August 1, 2013
53 mins read

ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን!

ጦቢያን ገረመው

መግቢያ፡-

(ከ18 ዓመት ዕድሜ በታች የሆነ ሰው እንዲያነብ የማይመከር)

የሰው ልጆች በሃይማኖት መከፋፈላቸውን አምርሬ ብቃወምም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች የውሸትና ለብዝበዛም የተፈጠሩ መሆናቸውን ባምንም፣ እጅግ ብዙዎቹ ሃይማኖቶች ሰይጣን የተጣባቸው ወይም የሰይጣናዊነት መንፈስና አሠራር በጉልህ የሚታይባቸው መሆናቸውን ብረዳም በትውልድና በገዛ ፈቃዴ ይዤው ያለሁት ሃይማኖት ክርስትና ነው፡፡ ክርስትና በራሱ በመቶዎችና ከዚያም በላይ የተከፋፈለ መሆኑንም አውቃለሁ – አንዳቸው ለአንዳቸው የእናት አባት ገዳይነት ያህል ዐይጥና ድመት የሆኑ የ“ክርስትና” እምነት ተከታይ አብያተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ መኖራቸውንም አውቃለሁ፡፡ ይህም ሁሉ ከንቱነት መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ‹እህሉ አንድ ዓይነት ሴቱ አሥራ ሁለት› እንዲሉ ለአንድ ክርስቶስ፣ ለአንድ እግዚአብሔር፣ ለአንድ ሠራፂ መንፈስ ቅዱስ በጥቅሉ ለአንዲት የክርስትና ሃይማኖት ያለን የሃይማኖት ጋጋታ ከቁጥሮች የመግለጽ አቅም በላይ እየሆነ ከመቸገራችንም በተጨማሪ ምዕመናን የቱን ይዘው የቱን እንደሚለቁ ክፉኛ እስኪቸገሩና እንዲያውም ከነአካቴው በማርክሳዊ አገላለጽ ሃይማኖት ከሚባል ‹አደንዛዥ ዕፅ›፣ በርግጥም ብዙዎች ለማጭበርበሪያነት ከሚጠቀሙበት ሃይማኖታዊ ተቋም ለመውጣት እስከመገደድ ደርሰዋል፡፡ በውነቱ አነጋጋሪ ነገር ነው፡፡ በአውሮፓ ቤተ ክርስቲያናት ወደ ጭፈራ ቤትነትና ወደሙዚየምነት እየተለወጡ መሆናቸውን ስንሰማ፣ የቀድሞ ምዕመናን የቀደመውን የክርስትና እምነታቸውን እየተው ወደ ዓለም ጭልጥ ብለው በመግባት ሚስተር ሉሲፈር እንዳዘዛቸው እየሆኑ በግብረ ሶዶምና በሌዝቢያኒዝም እንዲሁም በለዬለት ‹hedonism’ ሲጠፉ – ስንጠፋ – ስናይ የጌታየ የመድሓኒቴ የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስና ቡራኬ ከምድራችን በምን ያህል ኪሎሜትሮች – እንዲያውም በብርሃን ዓመታት – እንደራቀ መገንዘብ አያቅተንም፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ከዓመት በላይ ያስወራል፡፡ …

