አቋም ጥርት ባለ ሁኔታ ከታየ ሌላው ሁሉ ያንን አይቶ ሊስተካከል ይችላል ብዬ ነው የማምነው፡፡ በቤተክርስያን በኩል ያለው መከፋፈል ያው በይፋ የታወቀ ነገር ነው፡፡ እኔ በውጭ ያለው ሁኔታ ነው በይበልጥ የማውቀው፡፡ ከፖለቲካ ጋር አብሮ የተያያዘ ነገር ነው፡፡ አሁን ያለውን መንግሥት በመቃወም አንደግፍም የሚሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ከቤተክርስያን ውስጥ ገብተው ያንን የፖለቲካ ተግባራቸውን ስላካሄዱ ነው ቤተክርስቲያን የተከፋፈለችው፡፡
ምኒልክ፡- የሃይማኖት አባቶች ፖለቲካ ውስጥ መግባት ያስፈልጋቸዋል እንዴ?
አቡነ ማቲያስ፡- አያስፈልግም፡፡ እኔ እኮ የምለው እሱን ነው ፤ እርግጥ መቼም እነሱ የሚሉት በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ ተሾመ ነው ነገሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ የፖለቲካ ሰዎች በጀርባቸው ሆነው የራሳቸውን ዓላማ ያካሂዱባቸዋል በሚል ነው፡፡
ምኒልክ፡- በእርስዎ አመለካከት በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ መሾሙ አግባብ ነው?
አቡነ ማቲያስ፡- አግባብ አይደለም፡፡ ግን ፓትርያርኩ ራሳቸው ናቸው ከስልጣን የወረዱት፡፡ አቡነ መርቆርዮስ ችግር ቢያጋጥም እዛው መንበራቸው ላይ ሆነው መቀበል ነበረባቸው፡፡ አኔ አልነበርኩም፡፡ እሳቸው ደግሞኛል ፤ አሞኛልና ተቀበሉኝ ብለው ነው የወረዱት የተባለው፡፡ ጳጳሳቱም ሁሉ የሚመሰክሩት ይህን ነው፡፡ ሲወርዱ ሌላ ፓትርያርክ መሾም አለበት ብላ ቤተክርስቲያኒቱ ሌላ ፓትርያርክ ሾመች ፡፡ ይህ ደግሞ ከአሁን ቀደም ተደርጓል፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በህይወት እያሉ ነው ፓትርያርክ የተሸመው፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ እስር ቤት እያሉ ነው አቡነ ተክለሃይማኖት የተሾሙት፡፡ ይህ አግባብ አይደለም፡፡ በህይወት እያለ አንድ ፓትርያርክ ሊያው በደርግ ታስሮ ፤ በሃይማኖት አልባው ደርግ ታስሮ እያለ ስለዛ መጸለይ ሲገባ በላዩ ፓትርያርክ መሾም አግባብ አልነበረም፡፡ ሕጉ የተጣሰው ቀደም ብሎ ነው፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የመጣውን ሁሉ ይምጣብኝ ብለው ዝም እንዳይሉ ወረድኩኝ ፤ ስልጣኔን ለቀኩኝ አሉ፡፡ ስለዚህ ሲኖዶሱ ደግሞ የፓትርያርክ መንበር ባዶ መቀመጥ የለበትም ብሎ ሌላ ፓትርያርክ መረጠ፡፡
ምኒልክ፡- አሁን ረዥም ዓመት ወደ ኋላ ነው የምመልስዎት በደርግ ጊዜ የተለያዩ ችግሮች ተፈጥረውብኝ ነበር ብለዋል፡፡ እነዛን ችግሮች በዝርዝር ቢያስቀምጧቸው?
