የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ‹‹ስቴት ፈንድ›› በሚል በየወሩ የሚሰጣቸው 340 ብር አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ አንጻር በቂ ባለመሆኑ እንዲጨመርላቸው ለሶዶ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ ያቀረቡ ማየት የተሳናቸው ከ5-12 ክፍል የሚማሩ 90 ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች በፖሊስ እንደተደበደቡ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ተማሪዎቹ ጥያቄውን ከአራት አመት በፊት ጀምረው እንዳቀረቡ የገለጹ ሲሆን በተለይ በቅርብ ጊዜያት ጥያቄውን በተደጋጋሚ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎቹ ጥያቄውን ለሶዶ ከተማ ከንቲባ አቶ መንግስቱ ሲያቀርቡ ቢቆዩም አቶ መንግስቱ ስልጠና ላይ ናቸው በመባሉ አቤቱታውን የሚሰማ በማጣታቸው ወደ ወላይታ ዞን አስተዳደር ሄደው ማመልከታቸው ተገልጾአል፡፡ የአስተዳደሩ ሰራተኞችም ስለ ጥያቄው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመግለጻቸው ተማሪዎቹ ‹‹የመንግስት አካላት ናችሁ ለምን ጥያቄያችንን አላወቃችሁም? ለአቤቱታችንስ መልስ ለምን አትሰጡንም?›› በሚል ከአስተዳደሩ ቢሮ አንወጣም በማለታቸው የወላይታ ዞን አስተዳደሩ ሌሊሸ ኦሌና ሉቃስ ባልቻ በተባሉ ፖሊሶች የተመራው የሶዶ ከተማ ፖሊስ ማየት በተሳናቸው ተማሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ አድርገዋል ተብሏል፡፡
‹‹እስካሁንም ጥያቄውን ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ በተለይ የሚሰጠን 340 ብር አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር ሊመጣጠንልን ስላልቻለ እንዲጨመርልን ነው ጥያቄውን ያቀረብነው›› የሚለው ተማሪ አቤል (ስሙ የተቀየረ) ‹‹አስተዳደር ጽ/ቤት ከደረስን በኋላ መጀመሪያ ላይ አናስገባም አሉን፡፡ ጥያቄያችን ሳናቀርብ እንደማንመለስ በመግለጻችን ግቡ ተባልንና ገባን፡፡ ወደግቢው እንደገባን ፖሊስ በጣም የሚያሳዝንና በአካላችን ላይ በደረሰብን ጉዳት ላይ መሰረት ያደረገ ስድብ ይሰድቡን ጀመር፡፡ እናንተ አካለ ጎደሎዎች ብለው ሰድበውናል፡፡ ወደ ቢሮ ገብተን አቤቱታ ለማቅረብ ስንሞክር አትገቡም ተባልን፡፡ በዚህ ወቅት ነው ድብደባውን የፈጸሙብን፡፡ በተለይ ሴቶቹ ላይ ከባድ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በአካል ከደረሰብን ይበልጥ የስነ ልቦና ጉዳት ደርሶብናል›› ሲል ስለሁኔታው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ ወደ አስተዳደሩ ጽ/ቤት በሄዱበት ወቅት ዋና አስተዳዳሪው አቶ እዮብ እያታለሉ እንደመለሷቸው የሚገልጸው ዳዊት (ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ) ‹‹ትምህርት ቢሮ ሄደን ስንጠይቅ ወደ አስተዳደሩ ደብዳቤ ጻፉልን፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎች ደብዳቤውን ይዘው ቢሄዱም ዋና አስተዳዳሪው አቶ እዮብ አስተዳደሩ አታልለውን ጠፍተዋል፡፡ ምክትሉ አቶ ታደለ ‹አስተዳዳሪው የሉም› ብለው ቀጠሮ ሰጡን፡፡ ረቡዕ ጥቅምት 5/2007 ዓ.ም ከዚህም በኋላ ‹‹እንዲህ እየተራብንና እየተቸገርን ትምህርት አንማርም አልን›› በማለት ሂደቱን ያስረዳል፡፡
አንማርም ባሉበት ወቅትም ምክትል አስተዳዳሪው መጥተው ‹‹ጥያቄያችሁን እንመልሳለን፡፡ ገንዘቡም ይጨመርላችኋል፡፡ ሰኞ መጥታችሁ አወንታዊ መልሱን ታገኛላችሁ›› ብሎ ቃል ገብቶ እንደተመለሰ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ዳዊት ለነገረ ኢትዮጵያ ይናገራል፡፡ ሆኖም ሰኞ ጥቅምት 11/2007 ዓ.ም በቀጠሯቸው መሰረት 90 ተማሪ ወደ አስተዳደሩ ቢሮ በሄዱበት ወቅት ‹‹እናንተን አናውቃችሁም፤ ኃላፊውም የለም›› በሚል ፖሊስ ከተማሪዎች ጋር ግጭት እንደፈጠረና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተማሪዎቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
‹‹አስተዳደሩ ግቢ አስገብተውም ተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈጸሙ፡፡ በከፊል የሚያዩ ሴቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሴቶች ‹እናንተ ናችሁ መርታችሁ ያመጣችሁ› ተብለው ከፍተኛ ደብደባ ደርሶባቸዋል›› ሲል ዳዊት ስለ ድብደባው ገልጾአል፡፡
ተማሪዎች ከተደበደቡ በኋላ ዋና አስተዳዳሪው እንደደረሱ የገለጹ ሲሆን ለዋና አስተዳዳሪው ‹በርካታ ተማሪዎች ተደብድበዋል፡፡ በራጅ ይመርመሩ› ብለን ጥያቄ ብናቀርብም አስተዳዳሪው ‹ለሰላማዊ ሰልፍ ህጋዊ ፈቃድ ሳትይዙ ለምን ግቢ ውስጥ ገባችሁ ወትሮውንም እናንተ ነው ጣጣ ያመጣችሁት፡፡ እኔ የማውቀው ነገር የለም፡፡ አስተዳደሩን ቢሮ ደፍራችሁ ገብታችኋል ብትሞቱም ማንም አይጠየቅም› እንዳሉዋቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹ለማንም እንዳታወሩ፣ ከአሁን በኋላ በብዛት ከመጣችሁ ትታሰራላችሁ› የሚል ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹በርና መስታወት ባይሰበርም እነሱ ግን በርና መስታወት ሰብራችኋል ብለው ደበደቡን፡፡ በተለይ የሴት መብት ተከብሮበታል በሚባልበት በአሁኑ ጊዜ ሴቶች ላይ የደረሰው ድብደባ እንዲሁም በአካላችን ላይ በደረሰው ጉዳት መሰደባችን በጣም የሚያሳዝን ነው›› ሲሉ ተማሪዎቹ ቅሬታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