ቅድመ መነሻ፡-

ሰሞኑን በኃይሌ ገ/ሥላሤ ላይ -ሲያቀብጠኝ – በጻፍኩት የወቀሳና የ‹ስድብ› ናዳ ምክንያት አንዳንድ ወገኖቼን ማስቀየሜን ለዳግመኛ ጊዜ ተረድቻለሁ – ቀዳሚው ይህ እንደሚሆን ቀድሜ መገንዘቤ ነው፡፡ ኃይሌን በዚያ መልክ ለማቅረብ የተገደድኩት አለምክንያት አልነበረም – በዚያው ደብዳቤየ ላይ ገልጫለሁ፡፡ ምናልባት መጨመር የነበረብኝ ነገር ነበር – ያም በራሴው አማርኛ “የቅጠላ ቅጠልና የዕጽዋት አብዮት ወደኢትዮጵያ ለማምጣት የሚታገሉ ኃይሎችን እቃወማቸዋለሁ፡፡ መቃወም ብቻም አይደለም እዋጋቸዋለሁ፡፡ እኔ የምቆምለትን ወያኔ/‹ኢሕአዴግ›ን በማንኛውም ሥልት ከሥልጣን የሚያስወግድ ኃይል እኔ በሕይወት እያለሁ ሊኖር አይችልም፡፡ በሩጫና በማስታወቂያ ሥራ እንዲሁም በኢንቬስትመንት መስክ ተሰማርቼ ‹ሕዝቤን› በመበዝበዝ ያካበትኩት ሀብትና ንብረት ይጨነቅ እንጂ የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻነት ለማምጣት የሚታገሉ ወገኖችንና ነጻነት የተጠማውን ሕዝብ ትግል ባጠቃላይ እውን ከመሆኑ በፊት በቻልኩት አከሽፈዋለሁ፡፡ ለወያኔ ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ፡፡ የኔ ችግር አእምሮ እንጂ ገንዘብ ባለመሆኑ ወያኔን በገንዘቤና በዝናየ ለማገልገል የማይታጠፍ ቃል እገባለሁ፡…” በማለት ኃይሌያችን በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ያወጀውን የክተት ዐዋጅ ባለመጨመሬ አዝናለሁ – እናም ግና አሁን  ጨመርኩ፡፡ ይህን ባለጌ ሰውዬ አሁንም ፈ…ም በሉት፤ ወገኛ!  በምኑ ነው የሕዝብን ትግል ከእውንነት የሚያግደው? ራሱ ለራሱ ሩጦ ከማዕበሉ ያመልጥ እንደሆነ እንጂ በምን ተዋግቶ ነው ወያኔን ከውድመቱ የሚታደገው? እንደውሻ በበላበት መጮኹን ለጌቶቹ ለማሳወቅ እንጂ የኢትዮጵያን ነጻነት እንኳንስ ማይሙ ኃይሌ ወያኔም አይችልም – የወያኔ የመግነዝ ክር እየተፈተለ – ጉድጓዱ እየተማሰ ነው፤ የክሩ ክረትና የጉድጓዱ ርቀት ገና ትንሽ ስለሚቀሩት እንጂ በሁሉ ነገር አልቋል፡፡(በነገራችን ላይ የሀበሻነት ይሉኝታየን አያችሁልኝ? ፈ…ም በሉት ብዬ በነጠብጣብ የተውኩት እኮ ‹ፈሳም በሉት› ላለማለት ኢትዮጵያዊው ሥነ ልሣናዊ ወግ ልማድ አግዶኝ እንጂ ማንንም ፈርቼ አልነበረም፡፡) ‹የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ› ነውና ኃይሌ ሃሳቡን ካልለወጠ የነገር ጅራፌን ወደሰገባው እንደማላስገባ ወዳጆቹም ምኖቹም ዕወቁት፡፡ መጨነቅ ሰው ለሆነ ሰው እንጂ ለአሽቃባጭ የወያኔ አጫፋሪ አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ ለኃይሌ ተንገብግባችሁ በበቀደሙ ጽሑፌ ምክንያት ለሰደባችሁኝና ገምቢ አስተያየት ለሰጣችሁኝ ልባዊ ምሥጋናየን ማቅረብ እፈልጋለሁ – ‹የሚሰድቧችሁን መርቁ› ነውና መጽሐፉ እሚል፡፡ እኔ በማንም ላይ በቃላት የመረማመድ ያለኝ መብት ማንም በኔ ላይ እንዳለው እረዳለሁና ግድ የለኝም፡፡ ግን ግን እንዲህ እላለሁ – የጻፍኩትና የምጽፈው ጫት ወይም መጠጥ ይዤ አይደለም፡፡ ዕድሜ ለዕድሜ አሁን የምጽፈው ብቻየን ሆኜ ነውና አንዳንዶች ኃጢኣት እንዳትገቡ አደራችሁን – አማኑኤል ሆስፒታልን የጠቆማችሁኝን አልዘነጋሁትም – ግን ቦታ ያለ አይመስለኝም፤ ወያኔ ሁሉንም እያሳበደ ስለሆነ ጥቂት ጤነኛ ዘመድ አዝማድ ያላቸው ቀድመው ይዘውታልና ለኔ ቦታ አይኖርም፤ ቢሆንም በተመላላሽም ቢሆን መሞከሬ አይቀርም – ለሁሉም ግን ለአዘኔታችሁ እግዜር ይስጥልኝ፡፡ አጻጻፌን በሚመለከት የምጽፈው እንዲያውም ሌሊት ጭር ሲል ነው፤ ይህ ሰዓት የጥሞና ሰዓት ነው – ለመናደድም ያመቻል – የሚያናጥብህ አንድም ሰው ሳይኖር በቅጡና በአግባቡ መናደድ የሚቻለው ሌሊት እንደሆነ በተሞክሮየ አረጋግጫለሁ፡፡ ጫቱና መጠጡ ይልቅስ ወዲህ ነው – የሰዎች ብልግና!! የሰዎች ብልግና ከጫትና መጠጥ የበለጠ ‹ያሰክራል›፡፡ እናም ያናግራል፡፡ አንዳንዶች እንዳላችሁት አጋንንታዊ የስድብ መንፈስ አድሮብኝ ስለመሆኔም አላውቅም – ሰው በተናደደበት እንደልቡ መናገሩ ሰይጣናዊ መንፈስ አድሮበታል እሚያሰኝ ከሆነ ትክክል ነው የተባለው መንፈስ አድሮብኛል ማለት ነውና ራሴን እፈትሻለሁ፡፡ እርግጥ ነው – ‹እጀ ጠባብህን ለሚቀማህ መጎናጸፊያህን ድገምለት› ወይም ‹ቀኝህን በጥፊ ለሚያቀረናህ ግራህን አዙርለት› የሚለውን የጌ.መ.ኢየሱስ ክርስቶስን ምክረ ቃላት – ላልተወሰነ ጊዜ -ገሸሽ ማድረጌን ማስተዋል አያቅተኝም- እርሱ ራሱ አሁን ላይ ቢመጣ በነዚያ ወርቃማ ቃላቱ ምን ያህል እንደሚገፋባቸው አላውቅም፤ ከ1980 /ከአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ዓመታት/ ዓመታት በፊት ቀድሞ የተነገረን ምክር ዛሬ ለመተግበር ብቸገር አይፈረድብኝም – ሆድ ቢብሰኝ ነውና፡፡ ለብዙዎች ያልተለመደ በሚመስል ሁኔታ እንዲህ መናገሬ ጌታየን መገዳደሬ ሳይሆን የዘመኑን መክፋት ለመግለጽና ሰይጣን ፍቅርን የማያውቅና የማይገባውም ከንቱ ፍጡር ስለሆነ አንዳንዴ እንደሰውኛ አካሄድና እንደሰውኛ አስተሳሰብ መሆን የምንገደድ መሆናችንን ለማጠየቅ ብዬ ነው – እርግጥ ነው ያም ስህተት ነው፡፡ፈረንጆች እንደኔው ሆድ ሲብሳቸው ‹Little temper settles the dust.› ይላሉ የሚባለው ወደው እንዳልሆነ እየገባኝ መጥቻለሁ፡፡