አቡነ ማቲያስ፡- እንግዲህ በደርግ ዘመን የሆነው እኔ የእየሩሳሌም ጳጳስ ሆኜ ወደ እየሩሳሌም በሄድኩበት ጊዜ እዛ አንዳንድ ጥያቄዎች ይጠይቁኝ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምንድነው? በኢትዮጵያ የመንግሥት ሁኔታ ፤ የሰብዓዊ መብት ፤ የሃይማኖት ተጽህኖ የሚደረገው ምንድነው ? የሚል ጥያቄ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ በዚያን ምክንያት ደግሞ እየሩሳሌም በነበርኩበት ወቅት ከመንግስት የተጣሉ ሰዎች ይቀበላል፤ ደርግ አኩራፊዎችን እየተቀበለ መስቀል ያሳልማል ፤ ቤተክርስቲያን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያደርጋል ፤ እየተባለ ብዙ ችግር ብዙ ተጽህኖ ይደርስብኝ ነበር ፡፡ እኔ ደግሞ ቤተክርስቲያን የሚመጡትን ምዕመናን የፖለቲካ ሰው ነህ ፤ ከመንግሥት አኩርፈሃል ፤ ግባ ትግባ ፤ መስቀል አላሳልምም ፤ ቁርባን አላቆርብም ፤ አንተን ክርስትና አላነሳም ብዬ ማለት አልችልም፡፡ የመጣው ሁሉ ቤተክርስቲያን መጥቶ ማምለክ መብቱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አንዳንድ ችግሮች ይደርሱብኝ ነበር፡፡ ያ እየጸና እየበረታ ሲሄድ ከዚያም በላይ ደግሞ “የሃይማኖት እምነት ለአብዮት ጠንቅ ነው!” የሚል ጽሁፍ ከኢትዮጵያ መርሀ ብሔር በሚስጥር የተጻፈ ነው ፤ ፡፡ አምስት ገጽ አማርኛ ጽሁፍ ብርቱ ሚስጥር በሚል ተበተነ ፤ በዚህ መመሪያ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ማጥፋት አለብን ፤ መጀመሪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ከዛ ቀጥሎ ካቶሊክና ፕሮቴስታንትን ፤ በመጨረሻ እስላም የሚል የሚል ሃይማኖት መደምሰሻ ፕሮግራም ወጥቶ ወደ እየሩሳሌም ላኩልኝ፡፡ እሱን ሁሉ ትክክል አለመሆኑን ፤ የሃይማኖት አባቶች ለምን ታሰሩ ? አቡነ ቴዎፍሎስ ለምን ታሰሩ ? ፤ ሌሎች የሃይማኖት አባቶች ለምንድነው የታሰሩት ? ብዬ መቃወም ጀመርኩ፡፡ አሜሪካ ሀገርም ተቃውሞዬን ቀጠልኩ ፡፡
ምኒሊክ፡- ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?
አቡነ ማቲያስ፡- እኔ በእውነቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማስተላልፈው መልዕክት ጥንታዊ ፤ ታሪካዊ እና መሰረታዊ የሆነው ታሪካችንን መጠበቅ አለብን ፡፡ ሰው ኃላፊ ነው ፤ በስልጣን ላይ የሚወጣ ሰው ለዘላለም አይኖርም ፤ ታሪክ ግን ዘላለማዊ ነው ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን የሰላም ሀገር የአንድነት የሕብረት ሀገር መሆን ይኖርባታል፡፡ እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያም አንዲት ናት ብለን ነው እኛ የምናምነው ፡፡ ስለዚህ ስለ አንድነቱ እና ስለህብረቱ ማሰብ አለበት ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ሁሉ ነገር ሃላፊ ነው ፡፡ ነገር ግን ታሪካችን የሚቆይና የነበረ ስለሆነ ታሪካችንን መጠበቅ ይገባናል፡፡ ተባብረን ተስማምተን ተፈቃቅረን ተረዳድተን እገሌ እገሌ ሳንባባል በቋንቋ ፤ በጎሳ ፤ በወንዝ ፤ በሸንተረር ሳንለያይ ህብረታችንን ጠብቀን መኖር አለብን፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ እንደሆነ ተለዋዋጭ ነው፡፡ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአለም ላይ የሚካሄድ ነገር ነው፡፡ ያለውን ችግር ተደጋግፈን አንድ ላይ ሆነን ነው እንጂ ልናስወግድ የምንችለው በጎሳና በቋንቋ ተለያይተን ምንም የምናስወግደው ችግር አይኖርም፡፡ ተባብረን ችግራችንን ፤ ርሀቡን ፤ ድንቁርናውን በሽታውን ጦርነቱን ቸነፈሩን የምናስወግድበትን መንገድ ነው መፍጠር ያለብን ፡፡ በድህነታችን ላይ እርስ በእርሳችን ስንጣላ ተጨማሪ አጥፊ የሆነ ነገር ነው የምንገዛው ፡፡ ልጆቻችን መጥፎ ነገር እንዳይማሩ ፤ መለያየት እንዳይወርሱ ፤ ለእነርሱ መልካም የሆነውን ነገር እንድናወርስ ድሮ አባቶቻችን ያቆዩልንን እንድናስረክባቸው አደራ እላለሁ ፡፡ ሀገራችን አንድነትና ሰላም የሚመጣበት ጊዜ ይኖራል፡፡
ምኒልክ ፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
አቡነ ማቲያስ፡– እኔም አመሰግናለሁ