አዳክሞ ማደህየት የወያኔ ትልቅና ዋና መሣሪያ ሆኖ አገልግሎአል፤ ወያኔ ከኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አርባ ያህል መምህራንን ያስወጣው ገና በጠዋቱ ነበር፤ ከቴሌ ከመብራት ኃይልና ከባንክ ሰዎችን እየመነጠረ ያስወጣው በዘር አመካኝቶ ቢሆንም በትምህርታቸውና በልምዳቸው የጠጠሩበትን ሰዎች እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ነው፤ እንደፐሮፌሰር ዓሥራት ያለውን በሁለት የታወቁ የእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች የተመሰከረለትን ሰው በችሎታ ማነስ ብሎ ማስወጣት ችሎታ ያነሰው ማን አንደሆነ የሚያውቅ ያውቀዋል፤ እነዚህን የተለያዩ ባለሙያዎች በማስወጣት ወያኔ ሰዎቹን አልጎዳም፤ ሁሉም የተሻለ ኑሮና የተሻለ የሥራ እርካታ አግኝተዋል፤ የተጎዱት መሥሪያ ቤቶቹ ናቸው፤ ከወያኔ ጋር ወደኋላ የሄደችው ኢትዮጵያ ነች፤ ወደኋላ የሄደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።
በመሬት ያየነው እንደሆነ የወልቃይት-ጸገዴና የራያ-ቆቦ ድንበር ለትግራይ በሚጠቅም መልኩ ቢለወጥና ጎንደርንና ወሎን ቢያስቀይምም አዲስ የመሬት ድልድልን ፈጥሮአል፤ ከመሬቱም ጋር የ‹‹አማራ›› ሕዝብ ቁጥር እንዲቀንስ ሆኖአል፤ ይህ ሁሉ ማዳከም አይሆንም? አዳክሞ ማደህየት አይሆንም? ምርጥ የአገሪቱ መሬት ለውጭ አገር ባለሀብቶች በቸርነት የሚቸበቸበው ገበሬውን ለማዳከምና ወደኩሊነት ለመለወጥ አይደለም? ወደኩሊነት በመለወጥ የራሱን ዕድል በራሱ በመወሰን ፋንታ ሌላ ሰው፣ ምናልባትም ባዕድ ይወስንለታል፤ ከዚህ የበለጠ አዳክሞ ማደህየት ምን አለ?
አንድን ሕዝብ ካዳከሙ በኋላ ማደህየቱ በጣም ቀላል ነው፤ ደርግ ባያውቅበትም በማርክሳዊ-ሌኒናዊ ሰይፍ ደሀዎችን ከደሀነት ለማውጣት ሞክሮ ነበር፤ የደርግ ችግር ደሀዎችን ከደሀነት ለማውጣት ሀብታሞቹን በጠመንጃ ማደህየት ግዴታ አድርጎ መከተሉ ነበር፤ መሬት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ነው ብሎ አላቆመም፤ ወይም በባለቤቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም መሬትን ለውጭ አገር ሰዎች አልቸበቸበም፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ አደላደለ፤ የቤት ኪራይን ቀነሰ፤ በኅብረት ቤት ለመሥራት ለሚፈልጉ ሁሉ መሬቱንም ሆነ ገንዘቡን በቀላሉ የሚያገኙበት ሥርዓትን አመቻቸ፤ ብዙ ሰዎች ቤት ለመሥራት ቻሉ፤ ደርግ በጠመንጃ ደሀነትን ለማጥፋት ሲሞክር ሀብታሞች መቃብሩን ቆፈሩለት፤ ወያኔ ደግሞ ሀብታምነትን በጠመንጃ ለመትከልና ደሀነትንም በጠመንጃ ከአገር ለማስወጣት ሰፊ እቅድ አውጥቶ እየሠራበት ነው፤ ወያኔ መሬት የግል የሚሆነው በመቃብራችን ላይ ነው በማለት ተንብዮ ነበር፤ ትንቢቱ ከደረሰ ቀባሪዎቹ ደሀዎች ሳይሆኑ አይቀሩም።