በመሠረቱ ብዙ ምርጫዎች አሉን፡- ነፍስን የሚያለመልሙና ሥጋን የሚያስደስቱ የሌሎች ጸሐፊዎች ጽሑፎች የመኖራቸውን ያህል የኔን መሰሉ ብሶት ወለድ ጽሑፍ መኖሩ ሊጠላ አይገባም – ለለውጥ(ለቫራይቲ) ያህል፡፡ ለውጥ ደግሞ የሕይወት ቅመም ናት – ዴሞክራሲንና የንግግር ነጻነትን እንደገዳም መቁነን እነሱው በፈለጉት መክሊት እየሠፈሩ ለአንባቢዎቻቸው እንደሚያድሉት አንዳንድ ድረ ገፆች መሆን ተገቢ እንዳልሆነ አምናለሁ – ዴሞክራሲያዊ መብትን ከመሸርሸር አኳያ እመት ዴሞክራሲ ራሷ ካልከሰሰቻቸው በስተቀር ያን ማድረግም ማንም የማይሰጣቸው ወይም የማይነፍጋቸው ድረገፃዊ መብታቸው እንደሆነም እገነዘባለሁ – ሆ! ማን በጎበረበት ማን በማን ሚዲያ ሊያዝዝ ይችላል! እናም እኔ በበኩሌ የምለውን መስማት የሚፈልግ መስማት በሚችልበት መንገድ ይስማ፡፡ የማይሰማ ጆሮውን ይጠቅጥቅ – በዚያ ላይ ዕድሜ ለ‹delete› እና ‹trash box› – አሽንቀጥሮ መጣል ነው – የምን መናደድ፡፡ ብሶቴን የማሰማት ዕድሉን ግን ማንም አይንፈገኝ፡፡ ‹ዕብደቴ›ን ለሌሎች የሚያሰማ ያስሰማ፡፡ ይህን ዕብደቴን በዕብደትነትና በብልግና የሚመነዝር መብቱ ነው፤ ሲፈልግ አያንብበኝ፤ ወይም ካነበበም በፈለገው መንገድ ይተቸኝ አለዚያም በዝምታው ይቀጥል፤ ሰውን የሚያረክሰው ‹ከአፉ የሚወጣ እንጂ ወደሆዱ የሚገባ› ባለመሆኑ የሚሰማንን በነጻነት እንበልና ድፍርሱ ይጥራ፤ኮለል ይበልና በኋለኛው ዘመን ለሚመጡ ወገኖቻችን ምቹ የመኖሪያ ሀገር ልንፈጥርላቸው እንሞክር፡፡ ለሁላችንም ሁሉም መብት አለገደብ አለን፡፡ ትልቁ ነገር ግን በኢትዮጵያ የሚቀልድ እንዲቀልድባት ሊፈቀድለት እንደማይገባ ማወቃችን ላይ ነው፡፡ በተረፈ ኃይሌን ከኢትዮጵያ ለሚያስበልጥ በአፄ መለስ አባባል መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት  – አንቀልባ ገዝቶ ወይም ተከራይቶም ቢሆን አዝሎት ይዙር፡፡ በተጻፉልኝ አስተያየቶች ዙሪያ በዝርዝር ገብቼ ጊዜ ማጥፋት ብችል ደስ ባለኝ፡ ግን ያ መለኛ አያሰኝምና ከዚህ በላይ ይህን ጉዳይ መለጠጡ ይቅርብኝ፡፡

 

ዋና መነሻ፡-

ዓለማችን የትዕምርቶችና የኮዶች ክምር የሚታይባት የዕንቆቅልሽ ቦታ ናት፡፡ (ለማሳየው የቋንቋ ጉራማይሌ ከፍተኛ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡) እነዚህ signs or symbols ከቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ የነበሩና በተለያዩ secret lodges or secret societies ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡ በተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወይም እንደወታደራዊና የፀጥታ ተቋማትን በመሳሰሉ ወይም በሃይማኖት ቡድኖችና በጥንቆላና መተቱ ዓለም በተሠማሩ ወገኖች ለተለዬ መግባቢያነት የሚውሉ ተለዋዋጭ የምሥጢር ኮዶችና ቋሚ የጋራ ማንነት መታወቂያ ምልክቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ መስቀል ስናይ፣ ጨረቃ ስናይ፣ መልህቅ ስናይ ፣… የሚሰማን ስሜት ወይም የምናስታውሰው ነገር አለ፡፡ ከዚህም ባለፈ በምስልም ይሁን በአካል እባብ ስናይ፣ ፍየል ስናይ፣ በግ ስናይ … ከእማሬያዊነት ትርጉማቸው በዘለለ በፍካሬያዊ ትዕምርትነታቸው የሚታሰበን ነገር አለ፡፡ በምልክቶች ውስጥ ሰዎች ማንነታቸው ይነበባል፡፡ የጀርመኑን ሂትለርና የናዚን ፓርቲ በስዋስቲካው እንለያለን፤ የአሜሪካንን መንግሥት በአንድ ዐይናው የፒራሚዱ ስዕል እንዲሁም የፍየልን የካንገት በላይ ስዕል በሚመስለው የባለአምስት ጫፍ ኮከብና በፔንታግራማዊው የእንትን ትዕምርት እንለያለን(ፔንታጎን መባሉንም አብረን እናስብ)፤ የግብጽን መንግሥት በንሥር አሞራው (የአሜሪካንም ጦር እንዲሁ ነው ምልክቱ) እንለያለን፡፡ ይህም ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

ዓለማችን በሁለት ታላላቅ ጎራዎች መከፈሏን ማስታወሱ ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ይሄ ሁሉ በገሃድ የሚታይ አንደበታዊ እሰጥ አገባና ጦርነታዊ ዕልቂትና ፍጅት የነዚህ ሁለት ተጻራሪ ኃይላት የልፋት ውጤቶች ናቸው፡፡ ሁለቱ ታላላቅ መደቦች በደምሳሳው በብርሃንና ጨለማ የሚመሰሉ የእውነትና የሀሰት መደቦች ወይም ጎራዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ትዕምርቶች እንጂ ተጨባጭነት የላቸውም፡፡ ብዙ ነገሮች ምናልባትም ሁሉም ነገሮች በነዚህ ሁለት ጎራዎች ይገዛሉ፡፡ ክፉ ደግ፣ ጥሩ መጥፎ፣ እሺ እምቢ፣ እውነት ሀሰት፣ ቅዱስ እርኩስ፣ … የምንለው ሁሉ የነዚህ የሁለት አጥፊና ጠፊ የዓለማችን ምሰሶዎች ውጤቶች ናቸው – አሊያም የውጤቶች መገለጫዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም ታዲያ የየራሳቸውና ሰዎች የመደቡላቸው መታወቂያ ምልክቶች አሏቸው – ለምሳሌ ከሃያ አራቱ ሰዓት ውስጥ ገሚሱ የሆነው 12ቱ ሰዓት የጨለማው ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ በብርሃን ለሚመሰለው የደጉ ግዛት ምሳሌዎች ናቸው፤ እነዚህ ሁለት ተቃራኒ ይዘቶች በየሀገራቱና በየፍልስፍናዎቻቸው የተለያየ አመስጥሮ አላቸው፡፡ ለአብነት በቻይና ያንግ እና ዪን በመባል በወንድና በሴት ተመድበው ወንዱ በብርሃን ሴቷ በጨለማ – ወንዱ በፖዚቲቭ ኢነርጂ ሴቷ በኔጌቲቭ ኢነርጂ

