ከማግለል ማሳተፍ ይቅደም! (ልጅ ተክሌ በኢሳት ላይ ላቀረበው ጽሁፍ የተሰጠ ምላሽ)
ከአዋሽ አዳል
ሰሞኑን በ አንድ ድረግፅ ላይ “የኢሳት 3ኛ አመት ክብረ-በዓል የሙስሊሞች ብቻ ነው እንዴ?” በሚል ርዕስ ከልጅ ተክሌ የፃፈውን ካየሁ በሁዋላ ፀሐፊውን በልቤ ወቅሼ አለፍኩት። በነጋታው በሌላ ድረገፅ ላይ ሌላ ርዕስ ይዞ፣ ትንሽ ተቀይሮ አየሁት። መለስ ብዬ ሳየው ፅሁፉዋ ብዙዎችን ስታነጋግር ሳይ፣ አንድ ነገር ማለት አልብኝ ብዬ ወሰንኩ። ፅሁፌ አንኩዋር ነው ብዬ ያሰብኩት ላይ ብቻ የሚተች ስለሚሆን ብዙ ነገሮችን ሊዘል ይችላል። ስለዚህም አንባቢ ከዚህ በፊት የልጅ ተክሌን ፅሁፍ እንድያነቡ እመክራለሁ።
እንደኔ አስተያየት የፅሁፉ ፍሬነገር በዚህ ጥቅስ ውስጥ ይኖራል ብዬ እገምታለሁ ” . . . ባንድ በኩል ሙስሊሞች ለመብታቸው መታገላቸው የሚደገፍ፤ የሚያስቀና፤ የሚኮረጅ ቢሆንም፤ ሙስሊሞች ግን በኢትዮጵያ ውስጥ እንደአንድ ፖለቲካዊ ጎራ ወይም ቡድን ይታዩ ወይንም እንደ አንድ ፖለቲካዊ ቡድን ሆነው እንዲወጡ እናበረታታቸው ወይንም እውቅና እንስጣቸው የሚለውን ሀሳብ አልደግፈውም። . . . ”
የፀሐፊው ሃሳብ ትክክል ነው ቢባል እንኩዋን ፣ ፀሐፊው የተጠቀሱት ግለሰቦች ባንድ ወይም በሌላ ዝግጅት ላይ በመጋበዛቸው ብቻ አንደ “የፖለቲካ ኃይል” እንደሚታዩ አድርጎ መሳሉ ከምክንያትውነቱ ይልቅ ሰበብ ፈላጊነቱን ያጎላዋል። ምናልባትም በመግቢው ላይ አንደጠቀሰው “ለማበሳጨት ወይንም ለማስጨብጨብ” ፈልጎ ካልሆነ በስተቀር፣ ፅሁፉ እስላሞችን የመፍራት ወይንም የመጥላት ( ወይ የሁለቱም) መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በአንድ በዓል ላይ “ይህን ያህል እስላም ተጋበዘ” ብሎ ይህን ያክል መንሰቅሰቅና ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰበቦችን መደርደር “ጤናማና ነፃ” አስተሳሰብ ነው ለማለት ያሰችግራል ። በተለይም ፀሐፊው ከዚህ በፊት ለኢሳት ያደረገውን አስተዋፅኦ ስንመልከትና፣ አሁን በይፋ የኢሳትን ዝግጅት ለማደናቀፍ ያደረገው ጥረት ስናይ፣ ምን ያህል ለሙስሊሞች ፍራቻ ወይንም ጥላቻ አንዳለው መረዳት ያስችላል። ፀሐፊው :- ” . . . እነዚህን ሰዎች በመጋበዝ ልናመጣ ያሰብነው ትርፍ፤ በግልጽ ላንሰፍረው የማንችለው ትልቅ ኪሳራ እን ደሚያመጣብን፤ አደገኛ አካሄድ እንደሆነም አላስተዋልንም የሚል ራእይ ተገልጾልኛል . . . .” ይላል። እውን ይህ “ራእይ” ከተገለጠለት ምን ማድረግ ነበር ጥሩ የነበረው? ይህንኑ “ራእይ” ለደርጅቱ አስታውቆ ፈረንጆች አንደሚሉት ለ damage control መስራት ነው ወይስ ባደባባይ ይህን ሁሉ አናቅፅ አያዥጎደጎዱ “የተገለጠለትን የኪሳራ ራእይ” ማባባስ?