ወያኔ ሕገ መንግሥቱን አሳምሮ የመደራጀት መብትን ከሥራ ውጭ በማድረግ የሠራተኞች ማኅበርን፣ የመምህራን ማኅበርን፣ የነጻ ጋዜጠኞች ማኅበርን፤ የገበሬ ማኅበርንና ሌሎችንም በቁጥጥሩ ስር አደረጋቸው፤ አዳከማቸው ማለት ነው፤ እነዚህ ሁሉ ማኅበሮች ዛሬ ነጻ ህልውና የሌላቸው፣ ነፍስ የሌላቸው አካሎች ናቸው ለማለት ይቻላል፤ የሴቶች ማኅበርና የወጣቶች ማኅበር የሚባሉትም ሁኔታቸው ያው ነው፤ የተለያዩ የማኅበረሰብ ድርጅቶችም እንደእድር ያሉ ባህላዊ የሆኑትም ጭምር ወይ በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ ወይ ከሥራ ውጭ ሆነዋል፤ የፖሊቲካ ፓርቲዎችና ነጻ ጋዜጦች አሜሪካ በሽብርተኛነት ላይ ጦርነትን እስቲያውጅ ድረስ አሜሪካንን ለማባበያ ጠቅመው ነበር፤ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ረዳት ሆና በሽብርተኞች ላይ በሚደረገው ጦርነት ላይ ከአሜሪካ ጋር መሰለፍ ስትጀምር የኢትዮጵያ የፖሊቲካ ፓርቲዎችና ነጻ ጋዜጦች የአሜሪካን የይስሙላ ድጋፍም ማጣት ጀመሩ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም የፖሊቲካ ፓርቲዎችና ነጻ ጋዜጦች አፈና በከፋ መልኩ ተጀመረ፡፡
በሃይማኖት በኩል ያየነው እንደሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቁጥጥር ስር የዋለችው ገና ከመጀመሪያው ነው ለማለት ይቻላል፤ እንዲያውም በቅርቡ የቀድሞው የወያኔ መሪ እንደተናገረው የወያኔ ተዋጊዎችን መነኮሳት እያስመሰሉ በየገዳሞቹ ሰግስገው እንደነበረ አውቀናል፤ ስብሐት ነጋም ጳጳሳቱ ውስጥ ‹‹አንድም ሰው የለም፤ ቢገኝ አንዲሸለም አደርጋለሁ፤›› ብሎ በአደባባይ ሲናገር ቆብ ጭነው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሰፈሩት ሁሉ ከመምህራን ማኅበርና ከሠራተኞች ማኅበር ሹሞች የማይሻሉ መሆናቸውን በተደጋጋሚ አስመስክረዋል፤ አሁንም በመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ላይ የሚፈጽሙት የሚያሳየው የመንፈሳዊ አባቶችን ጠባይ ሳይሆን የጉልበተኞችን ማንአለብኝነት ነው፤
ለካህናትሰ ሰመዮሙ ጼወ፤ ወዓዲ ለካህናትሰ ሰመዮሙ ማኅቶተ፤ ካዕበ ሰመዮሙ ብርሃኖ ለዓለም፤ ወካዕበ ሰመዮሙ ጸሐየ ዘያበርህ ጽልመተ እንዘ ክርስቶስ ጸሐየ ጽድቅ ውስተ አልባቢሆሙ፤ ወካህንሰ ዘቦቱ ልቦና ይገሥጾ ለንጉሥ በእንተ ምግባራት ዘርእየ፤ … ክብረ ነገሥት
ይህንን ትእዛዝ ለመፈጸም ቃል ኪዳን የገባ ሰው ማንም ቢሆን ጥፋት ሲሠራ ከተመለከተ ‹‹ስደትንም ሆነ ሰይፍን ሳትፈራ›› ተቆጣው የተባለና ሥልጣን የተሰጠው ካህን እንዲያውም የጥፋቱ ተሳታፊ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ተልእኮ ማስተላለፍ አትችልም፤ በዚህም ምክንያት መሳለቂያ እየሆነች በሌሎች ባልተሻሉ ቤተ ክርስቲያኖች እየተገፋች ነው።