ተመስለው በአንድ ክብ ውስጥ እኩል በሚሳሉ የጨለማና ብርሃን ተምሳሌትነት ይታወቃሉ፡፡…

የቻይናው ይሄውና፡፡  ስዋስቲካ የሚባለውም ይሄውና፡-  በማጂክ ረገድም ይሄውልህ፡-

ሴክሬት ሶሳይቲስ በመባል የሚታወቁት ኅቡዕ ድርጅቶች በቀደምት አመራሮቻቸው የተቀረጹ ምልክቶች አሏቸው፡፡ እነዚህ ኅቡኣን ድርጅቶች አነሳሳቸው ጥቂትነታቸው ባሳደረባቸው የአናሳነት ስሜት ውስጣቸው ሲታወክ በሚፈጠር ሌላና ያልተገባ አጥፊ ስሜት ተነሳስተው የበላይነታቸውን በብዙኃኑ ላይ ለመጫን መሻታቸው ነው፡፡ ያኔ ተከታዮቻቸውን ለማነሁለልና ለምጡቅ ሰይጣናዊ ዕቅዶቻቸው ተገዢ ለማድረግ ለአብዛኛው ጎጋ ዜጋ እንደተዓምር የሚቆጠር ልዩ ልዩ ትልሞችን ነድፈው በተግባር ለማዋል ቀን ከሌት ይራወጣሉ፡፡ የእነዚህ አናሳ ቡድኖች መሪ ዕቅድ ሲቻላቸው የዓለምን፣ ካልተቻለ የክልላቸውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት በመቆጣጠር ብዙኃኑንና ለበላይነታቸው ያሰጋናል የሚሉትን የሰው ዘር በሙሉ ከተቻላቸው ሀብት ንብረቱን ዘርፈው  ድምጥማጡን ለማጥፋት ይጥራሉ፤ ያ ባይቻል ቢሊዮኖችን በማይምነትና በኋላ ቀርነት የአፍዝ አደንግዝ ገመዶች ተብትበው ባሪያና አገልጋያቸው አድርገው ያስቀራሉ፤ ለዚህ ሰይጣናዊ ዕቅዳቸው ስኬትም የተለያዩ ሰው ሠራሽ ጦርነቶችንና የተፈጥሮ መሰል የመሬት ውስጥና የመሬት ላይ አደጋዎችን ፈጥረው ዕልቂትና መከራን ያስፋፋሉ፡፡ የሚጠቀሙባቸው የማጥፊያ ዘዴዎች ፍጹም ሰይጣናዊ ናቸው፡፡ ምሕረትና ይሉኝታ ብሎ ነገር የላቸውም፡፡ መርሆኣቸው የትም ፍጪው ዱቄቱን ብቻ አምጪው  ነው – ፈረንጆቹ The end justifies the means. እንደሚሉት ዓይነት ነው፡፡  የዚህ ተቃራኒና The means justifies the end. የሚለው አባባል የጤናማ ሰዎች አካሄድ እንጂ እነሱን ሲያልፍ አይነካቸውም፤ አንጀታቸው የተሠራው ሰብኣዊ ርህራሄን ከማያውቀው ግዑዝ ደንጊያ ነው፡፡ እነዚህ ሰይጣናውያን የነሱ ፍላጎት እስከተሟላ ድረስ የሚጠቀሙበት ሥልት የዓለምን ሕዝብ ከመቶ ፐርሰንት ወደ አምስትና አሥር ፐርሰንት ቢያወርደውም ደስታቸው እንጂ ደንታቸው አይደለም- ከሰማይ የተባረረው የሉሲፈር ልጆች ስለሆኑ በሰው ልጆች መከፋትና ከእግዚአብሔር መንግሥት ተገፍቶ መውጣት እጅግ ይደሰታሉ፡፡ (በኢትዮጵያም ይሄው ዓይነት ነገር ወይም ወደዚህ የሚጠጋ አንዳች ነገር እየታዬ ነው ብዬ መናገር አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም የነገር አነሳሴ እሱ ስላልሆነ፡፡ ከፈለግሁ ልመለስበት ብችል መብቴ ነው – እንዴት ነው ዛሬ ይሄ የመብት ጉዳይ ተሰንቆኝ ያለ ጃል!)

እነዚህ አጥፊ ወገኖች በየሀገሩ አሉ፤ የዘመኑ በትረ ሥልጣን እንዲያውም በነሱ እጅ ውስጥ ነው የሚገኘው ማለት እንችላለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዕቅዳቸውን አሳክተው የሚቃዡለትን አዲሱን የዓለም ሥርዓታቸውን ለመዘርጋት ከሞላ ጎደል ሁሉንም ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ የሚቀራቸው የመጨረሻውን ጦርነት ማካሄድና ማጥፋት የሚፈልጉትን አጥፍተው ሰይጣናዊ ሥርዓቱን በይፋ ማወጅ ነው፡፡ ምልክታቸው በዋናነት ከወሲብ፣ ከገንዘብና ከሥልጣን አይወጣም፡፡ ሲፈልጉ ቁጥሮችም ምልክቶቻቸው ይሆናሉ፡፡ ዋናዎቹ 13 እና 666 ናቸው፤ ሌሎችም አሉ – ለአሁኑ ጉዳያችን አይደሉም እንጂ፡፡

ዋና ሐተታ፡-

‹ድፍረት የተሞላበት›ና ብዙ ስድቦችን ከ‹አጋንንት መንደር› እንዲጎርፍልኝ የሚያደርግ ነገር ላስከትል ነው(‹የትኛው ነው የቡዳው ሠፈር?› ተብሎ በየዋህ መንገደኛ የተጠየቀ አንድ በቡዳነት ከሚታማ ሠፈር ውስጥ የሚኖር መንገድ ጠቋሚ ‹እነሱም እኛን ይላሉ እኛም እነሱን እንላለን› ሲል የተናገረው ቀልድ አዘል ቁም ነገር አሁን ብልጭ አለብኝና ፈገግ አልኩ!)፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ቤተ ክርስቲያን በሰይጣናዊ ምልክት ተጠልፋለች፡፡ እሱም የአክሱም ሃውልት የሚታወቅበት የወንድ ብልት ማሳያ ምልክት ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶች ምልክቶች በታሪክ phallic statues ይባላሉ፡፡ Phallus ማለት በአማርኛ ‹ጀ…› እንደሚባለውና በተለይ ወንድነትን ለመግለጥ የምንጠቀምበት ትልቁ የወንድ ብልት ነው – ተራውና በብዙዎቻችን የወንዶች ማኅበረሰብ ዘንድ የሚገኘው በፈረንጅኛው ተራ አጠራር (penis) የሚባለው ዓይነት አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ባህል በጥንት ዘመን የነበረ ወንድነትን አመልካች የቅርጽ ምልክት ነው፡፡

ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ የተነሳሳሁት ለሆነ ጉዳይ ትናንት ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ስለነበር ያን በወንድ ብልት አምሳል የተሠራ የአክሱም ሃውልት ቅርጽ በየማዕዘናቱ ተመልክቼ ቤተ ክርስቲያናችን በጣዖት እምነት ሥር የመውደቋ ምሥጢር ስለ‹ተከሰተልኝ›ና በፊትም እናደድበት ስለነበረ  ነው፡፡ እኔ አሁን በግልጽ በመናገሬ ይሄኔ ስንቱ ቄስና መነኩሴ ‹በስመአብ ወወልድ… ምን ዓይነቱ ባለጌ ሰው ነው! ሰይጣን!› ይለኝ ይሆናል፡፡ ነገሩ ግን ወዲህ ነው – ብልግናው ያለው ቤተ ክርስቲያን ውስጥና ከመንበረ ጽላቱ ጀምሮ እዚያው ውስጥ ነው፡፡ ይህን ያደረገው ግን እግዚአብሔር ሳይሆን ሰው ነው፡፡ በቅድመ ክርስትና ጣዖታውያን የጥንት ሰዎች ያመልኩበት የነበረውን የወንድ ብልት በድኅረ ክርስትና እንዳለ ኮርጀው የወንድን ብልት አዳም ሔዋን ሳይል፣ ጀግናን ከፈሪ ሳይለይ፣ ፍቅርን፣ እምነትና መልካም ሥራን መሠረት አድርጎ ለሁሉም ለመጣው ክርስቶስ ማምለኪያነት አዋሉት፡፡ ይህ ነው ትልቁ ብልግና – ትልቁ ብልግና ወሲባዊ ወሬን በጨዋነትና በጨዋ ቃላት መናገር ሳይሆን ትርጉም በሌለው ሁኔታ ወይም ከመነሻ ትርጉሙ ጭራሽ ባፈነገጠና ጥንታዊ እሳቤውን ባለማወቅ የወንድ ብልት ቅርጽ በተቀደሰው ቦታ ማስቀመጥ ነው – ‹ነገርዬው› እርኩስ ነው ማለቴ አይደለም – ቦታው አይደለም ለማለት እንጂ፡፡ ይህ ነው ትልቁ ሰይጣናዊነት፡፡ መታረም ያለበት ትልቅ ስህተት ይህ ነው፡፡(አለቃ ገ/ሃና ሴት ጋር አደሩ ተብለው ካህናት በመቋሚያ እየዘወጡ ከቅኔ ማኅሌቱ ያስወጧቸዋል አሉ፡፡ እሳቸውም የማን ሞኝ ናቸውና በሴቶቹ መግቢያ ይገቡና ያን ሁሉ ሴት አስቀዳሽ ጀርባ ጀርባቸውን በከዘራቸው እየለመጡ ከቤተ ክርስቲያን ማስወጣት ይጀምራሉ፡፡ ያኔ “እንዴ! አለቃ፣ ምን ነካዎ? ምን ሆኑና ነው እንዲህ የሚያደርጉ?” ተብለው ቢጠየቁ “እንዴ! እኔ አብረህ አደርክ ተብዬ እንዲህ ተደብድቤ ከተባረርኩ እነሱ ከነአካቴው ይዘውት ሲገቡ እንዴት ዝም ይባላል?” አሉ ይባላል፡፡ ይቺ ቀልድ ለሊበራል ሃይማኖተኛ ጥሩ የፈገግታ ምንጭ ልትሆን እንደምትችል ቢገባኝም ለአክራሪ ደግሞ ጥሩ የስድብ ማፍለቂያ ግብኣት ልትሆን እንደምትችል እገምታለሁ፡፡ እባካችሁን – ዓለም ራሷ ከርራ ልትበጠስ ስለሆነ ፈታ ማለትን እንልመድ – ማክረር መጥፎ ነው፡፡

ቀደምት አባቶች ዕውቀታቸው ልክ እንደዛኔዋ ዓለም ሁሉ ውሱንና ጠባብ ነበር፡፡ ያኔ የገደሉትን አውሬ ወይ እንስሳ ምንነት ለማሳወቅ በለንጣና አለታማ ድንጋዮች ላይ ምስሉን ያስቀምጡ ነበር፡፡ ያ ልማድ የግዳያቸውን ዓይነት ለማሳወቅ ሲሆን ጀግንነታቸውን ለማሳየት ደግሞ የዘመኑ የወንድነት መለኪያ የነበረውን የወንዴ ፆታ አመልካች ዕቃ በስእልና በምስል መልክ ያሳዩ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ የወንድን ብልት ቅርጽ ቤተ ክርስቲያያ ግድግዳ ወይ ጣሪያ ላይ ማሳየት ወይም ፓትርያርክ ጽ/ቤትን በዚያ ቅርጽ ማሠራት ማለት ታዲያ ክርስትናን አለማወቅ እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ሃይማኖትና ባህል ደግሞ ሊዛነቁ አይገባም፡፡ አክሱማውያን አባቶቻችን ጀግንነታቸውን ለማሳየት የእናቶቻችንን ገድልና ሀገራዊ አስተዋፅዖ ደብቀው የወንዶቹን የበላይነት ብቻ አሳዩን፡፡ ያን እንዴት ወደ ቤተ ክርስቲያን እናመጣለን? ይህን አላግባብ የተዛነቀ የፖለቲካና የሃይማኖት ጉዳይ ሊለይና ሊያስረዳ የሚችል እንዴት አንድ የተማረ ካህን ይጠፋል? ባልጠፋ ክርስቲያናዊ ምልክት እስከመቼስ በዚህ ሞኝነት እንቀጥላለን? ምነው ቆም ብሎ የሚያስብ ጠፋ? ብንጠየቅ መልሳችን ምን ይሆን? ወይንስ የምናውቀው በሚመስለን ትንሽ ነገር የማናውቀውን ትልቅ ምሥጢር እያወለጋገድን ልናምታታ ነው?