ልብ በሉ በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ድርጅቶችና ስብስቦች ብዙ የክርስትና ሃይማኖት መሪዎችን በየመድረኩ ሲጋብዙ አንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች ጋዜጠኞች አንዲሁም አክትቪስቶች ወደ ቤተክርስቲያን ጎራ ሲሉ አይተናል ወደፊትም እናያለን፣ እኔ እስከማውቀው እነዚህ መድረኮች አንድም ጊዜ ክርስትያኑን እንደ አንድ “የፖለቲካ ያህል” የሚያውጡ ናቸው ሲባል አላየሁም። አሁን አንዳንድ ሙስሊሞች በተለያዩ መድረኮች ብቅ ለማለት ሲሞክሩ ሰበብ ፈልጎ ለማግለል መሞከሩ ለሀገራችን የሚያዋጣ አካሄድ አይደደለም። በመግቢያዬ ላይ “የፀሐፊው ሃሳብ ትክክል ነው ቢባል እንኩዋን” ያልኩበት ዋናው ምክንያት፣ የአንድ ቡድንን (የጎሳም ይሁን የሃይማኖት ወይንም የአካባቢ) “እንደ ፖለቲካዊ ኃይል” ሆኖ መውጣት የሚወስኑት መሰረታዊ ምክንያቶች፣ አንደኛ ቡድኑ አንግቦ የሚያራምዳቸው አላምዎቹና ሲቀጥልም የአንቅስቃሴው ሂደት ናቸው። በመጀምርያው ላይ “የሌሎች” ተፅዕኖ ወይንም አስተዋፅኦ ውሱን ሲሆን በሁለተኛው (በሂደቱ) ላይ ግን የተወሰነም ቢሆን የተሻለ ሚና ይኖራቸዋል። ይህንን ሚና “ሌሎቹ ” በጥሩ ጎኑ (positive aspect)ከተጠቀሙበትና “የቡድኑ” ሂደት አሳታፊ እንዲሆን የበኩላቸውን ከተጫወቱ፣ ወደ ጋራ መግባባትና አብሮ መስራት በፍጥነት ሊሸጋገሩ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ያ “ቡድን” ለብቻው እንደ ፖለቲካዊም ሆነ እንደ ሌላ ቡድን ሆኖ የመውጣት ፍላጎት አንዳይኖርበት ወይንም እንዳይገደድ (አንዳንዶች እንደሚሉት “በሁኔታዎች አስገዳጅነት”) ያደርገዋል ወይንም ያግዘዋል። የተክሌ ፅሁፍ ግን ጭራሽ ተቃራኒውን ነው የሚያደርገው፣ አንዱን ማግለልና አንዱን ማስፈራራት; ፀሐፊው “እንዳይሆን” እፈልጋለሁ የሚለውን ሳይሆን ተቃራኒውን ማስተጋባት ነው።
ወደ አንደኛው ምክንያት ብንመለስ; – አንድን “ቡድን” ደግሞ “ሌሎች” ሊተባበሩት የሚችሉት፣ ቡድኑ ያነገባቸው አላማዎች ቢያንስ “በሌሎችም” ተቀባይነት ሲኖረውና ያነሳቸውም ጥያቄዎች “ሌሎችም” የሚያነሱት ሲሆን ነው። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ያነሷቸው መሰረታዊ የማምለክ ነፃነትና መንግስት ከሀማኖት ቤቶች ውስጥ እጅህን አውጣ የሚሉ ጥያቄዎች፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄዎች ናቸው። ዓመት ከመንፈቅ ሊሞላው የተቃረበው ይህ እንቅስቃሴ አንድም ቀን ካነገበው መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥያቄ ቅንጣት ፈቀቅ አላለም። ምንም ያክል ትንኮሳ ቢፈፀምበትም ከሰላማዊነቱ ንቅንቅ አላለም። ምንም አይነት የፖለቲካ ስልጣን ወይንም የአስተዳደር መዋቅርን የመከለስ ጥያቄ አላነሳም። ንቅናቄው ከመጀመሪያውም “የፖለቲካ ቡድን” ሆኖ የመውጣት ወይንም የመቀጠል አላማ ይዞ አልተነሳም። ይልቁንም የክርስትና እምነት ተከታዮችን ለማሳተፍ የተቻለውን ያክል ሞክሯል። ይህ ዝም ብሎ የመጣ ነገር ሳይሆን ከመንግስት ወይንም በሌሎች አካላት (ከሕዝቡም መሃል ቢሆን) ጥያቄው ወዳልታሰበና