በእስልምናውም በኩል መንፈሳዊ መሪ ነጥሮ ሊወጣ አልተቻለም፤ ምእመናኑም እምነታቸውን እነሱ በፈለጉት መንገድ ለማስተናገድ ባለመቻላቸው ለመብታቸው ሲታገሉ ዓመት አለፋቸው፤ አሁንም እየታገሉ ነው፤ በእስልምናውና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኩል ያለው ቸግር ተመሳሳይነት ቢኖረውም የእስልምና ምእመናኑ በትግል ጥንካሬ በጣም ልቀው ሄደዋል፤ የትግሉ አካሄድ ግን እንቅፋቶች እያጋጠሙት በመሆኑ ጠመዝማዛ የሚሆን ይመስላል።
ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በጎሣ ላይ አተኩሮ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መከፋፈል በአጠቃላይ ሲታይ ያልተከፋፈለበት ነገር የለም፤ የሁለተኛ ደረጃን ትምህርት በጣም አዳክሞ የስም ዩኒቨርሲቲዎችን በቁጥር የበዙ በማስመሰል ትምህርትን ማዳከሙ ዋናና መሠረታዊ ነው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም በማናቸውም ዓይነት ማኅበራዊ ጉዳይ በነጻነት መደራጀትን አንቆ በመቆጣጠር ሕዝቡ መፈናፈኛ እንዳያገኝ አድርጎት ቆየ፤ ሌላውን ሁሉ መንገድ መቆጣጠሩ ከሞላ-ጎደል የተሳካ መሰለ፤ አሁን መጨረሻው ላይ የሃይማኖት ጉዳይ ከረር እያለ መጣ፤ ሰው ከሰው ጋር ያለውን ግንኙነት ለሃያ አንድ ዓመታት በማሻከርና በማዳከም ከፍተኛ ጉዳትን አደረሰ፤ አሁን ደግሞ ሰዎች ከፈጣሪ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻከርና ለማዳከም ቀድሞ የተጀመረው የቁጥጥር ጥረት አይሎ በአደባባይ ወጣ፤ በዚህ ጊዜ እንዳጋጣሚም ለወጉም ቢሆን ሃይማኖት ያለው ሰው በጠቅላይ ሚኒስትር ወንበር ላይ ተቀመጠ፤ ክብረ ነገሥት ‹‹እግዚአብሔርን ፈሪና አስተዋይ ካልሆነ አለቃ ይሆን ዘንድ አይገባውም፤›› ይላል።
በአገር ውስጥ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከላይ በአጭሩና በአጠቃላይ እንደተገለጸው ከታትፈው በቁጥጥራቸው ስር አድርገው እያሹ አዳከመው አልጋ ላይ ካዋሉት በኋላ ስደተኛውን እየመለመሉ በመሬትና በተለያዩ መደለያዎች እያባበሉ እየተስገበገበና እየተክለፈለፈ የሚገብርላቸውን አገኙ፤ እንዲህም ስደተኛውን በቤተ ክርስቲያን ሳይቀር ከፋፍለው አዳከሙት፤ የተዳከመ አይታገልም፤ ቢታገልም አያሸንፍም።
የተሸነፈንና የተዳከመን ሁሉ በኩርኩም ማደህየቱ ቀላል ነው፤ ነገር ግን ሁሉም ተከታትፎ ለመሸነፍና ለመደህየት የበቃው በወያኔ ኩርኩም ብቻ ሳይሆን በራሱ ስግብግብነትም ጭምር ነው፤ የሥላሴዎች እርግማን!
source: http://mesfinwoldemariam.wordpress.com/2013/07/31