አንዲት ሀገር የወንዶች ብቻ ሳትሆን የሴቶችም የወንዶችም የጋራ ሀብት መሆኗን ለጊዜው እንርሳው፡፡ አንዲት ሀገር ውስጥ ያሉ ሴቶች ሀገራቸው በጠላት በምትወረር ጊዜ እንደነሸዋረገድ ገድሌ ያሉ ቆፍጣና ሴቶች በጠበንጃ አፈሙዝ ጠላትን ድባቅ መምታታቸውን ለጊዜው እንዘንጋው፡፡ ይህንንም ሁሉ ረስተን አንዲት ሀገር በወንድ ብልት ብቻ መወከሏንና ሴቶቿ ያለሀገር መቅረታቸውን እናስብ፡፡ ይህንንም ለምን ሆነ ብለን መጠየቁን እንደቅንጦት እንቁጠረውና እንተወው፡፡

ግን ግን ክርስቶስ የመጣውና ያስተማረው “እኔ ወንዱ! ወንድነቴን አሳይሃለሁ! እየው ወንድነቴን! እንዲህ ካላደረግሁህ ወንድ አይደለሁም! ወንድ አታውቅም! አንተን ድራሽህን ካላጠፋሁ ቁጭ ብዬ ሸንቻለሁ!…” የሚሉትን የወንድ ትምክህቶችና ዕብሪቶች ለማስፋፋት ነበር ወይ? ቤተ ክርስቲያናችንስ በየምትሠራቸው አዳዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ያማረላት መስሏት ይሄን የወንድ እንጥልጥል ጠባብ ትናጋውን ወደሰማይ አንጋጥጦ እንዲቀመጥ ማድረጓ ለምን ይሆን? ዕቃው ምን እየለመነ ነው? ጦርነትን ወይንስ እንትን? ወገኖቼ፤ ለስድብ ከመጣደፋችሁ በፊት በጥሞና አስቡትና አስተንትኑት፡፡ ክርስቶስና የወንድነት አይበገሬነት ዐይንና ናጫ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ‹ፀያፍ› ነገር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳይሆን ቃልቻ ቤትና ጣዖት ማምለኪያ ቤት ውስጥ ብመለከት ያን ያህል ባልተሰማኝ – ስለሁለት ምክንያት፡- አንዱ እነዚህ ቤቶች ፀረ-ክርስቶስ ናቸው – ሌላው እነዚህ ቤቶች የዲያብሎስ መናኸሪያ ስለሆኑ ሕዝብን ለማሳሳት የቆሙ ናቸውና ከዚህም የባሰ ቢያደርጉ አንዴውኑ ወደውና ፈቅደው ገብተውበታል፡፡ እዚህ ላይ ወሲብን ‹ፀያፍ› ማለቴ ንግግር ለማሳመር እንጂ ከሕግ ውጪ ያልሆነ ነገር ሁሉ ፀያፍ ሊሆን እንደማይችልና እንደማይገባም አምናለሁ፡፡ ሰዎች በተለይም አንዳንድ ካህናት ወሲብን በፀያፍነት ለመፈረጅ ለምን እንደሚቸኩሉና ስለወሲብ ሲወራ ሰዎች ለምን አፋቸውን በመዳፋቸው እንደሚይዙ ወይንም በአበስ ገበርኩ እንደሚተመትሙ አይገባኝም – መብራት ሲጠፋ ግን እነሱ ይብሳሉ፡፡ ዋናው … ለነገሩ አሁን እዚህ ይሄ ምን አገባኝ?