ወዳልተፈልገ አቅጣጫ እንዳይሄድ አሁን በእስር ላይ ያሉ አመራሮቹ ሰፊና አድካሚ ሥራ ስለሰሩ ነው። ይህ የሙስሊሞች እንቅስቃሴ የሚመራው አገር ውስጥ ባሉ ዜጎች ሲሆን በዋነኛነት የሚካሄደውም እዛው አገር ውስጥ ነው። ውጭ ያለው ያቅሙን ያክል ድጋፍ ከማሳየት ውጭ የጎላ ሚና የለውም። ከነዚሁ ውጭ ከሚኖሩ ደጋፊዎች መሃል ለኢሣት ወይንም ለሌላ ዝግጅት ቢጋበዙ “እንደ ፖለቲካዊ ቡድን ሆነው እንዲወጡ” ማበረታት አድርጎ የሚወስድ ግለሰብ ራሱን ሊመረምር ይገባል። አቶ ተክሌ በፅሁፋቸው “. . . ብዙዎች የነቁም ያልነቁም የሙስሊሙን እንቅቃሴና አካሄድ በጥርጣሬ የሚመለከቱ ስጋት የገባቸው ኢትዮጵያዊያን አሉ። . . . ” ብለዋል፣ እርሳቸውን ከየትኛው እንደመደቡ ያውቁታል ብዬ እገምታለሁ።
እዚጋ ሁለት ነገሮች ትዝ አሉኝ። አንደኛው፣ የተለያዩ ግለሰቦች በብዙ መድረኮች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው ” ለምን ጥያቄው ውስን ሆነ?” ማለትም ለምን ሌሎች (ፖለቲካዊ የመብት) ጥያቄዎችን አልጨመረም፣ በማለት ስለአንቅስቃሴው “ድክመትና አላሳታፊነት” ያነሳሉ። (በአቶ ተክሌ አገላለፅ ወደ አንድ ፖለቲካዊ ቡድን ወደመሆን የሚገፋፋ ጉትጎታ ነው) መልሱ በጣም ቀላል ነው፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች፣ የአስተዳደር ወይንም የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ ከመስጊድ ወይንም ከቤተክርስቲያን መፍለቅ ከጀመረ አደጋው የከፋ ይሆናል። ለዚህም ነው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለጋራ ጥያቄው በጋራ መታገል ያለበት። ለዚህም ነው የእንቅስቃሴው መሪዎች ከመጀመሪያውኑ ጥያቄዎቹ በመሰረታዊና ሁሉንም በሚያስማሙት ላይ ብቻ እንዲሆን የወሰኑት። ለዚህም ነው ክርስቲያኑን ለማሳተፍ አቅደው የተንቀሳቀሱት። ወደ ሁለተኛው ስሸጋገር፣ አንድ የማዕከላዊ ደብዳቢ (በነሱ አጠራር መርማሪ) አንዱን የሙስሊሙን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል በድብደባው መሃል አንዲህ ይለዋል፣- “. . . ድብቅ አላማችሁ ተደርሶበታል” — — ምት — እርግጫ — ዱላ– ” አላማችሁ የሃይማኖት መበት ማስከበር ሳይሆን መንግስት መገልበጥ ነው” — — ምት — እርግጫ — ዱላ– ” በፃፍከው ወረቀት ላይ ክርስቲያኑ መሳተፍ አለበት ይላል” — — ምት — እርግጫ — ዱላ– ” ጥያቄያችሁ የሃማኖት ቢሆን ኖሮ ከክርስቲያኑ ጋር ምን ትሰራላችሁ?”
እንደው ለነገሩ፣
ይህ የተክሌ ፅሁፍ ስንቱን እንዳበሳጨና እንዳስጨበጨበ መረጃው ባይኖረኝም፣ አርግጥ ነው የወያኔውን ጎራ ከመቀመጫው አስነስቷል፣ በጭብጨባ ። ለነ እንደ አውራምባ ታይምሱ ዳዊትማ ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ከመሆኑም በላይ ምናልባትም ድንጋዩን መልሶ አንዲቀልበው ተመቻችቶ የተጻፈ ነው። ከምንም ወይም ከቅንጣት ተንስቶ ሙስሊሙንና የሙስሊሞችን እንቅስቃሴን፣ ታማኝንና ኢሳትን ከመሬት ለመደባልቅ ሌት ተቀን ለሚውተረተረው ዳዊት፣ ልጅ ተክሌ እራሱን እንደ ሶስተኛ ወፍ ሳያቀርብ አይቀርም ትላላችሁ?
ቸር እንሰንብት
አዋሽ አዳል