አሁን እኔ ማለት የምፈልገው ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ ከአክሱም ሃውልት ይውጣ ነው፤ የመንግሥት ለመንግሥት የቄሣርም ለቄሣር ይሁን፡፡ ሃውልቱ ከተፈለገ የመንግሥት መገለጫ ይሁንና በየቤተ መንግሥቱ ወይም በየመሥሪያ ቤቱ ይገተር – እኔ ግድ የለኝም፡፡ የወንድነት መገለጥ በሚያስፈልግባቸው የወያኔ መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ቢቆም በበኩሌ ቅሬታ አይሰማኝም – እውነታቸውን ነው – ወያኔዎች ብዙ ለፍተዋልና መኝታ ቤቴ አያምጡብኝ እንጂ እንትናቸውን የትም ይትከሉት፤ ችግሬ መቆም በማይገባው ሥፍራ እንደጅብራ ተገትሮ ወይ መስኮትና በሮችን ተጠግቶ በቤተ ክርስቲያናት ሳየው ነው – ይህ ጣዖታዊ ነው፤ ያሣፍራል፡፡ አሁን አሁን በተለይ ከዚህ ከፈረደበት የወያኔ መንግሥት ጋር በተገናኘ እወደድ ባይ መሃንዲስና አሽቃባጭ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሁሉ የትግሬውን መንግሥትና የትግሬውን የቤተ ክርስቲያን አመራር ለማስደሰት በሚመስል አኳኋን አዲስ የሚገነባ ቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ይህን የሾለ ብልት እንዲይዝ ይደረጋል፤ እኔ ፍርፍር እያልኩ እስቃለሁ – ተጸድቆ ተሞተ እያልኩ፡፡ በሰዎች ግብዝነትም እንዲሁ ፍቅፍቅ እያልኩ እስቃለሁ – የክርስትናን ሃይማኖት ከወንዴ ፆታ ጋር ለማቆራኘት በከንቱ ሲደክሙ እያስተዋልኩ፡፡ የፈረደበት ይህ የወንድ ዕቃ ባይገርማችሁ የብዙ ሰይጣናዊ ቤተ አምልኮቶች መለያ ምልክት ነው፡፡ ከፈለጋችሁ symbols of Satan and symbols of Christianity ብላችሁ ጎልጉሉና እውነቱን ተረዱ፡፡ የክርስትና ምልክቶች በዋናነት መስቀል – ሊያውም የተወሰነ ቅርጽና አቀማመጥ አለው – ሰይጣናውያንም ክርስቶስን ያዋረዱ መስሏቸው በማሾፊያነት መልክ የመስቀልን ምልክት በተለያዬ ቅርጽና አቀማመጥ ይጠቃማሉና – በግ፣ እርግብ፣ ለሰላምታ የተዘረጉ (የሚመስሉ) አምስት የእጅ ጣቶች፣ … ናቸው፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ለነገሩ የተቃዋሚ አባል በመሆኑ የሕይወት ታሪኩ እንዳይነበብ በምትከለክል ቤተ ክርስቲያን መተዳደር ራሱ ኃጢኣት ብቻም ሳይሆን ትልቅ ወንጀልም ነው፡፡ ይህ ነገር የሆነው ሰሞኑን ነው – በዘሃበሻ ድረገጽ ዛሬ ጧት ነው ያነበብኩት፡፡ ራሷ ከወንጀለኞች ጋር የምትተባበር ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን ወደ ጽድቅ ጎዳና ልታወጣ እንደማትችል ፊደል የቆጠረ ኅሊና ያለው ሰው ይቅርና የሰይጣን መንጋ የታጎረበት ዓሣማም ያውቃል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ከብዙ ነገሮች መጽዳት ይገባታልና ዘመቻችን ሁለንተናዊ ነው፡፡ ካህናቱም ማፈር አለባቸው፡፡ እኔ በቤተ ክርስቲያኔ እንደዚህ በሀፍረት የተሸማቀቅሁበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም፡፡ ችግሩ ታዲያ የሃይማኖቱ ሳይሆን የመሪዎቹ ከሰይጣን ጋር መዳበል ነው፡፡ በሰይጣን ከተጠለፈች ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ድኅነት አይገኝም፤ ጸሎቱ ከዳመና በላይ አይወጣም፤ ምህላውም ጣሪያን አያልፍም፡፡ ተያይዞ መጥፋት ማለት እንግዲህ ይህ ነው፡፡ የ‹ኩስ› ጠንቅ ሦስት ነው ይባላል፡፡ አንድም እግርህን ይነካል፤ ሌላም ምን ነካሁ(ኝ) ብለህ በእጅህ ትነካዋለህ፤ ሦስተኛም ምንነቱን ለመለየት ወደ አፍንጫህ ታስጠጋለህ  – ከተፈለገም በአራተኛነት በድንጋጤ ወደልብስህም ልትጠርግ ትችላለህ፡፡ በዚህ መልክ በወያኔ ጠንቅነት ምክንያት ሀገራችንን፣ ሃይማኖታችንን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ሞራላችንን፣ ባህላችንን፣ … በጥቅሉ ስብዕናችንን አጣንና ተንቀሳቃሽና ተናጋሪ እንስሳት ሆነን ዐረፍነው፡፡ የእነዚህን የታሪክ ጉግማንጉጎች የመጨረሻ ሳያሳየኝ ፈጣሪ  ከወሰደኝ – መቼም አያደርገውም አይባልምና – እዚያው በራሱ ችሎት በጸባዖት የጽርሃ አርያም አደባባይ ከስሼ ‹ማንነቴን አሳየዋለሁ›!

በመጨረሻም፡-

ማናት ያቺ ቀልማዳ ተስፋ የቆረጠች አርቲስት – አዎ፣ ጀማነሽ የምትባለዋ ሌላኛዋ የሴት ታምራት ገለታ የምትለውን አስገራሚ ነገር እየሰማን ነው፡፡ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ስትወልድበት ገደል ይገባል ይባላል – የባሰበት እመጫት ያገባልም ይባላል፡፡ የሆኖ ሆኖ ዘመኑ የተቃረበ በመሆኑ እንዲያውም ከዚህ የባሰ ገና ብዙ ጉድ ሊመጣ አለውና በቀላሉ የምንወናበድና እንደገበቴ ውሃ የምናወላውል መሆን እንደሌለብን በተለይ ለኔ ቢጤ ድንጉጣን ላስታውስ እወዳለሁ – ወደዝርዝሩ መግባት ጊዜ ይወስዳል እንጂ መጽሐፉ ጨርሶታል፡፡ እግዚአብሔር ሥራ ፈትቶ፣ ነቢዩ ኤሊያስ አማራጭ አጥቶ በ(ነ)ጀማነሽ ሲመጣ ይታያችሁ፡፡ ሰውን መናቄ አይደለም፡፡ በዚያ አቅጣጫ ከሆነ ፈጣሪ ከትቢያ አንስቶ ኃጢኣትን አጥቦ የራሱ ባሪያና አግለጋይ ማድረግ የማይሳነው የጌቶች ጌታ የንጉሦች ንጉሥ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ግን የነጀማነሽ ነገር ከጉዳይ የሚጣፍ የማይሆንባቸው ብዙ ምክንያቶቹ ስላሉ ነው፡፡ ልጂቱ አጭበርባሪና ከሰው የማትገጥም ‹ኦድ› መሆንዋን በባችነቴ (She was my batch at AAU some ‘50’ years back!) ማወቄ ከብዙዎች ዓመታት በኋላ ስለርሷ የአሁን ጠባይ እንድናገር ባያስችለኝም እርሷ ይዛው ስለተነሳቺው የስም ለውጥና የበዓላት አከባበር ጉዳይ የሚጨነቅ አምላክ የለም ብዬ ስለማስብ ነገረ ሥራዋ ከመጨነቅና ሥነ ልቦናዊ ችግርን ለመግፈፍ ከመፈለግ አንጻር እንደሚሆን ማመን እፈልጋለሁ – በዚህ ዘመን በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት ጭንቀት የሌለው ሰው ማግኘት ይከብዳልና ሃይማኖት ‹መሥራት›ም እንደወያኔው ጦርነትን የመሥራት ያህል እየቀለለ መጥቷል – ታምራት ላይኔስ በአዲሱ ኢ-ወያኔያዊ ሕይወቱ ክርስትናን ‹ተቀብሎ› የለምን? እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ላይ ሊሠራው የሚችለው ነገር ስንትና ስንት ነገር ሞልቶ በዓመት አራት የቅዱሳን ቀናትን አክብሩ ብሎ በጀማነሽ ሶሎሞን በኩል ይመጣል ብዬ ደግሞ አላስብም፡፡ ስለዚህ ልክ እንደኃይሌ ሁሉ ለዚህች በሽተኛ ልጅ – ለካንስ ልጅ ከመሆን አልፈናል! – ለዚህች ወፈፌ ሴትዮም አትጨማለቂ ብላችሁ ንገሩልኝ – ‹ተሳዳቢ መንፈስ› ይዞሃል ተብያለሁና ይለይልኝ – ደግሞ ለመሳደብ፡፡

ስለ አንዳንድ የወቅት ንፋስ ተንገላዋጆች ጥቂት ነገር ብናገር ደስ ባለኝ፡፡ አቤ ቶኪቻውን ስወደው ለጉድ ነው፡፡ ሰሞኑን ታዲያ አንዲት ጽሑፍ ጽፎ ሲያበቃ ባስነበበን አፍቲት በኋላ የወቅት የፖለቲካ ምች ያጠናገራቸው ከእናታቸው ማሕጸን ሳሉ ቢጨነግፉ የሚሻላቸው ጭንጋፍ ዜጎች አይወርዱበት መሰሏችሁ? መናደድ ባውቅ በተናደድኩ፡፡ መናደድ የማያውቅ ደግሞ ቁጭቱ ከሆዱ ስለማይወጣ ብግንግን ነው የሚል፡፡ እናም በአንዲት ዐረፍተ ነገር “ከእንግዲህ ወዲያ ጊዜው የኢትዮጵያውያን እንጂ ‹እንትናዬ መሆኔን በቅድሚያ ካላወቅህልኝ እንትንህን አላውቅልህም” የሚሉት እንደመለስ ዜናዊ በስብሶ ሊቀበር ሰዓታት የሚቀሩት አስተሳሰብ ከአሁን በኋላ በሀገሪትነ ኢትዮጵያ ቦታ አይኖረውም” በማለት አጭር መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር እንደገማ ዕንቁላል ክርፋት ጥንባቱ ከሩቅ የሚሰነፍጥ ወያኔ ያስታጠቃቸውን የጎሣ ፖለቲካ ተሸክመው የሚንከረፈፉ ወገኖች ሊጠነቀቁ ይገባቸዋል፡፡ እንዲህ የምላቸው በአሳደህ በለው ይህችን ጽሑፍ ለማሰናዳት ከምታስችለኝ ሌባ ጣት በስተቀር አንዳችም የጦር መሣሪያ የሌለኝ ምሥኪን ዜጋ እንጂ የምታገልበት ከባለቤቴ የወጥ ማማሰያ የዘለለ የጦር መሣሪያ ኖሮኝ አይደለም፡፡ በኃይል የሚያምኑ በኃይል እንደሚጠፉ አውቃለሁና መጽሐፉ ‹ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኃ ሠራዊቱ› እንዲል ከአሁን ወዲያ ልክ እንደወያኔ በማንኛውም መንገድ ሕዝብን ከሕዝብ ለመነጣጠልና በሰላም በሚኖረው ሕዝብ መካከል ሽብልቅ ለመቀርቀብ የምትማሰኑ ወገኖች ሁሉ አደብ እንድትገዙ በዜግነቴ እመክራለሁ፡፡ ሌላ ድብቅ ፍላጎት ኖሮኝ አይደለም – በዚህ ቂልነታችሁ እናንተው ስትጎዱበት ከወዲሁ እያየሁ ስለምታሳዝኑኝ እንጂ፡፡ በቃ – ሞኝነት የሚሠራው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መሆን አለበት – እንደዚያም ነው እውነቱ፡፡ የደንቆሮ ለቅሶ ሁልጊዜ አበባየ እንደሚባለው በወያኔ ቅኝት እየዘፈንን ሁልጊዜ ደንቁረንና ደድበን መቅረት የለብንም፤ ሰውስ ምን ይለናል ? እርግጥ ነው – ድንቁርናችንን ለወያኔ ሸጠን ጩኹ ባለን ጊዜ ሁሉ – ጃዝ ብለው ባሰማሩን ጊዜ ሁሉ በየድረገጹ በመጣጥፍም ይሁን በኮሜንት(አስተያየት) መልክ ብዙ ፀያፍና ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ ዝግንትል ልንለቀልቅ እንችላለን፡፡ ግን ግዴላችሁም – ሞኝነታችንን ዕልባት እናድርግለትና ወደጤናማ ኅሊናችን እንመለስ፡፡ በኛም ይብቃና በተለያዩ ችግሮች ወደተተበተበው ሕዝባችን እንመለስ፡፡

በተረፈ ኢትዮጵያን የነካ ሁሉ መጨረሻው ምን እንደሆነ ማስታወስ አልፈልግም፡፡ የጋዳፊ ሊቢያ፣ የዚያድ ባሬ ሶማሊያ፣ የሣዳም ኢራቅ፣ የአልበሽር ሱዳን፣ የሙባረክ ግብጽ፣ የአሣድ ሦርያ፣ የብሬዥነቭ ሶቪየት ኅብረት፣ የ‹ኢሣይያሷ ኤርትራ› … እነዚህና ሌሎችም ‹ዘተፀውዓ ወዘተኢፀውዓ ስሞሙ› ሁሉ ወያኔን በገፍ እየረዱ አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር ማድረጋቸው የሚታወስ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በሂደት እነዚህ ሀገሮች የደረሰባቸውና እየደረሰባቸው ያለው የተመሰቃቀለ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ንጹሓንን ከመበደል ሊመነጭ እንደሚችል መጠርጠር አይከፋም፤ አዎ፣ ወደላይ የወረወርከው ድንጋይ ይዋል ይደር እንጂ ማረፊያው አንተው ነህ፡፡ ፈጣሪ ሒሳብን በማወራረድ ረገድ የሚያማው የለም፡፡ ለነገሩ መነሻየ ባልሆነ ነገር ምን አገባኝ?

 

 

የመለያያ ምርቃት፡- In football, people of this profession say that football is attractive with all the fouls and the errors; likewise, I say life is attractive and worth living with all the taboos, comical funs, and linguistic flavors.

 

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop